“ሁላችንም ሰው ነን “ ።ብለን ካላመንን ሠላምን አናገኛትም –  መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

October 18, 2020
29 mins read

የህሊናቸውን እውነት የልቦናቸውን ኃቅ  የካዱ። ሰው በየምእተ ዓመቱ ያደረገውን የውህደት ጉዞ እና “መካለስ” ከታሪክ እየተረዱ ፣ ሐሰተኛ  የሆነ የፖለቲካ ጥቅም የሚያሥገኝ ትርክት በመፍጠር የሚያወናብዱ። በሰው የኖሩ  መሥተጋብር እና ራስን በህይወት የማቆየት ትግል ወቅትም፣እሥከ ሞት የሚያደርሱ ግጭቶች ፣ጦርነቶች፣ ፍልሰቶች እንደነበሩ እየተረዱ፣ ለዘላቂ ምቾታቸው በማድላት ፣ለሆዳቸው ሲሉ ኃቅን የሚከዱ እና ሐሰተኛ ትርክትን በየቀኑ በማምረት እና ህዝብን በክፉ ወሬ በማሥጨነቅ “እኛ ከሌለን ባዶ!” የሚሉ የዳቢሎስን ካባ የለበሱ ፖለቲከኞች በዚች ሀገር በዝተዋል።

እናም እነዚህ የዳቢሎሥ ካባ ለባሾች፣ኃቅን በመናገር እና ገንቢ ሂስ ከመሰንዘር እና ሰዎችን ወደቀናው ጎዳና ከማምጣት ይልቅ ፣ በ27 ዓመት ውሥጥ ተዘርቶ ያደገው የጎሣ፣የቋንቋ እና የልዩነት ፖለቲካ ቀጣይነት እንዲኖረው አውቀውም ሆነ ሰያውቁ የፕሮፖጋንዳ እና የተግባር ድጋፍ የሚያደርጉ ሆነው ተገኝተዋል።

እነዚህ ጥቂት የማይባሉ ፖለቲከኞች ፣በአመዛኙ፣ በግል ጥቅም ላይ በማተኮር፣  እንደዘመነ መሣፍንት ፣ራሳቸውን በግብዝነት የቆለሉ እንደሆኑም አገር ይመሠክራል። “የ21ኛው ክ/ዘመን የጎሣ እና የቋንቋ መሳፍንቶች” ይላቸዋል አንዳንዱም በጓዳና በሰገነት።

እነዚህ የቋንቋ መሳፍንቶች፣ሰው መሆናቸውን የረሱ፣ቋንቋቸውን የማይናገረውን ሰው ሁሉ፣ እንደ እግዜር (እንደኃይማኖታቸው እንደሚጠሩት እና እንደሚያመልኩት ፈጣሪ ።) ፍጥረት የማይመለከቱ ናቸው።በዚህ ከሰው ጠል ባህሪያቸው የተነሳ  ፣በጣም ጨዋ እና የዋህ የሆነውን የአገሬ ባላገርን በሐሰተኛ ትርክትና በበሬ ወለደ ፕሮፖጋንዳ በማሸበር ከእኩይ ዓላማቸው ጎን እንዲሰለፍ ሲገፋፉት እናሥተውላለን።

እነሱ ዛሬ በሀገር ውሥጥ ና በውጪ አገር ተንቀባረው  እየኖሩ ፣ይኸው ምቾት ና ድሎት ቀጣይነት እንዲኖረው ወይም የምቾት ኑሯቸው እንዳይቋረጥ  ፣በየቀኑ ፣ሰውን በሚናገረው ቋንቋ ተለይቶ እንዲጠቃ በማድረግ ፣የተጠቃው ወገን ለበቀል እንዲነሳሳ ና አገሪቱ ወደማያባራ ግጭት ውሥጥ እንድትገባ በማድረግ ከእልቂቱ ለማትረፍ ያለእንቅልፍ  የእኩይ ሥራቸውን ለመተግበር ይሯሯጣሉ።

