አባ መስፍንና ህክምናቸው   (ዘ-ጌርሣም)

በሀገራችን ህዝብ ላይ ሲደርስ የቆየውና እየደረሰበት ያለው መገፋትና በደል ተዘርዝሮ የሚያልቅ ባይሆንም ችግሩ በሁሉም ብሔር  ብሔረሰቦች ባህሎችና ወጎች የቋንቋ ልዩነት ይኑረው እንጅ ተመሳሳይነት ያለው ነው።ህዝቡን ለጥቃቱ ሰለባ የዳረገው ደግሞ አንድም ድህነቱ አለያም የመማር ዕድል አለማግኘቱ ሲሆን ይህ ደግሞ ለሰው ሰራሽ ችግሮችና መጠቃት አጋልጦታል።ትንሽ ዕውቀት ፋሲካ ነች እንዲሉ ከሥልጣን ጨባጩ እስከ ተራ አጭበርባሪው እኔ አውቅልሀለሁ ይለዋል።የባለሥልጣኑ ከዝርፊያና ከጨቋኝነት የሚዘል ባይሆንም ሌሎች ባህላዊ ተፅዕኖወች ግን ይበልጥ የጎዱት ሆነው ይታያሉ።

ደብተራው፣ቃልቻው፣ሃሳዊ  ምሁሩና ነቢይ ነኝ ባዩ በግንባር ቀደምትነት የሚታወቁት ሲሆኑ ፥

 • አጋንንት አስለቅቃለሁ
 • ለዐይነ ስውር ብርሃን አሰጣለሁ
 • የደንቆረን እንዲሰማ አስችላለሁ
 • አካለ ስንኩሉን አቁሜ አስኬዳለሁ
 • ለመካን ልጅ አስገኛለሁ
 • ነቀርሳ፣ኤድስ፣የጉበት በሽታ፣የስኳር በሽታን ወዘተ እፈውሳለሁ
 • ሀብትና ሹመት ለሚሹ መንገዱን አመቻቻለሁ
 • አዕምሮን ብሩህ አደርጋለሁ
 • ድክመተ ወሲብን አድናለሁ
 • ፍቅረኛሞችን በፍቅር አስተሳስራለሁ
 • ሌላም ሌላም አደርጋለሁ በማለት ሁብት ንብረታቸውን የሚያሸጡና እራቁታቸውን የሚያስቀሩ ቁጥር ስፍር የላቸውም (ብዙዎችንም በስም መጥራት ይቻላል)

ባህሉ ካለው  ወስጣዊና ውጫዊ ተፅዕኖ የተንሳም እነዚህን አጭበርባሪዎች ተው በቃችሁ ዳግመኛም  እንዳይደግማችሁ ብሎ የሚቆጣና በህግ እገዳ  የሚያደርግ የለም፤ከአንዳንድ ልዩ የተባሉ ክስተቶች በስተቀር ።ህብረተሰቡም በቁሙ ከመገፈፍና ከመዘረፍ በተጨማሪ ለሌሎች በሽታዎችና ጉዳቶች መጋለጡ ገሃድ ሆኖ እያለ ደፍሮ ለህግ ይቅረብልኝ ብሎ አቤት የሚል አይታይም፤ቢፈልግስ ለማን?  ከላይ እስከታች ድረስ የጥፋቱ ሰለባ አይደል ! በአሁኑ ወቅት እንኳን ስንትና ስንት ወገኖቻችን በሃሳዊ ነቢያትና አባይ ጠንቋዮች እጅ እየወደቁ የሚደርስባቸውን ጉዳት መደበቅ ከማይቻልበት ደረጃ ተደርሷል።ይህ እንግዲህ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣና መፍተሄ ሳያገኝ  የቆየ ችግር በመሆኑ ጊዜ ይፍታው በማለት ወደ ዋናው ርዕስ ልውሰዳችሁ።

ለዚህ ፅሁፍ መነሻ የሆነኝ ከሰው ሰምቸው ወይም ከመፅሐፍ አንብቤ ያገኘሁት ተረት ተረት ሳይሆን በአካልና በዓይኔ ያየሁትና ያጋጠመኝን አስቂኝ ቢመስልም አሳዛኝ ትረካ ላካፍላችሁ።

