April 3, 2020
17 mins read

የኮረና ቫይረስ ወረርሽን አደጋ እና የሀገርና ሕዝብ ደህንነት

በዲሴምበር 2019 እ.አ.አ በይፋ የታወቀው የኮረና ቫይረስ (ኮቪድ 19) ወረርሽን ዓለማችን በ20ኛው እና 21ኛው ከነበሩት ወሳኝ ክስተቶች አንዱ የሚሆን ይመስለኛል። ይህም ማለት የ1917ቱ የሩሲያ አብዮት፤ የ1939ቱ ጀርመን በፓላንድ ላይ ያደረገችው ወረራ፤ የ1949 እ.አ.አ የማኦ ቻይና ምስረታ፤ የ1989ቱ የበርሊን ግንብ መደርመስ እና በሴፕቴምበር 11 2001 ኒዮርክ የደረሰው የሽብር ጥቃት እንዳደረጉት ሁሉ ይኸኛውም ክስተት የዓለምን የፓለቲካና የኢኮኖሚ ሥርዓቶች ብቻ ሳይሆን አስተሳሰባችንንም ጭምር የሚቀይር ይመስለኛል። ይህን ሀሳብ ማብራት ከባድና ብዙ ገጾችን የሚጠይቅ በመሆኑ ለጊዜው አልሞክረውም።

ትኩረቴን አሁን ባለው ሁኔታና በኢትዮጵያ ላይ ብቻ ማድረግ እፈልጋለሁ፤ ለመነሻ ያህል ግን ከዓለም ዓቀፍ ሰዋዊ ደህንነት (human secuirty) አንፃር ጥቂት ትዝብቶቼን ላስቀድም።

1. የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ “አሜሪካ ትቅደም !” መፈክር አሜሪካ ወደ ራሷ ብቻ እንድትመለከት በማድረግ የዓለም መሪነት ሚናዋን አሳጥቷታል። አሁን ዓለም መሪ የላትም። አሁን ባለው የአሜሪካ ፓለቲካ ትራምፕ ደግመው እንደማይመረጡ መገመት ከባድ ነው፤ ባይመረጡ እንኳን አዲስ የሚመጣው ፕሬዚዳንት ትራምፕ ያበላሹትን ለመጠገን ብዙ ጊዜ ይወስድባቸዋል። ስለሆነም ላልተወሰነ ጊዜ አሜሪካን በመሪነት መመልከት ትክክልም አይደለም፤ አያዋጣምም።
2. ኮቪድ 19 ሰዎችን ማቀራረቡ እውነት ሊሆን ይችላል፤ አገሮችን ማቀራረቡን ግን እጠራጠራለሁ። የተባበሩት መንግስታት ጥሪ ሰሚ ጆሮ አላገኘም፤ ሩሲያ በነዳጅ ገበያ ላይ ያለው ቅራኔ ለማርገብ ፈቃደኛ አይደለችም፤ አሜሪካ ኢራን ላይ የጣለችውን ማዕቀብ አልቀነሰችም፤ ቱርክ ውስጥ ያለው ግጭት አልበረደም … የዓለም ዋና ዋና ቅራኔዎች እንዳሉ ናቸው። አገሮች ለኮቪድ 19 የወሰዱት እርምጃ የየራሳቸው አጥር መዝጋት ነው። የጋራ ፓሊሲ የሚባል ነገር የለም፤ እስካሁን እያንዳንዱ አገር ለብቻው እየታተረ ነው። የአውሮፓ ኅብረት አገሮች እንኳን ቀድሞ ያደባለቁትን ድንበር መልሰው እያሰመሩ ነው። የትብብር አስፈላጊነት ጎልቶ እየታየ፤ በባለስልጣኖች አንደበት እየተነገረ ቢሆንም እንኳን በተግባር ዓለም ዓቀፍ ትብብር ከቀድሞው መቀነሱን እንጂ መጨመሩን በበኩሌ አልታዘብኩም።
3. ሉላዊነት (globalisation) የመንግስታት አስፈላጊነትን ቀንሶ መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት (non-state actors) በተለይም የነፃ ገበያ ሚና አጉልቶ ነበር። የዘመኑ ልሂቃን መፈክር “እያደገ የሚሄድ ነፃ ገበያ እና እያነሰ የሚሄድ መንግስት” የሚል ነበር። ኮቪድ 19 ይህንን ቀይሮታል። ዛሬ በብዙ አገሮች (ያደጉም፣ ያላደጉም) የሕዝብ ተስፋ የተንጠለጠለው በገበያ ወይም በሌሎች መንግስታዊ ባልሆኑ አካላት ሳይሆን በመንግስታት ላይ ሆኗል። መጪው ጊዜ የመንግስት ወጪዎች የሚጨምሩበት፤ የመንግስት አገልግሎቶች እጅግ የሚስፋፉበት መሆኑ ካሁኑ እየታየ ነው።
4. አለቃ በሌለበት የዓለም ሜዳ ትናንሽ መንግስታት የሚከተሉት በወቅቱ ከሌሎች የተሻለ እያጠቃ ያለውን መንግስት ነው። አሁን እያጠቃ ያለው የቻይና መንግስት ነው። ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ ብዙ አገሮች ወደዱም ጠሉም የቻይናን መሪነት ለመቀበል ይገደዳሉ።

