May 24, 2020
52 mins read

የመርህ  አልባነት ፖለቲካችንና አስከፊ ውጤቱ – ጠገናው ጎሹ

ጠገናው ጎሹ

  • ሩብ ምዕተ ዓመት ሙሉ በህዝብ መብትና በአገር ደህንነት ስም እየማለና እየተገዘተ በንፁሃን ዜጎች   ላይ  የመከራና የውርደት መዓት (ዶፍ) ሲያወርድ የኖረውንና በጎሳ/በነገድ/በቋንቋ አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ  ላይ የተመሠረተውን ሥርዓተ ኢህአዴግ በበላይነት ሲዘውሩና ሲቆጣጠሩ በኖሩት  ጨካኝና ባለጌ የህወሃት ቁንጮዎች፣ እና ከሁለት ዓመታት ወዲህ  ደግሞ በአስከፊ የፖለቲካ ወለድ ወንጀል የተዘፈቀ   ማንነታቸውን እንደተከናነቡ  ለእራሳቸው ብልፅግና የሚል የለየለት የማጭበርበሪያ ስም  በመስጠት በመከረኛው የአገሬ ህዝብ ላይ በሚቀልዱ ሸፍጠኛና ሴረኛ የገዥ ቡድኖችና ግብረ በላዎቻቸው ምክንያት
  • በህወሃት አሳዳጊነት፣ አሠልጣኝነት፣ አደራጅነትና የህልውና እስትንፋስ ሰጭነት የድርጅትነት ቅርፅና ስያሜ ተሰጥቷቸው ሲያስፈልግ እንደ ደመ ነፍሱ አጋሰስ ሲጭኗቸው እና ሲያስፈልግ ደግሞ የጦር መሣሪያ አስታጥቀው በገዳይነትና በአስገዳይነት ሲያሰማሯቸው  በነበሩና አሁን ደግሞ ለውጥ መጣ ሲባል ተደናግጠው መቀሌ ውስጥ የተወሸቁትን የህወሃት ፖለቲከኞች በተረኝነት የመተካት   ቅዠት ውስጥ ለሚገኙት የኦዴፓ/ ኦነግ ፖለቲከኞች  በለመደባቸው የአሽከርነት ሥራና ደረጃ ምድብ ለመቀጠል ፈቃደኛ በሆኑት ብአዴኖች/አዴፓዎች/የአማራ ብልፅግናዎች እና ደህዴኖች/ የደቡብ  ብልፅግናዎች ምክንያት
  • ሸፍጠኛ ፖለቲከኞችን ፍላጎትና ትእዛዝ እየተቀበሉ የህግ የበላይነትንና የፍትሃዊነትን መሠረታዊ ምንነትና እንዴትነት በአፍ ጢሙ እንዲደፋ ባደረጉ (በሚያደርጉ) የጠቅላይ ፍርድ ቤት የበላይ ሃላፊ (ፕረዝደንት) ፣ጠቅላይ አቃቤ ህግ/  አቃቤ ህግ ፣ ዳኛና  የህግ ባለሙያ ተብየዎች ምክንያት ፣ 
  • እንወክለዋለን የሚሉትንና የኖሩበትን ወይም ያደጉበትን ማህበረሰብ ፍላጎትና ጥቅም ጨርሰው በማያውቁና የቀረበላቸውን ሁሉ እጅ አውጥቶ ከማሳለፍ ውጭ ማሰብ በማይችሉ ደናቁርትና ህሊና ቢስ   የፓርላማ (የህግ አውጭው አካል  አባላት) ተብየዎች ምክንያት
  • መከረኛው ህዝብ ለአያሌ ዘመናት የመከራና የውርደት ቀንበር ተሸካሚ ሆኖ የኖረው የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥን እውን ለማድረግ አለመቻላችን  የመሆኑን መሪር እውነት አሳምሮ ማወቅ ብቻ ሳይሆን  በሰብአዊ መብት ተሟጋችነት፣ በተቀዋሚ የፖለቲካ ድርጅት መሪነት እና በህግ ወይም በሌላ የሙያ ባለቤትነት እውቅና እና አድናቆት ተችሯቸው የነበሩ ወገኖች   በፖለቲካ ወለድ ወንጀል የበሰበሰውና የከረፋው ኢህአዴጋዊው /ብልፅግናዊው ሥርዓት እንደ ሥርዓት በቀጠለበት መሪር ሃቅ ውስጥ የተሻለ የሚመስል የጉልቻ ለውጥ ስለታየ ብቻ የመከራና የውርደት ማስፈፀሚያ በሆነው ሰነድ (ህገ መንግሥት ተብየ) እጃቸውን አንስተው እየማሉ እንደ ምርጫ ቦርድና የሰብአዊ መብት ኮሚሽን የመሰሉ  ተቋማት “መሪዎች” በመሆን   እራሳቸውን ወደ የሸፍጥና የሴራ ፖለቲካ ጨዋታ አጃቢነት  በማውረዳቸው ምክንያት
  • ከግላቸውና ከቡድናቸው ፍላጎትና ጥቅም በላይ አልፎ መሄድ  በተሳናቸው ፣ የሥርዓት  ለውጥ ጥያቄን በአፍጤሙ በደፉ እና  በፖለቲካ ወለድ ወንጀል የበሰበሰውና የከረፋው ሥርዓት ጥርሱን ነቅሎ ያሳደገው ፖለቲከኛ (ካድሬ) በተሃድሶ ስም “የዴሞክራሲያዊ ሽግግር አሻጋሪ ነኝ” የሚል ሸፍጠኛ ዲስኩር ስለደሰኮረላቸው  እግሩ ሥር በተንደፋደፉ (በሚንደፋደፉ) አሳፋሪ የተፎካካሪ ፖለቲካ መሪ ተብየዎች ምክንያት
  • ሳይወክላቸው ወክሎናል በሚሉት ጎሳ/ ነገድ/ ብሄረሰብ ስም የፖለቲካ ሥልጣን መዘውሩን በመቆጣጠር   እኩይ የግልና የቡድን ፍላጎታቸውን (ጥቅማቸውን) ለማርካት ሌት ተቀን በሚቃዡ (በሚቅበዘበዙ) የጎሳ/የቋንቋ አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ልክፍተኞች ምክንያት
  • ስለዴሞክራሲና ስለአገራዊ (ስለዜግነት) ፖለቲካ ተመሳሳይ ቋንቋ እየተናገሩ ልክ በሌለው የግልና የጎጥ የሥልጣን ፍላጎት(ጥም) ሊያስገኝልን ይችላል በሚሉት ክፉ ቅዠት በመጠመዳቸው ተለያየተው በመውደቅ አባዜ በተለከፉ የአንድነት ሃይል ነን ባይ ፖለቲከኞች ምክንያት፣
  • ሁለንተናዊ ሰብአዊ ክብርንና የተሟላ አገራዊ ኩራትን እውን ለማድረግ ከሚያስችለው መሠረታዊ የሃይማኖትና የገሃዱ ዓለም መርህ ላይ ፀንቶ መቆም ተስኖቸው ከክስተቶች ትኩሳት ጋር በመነሳትና በመውደቅ  ወደ ተግባር ለመተርጎም የማይችሉትን (የማይደፍሩትን) የፖለቲካና የፍልስፍና ትርክት ወይም የትንታኔ ድሪቶ በሚደርቱ ምሁራን (ልሂቃን)  ተብየዎች ምክንያት
  • እውነተኛው የመማር ትርጉምና እሴት (essence and value) ህብረተሰብ የሚያጋጥሙትን የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ውስብስብ ፈተናዎች (natural and man-made challenges and catastrophes)  በእውቀት ፣ በክህሎትና በፈጠራ  ላይ ተመሥርቶ ተገቢና ወቅታዊ መፍትሄ የመፈለግና የማስገኘት መሣሪያነቱ መሆኑን ዘንግቶ ጨካኝ የጎሳ/የነገድ/የብሄረሰብ/የቋንቋ አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ገዥ ቡድኖችና ፖለቲከኞች ሰለባ በሆነው ፣ የገንዛ እራሱን መልካም እጣ ፈንታ ደጋግሞ ባበላሸውና አሁንም ከዚህ ክፉ አዙሪት ለመውጣት ከሚጠበቅበት ጥረት (ትግል) አንፃር በእጅጉ በመልፈስፈስ ላይ በሚገኘው ፊደል ቆጣሪ (ወጣት ተማሪ) ምክንያት፣
