ከትግራይ ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት የተሰጠ መግለጫ

blgina 2

ምድረ ቀደምቷ ሃገራችን ኢትዮጵያ ባለ ብዙ ታሪክ፣ የብዙ ብሔር ብሔር ሰቦች እና ቋንቋዎች ባለቤት፣ የአይበገሬዎቹ ጀግኖች ሃገር፣ የልበ ሩህሩሆች እና ባለቀና ልብ አባቶች እና እናቶች ሃገር፣ የሰው ዘር መገኛ፣ እንግዳ ተቀባይ፣ ከምንም በላይ ሰብአዊነትን የሚያስቀድም ህዝብ ሃገር፣ ለፈጣሪ እንጂ ለማንም የማትንበረከክ እናት ሃገራችን በጣም ብዙ ፈተናዎችን አልፋ የውጭ እና የውስጥ ጠላቶችዋን ድል አድርጋ በታሪክ ላይ ታሪክ እየደራረበች እዚህ ደርሳለች፡፡

እነዚህን ፈተናዎች ስታልፍ ከምንም በላይ አንድነትዋን አጠናክሮ፣ በውስጥም በውጭም የሚፈጠሩ ባንዳዎችን ነጥሎ፣ ሴራቸውን እያከሸፉ የሃገራችንን ታላቅነት ማስጠበቅ ተችሏል፡፡
አሁንም ባንዳዎች ከውጭ ሃይሎች ጋር በጋራ በመሆን የግል ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ እና የሃገራችንን ጥቅም ለውጭ ሃይሎች አሳልፈው ለመስጠት ከሁሉም በላይ ሆዳቸውን በማስቀደም ሃገራችንን ለመበታተንና ህዝባችንን ለመከፋፋል ቆርጠው ተነስተዋል፡፡
የዚህ ሴራ ጠንሳሽ እና የነፍስ አባት ደግሞ አሸባሪው የህወሃት ቡድን ነው፡፡
የጥፋት ቡድኑ ሃገራዊ ለውጡን አልቀበል ብሎ ከሃገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ጋር ተነጥሎ ወደ መቀሌ ከፈረጠጠ በኋላ በየቦታው ካስቀመጣቸው ተላላኪዎቹ ጋር በመሆን ዜጎችን በማፈናቀል ብሔር ከብሔር ጋር በማጋጨት በየቦታው ሽብር በመፍጠር መንግስትን እና ህዝብን ለመነጠል በመሞከር ከውጭ እና ከውስጥ ሃይሎች ጋር ሴራ በማሴር ዓለም ያደነቃቸውን የመንግስት ስራዎች እና ውሳኔዎች በማጠልሸት እና በማናናቅ ተደጋጋሚ የውሸት ፕሮፖጋንዳ በመስራት ብሎም የትግራይን ህዝብ ጨቁኖ በመያዝ የጨረቃ ምርጫ በማካሄድ፣ በስተመጨረሻም በጀግናው የሃገር መከላከያ ሰራዊታችን ላይ ጭካኔ የተሞላው ክህደት በመፈጸም የትግራይ ህዝብ ልማት ሰላም እና አንድነት በሚሻበት ወቅት ህዝቡ እንዳይረጋጋ ክልሉን የጦርነት አውድማ አድርጎታል፡፡
በመሆኑም የትግራይ ብልፅግና ፓርቲ ፅ/ቤት የህወሓትን ሴራ እና ሃገር የመበታተን አጀንዳ በመቃወም የሚከተለውን የአቋም መግለጫ አውጥተናል፡፡
1. ህወሓትና የትግራይ ህዝብ አንድ ነው ብሎ የጥፋት ሃይሉ የሚያሠራጨው ትርክት በምንም ዓይነት መንገድ ተቀባይነት የሌለው የሀሰት ዲስኩር ነው፤ ፓርቲ እና ህዝብ አንድ ሆነው አያውቁም፣ አንድ ሊሆኑም አይችሉም፤ ይህን የውሸት ፕሮፖጋንዳ እናወግዛለን፡፡
2. ትግራይን ከኢትዮጵያ ለመገንጠል የሚደረገውን ሴራ እናወግዛለን፡፡
3. በሽብር ቡድኑ ላይ የተከፈተው ዘመቻ ፀረ-ትግራይ ህዝብ ነው እየተባለ የሚቀርበው ፕሮፓጋንዳ ተቀባይነት የሌለው ነው፤ ዘመቻው ህዝብን ምሽግ አድርጎ ህዝብን እያሥጨረሰ ህፃናትን ወደ ጦርነት እየማገደ ካለ የሽብር ቡድን ጋር መሆኑን እንገልፃለን፡፡
4. የጥፋት ቡድኑ የትግራይ ህዝብ ከሌሎች የኢትዮጵያ ወንድም ህዝቦች ጋር እንዳይገናኝ፣ አርሶ ሰርቶ እንዳይበላ፣ ነግዶ እንዳይገባ፣ በጭለማ እንዲኖር፣ ጦርነት ብቻ እንዲያሥብ፣ ልማት እና ብልፅግና እንዲረሳ፣ ህዝብ ከህዝብ ጋር እንዲቃረን ያደረገበትን አግባብ አጥብቀን እናወግዛለን፡፡