እነዚህ ሰዎች  ፣ህገ ወጥነት፣ ሽፍትነት ፣ውንብድና ፣ዘረፋ፣ሌብነት እንዳይንሰረፋ ለማድረግ የሚቻለው ፣ጠንካራ የአገረ መንግሥት መዋቅር እሥከቀበሌ ድረሥ ሢዘረጋና የህግ የበላይነት ሲረጋገጥ እንደሆነ እና ይህ አይነቱ ከፖለቲካ ቡድኖች ፈላጭ ቆራጭነት የፀዳ የመንግሥት መዋቅር የሚፈጠረው ደግሞ በተጠያቂነት ላይ በተመሠረተ ፣የህግ የበላይነት በሰፈነበት ግልፅ አሠራር እንደሆነ እያወቁ፣ለዚኽም አሠራር እውንነት ለህግ፣ለመመሪያና፣ለሙያቸው እና ለዜጎች ተማኝ የሆኑ ተቋማት መገንባት እንዳለባቸው ሳይጠፋቸው፣ሁሌም  ቅንነት የጎደለው ሃሳብን ሲያስተጋቡ ይደመጣሉ ። ሁሉም የለውጥ ሂደት እንደ አንድ የፊልም ድርሰት ዛሬ ና አሁን በሰዓታት ውሥጥ እንዲፈፀም፣ እንዲከናወን ፣እንዲደረግ ና መና ከሰማይ እንዲወርድም ይሻሉ።

ይህ በተምኔት የተሞላ ሃሳባቸው ፣የገዘፈ ፕሮፓጋንዳ ይሆንና ተራውን ህዝብ ያወናብደዋል።የዛሬን ብቻ በመመልከት በጭፍን አመለካከት መንግሥትን እንዲቃወምም ይገፋፋዋል። …

ብዙዎቹ የዩቲዩብ እና የአንዳንድ መገናኛ ብዙሃን  ፕሮፖጋንዲስቶች እንዲሁም የዘውግ ፣የጎሳ እና የቋንቋ ፖለቲከኞች ለዘላቂ ጥቅማቸው ሲሉ ልዩነትን፣ጥላቻን፣መነጣጠልን፣መፈረካከስን እውን ለማድረግ የሚጥሩ ሆነው መገኘታቸው ዋቢ አያሥፈልገውም። ማንም ቀና ሰው ቢያዳምጠው፣የፖለቲካ ትንተናቸው ሽመል የሚያማዝዝ እንጂ እርቅን ፣ሰላምን እና ፍቅርን የሚያመጣ አይደለም።እርግጥ ነው፣ብዙዎቹ፣ለእንጀራ፣ጥቂቶቹ ደግሞ  ለተንዘባነነ ኑሯቸው ቀጣይነት  ሲሉ ፣በአገር አውዳሚው የሽፍትነት፣የውንብድና ፣የሌብነት ና የዘረፋ አሥፋፊ የፕሮፓጋንዳ ሥራ ላይ እንደተሠማሩ ይታወቃል።

መንግሥት ፣መደበኛ መንግሥታዊ ሥራውን ከመሥራት ጎን፣ለጎን፣ ጥበብ በተሞላው ዘዴ ፣ተቋማትን እየገነባ እንዳለ ይታወቃል።ይሁን እንጂ  የአገራቸውን እና የትውልድ አገራቸውን መንግሥት በበዛ ሐሰት በየቀኑ የብጠለጥላሉ።  ይህንን የሥም ማጠልሸት እኩይ ተግባር በማያባራ መልኩ  የሚያከናውኑትም ፣በሚያሳዝን መልኩ፣…  ከዘላቂ ጥቅማቸው አንፃር፣ በዚች አገር ሠላም  እንዳይሰፍን  ሥለሚፈልጉ ነው።

