ከይርጋ ቦጋለ
15ኛው የአሜሪካ የዓለም ዋንጫ ሲወሳ በእግር ኳስ ታዳሚያን አዕምሮ ውስጥ የማይጠፋው ፀጉሩን ወደ ኋላ የሚያስረዝመው ሮቤርቶ ባጅዮ ነው። መልከ መልካሙ ጣሊያናዊ ያለ ግብ የተጠናቀቀውን ጨዋታ ከ120 ደቂቃ በኋላ አሸናፊውን ለመለየት ዳኛው የመለያ ምት ሰጡ። ጣሊያናዊው ወጣት ተራው ደርሶ ኳሷን ሊመታ ሲሄድ፣ እና ኳሷን ለተመልካች ሲሳይ ሲያደርጋት፣ ፊቱን ሸፍኖ ሀዘኑን ሲገልፅ ባጂዮን ማን ይረሳል? በአንድ አጋጣሚ ቡድሀው ወጣት በስፖርት አፍቃሪያን ልብ ውስጥ ይግባ እንጂ በውድድሩ አምስት ግቦችን ያሰቆጠረው ባለ ጠቃጠቆ ፊቱ ብራዚላዊ ግን የውድድሩ ድምቀት እና ኮከብ ሆኖ ነበር ያጠናቀቀው።
የተወለደውም እ.ኤ.አ ጥር 29/1966 ዓ.ም በብራዚል ግዙፏ መዲና ሪዮ ዲጀኔሪዮ ከደሃ ቤተሰብ ነው። በልጅነቱ ከሪዮ ዲጄኔሪዮ ወጣ ብሎ በሚገኘው አላሪዮ ክለብ ሲጫወት በደረሰበት በሽታ ፊቱ ጠቃጠቆ ሆኖ ቀረ። ታላቁን የዓለም ዋንጫ፣ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ እና ኮፓ አሜሪካን ውድድሮች በበላይነት አጠናቋል፣ በክለብ ፉትቦል ሕይወቱ ደግሞ በሄደበት ሁሉ ዋንጫዎችን ጠራርጎ ወስዷል። የዓለም ኮከብነትን ጨምሮ በድምሩ 89 ሽልማቶችን ሰብስቧል። በአጠቃላይ በሕይወቱ ፊፋ የመሰከረለት 1000 ( አንድ ሺ) ግቦችን በስሙ አስመዝግቧል። ይህ ሰው ፔሌ አይደለም፣ ሮናልዶ ሊዊስናዛሪዮ ዴሊማም ሊሆን አይችልም። ብዙዎቻችን ሮማሪዮ እያልን የምንጠራው ሮማሪዮ ዴ ሱዛ ፋሪዮ ነው።
ሮማሪዮ እና የክለብ ፉትቦል
አላሪዮ ከሚባለው የልጅነት ክለብ ወደ ቫስኮ ደጋማ ወጣት ቡድን ተዛውሮ ብዙም ሳይቆይ በ1987 ዓ.ም በ20 ዓመቱ ለቫስኮ ደጋማ ዋናው ቡድን መሰለፍ ቻለ። በቫስኮ ደጋማ ያሳየው ግብ ጨራሽነትና ቴክኒካል ችሎታ የደቡብ ኮሪያ ዋና ከተማ ሲኦል በ1988 ዓ.ም ያዘጋጀችውን ኦሎምፒክ በቴሌቪዥን ሳይሆን በአካል እንዲታደም የብሔራዊ ቡድኑ ጥሪ ደረሰው። በውድድሩም 7 ኳሷችን መጨረሻ መረብ ውስጥ አድርጎ ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ ተመለሰ። ምንግዜም ወጣት ብራዚላውያንን ከአገራቸው ወስዶ ችሎታቸውን ኮትኩቶ የሚያሳድገው የሆላንዱ ፒኤስቪ አይንድ ሆቨን የ22 ዓመቱን ላቲን አሜሪካዊ ይዞት በረረ። በቫስኮ ደጋማ 2 ዓመታትን እና 2 ዋንጫዎችን አንስቶ ወደ አውሮፓ ያቀናው ጠይሙ ልጅ በፒ ኤስ ቪ ቆይታውም ለ4 ተከታታይ ዓመታት የሊጉ ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ ጨረሰ። ክለቡንም ለ3 የሆላንድ ኤር ዲቪዚዮን ሻምፒዮንነት ሲያበቃው 2 የሆላንድ ሱፐር ካፕ ባላቤት እንዲሆንም የአንበሳውን ድርሻ ይዟል። በአጠቃላይ ለቀይና ነጭ ለባሾቹ ፒኤስ ቪዎች 125 ጊዜ ተሰልፎ 129 ኳሶችን መረብ ውስጥ አሳርፏል።
በ1992 ዓ.ም የዩሀን ክራይፍ ቡድን በነጆሴፕ ጋርዲዮላ፣ ሚሽል ለውድድሩ፣ ሮናልድ ኪዩማን እና ሪስቶ ስኮችስኮፍ እየተመራ ባለ ረጅም ጆሮውን የአውሮፓ ክለቦች ሻምፒዮና ቢያነሳም በቀጣዩ ዓመት አይኑን የጣለው በእዚህ ተአምረኛ ወጣት ላይ ነበር። ልክ እንደ ብራዚል እና ሆላንድ ሁሉ በስፔንም የመጀመሪያ ዓመት ቆይታው ለብሉ ግራናዎቹ 33 ጊዜ የላሊጋውን ሜዳ ረግጦ 30ኳሶችን ከበረኞች ጀርባ አሳርፏል። እነዚህ 30 ግቦች ደግሞ በሆላንድ የለመደውን የአገር ውስጥ ሊግ ኮከብ ግብ አግቢ አሁንም እንዲያረጋግጥ አስችለውታል። በክለብ እግር ኳሱ እጅግ ስኬታማ ጊዜን አሳልፎ ወደ ዓለም ዋንጫ ያቀናው አጭሩ ልጅ በዓለም ዋንጫ ታሪክ ስሙን በደማቅ ቀለም ያፃፈበትን ገድል ፈፅሞ እና አራተኛውን የዓለም ዋንጫ ለአገሩ አስገኝቶ ወደ ስፔን የሚወስደውን አውሮፕላን ተሳፍሮ ብራዚልን ለቀቀ።
ከዓለም ዋንጫ መልስ ከክለቡ አሰልጣኝ ጋር የፈጠረው አለመግባባት ከጉዳት ጋር ተደማምሮ ከባርሴሎና ጋር ያስተሳሰረው ገመድ እንዲበጥስ አስገደደው። 13 ጨዋታዎችን ብቻ ተጫውቶ 4 ግቦችን ብቻ አስቆጥሮ ወደ አገሩ ተመለሰ።
ሮማሪዮና ብሔራዊ ቡድን
በደቡብ ኮሪያው የሲኦል ኦሎምፒክ መሰለፍ የጀመረው ሮማ በአጠቃላይ 85 ጊዜ ቢጫውን ማሊያ ለብሶ መሀል ሜዳ ላይ ቆሞ ብሔራዊ መዝሙሩን ዘምሯል። 70ግቦችን ደግሞ ለሴልሳዎቹ (ለብራዚሎቹ) አበርክቷል። አገሩ ብራዚል በአገሯ ፓርቶ አሌግሬ–ሪዮ ግራንዴ ዶሱል ላይ ከጀርመን ጋር ላለባት የወዳጅነት ጨዋታ በአሰልጣኟ ካርሎስ አልቤርቶ ፔሬራ በኩል ጥሪ ስታቀርብለት አቤት ብሎ ይሁንታውን ሰጥቷል። ለ1994ቱ የአሜሪካው የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ በመጨረሻው የምድብ ጨዋታ ኡራጋይ ላይ 2 ግቦችን አሰቆጥሮ ብራዚልም 2 ለባዶ አሸንፋ ወደ አሜሪካ የሚወስዳትን ትኬት ቆረጠች።
