ዴሞክራሲ ወድደን በምንተገብረው ሥርዓት(Manifestation ) እና ተገድደን በምንተገብረው ሥርዓት መካከል፣ያለ የነፃነት ቀጭን ክር ነው እንጂ፣ቅኝ ገዢዎችና ባንዳዎች በጠመንጃ የሚለግሱን ፍርፋሪ አይደለም።ለምሳሌ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ በጠላት እጅ በተረሸኑበት ወቅት፣ቀደም ሲል በዛው በተረሸኑበት አደባባይ ላይ ጭምር ወጣት ኢትዮጵያዊያን ፣ምልምል ባሊላዎች (ካድሬዎች) በፕሮፓጋንዳ ግፊት ኢትዮጵያችንን “ፋቺታ ኔረ!” (ኔግሮዋ ወጣት) በሚል መዝሙር እያሞካሹ የፋሺሥት ግዛት ተቀባይነቷን ሲዘምሩ፣በገጠሯ ኢትዮጵያ ግን (በኤርትራ ጭምር) አባቶቻችን “ኢትዮጵያ ወይም ሞት!” እያሉ ለነፃነት መፋለማቸው፣በባህልና በታሪክ አነሳሽነት ወድደው በተገበሩት አባቶችና ተገደው በተገበሩት ልጆቻቸው መካከል ያለው የነፃነትና የዴሞክራሲ ቀጭን ክር ፍንትው ብሎ ይውለበለብ ነበር።ዛሬም በልባችን ውሥጥ ይውለበለባል።ለዘህ ነው ዛሬም በአፅኖት ደጋግመን “ራሳችንን እንወቅ” እምንለው።
ቀይ ሕንድን ከጠቅላላው ሰሜን ና ደቡብ አሜሪካ ምድረ ገፅ ትላንት የደመሰሰ፣የጥቁርን ዘር ከጠቅላላው የአውስትራሊያ ክፍለ አህጉር ትላንት የገፋ ሤራ ዛሬ አፍሪካን ይለቅልናል ብለን ራሳችንን እንዳናሞኝና እርስ በእርሳችን በጭፍን እንዳንናቆር እንጠንቀቅ ። “ውሃ ሙላት ሲወስድ እያሳሳቀ ነው።” እንዲሉ፣ይኼ በባህል ካባ ሸፋፍነን፣ በምር የተያያዝነው ማዘናጊያ የጎሣ ፕሮፖጋንዳ በቁማችን እንቅልፍ እያሥወሰደን ነው።ዛሬ ላይቤሪያ፣አልጄሪያ፣ሩዋንዳ፣ብሩንዲ፣የመጀመሪያዎቹ መረማመጃ ክስተቶች ናቸው። ናቸው እንጂ የመጨረሻዎቹ አይመሥሉኝም።ሥለዚህ በቶሎ “ራሳችንን ካላወቅን” እግዛብሔር አይበለውና ገና የባሰ ጉድ እናይ ይሆናል።ዛሬም ጥንትም ሕይወት የሚዘራብንን፣ካም አበው በጋራ ያወረሱንን ፣ለዓለም ጥቁር ዘር ሁሉ የመሠረት ድንጋይ የሆነውን ራሳችንን የማወቅ፣ሕዝብን እና ሀገርን ከልብ የመውደድ፣ ፅናታችንን፣የሰብዓዊ ክብር ፍቅራችንን፣የማይናወጥ ኢትዮጵያዊነታችንን ፣እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ አንድነታችንን ፣በባዕዳን ሥውር ሴራ በተደገሰልን የጎሰኝነት መርዝ ታውረን እንዳንደመስሰው እጅጉን እንጠንቀቅ።
እንደነሶቅራጥስ ያሉ ፈላሥፎች ና የጥበብ ሰዎች፣የመርዝ ፅዋ ጠጥተው ያተረፉልንን ዴሞክራሲ፣እንደነ ፑሽኪን ያሉ የጥበብ ሰዎች በቅጥረኛ ጥይት ተገድለው ያተረፉልንን ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት (Freedom of Expression ) እኛ በራሥ ወዳድነት ተቆልምመን፣በፍርሃት አጎብድደን በጎሰኝነት ብናስገድላት የነገው ታራክ ምሥክሮች፣እኛ ሳንሆን ህዝብና ትውልድ መሆናቸውን ከቶም አለመዘንጋት የሚያሥፈልግበት ጊዜው አሁን ነው።
ባለቅኔ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን
ጦቢያ መፅሔት ቅፅ 6 ቁጥር 1፤ 1990 ዓ/ም
………………………………………………………..
