ዝምታ ወርቅ አይደለም – ከአባዊርቱ!

መግቢያ!

የተከበሩ ልኡል ራስ መንገሻ ስዩም ለኢትዮጵያ ብዙ ውለታ የዋሉ ፣ ስመጥርና ምሁር የሆኑ የትግራይ ተወላጅ ፍፁም ኢትዬጵያዊ ናቸው። የ ሀያሰባቱ አመት ይቅርና ከሁለት አመት ለውጥ እድሜ በሁዋላ እንኳ በአንዳንድ ጉዳይ እንደምን እንዳስቻላቸው ግራ ይገባኛል። እነዚህ ፅልመቶች መቼስ ከማርስ አይደለም የፈለቁት ከትግራይ እንጅ። በትግራዋይ ስም ይህ ሁሉ ግፍ ሲፈፀም ትግራይ የኢትዮጵያችን አፅመእርስት እንዳልሆነች ነገር ሌላው ጥቅመኛና ባለጊዜ እንኳ ቢቀር የልኡልነታቸው አይነቱ የታሪክ ማህደር ዝምታ በበኩሌ እጅጉን አሳዝኖኛል። በተለይም ስለ መልካም ማንነታቸውም ስለማውቅ። እነ ህውሀት ወልቃይትን፣ የቤገምድርና ሰሜንን ግዛት በትግራይ ታሪክና በሳቸውና በአባታቸው እርስት የማይታወቁትን እየጠቀለሉና ከአማሮቹ ደም እያቃቡን እየሰሙ እንደምን አስቻላቸው ያሰኛል በውነቱ።

ውድ ኢትዮጵያውያን/ውያት ወገኖች!

አባቶቻችን ወረራን በደምና አጥንቶቻቸው በመከላከል ያቆዩልንን ሀገር እኛ በዝምታ ገመድ ተሸብበን አሳልፈን ልንሰጥ ነው። ፅልመቶቹ 24/7 ሀገር ለማፈራረስ ሳይታክቱ ይሰራሉ – እያንዳንዳችን ግን ምን አስተዋፅኦ እያደረግን ነው ብለን እንጠይቃለን? አቢይ መለኮታዊ ሀይል የለውም:: ለአቢይም ብሎ ነገር የለም:: አቢይ ማለት የሁላችንም ልብና አይምሮ በኢትዮጵያዊነት የመደመር እሳቤ ቤተሙከራ ነው። ስለሆነም ይህ ቅንና ወጣት መሪ በስራ ሂደት ላይ ያለ የሀገር ህዳሴ ችቦ እንጅ ሌላ አይደለም:: የአቢይ ህልውና የመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ድጋፍ ባይኖረውና በጉልበት ብቻ ቢሆን ኖሮ ወያኔና ቅልቦቹ በዚህ 2 አመታት ያወርዱት ነበር::

የአቢይ ሀይል ህዝብ ነው:: ይህ ደግሞ ከማንም ሰራዊት ጥንካሬ በላይ ነው:: እንዲህ አይነቱን የህዝብ ቅቡልነት እንኳንስ በፍራቻና በመገደድ የታጠቀ የሜርስነሪ ሚሊሻ ቀርቶ የነቡከደነፆር አይነትም ሰራዊት አይደፍረውም። ለምን? ከመደበኛ ሰራዊት ሌላ ለአቢይ ዛሬ በሁሉም የኢትዮጵያ ክልል የሚቆም እጅግ ብዙ ሚሊዮን ህዝብ አለ:: ህውሀትም የሰሜን ኮሪያን የመሰለ ወታደራዊ ሰልፍ እያደረገ በጎን ደግሞ ጫማ ለመሳም የሚያደርገው እሩጫም አቢቹን አጥብቆ ስለሚፈራም ነው:: ፍራቻውም ህዝብ ከጀርባው እንዳለ ስለሚያውቁ ነው:: በትግራይም ያለው ህዝብ ከአቢይ ጋር እንደሆነ ልቦናቸው በደንብ ይነግራቸዋል። ለህዝብ በይፋ ያልተገለጠው ወያኔ አፍኖ በቤተሰባዊ ዲነስቲ ቀፍድዶ ስለያዛቸው ብቻ ነው። አራት ነጥብ እስከሰረዙ።

ወገኖች!