  • በኢትዮጵያ የነፃነትና የፍትህ ሥርዓት እውን  ይሆን ዘንድ እጅግ ጉልህ ድርሻ የነበራቸውን የሙያና የሠራተኛ ማህበራትን (አንጋፋዎቹን የኢትዮጵያ መምህራን ማህበርንና የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማህበርን ልብ ይሏል)  የሸፍጠኛ፣ ሴረኛና ጨካኝ የገዥ ቡድኖች ርካሽ የፖለቲካ መሣሪያዎች ባደረጉና ህሊና ቢስ በሆኑ ወይም ከደመነፍሱ አጋሰስ በማይሻሉ  ወገኖች ምክንያት
  • በስሚታዊነት ከመጋለባቸው የተነሳ ሥርዓት ሳይሆን ግለሰብ “መሪዎች”  ስለተቀየሩና  ሸፍጠኛ ዲስኩራቸውን (ስብከታቸውን) በሰላ አንደበታቸው ስለአዥጎደጎዱላቸው “የዘመናችን ሙሴዎች” ብለው እስከማምለክ በደረሱና  እንዳሰቡት ሳይሆን ሲቀር ደግሞ  ሰበብ በመደርደር ከህዝብ አደባባይ (መድረክ) መጥፋታቸው (መሰወራቸው) አልበቃ ብሏቸው “በዚህ በኮሮና ቫይረስ ወቅት ስለሸፍጠኛና ሴረኛ የኢህአዴግ/ የብልፅግና ፖለቲከኞች የፖለቲካ ክርፋት አትናገሩ ወይም መናገር ነውር ነው” ሲሉን  ጨርሶ  ሃፍረት በማይሰማቸው አክቲቪስት ተብየዎች ምክንያት
  • ቅኔ መቀኘታቸውን (መዝረፋቸውንና መደርደራቸውን)   እንጅ  ቅኔው  ለምን? ለማን? እንዴት? ከየት? እና ወዴት ? የሚል ግንዛቤ ጨርሶ የሌላቸው ወይም ሊኖራቸው በማይፈልጉና ነገር ግን  ዙፋን ላይ የወጣውን ሸፍጠኛና  ባለጌ ፖለቲከኛ  ሁሉ በሚያንቆለጳጵሱ ባለቅኔ  ወይም ሊቅና ሊቀ ሊቃውንት  ተብየዎች ምክንያት
  • ለውጥ መጣ በተባለ ቁጥር ግልቡን ስሜት እየኮረኮረ ዳንኪራ የሚያስረግጥ ወይም በአንዳች አይነት ጊዜያዊ ተመስጦ/ቁዘማ ውስጥ የሚያቆይ ሙዚቃ መሞዘቃቸውን እንጅ ለምንና እንዴት እንደሚሞዝቁት በእውን በማያውቁ ወይም ማወቅ በማይፈልጉ ሙዜቀኞች ወይም ”የኪነ ጥበብ ሥጦታዎች ነን” ባዮች ምክንያት
  • ከሸፍጠኛና  ሴረኛ ፖለቲከኞች ጋር እየተላላሱ ከተቻለ በፍፁም ድህነት ውስጥ በሚማቅቅ ህዝብ መካከል ወፍራም ኑሮ ለመኖርና  ካልሆነ ደግሞ የእለት ተእለት ጉርስን ለማሸነፍ በሚደረግ እንስሳዊ  ግብግብ  ከሸፍጠኛና ባለጌ ፖለቲከኞች እግር ሥር ጭራቸውን  በሚቆሉ ምሁራንና የልዩ ልዩ ሙያ ባለቤቶች ነን ባዮች  ምክንያት
  • ዙፋን ላይ ከወጣው ባለጌ፣ ሙሰኛና ሸፍጠኛ ፖለቲከኛ ጋር በመሞዳሞድ ወይም በመሻረክ ወይም በመገላበጥ “በተአምራዊ ባለሃብትነት” ማዕረግ በተንበሻበሹ (በሚንበሻበሹ)  ባለሃብት ተብየዎች ምክንያት  
  • ከድርብ (ከምድራዊውና ከሰማያዊው) ተልእኳቸው አንፃር መሆን ያለባቸውን  ሆነውና ማድረግ ያለባቸውን  አድርገው መገኘት ተስኗቸው ከክስተቶችና መንበረ ሥልጣኑን ከሚቆጣጠረው ሸፍጠኛና ሴረኛ ፖለቲከኛ ጋር  በሚነሱና  በሚወድቁ  የሃይማኖት መሪ /አስተማሪ /ሰባኪ/  ተብየዎች  ምክንያት
  • “ተምረነዋል ወይም ተክነንበታል” በሚል የሚያነበንቡትን መነባንብ እና ከየመፅሃፉ (ከየፅፉ) እና ከየመንደሩ የሚለቃቅሙትን ተረትና ምሳሌ በሰላ አንደበታቸው እያቀነባበሩ የፖለቲካው ሥልጣነ መንበር (የቤተ መንግሥት) “የሥጋና የነፍስ አማካሪ” በመሆን የሚያማክሯቸው ጠቅላይ ሚንስትርና መሰሎቻቸው “የኢትዮጵያ ስም በተጠራ ቁጥር ከፍቅራቸው የተነሳ በእንባ ጎርፍ እንደሚጥለቀለቁ” የሚነግሩንን መሬት ላይ ከሆነውና እየሆነ ካለው ግዙፍና መሪር ሃቅ ጋር ለማገናዘብ የማንችል ደንቆሮ ፍጡሮች  መስለን በምንታያቸው አደገኛ  አድር ባይና  አሳሳች ሙሃዘ ጥበባት ተብየዎች  ምክንያት
  • መከረኛውን ህዝብ እየተፈራረቁ የመከራና የውርደት ዶፍ የሚያወርዱበትን ግፈኛና ባለጌ ገዥ ቡድኖች እንደ ታላቁ መምህር እንድ ክርስቶስና እንደ እውነተኛ ደቀ መዝሙሮቹ (ተከታዮቹ) “እጃችሁንና ሰይፋችሁን ከንፁሃን ህዝባችን ላይ አንሱ!” ለማለት ወኔው ጨርሶ ሲከዳቸው ግራ የተጋባውን መከረኛ ህዝብ በየአጋጣሚውና በየአደባባዩ “ፈጣሪ ያወረደብህ ቅጣት (መዓት) ነውና እግዚኦ ከማለት ውጭ ሌላ መውጫ የለህም” በሚል እጅግ  በኮሰመነ የማስተማር ልማድና ሥልት    ፈጣሪን ጨካኝ ፣የዋሁንና ሠርቶ አዳሪውን የአገሬን ህዝብ ደግሞ ፈጣሪን ከሃዲ የሚያስመስል የስብከት ውርጅብኝ በሚያወርዱ ሰባኪ፣ ባህታዊ፣ መምህር  ፣ ትንቢተ ተናጋሪ፣ ፈዋሽ (ተአምረኛ)፣ ወዘተ ተብየዎች ምክንያት፣  እና
  • በአጠቃላይ እንደ ነፃነትና ፍትህ ፈላጊ ማህበረሰብ ወይም ትውልድ ከመከፋፈል ይልቅ  በአብሮነት የሃሳብ ልዩነትንና ፍጭትን በሰለጠነ አቀራረብ የሚያስተናግዱ የክስተቶችንና የሸፍጠኛ መሪዎችን/ፖለቲከኞችን የፖለቲካ ትኩሳት እየተከተሉ በስሜት ከመጋለብ ይልቅ  ፅዕኑና ዛላቂ የሆነ በጎ ተልእኮን ወይም ዓላማን እውን ለማድረግ የግድ የሚሉ እና የነፃነት፣የፍትህና የጋራ ብልፅግና  የተረጋገጡባት የጋራ አገር  ለመመሥረት የሚያስችሉ  የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መርሆዎችን (fundamental democratic prinples) ከዲስኩር ወይም ከመነባንብ ወይም ከንግግር ማድመቂያነት ወይም ከመንበረ ሥልጣን የሚገኘውን ርካሽ የግልና የቡድን ፍላጎትን/ጥቅምን እውን ከማድረግ ያለፈ በእውነተኛው ትርጉማቸውና መሣሪያነታቸው አናውቃቸውም።

