ግብጽ በየአቅጫው ሩጫ ላይ ና – መሳይ መኮነን

በአንድ እጇ ዲፕሎማሲ፡ በሌላኛው የፕሮፖጋንዳ ጥቃት፡ በኋላ ኪሷ ደግሞ የጦርነት ካርድ ይዛ ኢትዮጵያን ለማንበርከክ ከምንጊዜውም በላይ እየሰራች ነው። የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከአባይ ላይ አይኗን አልነቀለውም። ሶስት ጄነራሎቿን ለነጠቀው የኮሮና ጥቃት ጀርባዋን ሰጥታ የኢትዮጵያን ህልም ለማጨናገፍ የሞት ሽረት ትንቅንቅ ላይ ናት። የአረብ ሊግ አባል ሀገራትን አስተባብራ ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር ያደረገችው ጥረት የኢትዮጵያን አቋም ሊያስቀይረው አልቻለም። በአሜሪካን በኩል የጀመረችው መንገድ ብዙም የሚያዋጣት አልሆነም። ለመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ያቀረበችው አቤቱታም ውጤት አላስገኘላትም። ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማትንና ትልልቅ አበዳሪ ድርጅቶችን አሳድማ ለኢትዮጵያ ገንዘብ እንዳይሰጡ ያደረገችው ሙከራ ቢሳካላትም የኢትዮጵያን ጉዞ የሚያቆም ግን አልሆነም። አሁን የቀሯት ሁለት ምርጫዎች ብቻ ሆኑ። ወደ ድርድር መመለስ አልያም ከኋላ ኪስ የሸጎጠችውን የጦርነት ካርድ መምዘዝ። ለጊዜው የሚያዋጣትን መርጣለች። ኢትዮጵያ ባቀረበችውና አፍሪካ ምድር ላይ በሚካሄደው ድርድር ላይ መሳተፍ ግብጽ እየተናነቃትም ቢሆን የምትውጠው የጊዜው ምርጫ ሆኖባታል።

ግብጽ በጊዜያዊ አስገዳጅ ሁኔታዎች ወደ ድርድር ለመመለስ ብትወስንም በዘላቂነት ኢትዮጵያን የማዳከም አጀንዳዋን እርግፍ አድርጋ የምትተወው አይደለም። ኢትዮጵያ የአባይ ግድብን መገንባት ከጀመረች ወዲህ ግብጻውያን በአንድ ዓይናቸው ነው የሚተኙት ይባላል። የፖለቲካ ልዩነታቸውን ወደ ጎን አድርገው በአንድ ልብ ከአልሲሲ ጎን ተሰልፈዋል። ግብጽ በእርግጥም ብዙ መጫወቺያ ካርዶች አሏት። በፕሮፖጋንዳው ፍላጎቷን የሚያስፈጽሙ ሚዲያዎችና ዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ በረጅም እጇ ገብታለች። የጎግል መበርበሪያ ቢፈተሽ የግብጽ ምሁራን ጽሁፎች በአይነት ዓይነቱ ተደርድረው ይገኛሉ። ስለግብጽ ጥቅም በክፍያ የሚጽፉ የሌሎች ሀገራት ኤክስፐርቶች የሚለቋቸው መሰል ጥናቶችም የኢንተርኔት ማስፈንጠሪያዎችን ለሚጫን ሁሉ በቀላሉ የሚገኙ ናቸው።

