March 22, 2013
25 mins read

የማልስማማባቸው የዳንኤል ክብረት ሃይማኖታዊ ትንታኔዎች

ከአዲስ

 

 

ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነኝ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት የወቅቱ የቤተክርስቲያን ጉዳይን በሚመለከት ከላይፍ መጽሄት የመጋቢት ወር እትም ቁጥር 102 ጋር ያደረገው ቃለ ምልልስ ነው:: ቃለ ምልልሱን በመጀመርያ ያነበብኩት አንድ አድርገን የተባለ ብሎግ ካወጣው በኋላ ነበር:: ጋዜጠኛው ያነሳቸው ጥያቄዎች በቤተ መንግስትና ቤተ ክህነት ላይ ያተኮሩ ነበሩ:: የቀድሞው ፓትርያርክ የአቶ ታምራት ላይኔ እና ያዲሱ ፓትርያርክ አቡነ ማቲያስንም ጉዳይ ተነስቷል:: የዲያቆን ዳንኤልን መልስ ግን ለኔ አስገራሚ ነበር:: የሰጣቸው በርካታ ምላሾች ሊዋጡልኝ አልቻሉም:: ባንዳንዶቹ አስተያየቶቹ ደግሞ ፈጽሞ አልስማማም:: ጥቂቶቹን ላንሳ በሶስቱ ፓትርያርኮች ዙርያ::

 

ፓትርያርክ ጳውሎስ

የላይፍ ጋዜጠኛ ÷ ከአቡነ ጳውሎስ ንብረት ጋር በተያያዘ ላቀረበለት ጥያቄ ዲያቆን ዳንኤል የሰጠው መልስ እንዲህ የሚል ነበር::

ንብረት በመያዝና በማስቀመጥ ረገድ እሰከ አሁን ብዙ ያልተሰማባቸው አባት አቡነ ጳውሎስ ናቸው፡፡

ምናልባት ዘመዶቻቸው ረድተው ይሆናል ካልተባለ በቀር ብዙ ንብረት የላቸውም፡፡[i]

 

እውነት ግን አቡነ ጳውሎስ ንብረት በመያዝና በማስቀመጥ ብዙ አልተሰማባቸውምን? ፓትርያርኩ አሁን ወደ እውነተኛው ቦታ ሄደዋል:: ለበጎም ለክፉም ስራቸው ዋጋቸውን ከፈጣሪ ያገኛሉ:: ነፍሳቸውን ይማራቸው:: ግን በዚህ ምድር ትተው ያለፉት ታሪክ ነውና እሳቸው ቢያልፉም ታሪካቸው ይወሳል:: እንደኔ ምልከታ ከሆነ ከኢትዮጵያ ፓትርያርኮች እንደ አቡነ ጳውሎስ በዚህ ጉዳይ የተወቀሰና ስሙ የተነሳ የለም:: የቤተ ክህነቱ ሰራተኞችም÷ የግል ፕሬሶችም ይሄንን ጉዳይ ደጋግመው አንስተውታል:: እጅግ ከበዙት የፕሬስ ምስክርነቶች ጥቂቶቹን ልጥቀስ:: መብሩክ የተባለው ጋዜጣ በመስከረም 22/ 1990 አመት እትሙ ” ፓትርያርክ ጳውሎስ በምስጢር ከቤተ ክህነት ወጥቶ በኒውዮርክ ባንክ ሶስት መቶሺህ ዶላር እንዲቀመጥ ያዘዙበትን ሰነድ ተገኘ ” በማለት ያስነበበ ሲሆን ሰነዱንም ጋዜጣው ላይ አብሮ አትሞታል:: ይሄው ጋዜጣ በወቅቱ ያስነበበው ዜናውን ብቻ ሳይሆን መረጃውንም ጭምር በመሆኑ የበርካታ ዜጎች መወያያ ሆኖ ነበር:: ሐዋርያ የተባለው ሌላው የግል ጋዜጣ ( በቅጽ ሶስት ቁጥር 4 ህዳር 9/1990እትሙ ) ባቡነ ጳውሎስ ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ እንደተነሳና ፓትርያርኩም በምስጢር ገንዘብ ሲያስቀምጡ በምስጢር እንደተደረሰባቸው በመረጃ የተደገፈ ሀተታ አቅርቦ ነበር:: ዘጋቢ የተባለውም የግል ፕሬስ በአንደኛ አመት እትሙ ቁጥር 33/ጥቅምት 1/1990 ባወጣው ዜና ፓትርያርኩ ልዩ ቪላ እንዳሰሩና ቪላቸውንም በሺዎች በሚቆጠር ብር በወር ኪራይ ማኮናተራቸውን ዘግቧል:: የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት የሆኑት ጳጳሳትም በተለያየ የግል ጋዜጦች ላይ አቡነ ጳውሎስን በዚህ ጉዳይ እየወቀሱ መግለጫ ሰጥተዋል:: በተለይም አቡነ ገብርኤል መብሩክ የተባለ የግል ጋዜጣ ላይ (መብሩክ ሁለተኛ አመት ቁጥር 52/104 ሀሙስ መስከርም22ቀን /1990 ) የጻፉ ግልጽ ደብዳቤ ላይ እንዳስቀመጡት ፖትርያርኩ ምን ያህል ንብረትን በማጋበስና አላግባብ ለቅንጦት በመርጨት የተወቀሱ እንደሆነ ተንትነው አስረድተዋል:: በቅርቡም ደጀ ሰላም የተባለው ብሎግ የአቡነ ጳውሎስን እረፍት ተከትሎ ባስነበበው ዘገባ