ወቅቱ አንደ ኤርፓ አቆጣጠር በ 1973 ዓ.ም የተፈፀመ ክስተት ነው፤በውቅቱ በአንዲት የምክትል ወረዳ ከተማ በስም አመድበር (አሁን ዓለምበር) በአስተማሪነት ለማገልገል የተመደብኩ ሲሆን በአጋጣሚም የተውለድኩበት አካባቢና ወላጆቸ ከሚኖሩበት በሰባት ኪሎ ሜትር ዕርቀት ላይ የምትገኝ ከተማ  ነበረች።በመሆኑም በወላጆቸ ምክንያት ተማሪዎቹና ወላጆቻቸው ሁሉም በሚባል መልኩ ያውቁኝ ነበር  ምንም እንኳን እኔ ባላውቃቸውም።

ከተማይቱ የሚደነቅ ታሪክ ያላት ነች፤ቅዳሜ ቅዳሜ በጣም የደመቀና ድልቅ ያለ የገበያ ቀኗ ነው፤ከአራቱም ማዕዘናት ገበያተኛው በጉን ፣ፍየሉን፣ከብቱን እየነዳ ይገባል፤የሚያቀናውንና የሚለዋወጠውን እህልና ሌሎች የግብርና ምርቶች በአህያዉና በፈረሱ ጭኖ ወደ ገበያው ይተማል፤ሰፊው የገብያ ቦታም ሆድ ዕቃውን ዘርግቶና ለሁሉም እንደ አቅሙና ፍላጎቱ ተመቻችቶ ሲያስተናግድ ይውላል፤ይህን ገበያ ልዩ የሚያደርገው ደግሞ የሚሸጥና የሚለወጥ ሳይዙ መሣሪያ ታጥቀው ወደ ገብያው የሚመጡት ናቸው።ሁኔታውን በደንብ ለሚከታተል ወደ ጦር ካምፕ የሚገቡ ወይም ከጦርነት የሚመለሱ ህዝባዊ ሠራዊት ይመስላሉ።

አርቂና ጠላ በስፋት የሚሸጥባት ከተማ በመሆኗ ለመሸጥና ለመግዛት የመጡት በገብያው ደፋ ቀና ሲሉ ለመዝናናት የመጡት በቀጥታ ወደ መሸታ ቤት ነው የሚያመሩት።በዚህ ቀን ነበር በከተማይቱ ውስጥ አስረሽ  ምችው የሚዘፈንባትና ሲጠጣ የዋለው መሸተኛ በአልኮል አዕምሮውን አነሁልሎ ለድል በዓል እንደሚተኮስ  ርችት የጥይት ጩኽት እያሰማ ጦርነት ተከፍቷል በሚያስብል መልኩ ተኩሱን ሲያዘንብ የሚያመሸው፤ጥይት መተኮስ ደግሞ የተለመደ የወንድነትነና የሀብታምነት መገለጫ ተድርጎ ነው የሚወሰደው በአካባቢው ባህል።በየሳምንቱ በዚህች ከተማ ወስጥ የሚፈፀመውን ትርኢትና ተዕይንት በፅሞና ለተከታተለ የአንድ ትልቅ  መጣጥፍ ባለቤት መሆን ያስችል ነበር።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የአማረ ገመና ሲገለጥ!

