ጠቢቡ ሰለሞን የፈተናት ሴትና ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚፎክሩት እርጉሞች! – በበላይነህ አባተ

በበላይነህ አባተ abatebelai@yahoo.com

ተሰው ልጅ የሥነ ልቦና ቀውሶች ሁሉ የዝቅተኝነት መንፈስን የሚያህል አደገኛና እርኩስ መንፈስ የለም፡፡ የመንፈስ መፍዘዝ (ዲፕሬሽን) ያለበት ሰው ራሱን ሊያጠፋ ይችላል፡፡ ነገር ግን ሕዝብን ወይም አገርን አያጠፋም፡፡ የመንፈስ ጭንቀት ያለበት ሰው ለራሱ ወይም ለቤተሰቡ ሳይጠቅም ሊቀር ይችላል፡፡ ነገር ግን እምብዛም ሕዝብን ወይም አገር አይጎዳም፡፡ የመንፈስ ዝቅተኝነት የተጠናወተው ሰው ግን ተአገር አልፎም አሀጉርንና ዓለምን ሊያናውጥ ይችላል፡፡

et23 429x455 ጠቢቡ ሰለሞን የፈተናት ሴትና ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚፎክሩት እርጉሞች!   በበላይነህ አባተ
et23

የመንፈስ ዝቅተኝነት የተጠናወታቸው ጉዶች ወጣንበት የሚሉትን ሕዝብ በተረት ተረት ወሬ እያወናበዱ በስንት ሰማእታት ደም ስትጠበቅና ስትገነባ የኖረቸዋን ጥንታዊት ኢትዮጵያን “እናፈርሳታለን” እያሉ በአደባባይ ሲዝቱ ይታያል፡፡ የዝቅተኝነት መንፈስ አንድ ቦታ ስለማያስቀምጥና በተናገሩት ስለማያቆይ በዘጠነኛው ምላሳቸው ደሞ “ኢትዮጵያን ስንጠብቃት የኖረነው እኛ ነን” ሲሉ ይደመጣል፡፡ ታዲያ እነሱ ሲጠብቋት የኖሯትን አገር ለማፍረስ ዲያብሎስ ለምን እንደ መስክ አለሌ ይጋልባቸዋል?

እነዚህ ዲያብሎስ በመንፈስ ዝቅተኝነትና በምቀኝነት የሚጋልባቸው እርኩሶች ጠቢቡ ሰለሞን የፈተናትን አንዲት ዓይና አውጣና ምቀኛ ሴት ያስታውሱናል፡፡

የብሉይ ኪዳኑ መጽሐፈ ነገስት ቀዳማዊ ምእራፍ ሶስት እነደሚያስተምረው በጠቢቡ ሰለሞን ዘመን በአንድ ቤት ውስጥ የሚኖሩ ሁለት ሴቶች በሶስት ቀን ልዩነት ውስጥ ልጆች ወለዱ፡፡ በኋላ የወለደችው ሴት ሌሊት ልጇን ተጪና ገደለችው፡፡ ይህቺ ልጇን የገደለችው ሴት በእኩለ ሌሊት ተነስታ የገደለችውን ልጇን እንቅልፍ ተወሰዳት ሌላኛው ሴት ጎን አስተኛችና የእሩሷ ያልሆነውን ልጅ ወሰደች፡፡ እንቅልፍ የወሰዳት ሴት ተእንቅልፏ ስትነቃ የሞተ ልጅ ተብብቷ ሥር አገኘች፡፡ ነገር ግን በብርሃን ስትመለከተው የእርሷ ልጅ የሞተው ሳይሆን ሴትዮዋ በጨለማ የሞጨለፈችው መሆኑን ተገነዘበችና ጉዳዩን ተንጉስ ሰለሞን ፊት ለፍርድ አቀረበች፡፡