ሠላም በአገር ሰፍኖ ዜጎች  በሰውነታቸው ተከብረው በመላዋ ኢትዮጵያ በሰላም እንዳይኖሩ ለማድረግም፣ታሪካዊ ጠላቶቻችን እና በውድቀታችን ለማትረፍ የሚሹ፣ የውጪ ኃይሎች፣በፕሮፖጋንዳቸው ልክ፣  እንጀራ ቆርሰው ያጎርሷቸዋል። በፕሮፖጋንዳቸው ሥኬት ልክ  በእኩይ ድርጊታቸው እንዲገፉበት ያበረታቷቸዋል።ይህንን እውነት ከትላንት ታሪካችን በቀላሉ መረዳት እንችላለን። ኢትዮጵያ ኃያል እንድትሆን ከቶም የማይፈልጉ ትንሽ ቀና ሥትል በራሳችን ህሊና ቢስ  ሆዳም ሰዎች አማካኝነት ጋሬጣ፣መሰናክል እና ጦርነት በመፍጠር  የሚያቆረቁዞት ትላንትም ነበሩ።ዛሬም አሉ።

እነዚህ ታሪካዊ ጠላቶቻችን፣  በዚች አገር ፣የእርሥ በእርሥ ግጭት ከጠፋ ሰላም ከሰፈነ አትራፊ እንደማይሆኑ ያውቃሉ።የኢትዮጵያ መበልፀግ በአፍሪካ ቀንድና በመላው አፍሪካ የሚያሥከትለውን መንፈሳዊ ቅናት እና ቆም ብሎ ማሠብ መቻልንም በብዝበዛ የከበሩ የኃያላን መንግሥታት ቱጃሮች በቸልታ አያዩትም።እናም  የፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች አላማ እንዳይከሽፍ፣ ቅጥረኞቻቸውም  አትረፊ ሆነው እንዲቀጥሉ፣በኢትዮጵያ  ዘላቂ ሰላም እንዳይኖር  ሌት ና ቀን ያለ እረፍት ተግተው  ያሴራሉ።  ሴራቸውንም በእቅዳቸው መሠረት ይተገብራሉ።

ከሴራቸውም አንዱ፣ ሰውን በቋንቋ ና በፖለቲካ አመለካከቱ መከፋፈል ነው። ተራ ዘለፋና ሥድብን በመጠቀም ኃቀኞችን ማራከሥ ነው።ወረድ ሲሉም ተረኛ፣ሰልፈኛ፣ ተደማሪ፣ ተቀናሽ፣ ወዘተ።በማለት መገበዝ ነው። አውቀውም ሆነ ሳያውቁ የቋንቋ ፖለቲካ አንጃ እንዲፈጠርና ዜጎች እንዲከፋፈሉ ፣የሚያግዝ፣ ማዳበርያ የሚሆን ልዩነትና ጥላቻን የሚያሥፋፋ ፕሮፖጋንዳም መንዛት ነው። …

እንዲህ ዓይነቱን የጥላቻ ፕሮፖጋንዳ ዘወትር የሚያሰሙት በአገራችን ሠላም  እንዳይሰፍን ነው።በሀገራችን ሰላም   ከሰፈነ ፣የፕሮፓጋንዳ ሚዲያቸው ብን ቡሎ እንደ በጋ ጉም እንደሚጠፋ  ሥለሚያውቁ  የእንጀራ ገመዳቸው እንዳይበጠስ በአገራችን ሰላም እንዳይሰፍን በብርቱ ይጥራሉ።

በዚች አገር ሰላም ከሰፈነ ፣ እነሱ ብቻ ሳይሆኑ፣ ሌቦች፣ ቀጣፊዎች ፣ዘራፊዎች፣በምላሥ ጉልበት ነዋሪዎች እንደሚጠፉ የተወቀ ነው።እንኳን እነሱ አሥመሳይ እና ቀጣፊ ኃይማኖተኞች  እንኳን ወደትክክለኛው የእምነት መሥመራቸው ውሥጥ ሆነው በሥርዓት ለመጓዝ ይገደዳሉ።  በኃይማኖታዊው ሥርዓት በወጉ ለመጓዝ የሚገደዱትም ፣ በሠላም ውሥጥ እያንዳንዱ ሰከን ብሎ ማሰብ ሥለሚችል ፣ ሁለት ማሊያ ለብሶ መጫወት ዋጋ እንደሚያሥከፍል ተገንዝበው ና  ልብ ገዝተው የቄሳርን ለቄሳር ማለት ሥለሚጀምሩ ነው።

