ሰው ሁለት ፊት አለው (ዘ-ጌርሣም)

በአርዓያ ሥላሴ የሰው ልጅ ሲፈጠር
የድርሻውን ኖሮ ሰው ሆኖ እንዲያልፍ ነበር
ለዚህም ሲባል ነው ሰውን:-
ባለ ሁለት ዓይኖች
የሚራመዱ እግሮች
ተንቀሳቃሽ እጆች
ለመስማት ጆሮዎች
ሌሎችን በሙሉ አሥራ ሁለት ክፍሎች
አሟልቶ የሰጠው
ከሌሎች ዕንስሳት ልዩ ያደረገው
የማሰቢያ አዕምሮ
አዛኝ ልብ ጨምሮ
አንዷ እንኳን ሳትጎድልው
አሟልቶ ያደለው
ከፍጥረታት መርጦ
ከሁሉም አብልጦ
የተሰጠው ሰው ነው
ታዲያ እንዲህ ተግባሩ ከንቱ ለሚያደርገው
ለዚህም እኮ ሰው ሁለት ፊት አለው
ተብሎ እሚተረተው
እንደ ብሂል ሆኖ ዛሬ ሚነገረው
ምንድን ነው ሁለት ፊት የተባለ እንደሆን ?
እንዲህ ያቀርቡታል የቃላት ትርጉሙን
ሰው ሁለት ፊት አለው
አንደኛው ብርሃን ሌላው ጨለማ ነው
ቀን ቀን በፍርሃት ፊቱን እያበራ
ጨለማን ተላብሶ ተንኮል እየሰራ
ዕድሜውን ይገፋል
የእሱ አልበቃው ብሎት ለትውልዱ ተርፏል
ሁለቱን ፊቶቹን በቅርበት ለሚያየው
የቀኑ ሙልጭልጭ የባህር ዓሣ ነው
ጨለማው ሲተካ እንደ እሾህ ይዋጋል
ያገኘውን ሁሉ ማድማት ይፈልጋል
በአንድ ፊት በአንድ አካል
እንዴት ሁለት አመል
በአብሮነት ይኖራል
በየትኛው መስፈርት ሰው መባል ይቻላል ?
ብርሃን ተስፋ ነው
ብርሃን ሙቀት ነው
ብርሃን ዕውቀት ነው
ብርሃን ዕድገት ነው
ብርሃን ዕይታ
ብርሃን ከፍታ
ብርሃን አብሮነት
ብርሃን ደግነት
ብርሃን ሰውነት
ብዙ መልካምነት
የሰው ልጅ ሙሉነት
እያለ ባለበት
መኖሩ ሌላ ፊት
ያውም ማይታየው
ድግዝግዝ ያለው
በስሙ ጨለማው
ፊት ተብሎ ሚጠራው
ጨለማ እኮ !!
የድንቁርና ከረጢት
የውድቀት ምልክት
የስግብግብነት
የጨካኝነት
የዕውርነት
የባዶነት
የግብዝነት
የዕርዛት
የመጠማት
የመደኽየት
የኋላቀርነት
የበታችነት
የብቸኝነት
የራስን ዓለም መፈለጊያ
የግዑዝነት መለኪያ
ሚዛኑ ያጋደለ
እውነትን ያጎደለ
ውድቀት ነው
በደንብ ከተረዳነው
ጨለማው ፊት
አቅመ ቢስነት
የተነፈገው ብሩሁን ማየት
የማስተዋል ድኩምነት
የሕሊና ውድቀት
ተብሎ ቢፈረጅ
ቢቀርብ ለዕውነት ሆኖ አስረጅ
ትርጉሙ ትክክል ነው
ሰው ሁለት ፊት አለው ያሰኘው
ዕውነት ነው !!
ሰው ሁለት ፊት አለው
አንድኛው ብርሃን ሌላው ጨለማ ነው
ማነነቱን ያስለየው

ተጨማሪ ያንብቡ:  እንበል…( መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ )

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share