በትምህርት ቤቱ ውስጥ ከዘብኛው ጋር በድምሩ አስራ ሦስት መምህራን ነበርን።በቁጥር የምንበልጠው ወጣቶች ስለነበርን ከሥራ ዉጭም ሆነ ቅዳሜና ዕሁድ ጊዜያችን የምናሳልፈው ኳስ ወይም ዳማ በመጫወት ነበር።በዚህ ወቅት ነበር አንድ በዕድሜ  በጣም ጠና የሚሉ ቀጭንና ረዥም የፊት ቅርፃቸው  ክብና ትንሽ ፤ፀጉራቸውን ጨምሮ ጥቁር ሕንዶችን የሚመስሉ ት/ቤት ድረስ መጥተው አስተማሪዎቹን  ይተዋወቁናል።በመጀመሪያ ከዕርቀት ስናያቸው ሕንድ አስተማሪ የተላከልን ነበር የመሰለን ፤ቀረብ ብለን ስንተዋወቃቸው በግራ እጃቸው ተጭሳ ትንሽ የቀራት የሲጋራ ቁራጭ ይዘዋል፤ፊታቸው ደግሞ ጥርስ የሚባል ነገር እንደሌላቸው ከወዲሁ ያሳብቃል፤ጉንጮቻቸው ስርጉድ ብለው ከንፈሮቻቸው ወጣ ገባ እያሉ የሚያወጧቸው ቃላቶች በአብዛኛው ፊደላትን የገደፉ ተብተብ የሚሉና ደስ የሚል ጣዕመ ዜማ ያላቸው ድምፆች ነበሩ። በዚያች አጭር ጊዜ ውስጥ ደግሞ ምንም እንኳን  በጥርሶቻቸው አለመኖር ከአፋቸው የሚወጡት የህፃን ቋንቋ የሚመስል ይሁን እንጅ ለእኛ የማይረዳን የጣሊያንኛ ቋንቋ ዘርነቅ ያደርጋሉ።በትውውቃችን ወቅትም ደጋግመው የተናገሯት ቃል ብትኖር ባፋንኩሎየምትለዋን ነበር ምንም እንኳ ትርጉሙ ለእኛ ግልፅ ባይሆንም።

በመቀጠልም ለምን ወደዚህ እንደመጡ ስንጠይቃቸው የመንግሥት ሠራተኛ ነኝ ነበር ያሉት፤ የሥራቸውን ዓይነት ግን መግለፅ አልፈለጉም።ከእኛ ጋር በዚያች ዕለት ይተዋወቁ እንጅ ለካስ ከመጡ ሦስት ዓመታትን አስቆጥረዋል፤ተያይተን ግን አናውቅም ነበር።ለትንሽ ጊዜያት ስናወራ ከቆየን በሁዋላ ዳይሬክተሩ አብረውን ወደ ሰፈራችን እንድንሄድ ስለጋበዛቸው ተያይዘን ሂደን መጨዋወት ጀመርን።

አባ መስፍን ሲያወሩ ማዳመጥ የሚሰለቹ  አልነበሩም ይልቁንም ፊልም የምናይ ወይም በአንድ የስብሰባ አዳራሽ ወስጥ ተሰብስበን የምናዳምጣቸው ይመስል ነበር።

አባ መስፍን ሲጋራ በጣም ያጨሳሉ፤አንዴ የለኮሱትን ሲጋራ ጨርሰው አያጨሱትም፣ሌላውን እስከሚለኩሱ የመጀመሪያዋን ያለ እሣት ከአፋቸው ወትፈው በሚኮላተፍ ምላሳቸው ሲያወሩ ማዳመጥ ይበልጥ ይማርካሉ፤ቀጥለውም ሌላ ሲጋራ ሲለኩሱ የተጀመርውን ይጥሉታል፤ሲጋራው ግሥላ በመሆኑ ሽታው አጭሶ ለማያውቅ ጥሩ አልነበረም።

በጨዋታ መካከል ዳማ መጫወት የሚችል ከመካከላችን እንዳለ ሲጠይቁ ሁላችንም እንደምንችል ሲነገራቸው ወደፊት እሳቸው እየመጡ ወይም እኛ ወደ እርሳቸው በመሄድ መጫወት እንድንችል ግብዣ ሲያቀርቡ አውንታዊ መልስ ከሁላችንም አገኙ፤ጊዜም ሳይወስዱ ከሁለት ቀናት በሁዋላ ከሥራ እንደወጣን ከእርሳቸው ቤት እንድንገናኝ  ስለጋበዙን ሁላችንም ተስማምተን በተባለው ቀን ሄድን።ከቤታቸው ስንደርስም የተለመደች ሲጋራቸውን በከንፈሮቻቸው እያጫወቱ ወጥተው ተቀበሉንና ወደ ወስጥ አስገቡን።በደንብ ተዘጋጅተው ነበር የጠሩን፤ፍየል አሳርደው ጠላና አረቂ አዘጋጅተው ሞቅ ያለ አቀባበል ነበር።በዕድሜ ከእርሳቸው በጣም ወጣት የሆነች ሴት ባለቤቴ ነች ብለው አስተዋወቁን ።