የኮረና ቫይረስ ወረርሽን እና ከላይ የተመለከቱት ትዝብቶቼ ለኢትዮጵያ ያላቸው እንድምታ ምንድነው ?
1. አሁን ባለው ሁኔታ እንደሌላው ዓለም ሁሉ ለኢትዮጵያዊያንም መድረስ የሚችለው መንግስት ነው፤ ስለሆነም ጠንካራ መንግስት ያስፈልገናል። በአሁኑ ሰዓት “ጠንካራ መንግስት” ማለት ብዙ ማኅበራዊ አገልግሎችን ማቅረብ የሚችል መንግስት ማለት ነው። የበርካታ ሚሊዮን ሕዝብ የዕለት ተዕለት ኑሮ፤ ቁጥሩ ቀላል ላልሆነ ሕዝብ ቁርስ፣ ምሳ፣ ራት፣ ህመሙ፣ ሞቱና ቀብሩ ሳይቀር የመንግስት የሥራ ኃላፊነት ሊሆን ይችላል። ይህን ሁሉ ኃላፊነት መንግስት ብቻውን ይወጣ ማለት አይደለም፤ የዜጎች ሁሉ ርብብርብ አስፈላጊ ነው፤ ሆኖም ተቀዳሚ ኃላፊነቱ የመንግስት ነው። ከመንግሥት ሌላ አስተማማኝ አማራጭ የለም። እነዚህ አገልግሎቶችን ማቅረብ ያልቻለ መንግስት የወደቀ መንግስት ይሆናል። እየመጣ ያለውን መከራ በደካማ የመንግስት አቅም መወጣት አይቻልም። ለጊዜው የተፎካካሪ ፓርቲዎች ሚና አሁን በስልጣን ላይ ያለው ፓርቲ ለመተካት መስራት ሳይሆን ያለውን መንግሥት ለማጠናከር መትጋት መሆን ይኖርበታል።
2. በኔ ግምት አፍሪቃ የወረርሽኙ አፍላ ስርጭት ወቅት የምትገባው አውሮፓ ማገገም በምትጀምርበት ወቅት ነው። ያኔ ያደጉት አገሮች በራሳቸው አቅም መልሶ-ግንባታ ላይ ያተኩራሉ፤ በሽታው ከውጭ ተመልሶ እንዳይገባባቸው በራቸው አጥብቀው ይዘጋሉ፤ ይበልጥ ደግሞ ለአፍሪቃ። አገራችን ኢትዮጵያ ከሌሎች አገራት ጋር ያላት ቀጥታ ግኑኝነት በአየር መንገድ ብቻ ነው፤ እሱም በርካታ ማዕቀቦች ይኖሩበታል። ስለዚህ:-
2.1. የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለተጨማሪ ግዳጅ መዘጋጀት ይኖርበታል። አሁን አየር መንገድ ላይ የሚቀርበው ትችት ተገቢ አይመስለኝም። አየር መንገዳችን ያሉትን ቀዳዳዎች ሁሉ በመጠቀም የሸቀጦች ማስገቢያና ማውጫችን መሆን ይኖርበታል።
2.2. አየር መንገድ የሚመላልሰው ሸቀጥ ብቻ አገሪቷን አያኖራትም፤ በዚህ ወቅት በጅቡቲ ወደብ ላይ መተማመን አያዋጣም። በዚህ ወቅት ለኢትዮጵያ ኤርትራን የሚያህል ወዳጅ አገር የለም፤ የአሰብ ወደብን በጋራ የማልማት ሥራ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል።
3. እንደ ዓለም ሁሉ፤ አፍሪካም መሪ የላትም፤ የጎበዘውን መከተል ግን የጨዋታው ህግ ስለሆነ የጎበዘ መሪ ሲመጣ ሌላው መከተሉ አይቀርም። ይህንን ክፍተት ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ለኢትዮጵያም ለአፍሪቃም ደህንነት ይጠቀሙበታል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኢትዮጵያ አልፈው ቀጠናው ከዚያም አልፎ አህጉሩን ለመወከል የሚያደርጉትን ጥረት መደገፍ የሁላችን ኃላፊነት ሊሆን ይገባል።
4. የብሔራዊ ደህንነትና መረጃ አገልግሎት ራሱን እንደገና እንደ አዲስ እንዲፈትሽ እጠይቃለሁ። በኔ እምነት ከ2018 ወዲህ የሀገራችን የውስጥ ደህነነት ስጋቶች በቅደም ተከተል (1) በክልል መንግስታት መካከል ያለው መናቆርና የመሳሪያ እሽቅድድም፤ (2) በመላው አገሪቱ በተለይም በከተሞች (ለምሳሌ አዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ፣ ሀረር፣ ጎንደር፣ ወልቂጤ፣ አጋሮ፣ ለቀምት) እየተስፋፋ የመጣው የተደራጀ ውንብድና (organised crime) [ይህ የተደራጀ ውንብድና የፓለቲካ ቅብ ያለው መሆኑ ልብ ይሏል]፣ እና (3) የደቡብ ክልል የመበተን አደጋ ናቸው። ሶስቱም ችግሮች የፓለቲካ ሥርዓታችን ዘውግን (ብሔርንና ብሔረሰብን) መሠረት በማድረጉ ምክንያት አሁን የደረሱበት አስከፊ ደረጃ ላይ የደረሱ በመሆኑ በዘለቄታ ለመፍታት ሕገመንግስታዊ ማሻሻያ ማድረግ ያስፈልጋል። ይህ ግን በአጭር ጊዜ የሚሆን አይደለም። ለእነዚህ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ እየተፈለገ በአጭር ጊዜ አገርንና ሕዝብን አደጋ ላይ እንዳይጥሉ መከላከል የደህንነቱ መሥሪያ ቤት ትኩረት መሆን አለበት።