ፓትርያርክ ጳውሎስ በተለያዩ ዘመዶቻቸው ስም ባስቀመጡት በአንድ የመንግሥታዊው ባንክ ቅርንጫፍ ሦስት አካውንቶች ውስጥ 22 ሚልዮን ብር በላይ እንደሚገኝ በይፋ ጠቁሟል::[ii]   ኢትዮጵያንሪቪው የተባለው ድረ ገጽም ከቤተ ክህነቱ ስልሳ ሚልዮን ብር እንደተዘረፈና ይሄም በፕትርያርኩ ዙርያ እንደሆነ ÷ መረጃውንም ያገኘው ከቅዱስ ሲኖዶስ አባል መሆኑንን በይፋ በመግለጽ ለህዝብ አስነብቧል [iii] ::ፓትርያርኩም በቤተ ክህነት ሃላፊዎችና ሰራተኞች ዘንድም የሚታወሱበት አንዱ ሌጋሲ ይሄው እንደሆነ ደጀ ሰላም የተባለው ብሎግ የቤተ ክሀነት ምንጮችን በመጥቀስ እንዲህ ሲል ነበር ያስነበበው “የሰውዬው [አባ ጳውሎስ] መታወሻቸው (legacy) አውዳሚነታቸው ነው፤ እርሳቸውም እኛም እየበላን ያለነው ቀደምት ፓትርያርኮች ያስቀመጡትን ሀብት ነው:” በማላት በቤተ ክህነቱ ሰዎች ዘነድ ክፉኛ እንደሚወቀሱ አስታውሷል::[iv]

 

የሚገርመው ጉዳይ ዲያቆን ዳንኤልም ፓትርያርኩ የሞቱ ሰሞን ባወጣው ጽሁፍ ላይ እንደማሳሰቢያ ያስቀመጠው ነገር አንዱ የፓትርያርኩን ሀብት በተመለከት ነበር:: “ማንኛውም የፓትርያርኩ ንብረቶች ወደ ሌሎች ከመጓዛቸው በፊት በጥብቅ ይቀመጡ፡፡ የባንክ ሂሳቦች ይዘጉ፡፡…ሀብት እና ቅርስን የማሸሽ አዝማሚያ እንዳይከሰት” [v]

ፓትርያርኩ የግል ሀብት ከሌላቸው ይሄንን ማለቱ ለምን አስፈለገ ይሆን?

