ወጉ የተጀመረው ድንገት ነው።ልክ እንደመብረቅ ብርሃን ብልጭታ ድንገት ቦግ ነበር ያለው።፣ልክ እንደ አውሎ ነፋሥ ሳይታሰብ ነበር ሁሉንም ሰው በወጉ ያሳተፈው።ልክ እንደ ደራሽ ውሃ ነበር የወንዙ መውረጃ አይደለሁም ያለውን ሁሉ ፣አጥለቅልቆ ወደ ወጉ የዶለው።
ወጉ ድንገት በድቅድቅ ጭለማ ውስጥ ብልጭ ያለ የመብረቅ ብለጭታ ዓይነት ነበር።መብረቁ ጨለማውን በብርሃን ሢሞላው ተደስታችሁ ሳታበቁ፣ መብረቁ እንደሚያሥደነግጣችሁ ሁሉ፣ወጉ ከጥርሳችሁ በልጭታ ኋላ ያለውን ሀዘን ያሳብቅባችኋል። እንደ አውሎ ንፋሱ ፣በሽክርክሪቱ እና በተአምረኛው የአቦራ ክምር ተመሥጣችሁ ሣታበቁ ፣በግሥንግሥ ሸፍኗችሁ ጣራችሁን ገንጥሎ እንደሚወሥደው ሁሉ፣ወጉም፣በሰው ለጅ የሥልጣኔ ህይወት ተገርማችሁ ሳታበቁ፣ ትካዜ ውስጥ የሚከታችሁ አያሌ ቅራቅንቧዎችን እግራችሁ ሥር ይተውላችሁና ያሥተክዛችኋል ።
ይህ ወግ የተፈጠረው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው።በአዳምና በሄዋን መረዳጃ ዕድር ውሥጥ።ይህ ዕድር በድፍን ኢትዮጵያ መንደሮች እንደየባህሉ እና ወጉ መኖሩን መቼም ታውቃላቻሁ። እኔም ከዚህ “የአዳም ና ሄዋን” መረዳጃ ዕድር ፣የዕድሩን አንድ ዓባል ልጅ ሞት ለማፅናናት ዕድሩ በጣለው ድንኳን ውስጥ ድንገት ተገኝቼ ነው የወጉ ተዋንያን የሆንኩት።
መቼም ህዝብ፣ ድንኳን እየጣለ፣ሐዘኑን ለመርሳት በሚቀመጥበት ሥፍራ ሁሉ ወግ አይታጣም ።ደግሞም ወደ ሠርግ እና ቲያትራዊ ቅንብር ወዳለው የሆቴል፣የወዘተ ምርቃት ሥፍራ መገኘት እምብዛም አያሥደሥተኝም። ከልቅሶ ድንኳን ውስጥ ተገኝቼ ነገ አፈር መሆኔን ሣሥታውሥ ነፍሴ በጣሙኑ ትደሳለች።
የነፍሴ ደሥታ ይኽ ምክንያት ብቻ አይደለም ።ወደለቅሶ ቤት መሄድ በእጅጉ የምወደው ፣ለቅሶ ቤት፣አጥር አልባ የሆነ እጅግ ዴሞክራሲያዊ መድረክ በመሆኑ ነው።
እዛ ፣ ጎሣ፣ዘር፣ኃይማኖት አይጠየቅም።የተወለድክበትን አካባቢ፣ ሺ ጊዜ የተሻገርከውን ወንዝ…ቁጠር የሚልህ የለም።
እነዚህን ሀሉ ጥያቄዎች ጠይቆ ካጣራ በኋላ፣ “ወዶ ገብ፣ሠርጎ ገብ፣ቀላዋጭ፣ ጎበና፣ኮንደም፣ ሆዳም፣አድርባይ፣ጆሮ፣እሥሥት፣ህሊና ቢሥ፣ ጭራ ቆሊታ ፤ጎጠኛ፣ዘረኛ፣ትምክህተኛ፣ነፍጠኛ…በማለት በነገር የሚወጋህ ከቶ የለም።…