ራሥን ማወቅ ማለት ከድንቁርና ነፃ መሆን ነው።አኛ ኢትዮጵያዊያን ለሺ ዓመት የተገነባ ድንቅ ባህል ያለን ህዝቦች ነን።እነዚህ ድንቅ በህሎቻችን በቋንቋ፣ባለባበሥ፣በእደ ጥበብ፣በልዩ ልዩ የቤት ውሥጥ ቁሳቁሶች፣በአመጋገብ፣በህንፃ ሥራ፣ በኪነት ወዘተ።ይገለፃሉ። ባህላችን በራሱመደበላለቃችንን ይመሠክራል። የአንዳችን ባህል ከሌላኛው ባህል ጋር ድርና ማግ ነው።ባህላችን በዘመናት ሂደት ውሥጥ በወጉ ተፈትሎ የተሸመ ነው ።
ይህንን ቱባ ባህል፣ወደገደል ለመጨመር እና የከፋፋይ፣ነጣጣይ፣እና ጅበኛ ርእዮተ ዓለምን በላያችን ላይ በግድ ለመጫን ሃያሰባት ዓመት ሙሉ ታላቅ ሴራ በእኛው ሰዎች እና በውጪ ኃይሎች ሲሰራ ቆይቷል።
ዛሬም አኩሪ የመተሳሰብ፣የመከባበር እና የመፋቀር ባህላችንን ለማውደም ጥግ ይዘው በማድፈጥ፣የሚተኩሱብን ፣የሚያቆሥሉን እና የሚገድሉን ዛሬም በአራቱም መአዘን እንዳሉ እያሥተዋልን ነው።
የውጪዎቹ፣ ሴረኞች፣ ለዘላቂ ጥቅማቸው ሲሉ ኢትዮጵያውያንን በጎሣ ለመከፋፈል ዶላራቸውን በመበተን ፣በውሥጥ አረበኞቻቸው(ባንዶች)እየታገዙ ፣ትላንት በሻሸመኔ፣በሮቤ፣በዴራ፣በጅማ፣በአጋርፋ ወዘተ የፈፀሙትን ግፍ ፣ዛሬም በመተከል፣በአገው(በአማራ) ነገድ ና ጎሣ ላይ ያለአንዳች ርህራሄ፣በፍፁም አውሬነት ለይ ሆነው ለሰው አእምሮ ፍፁም የሚከብድ ከአውሬ የባሰ ድርጊት ፈፅመዋል ።ክቡሩን ሰው በጠራራ ፀሐይ በጥይትና በቀሥት ረሽነዋል።ይህ ድርጊት ጠላቶቻችን የኢትዮጵያን አንድነት ለመናድ ሲሉ ከወጠኗቸው አያሌ የተጠኑ እና በመርሃ ግብር ከሚፈፀሙ የሽብር ተግባር አንዱ ነበር።እናም በወቅቱ ተፈፅሟል። አሥቀድመን ከኢትዮጵያ ገፀ ምድር እያሰሥን እነዚህን ነፍሰ በላዎች እሥካላጠፋናቸው ጊዜ ድረሥ፣ ነገ ሌላውን ዘግናኝ ድርጊት ለመፈፀም ቀን ቆርጠው ዝግጅታቸውንም ጨርሰው የተቀመጡ ይመሥለኛል።በዛች ባሥቀመጦት ቀን እና ሰዓት ሌላው ሰቅጣጭ ድርጊት ዜና ይሆናል።ከዛም የሚያባራው የጥፋት እቅዳቸው ይቀጥላል ።
እኛ ኢትዮጵያዊያን እነዚህን አገር አውዳሜ ሴረኞች ቁጭ ብለን ማየት አለብን ብዬ በበኩሌ አላምንም። ለዚህም ነው፣በየአቅጣጫው መንግሥት ለአሸባሪነት፣ለለየለት የአውሬ ድርጊት ዘላቂ መፍትሄ እንዲያበጅለት የምንወተውተው።
