የኔ ውብ ከተማ (ዘ-ጌርሣም)

ገና በልጅነት
በታዳጊው ስሜት
በነበረኝ ምኞት
ካርታዋን በልቤ ቀርጨ የሳልኳት
የኔ ውብ ከተማ የምድራችን ገነት
እንዲህ ትመስላለች
በውበቷ ምህሣሳብ ከሩቅ ትጠራለች
ሁሌም የምመኛት
መምሰል የሚገባት
እንደ አዲስ ሙሽራ ሆ ! በሉ እያሰኘች
በአጃቢ ሚዜዎች እንደተከበበች
ከቤቷ ሳትወጣ ገና ጫጉላ እንዳለች
ታዳሚው ሳይገባ የተሽሞነሞነች
ለሌሎች ከተሞች ትምሳሌት የሆነች
ጣፍጩ ዉኃዋ
የውስጥ መዓዛዋ
አልባብ አልባብ ሲሸት
እንደ ቤተ መንግሥት
በሚያምሩ ተራሮች ዘብ በሚጠብቁ
ምንጮች የሞሉባት የሚፍለቀለቁ
ሁለቱ ጅረቶች ጎን ለጎን ሲፈሱ
ያካባቢን ልማት ህይወት እያደሱ
ከሩቅ ይጣራሉ
ቤት ለእንግዳ ብለው ያስተናግዳሉ
የኔ ውብ ከተማ እንደዚህ ታምራለች
በፍቅር ኑሩብኝ ብላ እየጋበዘች
በመንገዶች ጥራት
በመብራቷ ውበት
ደምቃ የምታይዋት
በአራቱም ማዕዘናት
ለዕድገት በመነሳት
ሰላምን ትራሷ
አንድነትን ልብሷ
ልማትን ብርታቷ
ታሪክን ኩራቷ
አምራቹን አርክታ
ሸማች አስደስታ
አብራ የምታኖር
ያለምንም ችግር
እንደ አንድ ቤተሰብ
እንደ ሚተሳሰብ
ካባ እንደለበሰ
እንደተወደሰ
አምራና ተውባ
ቀዝቃዛውን አየር ከተራራው ስባ
ለቆላማው ምድር እስትንፋስ መግባ
ታስተናግዳለች ሁሉን አስመችታ
እስኪ ዳቦ እንቁረስ ስም ብታወጡላት
ንገሩኝ ልክተበው ማን ብለን እንጥራት
በውበት ላይ ውበት የተሽሞነሞነች
እንደ ንጋት ኮከብ ደምቃ ትታያለች
መጥታችሁ ኑሩብኝ ብላ እየጋበዘች
የኔ ውብ ከተማ ግብዣዋን ልካለች

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.