የኮሮና ቫይረስን ወረርሽኝ አስመልክቶ በታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ ምክንያት ለነሓሴ ወር ታስቦ የነበረው ስድስተኛው ብሔራዊ ምርጫ ላልተወሰነ ጊዜ መተላለፉን መንግሥት አሳውቋል። ይህንን የፌዴራል መንግሥትን ዓዋጅ በመቃወም በትግራይ ክልል ውስጥ አስቀድሞ በመተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ምርጫውን እንደሚያካሄድ የክልሉ መንግሥት በአደባባይ ገለጸ። ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘ ወዲህ በዚህ ደረጃ የፌዴራል መንግሥቱን ሥልጣን የሚገዳደር የክልል መንግሥት ብቅ ሲል የመጀመርያው በመሆኑ፣ ብዙዎችን ግር አሰኝቷል። ይህ ምክንያት ሆኖኝ እኔም እንደ አንድ ተቆርቋሪ ዜጋ፣ በዚህ ጉዳይ ላይ ያለኝን ያሳብ ለውይይት መነሻ ይሆነን ዘንድ ይህንን ጽሁፍ ለማቅረብ ወሰንኩ። ባገራችን ዛሬ ሁሉም ክስተት የሚለካው በፖሊቲካ መስፈርት መሆኑ ቢገባኝም፣ በዚህ ጽሁፌ ግን በተቻለኝ መጠን በፌዴራል ሕገ መንግሥቱ ላይ ብቻ እያተኮርኩ የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ምርጫን አካሄዳለሁ ማለቱ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ መሆኑን ለማሳየት እሞክራለሁ። ይህንን የትግራይ ክልላዊ መንግሥትን ውሳኔ በሕገ መንግሥቱ መስፈርት ገምግሜ ትክክለኛ አካሄድ ነው ወይስ አይደለም ብዬ ለመከራከር እንዲረዳኝ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 50፣ 51 ፣ 52፣ 55፣ 62፣ 102፣ እንዲሁም ከምርጫና የፖሊቲካ ፓርቲዎች ዓዋጅ ቁጥር 3፣ 4፣ 12፣ 13፣ 14፣ 19 እና 47ን ዋቢ አድርጌ ለማቅረብ እሞክራለሁ።
ለመንደርደርያ ያህል፣ በኔ ግምት በአገራችን ስለ ፌዴሬሽን ያለን ግምት እንደምንወክለው ማህበረሰብና አስተሳሰብ የተለያየ ነው። ፌዴራሊዝም በጣም ውስብስብ ያለ የአስተዳደር ሥርዓት ነው። በውስጡ የተለያየ የማህበረሰብ አመሠራረትና አስተዳደር ታሪክ የነበራቸውን ሕዝቦች አንድ ላይ አቅፎ በአንድ ሕገ መንግሥት ሥር የሚያስተዳድር ሥርዓት ነው። የፌዴራሉ አባላትም አስቀድሞ ከነበራቸው ወይም ሊኖራቸው ከሚገባው የግዛታቸውና የሕዝባቸው ሏዓላዊነት ላይ የተወሰነውን ክፍል በገዛ ፈቃዳቸው ቀንሰው ለጋራ ጥቅም ሲባል አንድ የፊዴራል ሕገ መንግሥት ደንግገው በሱ ይተዳድራሉ። የግል ሏዓላዊነትን በገዛ ፈቃድ ቀንሶ ከሌላ አካል ጋር በጋር ለመኖር የሚወሰነው፣ የአብሮነት ሕይወት የተሻለ ነው ከሚልና ያለኝን ትርፍ አካፍዬ ከሌላው የፌዴራሉ አባል ደግሞ የጎደለኝን አሟላለሁ ከሚል ተስፋ ነው። ስለዚህ፣ የፌዴሬሽን መሠረቱ በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረት አብሮነት ማለት ነው። በገዛ ፈቃድ የተቀነሰውን ሏዓላዊነትን ግን መልሶ ለማግኘት የሚቻለው የሌሎቹ ጥቅም እስካልተነካ ድረስ ብቻ ነው። የሁሉንም የፌዴራሉን አባላት ጥቅም ደግሞ የሚያስጠብቀው የፌዴራሉ ሕገ መንግሥት ስለሆነ፣ እሱን መገዳደር ማለት የሌሎችን የፌዴራሉን አባላት ጥቅም መንካት ማለት ነው። ዛሬ ሕወሓት ካቀረበው መገዳደር በኋላ ግን አብሮነቱ ራሱ ትልቅ ጥያቄ ውስጥ ይገባል። ይህንን የሕወሓትን ድርጊት የሚስተዋሉ ሌሎች የፌዴራሉ አባል ክልሎችም ተመሳሳይ እርምጃ ወስደው የፌዴራል ሥርዓቱን ሕልውና አደጋ ላይ ሊጥሉት ይችላል የሚል ሥጋት ባገራችን ሰፍኗል ቢባል የተጋነነ አይመስለኝም። አግባብ ያለው ሥጋት!
