ብዙዎች ያወራሉ ወልድያዎች ይሠራሉ…- ታርቆ ክንዴ – ከወልድያ

231586102 1603483629826625 8933341916490444987 n

ጀግኖች ይሠራሉ፡፡ ፈሪዎች ያወራሉ፣ በሚያወሩት ወሬ ራሳቸውን አሸብረው ሌላውንም ለማሸበር ይሞክራሉ። ልቡን ያመነ፣ በአንድነቱና በጀግንነቱ የተማመነ ይዘምታል፣ ለክብር ሲል ሕይወቱን፣ ምቾቱን፣ ጉልበቱን አሳልፎ ይሰጣል። እኔስ ጀግንነት አየሁ። ጀግንነት ያንስባቸዋል፣ ወሬ አያሸብራቸውም፣ የውሸት ነጋሪት አይበግራቸውም፣ ክብር፣ ሀገር፣ አንድነት፣ ማንነት አይደፈሬነት የየዕለት መገለጫቸው ነው፣ እንቅልፍ ትተዋል፣ ምቾት ረስተዋል፣ ደከመኝ ማለት ዘንግተዋል፣ ጀንበር በጠለቀችና በዘለቀች ቁጥር ዓይናቸውን ከጠላት እንቅስቃሴ ላይ ሳያነሱ ከተማቸውን ይጠብቃሉ፣ ብቅ የሚለውን ጠላት ያንቃሉ።

