One word frees us of all the weight and pain in life, and that word is Love.”
( Socrates )
የሰው ፈጣሪ ና ነፍሱን አስተዳዳሪ እግዚአብሔር ነው ። የሰውን ነፍስ በሲኦል ለማስተዳደር የሚፈልገው ደግሞ ሴጣን ነው ።ይህንን እውነት የገዛ አእምሯችሁ በህሊናችሁ በኩል ዘወትር ይነግረናል ። የፈጣሪንም ሆነ የሤጣንን መኖር የሚያረጋግጥልን ዘወትር ከጥላቻ ና ፍቅር ጋር እየታገለ የሚኖረው የገዛ አእምሯችን ነው ። የገዛ አእምሯችን እስከህሊናቸን እንድንሰነበት ያደርገናል ። አልያም ህሊና የሚባለውን የበጎ ነገር ወዳጅ የአእምሮ ክፍል አሶወግዶ መጥፎ ሃሳብን የሚያራምደው የባዶነት ቀፎ አእምሮ ከእና ዘንድ እሥከ ዕለተ ሞታችን እንዲሰነብት ያደርጋል ።
ብታምኑም ባታምኑም በሰው አእምሮ ያለው እውነት ይህ ብቻ ነው ። የሁለት ተቃራኒዎች ትግልና ውጤቱ ነው በየዕለት ኑሯችሁ በአእምሯችሁ አማካኝነት የሚስተናገደው ። የዛሬ እናንተነታችሁ አእምሮችሁ ውሥጥ በሚደረገው የክፋት ሠራዊትና የበጎ ሰራዊት ወይም የፍቅርና የጥላቻ ፍልሚያ ይወሰናል ። ከላይ እስከታች ፤ ከሊቅ እሥከ ደቂቅ ፤ በዚህ እውነት ውሥጥ ነው የሚያልፈው ። ንጉሥ ይሁን ሌላ ሥም የተሰጠው የአገር መሪ ፤ ተራ ሟች ይሁን ዘላለማዊ ሥም ያለው ፤ ማንም ይሁን ማ በአእምሮ ውሥጥ የሚካሄደውን ጦርነት በመልካም እና በቅን ሃሳብ ድል አድራጊነት እሥካልቋጨ ጊዜ ድረሥ ህሊናውን ቀስ በቀስ በማጣት ባዶ ቀፎ ጭንቅላት ይዞ ዝዋሪ ሆኖ ፣ ህይወቱን በመንቅዥቀዥ ኖሮ በቁጭት ወደ መቃብር እንደሚወርድ ህይወት በየቀኑ ታሳየናለች ። ከዚህ እረፍተ ቢስ የወከባ እና የመከውከው ኑሮ ፣ እከተለዋለሁ የሚለው ኃይማኖት እንኳ እንደማያድነውም ለተራ ሟቹ ታስገነዝባለች ።
ኃይማኖትህ የሚያድንህ ቅን ፣ በጎ እና ፍቅር የሚገዛህ ሥትሆን ብቻ ነው ። ከሞትክ በኋላ እንኳን ነፍስህ እረፍት የምታገኘው ይቅር በይ እና የሚፀፀት አእምሮ ኖሮህ ከሞትክ ብቻ ነው ።
ሰዎች ሆይ ! የፈለጋችሁትን ኃይማኖት ተከተሉ ። የምትከተሉት ኃይማኖት የፈጣሪን መኖር የሚያሥገነዝባችሁ በገዛ አእምሯችሁ በኩል ነው ።የገዛ አእምሯችሁ ውሥጥ የፍቅር ና የጥላቻ ትግል በየሰኮንዱ መካሄዱን አሥተውሉ ። አንድ በጎ ሃሳብ በተቃራኒው ሃሳብ ይሞገታል ። በሙግቱም ወይ ተቃራኒው ወይ ደግሞ በጎው አሳብ ያሸንፋል ። ወይ ፍቅር ወይ ጥላቻ አእምሯችሁን ይቆጣጠራል ።
ፍቅር ና ጥላቻ ሁሌም በአእምሯችን ውስጥ ያለፋታ ይሟገታሉ ። አውዳሚ ወይም ክፉ አሳብ እና ገንቢ የሆነ ቅን ሃሳብ ሁሌም በአእምሯችን ውሥጥ መፋለማቸውን እናውቃለን ። በማያቋርጠው የተቃራኒ ሃሳቦች ትግል ፣ ድል አድራጊው መልካሙ የፍቅር ሃሳብ የሚያሸንፍ ከሆነ ፤ በየቀኑ መልካም ሰው ሆነን እናድጋለን ። ክፉው እና ጠማማው የጥላቻ ሃሳብ እያየለ ና ፍቅር እየተዳከመ ከመጣ ደግሞ ፣ በየቀኑ እየሤጠንን ማደጋችን አይቀርምና ለእኛ የክፋታችን ጥግ ባይታወቀንም እንኳን ፣ ለቅን ሰዎች ጠማማነታችን ከጅምሩ የተሰወረ አይሆንም ። ለእኛ የማይታወቀን መጥፎው ሃሳብ ወይም ጥላቻ ቅን እና በጎ ሃሳቢውን ህሊና አሶጥቶ አእምሯችን በዶ ቀፎ እንዳደረገው ልባቸው በፍቅር የተሞላ ሰዎች ከእኛ ይበልጥ ይገነዘባሉ ፡፡