የዶር አቢይ አንድነት ፓርክን የሚያሳይ ቪዲዮ ከተለቀቀ በሁዋላ ለእውነተኛ የኢትዮጵያ ልጆች ኩራትና የዚህን ወጣት መሪ ፍፁም ብቃት ያየንበትና የከሀድያንን ክፉ በትርም የተቃመስንበትም በመሆኑ ለፈጣሪ ክብር ይግባው። የዚች አጭር መጣጥፍ አላማ ከሀድያንን ስለ ማውገዝ ሳይሆን እንዴት ሀገር ወዳድ ተብዬዎች (በማንም ስሌት የብዙሀንን ቁጥር የያዛችሁ) ዛሬም እንደትላንቱ ሁሉን ነገር በዝምታ ልናልፈው ነው? አሁንለታ መረረኝና ከንግዲህስ እራሴን ላሰናብት ብዬ፣ መልሼ ደግሞ ለማን አባቱ ብዬ አሰኘኝ። እንዴትስ ያስችላል? ለውጥ ላላመጣ ለምን ጉልበቴን ፣ ጊዜዬን አባክናለሁ ከሆነ መልሱ የአሜሪካንን፣ የህውሀትን ዲጂታሎች፣ የአክራሪያንን ተጋድሎ እዩልኝማ። የዘመናችን ጦርነት እየተካሄደ ያለው በሚዲያ እኮ ነው ወገኖች። ብርሀነመስቀል አበበ ሰኚ በሚዲያም አልነበር ከአሜሪካ የፅልመት ወታደሮቹን ያዝ የነበረው? ያስ ዳውላ ጁዋር በአንዲት ለሊት አልነበረም በፌስቡክ ጥሪ ለዛ ሁሉ ሁከት የበቃነው? የሩስኪና የትራምፕን የአየርባየር ጫወታና የ ምርጫ 2016ን ውጤት መካድ ይቻላል? ህውሀትስ ሲፈልጋት እንደ ማደጎ ልጆቿ ስትቀናጣም እንደፌዴራሌ አጋር ወንድሞቿ ምድረ አክራሪን በላያችን እንደ ተመች ለቃብን የምታጋድለን በየክፍላተ ሀገሩ እየዞራች ሳይሆን ከሞቀ መቀሌ ሆቴል አይደል እንዴ የምትዘውራቸው? ይህ ሁሉ ሲሆን ወገን ተብዬ ምንድነው የሚያደርገው? በዝምታ ናላው ዞሮ ነው የምታገኙት። ወቀሳ መፍትሄ ስለማይሆን ከዚህ አዙሪት እንዴት መውጣት እንዳለበት መፍትሄ ያልኳቸውን ልጠቁም እስቲ

፩) ወገንን በስፋት የሚያገለግሉትን እነ ዘሀበሻን የመሳሰሉ ሚዲያዎች ላይ በስፋት የሚፈነጩት (በየኮሜንቱ) የዲጂታል መናፍስት ናቸው። ሁለት ሶስት ከሀድያንን ካያችሁ አስራሁለት/አስራሶስት አገር ወዳድ ሆናችሁ የመናፍስት ልቅላቂያቸውን በፖዚቲቭ ፍሊት መርጨት። ለምን ይጠቅማል? አለመታደል ሆኖ ወያኔ የአንድ ትውልድ የማሰቢያ አይምሮ ስለገደለብን ቶሎ ቀልቦ ክፋታቸውን አየር ላይ አስጥቶ በተገቢው ፀበል መርጨት – በሀቀኛውና ያልተበረዘው እውነተኛው ፀበል።

፪) ታዋቂ ኢትዮጵያውያን /ውያት ዝም አትበሉ። ተናገሩ፣ ተፃፃፉ። አገሪቱ የሁላችንንም አስተዋፅዖ ትፈልጋለች። ሁሉም የበኩሉን ይለግስ። የቡናዋን መዋጮ ይሁን የአባይን አስታዋሽ አለመፈለግ። ሌላው ቢቀር ከሱማሌዎችና ኤርትራውያን ወንድሞቻችን እስቲ እንማር። ሲያወጡና ሲያዋጡ ግራ እጅ ቀኙን እንኳ አይመለከትም። የዜግነትን ልክ በቅጡ የተረዱ ይመስሉኛል በኔ ግምት ። እኝ አንድ ዶላር ከወረወርን የአቢይን የእራት ሜኑ ያህል ፕላን ይከጅለናል። ደግሞ ሁላችንንም እንዳይደለ ይሰመርበት – ብዙ የሚብከነከኑ ወገኖች አሉንና።