ምን አይነት ጀግንነት ነው ያለ መታከት መዋጋት፣ ማዋጋት፣ ስንቅ ማቀበል፣ የጠላትን አረም እየተከታተሉ መንቀል። ነዲዶች ናቸው የሚያቃጥሉ፣ መብረቆች ናቸው ከሩቅ የሚጥሉ፣ ቆራጦች ናቸው ነብስን ከስጋ የሚነጥሉ፣ ለካስ የጀግኖች መፍለቂያ ምንጭ አልነጠፈችም፣ ዛሬም ያለ ማቋረጥ ትፈስሳለች፣ በቸገረ ቀን ደርሳ አንጄት ታርሳለች። ጥም ትቆርጣለች።
ጨለማ ዘመነ ስልጣኑ ደርሶ ምድርን ጥቁር አልብሷታል። በተራራ የዋሉት እረኞች ወደየቤታቸው እየተመለሱ ነው። በመንገድ ላይ በሚገኙት ትንንሽ ከተሞች የሚኖሩ ወጣቶች በቡድን በቡድን ኾነው አካባቢያቸውን በትጋት እየጠበቁ ነው። ትጋታቸው አጃኢብ ያሰኛል። በየአቅጣጫው የዋለው ሁሉ ወደቤቱ እየከተተ ነው። ጨለማው ከበድ ባለበት ምሽት ወደ ወልዲያ እየገሰገስኩ ነው። ከተራራዎች ግርጌ የተጠለለችው ወልድያ በጨለማም ውስጥ ኾና የደስ ደሷን አልተነጠቀችም። በቀኝና በግራ የቆሙላት ተራራዎች ለክብሯ ሲሉ የክብር ጥላ አልብሰዋት የቆሙ ይመስላሉ። ወልድያ ከተማ ጫፍ ደርሻለሁ፣ ዘው ተብሎ ወደ ከተማዋ መግባት አይቻልም። እሳት የላሱ ወጣቶች በተጠንቀቅ ቆመዋልና። ወደከተማዋ የሚገቡትን ሠዎች በሚገባ አጣርተው፣ ፈትሸው ሰላማዊ ሰው ሲሆን ብቻ ነው ወደ ውስጥ የሚዘልቀው።
እኔም ወጣቶቹ ያስቀመጧቸውን የደኅንነት መስፈርቶች ሳሟላ ወደ ውስጥ እዘልቅ ዘንድ ተፈቀደልኝ። ቤቱ ውስጥ የተኛ ወጣት ያለ አይመስልም፣ የከተማዋ ጎዳናዎች ሁሉ በተደራጁ ወጣቶች በጥንቃቄ ይጠበቃሉ፡፡ አሸባሪው ትህነግ የሚያሰማራቸውን የሽብር ሰዎችን እየተከታተሉ ያንቃሉ። ከእነርሱ የሚሠወር የትህነግ ሰላይም ኾነ ተዋጊ የለም። እሳት በጨበጠው እጃቸው ቢሻቸው ይጠብሱታል፣ ቢሻቸው አቃጥለው አመድ ያደርጉታል።
የአሸባሪው ትህነግ ቅጥረኞች ወልድያን ያዝናት እያሉ ካስወሩ ቀናት ተቆጥረዋል። ዳሩ ግን ወልድያ ከተማ የሚያዝ ሰላይ እና ቅጥረኛ እንጂ የምትያዝ ከተማ አይደለችም።
አሸባሪው ትህነግ ይዤያታለሁ በሚላት ከተማ ነው ያደርኩት፣ ያለሁት። ወልድያን ችሎ የሚይዝ ተላላኪ የለም። ሁሉም እንደ ወልድያ ወጣቶች በፅናት ጠላቱን የሚታገል ከኾነ የአሸባሪው ትህነግ እድሜ ወራት ሳይኾን ቀናት ይኾናል። አሸባሪው ትህነግ በሚያስወራው ወሬ መሸበር፣ መደናገር አያስፈልግም፣ በንቃት አካባቢን መጠበቅ፣ ብቅ ሲል ማነቅ ነው አሸናፊ የሚያደርገው። እነርሱ እንደቆሙ ነው የሚያነጉት፣ እኔ ግን በሰላም ተኝቻለሁ።
በጠዋት ቀሳቀውስቱ ከአብያተክርስቲያናት ልብን በሚሰርቅ ዜማ ያዜማሉ፣ ምህላ ለፈጣሪያቸው ያቀርባሉ። አዛን የሚያደርሱት ሼህ በመስጂድ ለፈጣሪ ምስጋና እያቀረቡ ነው። ከእንቅልፌ ነቅቻለሁ።
የከተማዋ ወጣቶች በሥራ ላይ ናቸው። አይዝሉም፣ የልባቸው ትጋት ደስ ያሰኛል። እኔም በከተማዋ የዕለት ሥራዬን እየከወንኩ ነው። ሌሎችም እንዲሁ። አንተ የጀግና ልጅ ነህ፣ ሀገር ያፀናህ፣ ወገን ያኮራህ፣ የጠላትን አንገት ያስደፋህ፣ ጠላት ያስደነበርክ፣ በታሪክህ ጉድፍ የሌለብህ፣ መሸነፍ የማታውቅ፣ እንደ አንበሳ የምታደቅ፣ እንደነበር የምታንቅ ነህ።
የቀደመውን ክንድህን አሳዬው፣ ጠላትህን አበራዬው፣ ምርቱን ከገለባ ለየው፣ ወደ ፊት ብቻ ውጋ እንጂ አትስጋ፣ አንድ ሆነህ የምታሳርፈውን ክንድህን አይችሉትም። ጦርህን አይመክቱትም። ከጎራ መለስ እንዳይመጡ፣ ከመጡም ለወሬ ነጋሬ እንዳይወጡ አድርገህ ደቁስ እንጂ አትሸበር። የጥቁርን ዘር ከውጭ ወራሪ ባርነት ያወጣህ፣ የነጻነት ፀሐይን ያወጣህ ሕዝብ ነህ። የውስጥ ወራሪ ነጻነትህን ሊጋፋ ሲመጣ ታዲያ እንዴት ይችልሃል? ወልድያ ነኝ። ከተማዋ ሰላም ናት።
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ – ከወልድያ
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 30/2013 ዓ.ም (አሚኮ)
ተጨማሪ ያንብቡ:  ለቸኮለ! ማክሰኞ ጥር 17/2014 ዓ.ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share