ሥጋ አማረው ሆዴን (ዘ-ጌርሣም)

ሥጋ አማረው ሆዴን ሥጋ የት ተገኝቶ
አንተ ትብስ አንች በተባባሉበት
ክፉ ቀን ሲመጣ አብረው በቆሙበት
በደጎቹ ዘመን በቁርጡ ተበልቶ
የሙክት የጠቦት ብሎ እንዳልመረጠ
ጎረቤት ሰብስቦ
ዘመድ አዝማድ ጋብዞ
ቀይና አልጫውን አስፈትፍቶ አቅርቦ
ዱለትና ጥብሱን እንዳላስመረጠ
ሥጋ አማረው ሆዴን ብዙ የለመደው
የዶሮዋን አንኳን ማጣቱ ሳይገባው
ድንችና ጎመን
ፓስታ መኮሮኒ
ፓስቲና ሳንድዊች
ሾርባ ሚንስትሮኒ
ቃሪያና ቲማቲም
የአትክልት ዘር በሙሉ
የሆቴሎች ምግብ ባለዘመኖቹ
አጠፉት ሥጋውን ከሽንጥ እስከወርቹ
ሥጋ አማረው ሆዴን ሥጋ የት ተገኝቶ
በደጎቹ ዘመን በቁርጡ ተበልቶ
አረ ሥጋ አምሮኛል ሥጋ ፈልጉልኝ
ባይሆን ለአዲሱ ዓመት ለባዕሉ ቢሆነኝ
የግጦሹ ሜዳ ታርሶ በመድረቁ
ሥጋ ያስለመዱኝ ከብቶቹም አለቁ
ክትክታና ወይራ የደጋው አትክልት
አድልቦ እሚያሳድግ ሙክት ከጠቦት
ተመነጠረ አሉ አካባቢው ሁሉ
ሥጋ አማረኝ ብሎ መንደሩ በሙሉ
ሥጋ አማረው ሆዴን ሥጋ የት ተገኝቶ
በደጎቹ ዘመን በቁርጡ ተበልቶ
የሃምሣ ሳንቲም ዶሮ የለመደው ሆዴ
መቶን አልፏል ቢሉት ሆነበት ሁዳዴ
አንች ደግ ዘመን ግፍ የተሰራብሽ
ድኩላና ሰሣ እንዳልታደነብሽ
በሚዜ ቅዝምዝም ዶሮ እንዳላስጨረስሽ
ሥጋ ሆዴን ነስተሽ የሴት ድስት ውሀ አረግሽ
ሥጋ አማረው ሆዴን ሥጋ የት ተገኝቶ
በደጎቹ ዘመን በቁርጡ ተበልቶ
የጊዜው ክፉነት የትውልዱ ጥፋት
የት ታገኛት ብሎ ሆዴን ሲከተላት
በኔ የመጣው ጉድ አይር ላንድ ተወልዶ አውሮፓን በከላት
የሥጋ በሽታ መድኃኒት የሌለው
ሐኪም ቢሰበሰብ ቆርጦ የማይጥለው
ተጣብቶ እንደያዘ ጠብቶ ነው እሚገለው
ሥጋ አማረው ሆዴን ሥጋ የት ተገኝቶ
በደጎቹ ዘመን በቁርጡ ተበልቶ
የሰፈሩ ቅርጫ ድኃ አስተናጋጁ
ሁሉን እኩል አርጎ ያዋለው ከደጁ
ያ ጊዜ አለፈና ዘመን ተለውጦ
ሆዴን ሥጋ አሰኘው ከምግብ ሁሉ መርጦ
ሥጋን አትጣሉ እፈልገዋለሁ
ከወጥ ከተረፈ ለቁርጥ አቀርባለሁ
ሥጋ አማረው ሆዴን ሥጋ የት ተገኝቶ
በደጎቹ ዘመን በቁርጡ ተበልቶ
በሽሮና በአሹቅ የደረቀው ሆዴ
በተስፋ ይኖራል ሥጋ በመውደዴ
አረ ሥጋ አምሮኛል ሥጋ አፈላልጉልኝ
ከትውልድ ሀገሬ በአገልግል ላኩልኝ
ድንገት ካልተሳካ ከተጣለው ሰንጋ አንድ መደብ ያዙልኝ
እንዳልሞትባችሁ ሥጋ ሥጋ እንዳልኩኝ
ሥጋ አማረው ሆዴን ሥጋ የት ተገኝቶ
በደጎቹ ዘመን በቁርጡ ተበልቶ

ተጨማሪ ያንብቡ:  ምን ይሉታል ! - (ዘ-ጌርሣም)

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share