 

“ፓትርያርክ ጳውሎስ ንብረት በማስቀመጥና በመያዝ ብዙ አልተሰማባቸውም” የሚለው የዲያቆኑ አስተያየት ብዙም የሚያሳምን አይሆንም:: እንዲያውም “ፓትያርኩ ሀብት የላቸውም አላካበቱም” የሚለው አስተያየት የፓትርያርኩን ሀብት የግላቸው ለማድረግ ለሚፈልጉ አካላት ካሉ ለነሱ ከለላ መስጠት እንዳይሆን እፈራለሁ::ይልቁኑስ ፓትርያርኩ የግል ንበረት አላካባቱም የሚለውን የማያሳምን ሙግት ትተን ÷ የፓትርያርኩ ሀብት የቤተ ክርስትያን ሀብት÷ ከቤተ ክርስትያን የተወሰደ ነውና ያ ሀብት ወደ ቤተ ክርስትያኒቱ ካዝና የሚገባበትን መፍትሄ መጠቆም የሚሻል ይሆናል::

 

ፓትርያርክ ማቲያስ

 

የላይፍ ጋዜጠኛ ለዲያቆን ዳንኤል ክብረት ያቀረበለት ጥያቄ ዜግነትን በተመለከተ ነበር::ጥያቄና መልሱ ይሄን ይመስላል::

ላይፍ፡- አቡኑ መለስኩ ማለታቸው በራሱ ኢትዮጵያዊነትን በመተው የአሜሪካ ዜግነት ለማግኝታቸው ማረጋገጫ ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት አቡኑ ላይ ትችት ለሚሰነዝሩ ወገኖች ነገሩ በር አይከፍትም?

/ ዳንኤል፡ ሰማያዊና ምድራዊ ዜግነት ይለያያል፡፡ ለቤተክርስቲያን መሪነት የሚያስፈልገው መንፈሳዊነት ነው፡፡ በግሌ ዜግነቱ ምንም ቢሆን ልዩነት አይፈጥርም፡፡ በጣም ብዙ አባቶች በፖለቲካም ይሆን በኢኮኖሚ ጫና ወደ አሜሪካ ሄደዋል ፤ እነዚህ አባቶች በዚያ የተሻለ ነገር ለማግኝት ሲሉ በሁኔታዎች አስገዳችነት ዜግነታቸውን ይቀይራሉ፡፡ እንዲህ መሆኑ በቤተክርስቲያኒቱ እስከ አሁን ድረስ  እንደ ችግር አልታየም፡፡[vi]

 

እንደኔ ይሄም የዲያቆኑ መልስ ችግር ያለበት ነው:: አደገኛ አስተያየትም ነው:: አሜሪካን ለውጭ ዜጎች በሯ ክፍት ነው:: በፖለቲካም ሆነ በኢኮኖሚ የተሰደዱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በየአመቱ አሜሪካን ይገባሉ:: የፖለቲካና የሃይማኖት ጭቆና ደረሰብን ብለው ያመለክቱ ስደተኞች ጉዳያቸውን asylum case officer ዘንድ በማቅረብ ጥገኝነት ያገኛሉ:: ህጋዊ ሆነው እሰከተገኙ ድረስ የስራ ፈቃድም ( work permit) ሆነ የቋሚ መኖርያ ፍቃድ( green card) አይከለከሉም::በዲቪም አሜሪካ የመጣው በትዳርም አሜሪካ የገባው ጥገኝነትም የጠየቀው ወዘተ ህጋዊና ሰላማዊ እስከሆኑ ድረስ ግዜያቸውን ጠብቀው ግሪን ካርድ ያገኛሉ:: አንዴ ግሪን ካርድ ካገኙ መማር ÷ መስራት÷ቤት መግዛት÷ መበደር ወዘተ ለህይወት የሚያስፈልጉትን ማንኛውንም ነገሮች ማድረግ ይቻላል:: የግድ ዜጋ መሆን አያስፈልግም::

 