ከደራው ጨዋታችን መካከል አንድ የገጠር ነዋሪ ሰው ከሚስቱ ጋር ሆኖ ስለመጡ አስገቧቸው፤ብዙም ሳይቆዩ በአፈ ድስት ብርሌ አረቂ  ቀረበላቸው።አክብሮትና ሀፍረት በተቀላቀለበት ስሜት ጥግ ይዘው በመቀመጥ የቀረበላቸውን አረቂ መጠጣት ጀመሩ።ብዙም ሳይቆዩ ባለቤታቸው ሲሪንጅ የተቀቀለበት ብረት ድስት ይዛ በመምጣት ለአባ መስፍን ሰጠቻቸው፤እሳቸውም ተቀብለው ሴትዮዋን ወደ መጋረጃው ውስጥ በማስገባት መርፌውን አዘጋጅተው ተከትለዋት በመግባት ከጥቂት ደቂቃወች በኋላ ሁለቱም ተመለሱ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  በግልፅና በቀጥታ ካልተነገርን የመከራው ፖለቲካችን ማቆሚያ አይኖረውም  - ጠገናው ጎሹ

ከመካከላችን አንዱ አላስችለው አለና ሀኪም ነወት እንዴ! በማለት ሲጠይቃቸው አወ ሀኪም ነኝ አሉ፤በመቀጠልም የታካሚዋ ባለቤት ዶክተር እያለ ሲያወራቸው ይደመጣል።ብዙም ሳይቆዩ የአረቂውንና የህክምናውን ሂሣብ በመክፈል አመስግነው ሲሄዱ፤ እኛም በነገሩ ብዙም ጣልቃ መግባት ስለአልፈለግን የግላችን ተጨዋውተን ተለያየን።

ከዚህ በኋላ ነበር የአባ(ዶክተር) መስፍን ግንኙነት ከእኔና ከአንድ በጣም የቅርብ ጓደኛየ ከነበረ አስተማሪ ጋር ይበልጥ መጠናከር የጀመረው።የመጀመሪያውን የህክምና ክስተት ከአየሁ በኋላ ህሊናየ በመጠኑም ቢሆን እረፍት አጥቶ ነበር፤ ህክምና ፈልገው ለመጡ ታካሚዎች ለምን አረቂ በቅድሚያ አንዲጠጡ አስቀረቡላቸው የሚለው ሲሆን  ሁለተኛው የአካባቢው ልጅ በመሆኔ እንዴት ይህ ሊሆን ይችላል ? ተቆርቋሪና ለምን?  አንዴት?  የሚል በመጥፋቱ እኮ ነው በማለት ነገሮችን በትዕግሥትና በጥበብ ለመከታተል ወሰንኩ።

አባ (ዶክተር ) መስፍን ማናቸው?  ሙያቸውስ ምንድን ነው?  ለምንድን ነው የሚሠሩበትን መሥሪያ ቤት መናገር ያልፈለጉት?  ወዘተ ለሚሉት መልስ ለማግኘትና ለማወቅ ይበልጥ ልቀርባቸው ተነሳሳሁ።ስለማንነታቸው ሲነግሩኝ ሰሜነኛ ነኝ ብቻ ነበር የሚሉኝ፤ዐረብኛ፣ጣሊያንኛና የይሁዲ ቋንቋ በደንብ እንደሚችሉ ከነገሩኝ በኋላ  ለብዙ ጊዜ የኖርኩት ምስር አገር (ግብፅ ማለታቸው ነው) ነው፤ጣሊያንኛ የተማርኩት ግን በልጅነቴ ነው፤ሱዳን አገርም ነጋዴ  ሁኘ ለብዙ ጊዜ ኑሬያለሁ ይላሉ።እኔም ስለ እሳቸው ላውቅ የፈለኩትን በትዕግስትና በጥበብ ለማወቅ ስለፈለኩ ብዙም በሃሳብ አልጋፋቸውም ነበር።ዳማ ጨዋታ በጣም ስለሚወዱ ከሥራ ብኋላ አዘውትረን መገናኘት ጀመርን፤አብዛኛውን ጊዜ ከእርሳቸው ቤት ሲሆን ከአኔና ከጓደኛየ ቤትም መገናኘት ችለናል።በተለይ ከእርሳቸው ቤት በምንጫወት ወቅት በርካታ የገጠር ነዋሪ የሆኑ ሰዎች ስለሚመጡ ህክምና ያደርጉላቸው ነበር።የህክምናው ዓይነት ግን በጣም አስቂኚና አሳዛኝ ነበር፤ለሁሉም ታካሚ የሚሰጡት መድሃኒት አንድ ዓይነት ነው፤ፒኒሲሊን በመርፌ ወይም በክኒን መልክና  አረቂ ናቸው።ከኪሳቸው አንድ የልብ ትርታ ማዳመጫ ስቴትስኮፕ ፣አንዲት ሲሪንጅና በብልቃት ውስጥ ያሉ ቴትራሳይክሊን ክኒኖች አላቸው።