ለዚህ ነው ባለጌና ጨካኝ ገዥ ቡድኖች ሲፈልጉ በሃይል፣ ሲያሻቸው ደግሞ በተሃድሶ ስም ስያሜና የአደረጃጀት ቅርፅ እየለወጡ (ኢህአዴግን ብልፅግና እያሉ) በዴሞክራሲ ስም የመከራና የውርደት ሥርዓታችውን ለ50/60 ዓመታት ለማስቀጠል እንደተዘጋጁ ያለምንም ሃፍረት ወይም ማን አለብኝነት የሚነግሩን።

 

ቅንና ትልቅ ልቦና ላለው የአገሬ ሰው በእጅጉ ልቡን የሚያደማው አሁንም ዴሞክራሲንና መርሆዎቹን ለሸፍጥ ፖለቲካ ካባነት ካልሆነ በስተቀር መሬት ላይ አውርደን ህይወት እንዲዘሩ ማድረግ አለመቻላችን ነው።  አዎ! ከቃል ዲስኩርና ከወረቀት ላይ ድርሰትነት  ያለፈ ፅዕኑና ዘላቂ  ዴሞክራሲያዊ መርህ ላይ መቆም አልሆንልን ብሏልና የሚሻለው መሪሩን ሃቅ እየመረረም ቢሆን ተገንዝቦና ተቀብሎ ሳይውሉ ሳያድሩ ተገቢውን (ገንቢውን) እርምትና እርምጃ መውሰድ ነው።  አዎ! መሪሩን ሃቅ በቁርጠኝነትና በዘላቂነት በመጋፈጥ  በፖለቲካ ወለድ ወንጀል የተዘፈቀውና ግዙፍና መሪር ዋጋ የተከፈለበትን  የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ ወጋገንን መልሶ ያጨለመውን (ያኮላሸውን) ሥርዓተ ኢህአዴግን/ብልፅግናን በተገቢው የፖለቲካ ጨዋታ ማስወገድ  ሳይሆን የሸፍጥና የሴራ ተሃድሶው አካል/አጃቢ/ልጣፍ በመሆን  እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት  እንዲወለድ እናደርጋለን ብሎ ከመጠብቅ የከፋ (የባሰ) መርህ አልባነት ጨርሶ የለም።