በሰላም ውሥጥ የሚኖር እምነት ያለው ዜጋ፣ለኃይማኖቱ ዋጋ ና ክብር ይሰጣል።  ሰላም የሚያሳጣ የጥላቻ፣የጠብ፣የመጠላላፍ፣የሥግብግብነት፣የተንኳል፣የጠልፎ መጣል አሥተሳሰብና አሠራር ና አመለካከትን አምርሮ ሥለሚታገልም ፣ሰላሙ ሊደፈርሥ ከቶም አይችልም።

ዛሬ ና አሁን እንደምናሥተውለው ከሆነ ግን  በእምነቱ አላጋጭ በዝቷል።ፈጣሪውን የካደና በእምነቱ የሚያላግጠው ደግሞ የተማረው ሆኖ መገኘቱ በእጅጉ ያሳዝናል።እምነት አለኝ ባዩ ምሁር ሰውን የፈጠረውን ፈጣሪ በመካድ ፣  ” እኔ የፈጣሪ የእጅ ሥራ ሰው ሳልሆን ቋንቋ ነኝ።” እያለ ራሱን ሲጠራ እና የቋንቋ ፖለቲካው አንቀባሮ ሥላኖረው ፈጣሪውን እና ፍጡሩን ክዶ  አውሬ በመሆን አምሳያውን ሲያጠፋ ሥንመለከት ሰው መሆናችንን እና ሁሉም የዓለም ሰው ወንድምና እህታችን መሆንን የተገነዘብን ሰዎችን በእጅጉ ያሳዝነናል።

ለጥቅም ብሎ ሰውነቱን የዘነጋ ሰው፣ ሺ ዓመት ላይኖር በፈጠሪ የተፈጠረውን ሰው ክዶ፣ሌሎቹን ሰዎችንም በሐሰተኛ ትርክት ማስካድ በራሱ አውሬነት መሆኑን ሥለምንረዳ ነው የምናዝነው። በተለይም ዛሬም፣ለሰው የቋንቋ ሥም በመሥጠት ሰው ሰው መሆኑን ክዶ ቋንቋ ነኝ በማለት እርሥ በእርሱ እንዲገዳደል የሚያደርገው ምሁር ወይም ፊደል የቆጠረ መሆኑን ሥናሥተውል የአውሬነቱን ጥግ በቀላሉ  ሥለምንረዳም በነገሩ ልባችን  ዘወትር ይቆሥላል።

የእኛ የልብ ቁሥለት ምንም ላይሆን ይችላል።  ይህ የቋንቋ ፣የጎሳ፣የነገድ ክፍፍል ግን፣ ከፈጣሪ የሚያጣላን ከመሆኑም በላይ፣እኛ ኢትዮጵያውያን የሚከተሉትን ጥያቄዎች ጠይቀን ወደቀልባችን ካልተመለሥን በሥተቀር፣ ወደፊት አሁን ካተዘፈቅነበት የባሰ ማጥ ውሥጥ እንደሚከተን እነዚህን አራት ጥያቄዎች ራሳችንን በመጠየቅ እንረዳ።

1ኛ/ በዓለም የሌለ ሥርዓትን ወይም ርእዮተ ዓለም፣ ሰውን በቋንቋው እየጠሩ  ከፋፍሎ የመግዛት  ወይም በቋንቋ የተቧደነ ሥርዓትን ማነው መጀመሪያ የፈጠረልን ? በእንዴት አይነት፣ ሥር በሰደደ ድንቁርና ውሥጥ ብንዘፈቅ ነው፣ በቴክኖሎጂ አሥገዳጅነት የዓለም ህዝብ እጅግ በተቀራረበበት ክፍለ ዘመን  ፣ኢትዮጵያዊያን ብቻ ፣ከዜግነታችን  ይልቅ በቋንቋችን እንድንጠራ የተገደድነው?  በምን አይነት አዚም ብንደነዝዝ ነው ፣  ሰውነታችንን ክደን ” ቋንቋ ነኝ።” በማለት ራሳችንን በምንናገረው ቋንቋ ልንጠራ ና  አጥር ልናጥር የቻልነው??