ሰው ከመሆንህ ባሻገር፣ በቋንቋህ የሚፈርጅህ እና የሚያገልህ የለም።…ሲጀመር በራሥህ ፍቃድ ሐዘንተኛውን ለማፅናናት” ነግ በእኔ ብለህ” ድንኳኑ ውስጥ ተገኘህ እንጂ ማንም በቀበሌ ካድሬ አሥገድዶህ ፣ወይም የጥሪ ካርድ ልኳልህ በለቅሶ ቤት ዳሥና ድንኳን አልተገኘህምና ዘና ብለህ ትጫወታለህ።
አጠገባህ ካለ ሰው ጋር፣ብታውቀውም ባታውቀውም፣ሥለሞት እና ሥለህይወት ታወራለህ።በሚያግባባህ ቋንቋ።
የእናቴን ቋንቋን አትናገርም ብሎ ጀርባውን የሚሰጥህ የለም። ለምን መጣህ?እንዴት መጣህ? እጅህ ከምን ብሎ የሚያፈጥብህ እና የሚያፋጥጥህም እዚህ እንደ እብድ ነው የሚቆጠረው።
ወንድሜ ፣ ምሳ ወይም እራት ለመብላት እንኳ ለቅሶ ቤት ብትገኝ ማንም ሰው አንተን አያማህም።እንጀራም አይከለክልህም። ምሳ እና እራትህን በለተህ ነፍስ ይማር ብለህ ትወጣለህ። ይህን በማድረግህ ሐዘን የደረሰበት እንደ ዘመድ ይቆጥርሃል።በቸገረህ ጊዜም ከጎነህ ይቆማል። ሲያዝን አንተም ማዘንህን ለቅሶው በመድረስ ገልፀሃልና!
እናም ለቅሶ ቤት ነፃ እና ለሰው ሁሉ (ለለቅሶ ደራሽ) የመናገር፣የማፅናናት፣ ያሻህን በቀልድ መልክ መናገር ነፃነትን ይሰጣል።
እኔም በዛ ዴሞክራሲያዊ መድረክ በሆነ “የአዳም እና የሔዋን” ዕድር በጣለው ድንኳን ውስጥ ማነው የሞተው ሣልል ሰተት ብዬ የገባሁት፣ድንገት በመገዴ ላይ ድንኳኑ ሥለተጋረጠ ፣በጥጉ ሾልኬ ከማልፋ ፣ባላውቃቸውም፣ሞት እንግዳ ነውና በድንገት የመጣባቸው እንግዳ ፣ነገ ወደ እኔ እና ቤቴ መምጣቱ አይቀርም እና ለምን ገብቼ “እግዜር ያፅናናችሁ” አልላቸውም በማለት ነው ፣ወደ ድንኳኑ የዘለቅሁት።
አመሻሽ ላይ ነበርና ወደ ድንኳኑ የዘለቅሁት፣ ድንኳኑ በአሥተዛዛኝ ተሞልቶ ነበር፣ከሐዘንተኞቹ ፍራሽ በሥተቀኝ በኩል ፣ባገኘሁት አንድ ክፍት ወንበር ከማላውቃቸው ፣የሾለ አፍንጫ ፣ የሚያፏጭ ፊት እና እራሰበርሃ ከሆኑ ሽማግሌ አጠገብ ቁጭ አልኩ።
ከፍትለፊት የተቀመጠው ፣ጥቁር መነፅር ፣ጥቁር ጃኬት፣ጥቁር ጂንሥ፣ጥቁር ጫማ የለበሰ ጎልማሳ ፣በሌባ ጣቱ የመኪና ቁልፍ መያዣ አሠገብቶ እያሽከረከረ ያወራ ነበር።