የዛሬ ሁለት ዓመት ለመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ እውን መሆን የተመቻቸልንን ወርቃማ ሁኔታ (እድል) ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን በፖለቲካ ወለድ አስከፊ ወንጀል ተዘፍቀው የኖሩበትን ሥርዓተ ኢህአዴግ በተሃድሶ ስም “ሥርዓተ ብልፅግና” ብለው በመሰየም “የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አሸጋሪዎች ነን” ለሚሉ ሸፍጠኛና ሴረኛ ፖለቲከኞች/ካድሬዎች አሳልፈን በመስጠታችን  ይኸውና በአሁኑ ወቅት በሁለት ክፉ ቫይረሶች (ኮቪድ-19 እና የፖለቲካ ቫይረስ)  መካከል ሆነን የመከራና የጭንቅ መአልትና ሌሊት እንቆጥራለን።

ከሁለትና ከዚያም በላይ  አደገኛ የተፈጥሮም ሆነ ሰው ሠራሽ ፈተናዎች ሲገጥሙን ሁለቱንም በአንድ ላይና በተመጣጣኝ ሁኔታ ለመጋፈጥና ለማሸነፍ በእጅጉ ከባድ ስለሚሆን የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት የመስጠትና የጋራ ጥረት የማድረግ አስፈላጊነት አጠያያቂ አይደለም።አዎ ! እንደ ኮቪድ-19 ዓይነት የጎሳ፣የፖለቲካ፣የሃይማኖት፣ የክልል፣ የጎጥ፣ የፆታ፣የእድሜ፣ ወዘተ ማንነትን ሳይመርጥ አያሌ ዜጎችን ከመኖር ወደ አለመኖር በሚለውጥና ድሮውንም እጅግ ደካማ የሆነውን የሚሊዮኖችን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ህይወት ጨርሶ በሚያጨልም የቫይረስ ወረርሽኝ ላይ በመዝመት በአሸናፊነት ለመወጣት የሚደረገውን ጥረት ለመቀላቀል የፖለቲካና ሌላም ማንነት መመዘኛችን ከቶ መሆን የለበትም።

በሌላ በኩል ግን  ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን አያሌ ዜጎችን የቁም ስቃይና የሞት ሰለባዎች ያደረገውን እና የሚሊዮኖችን ህይወት ደግሞ ከሞቱት  የማይሻል ያደረገውን ህወሃት መራሽ ሥርዓትን ኦዴፓ/የኦሮሞ ብልፅግና/ኦነግ መራሽ በማድረግ እና በአገልጋይነት ልክፍት የተለከፉትን አዴፓዎችን/የአማራ ብልፅግናዎችን እና የደህዴንን/የደቡብ ብልፅግናዎችን በለመዱት እንዲቀጥሉ በማድረግ እየተካሄደ ያለውን እኩይና ርካሽ  (evil and cheap) የፖለቲካ ጨዋታን ከመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ የሥርዓት ለውጥ ግድ ባይነት አንፃር  ለመታገል ወይም ላለመታገል ኮቪድ-19ን እንደ ምክንያት (execuse) ማቅረብ መርህ አልባነት ብቻ ሳይሆን የፖለቲካና የሞራል ሰብእና ውድቀትም ነው።

የፅዕኑና ዘላቂ መርህ አልባነት አስከፊ ውጤት ያስከተለውና እያስከተለ ያለው የህመም ጥልቅትና ስፋት (intensive and extensive pain) የእያንዳንዱ መከረኛ የአገሬ ህዝብ ህመም ነው። አዎ! ከእኩይ እምነታቸውና ዓላማቸው የሚመመነጨውን እኩይ ተልእኳቸውን የቅድስና ካባ አጎናፅፈው “ከእኛ ወዲያ የዴሞክራሲ አሻጋሪነት ላሳር ነው” ሲሉን በፅዕኑና ዘላቂ የዴሞክራሲ መርህ ላይ ቆመን “ርካሽና በወንጀል የተጨማለቀ የፖለቲካ ጨዋታችሁ ይብቃችሁ” ለማለት የሞራልና የፖለቲካ ልዕልናው በእጅጉ ስለጎደለን  ከማማረርና ከማውገዝ (complain and decry) ያለፈ እርምጃ አልተራመድንም።ይህ መከረኛ ህዝብ አያሳዝንም?

ልክ በሌለው የግልና የቡድን ፍላጎት ልክፍት ምክንያት ከክስተቶች ትኩሳት ጋር እየሞቅንና እየቀዘቀዝን ባለመርህ የፖለቲካ ድርጅት ወይም ስብስብ ነን ማለት ጨርሶ ስሜት የሚሰጥ የፖለቲካ ምንነትና እንዴትነት የለውም። አዎ! በመግቢያነት  የጠቀስኳቸው አስከፊ ውድቀቶቻችን ዋነኛው  ምክንያት ይኸው ነው። የዴሞክራሲያዊ መርህ አስፈላጊነትንና ወሳኝነትን ወደ መሬት ጠብ የማይሉ የፖለቲካ ዲስኩሮቻችንና የትንታኔ ድሪቶዎቻችን  ማድመቂያ ከማድረግ በላይ የከፋ (የባሰ) የፖለቲካና የሞራል ኮስማናነት (ድህነት) የለም።