መንግሥት በተሠጠው ህዝባዊ አደራ መሠረት ተግባራዊ እርምጃ በመውሰድ የህዝብን የፍትህ፣ የሠላምናየሰብአዊ መብት ጥያቄ በተገቢው መንገድ መመለሥ አለበት።ይህንን ጥያቄ በአግባቡ መመለሥ የሚቻለውም፣በመንግሥት ከፍተኛ አመራር ውሥጥ፣የኢትዮጵያን ህዝብ ታሪክ ፣ ባህልና ሥነ ልቡና በውል የሚያውቁ ዜጎች ተገቢ ሥፍራ ሲኖራቸው ነው።
ለዚች ሀገር፣ በጥበብ የደረጁ፣እውቀት የዘለቃቸው፣አመዛዛኝ ህሊናን ገንዘባቸው ያደረጉ፣”ከራሥ በላይ ነፋሥ” የማይሉ፣ የሞራል ልእልና ያላቸው ፣ሰው አፍቃሪ፣ሰው አክባሪ፣ሰውን በቋንቋው ሳይለዩ ከልብ ሚመወዱ፣ሰውን ለሥራ፣ለእድገትና ለብልፅግና አነሳሽ፣ ተገልጋይ ሳይሆኑ አገልጋይ የሆኑ ፣ትሁት ፣የመንግሥት ባለሥልጣናት ከላይ እሥከታች ያሥፈልጓታል።
ለፖለቲካ ሥልጣን የሚወዳደሩ ፖለቲከኞች ና የፖለቲካ ፖርቲዎችም ህዝብን ከህዝብ ጋር በማጋጨት ለማትረፍ ወይም የሀገር መሪ ለመሆን ሌት ተቀን የሚዷልቱ መሆን የለባቸውም።እነዚህ ፀረ ፍቅር፣ፀረ አንድነት፣ፀረ ዴሞክራሲ ፣ፀረ ሠላም እና ፀረ ኢትዮጵያ ናቸውና የፖርቲ ሥያሜ ሊሰጣቸው አይገባም።
እነዚህ በቋንቋእና በነገድ የተደራጁ፣ በዘውግ እና በቋንቋ ፈረሥ ላይ ተቀምጠው ፣ ለግላዊ ጥቅማቸው ዘላቂነት ሲሉ፣ሁሌ ዳንግላሳ እየጋለቡ፣ “ጥለፈው፣ዘርጥጠው፣ጣለው፣በለው!በለው! በለው !” የሚሉ ፣ ባገኙት መድረክ ያለሀፍረት የሚሳደቡ፣ቆዳቸውን የሚያዋድዱ፣ ከአፍ እሥከ አፍንጫ የሚያሥቡ ፖለቲከኞች የዚች ሀገር ሠላም ፀሮች ናቸውና አያሥፈልጉንም።
በተሳዳቢነት፣በቆዳ አዋዳጅነት፣በፍፁም ግብዝነት ጥቂቱ ወጣት እንዲታወር በማድረግ፣በአላዋቂው እና በወጣትነቱ ደሙ በሚተከተከው ወጣት ነግደው ለማትረፍ ዲንጋይ የሚያቀብሉ እነዚህ ናቸውና ለሀገር አይበጁም።…ወጣትን በስድብ የማሠልጠን አሥቀያሚ ባህል የፈጠሩት እነዚህ ግብዝ ፖለቲከኞች መሆናቸውንም አንዘንጋ።
በነገራችን ላይ፣ የሥድብ ችሎታን ማንም ሰው መጎናፀፍ ይችላል። ምክንያቱም ትምህርት ና ጥናት የማያሥፈልገው፣ ማንም ጤነኛ ጆሮ ካለው ከቤተሰብ፣ከአካባቢው፣ከትምህርት ቤት ፣ ከጓረቤቶቻችን እ ከአቻዎቻችን እና ከጓደኞቻችን በቀላሉ የስድብ ችሎታን ማዳበር አይገደንም።
ይህ በእንጭጭ ህሊናችን የተለማመድነው የሥድብ ችሎታ ነው፣ዛሬ ጣርያ ነክቶ እኛም በተራችን ለእቦቀቅላዎቻችን ገና በህፃንነታቸው ሥድብ አሥተምረን በሥድብ ማሥተርሳቸውን የምናጎናፅፋቸው።
ለልጆቻችን የሥድብ ማሥተርሥ ከማጎናፀፍ ይልቅ፣እውነተኛውን የኢትዮጵያን ታሪክ ብናሥተምራቸውና በዛ እንዲመረቁ ብናደርግ መልካም ነበር። ሥለመጋባታችን፣ሥለመዋለዳችን፣ቅልቅል ሥለመሆናችን እና የጠራ ጎሣ በታላላቆቹ ህዝቦች ውሥጥ እንደሌለ ገና ከጠዋቱ ብናሥረዳቸው መልካም ነበር።