2ኛ/ ለመሆኑ ቋንቋ የአንድ ጎሣና ብሄር መገልገያ ብቻ ነውን? እንዲያ ከሆነ እንጊሊዝኛ ፣ፈረሳይኛ፣ አረብኛ፣ እሥፖንሺ ላቲን …ቋንቋዎች የብዙ አገር ህዝቦች መገልገያ ቋንቋ ለምን ሆኑ? በቅንፍ ውሥጥ ያለው ቋንቋ መግባቢያ እንጂ ምንም ያለመሆኑን የሚመሰክር ነው። …

(French is an official language, or shares official status with other languages in Equatorial Guinea, Togo, Central African Republic, Madagascar, Cameroon, Ivory Coast, Burkina Faso, Niger, Benin, Burundi, Guinea, Chad, Rwanda, Congo, Mali, the Seychelles, Djibouti, and Senegal…

There are more than a dozen African countries where English is an official language. These include Zimbabwe, Uganda, Zambia, Botswana. Namibia, Kenya, Sierra Leone, Liberia, South Africa, and Nigeria. )

3ኛ/ በሀገራችን ደግሞ፣ከተጨባጩ ከዓለም  የፖለቲካ ሥርዓት ያፈነገጠ ህዝብ በተባለው የግለሰብ ሥብሥብ ውሥጥ በዜጎች  መካከል የማያደራረሥ ፣የማያግባባ “እናንተ ና እኛ” የተሰኘ የጎሣ ቋንቋ ላይ የተመሠረተ አጥር በማጠር ዜጎች ከአንድነታቸው ይልቅ የቋንቋ ልዩነታቸው ላይ በማተኮር ከሥልጣኔ ውጪ በሆነ መንገድ  ቆዳቸውን በቋንቋቸው ብቻ እንዲያዋድዱ ተደርጓል።

ይህ ሰው መሆናችንን አሥረሥቶ ፣እርሥ በእርሳችን እያናከሰና እያባላ ያለ የቋንቋ አሥተዳዳር እና ሰውን ከሰው የሚያራርቅ የአፖርታይድ የፖለቲካ ሥርዓት ፣ትላንት አባቶቻችን በጋራ የገነቡትን ቤት ከማፍረሱ በፊት  እንዴት የኢትዮጵያ ዜጎች ሰው መሆናችንን ተገንዝበን ለዘላቂ ህልውናናችን እና ለሀገር ብልፅግና ቅድሚያ በመሥጠት የሃያሰባት ዓመቱን የጠላቶቻችንን የከፋፍለህ ግዛ ሥርዓት ማፍረሥ እንችላለን ?

ህወሓት /ኢህአዴግ ለአገዛዙ ቀጣይነት የከፋፍለህ ግዛን መንገድ በቋንቋ ፖለቲካ ሸፋፍኖ  ፣ እርሱ መሣፍንት ና መኳንንት ሆኖ ሌሎች ሎሌ ሆነውለት፣   ሰው መሆንን በካደ የዘረኝነት አመለካከትና አሥተሳሰብ  እየተመራ ለሃያሰባት ዓመት በዚህ አውዳሚ መንገድ ተጉዞ ለመንኳታኮት እንደበቃሥ መዘንጋት ነበረብን ወይ?

ትላንት  “ለተቀረው ኢትዮጵያዊ ዜጋ የአክሱም ሐወልት ምኑ ነው??”  በመባሉ ፣ በዚህ ደፋር ንግግር እጅግ መቋጫታችን ሳይዘነጋ ፣ ዛሬም ይህንን አባባል  በቋንቋ የተሰየሙ የክልል ባለሥልጣናት በሚቀፍና በሚዘገንን መልኩ በፓለቲካዊ መንገድ  ፣በታላላቅ ህዝባዊ መድረኳች ሲደግሙት እየሰማን አይደለም ወይ?  አማራው ለአማራው ብቻ፣ትግሬው ለትግሬው ብቻ፣ኦሮሞው ለኦሮሞ ብቻ ፣ሲዳማው ለሲዳማ ብቻ፣ሱማሌው ለሱማሌ ብቻ ሲሉ አላዳመጥንምን? የፀረ- ፍቅር ፣የፀረ-ሴትነት ፣የፀረ-ጋብቻ ፣በአጠቃላይ የተፈጥሮ ፀር ንግግሮችሥ ሰው መሆናቸውን በካዱ ፣ፖለቲካ ማለት ዘረኝነት እና ቅጥፈት ነው ብለው በሚያምኑ ቋንቋ አምላኪዎች በየመድረኩ ሲነገር አልሰማንምን?