ለመሆኑ መርህ (principle) ስንል ምንና ለምን? መርህ እንደ ግለሰብ ወይም እንደ ማህበረሰብ ወይም እንደ  መንግሥታዊ ሥርዓት ወይም  መንግሥታዊ እንዳልሆነ  ተቋም (ድርጅት) ማሳካት የምንፈልጋቸው ሃሳቦች ፣ ተልእኮዎች (ዓላማዎች) ፣እቅዶችና  አፈፃፀሞች ትክክልና  ውጤታማ በሆነ  እምነትና እሴት (beliefs and values) ላይ  መመሥረታቸውን የሚገልፅ  ጥልቅና ሰፊ ፅንሰ ሃሳብ ነው።  መርህ በህይወታችን ሂደት ውስጥ ልናከናውን  የምንፈልገው ቁም ነገር (ተልእኮና ዓላማ)  ፀንቶ  የቆመበት ወይም የሚቆምበት መሠረትና  ቃል ኪዳን (foundation and covenant)  ነው ። መርህ የተፃፈ ወይም ያልተፃፈ የዓላማችን/የግባችን፣ የሃሳባችን፣ የአመለካከታችን፣ የእቅዳችን ፣የአካሄዳችንና የአፈፃፀማችን መፈተሻና  ማመሳከሪያ  (reference) ነው ።

እናም ዴሞክራሲያዊ  መርህ

  • በህዝብ ልኡላዊ እና ነፃ ምርጫ የሚመሠረትና የሚሠራ ሥርዓተ መንግሥት ባለቤት የመሆንን ፣
  • ሥልጣን በህዝብ ንቁ ተሳትፎና ድምፅ (ይሁንታ) ሰጭነት ብቻ የሚያዝ መሆኑን አምኖ የመቀበልን፣
  • በህዝብ ያልተገደበና ንቁ ተሳትፎ ሥራ ላይ የሚውልና የግድ የሚሉ ሁኔታዎች ሲከሰቱ ማሻሻያዎች ሊደረጉበት የሚችል  ህገ አገር ወይም በመንግሥትና በህዝብ መካከል ያለውን የመብትና የግዴታ ግንኙነት የሚወስን የቃል ኪዳን ሰነድ (covenant/constitution) ባለቤት የመሆንን ፣
  • በህይወት የመኖር ፍፁም መብትንና ነፃነትን የማረገጋገጥን፣
  • እንደ ዜጋ በገንዛ አገር ተዘዋውሮ በመኖርና በመሥራት ደስተኛ ህይወት (ኑሮ) የመኖርን፣
  • ከህግ በላይ ነን ወይም እንሆናለን የሚሉትን መሪዎች ወይም ባለሥልጣኖች ወይም ፖለቲከኞች ከህግ በላይ እንዳልሆኑ የማሳወቅና አሻፈረኝ ካሉም በሰላም ወደ ላይ ከወጡበት የሥልጣን መሰላል ተመልሰው እንዲወርዱ የማድረግን ፣
  • የፍትህና የእኩልነት መብቶችን የማረጋገጥን፣
  • የሰብአዊ መብቶችን የማረጋገጥና የመክበርን፣
  • የመናገርና የመፃፍ ወይም ሃሳን የመግለፅ መብትና ነፃነትን እውን የማድረግን፣
  • ልዩ ልዩ መብቶችን በተደራጀ መልኩ (ሁኔታ) የማስከበርን፣
  • የመልካም ዜግነት  ሃላፊነትን በተሟላ የነፃነት ስሜት የመወጣትን ፣እና
  • የኢኮኖሚና ማህበራዊ ህይወትን ከህልውና አልፎ የአስተማማኝና የሁለንተናዊ ደስታ ምንጭ እንዲሆን የማስቻልን  ግዙፍና ጥልቅ  ፅንሰ ሃሳቦችን የተሸከመ ፅንሰ ሃሳብ ነው ።

ይህ ፅንሰ ሃሳብ ከመሠረታዊው የሰው ልጅ መብት ጋር የተቆራኘ በመሆኑ ፖለቲካ ነውና እኔን ወይም እኛን አይመለከትም” የሚባልበት ጉዳይ ከቶ አይደለም።

ከዶግማዊ የእምነት አስተሳሰቦች/አመለካከቶች (religious dogma) በስተቀር የሃይማኖታዊ እምነት መርሆዎችም ከመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ መርሆዎች ጋር የመጣጣም እንጅ የመጋጨት ግንኙነት ጨርሶ የላቸውም።ፈጣሪም ሰውን ሲፈጥር ከነ ሙሉ ነፃነቱ ነው የፈጠረው። ከፈጠረው በኋላ ማድረግ ያለበትንና ለነፍሱም ሆነ ለሥጋው የሚበጀውን እንዲያደርግ እና የማይበጀውን እንዳያደርግ የሚረዱ መርሆዎችን በክርስቶስና በደቀ መዝሙሮቹ አማካኝነት እንዲያውቅ አደረገው እንጅ የሰጠውን ነፃነት ከነስህተቱም ቢሆን መልሶ አልነፈገውም። ይልቁንም ክፉና ደጉን የሚለይበትን እጅግ ረቂቅ አእምሮና ያሰበውን የሚከውንበትን ሙሉና ብቁ አካል ሰጠው እንጅ እንደ አቅመ ቢስ ፍጡር እየተልፈሰፈሰ ወይም ስንፍናን እያዳመጠ በትንሹም በትልቁም እግዚኦ! እያለ እንዲኖር ኦላዘዘውም ፤ በመልክተኞቹ አማካኝነትም  አላስተማረውም።