በዳማ ጨዋታችን መካከል አንድ ታካሚ ከመጣ ያቋርጡና ባለቤታቸውን ይጠራሉ፤ሴትዮዋም ጥሪው ለምን እንደሆነ ስለተለማመደች በቀታ ትመጣና ለታካሚዎቹ አረቂ ታቀርባለች።አረቂው ከውጭ የሚመጣ ሳይሆን የራሷ መተዳደሪያ ሥራ መሆኑ ነው።በመቀጠልም አንዲት የተቀቀለች ሲሪንጅ ታመጣና ለአባ (ዶክተር ) መስፍን ታቀርብላቸዋለች።

    ታካሚው (ታካሚዋ) የቀረበላቸውን አረቂ  እንዲጠጡ ይደረግና ባለጉዳዩን  ወደመጋረጃዋ ውስጥ ይዘው ይገባሉ።ሲመለሱ ባለጉዳይ የአረቂውንና የህክምናውን ሂሣብ ከፍለውና አመስግነው ሲወጡ ሌላው ባለተራ ይቀጥላል፤የዳማ ጨዋታችንም በዚህ መልኩ እየተደናቀፈ በደንብ ሳንጫወት የምንለያየው ብዙ ጊዜ ነበር ፤እሳቸውም እንደተለመደው የህክምና ሥራቸውን ይቀጥላሉ።

ከዕለታት አንድ ቀን ነገሩ በጣም ስለከነከነኝና በወገኖቸ ላይ የሚደርሰው በደል ቁጭት ስለአሳደረብኝ ላነጋግራቸው ወሰንኩ፤እሳቸውን ከማነጋገሬ በፊት ግን የጓደኛየን አስተያየትና ድጋፍ ስለፈለኩ አማከርኩት፤እሱም ለካስ ከእኔ በባሰ መልኩ ተናዶባቸው ኖሮ ቢቻል ለፖሊስ ማጋለጥ ይገባ ነበር አለኝ፤አኔ ግን ያን ያህል ዕርቀት ሂጀ መጉዳት ስለአልፈለኩ ማነጋገሩን አስቀደምኩ።ቦታና ጊዜ በመምረጥም እኛም ዕረፍት በምሆንሆንበት ጊዜና ለእሳቸው ያመቻል ያልኩትን ዕሁድ ቀን መረጥኩና ብናወራ ይሻላል በማለት ከጓደኛየ ጋር ቀጠርናቸው፤እሳቸውም ያለምንም ማቅማማት ተሰማሙና ተገናኘን።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ይድረስ ለግንቦት ከየካቲት

በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ስናወጋ ቆየንና ስለህክምና ልምዳቸውና ስለአየሁት ያልተለመደ አረቂን ከፔንስሊን  ጋር የህክምና ዕርዳታ ፈልጎ ለመጣ ሰው ለምን እንደሚሰጡ ለስለስ ባለ አነጋገርና በተረጋጋ  መንፈስና ማወቅ በሚፈልግ ስሜት ስጠይቃቸው ከት ብልው ሣቁ።ጥርስ የላቸውም እንጅ  እኛንም አብረው በአሣቁን ነበር፤ ያም ሆኖ ፈገግታቸው በጣም ያዝናናል።ቀጠሉና አደን አድናችሁ ታውቃላችሁ?  የሚል ጥያቄ ሲያቀርቡ ጓደኛየ ተቀበለና ምን ዓይነት አደን? አላቸው፤አባ መስፍንም በመቀጠል አነበሳ፣ነብር፣ድኩላ፣ሚዳቋ፣ሰሳ፣አጋዘን ስንቱ ተዘርዝሮ በማለት በድጋሜ ከት ብለው ሣቁ።እኛም ግራ በመጋባት ምን ያስቃል እውነቱን ነው ያልነው ስንላቸው የአሁን ጊዜ ልጆች ብዙ ማወቅና መማር የሚገባችሁ በርካታ ነገሮች አሉ ብለው መሣቃቸውን ቀጠሉ።