5. ራሱን ንፁህ አድርጎ መንግስትን ጥፋተኛ ለማስመሰል ከባእድ ሀገራት ጋር የሚያደርገውን የሃገር ክህደት ግንኙነትን እናወግዛለን፡፡
6. በአፋር ክልል ወንድም/እህት ህዝባችን ላይ የፈፀመውን ጭፍጨፋ እና ማፈናቀል እናወግዛለን፡፡
7. በአማራ ክልል ወንድም/እህት ህዝባችን ላይ የሚፈፅመውን ጭፍጨፋ እና ማፈናቀል እናወግዛለን፡፡
8. በጊዜያዊ አስተዳደሩ የነበሩ አመራሮች ላይ የፈፀመውን ዘግናኝ ግድያ፣ አካል ማጉደል እና ንብረት ማውደም እናወግዛለን፡፡
9. በትግራይ ባሉት የጊዜያዊ አስተዳደሩ ቤተሰቦች እና ዘመዶች ላይ የሚደረግ ማሸማቀቅ፣ ዘለፋ እና ትንኮሳን እናወግዛለን፡፡
10. ከትግራይ ክልል ውጭ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጅ ወገኖቻችን እንደ ማንኛውም ዜጋ በሰላም እና በደህንነት ወጥተው እንዲገቡ፣ ሰርተው እንዲበለፅጉ ከሚመለከተው አካል ጋር በመሆን እንሰራለን።
11. በገንዘብ፣ በሞራል፣ በፕሮፓጋንዳ እና በመሳሰሉት የሽብር ሃይሉን የሚደግፉ ማንኛውንም አካል እናወግዛለን፤ በህግ እንዲጠየቁም ከሚመለከተው አካል ጋር በጋራ በመሆን እንሰራለን፡፡
12. በስህተት፣ በጥርጣሬ፣ ሳይጣራ እና ሳይረጋገጥ የታሰሩ፣ ንብረታቸው የታገደ እና ንግድ ቤታቸው የተዘጋ ተጋሩ ካሉ ቶሎ ፍትህ እንዲያገኙ ከሚመለከተው አካል ጋር በመሆን እንሰራለን፡፡
13. ማንኛውም በሃገራችን ላይ የሚደረግ የውጭ ጫና እና ጣልቃ ገብነትን በፅኑ እናወግዛለን፡፡
14. ጀግናው የሃገር መከላከያ ሰራዊታችን ለሚያካሂደው የህልውና ዘመቻ ማንኛውንም ዓይነት ድጋፍ እና እገዛ እናደርጋለን፡፡
15. በሁሉም ክፍላተ-ዓለማት የምትገኙ አንዳንድ ተጋሩ ዳያስፖራዎች ለሽብር ቡድኑ የምታደርጉትን ድጋፍ ትታችሁ ለሃገራችሁ እና ለህዝባችሁ ዘብ እንድትቆሙ ጥሪያችንን እናስተላልፋን።
በመጨረሻም የትግራይ ህዝብ ፍላጎት ሰላምና ሃገራዊ አንድነት እዲረጋገጥ እንጂ ሃገር የማፍረስ አጀንዳ ኖሮት አያውቅም፣ አሁንም የለውም፤ ስለሆነም እየተደረገ ያለው ሃገር የመበታተን አጀንዳ የሽብር ቡድኑ ፍላጎት እና እንቅስቃሴ እንጂ ህዝባችንን አይገልፅም፡፡
ተጋሩ በያለንበት አንድ በመሆን የዚህን የሽብር ቡድን እንቅስቃሴ ልናወግዘው ይገባል፡፡
አንድነታችንን ለማረጋገጥ የምንችለውን ሁሉ ከፌዴራል መንግስት ጎን በመሆን እንድንንቀሳቀስ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
የትግራይ ህዝብ ወደ ብርሃን ይሸጋገራል!!
ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ ፈጣሪ ትዘረጋለች!
የትግራይ ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት
ነሓሴ 2013 ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
ተጨማሪ ያንብቡ:  የምክር ቤት አባላት ለ ዐቢይ አሕመድ ያቀረቧቸው ጥያቄዎች

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share