ባለፉት ወራት ባገራችን የተከሰተውን አሳዝኝና ትርጉም የለሽ ግድያን በተመለከተ የተለያዩ የመንግሥትና የግል ሚዲያ ተቋማት በየፊናቸው ያስተላልፉ የነበረውን ዜና ከያለንበት ሆነን ስንሰማውና በቴሌቪዥን መስኮቶቻችን ስንመለከተው እንደነበር ይታወሳል። አዎ! ሰዎች በግልጽ በአደባባይ እየተቀጠቀጡ ሲገደሉ አይተን በእጅጉ አዘንን። እጀግ በጣም አሳዛኝና ምነው ኢትዮጵያ ውስጥ ባልተፈጠርኩ የሚያሰኝ የጭካኔ ጣራ የታየበት ዓመት! በወጣትነት ዘመናችን ሲነገረን የነበረውና እኛም እንደወረደ ስንጋተው የነበረው ኢትዮጵያዊ ጨዋነት፣ ባህሉን አክባሪና ከሁሉም ጋር ተስማምቶ በፍቅር ኗሪ፣ የደከመውን የሚያበረታታና ያዘነውን የሚያጽናና፣ ፈሪሃ እግዚአብሄርን በመላበሱ በአምላክ ፍጡር ላይ ጉዳትን የማያደርስ ቅዱስ ሕዝብ ወዘተ የሚባለው ባሕላዊ እሴቶቻችን ወዴት እንደተነኑ በበኩሌ አልገባ ካለኝ ውሎ ሰንብቷል። የዚያኑ ያህል የሚዘገንነው ደግሞ የሕዝባችን ከሚያየው ይልቅ ከሚሰማው ብቻ ተነስቶ እርምጃ ለመውሰድ ያለውን ችሎታ ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ እንዳስተዋልኩት ከሆነ ሕዝቦቻችን የሚሰሙትን ወሬ እውነተኝነት ለማረጋገጥ ሴኮንድ እንኳ ሳያጠፉ፣ የሰሙትን ወሬ እንዳለ፣ ከተቻለም ጆሮያቸው ሊሰማ በሚፈልገው ልክ አመቻችተው ተመሳሳይ አስተሳሰብን ለሚያስተናግዱ ጓደኞቻቸው ያቀብላሉ፡
- በዚሁ ሂደት ውስጥ ውጭ አገር የከተሙ የግል ሚዲያዎችና አፍቃረ – ፌስቡኮች ደግሞ ወሬው እንደደረሳቸው ለአርዕስታቸውም እንደሚመች አሳምረውት፣ አገሪቷ ከሰሜን እስከ ደቡብ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ታምሳና ሕዝቦች ተገዳድለው ሕልውናዋ በቀጭን ገመድ ላይ ተንጠንጥሎ ይገኛል ብለው ማስተጋባት ይጀምራሉ፡፡ የወሬዎቹ ይዘትም ወገንተኛና አንዱ ቡድን በሌላው ላይ ስላደረሰው ወይም ሊያደርስ ስለተዘጋጀው ጥቃትና እንዴት ለመከላከል ብሎም ለመልሶ ማጥቃት መዘጋጀት እንዳለባቸው ነው፡፡ በአጭሩ፣ በአገሪቷ ሰፍኖ ያለው ድባብ “እኛና” “እነሱ” በሚል ሁለት ጎራ የተከፈለ ይመስለኛል፡
- የዚህ ሁሉ ፊታውራሪ ደግሞ ከሁሉም ብሄር የተውጣጡ፣ ሳይወከሉ ተወክለናል ወይም የሕዝባችን አደራ አለብን የሚሉ ጽንፈኛ ኤሊቶች ናቸው፡፡