ሌላው ቀርቶ ምሥጢረ ሥላሴ የምንለው ረቂቅ ሃይማኖታዊ ምሥጢር ዝም ብሎ የሚነገርለት አየር ላይ ያለ ነገር ሳይሆን በገሃዱ ዓለም ያለው የአንድነትና የሦስትነት ግንኙነት የሚገለፅበትም ጭምር ነው። መልካም ወላጅና መልካም ልጅ እንደ ግለሰብነታቸው ሁለት ወይም ከዚያም በላይ ናቸው ። በመከካላቸው ያለውን መልካም ግንኙነት አጣብቆ የሚይዘው ደግሞ በእያንዳንዳቸው ውስጠ ነፍስ ውስጥ የሚገኘው ማንነታቸው/ምንነታቸው /አስተሳሰባቸው/ ፍላጎታቸው /እምነታቸው/እሴታቸው/ (spirituality) ነው። በአካል ሶስት ወይም ከዚያም በላይ ሆኖና በውስጠ ነፍስ (spiritualy) ተቆራኝቶ የጋራ ዓላማንና ፍላጎትን በተባበረ ተግባር እውን ከማድረግ የበለጠ የተቀደሰ ምንነትና ማንነት የለም። ይህ አይነቱ ጤናማ የልዩነትና የአንድነት መስተጋብር ከቤተሰብ አልፎ ማህበረሰባዊ፣ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ሲሆን ነው የፍቅር፣ የሰላምና የብልፅግና ትርጉም ስሜት ከመስጠት አልፎ የተሟላ የሚሆነው። እዚያ ለመድረስ ግን የየእራስን የቤት ሥራ ሠርቶ መገኘት የግድ ነው። እናም ጥያቄው እውን እኛ ወደ ዚያ ለመድረስ በሚያስችለን ፅዕኑና ዘላቂ መርህ ላይ ተገኝተን እናውቃለን ወይ? አሁንስ ? ነገስ? የሚልና እጅግ ፈታኝነት ያለው ነው።

ክስተትን እየተከተሉ መከረኛውን ህዝብ ሲፈልጉ “ምህረት መጣላህ” እና ሲያሻቸው ደግሞ “መዓት መጣባህ” እያሉ ግራ የሚያጋቡ ” የሃይማኖት  ሰባኪያን” እና ሸፍጠኛ ፖለቲከኞች እንደሚሉን አለመታደል ሆኖብን ሳይሆን ፈጣሪ የሰጠንን ረቂቅ አእምሮና ብቁ አካል ተጠቅመን  ለጋራ በጎ ነገር ለማዋል  በሚያስችል ፅእኑ መርህ ላይ መቆም ስለተሳነን/ስላቃተን  ይኸውና ኢህአዴጋዊያን ፖለቲከኞች ስምና የአወቃቀር ስልት እየቀየሩ ለዘመናት የዘለቁበትን ክፉ የፖለቲካ ቫይረስ ጥራሳቸውን ነቅለው ባደጉበት የሸፍጥ ፖለቲካ ስብከት እየሸፋፈኑ ማስኬዱን  ቀጥለውበታል።

ፍትህ ፣ ነፃነት ፣ግፍንና የሰብአዊ መብት ድፍጠጣን መቃወም ፣ እርስ በርስ መከባበር ፣ እርስ በርስ መፋቀር ፣ ሰላምን መሻትና ማጎልበት፣ እውነትን መውደድና ውሸትን መፀየፍ፣ ቀደምት ወላጅን ማክበር፣ የእራስ ያልሆነን አለመፈለግ፣ ማንኛውንም አመንዝራነት መፀየፍ፣ አምባገነንና ሸፍጠኛ ገዥ ቡድኖችን በጠንካራ  የሞራል የሃላፊነት ስሜት  መገሰፅ፣ የፀሎትና የምህላ እግዚኦታን ወደ መሬት አውርዶ በተግባር መፈተን ፣ወዘተ መሠረታዊ የሃይማኖታዊ እምነት መርሆዎች አይደሉም እንዴ? መሆናቸውን የሚጠራጠር ካለ ባለ ጤናማ አእምሮ የሚሆን አይመስለኝም።

የዘመናችን የሃይማኖት መሪዎች ፣ ሰባኪዎች፣ ባህታዊ ነን ባዮች፣ ተአምረኛ ፓስተር ነን ባዮች፣ እስላም ማለት ሰላም እንደሆነ እየሰበኩን ሰላም በውስጣቸው የሌለ ሸህ ነን ባዮች ፣ወዘተ እንደሚነግሩን  አለመታደል ወይም አንዳች አይነት መርገምት ሆኖብን ሳይሆን ፈጣሪ የሰጠንን ረቂቅ አእምሮና ብቁ አካል ለበጎ ነገር ያለማዋል ክፉ  ደዌ (አባዜ) ስለተጠናወተን አሁንም በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ያንኑ የለመድነውን መነባንብ ከማነብነብና መከረኛውን አማኝ ህዝብ ግራ ከማጋባት አልፈን አልሄድንም ። ለምን? ቢባል ከእውነት፣ከነፃነት ፣ ከፍትህና ከጋራ ብልፅግና መሠረታዊ መርሆዎች ጋር ፅዕኑና ዘላቂ መፍትሄና ውጤት በሚያስገኝ አኳኋን አንተዋወቅምና ነው ።  ይህ ደግሞ የፖለቲከኞች ብቻ ሳይሆን የሃይማኖታዊ እምነት መሪዎች/መምህራን/ሰባኪዎች ደካማነት (ውድቀት)  ጭምር የመሆኑ መሪር ሃቅ ፈተናውን ይበልጥ አክብዶታል ።

ዓላማችንና ግባችን  እውነተኛና መሠረታዊ ውጤት በሚያስመዝገብ ፅዕኑ እምነት (መርህ) ላይ የተመሠረተ ከሆነ  እንደ ግለሰብ ወይም እንደ ማህበረሰብ ወይም በተለያየ መስክና ፍላጎት እንደ ተደራጀ አካል (ቡድን) የሚያጋጥሙንን መሰናክሎች ለማለፍ የአካሄድ ወይም የሥልት ለውጥ እናደርጋለን እንጅ የመርህ ለውጥ አናደርግም። እውነተኛ ዓላማንና ግብን እውን በሚያደርግ  ተነሳሽነት/ፍላጎት ፣ ፅዕኑ እምነትና ጥረት ላይ የተመሠረተ መርህ የክስተቶች ተገዥ  መሆን የለበትም።  ክስተቶች ናቸው የመርሃችን  ተገዥዎች መሆን ያለባቸው ።

ለግለሰቦች እንደ እንደሚኖራቸው ሚና እና አስተዋፅኦ  ከሂሳዊ ድጋፍ ጋር ተገቢውን እውቅና እና ከበሬታ መስጠት ተገቢ መሆኑ አያወዛግም። አገርን ወይም ህዝብን የነፃነት፣ የፍትህና የብልፅግና ሥርዓት ባለቤት ለማድረግ በምናካሂደው የትግል ሂደት መነሻችንና ማመሳከሪያችን  የምንከተለውና የምናራምደው መርህ እንጅ የግለሰብ መሪዎች ሰብእና እና ቁመና ከቶ መሆን የለበትም ። ሊሆንም አይችልም።

