ኢትዮጵያ ጽጌሬዳችን ናት !

በግርማ ካሣ

ቺካጎ ([email protected])

ኢትዮጵያን በጽጌረዳ አበባ እመስላታለሁ። ጽጌሬዳ አበባ በጣም ተወዳጅ የሆነች አበባ ናት። ብዙ ጊዜ በማስቀመጫ ዉስጥ ተደርጋ የሚመጡ እንግዶች እንዲያይዋት በሚታይ ቦታ ትቀመጣለች። የክብር የፍቅርና የዉበት ምልክት ናት። ኢትዮጵያ አገራችንም በነጻነቷና በአንድነቷ ታፍራና ተክብራ የኖረች፣ ከተለያዩ ብሄረሰቦች የተወጣጡ ልጆቿ ዉበቷ የሆኑላት፣ ለኢትዮጵያዉያን ብቻ ሳይሆን ለጥቁር ህዝብ ሁሉ ኩራት የሆነች አገር ናት።

የቀድሞዉ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዘዳንት ኔልሰን ማንዴላ ሰለ ኢትዮጵይ ሲናገሩ “ኢትዮጵያ በሐሳቤ ልዩ ቦታ አላት፤ ኢትዮጵያን መጎብኘትም ፈረንሳይ እንግሊዝንና አሜሪካን ከመጎብኘት የበለጠ ይስበኛል” ይሉናል። ስለ ዳግማዊ አጼ ሚኒሊክ አንድ በተባበሩት መንግስታት ጽ/ቤት የኢኮኖሚክ ኮሚሽን ፎር አፍሪካ ከፍተኛ ባለስልጣን የነበሩ፣ ሴኔጋላዊ ከ አሥራ ሰባት አመታት በፊት የነገሩኝ ቁም ነገር ነበር። “ስለ አጼ ሚኒሊክና የአድዋዉ ጦርነት የሴኔጋል ተማሪዎች ይማሩታል። የአድዋዉ ድል የአፍሪካ የነጻነት ምዕራፍ ጅማሬ ነዉ። ሚኒሊክ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ አባት ናቸዉ” ሲሉ ነበር ኢትዮጵያ በሴነጋል ተወላጆች ዘንድ ያላትን ልዩ ቦታ በግልጽ ያስቀመጡልኝ። አዎ ኢትዮጵያ የኛ የኢትዮጵያዉያን ብቻ ሳይሆን የጥቁር ሕዝብ ሁሉ ጽጌሬዳ ናት።

ኢትዮጵያ እንዲህ ለጥቁር ሕዝብ ሁላ ኩራት የሆነችዉ በቀላሉ አይደለም። የኢትዮጵያን ነጻነትና ክብር ለማስጠበቅ የተከፈለዉ መስዋዕትነት እጅግ በጣም ትልቅ ነዉ።

በአድዋ፣ በማይጨዉ፣ በአዱሊስ በወልወልና በመላዉ የኢትዮጵያ ግዛት ከወራሪ ጣሊያኖች ጋር፤ በጉንደትና በጉራ ከግብጾች ጋር፤ በአፋር ምድር ከቱርኮች ጋርና እንዲሁም “ታላቋ ሶማሊያ” በሚል መርህ የተሰማራዉን የዉጭ ወራሪ ኃይል ለመመከት በሃረርጌ በተደረጉት ታላቅ ትንቅንቆች ትቅል የደም መስዋዕትነት ተከፍሏል።

በመተማ ከደርቡሾች በተተኮሰ ጥይት ያለፉትን አጼ ዮሐንስ አራተኛ፣ በመቅደላ ተራራ ለኢትዮጵያ ክብር ሲሉ እጃቸዉን ለእንግሊዞች ላለመስጠት የራሳቸዉን ጥይት የጠቱትን መይሳዉ አጼ ቴዎድሮስን ፣ የዘርዓይደረሰን፣ የአብዲሳ አጋን፣ የደጃች ባልቻ አባነፍሶን፣ የፊታዉራሪ ገበየሁን፣ የጥቁር አንበሳ ጀግኖችንና እንዲሁም በተለያዩ አጋጣሚ ለኢትዮጵይ ነጻነትና ክብር ሲሉ ህይወታቸዉን ሰዉተው ያለፉ ወገኖቻችንን ቁጠር እጅግ በጣም ብዙ ነዉ።

ጽጌሬዳ መልከ መልካምና ያማረች የሆነችዉን ያህል የሚዋጉና የሚያደሙ እሾሆችም አሏት። በአዲስ አበባ፣ በሃዉሴን፣ በአሲምባ፣ በከረን፣ በአስመራ፣ በአሶሳ፣ በጎንደር፣ በኦጋዴን፣ በምዕራብ ወለጋ፣ በበደኖ፣ በአርባ ጉጉ … በእሾህ ተወግቶ የስንቱ ኢትዮጵያዊ ደም ፈሰሰ ? ስንቱ በወንድሙ እጅ ታረደ ? የስንቱ ወጣት እናት ልጇን አጣች?