ዜግነት ለፈለገ ሰውም አሜሪካ በሯ ክፍት ነው:: አሜሪካ ዲሞክራሲ ያለበት ሀገር በመሆኑ ዜጋ ሁኑ ብሎ የሚያስገድድ የለም:: የፈለገና ብቁ ሆኖ የተገኘ ሰው ግን ዜጋ መሆን መብቱ ነው:: ለዛ ግን ቅድመ ሁኔታ አለው:: ያም የትውልድ ሀገርን መካድ ነው:: ይሄንን በመሃላ ማረጋገጥ ያስፈልጋል:: ዜግነትን የፈለገ ሰው እንዲህ ብሎ መማል ይጠቅበታል

I hereby declare, on oath, that I absolutely and entirely renounce and abjure all allegiance and fidelity to any foreign prince, potentate, state, or sovereignty, of whom or which I have heretofore been a subject or citizen; that I will support and defend the Constitution and laws of the United States of America against all enemies, foreign and domestic; that I will bear true faith and allegiance to the same; that I will bear arms on behalf of the United States when required by the law; that I will perform noncombatant service in the Armed Forces of the United States when required by the law; that I will perform work of national importance under civilian direction when required by the law; and that I take this obligation freely, without any mental reservation or purpose of evasion; so help me God.[vii]

ይሄ መሃላ ከባድ ነው:: ግርድፍ ትርጉሙ መፍጹምና ሙሉ በሙሉ የልውልድ ሀገሬና መንግስቴ ያለኝን ታማንነት እምነት ቃል ኪዳንና ዜግነት በመሃላ አፍርሻለሁ::ክጃለሁ::

በግሪን ካርድ እኮ ዜግነታችንን ሳንክድ የፈለግነውን መሆን አንችላለን:: መማርም ሆነ መኖር የሚከለክለን የለም:: ዜግነት የሚሰጠን አንዱ ጥቅም የሶሻል ሴኩሪቲ ( ጡረታ ) ሙሉ ዋስትና ነው:: ከዛ ውጭ ያለው ከመምረጥና መመረጥ እና የመሳሰሉ ጋር የተያያዘ ነው:: እና ለዚህ ሲባል የሚደረግን ሀገርን የመካድ ተግባር እንዴት ችግር የለውም ይባላል:: ሀገር መካድ እኮ ወንዝና ተራራውን ብቻ አይደለም:: ሀገር እኮ ሕዝብ ነው:: ሀገር መካድ ማለት በጡረታ ለሚገኝ ጥቅም ሲባል ሕዝብን መካድ እኮ ነው:: ሹመት ሳይኖር ሀገር መካድ ሹመት ሲገኝ ደግሞ “የለም የካድኩትን ትቼዋለሁ አሁን ኢትዮጵያዊ ነኝ “ ማለት በውኑ ችግር የለውምን? የሞራልና የሃይማኖት መሪዎችችን ከሆኑ የሃይማኖት አባቶችስ ይሄ ይጠበቃልን? በቤተ ክርስትያንስ ይሄ አንደ ችግር የሚታይ አይደለምን? ለሌላውስ ምእመን ምን እያስተማርነው ነው? እኔ እስከማውቀው ደረስ የቤተ ክርስትያን ትምህርት ይሄን አይደግፍም:: በባእድ ሀገርና አስጨናቂ ሁኔታ ውስጥም እንኳን ቢሆን ” ኢየሩሳሌም ሆይ ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ” የሚለውን ትምህርት ነበር እንጂ እንደ ኤሳው ለምስር ወጥ ብኩርናን መሸጥ አልነበረም:: እርግጥ ነው የኢትዮጵያ ፓትርያርኮች ከግብጽ የሚመጡ ግብጻውያን ነበሩ:: የሌሎችም ሀገር ዜጎች ኢትዮጵያ መጥተው በቤተ ክርስትያኗ የሃላፊነት ቦታ ላይ ተቀምጠዋል:: ግን ግብጻውያኑም ሆኑ ሌሎቹ አገራቸውን ክደው አይደለም የመጡት:: ግብጻዊ ግን የኢትዮጵያ ፓትርያርክ::ዜግነታቸውን ይዘው ኢትዮጵያን ለማገልገል ነው::

