የጥላቻ ንግግርን ና ሐሰተኛ መረጃን አሠመልክቶ የወጣው አዋጅ ግልፅነት ይጓድለዋል – መኮንን ሻውል ወለደጊዮርጊስ

 “እውነት ነፃ ታወጣሃለች”

“ፀረ ተሃድሶ ፀረ ለውጥ ” ነህ ብትሉኝም፤ እኔ ግን አይደለሁም።
ትላንት እንደምታውቁኝ ነኝ ፤ ኩሩነቴን አልተውኩም።
የምደሰት ሰው አይደለሁም ፤ እንደእናንተ ቅርፅ በመቀያየር
የኩኩሉ ጨዋታችሁን ብተውት ኖሮ ፣አበሬአችሁ በተሠለፉ ኩ  ነበር።
ለውጥ፣ለውጥ! ለውጥ አትበሉኝ ፣በልተለወጠ ነገር
ለውጦ፣እውነትን ያሳየን ያ የኖህ አብዮት ብቻ ነበር።
ያሥደንቃል፣ በሸፍጥ ያልተሞላው ለውጥ ፣በኦሪት ሲነገር።
በፈጣሪ የማያባራ ዝናብ  የታገዘ ፣ መሆኑ ሥር ነቀል
ኖህን ተሰናዳ ብሎ፣ፈጣሪያቸውን የዘነጉትን ሁሉ ሲገል።    ያ ታላቁ ለውጥ  ፣ የታጀበ በዶፍ ዝናብና በማዕበል።
ሁሉን ሲያንበረክክ ፣ወደ ጥርስ ማፏጨትም ሲዷል።
ታቃላችሁ እናንተም ያኔም ዳቢሎስ ዳግመኛ እንደተታለለ
ሰውን ከምድር አጠፋሁት ሲል፣ ኖህ በዘዴ ህይወትን እንዳሥቀጠለ።
ይህንን በማለቴ ፀረ ተኃድሶ፣ፀረ ለውጥ ብትሉኝም
ዛሬም፣በኖህ መርከብ ተሳፍሬአለሁ እና እኔን አታገኙኝም።
   (የግጥሙ ጭብጥ ከመክሲም ጓርይኪ ዩኒቨርስቲዎቼ ከተሰኘ ድርሰት የተወሰደ ግን ደግሞ የግል ምልከታ የታከለበት  ነው። በአንቀፅ 6 መሠረት የተፃፈ)
……………………………………………………..
የጥላቻ ንግግርና የሃሰተኛ መረጃ ስርጭትን …
 ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣው  አዋጅ ግልፅነት ይጎድለዋል።
     ይህንን ጉድለት የፈጠረውም ችኮላ እና ጥድፍያ ይመሥለኛል።ይህ ጥድፊያ  እና ችኮላ ደግሞ “ሊበሏት ያሠቧትን አሞራ ጅግራ ለማለት ታሥቦ ነው።”
የሚል አንደምታን ፈጥሯል።የዚህን  አዋጅ ፊትና ጀርባ መለየት አቅቶናል እና በሚገባ በእውቅ ባለሙያዎች ይጠረብ የሚሉ   በተለያየ ሚዲያ ድምፃቸውን ከማሰማታቸውም በላይ ፣ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ድርጅቶችም ” ይህ አዋጅ የመናገር እና የመፃፍ ነፃነትን ሊያፍን ይችላል።” በማለት ሥጋታቸውን ገልፀዋል።
   እርግጥ ነው፣ከሰለጠኑት ሀገሮች ፣የጥላቻ ንግግር ትርጉም አንፃር፣ የእኛ አዋጅ ሲቃኝ ግልፅነት ይጎለዋል።
በራሱ ብሔር የሚለው የግእዝ ቃል “ሀገር ” “ማለት  ሆኖ ሣለ፣ብሔረ ሰብ ደግሞ “የሀገር ሰው” የሚል ትርጉም እያለው “የጥላቻ  ንግግር” ማለት በአንድ ሰዉ ወይም የተወሰነ ቡድን ላይ ያነጣጠረ፣ ብሄርን፡ብሄረሰብንና ህዝብን፣ ሀይማኖትን፤ ዘርን፣ ጾታን ወይም አካል ጉዳተኝነትን መሰረት በማድረግ ጥላቻን፣ መድሎን ወይም ጥቃትን የሚያበረታታ ንግግር ነው። “ተብሏል። ይህ ቢጮኽ፣ቢለፈፍም ምሁር የተባለው ሣይቀር ለቃሉ የራሱን ፖለቲካዊ ትርጉም እየሰጠ  ይኸው  እሥከዛሬ በቃሉ ያልተገባ አተረጓጎም ሳብያ መነታረኩ እንዲቀጥል አዋጅ ሆኖ እየወጣ ነው።
  ንትርኩ ሳያባራ እና በተገቢው ቃል ፣ “እኛ የኢትዮጵያ ህዝቧች፣ብሔር ፣ብሔረሰቦች…” የሚለው ህገ መንግሥት  በተገቢው ቃላት ሣይሥተካከል፣የቋንቋ ፖለቲካው ከጥላቻ ሣይላቀቅ ይህ አዋጅ  መውጣቱ ተገቢ አይደለም።ጥላቻን የሚዘራ ቋንቋዊ አከላለል(የእኛ እና የነሱ ) እያለ እንዴት ነው የጥላቻ ንግግር አዋጁ ተግባራዊ የሚሆነው??? በማለት የበሰሉ ምሁራን ጥያቄ ያነሳሉ።
     አንድ ሰው ለሌላ ሰው ጥላቻ አይኑረው ማለት አይቻልም። ሰው፣ሰውን  የጠላበትን ምክንያት ጠቅሶ ፣ቢናገር አትናገር ማለት እንዴት  ይቻላል?ይህ እኮ ተፈጥሯዊ መብቱን መከልከል ነው።አንድ ሰው ዲዳ ካልሆነ በሥተቀር ከንግግር እንዴት ታግደዋለህ ???መጥላትም ሆነ መውደድ ግለሰባዊ ሆኖ ሣለ እንዴት በቡድን እንዲያሥብ በአዋጅ ልታሥገድደው ትችላለህ???
   መባል የነበረበት ፣ “በዚህ አዋጅ አግባብ መሠረት የጥላቻ ንግግር ማለት ፣በህዝብ መካከል ፣ያለመተማመንን የሚፈጥር፣ለግጭት የሚያነሳሳ፣ድንገተኛ ሁከትን የሚፈጥር፣በጎሣ፣በዘር፣በኃይማኖት፣በባህል፣መልክ እና መሰል በሆኑ ማንነቶች ላይ ያነጣጠረ በማንኛው መንገድ ለህዝብ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የሚሰራጭ ንግግር ነው።(ሐሰተኛ መረጃም  በዚሁ ትርጉም መሠረት ይተነተናል።)
    ይሁን እንጂ፣ የጥላቻ ንግግርም፣ሃሰተኛ መረጃም “ንግግር” ተብለው መተርጎማቸው የሚያወነዣብር ነው።መረጃ እንዴት  ንግግር እንደሚሆን ግልፅ ትንተና የለውም።”በሐሰት የተቀነባበረ  የጥላቻ መረጃ በንግግር፣በፅሑፍ፣በመልዕክት ወዘተ ማሰራጨት እና ህዝብን፣ቡድንን፣ተቋምን ወዘተ  ማሸበር ” ቢባል እንኳ ያሥኬዳል። ሃሰተኛ መረጃ እውነት ያልሆነ ዜና፣ኩነት  ፣የጥቃት፣የሁከት፣የመንግሥት ድርጊት፣ሞት፣ወዘተ ሊሆን ይችላል።…
  ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ፣በተለያዩ ሶሻል ሚዲያዎችም ሆነ ፣ “በአውራ ሚዲያዎች” ማለትም በሠለጠኑ ጋዜጠኞች በሚመሩ ጋዜጦችና ቴሌቪዢኖች ሊተላለፍ ይችላል። እነዚህ የወሬ፣የማንቅያ እና የማዝናኛ አውታሮች ደግሞ በሀገር ውስጥ እና በውጪ ሀገር የሚገኙ መሆናቸው ይታወቃል። እነዚህ  “በተለያየ መንገድ የሰውን ሃሳብ በመቀበል የሚያሥተናግዱ ሃሰተኛ መረጃ አሥተናግዳችኋል ። “በማለት እንዴት ሊከሰሱ ይችላሉ? ሃሰተኛ መረጃ የሰጠው ሰውም ፣ ሆነ የጥላቻ ንግግር የተናገረው ውጭ ሀገር እሥከሆነ ድረስ የኢትዮጵያ መንግሥት ህጉን ተግባራዊ ማድረግ እንዴት ይችላል?።ያወጣው ህግ በዓለም አቀፍ ህግ ባለመደገፉ የሚተባበረው የለምና!