ግብጽ ታላላቅ የሚዲያ ተቋማትን በእጅ አዙር ትደርስባቸዋለች። በአረቡ ዓለም ያሉት የመገናኛ ብዙሃን አባይ ግድብ ቀዳሚ አጀንዳቸው እንዲሆኑ አድርጋለች። በታላላቆቹ ኒውዮርክ ታይምስና ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጦች ላይ ምሁራኖቿ በውሸትና ብልጣብልጥ መረጃዎች የተለበጡ ጽሁፎችን፡ የተቀሸቡ ጥናቶችን በስፋት ያወጣሉ። በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በሚዘጋጁ የዓለም ዓቀፍ የግጭትና ቀውስ ጥናት መድረኮች ላይ ግብጻውያን ፕሮፌሰሮች የአባይን ጉዳይ ሳይጠቅሱ አያልፉም። ከዋሽንግተን ዲሲ፡ እስከ ለንደን፡ ከዶሃ እስከ ካይሮ ፈርኦኖች እረፍት የላቸውም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሚኒሶታ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ቤ/ክ ለሰላምና ለአንድነት ከቆሙ ምእመናንን የተላለፈ ማብራሪያ

የሰሞኑ የአምኒስቲ ኢንተናሽናል ሪፖርትን እንደቀድሞዎቹ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሪፖርቶች ለመውሰድ የሚተናነቀኝ የግብጽን እረፍት ያጣ ሩጫ የት እንደሚያርፍ ጥርጣሬ ውስጤን ስለሚንጠው ነው። አምኒስቲ የኢትዮጵያን መንግስት ክፉኛ የተቸበት የሰሞኑ ሪፖርቱ በጉድለት መሞላቱ፡ ከተለመደው የመረጃ መስበሰቢያና ሳይንሳዊ የትንተና ዘዴዎቹ ይልቅ የመንግስት ተቃዋሚ የሆኑ ወገኖችን የሚያሰራጩትን ዜናዎችና ፖለቲካዊ ክሶች ሰብስቦ በማጠናቀር የተዘጋጀ መሆኑ የግብጽ እጅ እስከየት ይረዝማል የሚል ጥያቄ እንዳነሳ ተገድጄአለሁ። የግብጽ የስለላና የሴራ ክር ቢተለተል ጫፉ አምኒስቲ ኢንተናሽናል ጓዳ መድረሱን መጠርጠር ሃጢያት አይደለም።

ግብጽ ኢትዮጵያን የቀውስ ጎተራ፡ የብጥብጥ መናሃሪያ፡ ለማድረግ የምትመጣበት መንገድ አንድ ብቻ አይደለም። የፊት ለፊት ጦርነት ውስጥ ከመግባት ይልቅ በተለያዩ መንገዶች ውስጣዊ ሰላም በመንሳት የኢትዮጵያ መንግስት ትኩረቱን ከአባይ ግድብ ላይ እንዲያነሳ ማድረግ የግብጽ ቀጣዩ ስውር አጀንዳዋ ነው። ከካይሮ፡ መቀሌ፡ አዲስ አበባ በተዘረጋው መስመር ህወሀቶችና የኦሮሞ ጽንፈኛ ሃይሎች መሰለፋቸውን ነገ ከነገ ወዲያ ከኢትዮጵያ የደህንነት መስሪያ ቤት እስክንሰማ የምንጠብቀው ጉዳይ አይደለም። ምልክቶችን እየታዩ ነው። ነጠብጣቦችን ገጣጥሞ ለሚያነብ ሰው ካይሮ መነሻውን መቀሌ ማረፊያውን፡ አዲስ አበባ መዳረሻውን ያደረገው ሀዲድ በግልጽ የሚታየው ይሆናል።