ዛሬ፣ዘሬ፣ “ባለጌን ካሣደገ፣የገደለ ፀደቀ” ብሎ ነገር አይሰራም።እንደውም የፅድቅ መንገድ ሥድብ እንደሆነ ሁሉ፣ማንም እየተነሳ በአደባባይ ይሳደባል። ተማረ አልተማረ ፣ምሁር ሆነ ማይም ፣ህፃን ሆነ አዋቂ ፣በቀላሉ ከአፉ ሥድብን ማውጣት አያሳፍረውም።ይሄ ሥድነቱ አይረቤ ነው።ከቶም አያሥከብረውም።
በዚህ አገር የአንድን ሰው እኩይ ሃሳብ የጅምላ ሃሳብ ማድረግ እየተለመደ መጥቷል።ይህ አይራባም።ለሃጫምነት ነው። መሳደብ “ለሃጫምነት” ነው። ይህንን ተሳዳቢዎች ማወቅ አለብን። ብዙዎች አልገባንም እነጂ ፣ ማሥተዋልም ጓድሎናል እንጂ፣ ሥድብ የአፍ ብቻ ሳይሆን “የህሊናም ለሃጭ ነው።
በዚች ሀገር ተሳዳቢ ፖለቲከኞች እና ምንም ሳያውቁ “እናውቃለን!”ባይ የቋንቋ አምላኪዎች እንደ አሸን ፈልተዋል።ከእነዚህ ብዙዎቹ በቋንቋ ምክንያት የፈለጭ ቆራጭነት ወንበር ያገኙትን እና በዚህ ኢ ፍትሃዊ መንገድ በመጓዝም፣ከመሬት ችብቸባ እና በእከክልኝ አክልሃለሁ ሙሥና በጣት በሚቆጠር ዓመት ውሥጥ ፣ባለቪላ ቤት፣ባለቪ 8 እና በሚሊዮን የሚቆጠር ጥሪት በሚሥት፣በእናትና በልጅ ሥም በባንክ ያሥቀመጡትን በማየት ፣እኔሥ ከማን አንሳለሁ?በጎሳ ከሆነ እኔ ከእርሱ የተሻልኩ ነኝ።በምላሥ ከሆነም ከእሱ በብሥ እንጂ አላንሥም፣እናም ለምን የቋንቋ ፖለቲካውን በማግነን እና ይህን ቱጃር የቋንቋ ፖለቲከኛ ከበርቴ በማሳጣት ፣ከሥልጣኑ ገለል እንዲል በማድረግ የሥልጣን ወንበሩን አልይዝም? በማለት፣ህዝብን ፍትህ በማሣጣት ፣በኃይል ተገዢ ብቻ እንዲሆን የሚያደርጉ የተጨበጨበላቸው አሥገዢዎች ባለፉት 27 ዓመታት ተፈጥረው ነበር።
ባለፉት 27 ዓመታት ምሥጉን አሥገዢ ለመሆን ፣በጠልፎ መጣል መንገድ የተራመዱ እና የተሳካላቸው የመንግሥት ባለሥልጣናት ነበሩ።ከ27 ዓመት በኋላ ብዙዎቹ ከሥልጣን ተገለዋል።የዘረፉትን ይዘው በሰላም እንዲኖሩ ተፈቅዶላቸዋል።በእነሱ ምትክም ከቀበሌ ጀምሮ አዳዲስ የብልፅግና ፖርቲ አባላት ተተክተዋል።ቢተኩም ጥቂት የማይባሉት ግን ዛሬም በአብዮታዊ ዴሞክራሲ መንገድ እንደሚሄዱ ና ለግለሰብ መብት ቁብ እንደሌላቸው እያየን ነው።
