የተከዜው መብረቅ ቦንብ አጉራሽ ልዩ ኀይል!

234942391 1609722479202740 8214558128413785687 n

የበርሃው ሙቀት ተፈጥሯዊ የሆነውን የጊዜ ዑደት ለመገመት ባይመችም ጀንበር ወደ መግቢያዋ እያዘቀዘቀች መሆኑን ስዓቱ ይናገራል፡፡ ሰኔ 24/2013 ዓ.ም 10፡50 አካባቢ ከተከዜ ወንዝ ወዲያ ማዶ የጦርነቱን መጀመር የሚናገረው የተኩስ ድምጽ ከመሰማቱ ቀድሞ ከተከዜ ወዲህ ማዶ ላሉት አናብስት ትንኮሳ እንደሚኖር መረጃው ደርሷቸዋል፡፡
ቀጠን ያለ ወታደራዊ ትዕዛዝ የደረሳቸው የአካባቢው ጥምር ጦር አባላት በየምድቦቻቸው ወታደራዊ ስትራቴጅክ የሆነ ቦታ ቦታዎችን ይዘው መሽገዋል፡፡ አዛዦች ከላይ ወደ ታች እና ከታች ወደ ላይ መረጃዎችን በበቂ ሁኔታ ይለዋወጣሉ፡፡ ተዋጊዎቹ ደግሞ ራሳቸውን ለውጊያ አዘጋጅተዋል፡፡
የዲሽቃዎቻቸው አፈሙዝ ይመጣል የተባለውን ወንበዴ ይጠባበቃሉ፡፡ ብሬኖቻቸው ከመሬት ቀና ብለው የሚመጡትን ሊለቅሙ ተዘጋጅተዋል፡፡ ስናይፐሮቻቸው ከተከዜ ወዲያ ማዶ የሚመጡትን የእናት ጡት ነካሾች ኮቴ ያነፈንፋሉ፡፡ ክላሽንኮቭ መሣሪያ የታጠቁ ተኳሾች የማይደፈረውን ምድር ይጠብቃሉ፡፡ አካባቢው ላይ ቅጠል እንኳን ብትወድቅ ድምጿ እስኪያስተጋባ ድረስ ጸጥታ ሰፍኖ ነበር ይላሉ የወቅቱ የወጊያው ተሳታፊዎች፡፡

233199205 1609722559202732 5415331872454372403 n

ወታደሮቹ የኢትዮጵያን ነቀርሳ ለመንቀል፤ የአማራ ሕዝብን ክብር ለማስጠበቅና ውጊያውን በድል ለማጠናቀቅ ተዘጋጅተዋል።
አሸባሪዎቹ መግባት በማይገባቸው ቦታ እግራቸውን ሰደዱ፡፡ የያዙትን መሣሪያ ምላጭ ስበው ለመልቀቅ የወደዱት አናብስት ትዕዛዝ ዘግይቶባቸዋል፡፡ ግን ቤቱ የወታደር ቤት ነው፤ ትዕዛዝ በእጅጉ ይከበራልና ወታደሮቹ የልባቸውን መሻት በውስጣቸው ይዘው ለሙያቸው እንደተገዙ በመጠባበቅ ላይ ናቸው፡፡ “ተዋቸው ይግቡ” የሚሉት አዛዦች በዚህ ጦርነት ድል እንደሚያደርጉ ተማምነዋል፡፡
ከወዲያ ማዶ የቀረበ የጠላት ኀይል እንደሌለ ሲያረጋግጡ እና “በለው” የሚለው የአዛዦች ትዕዛዝ እንደተሰማ የመሣሪያዎቻቸው ድምጽ ሕብረ ዝማሬ ፈጠረ፡፡ ጦርነቱ ቀሎባቸዋል፤ የጠበቁትን አይነት ፈተና የለም፡፡ ግን በድሎቻቸው አልታበዩም የወታደር ቤት ነውና መጠርጠር አንዱ መሣሪያ ነው፡፡ ቢያዩ የሚታይ የለም፤ ቢተኩሱ ምላሽ አልነበረም፡፡ ግን ባሉበት አሁንም ሌላ ትዕዛዝ እየተጠባበቁ ነው፡፡ የገቡት ሁሉ እንደመሻታቸው ሳይሆነ ቀርቶ እስከወዲያኛው አሸለቡ።
አንዱ ቡድን ሲያልቅ ሌላው ይተካል በወቅቱ የሆነውም እርሱ ነበር፤ ከገባው የተመለሰ ባይኖርም ከተከዜ ወዲያ ማዶ ሌላ ሟች ደግሞ በገፉ ቀርቧል፡፡ አሁን እንዳለፈው ጠላት ሰተት ብሎ አልገባም ተኩሱ ግን እንደቀጠለ ነው፡፡

