አጼ ምኒሊክ ለሩሲያው ንጉሥ ኒኮላይ ሁለተኛ ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት እ.ኤ.አ በ1897 የመጀመሪያዎቹ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ወደ ሩሲያ መጥተው እንዲሰለጥኑ ተደርጓል፡

በአድዋ ጦርነት ወቅት ለአገራችን የሕክምና እርዳታ ሲሰጡ የነበሩ ሩሲያውያን ሀኪሞች ወደ አገራቸው ሲመለሱ አምስት ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች አብረዋቸው ወደ ሴንትፒተርስበርግ ከተማ መጡ፡፡ የተማሪዎቹ ስም ዝርዝርና እድሜያቸው እንደሚከተለው ነው፡-
1. ገኑ አራዶ – እድሜ 20 ዓመት
2. ዳኜ ቸርነት – እድሜ 20 ዓመት
3. ሰሙንጉስ ወልደሚካኤል – እድሜ 19 ዓመት
4. ግዛው ወልደመስቀል – እድሜ 18 ዓመት
5. ክብረት ማሩ – እድሜ 17 ዓመት
ተማሪዎቹ ከአገራቸው ሲመጡ በመንግሥት የተሰጣቸው ገንዘብ ከትራንስፖርት ወጪ ያልበለጠ በመሆኑ የገንዘብ እጥረት አጋጥሟቸው ስለነበር በሊጐቨድስኮይ ሠፈር በሚገኘው የጀነራል ሊቬደቭ ቤት ለተወሰነ ጊዜ ኖረዋል፡፡ አምስቱም ከኦርቶዶክስ ቤተክህነት ትምህርት በቀር ዘመናዊ ትምሕርት ስላልነበራቸው እና ከአማርኛ ውጭ ሌላ የአውሮፓ ቋንቋ ስለማያውቁ እንዲሁም በዘመኑ ሩስኪኛ አማርኛ መዝገበ ቃላትም ሆነ ለአፍሪካውያን የሩሲያ ቋንቋ ማስተማርያ ዘዴ ስላልነበር ችግር አጋጥሞ ነበር፡፡
ተማሪዎቹ በሁለት ዓይነት የትምሕርት መስክ ማለትም በሕክምና እና በእደ ጥበብ ትምሕርት እንዲመደቡ በመደረጉ፡- ግዛው ወልደመስቀል፡ ክብረት ማሩ እና ዳኜ ቸርነት በወታደራዊ ሕክምና ረዳትነት፤ ገኑ አራዶ እና ሰሙንጉስ ወልደሚካኤል በእደ ጥበብ ትምሕርት ቤት እንዲገቡ ተደረገ፡፡ የእደ ጥበብ ትምሕርት ቤት የሚቀበለው እድሜያቸው ከ12 እስከ 15 አመት የሚሆናቸውንና የመግቢያ ፈተናውን ያለፉትን ብቻ በመሆኑ ለገኑ እና ሰሙንጉስ የት/ቤቱን መሥፈርት ማሟላት አዳጋች ነበር፡፡ በመሆኑም ሁለቱን ብቻ የሚያስተምሩ ልዩ መምህራን ለመመደብ ቢታሰብም የገንዘብ እጥረት ስላጋጠመ የንጉስ ኒኮላይ ሁለተኛ ልዩ ፍቃድ በማስፈለጉ፤ አኘሪል 6/1898 የገንዘብ ሚኒስትሩ ሰርጌ ዊቲ ለንጉሱ በፃፋት ደብዳቤ ለተማሪዎቹ ተጨማሪ በጀት እንዲፈቀድ ጠይቀው ነበር፡፡ ንጉሱም ለገኑና ለሰሙንጉስ ለእያንዳንዳቸው ማስተማሪያ በአመት 250 ሩብል እንዲሁም ለልዩ ልዩ ወጪዎች ለአመት 1200 ሩብል ከመንግሥት ካዝና ወጪ እንዲደረግ ፈቀዱ፡፡