ግን ለምን እንዲህ ሊሆን ቻለ? ለምንድነው ታዋቂ በሆኑ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ የትምህርት ተቋማት ሳይቀር የፊደል ቆጠራ ጉብዝናቸውን ያስመሰከሩ ኤሊቶቻችንን ስላገራችን ነባራዊም ሆነ ወቅታዊ ፖሊቲካዊ፣ ኤኮኖሚያዊና ማሕበረሰባዊ ችግር በትክክል እያወቁ ወይም ማወቅ ሲገባቸውና፣ ለዘመናት ነቀርሳ ሆነው ውስጥ ድረስ በልተውን ከደሃ አገሮች ተርታ ብቻ ሳይሆን መጨረሻ ላይ ያሰለፉንን እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ መረባረብ ሲገባቸው፣ ሁላቸውም በየጎሬያቸው መሽገው “የማንነትን ጥያቄ” በማንገብ ሕዝብን ለሕዝብ ጋር ለማጋጨት የተሰለፉት? ለምንድነው ዛሬ ባገራችን ያብዛኛው ኤሊት ቀዳሚ ታማኝነት ለተወለደበት ብሄር እንጂ ለሰማኒያ አምስቱ ብሄር ወይም “ለኢትዮጵያ ሕዝብ” ያልሆነው? እንደው የሶስት ሺህ ዘመኑን ታሪክ እንተውና ላለፉት አንድ መቶ ሃምሳ ዓመታት እንኳ ኢትዮጵያ በምትባል አገር ውስጥ ባንድ መንግሥትና ባንድ ባንዲራ ሥር እየኖሩ፣ ለምንድነው ሕዝቦቿ በሌሎች አገራት እንደታየው አንዱ ባንዱ ውስጥ ቀልጦ “አንድ ሕዝብ” መሆን ያልቻለው? ምን ዓይነት የሂደት ችግር ቢፈጠር ነው የዛሬ መቶ ሃምሳ ዓመት የነበረው ሰማኒያ አምስት የየራሱ ቋንቋ የነበረው ብሄር ዛሬም ከመቶ አምሳ ዓመት በኋላ ሰማኒያ አምስት ብሄርና ሰማኒያ አምስት ቋንቋ እንዳለ ይዘን የቀረው? የት ቦታ ላይ የአገር ምሥረታው ስልት ቢጠፋብን ነው ዛሬ፣ ከመቶ አምሳ ዓመታት በኋላ፣ “ማንነቱና ቋንቋው ከስሞ አማራ ሆነዋል” በመባል የታወቁ የአገውና የቅማንት ሕዝብ፣ “የለም በአማራ ተጨቁነን ማንነታችን ተዳፍኖ ነው እንጂ አልከሰምንም” ብለው የማንነት ጥያቄ የሚያቀርቡት? አዎ ባንድ ባንዲራ ሥር ለዚያን ያህል ዓመታት የኢትዮጵያ የግዛት አንድነቷ ተጠብቆ፣ ሕዝቦቿ ደግሞ በተለያዩ ጊዜያት የውጪ ወራሪ ኃይልን ባንድ ላይ ሆኖ ተከላክሎ የግዛቷን አንድነት አስከበሮ የኖረውን ያህል የሕዝቦቿ አንድነት ዕውን ሆኖ አንድ ሃገረ ብሄር ለመሥረት ያልቻልነው ለምንድነው ብሎ መጠየቅ ተገቢ ይመስለኛል። አንዳች ዓይነት ምክንያት ቢኖር ነው እንጂ፣ የውጪ ወራሪ ኃይል ሲመጣ ሆ ብሎ ባንድ ላይ ዘምቶ ድልን ከተጎናጸፈ በኋላ ሁሉም ወደየጎሬው ተመልሶ ባንድ ላይ የተጎናጸፈውን ድል አንድ ላይ ሆኖ እንደማጣጣም፣ ውሃና ዘይት ሆኖ ጎን ለጎን መኖርን እንደ ትክክለኛ የጉርብትና ኑሮ ዘይቤ አይቆጥርም ነበረ። ይህንን ምክንያት ለይቶ አውቆ መፍትሄ ፍለጋው ላይ መረባረብ ግን ተምረናል ከምንል ኤሊቶች የሚጠበቀብን አገራዊ ግዴታ ነበር። እየሆነ ያለው ግን ተቃራኒው ነው።