በዚህ ጊዜ ትንሽ እንደ መናደድ አልኩና ይህ የሚያስቅ ነገር የለውም ፤እኔ ድርጊቱ  ከንክኖኝ ነው ይህን ጥያቄ ያነሳሁትና ከቻሉ ይመልሱልኛል እንጅ ሊስቁብኝ አይገባም ስላቸው ከምንም ነገር ባለመቁጠር መሣቃቸውን ቀጠሉ።በዚህ ጊዜ ጓደኛየ በጣም ተናደደና ለመሆኑ እርስዎ  በህግ የተረጋገጠ የህክም ዕውቀትና ልምድ አለዎት?  ወይስ በተለምዶ አውቃለሁ እያሉ ህዝብን የሚዘርፉና የሚያታልሉ የሀሰት ሀኪም ነዎት ሲላቸው ፊታቸው በድንጋጤ አመድ ለበሰ፤በድንጋጤ ቆፈን ውስጥ እንዳሉ ፈራ ተባ እያሉ የህክምና ዘዴዬን ልንገራችሁ አዳምጡኝ አሉና ቅድም አደን  ትችላላችሁ ወይ? ብያችሁ ነበር፤ ያለ ምክንያት አይደለም የጠየኩት፤ እናንተን በቀላሉ እንዲረዳችሁ በየ አንጅ። አንድ ሰው አደን ወጥቶ የዱር አውሬ ሲያድን አውሬው ጥቅጥቅ ያለ ጫካ ውስጥ መሽጦ ሲደበቅ ያለው ምርጫ አንድ ነው ፤ወይ አደኑ አልተሳካልኝም ብሎ ባዶ እጁን ቤት መመለስ አለዚያም ቀንቶትና ድልን ተቀዳጅቶ በደስታና በፈንጠዝያ በድል ወደ ቤት መመለስ ነው።አደኑን የተሳካ ለማድረግ ደግሞ ምርጫው አንድና አንድ ነው ፤አውሬውን ከጫካው ማስወጣትና ሊያመልጥ ሲሮጥ አነጣጥሮ በመተኮስ ግንባር ግንባሩን መትቶ ድልን መቀዳጀት ወይም አውሬውን ከጫካው ለማስወጣት ደግሞ እሣት ወይም ጉንዳን  መልቀቅ ነው፤የሰውን ልጅ በሽታም በዚህ መልኩ ነው ከሚጠቃው ሰው ህዋሳት ማስወጣት የሚቻለው።በሰውነት ውስጥ የተደበቀን በሽታ አድፍጦ ከተኛበት ለመቀስቀስ ደግሞ አረቂ  አንጡ ድገሙ የተባለለት አዳኝ  መጠጥ ነው፤በደም ውስጥ የተደበቁት የተለያዩ በሽታዎች ከአደኑ ለማምለጥ እንደ አፍላ የውሃ ሙላት ሲርመሰመሱና በስካር ሲወራጩ አረቂ ሆየ እየተቀበለ ማጅራት ማጅራታቸውን በማነቅ በአጭር ጊዜ ውስጥ አስክሮና አደንዝዞ ከመድሃኒቱ እጅ ይጥላቸዋል ማለት ነው።በመሆኑም አረቂውን የምንጠቀመው ለመቀስቀሻነት እንዲያገለግለን እንጅ ለመጠጥነቱ ፍቅር አይደለም።እስኪ በሁሉም ደብር ዙሩና ስለእኔ የህክምና ችሎታ ጠይቁ፤ይህን ያህል ዓመት በዚህ ሙያ  ስሠራ  በእጀ ላይ የአንድም ሰው ህይወት አላለፈችም እንዲያውም በምሰጣቸው ህክምና በእጅጉ ስለሚረኩ እሸቱን ፣ወተቱን፣ቅቤውን፣ማሩን፣ጤፉንና ጥራጥሬውን እየጫኑ በመምጣት የሚያመሰግኑኝና ወዳጅ ያደረጉኝ ቁጥር ስፍር የላቸውም፤ ነፍሰ ጡር ሳይቀር ያለምንም ጭንቀትና ስጋት በሰላም እንድትገላገል የማድረግ ችሎታ ያለኝ ፍቱን ሁኪም ስለመሆኔ በአደባባይ ህዝቡን መጠየቅ ይቻላል በማለት ፌዝ የተሞላበት ጨዋታቸውን ሁሌም ሳስታውሰው እኖራለሁ።እኔ የማውቃቸው አንድ አባ (ዶክተር) መስፍንን ይሁኑ እንጅ ስንት መስፍኖችና  የሀሰት ሃኪሞች እንዳሉ ቤት ይቁጠረው!!