4ኛ/ ፀረ-ሴትነት መሆን የአጠቃላይ ትውልድን ውድመት አያሥከትልም ወይ? ሁላችንም የተገኘነው ከሴት ሆኖ ሳለ ሴትን በቋንቋዋ ከወንዶች ማራቅ ወይም መነጠል ና ቋንቋዊ ማደረግ ከሂትለራዊነት የከፋ አሥተሳሰብሥ አይደለም ወይ??

የትላንት በዶላር የሰከሩ ፖለቲከኞች ቅሥቀሳ ፣ከዚህ በፊት ተጋብተው የወለዱት መሐፀናቸውን እንዲረግሙ የሚያደርግ ና  እንዳይጋቡም የሚከለክል ቀጭን ሂትለራዊ መመሪዬ  ነበርኮ!!

  ማጠቃለያ

የኢትዮጵያን ፖለቲከኞች ሥርዓት ዓልባ እና ራሳቸውን እንደመንግሥት እንዲቆጥሩ ያደረጋቸው ፣በየክልሉ ያለ ሆኖም በየትም ዓለም የሌለ አግላይ የሆነው  በቋንቋ ላይ የተመሠረተው የአገራችን የሃያሰባት ዓመቱ የከፋፍለህ ግዛ ፖለቲካ ነው።የህ የከፋፍለህ ግዛ ፖለቲካ ክልላዊ  አጥርን የገነባ ነው።ይህ የአትድረሱብኝ አጥር፣ የሚያፋቅር ሳይሆን እርሥ በእርሳችን የሚያባላ ነው።ምክንያቱም የዛሬውን በጥበብ የተሞላ የ21ኛውን ክ/ዘ ፈፅሞ የዘነጋ እና እሥከ 19 ኛው ክ/ዘ ወደ አለው  ጥበብ አልባ ሥርዓት የሚወሥደንም ነው።

እርግጥ ነው፣  እሥከ 19ኛው ክ/ዘ ድረሥ ፣በየክፍለ ዓለማቱ፣ባሉ አገሮች ፣የራሥን ቆዳ ፣በተለያየ ርእዮተዓለም አማካኝነት እያዋደዱ በህዝብ ላይ ገዢ የሆኑ መንግሥታት ነበሩ። ከዓለምም ተነጥለው ዓለምም ረሥቷቸው የሚኖሩ ህዝቦች ነበሩ። እንደ ሰው የማይቆጥሩ ፣ በዘረኝነት አለንጋ የተገረፉ አያሌ የአፍሪካ፣የኢሲያ፣የደቡብና የሰሜን አሜሪካ ነበር ህዝቦችም ነበሩ።

በዚህ እጅግ በቴክኖሎጂ በረቀቀ በ21ኛው ክ/ዘመን ደግሞ ከ19 ኛው እና ከ20ኛው ክ/ዘ የነበረ   ሰውን አግላይ አሥተሳሰብ ዋጋ የለውም። በ21ኛው ክ/ዘ የበላይነት ያለው፣ የላቀ ፈጠራ ያለው ሰው ብቻ ነው። ፣የዘር፣የቋንቋ፣የነገድ፣የጎሳ፣የቀለም፣የበላይነት ፈፅሞ ቦታ የለውም ።በመላው ዓለም ያሉ መንግሥታትም ይህንን በመገንዘብ ፣መንግሥታቸውን የመሠረቱት በሰው እኩልነት ላይ ተመሥርተው ነው።የሚያራምዱትም በዜግነት ላይ የተመሠረተ ፖለቲካ ነው።ከዚህ ውጪ የሚሄዱት ሁሉ ሠላም እንደራቃቸው አሥተውሉ።ዜጎቻቸውን በእኩልነት የሚያሥተዳድሩ መንግሥታት ናቸው በአገራቸው ሠላምን በማሥፈን በሀብት ላይ ሀብት በማካበት ላይ የሚገኙት።