“…እውነት ነው ማለቢያ ማሽን አለ።ማሽኑ ወተቱን አልቦ ወደማጠራቀሚያ ጋኑ ፣ሲገለብጥ፣ ሌላው ማሽን ተቀብሎት ደግሞ ወደማቀነባበሪያ ማሽኑ ያደርሰዋል።ወገኖቼ በአሜሪካ የወተት ማለብና ፣ወተትን አቀነባብሮ ለገብያ ማቅረብ ብቻ ሣይሆን አበዛኛውን የፈብሪካ ሥራ ማሽን ወይም ሮቦት ይሰራዋል።እነሱም ይሄ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ወጤት ነው ይሉታል።እናም ይህ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንሥ ውጤት ፣ ሮቦት፣ በመረጃ የታጨቀ ሰው መሰል ጭንቅላት ሥላለው በሊቃውንቶቹ የተሞላውን ማንኛውንም ተግባር ይፈፅማል።ወደፊት ከዓለም ምርጥ የእግር ኳሰ ተጫዎቿች ጋር ሁሉ ይህ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ውጤት የሆነ ሮቦት መልያ ለብሶ ከሰዎች ጋር ሲጋጠም ልናይ እንችላለን።ወይም የቻይና የሮቦት የእግር ኳሥ ቡድን ከአሜሪካው የሮቦት ቡድን ጋር ሲጋጠም ልናይ እችል ይሆናል !ዕድሜ ከሰጠን።
“እናም፣ እንዳልኳችሁ የአሜሪካ ላም ማርባት አዋጪ ነው። ይሁን እንጂ እንደ አሜሪካ ሀብታም ካልሆንክ የአሜሪካን ላም ጥጃ ገዝቼ አሳድጌ ሀብታም እሆናለሁ ብለህ ፈፅሞ እንዳታስብ።ድንገት ተስፈኛ በመሆን ይህንን ከንቱ ህልም ካሰብክ ፣ቀድመህ ለንስሐ አባትህ አማክር።አሥራ አራት ቀን ጠዋት፣ጠዋት፣ እንድትጠመቅ ያዙሃል ። አሜሪካን አሜሪካ ያደረጋት የማይነጥፈው የላሞቿ ጡት እንደሆነ ቢታወቅም ለአንተ ለድሃው በላሞቿ መክበር አልተፈቀደም። ወገኔ ለጊዜው በቻይና ላም ተዝናና።ከነዚህ ላሞቾ ጡት የማያበራ ማለቂያ የሌለው ወተት እንደማታልብ ግን ተረዳ። ” እያለ ሲያወራ ነበር የደረስኩት። ወሬውን እንዳበቃ፣
“ምሥኪን የአሜሪካ ጥጄዬ!እንሆ ከሞትሽ ዛሬ ሁለት ዓመት ሞላሽ። ባትሞቺ ኖሮ ወልደሽ፣ለወተትሽ ማለቢያ ማሽን ይገዛልሽ ነበር።…” በማለት ጮክ ብዬ ሥናገር ይህንን የብሶት ንግግር የሰማው ባአዳራሹ የሞላው ለቅሶ ደራሽ ሁሉ በሣቅ ገነፈለ።
“እውነቴን እኮ ነው።ይሄ ያሥቃል?” በማለት ኮሥተር ብዬ ካረጋጋኋቸው በኋላ የአሜሪካ ጥጃዬን ታሪክ አሳጥሬ፣ ችግሬን ትቀርፍልኛለች ያልኳት ጥጃ በምግብ እጥረት ሥጋዋ ከአጥንቷ ጋር ተጣብቆ በወጣው በገባው ቁጥረ፣ ሥታየኝ ፣ዓይኖ እየተንከራተተ ፣እኔም በሞባይሌ አያሌ ፣የጭድ ክምር እና አረንጓዴ ምድር አያሣየኋት፣ተሥፋን በመመገብ ላኖራት ሥላልቻልኩ፣ እጅግ እያዘንኩ ለሦስት ሰው እንዳቃረጥኳት አውርቼ ሣበቃ…