በአሁኑ ሰዓት ተጨማሪ የደህንነት ስጋት ተፈጥሯል – የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ !ወረርሽኙ ከላይ የተዘረሩትን ሶስቱንም የደህንነት ችግሮችን ሊያባብስ ይችላል።
4.1. ወረርሽኙ የክልል መንግስታትን ፉክክር አዲስ ገጽታ ሊሰጠው ይችላል። እያንዳንዱ ክልል የራሱን ክልል ደህንነት ብቻ የሚጠብቅ በሚመስል መንገድ ያልተናበቡ የክልል የወረርሽን መከላከል ፓሊሶዎች ማውጣት “የመሳሪያ እሽቅድድሙን” በሌላ መንገድ ማስቀጠል ይሆናል።
4.2. ወረርሽኙ የተደራጀ ውንብድናን ሊያጠናክር እንደሚችል መገመት ይጠቅማል። የተደራጀ ውንብድና ድሮም የርስበርስ ንክኪ አነስተኛ በሆነበት ትስስር የሚፈፀም ነው። ኮረና ለተደራጀ ውንብድና አመቺ ሁኔታ ሊፈጥር ይችላል። እንዲያውም የደህንነቱን መሥሪያ ቤት ጨምሮ የመንግስትን መዋቅር ሊጠልፍ ይችላል።
4.3. ሲዳማ በአሁኑ ሰዓት ክልል ምሥረታ ይጀምር ቢባል ተከታታይ ችግሮችን መፍጠሩ አይቀርም። በመሠረቱ አሁን እንደ አዲስ የሚደራጁ ተቋማት የወደፊቱን ”ዓለም” አስበው ቢመሠረቱ ይመረጣል። ከወረርሽኙ በኋላ የብዙ መሥሪያ ቤቶች ጽ/ቤቶች “ደመና“ ላይ እንደሚሆኑ እገምታለሁ (virtual offices)። ይህንን ደግሞ የመለማመጃ ጊዜ ይፈልጋል። ሲዳማ ክልል ሲመሠርት ደግሞ ሌሎችም መጠየቃቸው አይቀርም፤ ለአንዱ ተሰጥቶ ለሌላው መንሳት ኢፍትሃዊ ነው፤ ሰላምን አያሰፍንም።