በአገራችን ለዘመናት በነበረዉ የእርስ በርስ ጦርነት ያለቁት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ተምረዉ፣ ትዳር ይዘዉ፣ ልጆች ወልደዉና ከብረዉ ለወግ ለማዕረግ መድረስ የሚችሉ ነበሩ። አሁን በሕይወት እንዳለን እንደ ማናችንም አንዳንዶቹ ሀኮሚች፣ አንዳንዶቹ መሃንዲሶች፣ አንዳንዶቹ ምሁራን፤ አንዳንዶቹ የሕግ ባለሞያዎች ሆነዉ ህብረተሰባቸዉንና አገራቸዉን ሊጠቅሙ የሚችሉ ነበሩ። ታዲይ ምን ያደርጋል የኢትዮጵያ ኋላ ቀር የደም መፋሰስና የመገዳደል ባህል ሰለባ ሆነዉ ቀሩ።

በአኩሪ ታሪካችን እንደምንኮራዉ ሁሉ በአሳፈሪዉ ታሪካችንም ማፈር አለብን እላለሁ። አገር እያለን ተሰደናል። ወገን እያለን ብቸኞች ሆነናል። ለሌሎች አገሮች የተረፈ ታላላቅ ወንዞች እያሉን ተጠምተናል። ምግብ እያለን ተረበናል። የአገራችን መሬቶች በደም ከመራሳቸዉ የተነሳ እህል ማብቀል አቁመዉ ከአመት እሰከ አመት ለህልዉናችን የፈረንጆችን እጅ እየጠበቅን ኖረናል። (ስንዴና እሩዝ ዘይትና ብስኩት እየለገሱን)

ታዲያ ለዚህ ሁሉ መከራና የሰቆቃ እሽክርክሪት ተጠያቂዉ ማን ሊሆን ይችላል ? አንዳንዶቻችን በአገራችን ለተፈጠረዉ ችግርና መከራ እጆቻችንን መንግስት ላይ እንቀስራለን። በንጉሱ ዘመን የዓጼ ሃይለስላሴ ቀዳማዊን አገዛዝ ስንረግምና ስንቃወም አብዮቱ ፈነዳ። “ኢትዮጵያ ትቅደም ያለ ምንም ደም” ተብሎ ተለፈፈብን። ወታደራዊዉ መንግስት ዙፋኑን በልጆቻችን አስክሬን ላይ ሰርቶ ገዛን። ከዚያም ቁምጣ የታጥቁ፣ “ከደርግ ብሶት የተወለድን ነን” የሚሉ “ነጻ ልናወጣችሁ፣ ዲሞክራሲ ልናመጣላችሁ ነዉ” አሉን። የከተሞቻችንን በሮች ከፍተን አስገባናቸዉ። ብዙም የተሻለ ነገር አልመጣም። አገር ወደብ አልባ ሆነች። ሃብት በጥቂቶች ተመዘበረ። ህዝብን በጎሳና በዘር ለመከፋፈል ተሞከረ። በዲሞክራሲ ስም ከአንድ በመቶ በታች የሆኑት ጨረቃ ላይ ሲመጠቁ ዘጠና ዘጠኝ በመቶ የሆነዉ ህዝባችን ቁልቁል ወረደ። ለሰላምና ለፍትህ የቆሙ ለወራት ጨለማ ቤት ይበግፍና በጭካኔ ይታሰራሉ። የፍርድ ቤት ትእዛዝ አይከበርም።

አዎን – በኢትዮጵያ ለተፈጠረዉ ችግር ዋነኛዉ ምክንያት የመልካም አስተዳደር ጉድለትና የህግ የበላይነት አለመኖር መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነዉ።

ነገር ግን በዚህ ጽሁፌ ከመንግስት ሌላ መጠየቅ ያለበት አካል እንዳለ ለማሳየት እሞክራለሁ። ይህም አካል እኔና እናንተ ነን። እያንዳንዳችን ለኢትዮጵያ አገራችን ድህነትና መቆርቆዝ በርግጥ ተጠያቂ እንደሆንን ማወቅና መቀበል ይኖርብናል። ሁላችንም መጠኑ ይለያያል እንጂ አገራችንና ወገናችንን ጎድተናል። ጥይት ላንተኩስ እንችላለን። ነገር ግን ወንድሞቻችን ሲገደሉ ዝም ማለታችን እራሱ ተጠያቂ ያደርገናል።

በአገራችን እኮ ነፍሰ ገዳይና ጨቋኝ የሚበዛዉ እኛ ስለምንፈቅድላቸዉ ነዉ። በጥቅም ይገዙላን፣ ያስፈራሩናል ከዚያ ለፍቃዳቸዉ ሕሊናችንን ሸጠን እንገዛለን። በኛ ላይ ቆመዉም በአገራችን ላይ ግፍ ይፈጽማሉ። ስለዚህ አሁን ያለዉን አገዛዝ ብቻ ከመርገም ይሄንን አገዛዝ የፈጠርነዉንና እንዲኖር ያደረግነዉን እኛኑ እርሳችንን እንውቀስ።

መተሳሰብና መደጋገፍ እንደሚያስፈልግ ለማስረዳት፡ “አሁን አንድ ኢትዮጵያዊ ጂንስ መልበስ አለበት ? ካኪ አይለብስም ። ዊስኪስ መጠጣት አለበት ? ጠጅ አይጠጣም” ብሎ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢንጂነሪንግ ፕሮፌሰር የነበረ አንድ ምሁር ከ አሥር ሶስት አመት በፊት የተናገረዉ ቁም ነገር ትዝ ይለኛል። ብልጽግና፣ ሃብትና መሻሻል መልካም ነገር ነዉ። ግን ከራሳችን አልፈን የወደቀዉን ሌላዉ ኢትዮጵያዊ ወገናችንን ለማንሳት እጆቻችን አጥረዉ ካልተዘረጉ ይህ የሞራል ዉድቀት ነዉ።

በሰሜን አሜሪካ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያዊያን ይኖራሉ ተብሎ ይገመታል። በህግ አንድ ሰራተኛ በሰዓት ከ 7$ በታች አይከፈለዉም። በጣም ዝቀተኛ ደሞዝ አገኘ ቢባል አንድ ሰዉ ቢያንስ በአመት 15000$ ያገኛል ማለት ነዉ። የካናዳ ወይንም ለአሜሪካ መንግስት ቢያንስ 15% (2500$ በአመት) ግብር ያስከፍላል። በሺህ የሚቆጠሩ የተማሩ ከ50 ፣ ከ70፣ ከ100 ሺህ በላይ የሚያገኙ ኢትዮጵያዉያን አሉ። በንግዱ ሥራ ተሰማርተዉ የከበሩና በርካታ ሱቆችና ኢንቨስትመንቶች ያሏቸዉም የሚናቁ አይደሉም።

እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በቀን አንድ ዶላር ለኢትዮጵያ ቢለይ በአመት 365 ሚሊዮን ዶላር ይደርሳል። በዚህ ገንዘብ በአየር ጠባይ መለዋወጥ በየጊዜዉ ለረሃብ የሚጋለጠዉን ወገናችንን የፈረንጆችን እጅ ሳንጠብቅ ማዳን እንችል ነበር። ታዲያ አሁንም የነጮች ጥገኛ መሆናችን መንፈሳዊ ክስረታችንን አያሳይምን? በአገራችን ላለዉ ድህነት ተጠያቂዎች አያደርገንምን ? ለካናዳና ለአሜሪካ 15% ከከፈልን ወገኖቻችንን ከረሃብ ለማዉጣትና ኢትዮጵያ በረሃብ ምሳሌነት እንዳትጠቀስ ለማድረግ ከደሞዛችን ከ 0.3 % በታች መክፈል ያቅተናል? ለልመና በጂ-20 በጂ-ስምንት ስብሰባ መጋበዝ የሚያኮራና አንበሳ የሚያሰኝ ነዉ ?

እኛ ኢትዮጵያዉያን ከቻይናዎች፤ ከጃፓኖችና ከነጮች በምን እናንሳለን ? አገራችንስ የተፈጥሮ ሃብት ከማናቸዉም ባላነሰ መልኩ እግዚአብሄር የቸራት አይደለችምን ? በአለም የተደነቁ ምሁራን፣ ሳይንቲስቶች፤ የሕግ ባለሞያዎች፣ መሃንዲሶች፣ ሃኪሞች ያሏት አገር ሆና ኢትዮጵያን ከድህነቷ ማንሳትና መቀየር እንዴት ያቅተናል?መልሱ “አያቅተንም” ነዉ። ከቃሊቲ እሥር ቤት እንደተፈቱ አንድ ወቅት ዶ/ር በፈቃዱ ደግፌ በስዊድን ለሚገኝ የሬዲዮ ጣቢያ የተናገሩት አንድ አባባል ነበር። “ኢትዮጵያን የተቸገሩና የተጨቆኑ ከእርሷ የሚሸሹ ሳይሆን ወደ እርሷ የሚሸሹ እናደርጋታለን፤ ይቻላል” ነበር ያሉት። እዉነታቸዉን ነዉ። ኢትዮጵያን የአፍሪካ ጃፓን ማድረግ ይቻላል። የሚያስፈልገዉ አንድ ነገር ብቻ ነዉ። እርሱም ፍቅርና መተሳሰብ ነዉ።