፫) የዝምታችንን መውረድ ማሳያ ምሳሌ ልስጣችሁ። አንድ ዩቀድሞ ወያኔ ሰውዬ የነ ቱባ ወያኔ አንድ ቤተሰብን አስከፊነትና የብዙ አመታት ከጅምሩ አንስቶ እንዴት የገዛ ወገኖቻቸውን በተለይ የተማሩትን እየቀረጠፉ እንደመጡ ይተርኩልናል። መቼስ ኢትዮጵያዊ ሆኖ ተፈጥሮ ይህን ሰምቶ የማያዝን አይኖርም ። ፍሬ ነገሩ ግን ይህ አይደለም። ይህ አይነት የሰቆቃ ታሪክ እንዲህ ደምቆ ሌላው ቢቀር በጥቁርነት የሚያሸማቅቅን ታሪክ ከመስማት በትላንትናው ቪዲዮ ላይ ተመርኩዘን እንደምን አገራችንን ወደፊት በይበልጥ እንደምናስፈነጥራት ሁላችንም ዝምታችንን ብንሰብር ወያኔ ትሁን በ ሰላሳ ምናምን እድሜዋ የፈለፈለችብን የሽል ደመነፍስ ዲጂታሎች መጫወቻ ሆነን ባልቀረነው ነበርን ። ፀረ እውቀትና ፀረ እድገት ለመሆናቸው ቀዳማይ ይሁን ዳግማይ ይሁን ሳልሳይ ወያኔ ከሚነግረኝ የገዛ ዘመዶቼ “የምሁራን” ደናቁርት ሆነው በሰላሳ ምናምን አመታቸው ለስሙ ማስተርስና ባችለርን ተላብሰው ቢከፍቷቸው ግን የሚያስለቅሱ ለመሆናቸው የቋሚ ምስክሮች አለን አይደለም እንዴ? በተለይ በዖሮሚያ ምድር የትምህርት ይዞታውን የምታውቁ ታውቃላችሁ። ይህ ሁሉ እየሆነ ዝምታው እስከመቼ ነው?

፬) የሚሠራን ከመተቸት ደግሞ ተጠርቅሞ መቀመጡ ይሻላል

በዬትም በሰለጠነው አለም ክሪቲክ ያለና የኖረ ነው። የኛ አገሩ ግን የመሻሻል ክሪቲክ ሳይሆን የመሰሪነት አቃቂር ነው በሰፊው የሚስተዋለው። አቢይ አህመድ የገባው ድንቅ ወጣት መሪ ለመሆኑ ማስረጃው የትላንቱን ዘጋቢ ፊልም ማየቱ ይቀላል። አንድ ትውልድ በፅልመት ክፉ ምግባር እንደወደመብን ተገንዝቦ ሁለተኛውን ትውልድ ከጥፋት ለመታደግ እቅድ አውጥቶ ምናልባት በሱ እድሜ ሊያይ የማይችለውን ለኢትዮጵያ ፍቅር የብልፅግና ፍኖተካርታውን የሚያጣጥል በትዊተር ገፁ ላይ ማሳረፍ ምን አይነት የክፋት አዝመራ እያጨድን መሆኑን ተገንዝቤአለሁ። በ ፫-፬ ወራት እንዲህ አይነቱን መተግበር ማለት ሥራ የቱን ያህል ቦታ እንዳለው ማሳያ ነው በአቢይ አስተዳደር። ካልሰራችሁ አታሰሩምና ተጠርቅማችሁ ቁጭ ብትሉ ደግሞ ለአገር ውለታ ታደርጋላችሁ።

ማጠቃለያ!