እነዚህን ሁሉ ታሳቢ በማድረግ የብሔራዊ ደህንነትና መረጃ አገልግሎት ወቅቱ ለሚጠይቀው ተግዳሮት ራሱን ማዘጋጀት አለበት።

5. ወረርሽኙ ያመጣቸው አንዳንድ ልማዶች ከወረርሽኙም በኋላ መቀጠላቸው ስለማይቀር ተቋሞቻችንን ሁሉ ራሳቸውን መፈተሽ ይኖርባቸዋል። ለምሳሌ የትምህርት ተቋማት አጫጭር ስልጠናዎችን ብቻ ሳይሆን የዲግሪ ትምህርቶችንም ኦንላይን እንዲሰጡ ማዘጋጀት ይገባል። ይህን ማድረግ ደግሞ ይቻላል የሚል እምነት አለኝ። ለምሳሌ በትላልቅ ከተሞች በየቀበሌው በየትናንሽ ከተሞች ደግሞ በአንድ ቦታ ተማሪዎች ከዩኒቨርቲዎቻቸውና ከቤተመፃህፍቶቻቸው ጋር የሚገናኙባቸው በኔትዎርክ የተገናኙ ኮምፒተሮች ያሉባቸው የተማሪዎች ማዕከላት(student hubs) ማደራጀት፤ ሆስፒታሎች በየቀበሌው patients hubs አማካይነት በቪዲዮ የሕክምና አገልግሎት የሚሰጡበት መንገድ ማመቻቸት ይቻላል። ይህ ዛሬውን መፈፀም ባይቻልም በተሠራበት በጥቂት ዓመታት ውስጥ ተግባራዊ ሊደረግ ይችላል።

ስለኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ ስናስብ በአጭር ግዜ ተከስቶ እንደሚጠፋና ቶሎ ወደ ቀድሞው ኑሮዓችን የምንመለስ አድርገን ባናስብ የተሻለ ነው። ወረርሽኙ ከፍተኛ የማኅበረሰብ ጤና ችግር ነው፤ ለጊዜው ያሉት መፍትሄዎች ራስን ከንኪኪዎች ማራቅ፣ አካላዊ ርቀት መጠበቅ እና የእጅና የአካል ንጽህናን መጠበቅ ናቸው። እነዚህን እናክብር፤ በጣም አስፈላጊ ካልሆነ በስተቀር ከቤት አንውጣ። ሁላችንም ይህን ከፈፀምን የወረርሽኑን ስርጭት መቀነስ ከዚያም መግታት እንችላለን።

ይሁን እንጂ ወረርሽኑ የማኅበረሰብ ጤና ብቻ ሳይሆን የአገርና ሕዝብ ደህንነት አደጋ እንደሆነ መረዳት ይገባናል። ለዚህም መንግሥት በተለይም የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ከፍተኛ ኃላፊነት አለበት። በዚህም ወቅት ሁላችንም ከመንግስት ጎን መቆም ይኖርብናል፤ ከአገራችን መንግስት ሌላ የሚደርስልን አካል የለም። ከወረርሽኙም በኋላ አኗኗራችን አስተሳባችን መቀየሩ አይቀርም፤ ለዚህም ከአሁኑ ዝግጁ እንሁን።

ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጤንነትን እመኛለሁ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። ) “ገብርዬ ነበረ

ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ?

January 3, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ዛሬ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ጥር 1ቀን 2025 ዓ/ም ነው ። አውሮፓውያኑ አዲስ ዓመትን “ሀ” ብለው ጀምረዋል ። አዲሱን ዓመት ሲጀምሩም ከልክ ባለፈ ፈንጠዚያ ነው ። ርቺቱ ፣ ምጉቡና መጠጡ

ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። )

ትላንት አንድ ወዳጀ ደውሎ “አሳየ ደርቤን” ታውቀዋለህ ወይ” አለኝ፡፡ እኔም አላውቀውም አልኩት፡፡ ኢንጅኔር “ኡሉፍ” የተባለ ሰው የዛሬ ሰባት ዓመት ያሰራረውን ጥልቀትና ስፋት ያለውን ዘገብ አቅርቦታልና አዳምጠው አለኝ፡፡ እኔም “ጉድሺን ስሚ ኢትዮጵያ–ከባድ አደጋ

ተቆርቋሪ የሌላት ኢትዮጵያ – አክሎግ ቢራራ (ዶር)

ወገኖቸ፤ ለጊዜው ትችቱን እናቁምና ለወገኖቻችን እንድረስላቸው፡፡፡ በቤተ አማራ ወሎ ቡግና የተከሰተው ርሃብ ጉዳት ቀላል አይደለም፡፡ ለወገን ደራXኡ ወገን ስለሆነ እባካችሁ ህሻናትን እናድን፤ ለግሱ፡፡ ጦርነት ያመክናል፤ ተከታታይ ጦርነት አረመኒያዊነት ነው፡፡ ጦርነት ካልቆመ የረሃቡ

እግዚኣብሔር ግን ወዴት አለ?

Go toTop