   “ሐስተኛ መረጃ” ማለት፣ ውሸት የሆነና የመረጃውን ውሸት መሆን በሚያውቅ፣ ወይም መረጃውን የሚያሰራጨው ሰው ካለበት አጠቃላይ ሁኔታ አንጻር የመረጃውን ሃሰተኝነት ሊያውቅ ይገባ ነበር የሚያስብል በቂ ምክንያት እያለ የሚሰራጭ ሁከት ወይም ግጭት የማስነሳት፣ ወይም ጥቃት እንዲደርስ የማድረግ እድሉ ከፍ ያለ ንግግር ነው።”
   ይህ ትርጉም በራሱ፣በቋንቋ ምሁራን ያልታየ ዝብርቅርቁ የወጣ ሃሳብን የያዘ እና የተወሳሰበ፣ ለትርጉም፣ የሚያሥ ቸግር  ነው።
   “ውሸት የሆነ እና ውሸት መሆኑን በሚያውቅ …መረጃውን ያሰራጨው ሰው ካለበት ካጠቃላይ ሁኔታ አንፃር የመረጃውን ሐሰተኝነት ሊያውቅ ይገባ ነበር የሚያስብል የሚሰራጭ ሁከት ወይም …” ማለት ምን ማለት ነው?
     ሃሰት ወይም ውሸት በዜና በዓለም ላይ ሊቀርብ የሚችልባቸው አጋጣሚዎች እልፍ ናቸው።ውሸት የሰው ለጆች ኑሮ ማጣፈጫ ነው።በተለይም ነጭ ውሸት።ሰውን ሊጓዳ የማይችል ውሸት። ለምሳሌ አዲስ አበባ ቤትህ ተቀምጠህ ናዝሬት ነው ያለሁት ብለህ ፣ብር ላበደረህ ሰው በሞባይልህ መልስ መሥጠት። ይህ “White lie ”  ይባላል።
   ነጭ ውሸት  በዚህች ዓለም ባይኖር  ኖሮ ሰው ልጅ፣ በዚህ ዓለም ሊኗኗር ከቶም አይችልም።ሰው ከሰው ጋር ተሥማምቶ ለመኖር መዋሸት ግዴታው ነው። ይሁን እንጂ
“የአንድ ሀገርን ህዝብ ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል፣ ድንገተኛ ና ሀገር አውዳሚ የእርስ በእርስ ጦርነትን ሊያሥነሳ የሚችል ፣የጥላቻ ንግግርን እና የተቀነባበረ፣በሐሰት ፎቶ፣ፊልም፣እና ፅሑፍ የተደገፈ መረጃ በማንኛውም ‘ሚዳያ’፣ማሠራጨት ክልክል ነው።ይህ ድርጊትም  አንድን ዘር ወይም ጎሣ በሥሜት ገፋፍቶ ያልተፈለገ እርምጃ ወይም ጥቃት እንዲያደርስ የሚያደርግ መሆኑ እየታወቀ  በብሮድካስት፣ በህትመት ወይም በማህበራዊ ሚድያ በጽሁፍ፣ በምስል፣ በድምጽ ወይም በቪድዮ ከተሰራጨ በ… እስራት ወይም የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል። “ቢባል በአዋጁ እሥማማ ነበር።
   ከሁሉ በላይ በአንቀፅ 6″ ልዩ ሁኔታ ”  ብሎ አዋጁ ያሥቀመጠው ፣በቁጥር 4 እና 5 እንደተጠበቁ ናቸው ብሎ ማሥቀመጥ አልነበረበትም።
. ልዩ ሁኔታ
1/ የዚህ አዋጅ አንቀፅ 4 እና 5 እንደተጠበቁ ሆኖ አንድ ንግግር እንደ ጥላቻ ንግግር
ወይም እንደ ሃሰት መረጃ ተወስዶ ማሰራጨት የማይከለከለው፡-
ሀ) የትምህርታዊ ወይም ሳይንሳዊ ምርምር አካል እንደሆነ፤
ለ) የዜና ዘገባ፤ ትንታኔ ወይም የፖለቲካ ትችት አካል እንደሆነ፤
ሐ) የኪነጥበበ ፣ ትወና ወይም መሰል የስነጥበበ ውጤት ከሆነ፣
መ) የሃይማኖታ አስተምህሮት አካል እንደሆነ ነው።
    እንዲህ ዓይነቱ ያልተብራራ ህግ፣”ና በለው ሆኖም እንዳይመጣ አድርገው።ወይም እንዲመጣ ጥራው እንዳይበላ ግፋው። “በተባለ  የአበው ቅኔ ታሽቶ የተቀረፀ ይመሥላል።
   ይህ አዋጅ ፣ ህግ አሥፈፃሚውን  ያልተገባ እሥር እንዲፈፅም ያደርገዋል። በህጉ ክፍት ሳቢያም  ንፁህና ባለእምሮ ሰዎች ሊታሰሩ ይችላሉ። ሀግ ነፃ እሥከሚያወጣቸው  ድረሥም፣ በእሥር ሊንገላንቱ ፣ሊጉላሉ  ፣ባሥ ሢል ደግሞ ሥቃይ ና ቶርቸር ሊደርስባቸው ይችላል።…
    ይህ እኩይ ድርጊትም  ቀና መንገዶችን የሚያመላክቱ፣ ፀሐፍትን፣ሐያሥያንን፣ በአጠቃላይ የነቁ እና የበቁ  የብዕር ሰዎችን ያሸማቅቃል። ነፃነታቸውንም ያኮሥሣል።በእጅ አዙርም ሣንሱር ነግሦ ፣ተፈጥሯዊ የሆነውን የመናገር መብት ያፍናል።ሰው ሃሳቡን በነፃነት በፅሑፍ እንዳያቀርብም እጁን አሥሮ ላልተገባው ህግ ሠጋጅ ያደርገዋል።
     የዚህ ያለተገባ ድርጊት ፍፃሜም  አጠቃላይ የሀገር ውድቀትን ያሥከትላል።ህዝብ ፊት ለፊት ሐሳቡን እንዲናገር
ያለመሸማቀቅ እንዲተች የሚያሥችሉ የተለያዩ መድረኮችን መፍጠር ሲገባ፣ ያለውንም መድረክ ሊያጠፋ የሚችል ግልፅ ያልሆነ አዋጅ ማውጣት ፣ ህዝብ በየቀየው በመንግሥት ላይ እንዲያጉረመርም ያደርገዋል። ለጥላቻ ንግግርም ሆነ፣ለሐሰተኛ መረጃ የወንጀለኛ መቅጫ ህጋችን በቂ ነበር።…
ተጨማሪ ያንብቡ:  ኣላሙዲን ሶስት ዘፋኞችን ሚሊየነር አደረጉ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share