“ይህ ወግ ‘ከፍራሽ አዳሹ ‘ ከጋሼ ተስፋሁን ወግ ይበልጣል።ኧረ ፣ እንደውም እጥፍ ያሥከነዳል። “ብሎ ተረበኝ።አጠገቤ የተቀመጠው እራሰ በርሃ “እንዴት!?” ብዬ በመገረም ጠየቅሁት።
“እንዴት ማለት ጥሩ ነው።”በማለት ወገኛነቱን አሥመሰከረ ና በሞጭሞጫ ዓይኑ አተኩሮ ተመለከተኝ።
“ምን ታፈጣለህ።”እንዴት?” ብዬ ለጠየቅሁ መመለሥ እንጂ ወግ ሥታሳምር ልትከርም ነው እንዴ? በማለት ጮኹበት።
“ምን ያሥጮህኻል።የዛሬ ሁለት ዓመት የሞተችው ጥጃህ ሐዘን እንዴት እሥከዛሬ አለቀቀህም እንዴ ?! ” ብሎ ድንኳን ሙሉ ሣቅ አሸከመኝ። በዚህ መች በቃው ቀጠለና
“ደሞ አያፍርም በቁሟ የሟተችውን ጥጃ ፣ለአራት እንዲቃረጡ ለምኜ ‘ይህቺ አጥንታም፣ለአራት ይቅርና ለሦሥትም አትሆን።እንደው ሥላሳዘንከን በ150 ብር ለሦሥት ተቃርጠን አጥንቷን እንቆርጥም።አሉኝ።ለሦሥት ካልሆነ ምን ሥጋ አላትና ምኗን እንበላዋለን ? ‘አሉኝ ይለናል እነዴ? “በማለት ፣ጮክ ብለው ሢናገሩ፣ የለቅሶ ቤት ድንኳኑን በሳቅ ብዛት ተተረተረ።አሥባለብኝ።ድፍን አሥተዛዛኙ የኮረኮሩትን ያህል በመሣቁ እኮ ነው።ድንኳኑ የተተረተረው።
“በህዝብ ሣቅ ለመጀመሪያ ጊዜ ‘የአዳም እና ሄዋን መረዳጃ ዕድር ‘ ድንኳን ጣሪያ በመተርተሩ በዓለም ‘የጂነሥ’ መዝገብ ዕድርተኛው በሙሉ እንዲመዘጉብ አደርጋለሁ።” ሲሉ የዕድሩ ዳኛ በኩራት ተናገሩ።
“እሱ ይቅርና ዕድሩን ለዕድርተኛው ሣይሆን ለራሳቸው መጠቀሚያ ያደረጉት ከነገ ጀምሮ ቢሙዘገቡልን መልካም ነው።ማነው አዲሥ ድንኳን ለገንዘብ ሲባል ለሰርግ፣አሮጌ ድንኳን ደግሞ ለለቅሶ ሲል ያወጀው? አቃቢ ህግ የሚባል ካለ ይህንን ያጣራልን” አሉና “ወንድሜ ፣እንዴት ?ብለህ በጨዋ ደንብ የጠየቅኸኝን ጥያቄ ልመልስ። እየውልህ…”በማለት ወጋቸውን ቀጠሉ።
“…እኔም የአሜሪካን ላሞች ከ17 ዓመት በፊት ገዝቼ ፣ ውይ!ውይ!ውይ!” ሲሉ ጮኹ።በለቅሶ ድንኳኑ ውስጥ ያለ ሰው ሁሉ እንደገና በሣቅ ፈረሰ።
“አንዴ ምን ሆኑ?አመመዎት እንዴ?”
“ሂድ ወድያ! ‘አመመዎት ‘ እያለ ያሞርትብኛል እንዴ? የሤጣን መቋምያ ይዝህ አትዙር።ጣለው።”አሉና በረጅሙ ተነፈሱ።ትንፋሻቸው የነሐሴ ጎርፍ ሆኖ አፍንጫዬን ሰርስሮ ናላዬን አዞረው እና ሦሥቴ አሥነጠሥኩ።እሳቸው ይማርህም ሣይሉ ወደወጋቸው ተመለሱ።
“ያሥጮኸኝ እነዛ ከተቸገረ ሰው የገዛኋቸው አራት የአሜሪካ ላሞች ቀለባቸውን አልችል ብዬ በአንድ ዓመት ውስጥ ከላምነት ወደ ጥጃነት መቀየራቸው ፊቴ ድቅን ብሎ ነው። የጮኩት።ከዛ በኋላ ግን በጣም በመንቃቴ የቻይና ላሞች ከቤጃንግ ከሚያሥመጣ አንድ ወዳጄ ላይ ገዝቼ ከቀለብም ሆነ ከሌላውም ወጪ ተገላገልኩ።”
“እንዴት?”
“ምን መሰለህ፣የቻይና ላሞችን ታያቸዋለህ እንጂ አትዳሥሣቸውም።ትገዛቸዋለህ እንጂ አትሸጣቸውም።ታልባቸዋለህ እንጂ ወተታቸውን አጠጣም።ታርዳቸዋለህ እንጂ ሥጋቸውን አትበላም።በአጠቃላይ ለላንቲካ ነው የምትገዛቸው።
ግልፅ ላድርግልህ፣የቻይና ላም ማለት በ25 በር የምትገዛው የሚያምር ‘የአሜሪካ ላም ፖሥተር ‘ ያለበት፣ ምሥል እኮ ነው።..”በማለት የወሬ ቅኔውን ሢያሣርግ፣ የዕድሩ ዳኛ ከሰው ጋር እየተንከተከቱ ፣
ኧረ ለድንኳኑ እዘኑለት ጎበዝ። በማለት ህዝቡ ሣቁን እንዲቀንሥ አሥጠነቀቁ።
‘አይገርምላችሁም !’ ለድንኳኑ እዘኑለት ይላሉ።ቅኔ መሆኑ ነው ?ለመሆኑ ድንኳን በምን ይመሠላል?… የእኛ ሰው እኮ በእንደዚህ ዓይነት ቅኔነው፣”ጠቅ ” የሚያደርግህ። አዳሜ በነገር መርፌ ጠቅ ማድረግን ተክኗል።የከተሜው ሰው፣ ከሊቅ እሥከ ደቂቅ፤ ከጎረቤትህ፣ከሥራ ባልደረባህ፣ከትምህርት ቤት ጓደኛህ፣ከዕድር እና ባልትና አባልህ አለፍ ሲል ደሞ ፣ ከፖለቲካ አባልህ ጀምሮ፣ ሁሉም በነገር ጠቅ አድራጊና እና አሽሙረኛ ነው። “ዞር ሲሉ ቡጭቅ። ” ሆናል እውነተኛ ኑሮአችን።
ማንም ሰው፣ኃይማኖተኛም ሆነ ኢ አማኒ ሥለ ሰው እና ሰው መሆን አብዝቶ ሲጨነቅ አይሥተዋልም። ትግሉ የተሻለ ኑሮ ለመኖር ምን ልፍጠር ነው?..ወዳጄ ከሺ አንድ ፀሎተኛ ብታገኝ ታድለሃል።እውነተኛ ፀሎተኞቹ ዋልድባ ናቸው።ጓለጓታ ላይ የምናገኛቸው እነሱን ብቻ ነው።
ህዝብ አዳም፣ እራቁቱን ተወልዶ፣ዛሬ የተሻለ ፣ባሥ ሲልም “የአሜሪካን ላም ኑሮ” ቢኖርም፣ ነገ ወደአፈር ሲገባ አንዳችም ይዞት የሚሄደው ነገር እንደሌለ አለመገንዘቡ ያሣዝናል። …
በእውነት ያግኝ አልያም በማጭበርበር ወይም በዝርፊያ ፣ ሁሉንም ሀብቱን ላሉፋበት፣ላልደከሙበት ትቶት ይሄዳል። ” ቻው ቸልሲ።” አለ ሞሪኖ።