ዲያቆኑ እዚሁ መጽሄት ላይ ነገር ግን ሁል ጊዜ የተሰደደ ሰው ብቻ እንደ ጀግና ለምን እንደሚቆጠር አይገባኝም፡፡ ብሎ ስደትና ስዱዳንን ከኮነነ በኋላ ቀጥሎ ለቀረበለት ጥያቄ ደግሞ እንዲህ በማለት መልሷል በጣም ብዙ አባቶች በፖለቲካም ይሆን በኢኮኖሚ ጫና ወደ አሜሪካ ሄደዋል እነዚህ አባቶች በዚያ የተሻለ ነገር ለማግኝት ሲሉ በሁኔታዎች አስገዳችነት ዜግነታቸውን ይቀይራሉ፡፡ እንዲህ መሆኑ በቤተክርስቲያኒቱ እስከ አሁን ድረስ እንደ ችግር አልታየም፡፡ የተምታታ ነገር ነው::

 

ፓትርያርክ መርቆርዮስ

 

ዲያቆን ዳንኤል በዚሁ መጽሄት ቃለ መጠይቅ ላይም ያቀረበው ትችት እንዲህ ይላል

“አቡነ መርቆሪዎስ ከአሁን በኋላ አልሰራም በማለት ለሲኖዶስ ደብዳቤ አስገብተው ነበር፡፡ ስለዚህ ቦታውን ለመልቀቃቸው ማረጋገጫ ነው፡፡ በፓትርያትክ ላይ ፓትርያርክ ተሾመ በማለት አቡነ ጳውሎስን መውቀስ ከብዙ ነገር አንጻር ተገቢ አይደለም፡፡”

ከላይ የተጠቀሰውን አስተያየት የሰጠው በያዝነው አመት መጋቢት ወር ሢሆን ከሁለት አመት በፊት (ሜይ 12/2011) ብሎጉ ላይ ያወጣው ጽሁፍ እንዲህ የሚል ነበር


በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ የጠራ መረጃ ከማይገኝባቸው ወቅቶች አንዱ ከ1983 እስከ1984 ዓም በቤተ ክህነቱ የተከናወነው ታሪክ ነው፡ ይህንን ወቅት በሚገባ የሚያሳዩ እና በመረጃየተጻፉ በቂ የጥናት ውጤቶች አላገኘንም፡ በሂደት ግን ይኖራሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡ እስኪያንን ወቅት ከሚያስታውሱን የታሪክ መረጃዎች አንዱን ደበዳቤ እንየው፡ በወቅቱ የሲኖዶሱ ጊዜያዊሰብሳቢ የነበሩት ሟቹ ብጹዕ አቡነ ዜና ማርቆስ ለብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ የጻፉት ደብዳቤነው፡፡

 

ካለ በኋላ ደብዳቤውን ያስነብባል::

“በደብዳቤ ቁጥር 69/298/84 መስከረም 24/1984) የተጻፈው ደብዳቤ ሁለቱ አንቀጽ እንዲህ ይላል

“ቅዱስነትዎ መንበረ ፓትርያርኩን ያልለቀቁ በመሆኑ ቀደም ሲል ከያቅጣጫው የነበረው ግፊት አሁንም እንደቀጠለ ነው::ስለዚህ ለቅዱስነትዎም ሆነ ለቤተ ክርስትያን ሰላም ሊገኝ የሚችለው የቅዱስነትዎ መኖርያ ቦታ ሲለወጥና መንበረ ፓትርያርኩን ሲለቁ ስለሆነ ቅዱስነትዎ ስለዚህ ጉዳይ ያስቡበትና የመረጡት ቦታ ካለ ባስቸኳይ እንዲገለጽና ቅዱስ ሲኖዶስም በውሳነዎ መሰረት ለመፈጸም የሚተባበር መሆኑን እናሳስባለን”[viii]