“የለውጥ ሃይሉን ቡድን መቶ በመቶ አምነዋለሁ” የሚለው “የምሥክርነት” ሃይለ ቃል በተለይ  “ጠቀም ያለ ፊደል መቁጠር ብቻ ሳይሆን  የፖለቲካ ተሞክሮየም የዋዛ አይደለም”  ለሚል  ፖለቲከኛ የሚመጥን የፖለቲካ ሰብዕና አይደለም። እንኳን እጅግ አስቀያሚ በሆነው የጎሳ/የነገድ/የቋንቋ አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ  በተለከፈ (በተመረዘ)  ሥርዓት ውስጥ ጥርሱን ነቅሎ ያደገ ፖለቲከኛ “ከመላእክታን አንዱ ነኝ” የሚል (ከተገኘ) ቢመጣም የቆሙበትን የእራስ እምነትና እሴት (መርህ) ባፍ ጢሙ ደፍቶ መርህ አልባ መሆን ባይገርምም አንገት ያስደፋል ።  “ የኢህአዴግ ጭራቃዊ የጎሳ/የቋንቋ አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ሥርዓት ተወግዶ እውነተኛ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እስኪመሠረት የማንከፍለው ዋጋ የለም” በሚል ያዙንና ልቀቁን ሲሉ የነበሩት የግንቦት 7/ኢዜማ መሪዎች የህወሃት  ፖለቲከኞች ሴራውን ሲቀይሱና ሲያስፈፅሙ ከኖሩበት የአራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ለመውጣት መገደዳቸውን እንደ አልፋና ኦሜጋ ድል በመቁጠር የህወሃትን የግፍና የውርደት ተልእኮ በአሽከርነት በመፈፀምና በማስፈፀም ፖለቲካ ወለድ ወንጀል ተዘፍቀው ከኖሩ  ኢህአዴጋውያን/ብልፅግናዊያን ጋር በፖለቲካ አመንዝራነት እየተሻሹ የዴሞክራሲና የሞራል መርህ ባለቤት ነኝ/ነን ከማለት የከፋ(የባሰ) የፖለቲካ ሰብዕና ባዶነት ወይም ድህነት የለም።

 

አዎ! “የትግላችን አልፋና ኦሜጋ በፅዕኑና ዘላቂ በሆነ መርህ ላይ ቆሞ መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ለውጥን እውን በማድረግ የነፃነትና የፍትህ ሥርዓት መመሥረት ነው” ይሉ የነበሩ የተፎካካሪ ፖለቲካ ድርጅት መሪዎችና ፖለቲከኞች መርህ አልባነታቸውን የነገሩን  “ጠ/ሚ አብይንና የለውጥ ቡድኑን  በዴሞክራሲያዊ አሻጋሪነታቸው መቶ በመቶ (የፈጣሪን ያህል)  እናምናቸዋለን”  ብለው የተናዘዙ እለት ነው።

 

ለዘመናት አደንቁረው መከራና ውርደት ሲያስቆጥሩት የኖሩትን የዋህ የአገሬ ህዝብ ስስ ሥነ ልቦና አሳምረው የሚያውቁት መርህ አልባ (በአሽከርነት ተደራቢ) ፖለቲከኞች  እውነተኛ ለውጥ ጨርሶ በሌለበት “የአብይ፣ የለማ፣ የደመቀ፣ የደጉ ፣ እና የሌሎችም  አስደናቂ የለውጥ ድል ከተደናቀፈ አገር እንደ ሸክላ ትፈረካከሳለች”  የሚል “የፍፃሜ ኢትዮጵያ” መዝሙር  ሲዘምሩብን “ያደቆናችሁና ያቀሰሰችሁ ክፉ የፖለቲካ ልክፍት እናንተኑ ያፈራርሳችኋል እንጅ አገርስ አትፈርስም” ለማለት የሚያስችል የመልካም ዜግነት ወኔው ለምን እንደራቀን የየእራሳችን ህሊና መጠየቅ ይኖርብናል።

በግዙፍና መሪር የንፁሃን ዜጎች መስዋዕትነት የዛሬ ሁለት ዓመት ብልጭ ያለውን የለውጥ ብልጭታ የተቀበልነው በቃል የምናነበንበውንና  በወረቀት ላይ የምናሽሞነሙነውን የፅዕኑ መርህ  አስፈላጊነት ከምንኖርበት የገሃዱ ዓለም እውነታ ጋር በተግባር  ለማገናኘት ካለመቻል/ካለመዘጋጀት ውድቀት ጋር ነበር። በሌላ አገላለፅ የመርህ ሰውነትን በዲስኩርና በድርሰት እንጅ በተግባር አልኖርነውም ። በስሜታዊነት ፈረስ ከክስተቶች ትኩሳት ጋር ከነፍን እንጅ ክስተቶችንና ስሜታዊነታችንን የመርህሃችንና የዓላማችን ተገዥዎች ለማድረግ አልቻልንም ወይም አልፈለግንም ። የክስተቶችና የስሜታዊነት ፖለቲካችን አስከፊነት የሸፍጠኛና ሴረኛ ፖለቲከኞች መጫወቻዎች አድርጎን ቀጥሏል።

የጎሳ/የቋንቋ አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ  የበላይ መሪነትን  ከአሳዳጊያቸው ህወሃት ላይ ነጥቀው በተረኛነት የተቆጣጠሩት የኦሮሞ ብልፅግና/የኦዴፓ ፖለቲከኞች  በለመዱት የጭካኔና የሸፍጥ ፖለቲካ ጨዋታ መቀጠል እንደማይችሉ ሲረዱት በተሃድሶ ስም በፖለቲካ ወለድ ወንጀል የበሰበሰውንና የከረፋውን ሥርዓታቸውን  ማስቀጠሉን ነው የመረጡት ። ለእነርሱ የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ መርህ አስፈላጊነት ጨርሶ አይታያቸውም። ለምን? ቢባል በፅዕኑና ዘላቂ መርህ ላይ ቆሞ የሞገታቸውና የሸፍጥና የሴራ ፖለቲካ ጨዋታቸውን  ከቻሉ እንዲያስተካክሉና ካልሆነ ግን ለዘመናት የመከራና የውርደት  ቀንበር አሸክመውት ከኖሩት ህዝብ ትከሻ ላይ እንዲወርዱ እንቅጩን የነገራቸውና የተፈታተናቸው  የፖለቲካ ሃይል (ድርጅት) አልተገኘምና ። አያሳዝንም?