ሌላው ከዚህ ጋር የተያያዘው አሳሳቢ የሆነው ጉዳይ ደግሞ፣ የፖለቲካ ድርጅቶች ደጋግመው ሲያነሱት የምናየው የውሸት መፈክር “ሕዝቡ አደራ ሠጥቶናል” “ሕዝቡ ይህንን ወይም ያንን ይፈልጋል” “ከሕዝቡ አደራ ተቀብለናል” “ይህንን አደራ ከግቡ የማድረስ ግዴታ አለብን” ወዘተ የተሰኙ ወና የሆኑ ቅጥፈቶች ናቸው፡፡ ለወደፊት የሚሆነውን አላውቅም እንጂ በዘመናዊው ያገራችን ታሪክ ውስጥ ሕዝባችን ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ አንድም ጊዜ “ወክሉኝ” ብሎ አደራ የሠጣቸው ግለሰቦችም ሆኑ የፖሊቲካ ድርጅቶች አልነበሩም፡፡ ሳያድለን ቀርቶ፣ የሶስት ሺህ ዓመት ሥልጣኔም ሆነ ለቅኝ ገዢዎች ያለመንበርከክ አኩሪ ታሪካችን ግን የፖሊቲካ ንቃታችንን በአንዲት ሴንቲሜትር እንኳ ከፍ ሊያደርግ አልቻለም፡፡ ስም ያልተገኘለት ሁላችንንም
- ጸሃፊው ቀድሞ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባላሥልጣን የነበሩ የዓለም አቀፍ ሕግ ባላሙያ ናቸው፡፡
እያጠቃን ያለው በሽታ! የዚህ ጽሁፌ ዓላማ የዚህን መሆን ስለነበረበት ግን ደግሞ ስላልሆነው “የሕዝቦች አንድነት” ወይም ስለከሸፈው “የሃገረ ብሄር ምሥረታ” ሂደት ሳይሆን፣ ላለፉት ጥቂት ወራት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ራሴ በግልም ሆነ በቡድን በመካፈል ስላካሄድኳቸው የሁለትዮሽ ወይም የጋርዮሽ ውይይት፣ እንዲሁም ባጠቃላይ በየዕለቱ የታዘብኳቸውን አሳሳቢ የሆኑ አገራዊ ጉዳዮችን በተቻለኝ መጠን ገለልተኝነቴን ጠብቄ ለኤሊቱ ለማቅረብ ነበር። ኤሊቶቹም አንብበው ዝም እንዲሉ ሳይሆን፣ እየሄድንበት ያለው ጉዞ ወደ ጥፋት እንጂ ወደ ልማት የማያመራ ስለሆነ ይህንን አሳሳቢ ጉዳይ በጋራ ሆነን መፍትሄ የምናገኝበትን መንገድ ማፈላለጉ ላይ እንዲተጉ ለማሳሰብ ነበር።
ባገራችን ዛሬ ወደድንም ጠላን፣ ብሄር ተኮር ግጭቶች በያቅጣጫው እየተከሰቱ ነው። ለምን ተከሰቱ ለሚለው ሂሳባዊ ፎርሙላ ባይኖረኝም የተወሰኑ ምክንያቶችን አሁን ጊዜና ቦታው አይደለም እንጂ ለማቅረብ እችላለሁ። የብሄር ጥያቄን በለመለከተ በስድሳዎቹ አካባቢ በኢትዮጵያ ምሁራን ጭንቅላት ተቀርጾ ወደ ተግባር ከተመነዘረበትና እኔም እንደ ያኔው ተከታይ ትውልድ ጥያቄውን በተማሪ ማህበራት ስብሰባችን ስንነታረክበት የተካፈልኩበት ስለሆነ፣ ለጉዳዩ አዲስ አይደለሁም፡፡ አዲስ ሆኖ ያገኘሁት ግን ያኔ የኢትዮጵያን ሕዝብ በተለይም የደቡብን ሕዝብ በግፍ ሲገዛት የነበረው ጨቋኝ ሥርዓት የመበዝበዣ መሳርያ