234144184 1609722622536059 1265090250859261415 n

ከምሽጎቻቸው ያልወጡት ኀይሎች እስከ ምሽቱ 4:00 ገደማ ያልተቋረጠ ውጊያ አደረጉ፡፡ አሁን ከወዲያ ማዶ ያለው ኀይል የተዳከመ በመምሰል ተኩሱን አቁሟል፡፡
ሌሊት 10 ሰዓት ላይ ሟቾቹ ድጋሚ ጦርነቱን ከፈቱት በቂ ምላሽ እየተሰጣቸው እና እየተመቱ እስከ ረፋድ ቀጥለዋል፡፡ አልቻሉም የሞተው ሞቶ እና የቆሰለው ተኝቶ የተረፉት ወደኋላቸው ዞረው ሽምጥ እየጋለቡ ነው፡፡ በዚህ መካከል ግን የረሱት አንድ ኀይል ነበር፤ የቀድሞ ርዝራዦች ቆረጣ በሚል ሂሳብ አንድ ሸጥ ውስጥ እንደተቀረቀሩ ናቸው፡፡ ቆራጮቹ እንዳልነበሩ ሆነው ከመቆረጣቸው በፊት ከያዙት ትጥቅ መካከል የቀራቸው ቢኖር ምሽግ ላይ የሚጥሉት የእጅ ቦንብ እና ውስን ትጥቅ ብቻ ነበር፡፡
ከዚህ ጦርነት ማክተም በኋላ አካባቢውን እየተዘዋወሩ ከሚፈትሹ የአማራ ልዩ ኀይል አባላት መካከል አንዱ ዋና ሳጅን አስፋው ዘለቀ እነዚያ ቆራጮች ከተቀረቀሩበት ሸጥ አካባቢ ደረሰ፡፡ ፊት ለፊት ተያይተዋል፤ አይቷቸዋል እነርሱም አይተውታል፡፡ የተወሰኑ ቡድኖችን ፍላጎት ለማርካት ቅዥት ውስጥ የነበሩት ርዝራዦች ጀምበር እንደጠለቀችባቸው ቢያውቁም የሞት ሞታቸውን እና የእውር የድንብሱን የሚችሉትን መሞከራቸው አልቀረም ነበር፡፡ ወፍ ዘራሽ ከሆኑት ጥቂት ጥይቶች አንዷ በዋና ሳጅን አስፋው ላይ ቀላል ቁስል ፈጥራለች፤ ይህንንም ያወቀው በስኬት ከተጠናቀቀው ግዳጅ በኋላ ነበር፡፡
በፍጥነት ቦታ የያዘው ዋና ሳጅን እነዚህ ቡድኖች ከቀበሮ ዋሻቸው እንዲወጡ እድል መስጠት አልፈለገምና ደጋግሞ አርከፈከፈባቸው፡፡ “ጀግና” የሚላቸው የሻንበል አመራሮች እና የትግል ጓደኞቹ ከጎኑ በፍጥነት ደርሰዋል፡፡ በዚህ ወቅት ነበር አለመውጣታቸውን ያረጋገጡት ቆራጮች ተስፋ ቆርጠው የእጅ ቦንባቸውን ቀለበቱን አሹልከው ወደ ዋና ሳጅን አስፋው እና ጓደኞቻቸው ላይ የወረወሩት፡፡
ዋና ሳጅን አስፋው የወረወሩትን ቦንብ በሰማይ ላይ ተቀበላቸው እና መልሶ ወረወረላቸው፤ በዚህም ላይመለሱ ተሸኙ፡፡
የዚህ ጦርነት ጀግና ሁሉም የግዳጁ አባላት ቢሆኑም ዋና ሳጅን አስፋው “ቦምብ አጉራሽ” ኮከብ ሆኖ አጠናቀቀ የሚሉት ከግዳጁ አዛዦች መካከል አንዱ ሻምበል ደሳለኝ አምባው ናቸው፡፡ ዋና ሳጅን አስፋው በተኩስ ልውውጡ ወቅት ቆስሎ ነበር ያሉት ሻምበል ደሳለኝ ከሁሉም የሚለየው ግን ከጉዳቱ በደንብ ሳያገግም ለዳግም ግዳጅ ሰኔ 29/2013 ዓ.ም መሳተፉ ነው ይላሉ ምስክርነታቸውን ሲሰጡ፡፡
ውትድርና የቡድን ሥራ ነው ብለው የሚያምኑት ሻምበል ደሳለኝ በጦርነት ወቅት በጠላት ላይ ልቆ ለመውጣት ትብብር ወሳኝ መሆኑንም ይናገራሉ፡፡ እስካሁን በተደረጉ አውደ ውጊያዎች በርካታ ያልተዘመረላቸው ጀግኖች ታይተዋል፤ ገድላቸው እንዳይደበዝዝ ሆኖ በደማቁ በታሪክ ማህደር ውስጥ ይጻፋል ብለውናል፡፡
ዋና ሳጅን አስፋው ዘለቀ ዛሬ ደግሞ ለሌላ ብሔራዊ ግዳጅ ዝግጁ ሆኖ እንደሚጠብቅ ይናገራል፡፡ “አሸባሪዎቹን እንኳን በሕይዎት ቆመን ሞተን እንኳን አጥንታችን የተከዜን ወንዝ አያሻግራቸውም” የሚለው የተከዜው መብረቅ ሕዝቡ አምኖ እምነቱን እንደጣለብን እኛም ታማኝነታችን በብቃት የምናረጋግጥበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም ብሏል፡፡ በዳግም ድል ዳግማዊ ጀብዱን እንሰማለን!
በታዘብ አራጋው -ከሁመራ ግንባር
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 08/2013 ዓ.ም (አሚኮ)

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.