ጭቃው – አሁንገና ዓለማየሁ

በግንቦት ታርሰናል
ሰኔ ለስልሰናል
ነጎድጓዱ መጣ
መብረቅ ከማለፉ
በዶፍ የሚወቃ
ሊጫወትብን ነው የክረምቱ ጭቃ።
ሰኔ 2011

አዲስ ቀዳም
አዲስ ነው ካላችሁ እሺ አዲስ ይሁን
ታድያ በቀደመው አትቅደሙን አሁን።
(ቀዳም የበፊት፣የመጀመሪያው፣ የቀድሞ ማለት ነው። አዲስ ነው እያላችሁ በቀድሞው ስልት ነው የምትጓዙት የሚል አንድምታ ያለው ግጥም ነው። አንድም በፈጣሪ(በቀደመው) ብለህ፣ ስለፈጣሪ ስትሉ እኩል እዩን፣ እኩል እንጓዝ፣ አትብለጡን፣ እኔ ልቅደም አትበሉ።)

ቄሳር
በምጥ ሞታ እናቱ
ቀደው ያወጡቱ
ቀዶ አወጣቸው
ያንን ቀን ረገሙ
ዓለም ባትገባቸው።
ሰኔ 2011 ዓ. ም.

በዳዊት ሙስና
ጎልያድን በጠጠር ስትደፋው አምና
ፈጥነህ ይዘህ ነበር የዳዊትን ዝና
ኦርዮንን ዘንድሮ ስትነሳው ጤና
ፈጥነህ ወደቅህ እንጂ በዳዊት ሙስና
ሰኔ 2011

እዚያ አልደረስንም
ሐሳዊ መሲሆች ይመጣሉ ያልከን
የኛ እድገት ገና ነው/ ለእርሱኛው እርከን
በግብጽ በረሃ ውስጥ በቁም ግስጋሴ
ገና እየፈጋን ነው በሐሳዊ ሙሴ።
ሰኔ 2012

ታላቁ ኤክሊፕስ
ኢትዮጵያ ሕዝቦችሽ
በኑራቸው ምጣድ ሙግድ ሆኖ ከላዩ
በእኩለ ቀን ዓለም፣ ጨልሞ ሰማዩ
ግርዶሽ ውስጥ ተቀምጠው ግርዶሽን እያዩ
ለእኩል ሰዓት ያህል አጀብ ሲሉ ቆዩ
ግርዶሹም ጠፋና ጀምበሩ ብቅ አለ
ዋናው ግርዶሽ ቀረ እንደ ተጀጎለ።
ምነው እሱም ግርዶሽ እንዲህ በቸኮለ!
ሰኔ 2012

ፌላሌምሌሞኒም
ባንቺ የደረሰውን
አድርገውት ነበር
ሂትለር ሙሶሎኒም
ፌላሌምሌሞኒም።
ሞራ ገልጦ ማየት
ጋደል አርጎ ሲኒም
አያሻውም እጣሽ
ፌላሌምሌሞኒም።
(ፌላሌምሌሞኒም — ስድስቱ ቀለማት (syllables) ለስድስቱ ወራትና ለምሥጢራዊው ግፍ ወካይ ናቸው።)
መታሰቢያነቱ 6 ወር ላለፋቸው ለታገቱ የደምቢ ዶሎ ዪኒቨርሲቲ ተማሪዎች ይሁን።
ሰኔ 2012

ተጨማሪ ያንብቡ:  ይህንን አውቃለሁ !... -መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

የግርዶሹ ግርዶሽ
ሰኔ ገጠመና ዘንድሮ ከሰኞ
አንጋጠን ስንታይ መሰልን እነሞኞ።
ዓለም ተደነቀ በኛ ያለ መጠን
አይቶን ስንጓጓ
ግርዶሽን ለማየት ግርዶሽ ውስጥ ተቀምጠን።

አሁንገና ዓለማየሁ ሰኔ 2012

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share