በዓለም ዋንጫውም አምስት ኳሶችን ያስገባ ሲሆን በአጠቃላይም ሁለተኛው ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ ዋንጫውንና የኮከብ ተጫዋችነት ሽልማቱን ደርቦ ወደ አገሩ ተመልሷል። በቀጣዩ ዓመትም (በ1997) የኮንፌዴሬሽን ዋንጫን ደርቦ እነሆ በረከት አላት። ለግሉም የግብ አምራች ሽልማቱን የወርቅ ጫማ በመውሰድ የስጦታ መደርደሪያውን ሞላ።
ሮማሪዮና ያመለጡት የዓለም ዋንጫዎች
የፈረንሳዩን የዓለም ዋንጫ ሮማሪዮ በጉጉት ቢጠብቀውም መካፈል ሳይችል ቀረ። ምክንያቱ ደግሞ ጉዳት እንደሆነ ሐኪሞችም ሰምተው ሚዲያዎች አወሩ። ሮማሪዮም የብሔራዊ ቡድን ጓደኞቹን እያለቀሰ ቸር ይግጠማችሁ ሲል ሸኛቸው።
ጃፓንና ኮሪያ የዓለም ዋንጫን በጋራ ሲያዘጋጁ ብራዚልም በዓለም ዋንጫ የመካፈል ሪከርዷን ለማስጠበቅ ተዘጋጀች። ዳሩ ጠንካራዋ አርጀንቲና እና ቺሊ እንዲሁም የነፓትሪስ ክላይቨርት አገር ፓራጓይ ለብራዚል ከባድ ችግር ፈጣሪዎች ሆኑ። ከምድቧም አምስተኛ ሆና ሁለት ጨዋታዎች ቀሯት። የሉይስ ፍሊፕ ስኮላሬ ጥሪ የደረሰው ሮማርዮ አቤት አገሬ ብሎ ቢጫውን ማሊያ ለብሶ ወደ ሜዳ ገባ። በሁለቱ ጨዋታዎችም 7 ግቦችን ሲያስመዘግብ ብራዚል ከገጠማት የግብ ድርቅ ረሰረሰች። አመለ ቁጡው ስኮላሬ ውለታ የዋለላቸውን ሮማሪዮ ትተው ከጉዳት ያገገመውን የኢንተር ሚላን ተጫዋች ሮናልዶንና የፈገግታው ንጉስ የሚባለው ሮናልዲንሆን ይዘው አውሮፕላን ውስጥ ገቡ። ከአገሩ ጋር አንድ የዓለም ዋንጫና የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ፣ 2 የኮፓ አሜሪካ ዋንጫና የደቡብ አሜሪካውያን ዋንጫን ቢያገኝም የሩቅ ምስራቁ የአገሩ ድል ከእርሱ አስተዋፅኦ ውጪ ሆነ።
ሮማሪዮ ያላገኛቸው ድሎች
በተሰለፈበት ሁሉ ግብ የሚያሰቆጥረው የግብ ማሽን ውድድሮቹ ሲጠናቀቁ የዋንጫ ባለቤት እየሆነ ዓመቱን ቢያጠናቅቅም ለአገሩም ሆነ ለክለቡ መስጠት ያልቻላቸው ዋንጫዎች ቢኖሩ ኦሎምፒክ እና የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎች ናቸው።
ሮማሪዮ አሁን
በፊፋ የተመዘገቡለት አንድ ሺ ግቦችን ያስቆጠረው ራስበራ ብራዚላዊ አሁን ወደ አንድ ሺ መቀመጫዎች ባሉት የአገሩ ፓርላማ የሶሻሊስት ፓርቲን ወክሎ እየተሳተፈ ይገኛል። በዚህ ግዙፍ ፓርላማ ከገባ በኋላ የእግር ኳስ ጉዳይ አይመለከተኝም ያለ ይመስል ድምጹን ከሚዲያ አርቋል። ሮማሪዮ ከአንድ ዓመት በኋላ አገሩ በምታዘጋጀው የዓለም ዋንጫ ዙሪያ የሚሰጠውን አስተያየት መስማትም አጓጊ ሆኗል።