የአምኒስቲ ኢንተናሽናል የሰሞኑ ሪፖርት በህጸጾች መሞላቱ ብቻ አይደለም። ሀቆች ተደፍጥጠዋል። እውነቶች ተወላግደው ቀርበዋል። የተጠቂዎች ድምጾች ታፍነውበታል። በግፍ የተገደሉ ዜጎች ሆን ተብሎ ወደ ጎን ተገፍተዋል። በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ የሚጮሁ የፍትህ ልሳኖች ጆሮ ዳባ ልበስ ተብለዋል። በቀን በጠራራ ጸሃይ የተፈጸሙ አሰቃቂ ግድያዎች ተድበስብሰዋል። በአምኒስቲ ሪፖርት ሴጣን መላዕክ ሆኖ ቀርቧል። በደል ፈጻሚዎች፡ በደለኛ ከሳሽ ሆነው ታይተዋል። ምንም እንኳን በጥሬ ሀቅ ከታየ ሪፖርቱ ያነሳቸው ክስተቶች በኢትዮጵያ ምድር የተፈጸሙ ቢሆኑም ግልብ በሆነና ከጀርባ የፖለቲካ ሴራ በቀመረው መልኩ የተዘጋጀ መሆኑ በሚያምር መጠቅለያ የተሸፈነ መርዝ መሆኑን ለመረዳት የሚያዳግት አይደለም። ተቋሙ በሚታወቅበት ቁመናና ለተሰለፈለት ዓለማ የሚመጥን ሪፖርት ከማዘጋጀት ይልቅ መንገድ ላይ የተጠለፈ ይመስላል። እንደግብጽ ያሉ እጃቸው ረጃጅም የሆኑ የሆኑ መንግስታት በእነዚህ ተቋማት አማካኝነት ማስቆጠር የሚፈልጉት ነጥብ እንዳለ አለማሰብ የዋህነት ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የሰንሹ የጦርነት ጥበብ ላማራ ሕዝባዊ ግንባር፤ ማጥቃት መከላከል ነው

በእርግጥ የአምኒስቲ የሰሞኑ ሪፖርት ላይ የተገለጹት መረጃዎች ላይ ላዩን ሲታዩ አሳሳች ናቸው። ሰዎች ተገድለዋል ይላል። ልክ ነው። ህዝብ ተፈናቅሏል በሚል ይከሳል። ስህተት የለውም። ግጭቶች በርክተዋል። የአምኒስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት በዚህም ችግር የለበትም። ግን ማን ፈጸማቸው፡ ተጎጂዎቹ እነማን ናቸው፡ ከግጭት መፈናቀሉ ጀርባ ያለው ፖለቲካዊ ምክንያት ምንድን ነው፡ ሌሎች አሰቃቂ የሆኑ ጭፍጨፋዎች አልነበሩም ወይ፡ የሚሉና ሪፖርቱ እንዲመልሳቸው የሚጠበቁ ጥያቄዎች ማንሳት ለፈለገ መልስ አያገኝበትም። ሪፖርቱ አንካሳ ነው። በሙሉ እግር መቆም የማይችል ነው። የህወሀቶችን የእጅ አዙር የቀውስ ድግስ ቡራኬ ሰጥቶ፡ የበዳዮችን ትርክት ቀይሮ ያቀረበ ሪፖርት ነው። በተለያዩ የኦሮሚያ አከባቢዎች በግፍ የተገደሉና የተፈናቀሉ ዜጎችን አስከፊ አጋጣሚ ለመጥቀስ ወኔ ያጠረው ሪፖርት ነው።

ይህ የሆነው ደግሞ በመረጃ እጥረት የሚል ሰበብ ቢሰጠው ከትዝብት ላይ የሚጥል ነው። ወይም በመንግስት በኩል መረጃ የሚሰጥ ባለመኖሩ ነው የሚል ምክንያትም አይሰራም። በአፋኙ የህወሀት ዘመንም አምኒስቲ የገጠር ቀበሌ ድረስ የዘለቀ የመረጃ ማሰባሰቢያ መንገዶች ነበሩት። ይህን ሪፖርት እንደተለመደው የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚያትት፡ የተበዳዮችን ድምጽ ለማሰማት ብቻ የወጣ ነው በሚል ለመቀበል የሚያስቸግሩ አያሌ ምክንያቶች ያሉት እንደሆነ በግሌ በግልጽ ተረድቼአለሁ። ሪፖርቱ አንዳች ድብቅ አጀንዳ አለው። አራት ነጥብ። የግብጽ ፍላጎትን፡ ወደፊት ያሰበችውን በጨረፍታ የተመለከትኩበት ሪፖርት ነው።