የዚህች ማስታወሻ አላማ ዝምታው እንደ አገርና ህዝብ ስለማይጠቅመን ኢትዮጵያን ያላችሁ የኢትዮጵያ ልጆች ከዚህ ሰፊ ራእይ ካለው ሰውዬ ጎን እንድትቆሙና ዝምታችሁን እንድትሰብሩ ነው። አንድ እጅግ የምስማማበት አቢይ ደጋግሞ ካነሳው የሰሞኑ ውይይት እንዲህ ብሎ ነበር (በጥቅሉ) ” ባላንጣዎቼ ጥምረት የሚሉት እኮ ለስራ መፈለግያ ስልጣን መወጣጫ እንጅ ኢትዮጵያን እንደ ሀገርማ ለማሻገር ቢሆን ምን ገዶኝ?” አይነት አገላለፅ። እውነት እኮ ነው ። ጁዋር የሚሉት ዳውላ እንኳ የጥቅምቱን እልቂት ተከትሎ ለነ አልጀዚራ ልክ እንደ ዴሞክራት ሲደሰኩር የስልጣኗን ጉዳይ በገደምዳሜ ነካክቶ ነበር ያለፈው። አለመታደል ሆኖ በተለይ በአፍሪካ፣ የፖለቲካ ስልጣን ልክ እንደ ቴክኖክረሲ የ “እራት” ማባያና መጨለፍያ እንጅ ለህዝብ ብሶትና እጦት መብት ማስከበርያ መሰላል አይደለም ባብላጫው። ለዚህም ነው አብዛኞቹ የፖለቲካ ተመላሾች ምንም ጥሪት ሳይቋጥሩ ተመልሰው የአልቤርጎና አስቤዛ የደሀው መንግስታቸው ሲሰፍርላቸው የነበረው። የጁዋር አይነቱ ሚሊየነር ስልጡን ፖለቲሻን ከኪሱ ረብጣ ዶላር እንደመመንዘር የደሀው መንግስታችንን ዳረጎት እየተቃመሰም ነበር በጎንም የሚያገዳድለን የነበረው – ሊያውም ለሙስሊም ወገኖቻችን ክቡር የሆነውን የሀጅን ማእረግ ተላብሶ። ምን ያደርጋል ብቻ። ደግሞ እሱን በሽምግልና ለማስፈታት የሚዳክሩ የሀይማኖትና ባህላዊ ሰዎች መኖራቸው እራሱ የሚደንቅ ነው። ሌላው ዝምታ መሰበር ያለበት አገሩን የሚወድ ኢትዮጵያዊ ሁሉ በአንድ ድምፅ እነዚህ ከሀድያን አይወክሉንም ብሎ ማለት አለበት። ደጋግሞ።

በተረፈ በየሙያችሁ ተደራጅታችሁ ወገንን ለመታደግ መከራ የምትበሉ የአገሬ ልጆች ፈጣሪ ይባርካችሁ። የአባይንም ጉዳይ ሳንረሳ ኮንሰርት እያደረግን መዋጮውን በፉክክር እያደረግን አገራችንን እንታደግ። መቼስ የዶር አቢይ ዘጋቢ ፉልም ውስጣችሁን ተስፋ አሰንቆ በፅናት ለአገራችን መፃኢ እድል እያንዳንዳችን ባለሙሉ እንደራሴ እንደሆን ይሰማኛል። የኢትዮጵያ ትንሳኤም እውን ይሆናል። ረጅም እድሜ ለወጣቱ ብርቅዬ መሪያችን! የቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸውስ በዝምታ የውስጥ ስራ ፈጣሪ ብድሮትን ይመልሰው። ምናለ ቀዳማይ እመቤት አዜብ ጎላ እንኳ ከርስዎ ተምረው የተሰረቀበት ንብረቱ እንኳ ቢቀር ስለሚሰቃዩት የወልቃይት አማራ ልጆች ሀቁን ቢናገሩና ተወላጆቹን ቢታደጓቸው።
አመሰግናለሁ

