ዲያብሎስ ሠራዊቱን ከሲዖል ቢጠራም
የተዋሕዶ ልጆች ሞትን አንፈራም
አንፈራህም ከቶ የዲያብሎስን አሽከር
ክብራችን ነውና ለእምነት መመስከር።
እንደነ ሚልክያስ እንደነ ሚሊዮን (የ 22 ማዞሪያ ሰማዕታት)
ደማችን ፈሶበት ቢደፈርስ ጊዮን
በዲያብሎስ ሠራዊት እኛ መሞት ፈርተን
ከቤተ መቅደሱ አንሄድም ሸሽተን።
ታዝዢያለሁ ብለህ ታቦት ላይ ብትተኩስ
የተጣባህ መንፈስ ያ እርጉም! ያ እርኩስ!
በገንዘብ በሥልጣን ያው ቢደልልህም
ካምላካችን ቁጣ አይታደግህም ።
ጦር ጎራዴ ይዘው በእምነት የዘመቱ
ዮዲትና ግራኝ ግራዚያኒም ሲሞቱ
ተዋሕዶ ቆሟል ጸንቶ መሠረቱ
ይጠፋል ብላችሁ አትድከሙ ከንቱ።
አረብና ግብጹ ፈረንጁም ከማዶ
ነጃሳ ብርና ነጃሳ ሰው ሰድዶ
አገርን ሰርስሮ ዳርቻዋን ንዶ
ሊያጠፋት ቢሞክር ዛሬ ተዋሕዶ
ጸንታ በመቆሟ ሆኖበታል መርዶ።
ሰዓቴ ነው ብሎ ቢያበዛ ሸብ እረብ
እየተጠራራ ዲያብሎስ ቢረባረብ
ሚካኤል ምን ይዟል? ገብርኤል ምን ይዟል?
ጽዋው እንደሁ ሞልቷል፣ ሰይፉ እንደሁ ተመዟል።
ሰይፉ እንደሁ ተመዟል ይልቅ ይሄን ቅጽበት
በሲዖል ጉዟችን ከምንገፋበት
እንታረቅና ንሥሐ እንግባበት
ዘየማን እንሁን እንጠቀምበት።
ሲዖልን በምድር አንፍጠር በዓለም
ባምናው መንገዳችን አንበል ወለም ዘለም
ይቅርታ እንባባል ያልበደለ የለም
ጥሪያችን ይመጣል አንኖርም ዘላለም።
መታሰቢያነቱ በሐረር፣ በወልዲያ፣ በጂግጂጋ፣ በ22፣ በጂማ፣በዶዶላ፣ በሲዳማ፣ በድሬ ዳዋ በታቦት ፊት ለተሰዉ የተዋሕዶ ካህናት እና ምእመናን ይሁንልኝ።
ከአሁንገና ዓለማየሁ። የካቲት 2012