ተቀበል በገና (ዘ-ጌርሣም)

ተቀበል በገና ስሜቴን ቃኝልኝ በአንተ ላንጎራጉር
የማሲንቆ ቅኝት ስለሚያደናግር
በማለት ልጀምር እንደሚከተለው
የስሜቴን ቅኔ አንተው አስተካክለው

ተቀበል በገና
ስሜትን ለመግለፅ ትመቻለህና

የጎረቤት አሣት ጫሪ
ጥሎ ይሄዳል ፍንጣሪ
የኔ ቤት ሲጋይ ያኔ ስቋል
የሱስ ቢሆን የት ያመልጣል
የራስን ዕረፍት ሳያጤኑ
ምነው ለኔ ሞትን ለመኑ

ጊዜና ጊዜ ተወራርደው
አሰጥ አገባ ተባብለው
ጊዜ ተረታ በጊዜ
ዕጣ ወጥቶለት ያንጊዜ

የቆላ ተክል ደጋ ወጥቶ
በገብሷ ምርቃን ተወግቶ
ዳኛ ሲፈለግ ሳማ መጣ
መቀመጫ እንኳን የሚያሳጣ

በጠላት ወሬ ተፈትቸ
ከወገኖቸ ተጣልቸ
እስከመቸ እኖራለሁ
ሥጋን በሥጋ እያባላሁ

ተቀበል በገና
ሃሣቤን ቃኝልኝ በሙዚቃህ ቃና

ትልቁን ሰንጋ በር አቁሜ
ትንሿን ጠቦት መጠቀሜ
ቅመማ ቅመም ቀምሜ
ለመብላት እንጅ አጥሜ

ካንጋዳው ሆዴ ተጣልቸ
አሰስ ገሠሱን አስፈጭቸ
ተቀበል ብለው እምቢ አለኝ
የገባው ሳይቀር ወጣብኝ

ተቀበል በገና
እንጉርጉሮ ሳይሆን ሙዚቃ ነውና

ተው ሆዴ ምረጥ ምግብህን
በወግ ተቀበል ያቅምህን
የታየው ሁሉ ምግብ ላይሆን
ይልቅ ተጠንቀቅ ከሰው ዓይን
የሰው ዓይን እኮ እሣት ነው
ዋርካ ያደርቃል ያለ ዕድሜው
አንኳንስ አንተን ሰውንና
መብረቅ ያወርዳል በገና (ዝናብ በማይታሰብበት ወቅት)

ተቀበል በገና
ለቅላፄህ ፍሰት አድናቂ ነኝና

ወንዙን አቋርጦ ላይዋኝበት
መንቦራጨቁ ስም ሆነበት
የዋነተኛ ችሎታው
አፍላ ሙላትን ማሳለፍ ነው
አዩኝ እዩኝ ያለማ ዋናተኛ
ተጠርጎ ሄያጅ ነው ባፍለኛ
ሌላው ሳይነቃ እንደተኛ

ተቀበል በገና ሃሣቤን ቋጭልኝ
ለሚያዳምጥ ጆሮ ፈጥነህ አድርስልኝ

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.