ሐዋርያዉ ቅዱስ ጳዉሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈዉ መልእክቱ የፍቅርን ትርጉም ይሰጠናል።“ፍቅር ይታገሳል፣ ቸርነትንም ያደረጋል፤ አይቀናም አይመካም አይታበይም፤ ፍቅር የማይገባዉንም አያደረግም፣ የራሱንም አይፈልግም፤ ፍቅር አይበሳጭም በደልንም አይቆጥርም፤ ከእዉነት ጋር ደስ ይለዋል እንጂ ሰላ አመጻ ደስ አይለዉም ..” በማለት በዝርዝር አስተምሯል።

ፍቅር ካለን አንዳችን በአንዳችን ላይ በበቀል በእልህና በጭካኔ አንነሳም። ፍቅር ካለን ያለፈዉን መጥፎ ታሪካችን ላይ ብቻ “እኝ” ብለን ልባችንን ለእርቅና ለይቅርታ አንዘጋም። ፍቅር ካለን በወንድማችን እሬሳ ላይ እየተረማመድን በደም የተገኘ ሃብት አናከማችም። ፍቅር ካለን ጎንበስ ብለን የወንድማችንን እግር እናጥባለን እንጂ በባዶ ትዕቢት አንሞላም። ፍቅር ካለን ያለችንን አንድ ዳቦ ግማሹን ቆርሰን ለተራበዉ ወንድማችን እናካፍላለን። ፍቅር ካለን በሚሊዮን የሚቆጠር ወገናችን የሰቆቃ እንባ እያለቀሰ በዳንኪራና በጨዋታ ንዋያችንን አናጠፋም። ፍቅር ካለን ያለፈን ክስ በመምዘዝ ሰላምዊ ሰዉን በጨለማ ቤት ዉስጥ በግፍና በጫካኔ አናስረም።

“ፍቅር ከወዴት ትመጣለች ?” የሚል ጥያቄ ሊጠየቅ ይችላል። መልሱ ግልጽና ቀላል ነዉ። ፍቅር የፍቅር አምላክ ከሆነዉ ከእግዚአብሄር ዘንድ ብቻ ትገኛለች። መጽሐፍ እንደሚል እግዚአብሄር እራሱ ፍቅር ነዉ።

አሜሪካኖች አገራቸዉን የመሰረቱት በእግዚአብሄር ላይ ነዉ። የሚጠቀሙበትን ገንዝብ አገላብጠን ብንመለከት እንኳን ”በእግዚአብሄር እናምናለን” የሚለዉ አረፍተ ነገር ተጽፎበታል። በእርሱ ላይ ተመስረተዋልና እግዚአብሄርም ባረካቸዉ።

እኛ ኢትዮጵያዊያን በጣም ሃይማኖተኞች ነን። ነገር ግን ሃይማኖተኝነታችን ብዙዉን ጊዜ በዉጭ ብቻ ነዉ። መንፈሳዊ አባቶቻችን በአንድ ጎን እየተራገሙና እየተወጋገዙ ሰጋ ወደሙን ይዘዉ ይቀድሳሉ። “ይህ ህዝብ በከንፈሩ ያከበረኛል ፤ ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነዉ” ተበሎ እንደተጻፈ በከንፈራችን እንጂ በልባችን እግዚአብሄርን አልፈለግነዉም። በከንፈራችን ፍቅርን እናወራለን ልባችን ግን በጥላቻና በቂም የተሞላ ነዉ። ታዲያ እግዚአብሄር እንዴት አደርጎ ይታረቀን ?

እግዚአብሄር ሊባርከን፣ ሊያድሰንና ሊጎበኘን የታመነና ጻድቅ ነዉ። በግላችን በቤተሰባችንና በአገራችን መጀመሪያና ተቀዳሚ ካደረግነዉና “በእግዚአብሄር እናምናለን” የሚለዉን ቃል በልባችን ካተምን የፍቅር መንፈስ በምድራችን ይፈልቃል። ፍቅሩም እንድንተቃቀፍ፤ እንድንሳሳም፤ እንድነሸካከም ያደርገናል።

እኛ የአስተሳሰብ ለዉጥ ካደረግን፣ ከራሳችን ያለፉ ሥራዎችን ለመሥራት ከወሰንን፣ ከታጠርንበት ግላዊ የአስተሳሰብ መአቀፍ ከወጣን፣ በርሳችን ከተማመንን በጋራ በአንድነት መለወጥ የማንችለዉ ነበር የለም። ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳንና ሌሎች የሕሊና እሥረኞችን ማስፈታት እንችላለን። በኢትዮጵያ የምንፈልገዉን የዲሞክራሲ ሥርዓት መገንባት አገራችንንም ከድህነት ማወጣት እንችላለን።