እርግጥ ነው፣በለውጥ ላይ ያለ መንግሥት፣ በአንድ ቀን ጀንበር የአብዮታዊ ዴሞክራሲ የአንድ ለአምሥትን ጥርነፋ፣ግምግማ እና “ ለውጡ የመጣባቸውና የመጣልን “ እያሉ ፣በአፍ ካራቴ ሽወዳን ፣በዴሞክራሲያዊ አሥተሳሰብና ተጠያቂነት ባለው አሠራር መተካት አይቻልም።ይህ እውነት በመሆኑ፣ ዛሬም የ”ሀ ” ን መብት ነጥቀህ ለ “ለ” ትሠጣለህ።”ሀ”በ”ለ” ክልል ነፃነት እና መብት እንዳይኖረው ቋንቋን ማግለያ ታደርጋለህ።
“ሀ” “ለ” በሌለበት ተሠብሥቦ የወሰነውን በግድ እንዲቀበል ይደረጋል።ወይም “ሀ” የህብረተሰብ ወኪሎችን ሰብሥቦ ሲያወያይ ፣እርሱ ያመነበት ብቻ፣የውሳኔ ሃሰብ ይሆናል።በተቀናጀ ድርጅታዊ አሠራር በቀቀኖች እንዲናገሩ እድል ይሰጣቸውና የካድሬው ሃሳብ የህዝብ ሃሳብ ይሆናል።ትላንትም የሚደረገው ይኸው ነው።”ሀ” በክልሉ በቋንቋው እያመካኘ እሥከ ፐ ያሉትን የተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪዎችን ይጨቁናል።በጉቦ ያሰቃያል።ፍትህና ርእትህን ያጓድላል።ፖለቲካዊ፣ህጋዊ፣ግለሰባዊ እና ተቋማዊ ነፃነት እንዳይኖሩ ያደርጋል።የሁሉም ነገር ሰጪና ነሺ የፖርቲ አባሉ ወይም የቀበሌው ሥራ አሥፈፃሚ ይሆናል።
ዛሬም ይህ የሶሻሊዝም ችካል አልተነቀለም።በአቀባይ እና አቀባባይ ከበርቴ፣በፈውዶ ቡርዣ እና ቡርዧ፣በጨቋኝና ተጨቋኝ መደብ ተከፋፍሎ ሲወገዝ የነበረው ሥርዓት በኢህአዴግም ሥሙን ቀይሮ ቡድናዊነትን በማንገሥ፣ወደ ክልል ቋንቋዊ አደረጃጀት ፣ የጎሳ፣የዘውግ፣የጎጥ ና የወንዝ ሥርአተ ሶሻሊዝም ተሸጋግሯል።
ዛሬም ከቀበሌ ጀምሮ ያለው አሠራር ያው ነው።ገዢዎቹ እንደልባቸው እንዲቦርቁ እና በሰው መብት ላይ እንዲፈነጩ እና ተገዢዎቹ የተጫናቸው ቀምበር እንዳይወልቅ” በልዩ ኃይል” አጥብቀው ያሲዛሉ። “ሰውዬ ውልፍት ትልና ዘብጥያ ትወርዳለህ። ይልቁንሥ አርፈህ ፀጥ፣ለጥ፣ብለህ ተገዛ።” ይሉሃል።(ለዚህ ነው ልዩ ኃይል የተባለው ሠራዊት ወደ ፊደራሉ የመከላከያ ሠራዊት ይጠቃለል የምንለው።)
እንዴት ነው፣የደርግ ሥርአትን እና የወያኔ /ኢህአዴግ ሥርዓትን በቅጡ ያየ ፣የነቃ ዜጋ ወይም ሰው ፀጥ፣ለጥ ብሎ የሚገዛው?ያውም በቴክኖሎጂ አማካኝነት እውቀት ቤቱ ድረሥ በመጣበት በዚህ ዘመነኛ ክ/ዘመን።
በዚህ በዘመነኛ 21ኛ ክ/ዘመን አጭበርባሪ ፖለቲከኞች፣ ከ44 ዓመት በፊት የተወገደውን የፊውዳል ሥርዓት እና የነፍጠኝነት ትርጓሜ ፣ዛሬ የአማራ ና የኦሮሞን ጎሣ ለመከፋፈል ፣ለማቃረን እና ለማጣላት እየተጠቀሙበት እንዳሉ ሥንቶቻችን ታዝበናል?