አባዊርቱ

3 Comments

 1. ይገርመኛል የአንዳንድ ስው ልቡና!ሁሉም ባይባል ጥቂቶች መብል ባለበት ቦታ ሲጮሁ እየሆነ ያለውን ሊሆንም ያለውን ነገር ጭልጥ አድርገው ረስተው እንደ ሽመልስ ቁማር ሲጫወቱ ሳይና ጭብንል ሊያጠልቁልን በእነርሱ ስሪትም ልክ እንድናስብ አጀንዳ እየቀያየሩ በደላችንን መታረዳችንን ንብረታችን መቃጠልም በሀስት መታስራችንን እንድንረሳ ይቀባጥራሉ!!በተለይም በአብዛኛው ኦሮሞ የሆኑ ፊደል የቆጠሩ የሽመልስን ወይንም የአብይን ፓለቲካ ሽርሙጥና አይናችን እያየ ሊያጃጅሉን ይዳዳቸዋል !ምናልባትም እነዚህ ምቱሮች ጌታችን መድሃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ እንደገለፃቸው ” አይን አላቸው አያዩም ጆሮ አላቸው አይስሙም አእምሮ አላቸው አያስተውሉም”የተባሉት አምላካቸውን ፈጣሪቸውን የገረፉ የስቀሉትን ከሃዲዎችን ነበር!!
  እነ አባዊርቱም መነጋገርያ አየቀያየሩ በኦሮምያ ክልል የራሳችን ብለን ያሳደግናቸው ያስተማርናቸው ያበላናቸው በክፉም በደጉም አብረን የነበርን ከሃዲዎች ፍፁም ስው በራሱ ወገን ያ ሁሉ ጭካኔ ደርሶብን በቅጡ ሀዘናችንን ሳንወጣ ስለ ህውሃትና ስለወልቃጥ በህውሀት የሚደርስውን ስቃይና የአብይን አስተዋይ ወጣት መሪነት ሲርተርክልን ምንያህል ዝቅ ብሎና የማስተዋል አእምሮውን ደፍኖ የሚወርድልት ወይም ያስበውን ርጥባን ረስቶ ነው?
  ከቶ እንድያው ለመሆኑ በሃያ ስባት ዘመን በህዋት መሪነትና በሁለት አመቱ በህዝባችን ላይ የትኛው ነበር የከፋውአንዳንድ ግዜ ደርግም ገዝቶል ህውሀትም ገዝቶል እነርሱ ተመልስው ቢገዙን ይሻል ነበር ብለን ሳናስብ እንቀር ይሆን?የቄሮን ፍፁም አረመኔነት በዚህ አለም ላይ ከተፈፀሙት የዘር ማጥፋት ወንጀሎች በአፈፃፀሙ ከየትኛው ጋር እናመሳስለው ይሆን?
  አባዊርቱ !ይገባኛል እርስዎ እያመስሉ ከሚገዙን ወገኖች ስለሆኑ ስለምን አይተውኑም?ስለምን ይቆስቁሱናል?የአብይን አስመሳይነትና ፓለቲካ ሽርሙጥና ከቶ የማናስብ መስሎት ነው እንዲህ ህሊናዎን ሸጠው እንደ ሽመልስ ሊያደነዝዙን የሚዳዳዎ!በእነ እስክንድር ላይ የሀስት ምስክር ከመጋረጃ አድርገው ሲከሱ አይኖ እያየ ጆሮዎም እየሰማ በልብዎ ደግ አደረጉ እይሉን ነውኮ?ወልቃይቶች እኮ ቢያንስ በቀያቸው ይኖራሉ!በእርስዎ ክልል ግን ስው በተለይምአማራ በገጀራ እየተቀጠቀጠ ሲገደል በድኑ በቢላ እየተለተለ ይቃጠላል ንብረቱ ይወድማል እኮ!!ስለምን ያን ተው አይሉም?ለምን አስመሳዩን ቁማርተኛውን ግዜ ያልፋል ለመጥፎ ለማያልፍ ታሪክ አታድርግ አታስመስል ለምን አይልም?ፓርኩ ገለመሎው የሚስራው እኮ ለስው ነው?ቅድምያ የስው ደህንነት ይበልጣል!ተጎጅዎች በአፋጣኝ መቆቆም አለባቸው ለስው ርህራሄ ከአልዎት!በእግዚአብሔርም በስውም የሚታየውን የዕለት ህይወትማቆየት ነው ቅድምያ የሚስጥ!ግን አብይ አህመድምሆነ መስሎች እርስዎ ጨምሮ ይህ እንዲሆን አትፈልጉም!ህዝቡ እንዲፈናቀል ትፈልጉታላችሁ አይደል?ከሱማሌው ክልል መሪ አቶ ሙስጠፌ ጥሩ ምሳሌ ነው ዛሬ ስላም ነው ክልሉ!ምናልባትም ወደፊት ቢመጣና የጠቅላይ ሚንስተሩን ቦታ ቢይዝ መልካም ርእንድሚሆን ጥርጥር የለኝም’
  አባዊርቱ ብዙ አልኩኝ መስል?ብሶት ንዴት ቁጭት ስለአለብኝ ነው!በኦሮምያ ክልል ከሱማሌው ከደሬው ከአርጎባው ከኦሮሞው(ቄቱ) ጋር በፍቅር በመተሳስብ በመረዳዳት ለዘመናት ስለኖርኩብት ነው
  እናም በሀስት ክስ ከመጋረጃ ጀርባ ምስክር የሚደመጥባችውን ንፁሀን በህሊናዎ በብእርዎም እውነተኛ የእግዚአብሔር ስው ከሆኑ ያስቡቸው
  ይብቃኝ
  ኃያሉ እግዚአብሔር ስላም ለሀገራችን ያውርድ!በቃችሁ ይበለን!
  እናንተ የዚህ አምድ አዘጋጆች እግዚአብሔር ስራችሁን ይባርክ!ያብዛችሁም!!