ንጉስ ሰለሞን የሁለቱንም ሴቶች የይገባኛል ክርክር ታዳመጠ በኋላ “ልጁን ለሁለት ሰንጥቄ እኩል አካፍላችኋለሁ!” የሚል ፈታኝ ሐሳብ አቀረበ፡፡ እውነተኛይቱ እናት “ጌታዬ ሆይ ለእርሷ ስጣት እንጅ አትገድል” ስትል ንጉስ ስለሞነን ተማጠነች፡፡ ልጇን ተጭና የገደለችው ምቀኛ ሴት ግን “ይገደል እንጅ ላንቺም ለኔም አይሆንም ስትል” ዛተች፡፡ ንጉስ ሰለሞንም እውነተኛዋ እናት የትኛዋ እንደሆነች በዚህ ጥበብ ተገነዘበ፡፡

ኢትዮጵያ ተመተራ ትሙት በሚሉ የትኛውንም ሕዝብ በማይወክሉ ነገር ግን መንጋን በሚያደናብሩ ጥቂት ጭራቆችና ኢትዮጵያ ተመትራ ተምትሞት እኛ እንሙት በሚሉ ብዙሐን ክርክር ውስጥ ትገኛለች፡፡ ይኸንን ተመልክቶ በመለኮታዊ ፍርድ ተጭራቆች የሚገላግላት ጠቢብ ወይም የጭራቆችን የሰይጣን ሰይፍ የሚቀለጥምላት ብርቱ ኃይል ቅዱሳን መጻሕፍት የሚያወሷት ኢትዮጵያ በመጠባብቅ ላይ ትገኛለች፡፡

ዛሬም እንደ ጥንቱ ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ ሰማይ ዘርግታለች፡፡

 

ነሐሴ ሁለት ሺ አስራ ሶስት ዓ. ም.

 