ሥለማጭበርበር ሲነሳ ምን ትዝ አለኝ መሰላችሁ? በዚህ ሰሞን ለብልፅግና ፖርቲ ማጠናከሪያ ገንዘብ አዋጡ መባሉን ታውቃላችሁ አይደል? እናም አንድ የዋህ ሱቁ ካድሬዎች ዘልቀው “ለብልፅግና አዋጣ “ቢሉት
እንዴት ለብልፅግና አዋጣ ትሉኛላችሁ? የምን ማሾፍ ነው? በማለት አገር ይያዝልኝ አለ። የብልፅግና ካድሬዎችም ያው ከደርግ ሲወርድ፣ሢዋረድ የያዛቸው ፣ህዝብን በእጅ ጥምዘዛ መዝረፍ አለቀቃቸውምና ፣በነጋዴው መልሥ ተናደዱ። እናም በቁጣ “ምነው ‘አብን’ ነው ፣የምትደግፈው አንዴ!?”በማለት አንዱ ካድሬ እንደ ተዋጊ በሬ ፊቱ ላይ ግንባሩን አሥጠግቶ ጠየቀው።
“በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ! ድሮስ የማን ደጋፊ ልሆንላችሁ ነው ?’አብን’ ካልደገፍኩ በወልድ መደገፍ ከቶስ እችላለሁን? ደግሞስ ሥለ ምንድነው በዚች የሦሥት ሺ ዕቃ ባልያዘች ሱቅ እኔ ደሃ ሆኜ ለብልፅግና የማዋጣው ?ማነው በእኔ ገንዘብ መበልፀግ ያማረው? ሰው ነው ወይስ ጉም? የምታወሩት ፈፅሞ አልገባኝም። እኔን ለማበልፀግ ከፈለጋችሁ ግን ትንሿን ጣቴን አትቁረጡ።ተውኝ።…” አላቸው።……..
ይህ ሽሙጥ፣ከላይ ከተነሣው ከአሜሪካ እና የቻይና ላም የልዩነት ትረክት ጋር ተደምሮ ብቻዬን ያብሰለሥለኝ ጀመር። ፊት፣ለፊት የማያቸውን የሐዘንተኞቹን የተጎሣቆለ ፊት ሳስተውል ደግሞ የበለጠ አዘንኩ።
በመሥተዋል መነፅር ፣ዙሪያ ገባዬን ሣሥተውልም፣በዙሪያዬ የተቀመጠው ሁሉ፣ ጎሥቋላ ነው። በድንኳኑ አንድ በቸኛ የድሎት ሰው ባለመኪና ቁልፉ ይመሥላል። የሚያወራው ሥለአሜሪካ ብልፅግና እና የአሜሪካ ላም ነው። አሜሪካ ላሞቿን የምትቀልበው ማንን እየበዘበዘች እንደሆነ ግን አያውቅም።…ወይም ራሱ በህዝብ ላይ ተጠብቆ የሚበዘብዝ ጥገኛ በመሆኑ የአሜሪካ ብዝበዛን ቢያውቅም እሱም ‘ሚጢጢው በዝባዥ’ በመሆኑ የህዝቡ ህመም አይሰማውም።
ለመሆኑ፣ መቼ ይሆን የእኛ ምሁር፣ባለፀጋ ና የፖለቲካ ሰው፣ እንደአሜሪካ ምሁር፣ባለፀጋና የፖለቲካ ሰው የሚያሥበው?!ህዝቡሥ መቼ ይሆን ቻይና ሀገር የታተመውን የአሜሪካን ላም ሥእል እየገዛ እና እሱን ቤቱ ሠቅሎ በማየት በተሥፋ መኖር በቃኝ ማለት የሚጀምረው?!…እየልኩ በጥልቅ እያሰብኩ እያለሁ ፣ በድንኳኑ ወሰጥ የተገኘውን አሠተዛዛኝ በሞላ ራት የሚያበሉ ፣የሐዘንተኞቹ ጎረቤቶች ራት ለማብላት ሲያወካኩ ከሃሳቤ፣አናጠቡኝ።