“እኛ ለማንነታችን ብንሞት ኩራት ነው፤ ወራሪ ያለቦታው ሲሞት ግን ውርደት ነው” ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ

ከግል ክብር የሀገር ፍቅር፣ ከራስ ሕይዎት የሀገራቸው ሉዓላዊነት፣ ከግለሰባዊ ዝናና ሃብት የሰንደቃቸውን ከፍታ እና የተከበረ ማንነትን አጥብቀው የሚሹ ኢትዮጵያዊያን ትናንት ነበሩ፤ ዛሬም አሉ፤ ነገም ይኖራሉ፡፡ ኢትዮጵያዊነት ከዘር፣ ከእምነት እና ከቋንቋ በላይ መሆኑ የገባቸው ኢትዮጵያዊያን የሀገር ፍቅር ምንጫቸው ጥቅም ሳይሆን ለሀገራቸው የነበራቸው ቀናዒነት እና እምነት ነበር፡፡ የትናንቷ ኢትዮጵያ ፈተናዎቿን በልጆቿ አጥንት እና ደም እያለፈች ታፍራና ተከብራ የኖረች ነፃ ሀገር ናት፡፡ ነፃነት ለኢትዮጵያ ከአጥንቷ አጥንት ከደሟ ደም የወረሰ እስትንፋሷ ነው፡፡

demeke
demeke

ከማይጨው እስከ ውጫሌ፣ ከካራማራ እስከ መተማ፣ ከዓድዋ እስከ ዘይላና በርበራ ኢትዮጵያ በጭንቅ ጊዜዋ ሁሉ ተስፋዋ ፈጣሪዋ እና ልጆቿ ብቻ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ በመታመኗ አፍራ፤ በልጆቿ አንገቷን አቀርቅራ አታውቅም፡፡ ኢትዮጵያ በማሸነፏ መታበይን እና በጉልበቷ መሰናከልን አትሻም፡፡ ኢትዮጵያ ጦርነትን አትወድም ነገር ግን በሉዓላዊነቷ ድርድር አይዋጥላትም፡፡ ኢትዮጵያ ከራስ ደጀን የገዘፈ፣ ከኤርታሌ የበረታ፣ ከዓባይ ወንዝ የረዘመ እና ከዓድዋ ከፍ ያለ የነፃነት ታሪክ ያላት ሀገር ናት፡፡ ልጆቿ በኢትዮጵያ አያፍሩም ኢትዮጵያም በልጆቿ አንገቷን ዘንበል አድርጋ አታውቅም፡፡

 

ኢትዮጵያ ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች አርነት መውጣት ምክንያት ነች፡፡ ከሞኖሮቢያ እስከ ካዛብላንካ፤ ከአሜሪካ እስከ ደቡብ አፍሪካ በዓለም ላይ ያሉ ጥቁሮች ለነፃነታቸው ሲታገሉ ራዕያቸው እንደኢትዮጵያ ነፃ ሀገር እና ነፃ ሕዝብ መሆን ነበር፡፡ ኢትዮጵያዊያን አያት ቅድመ አያቶች ከኮሪያ እስከ ሊቢያ፤ ከሶማሊያ እስከ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ለፍትሕ፣ ለነፃነት እና እኩልነት በዓለም አደባባይ እስከ ወዲያ ማዶ ድረስ ተሻግረው ዘብ ቆመዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዘላለማዊ ነፃነት እና ክብር በፍላጎት ብቻ የመጣ ሳይሆን ልጆቿ ቁልቁለት ወርደው፣ ዳገት ወጥተው፣ በጀምላ ተቀብረው፣ አጥንታቸው ተከስክሶ እና ደማቸው ፈሶ የተገኘ ነፃነት ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ዘላለማዊ ነፃነት እና ክብር ሲባል እልፍ ህጻናት ያለአሳዳጊ አዕላፍት አረጋዊያን ወላጆች ያለጧሪ ቀባሪ መከራን ተቀብለዋል፡፡ እናት ስለልጆቿ ህልፈት በመቀነት ፋንታ ገመድ ታጥቃ እየየ ብላለች፡፡

 

የኢትዮጵያዊያንን የነፃነት ተጋድሎ ዋጋ ይውጣለት ቢባል እንኳ ወርቋ የማይበቃው፣ ተፈጥሮ ሃብቷ የማይመጥነው እና ውበቷ የሚያንስበት እንጅ የሚበዛበት አይደለም፡፡ ኢትዮጵያዊያን ለሀገራቸው የከፈሉት ዋጋ ልኩ “የሀገር ፍቅር ስሜት” ብቻ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ዘላለማዊ ነፃነት መከበር ከወታደር እስከ ምሁር፣ ከቄስ እስከ ቆሞስ፣ ከአርሶ አደር እስከ ሚኒስቴር፣ ከእመበለት እስከ እመቤት፣ ከንጉሥ እስከ ንግሥት፣ ከደረሳ እስከ ዑላማ፣ ከህፃን እስከ አዋቂ ሁሉም በነቂስ እየወጣ ዋጋ ከፍሎላታል፡፡

 

ይህ ለኢትዮጵያ ዘላለማዊ ክብር እና ነፃነት ሲባል የሚደረግ የትግል ታሪክ ብቻ አይደለም፤ በዚህ ትውልድ ሳይቀር የሚፈጸም ኑባሬ ገድል ጭምርም እንጅ፡፡

 

በዚህ ዘመንም ለኢትዮጵያ ነፃነት የአማራ ሕዝብ ከከፈለው ታላቅ የመስዋእትነት ጀብዱ መካከል አንዱ ሐምሌ 5/2008 ዓ.ም በአፍሪካ ካሜሎት የኢትዮጵያ ወርቃማው ዘመን መዲና በሆነችው ጎንደር የተፈጸመው ተጋድሎ ነው፡፡

ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት የኢትዮጵያን የሥነ-መንግሥት እርካብ ተቆናጥጦ የነበረው አሸባሪው ትህነግ ጣሊያን በአደባባይ ከፈጸመችው ግፋ ጋር ሲነጻጸር ወደር የማይገኝለት በደል እና ሴራ በወገኖቹ ላይ አዝንቧል፡፡

 

ኢትዮጵያዊ ቱባ ባህል እንዲከስም፣ ፈሪሃ ፈጣሪ እንዲመነምን፣ መከባበር እንዳይኖር፣ ኢትዮጵያዊነት እንዲዳከም እና መተማመን እንዳይኖር ሳይሰለች ቀን ከሌሊት ሠርቷል፡፡ በዚህም ጥረቱ ከሀገር የወረደ ጎጠኝነት፣ ከሰብዓዊነት የወረደ ስርቆት፣ ከወገን ፍቅር የራቀ ግለኝነት እና ከሞራል የተናጠበ ስብዕና ታይቶ ነበር፡፡

በርካቶች በሀገራቸው ባይተዋር ሆነው በግፍ ተሰደዋል፣ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ እድሜ ዘመናቸውን ገፍተዋል፣ መቃብራቸው እንኳን ሳይታወቅ ደብዛቸው የጠፉም ብዙዎች ናቸው፡፡ አካላቸው የጎደለውን፣ መንፈሳቸው የተሰበረውን እና አንገት ደፍተው የኖሩትን ቤት ይቁጠረው፡፡

 

አሸባሪው ትህነግ ባለፉት 30 ዓመታት ኢትዮጵያን በመዝረፍ፣ አሳልፎ ለውጭ ኀይል በመስጠት፣ ዜጎቿን በጎሳ ፖለቲካ ከፋፍሎ የሐሰት ትርክት በመፈብረክ በጥላቻ እንዲተያዩ ከማድረግ ባለፈ በተስፋፊነት ባህሪው በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩትን አሰድዷል፣ ገድሏል፣ አፈናቅሏል፣ የግፍ ግፍ ፈፅሟል።

 

ከዚህ ሁሉ ግፍና መከራ በኋላ የዚህ ዘመን ትውልድ የነፃነት ትግል ፋና ወጊ፣ መንገድ ጠራጊ እና ስትራቴጂ ቀያሹ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ነው፡፡ የጀመረውን ትግል የነፃነት ጎህ ሲቀድ አላቆመም፤ ይልቁንስ የደከመውን እያበረታ፣ የጎደለውን እየሞላ እና ከልምድ ያገኘውን ወታደራዊ ጥበብ እያካፈለ ዛሬም ከትግሉ ፊት ላይ ነው፡፡

 

ነፃነት ለሰው ልጅ የተሰጠ ጸጋ ነው ብሎ የሚያምነው ኮሎኔል ደመቀ ነገር ግን ያለ መራር ተጋድሎ ነፃነት አይገኝም ይላል፡፡ የምንፈልገው ማንነት እንጂ የምንፈልገው ሰላም ገና አልመጣም፤ ለዚህም ሲባል ጨርቄን እና ማቄን ሳንል ለሕልውና ዘመቻው ወደፊት መግፋት ግድ ይላል ባይም ነው፡፡

 

ሕዝባዊ ወረራ ከተፈጸመ ሕዝባዊ ሆኖ ሕልውናን መታደግ እና ምላሽ መስጠት ጥፋት የለውም የሚለው ኮሎኔል ደመቀ ወቅቱ የአማራ ሕዝብ በመራር ተጋድሎው ዘላለማዊ ነፃነቱን የሚቀዳጅበት ወሳኝ ወቅት እንደሆነም ይናገራል፡፡ “በባህላችን ስለማንነቱ የማይሞት ወንድ ልጅ፣ ባይወለድ ይመረጣል ነው የሚባልና ዳግም ሴቶቻችን እና እናቶቻችን አንገት የሚደፉበትን ጊዜ ማየት አንሻም” ብሎናል፡፡ ለዚህም በየተሰማራንበት የሙያ እና የሥራ ዘርፍ እውቀት ያለው በእውቀቱ፣ ሃብት ያለው በሃብቱ፣ ጉልበት ያለው በዘመቻ እና ያልቻሉ ደግሞ ስለነጻነታቸውና ስለመበደላቸው ግፍ ሲሉ በጸሎት የሚያግዙበት ወቅት እንደሆነ ይናገራል፡፡

 

“እኛ ለማንነታችን ብንሞት ኩራት ነው፤ ወራሪ ያለቦታው ሲሞት ግን ውርደት ነው” ያለው ኮሎኔል ደመቀ በየትኛውም አካባቢ ያለውን የአማራ ሕዝብ የሕልውና ዘመቻ ሁሉም በነቂስ ወጥቶ መቀላቀል አለበት ብሏል፡፡

ኮሎኔል ደመቀ አማራ ጠላቴ ነው ብሎ በማኒፌስቶ ሳይቀር ካወጀ ኀይል መልካም ዜና መጠበቅ ሞኝ ያስብላል ካለ በኋላ ጠላት በፕሮፖጋንዳ ለመረበሽ ይሞክራል ነገር ግን በወሬ መፈታት የአማራ ሕዝብ የሥነ ልቦና ስሪት አይደለምና አማራ በየግንባሩ ከትቶ በየአውደ ውጊያው እንገናኝ ብለዋል፡፡

 

ዘጋቢ:–ታዘብ አራጋው -ከሁመራ ግንባር
አሚኮ

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.