የትዝብት ትውስታየን በዚህ  ቋጨሁ

የእርስዎንም ትዝብት ያስነብቡን

 

 

 

1 Comment

 1. ዘ ጌርሣም እሰይ መልካም አስነብበህናል፡፡ እኔም ከገጠመኝና ከሰማሁት እንሆ፡፡ ጊዜው ሁሉ እንዳሻው የሚፈነጭበት ነበር፡፡ ሴት እንደ ልብ ነው፡፡ ያው ወጣቱነቱም ስላለ ጉልበትም በሽ ነው፡፡ የወሲብ ግንኙነት ለማድረግ ታብሌት የማይዋጥበት ጭዋ ዘመን፡፡ ታዲያ በዚህ ግርግር ውስጥ አንድ ጓደኛዬ አሁንም በህይወት ያለ በወሲብ የሚተላለፍ በሽታ ይይዘውና መድሃኒቱ አዲስ አበባ ተፈልጎ ይመጣል፡፡ በጊዘው በጣም ውድ መድሃኒት፡፡ የመድሃኒቱ ስም ትዝ ይለኛል Togamycin ይባላል፡፡ በቅርብ ወዳሉት ፋርማሲዎች ወደ አንድ በመሄድ መድሃኒቱን ይሰጥና ውጋኝ ይለዋል፡፡ የህክምና አዋቂውም ራሱ በበሽታው ይሰቃይ ስለነበር ልጅን ውሃ መሳይ ነገር ይወጋውና መድሃኒቱን ለራሱ ያስቀራል፡፡ ይህች ነች አራዳ ከዚያ በህዋላ የተፈጠረውን መዘርዘር በዚህ ላይ አይቻልም፡፡ ግን እዚያው የሚሰራ ጓደኛው ነው እከሌን የወጋሁት መድሃኒት ጭራሽ በክፍለሃገሩ የለም ሲለው ምን መድሃኒት ነው ቢለው የልጅ መድሃኒት መሆኑ የታወቀው፡፡
  አንዲት መልከ መልካም ልጅ ትታመም እና ወደ ጠንቋይ እናቷ ትወስዳታለች፡፡ ጠንቋዪም ቡናውን አስፈልቶ ዲቡን እየመታ ልጅቷን ከመጋረጃ ውስጥ እንድትገባ አድርጎ ይደፍራታል ዘመኑ የኤድስ ዘመን ነበርና እሷ በእርሱ ተለክፋ ታልፋለች፡፡ ጉዳዪንም ለቤተሰ ከመሞቷ በፊት ትናገራለች፡፡ ግን ምን ሊደረግ እሱም አፈር ለብሷል፡፡ ሌላዋ እድን ባይ ጠበል በሚባል የውሸት መድሃኒት ሃገር አቋርጣ፤ ስንቅ ከውና ከቦታው ስትደርስ ስፍራው በሰው ተጨናንቋል፡፡ ያው ወረፋዋ ደርሶ ከጠበሉ ጠጥታና ተረጭታ ስትመለስ የያዛት ነገር ብሶባት በመንገድ ላይ ትሞታለች፡፡ ወደ ዘመኑ የውስልትና የሃብት መፈለጊያ ወንጌል ስንመጣ ደግሞ ክራራይሶ ያሰኛል፡፡ በህዝባችን ላይ የሚቀልድት ቄሶች፤ ደብተራዎች፤ ኣለም ልታልፍ ነው እያሉ የሚያስፈራሩ ወስላቶች፤ ፓስተሮች፤ ሃዋሪያ ነን ባዪች፤ ነብይ ነን ብለው የሩቁን የሚናገሩና ከተናገሩት አንድም