  • “ከቶ እንድያው ለመሆኑ በሃያ ስባት ዘመን በህዋት መሪነትና በሁለት አመቱ በህዝባችን ላይ የትኛው ነበር የከፋውአንዳንድ ግዜ ደርግም ገዝቶል ህውሀትም ገዝቶል እነርሱ ተመልስው ቢገዙን ይሻል ነበር ብለን ሳናስብ እንቀር ይሆን”

   አዎ ለዘራፊው ወያኔ እንዲመልስ ምኞታችሁ ይሆናል:: 2 አመታት ያላቋረጠ ጦርነትና ጭፍጨፋ ዐቢይ ያመጣው ሳይሆን እባቡ ህውሀት የሚተገብረው ኢትዮጵያን የማፍረስ አጀንዳ ስራ ነው:: ለአማራ እቆረቆራለሁ ስትል ያቅረኛል:: አማራ ጅል አይደለም::

 2. አባ ዊርቱ፣
  ብዙ ጊዜ ጽሁፍህንም ሆነ አስተያየቶችህን ሳነብ እጅግ እረካለሁ። ለምታደርገው ተጋድሎ ትልቅ አክብሮት አለኝ።
  እንደአልከው የ ሁሉም ዜጎች ተሳትፎ የሚጠበቀውን ውጤት ያመጣል እንጂ በ ጥቂቶች ብቻ ሊመጣ አይችልም። ነገር ግን ብዙ ሰዎች፣ ከ ደርግ ዘመን ጀምሮ በ ፖለቲካው ውስጥ ተሳትፎ የነበራቸው፣ ከ መዳከም የተነሳ አርፎ መቀመጥን መርጠዋል። በ ውጭ አገራት የተወለዱ ወጣቶች ተሳትፎአቸው ዝቅተኛ ነው። ብዙ ሺዎች በሚኖሩበት ክተማ 100 ሰዎች ለ ተቃውሞ ማግኘት ችግር ሆኗል። ችግራችን ይህን ይመስላል። ነገር ግን ታሪክን ሊያስተምሩ የሚችሉ አልፎ አልፎ ጽሁፎችን ከ ማቅረብ ሊሸሹ አይገባም። አለበለዚያ እውነቱ ውሸት፣ ውሸቱ ደግሞ እውነት እንዳይሆን እሰጋለሁ።
  ከ ሁሉም በላይ በ ሃይለ ሥላሴ ዘመን የ ትግራይ ንጉሥ የነበሩት ልኡል ራስ መንገሻ እውነቱን ማጋለጥ ነበረባቸው። በ አንድ ወቅት ወልቃይት በ ትግራይ ሥር ሆና አታውቅም ብለው ነበር። ግን ተደባብሶ ቀረ።
  ኢትዮጵያ ተስፋ የሚኖራት ጠሚ አቢይ ያለአድልዎ ህግን ከ አስከበረ እና በ እኩልነት ከ አስተዳደረ ብቻ ነው። ያን ከ አደረገ ከፍተኛ ድጋፍ ይጎናፀፋል። በዚያም የ ድጋፍ ሃይል የ ኢትዮጵያን የተመሰቃቀለ ችግር ሊፈታ ይችላል።
  ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይጠብቅ። አሜን።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.