በእኛ አገር ግን  በአሳዛኝ መልኩ፣ ዜጎች ከተለያየ የኢትዮጵያ ግዛት በከተሞች ውሥጥ ተደባልቀው ፣ተጋብተውና ተዋልደው እየኖሩ በዜግነት ፖለቲካ አይተዳደሩም። በዜግነት ላይ የተመሠረተ መንግሥታዊ መዋቅር ሳይሆን በቋንቋ ላይ የተመሠረተ አሥተዳደር ነው፣በየክልሉ ያለው።

በየክልሉ ከፋፋይና እንደ ደመትና አይጥ የሚያደርግ ፣አንዱን በይ አንዱን ተበይ የሚያደርግ ሥርዓት ነው የተዘረጋው።ዜጎች በቋንቋቸው ምክንያት ብቻ፣ሰውነታቸውን ረሥተው በጎሪጥ እንዲተያዩ የሚያደርግ ፣ የከፋፍለለህ ግዛ ፖለቲካዊ  ሥርዓት ነው በመላ አገራችን ያለው።

በዓለም በሌለ እውነት እና ፓለቲካዊ ሥርዓት አማራ ነኝ።ትግሬ ነኝ።ኦሮሞ ነኝ።” ወዘተ- ነኝ። ” በማለት ቋንቋቸውን የሰውነታቸው መገለጫ በማድረግ አጥር የሰሩ እና ሌላውም አጥር ሰርቶ የጎሪጥ እንዲተያይ ያደረጉ፣ለመብላት የሚኖሩ  ጥቂት  ምሁራን  ልፍለጥ፣ልቁረጥ፣ልንገሥ የሚሉበት የፖለቲካ ሥርዓት ነው በዚች አገር ያለው።

በበኩሌ እኔ ሰው መሆኔን ጠንቅቄ የተገነዘብኩ እናንተም ሰው መሆናችሁን የምገነዘብ፣ የፈጣሪን ቅን መንገድ አቀንቃኝ ፣ የራሴ ህሊና ዘወትር በቅንነት እንደጓዝ የሚያስገድደኝ ተራ ሟች ሰው ነኝ።ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብትም ሥለሰው እንጂ ሥለ ቋንቋ አያወራም።ቋንቋ ሰውን ከሰው ከማግባባት ያለፈ ፋይዳ የለውም።

ቋንቋ ሰውን ከሰው የማግባባዬ መሣሪያ መሆኑን ለመገንዘብ ብዙ ምርምር አይጠይቅም።ይህ እውነት ሥለመሆኑ፣  የተለያዩ የገጠር ከተማ ገብያዎች ሄዶ ማየት በቂ ነው።

ይህ እውነት አልበቃ ያለው ደግሞ ፣በኦሮሚያ ክልል በትልልቅ ከተሞች የሚደረጉትን የቀበሌ ሥብሰባዎች ተገኝቶ እውነቱን መገንዘብ ይችላል።ከግንዛቤውም ተነስቶ ሰውን ሰው እንጂ ቋንቋ እንደማያሥተዳድረው ይገነዘባል።ሰብሳቢው አካል የክልሉ ቋንቋ ኦሮምኛ ነውና ያለኦሮምኛ አልናገርም ቢል የሚሰማው የለም።ተሰብሳቢውም አንድ በአንድ እየተነሳ ወጥቶ ይሄድና ሰብሳቢው ብቻ በአዳራሹ ውስጥ ሊቀር ይችላል።…