እናም ማስተዋል ካለን ፣ ሰው ሁሉ ሲወለድ ሁለት ምርጫ በአእምሮው ይዞ እነደሚወለድ ከገዛ አእምሯችን የዘወትር ንትርክ እንገነዘባለን ።ሁሌም ህይወት ሁለት ተቃራኒ ምርጫ ነው ያለት ፡፡ በበጎና በቅን ፣ በፍቅር መንገድ ሁሌም በመጎዝ ህይወቱን አጣፍጦ ፣ ህሊናን አርክቶ እሥከ ዕለተ ምት መኖር አንዱ ምረጫ ሲሆን ሁለተኛው ምርጫ ፤ በተቃራኒ መንገድ በመጎዝ ፣ በቅጥፈት ፣ በማጭበርበር ፣ በብልጣብልጥነት ፣ በተንኮል ፣ በማታለል ፤ በጭካኔ ፣ በግፍ ፣ በአጠቃላይ በጥላቻ አእምሮውን ሞልቶ ፣ህሊና ቢስ ሆኖ ለሥጋ ብቻ ተገዝቶ ፣ ዘወትር አየተደናበሩ በመኖር ፣ በቁጭት መሞት ።
ይኸው ነው ። የሴጣን ደቀመዝሙር ከሆንን የሤጣንን ፣ ፈቃድ ፈፃሚ ፤ ህሊናውን የተነጠቀ ሰው መሆናችን እርግጥ ይሆናል ። እናም ለአእምሮአችን የበላይ አካሉ ሴጣን ሆኖ እናገኘዋለን ። ትዕዛዝ ሰጪው አዛዥና ናዛዡ እርሱ ሆኖ ያርፈዋል ።
ህሊናችን የሴጣንን ፈቃድ ፈፃሚ “ በለሌላ ማዕረግተኛ “ ከሆነ ፤ የበላዩ ሤጣን ሥጋን በጣም በሚወደው ነገር ገዝቶታል ማለት ነው ። የተገዛ ህሊና ቢስ ሥጋ ደግሞ የገዢውን ፈቃድ ፈፃሚ ነው ፤ የሚሆነው ። የሴጣን ፈቃድ ደግሞ የታወቀ ነው ። ጥላቻ ፣ክፋት ፣ ተንኮል ፣ ሴራ ና ሸር ፣ ጠልፎ መጣልና ወጥመድ ፣ እንግልት ና መከራ ፣በመጨረሻም ፣ መፈጠርን የማያሥጠላ ሥቃይ ና ሞት ነው ።
ሞት እንጂ ህይወት የሴጣን ፈቃድ አይደለም ። ጥላቻ እንጂ ፍቅር የሴጣን ፈቃድ አይደለም ። የሴጣን ፈቃድ ተጀምሮ እሥኪጨረሥ በሰው መካከል ጠብን መዝራት እና ሞትን ማዋለድ ነው ።
ሰው ቆም ብሎ በማሰብ በአእምሮው ውሥጥ እየተመላለሰ ፣ የፍቅርን አሳቢ አእምሮ ያለመታከት የሚዋጋውን የሤጣን መንፈሥ ከአእምሮው ካላሶጣ በሥተቀር በዚች ምድር ላይ ሰላም ከቶም አይኖርም ።
የዓለም ሰላም ማጣት መንስኤ በሰው አእምሮ የነገሰው የጥላቻ መንፈስ ነው ። የጥላቻ መንፈስ ሁል ጊዜም ከፍቅር ፣ ከመተሳሰብ ፣ ከመዋደድ መንፈስ ጋር አይዋደድም ። እነዚህ የእሱን ጥቅም የሚያሳጡ አድርጎ ሥለሚመለከታቸው በዓለም እንዲኖሩ አይፈልግም ።
ዓለም ዛሬ እየተናወጠች ያለችው አእምሮአቸው በጥላቻ በተሞላ ሰዎች ነው ። የእነዚህ ሰዎች አእምሮ ፍቅርን ገደል በመክተት ጥላቻን አንግሦልና ፣አንዳችም ቀና እና በጎ ነገር አያሥብም ። ከላይ እንደጠቀስኩት ከልጅነቱ ጀምሮ ፍቅርን በማሶጣት ጥላቻ ብቻ በህሊናው እንዲቀመጥ በማድረጉ የሤጣን ደቀመዝሙር ሆኖል ።
የሤጣን ደቀመዝሙር የሆነ ሰው ደግሞ ፣ ከፋትን ፣ መጥፎ ነገሮችን በሙሉ እንደ በጎ በመቁጠር ጥላቻውን ሙጥኝ ብሎ እንደሚኖር የዛሬ 2013 ዓ/ም ታይቷል ።
የዛሬ 2013 ዓ/ም እየሱስ ሲሰቀል ከጥቂት በፍቅር ልባቸው ከተሞላ ወንዶችና ሴቶች በሥተቀር ብዙሃኑ ምንም ሐጢያት የሌለበትን ” ኢየሱስን ሰቀሉትና በርባን የተባለውን ነፍሰ ገዳይ ፍቱልን ፡፡ ” በማለት ጲላጦስን በጩኸታቸው ብዛት አሥገድደውት እንደነበር አሥታውሱ ።
ማርቆስ 15
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
- በዚያም በዓል የለመኑትን አንድ እስረኛ ይፈታላቸው ነበር።
- በዓመፅም ነፍስ ከገደሉት ከዓመፀኞች ጋር የታሰረ በርባን የተባለ ነበረ።
- ሕዝቡም ወጥተው እንደ ልማዱ ያደርግላቸው ዘንድ እየጮኹ ይለምኑት ጀመር።