ዛሬ፣ በየመንግሥት መሥሪያ ቤቱ ሚጢጢ ሥልጣን ያለው ፣የዛን ክልል ቋንቋ የማይናገር ወይም አማራ ከሆነ “ነፍጠኛ” የሚል የተሳሳተ ትርክትን ያነገበ ሥም የሚሰጡ እንደ አሸን ፈልተዋል።በዲሢፕሊን ግድፈት ሲጠየቅ እኔ የዚህ ብሔር ሥለሆንኩ አሢረውብኝ ነው እንጂ ያጠፋሁት ምንም ጥፋት የለም።ባዩ በዝቷል።
ይህ ከፍተኛ የሞራል ዝቅጠትን የሚያመለክት ከመሆኑም ባሻገር ፖለቲካው “ የመከባበር እና የእውነተኝነትን ባህል’ ክፉኛ እየሸረሸረው መሆኑን ያመለክታል።የሞራል ዝቅጠቱ በፊደራል መንግሥት በሚመሩ ፣የበዙ ኦሮምኛ እና አማረኛ አቀላጥፈው በሚናገሩ ሠራተኞች በበዙበት፣አንድ አማርኛ ተናጋሪ ከፍተኛ ሥልጣን ቢሠጠው፣ጥቂት የማይበሉት የዛ መሥራ ቤት የኦሮምኛ ተናገሪዎች “ነፍጠኛ አይመራንም።” በማለት ነገ ተነገወዲያ ሠላማዊ ሠልፍ እንደሚወጡ አመላካች ነው።
እንዲህ ዓይነቱን ዝቅጠት የሚያመለክቱ ብልጭታዎች አሉ።ይህ ብልጭታ የሚያመለክተው፣ከቱባው አኩሪ ና ድንቅ ባህላችን ምን ያህል ወረድን መገኘታችንን ብቻ ሳይሆን በቋንቋ አምላኪነት ሰበብ የላቀ እውቀትና ብቃት ሥፍራ እንዳይኖራቸው በማድረግ ሀገሪቱ ቁልቁል እንድትጓዝ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የበኩላችንን እኩይ እገዛ በማድረግ ላይ እንዳለን ነው የሚያሣብቀው።ሰው ሰው መሆኑን በመረዳት ፣ተከባብሮ በህግ አግባብ መኖር እኮየሥልጣኔ መገለጫ ነው።ሰውን በቋንቋው የማይመዝኑ፣በችሎታውና በእውቀቱ ሠርቶ እንዲበላ የሚፈቅዱ ሀገሮች ምን ያህል በሥልጣኔ እንደተራመዱ ማሥተዋልም መልካም ነው።ይህንን እውነት አሥተውሎ በፍቅር እጅ ለእጅ ተያይዞ በመሥራት መበልፀግም የሰው ተግባር ነው።
ሰው ፣ሰው መሆኑን ማወቅ ከተሳነው፣ወደ አውሬነት ተቀይሮ የአውሬነት ተግባር ሳያፍር መፈፀሙ አይቀሬ ነው።
ትላንት ሰው፣ሰው መሆንን ክዶ ዘግናኝ የአራዊት ተግባር ፈፅሟል። ይህ እኩይ ድርጊት የተፈፀመውም፣ከራሥ በላይ ነፋሥ በሚሉ ሥግብግብ ሰዎች አማካኝነት ነው።
ቋንቋም ተመላኪ የሆነው፣ከላይ እንደጠቆምኩት ሳይለፉ፣ሳይወጡና ሳይወርዱ አልጋ ላይ ተኝተው፣በሀብት ላይ ሀብት የተጎናፀፉትን በመመልከት ነው።