ግብጽ ኢትዮጵያን ለማመስ ተዘጋጅታለች። በኢትዮጵያ የሚስተዋሉና በቀላሉ ልትጠቀምባቸው የምትችላቸው ፖለቲካዊ ኩርፊያዎች በርክተዋል። ህወሀቶች አንዱ ክራንቻቸው ግብጽ ናት። በእስከአሁን የዶ/ር አብይን መንግስት ለማዳከም በህወሀቶች በኩል የተወረወሩት ፈንጂዎች በሙሉ ክሽፈዋል። የፌደራሊስት ግንባር በሚል የተደራጁት ባለሳምሶናይት ፓርቲዎች ምርኩዝ ሆነው ከአዲስ አበባ የሚያደርሱ አልሆኑም። ከጽንፈኛ የኦሮሞ ሃይሎች ጋር መጣመሩ ያለግብጻ ድጋፍ የሚሳካ እንዳልሆነ ህወህቶች ያውቁታል። ህልማቸው የአዲስ አበባውን መንግስት ማፈራረስ ነው። ከተቻለ የተነጠቁትን ዙፋን ማስመለስ ነው። ያም ካልሆነ እንደአሻንጉሊት የሚጫወቱበትን ደካማ መንግስት አራት ኪሎ ማስቀመጥ ነው። ይህ ከተሳካ ለግብጽም ያዋጣታል። አባይን በጭልፋ እንኳን የማይነካ አቅመ ቢስ መንግስት ኢትዮጵያን እንዲመራት ማድረግ ለግብጽ ታላቅ ብስራት ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  በዘሀበሻ ላይ የወጣውን የቅዳሜ ዕለት የደብረሰላም መድሐኒአለም ውሎ ተከታትዬ በጣም አዘንኩኝ (ታዛቢ)

የኦሮሞ ጽንፈኞችም የዚህ የጸረ ኢትዮጵያ ንቅናቄ አካል ከመሆን የሚያፈገፍጉ አይሆኑም። ከህወሀትና መሰል የጥፋት ሃይሎች ጋር እየተናበቡ ይሰራሉ። ግባቸው ዶ/ር አብይን ከቤተመንግስት ማፈናቀል ነው። ከዚያ በኋላ ስለምትኖረው ኢትዮጵያ ህወህቶችም ሆኑ ጽንፈኛ የኦሮሞ ሃይሎች የሚያስጨንቃቸው አይደለም። የሚያስቡት እስከኢትዮጵያ መፈራረስ ነው። በፈራረሰችው ኢትዮጵያ የእነሱ ህልውና የሚቀጥል ይሁን አይሁን ለጊዜው አያሳስባቸውም። ይህ አቋማቸው ለግብጽ አዱኛ የሆነ ታላቅ አጋጣሚ ነው። አምኒስቲ ኢንተናሽናል ደግሞ የዶ/ር አብይን መንግስት ገጽታ በሚያጠቁሩና በሚያጠለሹ ሪፖርቶች የግብጽን አጀንዳ ወደፊት እንዲሄድ ያግዛል። የአምኒስቲ ኢንተናሽና የምስራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር አፍቃሪ ህወሀት መሆኑን እዚህ ላይ መጥቀሱ ተገቢ ይመስለኛል። ይህ ግለሰብ በግልጽ የዶ/ር አብይን መንግስት በማጥላላት በተለያዩ መድረኮች ላይ ማን እንደሆነ አሳይቶናል። በዘር መስመር የህወሀት ወገን በመሆኑም የዘሬን ብተው ያንዘርዝረኝን እየተጫወተ ለመሆኑ በቀረበባቸው የተለያዩ መድረኮች ማረጋገጥ ችለናል።