ከሩብ ምዕተ ዓመቱ እጅግ ረጅምና መሪር ተሞክሮ ተምረን የዛሬ ሁለት ዓመት ብልጭ ያለውን የለውጥ ብልጭታ አቅጣጫውንና መዳረሻውን  ለመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ  እውን መሆን  በሚያስችል ፅዕኑና ዘላቂ መርህ ላይ እንዲቆም አለማድረጋችን  ያስከፈለን ሁለንተናዊ ዋጋ ከቶ በስሌት የሚተመን አይደለም።

በአሰቃቂ ሁኔታ መግደልና መገዳደል በማንነት ምክንያት  በገንዛ አገር ላይ  በጅምላና በጭካኔ ተፈናቅሎ ምድራዊ ፍዳን መቀበል በእምነት  ማንነት ምክንያት ከቤተ እምነቶች ጋር በእሳት ጋይቶ  መሞት   ወዘተ  የአሳዛኙና የአሳፋሪው  የታሪክ ገፅታችን አካል  ሆኖ ይኖራል። ልብ ያለው ይማርበትና በጎ ታሪክ ያስመዘግብበታል፤ ልብ የሌለውም የመከራና የውርደት ታሪክ እየቆጠረና እያስቆጠረ ይቀጥላል። ምርጫው የእኛው የራሳችን ነው። የፅዕኑ፣የዘላቂና የበጎ መርህ ባለቤት በመሆን በነፃነትና በፍትህ የሚኖርበትን ሥርዓት እውን ማድረግ ወይም በመርህ አልባነት የሸፍጠኛና ሴረኛ ፖለቲከኞች የመከራና የውርደት ቀንበር እንደተሸከሙ መኖር (መኖር ከተባለ)።

በፅዕኑ መርህ ላይ ያልተመሠረተ (ያልቆመ) መንፈሳዊም (ሃይማኖታዊም) ይሁን ፖለቲካዊ (ዓለማዊ) አስተምህሮት፣ ፍልስፍና፣ ንድፈ ሃሳብ፣ ትርክት፣ እቅድ፣አፈፃፀም (ክንውን)፣ ወዘተ የክስተቶች ጥገኛ ከመሆን ከቶ አያልፍም።  ሁለንተናዊና አስከፊ ውድቀት ማለት መርሆቻችን የክስተቶችና የስሚታዊነታችን ተገዥ እንዲሆኑ የፈቀድን እለት ነው።   ይህ ደግሞ ተማርኩና ተመራመርኩ የሚል ወገን ማንነት መገለጫ ሲሆን የህሊና ህመሙ ከባድ ነው።

እራሳችንን በእራሳችን እያታለልንና ለእራሳችን እየዋሸን የሸፍጠኛ ፖለቲከኞች መጫወቻዎች ሆነን መቀጠል ካልፈለግን በስተቀር ለዘመናትየዘለቅንበትና ዛሬም የቀጠልንበት ክፉ የፖለቲካ ቫይረስ ምንጩ  ይኸው የፅዕኑ መርህ አልባነት ክፉ  ልማዳችን ነው ።

ይህን አባዜ (ልማድ) በእጅጉ የከፋና የከረፋ የሚያደርው  ደግሞ በአሽከርነት የመደመር  ፖለቲካ  የእራስን ሰብእና እና ቁመና  በማበላሸት የማያቆም መሆኑ ነው። እንደማነኛውም ሲሰራ እንደሚሳሳት ቅን ዜጋ ሊሳሳቱ  መቻላችው እንደ ተጠበቀ ሆኖ ለዘመናት ተደጋጋሚ የእስር ጊዜ  ካሳለፉበትና ከነቤተሰቦቻቸው ከባድ ዋጋ (መስዋትነት) ከከፈሉበት የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ መርህ ጋር በፅዕናት በቆሙ  (እስክንድር ነጋንና የትግል ጓደኞቹን ልብ ይሏል) ንፁሃን ዜጎች  ላይ ከሸፍጠኛና ሴረኛ ገዥ ቡድኖች ባልተናነሰ የማጥላላትና የማጣጣል  ዘመቻ እስከ ማካሄድ  መደረሱን ለሚታዘብ ቅን ዜጋ የአገራችን ፖለቲካ የፅዕኑና የዘላቂ መርህ ባለቤት ባልሆኑ ወይም መርህ አልባ በሆኑ ፖለቲከኞች የተበከለ መሆኑን ለመረዳት አይቸገርም  ።

ይህ አስቀያሚ የፖለቲካ ባህላችን አዙሮ የሚያይ ህሊና ባለቤት በሆኑና እና ነፃነት፣ፍትህና የጋራ የብልፅግና የተረጋገጠባት ኢትዮጵያን በመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ  አግባብ እውን የማድረግ ራዕይና የአርበኝነት ወኔ ባላቸው መልካም ዜጎች አነሳሽነትና አስተባባሪነት እንደሚለወጥ ያለኝን እምነት እየገለፅሁ አበቃሁ።

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

ከነፃነት ዘገዬ የአራት ኪሎው ኦነግ ሸኔ ከቁጥር ጋር እንደተጣላ ዕድሜውን አገባደደ፡፡ ኦነግ/ኦህዲድ ዛሬም ሆነ ዱሮ፣ በቤተ መንግሥትም ይሁን በጫካ ቁጥር ላይ ያለው አቋም ምን ጊዜም ያስደንቀኛል፡፡ ደግሞም እየባሰባቸው እንጂ ሲቀንሱ አይታዩም፡፡ ጥቂት

80 ቢሊዮን ብር ስንት ብር ነው?

በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና

ሰው ሆይ!

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

Go toTop