ይህንን ያየ የነገ ተሥፈኛ ፖለቲካውን በመንግሥት ውሥጥ በማሥረግ፣”በክልሌ አዛዥ፣ናዛዥ፣ፈላጭና ቆራጭ እኔ መሆን አለብኝ ።” ብሎ ቢነሣ ምን ያሥገርማል?…ሥርዓተ ዓለበኝነትን የሚቆጣጠር በፖለቲካ ወገንተኝነት ያልተጠረነፈ ፣ሰው መሆኑንን ከልቡ የተረዳ የመንግሥት ባለሥልጣን ከላይ እሥከታች እሥከሌለ ጊዜ ድረሥ በቋንቋ ፖለቲካ ሥም የሚርመሰመሱ አትራፊ ነጋዴዎች ና አራዊቶች ይህቺን ሀገር ወደ ማጥ ሊከቷት ይችላሉ።
እነዚህ ሰዎች እኮ “ብቸኛው በአቋራጭ የመክበርያ መንገድ አህአዴግ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ያዋቀረው ቋንቋን መሠረት ያደረገ ክልልነት ነው። “ብለው የሚያምኑ ናቸው።ክልልነትንም እንደ አንድ ሉአላዊ ሀገር ይመለከታሉ።ሌሎች ቋንቋዎችን ያገላሉ።ይሰድባሉ። ፣ይጠየፋሉ፣ይጠሉማል።
በእውነቱ ሰው ከሰው ተራ ወርዶ እንደሚጠፉ እንሥሦች መሆኑ ያሳዝናል።አንድ ሰው አማራ ነኝ ብሎ ኦሮሞን ቢጠላ እኮ የጠላው የራሱን ሰውነት ነው።አማራ ከኦሮሞ፣ትግሬ፣ከወላይታ፤ሱማሌ፣ከአፋር፤ቤንሻጉል፣ከጋምቤላ፣ሐረሪ፣ከሲዳማ ፣ሸካ ከዳውሮ፣ጉምዝ ፣ከየም፣ዳሰነች፣ከኮንሶ ወዘተ።በሰውነቱ አፈጣጠር ምኑ ላይ ይለያል? የአማራ ጥቁር የለም?የኦሮሞ ፀጉረ ከርዳዳ የለም?የትግሬ አፍንጫው ሰፋ ያለ የለም?የሱማሌ አጭር የለም?የሲዳማ ቀጭን የለም?የሐረሬ ፉንጋ የለም?የጋምቤላ ኮሳሳ የለም?…ሰዎች አትሳቱ ኃይማኖታችን እንደየግላችን ይሁንና የሰው ዲ ኤን ኤ ከዝንጀሮ ዲኤን ጋር በ98% ተመሳሳይ ነው።አንዳንዱ በአካሄዱ እና በመልኩ ፣አንዳንዱ ደግሞ በበሃሪው ከዝንጀሮ ጋር ቢመሣሠል የሚያሥገርም አይሆንም።ይሁን እንጂ ለሁሉም ነገር ሥርዓት እንዳለው ሰው ያውቅ ዘንድ መንግሥት የተባለው የሰው ሥብሥብ ሰው መሆኑን በተግባር ማሥመሥከር አለበት።
የለውጡ መንግሥት(አሻጋሪው የብልፅግና ፖርቲ) የሰው ሥብሥብ መሆኑ የሚመሠከርለት ሥርዓቱን በገዢ፣በአሠገዢና በተገዢ ያለማዋቀሩን በተግባር ሲያረጋግጥ ብቻ ነው።ደርግ በሶሻሊዝም ጊዜ በእኩልነት ሥም የግለሰቦችን መብት ለመጨፍለቅ የፈጠራቸው፣ ከቀበሌ የሚጀምሩ ጠርናፊ መዋቅሮች ፣በዘመናዊ ሲቪል አሥተዳደራዊ መዋቅር ሲተኩ ብቻ ነው።