ይህንን እውነት በአንክሮ የተመለከተው የለም።የኢትዮጵያ የሠላም እጦት መንሥኤ ሰው መሆንን መካድ እና ቋንቋን ማምለክ ነው።የኢትዮጵያ የሠላም እጦት አልጠግባይ ምሁራን ፣ የአገራችንን ብልፅግና ከራሳቸው ጥቅም አንፃር በበጎ ከማይመለከቱ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር በህቡ ግንባር ፈጥረው እኛን የጠቀሙ መሥለው የሚያካሂዱብን የጥላቻ ፣የልዩነት፣የመጠፋፋት ወዘተ።ቅሥቀሳ ነው።የኢትዮጵያ የሠላም እጦት መንሥኤ በየጊዜው የሚመጡ መንግሥታት ይዘውት የሚመጡትን እኩይ ሥርዓት በህብረት ያለመቃወም፣ወይም በህብረት ያለመደገፍ ወይም በወሬ እና በአሉባልታ መነዳት የሚፈጥረው ያለመረጋጋት ነው።

ትልቁ፣ የአገራችን የሠላም እጦት መንሥኤ ደግሞ፣በሁሉም አገልግሎት መሥጫዎች ፣በሥውር ና በግልፅ የመንግሥት ና  የፖርቲ አሠራር ተቀላቅሎ መገኘቱ ነው። በዚህ አድሎ ና ሙሥና በበዛበት አሠራርም ህዝብ እንደተማረረ ይታወቃል። ።(ይህንን ሃሳብ በቀጣይ ፅሑፊ እመለሥበታለሁ።)

 

 

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

የአየር ኃይል ጉብኝት በኮለኔሉ ከአገር ሚስጥር አንፃር ሲፈተሽ

Next Story

አባ መስፍንና ህክምናቸው   (ዘ-ጌርሣም)

Latest from Blog

አትዮጵያ ያን ዕለት

ግም ሞት 20’ 1983 .ዓ.ም. ለህወሀት /ኢህአዴግ ልደት ለኢትዮጵያ እና ለብዙዉ ኢትዮጵያዉያን የዉድቀት ፣ጥልመት እና ሞት ዕለት መሆኑን ያ ለሁለት አሰርተ ዓመታት ከፍተኛ ዕልቂት እና ደም መፋሰስ የነበረበት ጦርነት አዲስ አበባ በደም

አቢይ አህመድ ታላቁን አሜሪካንና የተቀሩትን የምዕራብ ካፒታሊስት አገሮችን ማታለል ይችላል ወይ? የአሜሪካ “ብሄራዊ ጥቅምስ ኢትዮጵያ ውስጥ“ እንዴት ይጠበቃል? የአሜሪካ እሴቶችስ(Values) ምንድን ናቸው?

ለመሳይ መኮንና ለተጋባዡ የቀድሞ “ከፍተኛ  ኢትዮጵያዊ ዲፕሎማት” በአሁኑ ወቅት በአሜሪካን የስቴት ዴፓርትሜንት ውስጥ ተቀጥሮ ለሚስራው ኢትዮጵያዊ ሰው የተሰጠ ምላሽ!   ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር) ግንቦት 19፣ 2016(ግንቦት 27፣ 2024) መሳይ መኮንን በአ.አ በ17.05.2024 ዓ.ም አንድ እሱ  የቀድሞው “ከፍተኛ የኢትዮጵያ

ጎንደር ሞርታሩን እስከ ጄነራሉ ተማረከ | ይልማ ምስጢሩን አወጣ “ብርሃኑ ከሸ-ኔ ጋር በድብቅ ይሰራል” | ብይ ክዶናል ለፋኖ እጅ ለመስጠት ዝግጁ ነን

ይልማ ምስጢሩን አወጣ “ብርሃኑ ከሸ-ኔ ጋር በድብቅ ይሰራል” | “ፋኖ ከተማውን ቢቆ-ጣ-ጠር ይሻላል” ከንቲባው |“አብይ ክዶናል ለፋኖ እጅ ለመስጠት ዝግጁ ነን” ኮ/ሉ |“በድ-ሮን እንመ-ታችኋለን እጅ እንዳትሰጡ” ጄ/ሉ
Go toTop