ግብጽ የኢትዮጵያና የሱዳን የድንበር ውዝግብን በማራገብ የፖለቲካ ድል ለማስቆጠር እየለፋች መሆኑን የሰሞኑ የሚዲያዎቿን ፕሮፖጋንዳዎች በማየት መግለጽ ይቻላል። ድንበር አከባቢ የሚስተዋለው፡ ለዓመታት ያዝ ለቀቅ የሚያደርገውን ግጭት የተለየ መልክ ሳይኖረው የሰሞኑን ቀዳሚ አጀንዳቸው አድርገው የሚያቀጣጥሉ የግብጽ ሚዲያዎች ስለኢትዮጵያ ጉዳይ እንቅልፍ እንደማይወስዳቸው የሚያሳይ ይመስለኛል። ሱዳኖችና ኢትዮጵያውያኑ የግብጽን ተንኮል በቶሎ ካልባነኑት የድንበሩ ግጭት የአባይ ግድብ መደራደሪያ እንዲሆን ከጠረጴዛ ላይ ማስቀመጥ የግብጻውያን ፍላጎት ነው። ግብጻውያን በአንድ አይናቸው በመተኛት ሌላኛውን አባይ ላይ ተክለዋል። የኢትዮጵያውያን የወቅቱ እንቅልፍም የግብጽን አካሄድ እያሰላ የምንተኛው መሆን አለበት። ለሙሉ ጊዜው እንቅልፍ ሌላ ጊዜ ይደረስበታል። ሁለቱንም አይኖቻችን አባይ ግድብ ላይ መትከል የግዜው ወሳኝ እርምጃችን መሆን አለበት። ፈርኦኖች የቀኝ ግዛት ስምምነት እንዲጸና በዚህ መልኩ ከተሯሯጡ፡ እኛ ደግሞ ለነጻነትና ክብራችን እስከሞት ድረስ የምንሰዋለት ቃልኪዳን ልንገባ ግድ ይላል።

1 Comment

  1. መሳይ ትክክል ብለሀል ግብጽ የማትገባበት የለም ኢትዮጵያም ዉስጥ ዘላቂ ሰላምም አትፈልግም ያንን አምነስቲን ታክኮ የመጣዉን የስብሀት ነጋን ልጂ ስሙን ብትጠራዉ ምንም አልነበረም። የሆነ ሁኖ አምነስቲም በጁዋር አዋጂ ያለቀዉን የተፈናቀለዉን ሳይዘግብ የዶ/ር አብይን መንግስት ጤና መንሳቱ አግባብ አልነበረም።

    ኢትዮጵያ ዉስጥ በትግሬዎችና በኦለፍያዉያን ምን ያልተሰራ ግፍ አለ? እሱ ሁሉ ተዘሎ ይህ መመዝገቡ ሚዛናዊነት ይጎድለዋል።
    ለዚህ ነበር ባለፈዉ ጊዜ ግምቦት 7 ኢሳት ወደ ግብጽ መለስ ቀለስ ሲል ስራ ማስኬጃ ነገርም ሲቸረዉ ተዉ ዘላቂነት ያለዉ ስራ ይሰራ ከግብጽና ከኢሳይያስ ለኢትዮጵያ የሚበጂ ነገር አይመጣም ስንል ብርሀኑ/ነአምን/አንዳርጋቸዉ ዝም በሉ ነጻነት በዛ በኩል ነዉ አሉን ይኸዉ ሳይዉል ሳያድር የፈራነዉ ደረሰ።

    ብቻ በግልህ አንተ ነገሩ ጸጸቶህ እዚህ ላይ መድረሰህ ጥሩ ነዉ አንተ መጥራት ያልደፈርከዉን ሐጎስን እኛ ፈልፍለን እናገኘዋለን። ዋልታ ላይ የተለቀቀዉን የትገሬዎችን ሰቆቃ አይቼማ ካሁን በሗላ እየሰረጉ የሚገቡትን ትግሬዎች ባይነ ቁራኛ ማየት አስፈላጊ ነዉ።
    ለመሪዎች ሳይሆን ለኢትዮጵያ ቀና ነገር አስቡ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share