 

እንግዲህ ከዚህ ደብዳቤ መረዳት የምንችለው ነገር አለ:: ያም በደብዳቤው ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው ፓትርያርክ መርቆርዮስ እንዲወርዱ ከፍተኛ ግፊት ነበር:: እሳቸው ካልወረዱና መንበረ ፓትርያርኩን ካልለቀቁ ለቤተ ክርስትያንም ሆነ ለራሳቸው ሰላም እንደማይኖር በግልጽ ለፓትርያርክ መርቆርዮስ በይፋ ደብዳቤ ተነግሯቸዋል:: ( ደብዳቤውን ይመልከቱ):: ስለዚህ ፓትርያርኩ ለሲኖዶሱ አስገቡ የተባለው ደብዳቤም የነዚህ ግፊቶች ውጤት ሊሆን እንደሚችል ያመላክታል:: ፓትርያርኩ ለሲኖዶስ ደብዳቤ ማስገባታቸው ብቻ ቦታውን ለመልቀቃቸው ማረጋገጫ ሊሆን አይችልም:: ታላቁ የቤተ ክርስትያን ሊቅ አለቃ አያሌው ታምሩ ይሄን ጉዳይ ሲያብራሩ እንዲህ ብለው ነበር

“ቤተ ክርስትያኒቱ ያለ ፓትርያርክ መቅረት የለባትም ነገር ግን በጉባኤ መወሰን ነው ያለበት:: ዝም ብሎ አይደለም ሊደረግ የሚገባው:: ከፍተኛ ቤተ ክርስትያናዊ ጉባኤ ተሰብስቦ ጉዳዩን ማጥናት አለበት:: ሕመማቸውስ እርግጠኛ ነው? ስራስ ይከለክላቸዋልን?እነዚህ ነገሮች መጠናት አለባቸው::አቡነ መርቆርዮስ ከቤተ ክርስትያን ሲወጡ ስለ ሕመማቸው እውነተኛ መረጃ ለቤተ ክርስትያኒቱ አልቀረበም:: በሽታቸው ተገምግሞ ለስራ ያስችላቸዋል አያስችላቸውም የሚለው የሚል ጉባኤ አልተከናወነም::ይህ እስካልሆነ ድረስ ተሽረዋል ማለት አይቻልም::ስለሆነም ደግሞ ቤተ ክርስትያን ይመራሉ ማለት አይደለምና ሕጋዊ ጥናት አልተደረገም::ሕጋዊ ዝውውር አልተደረገም::ይህ ከሆነ የሳቸውም መውረድ የተከታዩም መሾም ተቀባይነት የለውም ” ብለው ነበር::

ስለዚህ የፕትርያርክ መርቆርዮስን ከስልጣን የመውረድ “እንዲህ ነው ብሎ ” ለማለት ብዙ ብዙ መጥራት ያለባቸው ነገሮች አሉ:: ስለዚህ “አቡነ መርቆሪዎስ ከአሁን በኋላ አልሰራም በማለት ለሲኖዶስ ደብዳቤ አስገብተው ነበር፡፡ ስለዚህ ቦታውን ለመልቀቃቸው ማረጋገጫ ነው” የሚለው የዲያቆን ዳንኤል ድምዳሜንም ለመቀበል ያዳግታል::

አንደማጠቃለያ

ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ከፍተኛ አክብሮቱ አለኝ:: እኔ ብቻ ሳልሆን የኔ ትውልድ (generation) በምግባርና በሃይማኖት ተኮትኩቶ እንዲያድግ አስተዋጾ ካደረጉ ሰዎች ውስጥ አንዱ ነው::  የግለስበ ብቻ ሳይሆን የትውልድ ባለውለታ ነው:: የማህበረ ቅዱሳን ምስረታ : የሐመርና ስምኣ ጽድቅ እትሞችና ሌሎች መሰል ጉዳዮች ላይ የዲያቆን ዳንኤል ጉልህ አሻራ አለባቸው:: ቤተ ክርስትያንን ለመበተን ተነስተው የነበሩ የተሐድሶ መናፍቃንን በመዋጋትም የዲያቆን ዳንኤል ሚና ወሳኝ ነበር:: በዚህ ዘመን : በቤተ ክርስትያን ዙርያስ እንደሱ መጻሕፍትን የጻፈ ይኖር ይሆንን? ሌሎችም ሌሎችም:: በዚህና መሰል ምክንያቶች ያይናችን ማረፊያ ነበር::