የነበረው “መሬት” በዓዋጅ የሕዝብና የመንግሥት ከሆነ አርባ ዓመታት በኋላና፣ ከ1991 ጀምሮ ደግሞ ብሄሮች የራሳቸውን ክልል በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ተብሎ የፌዴራሊዝም ሥርዓት ከሰፈነ በኋላ፣ ዛሬም ዜጎች “አማራ” “ኦሮሞ” “ቅማንት” “አገው” “ትግራይ” ወዘተ እያሉና የብሄር ጥያቄያችን አልተመለሰልንም ሲሉ መስማትን ነው። ዛሬ የትኛው ብሄር ሌላውን ብሄር እየጨቆነ ወይም የየትኛው ብሄር ቋንቋ ወይም ባሕል እንደ ብሄራዊ መገለጫ ሆኖ በሌሎች ላይ እንደተጫነ ማወቁ በጣም አዳግቶኛል፡፡
ማሕበረሰባዊ ግጭቶች እንዳይከሰቱ ለማድረግ አንችልም፡፡ የግጭቶቹን መንስዔዎች መርምሮ አጥንቶ በሠለጠነ መንገድ ችግሩን መፍታት ግን ሊሳነን ባልተገባ ነበር፡፡ ያልተማሩ አባቶቻችንና አያቶቻችን በጊዜያቸው በዘረጉት የአስተዳደርና የፍትሕ መዋቅር ተመርተው ማህበረሰባዊ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ እየፈቱ ሰላምን ማስፈን ብቻ ሳይሆን አገራችን ኢትዮጵያን ለዘመናት ዳር ድንበሯን አስከብረው ለመኖር ከቻሉ፣ እኛ ለዘመናዊ ትምህርትና እውቀት የተጋለጥን ትውልድ እንዴት የቀሰምነውን ዕውቀት በተግባር አውለን ግጭቶችን መፍታት እንዳቃተን ማወቁ ግራ የገባ ነገር ነው፡፡ ለምንድን ነው የዛሬው ኤሊት ጉድለትን ብቻ አጉልቶ በማሳየት ሕዝባችንን ለግጭት ማዘጋጀት ብቻ ላይ ያተኮረው? ሕዝባችን ከኛ የሚጠብቀው እኮ፣ ለዘመናት ያርስበት የነበረው ማረሻ፣ ሞፈር እና ቀንበርን ወደተሻለ የእርሻ መሣርያ ቀይረንላቸው ሕይወታቸው ዋጋ እንዲኖረው እንጂ፣ ሞፈርና ቀንበሩን ሰቅሎ እኛ ራሳችን ለግል ፖሊቲካ ዓላማ ለቀየስንለት “የፖሊቲካ ጥያቄ” ስኬት እርስ በርሱ እንዲዋጋ አይደለም፡፡ አዎ! ለኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን በጎ በጎውን እየተመኘን መቆርቆሩ ዜጋዊ ግዴታችን ነው፡፡ ብሄርን ከብሄር ለይቶ “ለራሴ ብሄር ብቻ” በማለት ላንዱ ወገን አድልቶ ለግጭት መቀስቀስ ግን በምድራዊውም ሆነ በሰማያዊ ሕግ ዋጋ የሚያስከፍል ይመስለኛል፡፡ ማንናችንም ወድደን ወይም ታግለን የዚህ ወይም የዚያኛው ብሄር ተወላጅ ስላልሆንን፣ የዚህ ወይም የዚያኛው ብሄር ተወላጅ መሆን አንዳችም የሚያኮራ ነገር የለበትም፡፡
ኦዎ! ችግሮቻችን ባብዛኛው ሰው ሠራሾች ናቸው፡፡ ሰው ሠራሽ ችግር እስከሆነ ድረስ ደግሞ መፍትሄው ያለው በኛው ችግሩን በፈጠርን ሰዎች እጅ ነው፡፡ ከዚህ ሌላ የችግራችን መፍቻ ተዓምራዊ ዘዴ የለም፡፡ ስለዚህ ወደድንም ጠላንም ከልብ አገራችንና ሕዝባችንን የምንወድና ቅንነቱና ፍላጎቱ ካለ ዘመኑ በሚፈቅደው “ሰጥቶ መቀበል” የውይይት ስልት ተመርተን ችግሮቻችንን በሰላም ለመፍታት ዛሬውኑ መጀመር አለብን፡፡ (“ችግሮቻችንን” ያልኩት ዛሬ በየክልሉ የምናስተውላቸውን ግጭቶች ፈጣሪዎቹ እኛ የተማርን ነን ባዮች ጽንፈኛና እፍኝ የማንሞላ መኃይም ምሁራን እንጂ መቶ ሚሊዮን የኢትዮጵያ ሕዝብማ አማራው ከኦሮሞው፣ ትግሬው ከአፋሩ፣ ጉጂው ከጌዴዎ ጋር ተስማምተው ለዘመናት ኖረዋል)፡፡ በግሌ ዛሬ ላሉን ችግሮች መፍትሄ ይሆናሉ ብዬ የማስባቸው ፎርሙላዎች አሉኝ፣ ያ ማለት ግን የኔ ፎርሙላ ፍቱን ነው ማለቴ አይደለም፡፡ እያንዳንዳችን ያሉንን ፎርሙላዎች ይዘን ባንድ ዋርካ ሥር ተሰባስበን በቅንነት ከተወያየን ግን ዘላቂ መፍትሄ የማናገኝበት ምክንያት የለም፡፡ የሚከተሉትን የግሌን አስተያየቶችና “ምክሮች” የማቀርበው በዚሁ መንፈስ ሆኖ በትክክል ሥራ ላይ ካዋልናቸው ረጅሙን ጉዞ በመጠኑም ቢሆን ያሳጥርልናል የሚል ግምት አለኝ፡፡
ሀ) ከሁሉም በላይ፣ ነገ አብረን መኖራችን ላይቀር፣ ዛሬ “በየብሔሮቻችን ጥላ ሥር ተከልለን” እና ጽንፈኛ የሆነ አቋም ይዘን እርስ በርስ መቆሳሰሉን ማቆም አለብን፡፡ መቆሳሰል በጣም ቀላል ነው፣ ቁስልን ማዳን ግን ምናልባትም ያንድን ትውልድ ዘመን ሊጠይቅ ይችላል፡፡ አንድ ሊሠመርበት የሚገባ ጉዳይ ቢኖር፣ ዛሬ የኢትዮጵያን ሕልውና የሚፈታተን ወይም ኢትዮጵያን ለማፍረስ ፕሮግራም ያለው የፖሊቲካ ድርጅት እኔ እስከማውቀው ድረስ አንድም የለም፡፡ ያ ባይሆን ኖሮ በሕገ መንግሥቱ
የተካተተውንና በዓለም አቀፍ ደረጃ እጅግ ቀላል በሆነ መንገድ መገነጣጠልን ሊያስተናግድ የሚችለውን አንቀጽ 39ን ተጠቅሞ ብዙ ድርጅቶች የመገንጠልን ጥያቄ አንስተው አገራችንን ሰማኒያ አገር አድርገዋት ነበር፡፡ ከዚያም በላይ፣ የመገንጠል ዓላማ ነበራቸው የተባሉ ድርጅቶችም ሳይቀሩ በሕገ መንግሥቱ መሠረት በሰላም መንገድ ታግለን ከሌሎች ጋር በመሆን ዲሞክራሲያዊቷን ኢትዮጵያን እንገነባለን ብለው አገር ቤት ገብተው ለሚቀጥለው ምርጫ እየተዘጋጁ ናቸው፡፡ ስለዚህ አንዳንዶቻችን ከሌሎች የበለጠ ለኢትዮጵያ አንድነት የምንቆረቆር አድርገን ራሳችንን ከፍ ከፍ ባናደርግ ጥሩ ነው፡፡ ማንም ከማንም በላይ ኢትዮጵያዊ ወይም ማንም ከማንም በላይ ኢትዮጵያን የሚወድ የለምና! የተለያየ አስተሳሰብ ማስተናገድ ደግሞ ተፈጥሮያዊ ነው፡፡ ስለዚህ “ለዘመናት አብረን የኖርን” ብለን የምንለፍፈውን ያህል፣ በተግባርም “ጽንፈኞች ከፋፍለውን ነው እንጂ ድሮም በሕዝባችን መካከል አንዳችም ልዩነት አልነበረም” ብለን በሕዝቦች መካከል የርስ በርስ ግጭትን ለመጫር ሌት ተቀን የሚተጉትን ግለሰቦችንና ቡድኖችን በጋራ ሆነን ዓላማቸውን እናክስምባቸው፡፡