9 ጲላጦስም፦ የአይሁድን ንጉሥ እፈታላችሁ ዘንድ ትወዳላችሁን? ብሎ መለሰላቸው፤
10 .የካህናት አለቆች በቅንዓት አሳልፈው እንደ ሰጡት ያውቅ ነበርና።
- የካህናት አለቆች ግን በርባንን በእርሱ ፈንታ ይፈታላቸው ዘንድ ሕዝቡን አወኩአቸው።
12 .ጲላጦስም ዳግመኛ መልሶ፦ እንግዲህ የአይሁድ ንጉሥ የምትሉትን ምን ላደርገው ትወዳላችሁ? አላቸው።
- እነርሱም ዳግመኛ፦ ስቀለው እያሉ ጮኹ።
- ጲላጦስም፦ ምን ነው? ያደረገው ክፋት ምንድር ነው? አላቸው። እነርሱ ግን፦ ስቀለው እያሉ ጩኸት አበዙ።
ያ ፣ የዛን ጊዜው በግፈኞች የሚመራ “ የመንጋ ፍርድ “ እኛ እንድንማርበት ከ2013 ዓ/ም በፊት ፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ በራሱ መከራ ሥቃይ ፣ ምት እና ትንሣኤ ያሳየን ነው።
ዛሬ ደግሞ ፣ ስለ እኛ ሥለ ፍጡራኑ ፣ ዘላለማዊ ህይወት ሲል ዓምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መከራ ና ሥቃይ አይቶ መሠቀሉን የምናሥብበት ቀን ነው ። በዚህ ቀንም የፍቅርን ኃያልነት እንመሰክር ዘንድ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ያስገድደናል ።
ክርስቲያን ወድሞቼ ና እህቶቼ ሆይ እሥቲ ዛሬ ቆም ብለን በአእምሯችን ውሥጥ የነገሰው ማን እንደሆነ እንመርምር ? በአእምሮችን የነገሰው ፍቅር ነው ወይሥ ጥላቻ ? ይህንን በእርግጠኝነት መመለሥ የነገ ህይወታችንን ያቃናልናል ።
እውን ክርስቲያን ነን እያልን በዘር ና በቋንቋ በመቦደን ወንድምና እህታችንን እናገላለንን ? እንዲህ የምናደርግ ከሆነ እኛ በሴጣን ቁጥጥር ሥር መሆናችንን አውቀን ከወጥመዱ በዚህ በትንሣኤ ቀን በመላቀቅ ንሥሐ እንግባ ።
እወቁ ዘረኛ በጥላቻ የገዘፈ የዘር ቀንበሩን ካላወለቀ አይፀድቅም ። በምድርም ላይ እየተቅበዘበዘ ይኖራል እንጂ ፣ የህሊና ሠላም ከቶም አይኖረውም ። ይልቁንስ ሳይረፍድበት ጥላቻን ከልቡ በማሶጣት ፍቅርን ቢያነግስ ነፍሱ በሐሴት ትሞላለች ፡፡
1ኛ ቆሮንቶስ 13
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሽዋሽዋ ጸናጽል ሆኜአለሁ።
² ትንቢትም ቢኖረኝ ምሥጢርንም ሁሉና እውቀትን ሁሉ ባውቅ፥ ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ።
³ ድሆችንም ልመግብ ያለኝን ሁሉ ባካፍል፥ ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል አሳልፌ ብሰጥ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም።
⁴ ፍቅር ይታገሣል፥ ቸርነትንም ያደርጋል፤ ፍቅር አይቀናም፤ ፍቅር አይመካም፥ አይታበይም፤
⁵ የማይገባውን አያደርግም፥ የራሱንም አይፈልግም፥ አይበሳጭም፥ በደልን አይቆጥርም፤
⁶ ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል እንጂ ስለ ዓመፃ ደስ አይለውም፤
⁷ ሁሉን ይታገሣል፥ ሁሉን ያምናል፥ ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፥ በሁሉ ይጸናል።
⁸ ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም፤ ትንቢት ቢሆን ግን ይሻራል፤ ልሳኖች ቢሆኑ ይቀራሉ፤ እውቀትም ቢሆን ይሻራል።