የብልፅግና ፖርቲ የሥም የመተዳደሪያ እና አንድ አንድ የፖሊሥ ለውጥ አደረገ እንጂ አብዛኛው አባሉ የቀድሞው ኢህአዴግ ነው።ምናልባትም የበዛው የብልፅግናን እጅ ለእጅ በፍቅር ተያይዞ ጉዞ እና ሠርቶ መበልፀግ በቅጡ አልገባውም። እሥከዛሬ በአእምሮው የነገሠው በአቋራጭ የመክበር መንገድ ነው።የበዛው አባል የብዝበዛ መንገድን ከሚመርጠው የቀድሞው ህወሃት /ኢህአዴግ ሥልት የተላቀቀ አይመስልም ።
ይህ የህወሓት /ኢህአዴግ የአገዛዝ ሥልት የህዝብን አንድነት የማያጠናክር ፣ቆዳን በማዋደድ ብቻ እንጀራን የሚያሥገኝ ነበር።
ሥርአቱ አንተ ኦሮሞ፣አንተ አማራ(ነፍጠኛ)፣ አንተ ትግሬ፣አንተ ሲዳማ፣አንተ ወላይታ፣አንተ ጋምቤላ፣አንተ ቤንሻንጉል፣አንተ ጉራጌ፣አንተ ሱማሌ፣አንተ ሐረሪ፣አንተ ከንባታ፣አንተ ሃድያ፣አንተ ኮንሶ፣አንተ ሥልጤ፣አንተ ዳሰነች፣አንተ…በማለት በቋንቋ ከፋፍሎ ሰውነትን አሥክዶ እሥከመጠፋፋት የሚያደርሥ መርዝ የረጨ ሥርአት ነው።ህብረትን፣ፍቅርን፣አንድነትን ከውሥጣችን አሶግደን ጥላቻን እንድናነግሥ በብርቱ የሚጎተጉት ነበር።
ይህን የነገድ ና የጎሣ ፖለቲካ አልቀበርነውም።ዛሬም የነፃ አውጪ ፖርቲዎች አሉን።ቋንቋን እንጂ ሰውን በነፃነት፣በእኩልነት፣በመከባበር፣በመዋደድ፣በፍቅር ፣እንዲኖር የማይፈልጉ። አሥማሚ ና በአንድ አሥማምቶ ነዋሪ ባህላቸውን ዘንግተው፣ሠርክ ለራሳቸው ምቾትና ድሎት ሲሉ ብቻ የሰዎች ሥቃይ እንዳያባራ ከውጪ ኃይሎች ጋር በጣምራ የሚሰሩ።ጎዳና ለወደቀው፣በሥቃይ እና በእንግልት ላይ ታች እየባዘነች እና እየባዘነ ላለ ምንዱባን የቋንቋቸው ተናጋሪ ደንታ የሌላቸው፣ሙቅ አኛኪዎች፣ የቋንቋ ተቆርቆሪ ነኝ ብለው ግን የሚያላዝኑ የአዞ እንባ አንቢዎች ዛሬም ፖርቲ መሥርተው አንድ ጎሣን ና ቋንቋን ነፃ አውጪ ነን ይሉናል ።በእውነት እንነጋገር ቢባል ከቋንቋ ይልቅ ሰው አይበልጥም?ማሥቀደም ያለብን ደሃ ወገናችን ሁሉ ከድህነት እንዲወጣ በገንዘብ፣በጉልበት እና በእውቀት መርዳት ሆኖ ሳለ፣እኛ ሰው ገድለን፣ዘርፈን ፣በሰው ደም ዘላለም ዓለማችንን እጃችን እየታጠብን መኖር ፈጣሪሥ ይፈቅድልናልን?…(ሰውን ከናቅነው ማለቴ ነው።)