የፌዴራል ሕገ መንግሥቱ ካስቀመጠው ውጪ፣ የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ብሔራዊም ሆነ ክልላዊ ምርጫ ማካሄድ ይችላል ወይ ለሚለው ጥያቄ መልሱ፣ አዎ ይችላል ነው። ድርጊቱ ግን ሕጋዊ ነው ወይ አይደለም ከተባለ ግን መልሱ የማያወላውል “ሕጋዊ አይደለም” ነው። መቻልና ሕጋዊነት የተለያዩ ነገሮች ናቸው። አንድ ሽጉጥ የታጠቀ ግለሰብ ሌላውን ሊገድል ይችላል፣ ያን የማድረግ ችሎታው ግን ከወንጀለኝነት አያድነውም። ስለዚህ ሕወሃት ዛሬ በክልሉ ብሔራዊውንም ሆነ የክልሉንም ምርጫ የማካሄድ አቅምም ልምድም አለው። ግን ድርጊቱ ሕገ መንግሥቱ ለፌዴራል አባላት ካስቀመጣቸው ሥልጣን በላይ ስለሆነ ጸረ ሕገ መንግሥት ነው። (የሚገርመው ደግሞ ሕወሃት፣ ከሌሎች ስምንት የፌዴራሉ አባላት በበለጠ ይህንን ሕገ መንግሥት እንደሚመቸው አድርጎ ጠፍጥፎ የሠራውና የተዋደቀለት መሆኑ እየታወቀ፣ ዛሬ ላይ በኢህአዴግ ውስጥ የፊታውራሪነት ሚናውን ስለተነጠቀና ራሱን ከድርጅቱ ስላገለለ ብቻ፣ ሕገ መንግሥቱን የመጣስ እርምጃ እወስዳለሁ ማለቱ ነው)። የዚህ ዓይነቱን ሕገ ወጥ መሆኑን እያወቁ ሕግ የሚጥሱትን የመንግሥት ድርጊት እያዩ ነው ለካ አንዳንድ የፖሊቲካ ድርጅቶችም “የፖሊቲካ ሥልጣን መያዝ የሚቻለው በሕዝባዊ ምርጫ ብቻ ነው” የሚለውን የሕገ መንግስቱን ድንጋጌ እያወቁ በመጣስ “ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ያቀፈ የሽግግር መንግሥት ያስፈልጋል” እያሉ በአደባባይ የሚለፍፉት። የሕገ መንግሥቱ ጋሻ ጃግሬ የሆነው መንግሥት ራሱ ሕገ መንግሥቱን ሲጥስ፣ እኛስ ለምን አንጥስም ከሚል የመነጨ ይመስላል። ውሻ በቀደደ ጅብ ይገባል እንደሚሉት ነው።
ወደ ቁም ነገሩ እንመለስና፣
ከላይ ባጭሩ እንደ ጠቀስኩት፣ የፌዴራሉ አባላት በሆኑ ዘጠኝ ክልሎች ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ ምንም እንኳ የዲሞክራሲን መስፈርት የማያሟላ ቢሆንም፣ በ1995 ዓ/ም “በተወካዮቻቸው” በኩል የፌዴራል ሕገ መንግሥቱን አጽድቀዋል። ሕገ መንግሥቱም በየክልላቸው ውስጥ ከሚያወጧቸው ሕገ መንግሥታት የበላይ መሆኑን አምነው መቀበላቸውንም