የት/ቤቱ ዳይሬክተር ተማሪዎቹ የሴንትፒተርቡርግ ከተማን ለመላመድ ከብዷቸው እንደነበር የሚገልጽ ደብዳቤ ጽፈዋል፡፡ ተማሪ ገኑም በአገሩና በቤተሰቡ ናፍቆት ሳቢያ ለስድስት ወራት በመታመሙና ሀኪሞች የጤንነቱ ሁኔታ የመሻሻል ምልክት ካላሳየ በሩሲያ መቆየቱ የበለጠ እንደሚያብስበት ስለገለፁ ወደ ትውልድ አገሩ እንዲመለስ ተወሰነ፡፡ የጤንነቱ ሁኔታ ለብቻው ወደ አገሩ እንዲመለስ ስላልፈቀደ ከአርኖልድ ሪጅመንት አባል ጋር በመርከብ አብሮ እንዲመለስ ተወሰነ፡፡ ት/ቤቱም የገኑን እና የሪጅመንት አባሉን የትራንስፖርት ወጪ የሴንትፒተርበርግ ከተማ ነጋዴና ባለሀብት ከሆኑት ከዩሶብ በብድር ወሰደ፤ በቀጣይም ለገኑ የወጣውን የትራንስፖርት ወጪ አጼ ምኒሊክ እንዲተኩ አዲስ አበባ በሚገኘው የሩሲያ ሚሲዮን አማካይነት እንዲጠየቅ ተደረገ፡፡
በሴንትፒተርስበርግ ከተማ ትምሕርታቸውን የተከታተሉት ሁለቱ ተማሪዎች የተመደቡበትን የሕክምና ረዳትነት ትምህርት ስላጠናቀቁ ለአንድ አመት ወደ ኦዴሳ ወታደራዊ ሆስፒታል ተዛውረው ልምምድ እንዲያደርጉ የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ወዳጅ ለሆኑት ለሚስተር አርሎብ ጁን 26 ቀን 1901 በፃፈው ደብዳቤ መመሪያ ሰጥቶ ነበር፡፡ እቴጌ ጣይቱና አጼ ምኒሊክ ግን ተማሪዎቹ ወደ ኦዴሳ መዛወራቸው ስላላስደሰታቸውና የአየር ፀባይ ለውጥ በጤናቸው ላይ ጫና ሊያሳድር ይችላል በሚል ስጋት ውሣኔውን ሳይቀበሉ ስለቀሩ የተግባር ልምምድ ሳያደርጉ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ ተወሰነ፡፡
በእደጥበብ ዘርፍ የተመደበው ተማሪ ሰሙንጉስ በተለያዩ የትምሕርት አይነቶች የጽሁፍና የቃል ፈተና እንዲሁም በሙያዊ የተግባር ትምሕርት ጥሩ ውጤት አግኝቷል፡፡ የትምሕርት ቤቱ አስተዳደርና መምህራን ሰሙንጉስ ወደ አገሩ ሲመለስ ወርክ ሾኘና ለሙያው የሚሆኑ ቁሳቁሶች ላያገኝ ይችላል በሚል ሥጋት የሥራ መሣሪያዎችን በስጦታ ሰጡት፡፡ ሰሙ ንጉስ ወደ አገሩ ከተመለሰ በኋላ እንዴት እንደኖረ የሚገልጽ መረጃ የለም፡፡ ግዛው በምንሊክ ሆስፒታል ተመድቦ ይሰራ ነበር፡፡ ገኑ ትምሕርቱን ባያጠናቅቅም ወደ አገሩ ከተመለሰ በኋላ በሩሲያ የቀይ መስቀል ሆስፒታል /በባልቻ ሆስፒታል/ በሩሲያ ቋንቋ በአስተርጓሚነት ይሰራ እንደነበርና የአጼ ምኒሊክ ልኡክ ወደ ሩሲያ በመጣበት ወቅት በአባልነት እንደመጣ ተጽፋል፡፡ /ተፃፈ በቀለመወርቅ ፀሀዬ ወልደልኡል – ከሞስኮ
Source; НЕГОСУДАРСТВЕННЫЕ ФАКТОРЫ МЕЖДУНАРОДНЫХ ОТНОШЕНИЙ,Микаэль Н.
የሀኪም ዳኜ የልጅ ልጅ ልጅ ጀርመን ኦግስበርግ ከተማ እንደሚኖር መረጃ አግኝቼ ነበር እስካሁን ግን አላገኘሁትም፡፡ ፎቶግራፋ የአምስቱ ተማሪዎች ሳይሆን የሶብዬት ሕብረት ተማሪዎች በሚል ከኢንተርኔት ላይ ያገኘሁት ነው፡፡
ተጨማሪ ያንብቡ:  አብይ አህመድ የስድስተኛ ክፍል ደረጃ ሙህር ዶ/ር ለካቢኔው የሰጠው ሁለተኛው ፈተና

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share