ሳይሆን ዛሬም ቆመው የሚለፈልፉ ዘማሪ ደረጀ ከበደ እንዳለው “የወንጌል ተጧሪዎች” እልፍ ናቸው፡፡ በመሰረቱ የህዝባችን ሰቆቃ አጉል እምነትና መሰረት የለሽ ሃይማኖት ነው፡፡ በእስልምናው እምነት ዙሪያ ስንሄድ ደግሞ ያው ግፍ የደረሰባቸው በየሚዲያው የሚዘረዝሩት ስለሆነ ባልፈው ይሻላል፡፡ ባጭሩ ህዝባችን የሚያማቱትና የሚዘርፉት ፓለቲከኞችና ዘረኞች ብቻ ሳይሆኑ በሃይማኖት ስም ነጋዴዎች፤ ጠንቋዪች፤ አታላዪችና አስመሳዬች፤ የምድር ሥርና ሃረግ መድሃኒት ይሆናል በማለት የሚምሱና የሚቆርጡ አላዋቂዎች የሚያስከትሉት ሰቆቃ እልፍ ነው፡፡ ከወያኔ የዘር ፓለቲካ ወደ ኦሮሞው የዘር ፓለቲካ ተዘዋውረን ይኸው እንሆ ቋንቋችን ሁሉ ከመደባለቁ የተንሳ ራበኝ፤ እርዳኝ፤ ድረስልኝ ለማለት እንኳን የከበደ ጊዜ ደርሰናል፡፡ የምችለው ስጠኝ የሚሉት አበው ነገር ሁሉ ጨለማ ሲሆንባቸው ነው፡፡ የጋራ የመግባቢያ ቋንቋ የሌለው ሃገር ለእድገቱም ሆነ ለአንድነቱ ጭራሽ እንቅፋት ነው፡፡ ግን ሁሉም ሃገር ሆኖ ባንዲራ በሰቀለባት ምድር አንድነትን መሻት እብደት ነው፡፡ የመንዘላዘሉ የሃበሻ ፓለቲካ ምንንም ሳይጠቅም ልክ እንደ ጠበሉና ጠንቋዪ በወረፋ ሌላ ይተካበታል፡፡ህዝባችንም በማያድን መድሃኒት፤ ቃላቸው በማይደር ነብያትና ሃዋሪያት፤ በአጠቃላይ በውሸት የሃይማኖት ጫና እንደ ጎበጠና እንደተጭበረበረ ይኖራል፡፡ የሚያሳዝነው ተምረናል አውቀናል የሚሉትም የዚህ የማያድን የጠበልና የሃይማኖት ልፍለፋ ተካፋይ መሆናቸው ነው፡፡ ሃኪም አትድንም መንገድህን አሳምር ትሞታለህ እያለው አጭበርባሪው ቀርቦ ጌታ ፈውሶሃል እያለ ያለውን ሲዘርፈው ማየትና መስማት አስነዋሪ ነገር ነው፡፡ ከተፈወሰ ራሱን ትሞታለህ ላለው ሰው ሂዶ ማሳየትና በእርግጥም እንደተፈወሰ ሳይንሱ ሊነግረው ይገባል፡፡ ውሃ አያድንም፤ ቄሱ፤ ፓስተሩ፤ ጠንቋይና ቃልቻው ለራሳቸው አያውቁም፡፡ ህዝባችን ሊጠነቀቅ ይገባዋል፡፡ እንደ በፊቱ ቀማኞች ጫካ አይደሉም በመንደሮችና በከተማ ውስጥ እንጂ፡፡ በቃኝ!

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.