በፊርማቸው አረጋግጠዋል። በፌዴራል መንግሥቱና በክልል መንግሥታት መካከል ስለሚኖራቸው ግንኙነት በግልጽ ሲያስቀምጡ “በሕገ መንግሥቱ ለፌዴራሉ መንግሥት በተለይ ወይም ለፌዴራሉ መንግሥትና ለክልሎች በጋራ በግልጽ ያልተሠጠ ሥልጣን የክልል ሥልጣን ይሆናል” የሚለውን አንቀጽ 51 አካትተዋል። አንዳንዶች “ሕዝቡ ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብት አለው” ሲባል ፌዴራል ሕገ መንግሥቱን እንኳ አሻፈረኝ ለማለት ይቻላል ብለው “ሲተነትኑ” ይሰማል። አዎ! በመሠረቱ የኢትዮጵያ ሕዝቦች (ብሄር፣ ብሄረ ሰብ ሕዝብ) የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን መብት አላቸው ሲባል፣ ሕገ መንግሥቱ በፈቀደው መሠረት ብቻ እንደሆነም አብሮ መታየት አለበት። የተለያዩ ሕዝቦች ፌዴራል ኢትዮጵያን ሲመሠርቱ፣ ከላይ እንዳልኩት የሕዝባቸውን ሏዓላዊነት በተወሰነ ደረጃ ቀንሰውት ነው። በዚህም ምክንያት፣ የፌዴራል መንግሥቱ አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ያለ ክልል መንግሥታት ፈቃድ በክልሉ ውስጥ ጣልቃ ሊገባ ይችላል። ለምሳሌ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 55(16) በተጠቀሰው መሠረት፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “በማንኛውም ክልል ሰብዓዊ መብቶች ሲጣሱና ክልሉ ድርጊቱን ማቆም ሳይችል ሲቀር፣ በራሱ አነሳሽነትና ያለ ክልሉ ፈቃድ ተገቢው እርምጃ እንዲወስድ ለፌዴራል ምክር ቤትና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጋራ ስብሰባ ጥያቄውን አቅርቦ በተደረገበት ውሳኔ መሠረት ለክልሉ ምክር ቤት መመርያ የመስጠት ሥልጣን አለው። የክልል መንግሥታትም ይህንኑ አምነው ተቀብለው፣ በሕገ መንግሥታቸው ውስጥ “የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሕገ መንግሥት የበላይነት እንደ ተጠበቀ ሆኖ……..” የሚለውን ሓረግ ሲያካትቱ፣ የክልላቸውን ሥልጣን ከፌዴራሉ ያነሰና ለፌዴራሉ ሕገ መንግሥት ተገዢ መሆናቸውን ለማሳየት መሆኑን ከሁሉም ክልሎች ሕገ መንግሥታት መረዳት ይቻላል።
ብሄራዊ ምርጫን በተመለከተም የፌዴራሉ ዓዋጅ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ሥልጣን እና ተግባርን አስመልክቶ አንቀጽ 102(1) “በፌዴራልና በክልል ምርጫ ክልሎች ነጻና ትክክለኛ ምርጫ በገለልተኝነት እዲያካሄድ ከማናቸውም ተፅዕኖ ነጻ የሆነ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ይቋቋማል” ሲል ብሄራዊ ምርጫን ለማካሄድ የሚችለው የምርጫ ቦርድ ብቻ ነው ማለት ነው። ይህ ሥልጣን በግልጽ ለፌዴራል መንግሥቱ የተሠጠ ስልሆነ ለክልሎች ሌላ ምንም ቁራጭ አላስተረፈም። የኢትዮጵያ የምርጫና የፖሊቲካ ፓርቲዎች ዓዋጅን ተፈጻሚነትን ሲያስረዳ “በኢትዮጵያ ውስጥ በሚደረግ ጠቅላላ ምርጫ እንዲሁም እንደ አግባቢነቱ የአካባቢ ምርጫ፣ የማሟያ ምርጫና የድጋሚ ምርጫ በሕገ መንግሥቱ መሠረት በሚካሄድ ሕዝበ ውሳኔ ላይ ተፈጻሚ ይሆናል” (ቁጥር 3/1) ማለቱ ይህንኑ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ በግልጽ የተቀመጠውን የምርጫ ቦርድ ሥልጣን እና እነዚህን ሁሉ ምርጫዎች የማካሄድ ሥልጣን ያለው ብሔራዊው የምርጫ ቦርድ ነው ብሎ በጥብቅ ለማሳሰብ ነው።
በየክልሉ የምርጫ ክልሎችንና የምርጫ ጣቢያዎችን የማቋቋምና በያንዳንዱ ክልል የቦርዱን ጽ/ቤት የማቋቋም፣ ራሱ በሚያወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ዕጩዎችን ሳይቀር የመመዝገብ ኃላፊነት (ሥልጣን) የተሠጠው ለምርጫ ቦርድ ብቻ ነው። (ቁጥር 12/2)። በዓዋጁም መሠረት ለምሳሌ፣ “የጠቅላላ ምርጫ ምዝገባ በአገር አቀፍ ደረጃ ቦርዱ በሚወስናቸው ቀናት የሚጀመርና የሚጠናቀቅ ይሆናል”። (ቁጥር 19(1)። ከዚህም በተጨማሪ፣ ልዩ ሁኔታ ሲያጋጥምና የተለየ የምዝገባ ቀን መወሰን አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ የመወሰን ሥልጣን የተሠጠው ለብሔራዊው የምርጫ ቦርድ ነው። (ቁጥር 19/3)። በዓዋጁ ቁጥር 47/1 እና 47/2 መሠረት “የድምፅ መስጠት ሂደት በሁሉም ምርጫ ጣቢያዎች ቦርዱ በሚወስነው ቀን አንድ ላይ የሚጀመር” መሆኑን እና፣ “አስገዳጅ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ የሚመለከታቸው ምርጫ ጣቢያዎች ሥራቸውን በተለየ ቀን እንዲጀምሩ ቦርዱ ሊወስን ይችላል” ይላል።
እነዚህ ከላይ የጠቃቅስኳቸው የሕገ መንግሥቱ አንቀጾችና የምርጫና የፖሊቲካ ድርጅቶች ዓዋጅ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ሥልጣንና ተግባራት በግልጽ ያሳያሉ ብዬ የመራረጥኳቸው ናቸው። በግሌ በሕገ መንግሥቱም ሆነ በዓዋጁ ውስጥ ቦርዱንና ሥልጣኑን በተመለከተ አንዳችም ክፍተት አላይባቸውም። በርግጥ በክልል ሕገ መንግሥቶች ውስጥ “የክልሉ ሕዝብ የበላይ ሥልጣን ባላቤት ነው፣ የሕዝቡ የበላይነት የሚገለጸው በሚመርጣቸው ተወካዮች ነው” እየተባለ የሏዓላዊነት መገለጫቸው የሆነውን ክልላዊ ምርጫ እንኳ የማካሄድ ሥልጣን እንዴት አልተሠጣቸውም የሚለው መሠረታዊ የፖሊቲካ ጥያቄ ቢኖርም፣ ከነዚህ ከጠቀሷቸው የክልል ሕዝቦች ሏዓላዊነት አስቀድሞ በያንዳንዱ የክልል ሕገ መንግሥት ውስጥ “የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሕገ መንግሥት የበላይነት እንደ ተጠበቀ ሆኖ” የሚል ዓረፍተ ነገር ማካተታቸው፣ የክልሎች ሏዓላዊነት አንጻራዊና ከፌዴራላዊው ሏዓላዊነት ዝቅ ያለ መሆኑን ለማሳየት ነው። ይህ እንግዲህ ራሱን የቻለ የፊዴራሊዝም ሥርዓት አንደኛው መገለጫ ጠባይ ስለሆነ ማስተካከል የሚቻለው በፖሊቲካዊ ውሳኔ ብቻ ነው። ያ እስኪሆን ድረስ ግን አሁን ከፊታችን ለተደቀነው የክልሎችና የፌዴራል መንግሥቱ ሥልጣንን በተመለከተ መወያየት የምንችለው በፌዴራሉ ሕገ መንግሥት መነፅር ብቻ መሆን አለበት። የፌዴራሉ አባል የሆኑት ክልሎች ከዛሬ ኸያ አምስት ዓመት በፊት በፈቃዳቸውም ሆነ ዓቅም በማጣት ብቻ ተገደው የተስማሙበትን ወይም እንዲስማሙበት የተገደዱበትን የፖሊቲካ ጉዳይ አንስቶ ዛሬ ለሕጋዊ ውይይት ማቅረቡ አይታየኝም። ቢያቀርቡም ለችግሩ መፍትሔ አይሆንም። ሕገ መንግሥቱም ሆነ የምርጫና ፖሊቲካ ፓርቲዎችም ዓዋጅ በማያሻማ ሁኔታ ብሄራዊ ምርጫን ማካሄድ ባለ ሥልጣኑ የምርጫ ቦርድ ብቻ ስለሆነ ዛሬ የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ከምርጫ ቦርድ ዕውቅና ውጭ የክልሉን ምርጫ ማካሄድ ሕጋዊ አይደለም።
እንደው በቅንፍ ውስጥ የሚከተለውን ልጨምር፣
በኔ ግምት፣ የትግራይ ክልላዊ መንግሥት (ሕወሓት) ምርጫን የማካሄድ ሥልጣን ያለው ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ መሆኑ ጠፍቷቸው አይመስለኝም። ሕገ መንግሥቱን ከመጀመርያው ጀምሮ እስከ መጨረሻው ማለትም ከማቡካት እስከ መጋገር ድረስ ሂደቱን በጠቅላላ ለሱ እንደሚጥመው አድርጎ ይመራ ስለነበር፣ ዛሬ ሁኔታዎች ስለ ተቀየሩ ብቻ ትናንት “የተነጠረና ተወዳዳሪ የሌለው ሕገ መንግሥት” ብለው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያቀረቡትን ዛሬ ራሳቸው ሊጥሱት ሲሞክሩ ማየት፣ የኢትዮጵያ ፖሊቲካና የፖሊቲካ ሥልጣን ያላቸው አካላት አንድን ሕግ ወይም ሕገ መንግሥት ሲያስጸድቁ ለራሳቸው ሥልጣን ላይ መቆያ እንጂ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በጎ ከማሰብ እንዳልሆነ ይህ የሕወሓት ሙከራ ዓይነተኛ መገለጫ ነው።
ለውይይት መነሻ ያህል በቂ መሰለኝ። እስቲ ባለሙያዎች ደግሞ አክሉበትና በተቻለ መጠን ሕወሓት ከዚህ የተሳሳተ አካሄድ ራሱን እንዲገታ ሙያዊ ምክር እንለግስ። እንዳልኩትም አካሄዳቸው የተሳሳተ መሆኑ ጠፍቷቸው ባይሆንም፣ ይህንን የተሳሳተ አካሄዳቸውን “እኛ ሕዝቦች” በውል እንደምንረዳ እንዲያውቁት ለማለትም ያህል ነው
****
ጄኔቫ፣ ሜይ 20 ቀን 2020 ዓ/ም