ከቅርብ ግዜ ወዲህ ግን ዲያቆን ዳንኤል የሚሰጣቸው አስተያየቶችና ትችቶች እያስደነገጡኝና እያስገረሙኝ መጥተዋል:: በማህበረ ቅዱሳን ላይ አውጥቶት ይቅርታ የጠየቀበት ጽሁፍ÷ ሁለቱ ሲኖዶሶችን ለማስታረቅ ይተጋ የነበረው አስታራቂ ኮሚቴ ላይ ያቀረበውን ትችት እንደ አብነት ማንሳት እችላለሁ:: ሌሎችም ሌሎችም:: እነሆ ይሄም ቃለ መጠይቅ ላይ የሰጣቸው መልሶችን መዋጥ አቃተኝ:: ዝምታዬ ፈነዳና እነሆ የመሰለኝን ከብዙ በጥቂቱ ጽፌአለሁ::

 



[i] http://andadirgen.blogspot.com/2013/03/blog-post_10.html#more

[ii] http://www.dejeselam.org/2012/08/blog-post_151.html)::

[iii] http://www.ethiopianreview.com/forum/viewtopic.php?f=2&t=14462)

[iv] http://www.dejeselam.org/2012/08/blog-post_151.html)

[v] http://www.danielkibret.com/2012/08/blog-post_7924.html?spref=tw)

[vi] http://andadirgen.blogspot.com/2013/03/blog-post_10.html#more

[vii] http://www.uscis.gov/ilink/docView/SLB/HTML/SLB/0-0-0-1/0-0-0-29/0-0-0-10309.html#0-0-0-449

[viii] http://www.danielkibret.com/2011/05/blog-post_12.html

Latest from Blog

መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። ) “ገብርዬ ነበረ

ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ?

January 3, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ዛሬ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ጥር 1ቀን 2025 ዓ/ም ነው ። አውሮፓውያኑ አዲስ ዓመትን “ሀ” ብለው ጀምረዋል ። አዲሱን ዓመት ሲጀምሩም ከልክ ባለፈ ፈንጠዚያ ነው ። ርቺቱ ፣ ምጉቡና መጠጡ

ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። )

ትላንት አንድ ወዳጀ ደውሎ “አሳየ ደርቤን” ታውቀዋለህ ወይ” አለኝ፡፡ እኔም አላውቀውም አልኩት፡፡ ኢንጅኔር “ኡሉፍ” የተባለ ሰው የዛሬ ሰባት ዓመት ያሰራረውን ጥልቀትና ስፋት ያለውን ዘገብ አቅርቦታልና አዳምጠው አለኝ፡፡ እኔም “ጉድሺን ስሚ ኢትዮጵያ–ከባድ አደጋ

ተቆርቋሪ የሌላት ኢትዮጵያ – አክሎግ ቢራራ (ዶር)

ወገኖቸ፤ ለጊዜው ትችቱን እናቁምና ለወገኖቻችን እንድረስላቸው፡፡፡ በቤተ አማራ ወሎ ቡግና የተከሰተው ርሃብ ጉዳት ቀላል አይደለም፡፡ ለወገን ደራXኡ ወገን ስለሆነ እባካችሁ ህሻናትን እናድን፤ ለግሱ፡፡ ጦርነት ያመክናል፤ ተከታታይ ጦርነት አረመኒያዊነት ነው፡፡ ጦርነት ካልቆመ የረሃቡ

እግዚኣብሔር ግን ወዴት አለ?

Go toTop