ደም በስብከት አጥቦ ሟችን እሚረሳው፣
አቢይ ጉድጓድ ሲምስ ዝምሎ እሚከተለው፣
በጅ የማይጨበጥ ሰውነት ውሀ ነው፡፡
ሲክብ እንደ ደለል ሲያፈርስም እንደ ጎርፍ፣
ሰውነት ውሀ ነው ቦይ ሲያገኝ እሚፈስ፡፡
በስድስተኛው ቀን መለኮት ሲፈጥረው፣
ቀጥ ብሎ እንዲሄድ ከአፈር ቢያበጃጀው፣
ትዕዛዙን አፍርሶ እጥፍ ዘርጋ እሚለው፣
ቦይ ባየበት ፈሳሽ ሰውነት ውሀ ነው፡፡
የግሪኩ ጠቢብ ቴልስ እንዳስተማረው፣
የገላ ይዘቱ ሰውነት ውሀ ነው፡፡
የጦቢያ ሊቃውንት ጥንት እንደጠበቡት፣
ገላ የተሰራው ከውሀ አፈር እሳት፡፡
ሳይንስ በምርምር እንዳረጋገጠው፣
ሰባ በመቶውን ሰውነት ውሀ ነው፡፡
አስተዋይ ተመልካች እንደሚታዘበው፣
ስግብግቡን ገላ ሰውነት የሞላው፣
ቦይ ሲቀደድለት እሚፈስ ውሀ ነው፡፡
ቀና ብሎ ሲሄድ ጠጣር መስሎ ታይቶን፣
ሰው ፈሳሽ መሆኑን ደጋግመን ዘነጋን፡፡
ቀጥ ብሎ እሚቆም ግማዴ መስቀሉ፣
ጥምዝ እሚዞር ግን ፈሳሽ ሰውነቱ፡፡
ቀለም ብታጠጣው እውቀት ብትመግበው፣
መውረዱን አይተውም ሰውነት ውሀ ነው፡፡
ቆብም ብትደፋበት ዲግሪም ብትጪነው፣
መፍሰሱን አይተውም ሰውነት ውሀ ነው፡፡
እንደ ንጋት ጤዛ እማይቆይ በቦታው፣
ሰውነት አልፎ ሐጅ የበጋ ዝናብ ነው፡፡
አዞ እሚዋኝበት ዘንዶም እሚውጠው፣
እንደ ወንዝ የሚወርድ ሰውነት ውሀ ነው፡፡
አሳማው አህያው ረግጦ እሚጠጣው፣
ፋንድያ መጣያ ሰውነት ውሀ ነው፡፡
አተላው አዛባው ቢገባ ቆሻሻው፣
እስከ ሞላ ድረስ ደንታ የማይሰጠው፣
መዋጥን የሚወድ ሰውነት ውሀ ነው፡፡
በአንኮላ በጣሳ በቅል እሚዛቀው፣
በቧንቧ በቱቦ ተስቦ እሚጠጣው፣
ክብሩን ጥሎ እሚኖር ሰውነት ውሀ ነው፡፡
ወቅት እየጠበቀ እሚጥለቀለቀው፣
ወረት የሚነዳው ሰውነት ውሀ ነው፡፡
ተስቦ በሆዱ ሲጓዝ እሚውለው፣
እንደ መስኖ ወራጅ ሰውነት ውሀ ነው፡፡
የነፋስ ሽውታ የሚያንቀሳቅሰው፣
እንደ ሰፌድ እህል እሚያንገዋለለው፣
በእጅ የማይጨበጥ ሰውነት ውሀ ነው፡፡
ከፍጥረት ከፍ አርጎ ባምሳሉ ቢፈጥረው፣
በለሱን ጠሽቅሞ መሬት የወረደው፣
እመሬት ላይ ወርዶም በሆዱ እሚሳባው፣
እንደ ጎርፍ እሚፈስ ሰውነት ውሀ ነው፣
እንኳንም አላፊ ተጓዥ አደረገው፡፡
በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)
መጀመርያ ሚያዚያ ሁለት ሺ አሥር ዓ.ም.
እንደገና ነሐሴ ሁለት ሺ አስራ ሁለት ዓ.ም.