1 Comment

  1. በኢትዮጵያ ውስጥ ወያኔን ለመፋለም ቁርጠኝነት በህዝቡ ውስጥ እንዳለ ለመረዳት ቀላል ነው። 27 ዓመት ሲረግጠውና በጎሳና በክልል ከፍሎ ሲነግድበት የነበረውን ወያኔን ለአንድ ጊዜና ለመጨረሻ ጊዜ ለመፋለም እንቅስቃሴው ሰማይ ደርሷል። ይህ የሃይል ስብስብ ግን ጠንካራ አመራር ከተቀናጀ ስሌት ጋር ካልተሰጠው ይገኛል የተባለው ውጤት ሊዘገይ ወይም ሊደናቀፍ ይችላል። ዝም ብሎ እንካ ጠበንጃ ሳንጃ ወድር ወደፊት ማለቱ ብቻውን በቂ አይደለም። የሲቪልም ሆነ ወታደራዊ ሰራዊቱ ጥብቅ መመሪያ ሊሰጠው ይገባል። ውጊያ ከባድ ነገር ነው። ከጎንህ ከደቂቃ በፊት ቆሞ ይተነፍስ የነበረው ጓደኛህ ሲገደል ስታይ እይታህን ሁሉ ይቀይራል። ብቀላ፤ ገዳዪን አሳዶ መግደል ብሎም የጠራ አስተሳሰብ በውጊያው ላይ እንዳይኖር ያደርጋል። ለዚህ ነው በዲሲፒሊንና በውጊያ ስልት ልምድ ያላቸውን ሰዎች እንዲመሩ በማድረግ ፍልሚያው ንጽሃንን በማይጎዳ ሁኔታ መካሄድ ያለበት። ይህን በዚህ ልቋጭና ወደ ሌላው ነጥብ ልለፍ።
    አምነስቲ ባወጣው ዘገባ መሰረት ሴቶች በትግራይ ግጭት ተደፍረዋል። ይህ አሊ የሚባል ነገር አይደለም። ግን ደፋሪው ሃይል ማን ነው? እንደሚባለው የኢትዮጵያና የኤርትራ ሰራዊት አባላት ናቸውን? ወይስ ራሱ የትግራይ ወንድ ህግና ደንብ መፍረሱን አይቶ የፈጸመው ተግባርም አለበት? ጉዳዪ አወዛጋቢ ነው። ልብ ያለው ግን አንድ ነገርን ይረዳ። የትግራይ ሴቶች ግጭቱ ከመፈጠሩ በፊት በሴቶች ላይ የሚደረገው ጾታዊ ጥቃት ይቁም በማለት ሰልፍ ወጥተው እንደነበረ ነው። ያኔ ማን ነበር ያለፍቃዳቸው ይደፍራቸው የነበረው? አምነስቲ የአሜሪካ ጡሩንባ ነው። በአፋር ህጻናትና አዛውንት ሳይቀሩ በግፍ ሲጨፈጨፉ ለዓለም ህዝብ በመሪ ዜናው ላይ ይዞ የቀረበው ስለ ትግራይ ሴቶች መደፈር ነው። የትግራይ ሴቶች በወያኔ በበረሃም በከተማም ሃበሳቸውን ያዪ ለመሆናቸው ከሞት የተረፉትን ጠይቆ መረዳት ነው። እርግጥ ነው በዚህ ግጭት ላይ በትግራይ ሴቶች ላይ ጾታዊ ጥቃት የፈጸመ ማንም ሃይል ቢሆን መጠየቅ አለበት። አምነስቲ ግን ትንኝን በመዶሻ ለመግደል የሚጥር ከእውነት ጋር የተጋጨ ዜና ኢትዮጵያን ለማጠልሸት መልቀቁ ከአሜሪካውና ከአውሮፓው ህብረት የዝሆን ጀሮ ይስጠኝ ፓለቲካ ስልት የተቀዳ ነው። በሃሺሽ ጠብረው፤ በልጅነታቸው በወያኔ አስገዳጅነት ጦር ሜዳ ስለተሰለፉት የትግራይ ልጆች ምንም አላሉ። በወያኔ ወረራ ከ 300 ሺህ ህዝብ በላይ ስለተፈናቀለው የአማራ ህዝብ ለምን አያወሩም? የነጩ ዓለም ቀዳሚ እቅድ እርስ በእርሳችን ስንገዳደል ቆሞ ማላገጥና አልፎ ተርፎም እሳት ማቀበል ነው። ዛሬ ከ 20 ዓመት ወረራ በህዋላ አፍጋንስታንን ጥሎ የወጣው የአሜሪካ ደንባራ የውጭ ፓሊሲ ገና ብዙ መዘዝ ያመጣል። የአፍጋንስታንም እድል ፈንታ በአክራሪዎች እጅ ዳግም መውደቅና እንደ እንስሳ መነዳት ነው። ከአጋም የተጠጋ ቁልቋል ሁሌ ሲያለቅስ ይኖራል እንዲሉ አሜሪካ በሃገሯም ዲሞክራሲ የላትም ለሸቀጥም የምታቀርበው ጭላፊ ዲሞክራሲን አታውቅም። ለዚህ ነው ከዲክተተሮችና ክደም አፍሳሾች ጋር የውጭ ፓሊሳቸው ክርችም ብሎ ግጣም የሚሆነው። አሁን ሰው ነኝ የሚል ሳውዲ አረቢያ ውስጥ ዲሞክራሲ አለ ብሎ ያምናል? ግን ለእኛ ከጠቀመ ድቄቱን አምጭው የትም ፍጭው አይነት ነው። የሱዳኑ የቀድሞ መሪ አል በሽርን ወደ ሄግ የአለም ዳኝነት እልካለሁ ያለችው ሱዳን የምታስቅ ሃገር እየሆነች ነው። በዳርፉርና በሌሎች አካባቢዎች የሰው ልጆችን መብት ገፎ ሰውን እንደ እንስሳ ይገድል የነበረው እኮ አል ባሻር ብቻ አልነበረም። አሁን በጊዜአዊ አስተዳደሩ የተዋቀሩት ስመ ጄኔራሎችና ሌሎች መኮንኖችም ጭምር እንጂ። ግን አሜሪካ ለይስሙላ አል ባሽርን ብቻ ሱዳን አሳልፋ እንድትሰጥ መጠየቋ ሌሎች ጄኔራሎች የራሷ የአሁን ሰራተኞች እንደሆኑ ያመላክታል።
    ባጭሩ ሃገራችን ምጥ ውስጥ ናት። በየጊዜው በወያኔው ሚዲያ ቢቢሲ ብቅ እያለ የሚደነፋው ጌታቸው ረዳ እንደ እስስት መልክና ሃሳቡን እየቀየረ የሚለው ሁሉ መላ ያጣ ሃሳብ እንደሆነ የትላንቱን ከዛሬው ሃሳቡ ጋር አመሳክሮ ማየት ይቻላል። ጌታቸው አሁን ደግሞ የሚለን የትግራይ ከበባ እስኪፈርስ ድረስ ነው የምንዋጋው ሌላ ዓላማ የለንም ይለናል። አሁን ከሃገሪቱ ክፍል እየተመለመለ የሚመጣውም የሚጠብቀው ሞት ብቻ ነው በማለት ደንፍቷል። ገዳይ ባለበት ሟች ይኖራል። ገዳይ ነኝ እኔ ብቻ ብሎ ማጓራት ግን ከነጠፈ ጭንቅላት የሚወጣ ድፍድፍ ሃሳብ ነው። ቆም ብሎ ተፈጥሮ የለገሰውን ጭንቅላት ተጠቅሞ ላሰላሰለ በ 21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ተቀምጠን ወንድም ወንድሙን እህት እህቷን ገላ የምንፎክር የነፎዝ ክምሮች ነን። ወያኔ ለትግራይ ህዝብ ገዶት አያውቅም። ወደ 50 ዓመት እየተጠጋ በመጣው ታሪኩ ውስጥ አሁን እንደገባበት ያለ ማጥ ውስጥ ጭራሽ ገብቶ አያውቅም። መውጫም የለውም። ይታየኛል የትግራይ ህዝብ አንገፍግፎት ሆ ብሎ ተነስቶ የወያኔን አስከሬን እንደ ሞሶሎኒ ዝቅዝቆ ሲሰቅል። የትግራይ ህዝብ ጦርነት ሰልችቶታል። የተከፈለው ካድሬ ሁሉ በፎከረ ቁጥር የትግራይ ህዝብን ጦረኛ አርጎ ማየት አይቻልም።
    ለኢትዮጵያ መንግስት ሃሳብ እባካችሁ ማረክን የምትሏቸውን ልጆች አሰልፋችሁ አታሳዪን። ምን ያደርጋል? በመልካም እንክብካቤ እንዳሉ ብቻ አሳዪን እንጂ ሰልፉን ወያኔ ያልማረከውን ማረኩ እያለ ካለፈ ታሪክ እየቀነጨበ በውሸት ቪዲዮና ዲስኩር አስልችቶናል። የመግለጫ ጋጋታችሁም ይቁም። እረ በፈጠራችሁ ተውን? ያው እንደ ደርግ ለይቶላችሁ ከበሮ ደልቃችሁ የፍየል ወጠጤ ማለት ነው የቀረቻሁ። ሙያ በልብ ነው። ጸጥ ረጭ ባለ አሰራር የጦር ሜዳውንና የቢሮውን ውሎ በፊልም በመዘገብ ሥራን መስራት ነው። ቀረርቶ ሰለቸኝ! በመጨረሻም ጸሃፊው ” ዛሬም እንደ ጥንቱ ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ ሰማይ ዘርግታለች” ይላል። ይህ ከእውነት የራቀ ሃሳብ ነው። የምንዘረጋው እጅ የለንም። እጃችን ላይ ተቀምጠንበታል። እንዲያ ቢሆንማ ፈጣሪ ጸሎታችን ሰምቶ ከመተላለቅ እንተርፍ ነበር። ያ ግን አልሆነም። ትላንትም ሞት ዛሬም ሞት። ደጋግሜ እንዳልኩት የኢትዮጵያ ፓለቲካ ውስጥ ፈጣሪ የለም። ዝም ጭጭ ብሏል። እኛም ባናስቸግረው መልካም ነው። በቃኝ!

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.