ለ) ከሁሉም በላይ፣ ለምናደርገው የፖሊቲካ እንቅስቃሴ መነሻውና መድረሻው አሁን ያለው ሕገ መንግሥት መሆኑን ጠንቅቀን ማወቅ አለብን፡፡ “ሕገ መንግሥቱ ሕዝባዊ ስላልሆነ አይመለክተንም” ማለት የትም አያደርስም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በዘመናዊ ታሪኩ ውስጥ የራሱ የሆነ ሕገ መንግሥት ኖሮት አያውቅም፡፡ ለዚህም ነው “ሕገ ሕዝብ” ሳይሆን “ሕገ መንግሥት” የተባለው! ሕገ መንግሥቱ ብዙ የማይጥሙን ግን ደግሞ በቅንነት ከተወያየንባቸው በቀላሉ ሊሻሻሉ የሚችሉ ብዙ አንቀጾችን አቅፏል፡፡
- ደግሞ ዕውን ሊሆን የሚችለው ከሚቀጥለው ዲሞክራሲያዊ ምርጫ በኋላ ተወካዮቻችን ተወያይተውበት ለውሳኔ በሚያቀርቡልን ረቂቅ ሕገ መንግሥት ላይ ተነጋግረንበት ስንመኘው የኖርነውን እውነተኛውን ሕገ ሕዝብ ስናስጸድቅ ብቻ ስለሆነ ዛሬውኑ ሕገ መንግሥቱ ካልተቀየረ በሚል ቅስቀሳ ጊዜ ማጥፋቱን ትተን የሚቀጥለው ምርጫ ነጻና ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን በጋራ መሥራት ነው፡፡
ሐ) ምርጫው ከስድስት ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ እንደሚካሄድ መንግሥት አስታውቋል፡፡ ብዙዎቹ የፖሊቲካ ድርጅቶች ለብሔራዊ ምርጫ አዲስ ስላልሆኑ የቀረው ጊዜ ለዝግጅቱ የሚያንሳቸው አይመስለኝም፡፡ ለመስኩ አዲስ የሆኑ ፓርቲዎችም “ከለማዳዎቹ” ተሞክሮ በጎ በጎውን ተምረው ለምርጫው ለመዘጋጀት የሚችሉ ይመስለኛል፡፡ አንድ መረዳት ያለብንና በቅድሚያ ራሳችንን ማዘጋጀት ያለብን ጉዳይ፣ ምርጫው ያላንዳች አድልዖና ተጽዕኖ እስከተካሄደ ድረስ የምርጫውን ውጤት ለመቀበል ዝግጁ መሆን አለብን፡፡ ባገራችን ዘወትር ሲነገር የምንሰማው፣ በምርጫ መወዳደር ማለት ወይ ማሸነፍ አለያም መሸነፍ እንደሆነ ብቻ ነው፡፡ ይህ እጅግ በጣም የተሳሳተ ግምት ነው፡፡ ምርጫው ነጻና ዲሞክራሲያዊ እስከ ሆነ ድረስ በምርጫ ውጤት አናሳ ድምጽ ያገኘው የፖሊቲካ ፓርቲ ከሌላው ጋር ግንባር ፈጥሮ መንግሥት ሊመሠርት የሚችልበት ሁኔታም ሊፈጠር ይችላል፡፡ በተፈጥሮያቸው ሊቀራረቡ አይችሉም ብለን የምንገምታቸው ፓርቲዎችም “በሰጥቶ መቀበል” መሪህ መሠረት የጋራ ግንባር ፈጥረው መንግሥት ሊመሠርቱ ይችላሉ፡፡ ምርጫው ነጻና ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን ደግሞ መንግሥት ብቻ ሳይሆን እያንዳንዳችንም እንደ ዜጋ መጫወት ያለብን ሚና አለን፡፡ በየክልሉ በዞንና በየወረዳው ምርጫውን እንዲታዘቡ ብቻ ሳይሆን የምርጫን ሂደት ጠንቅቆ የሚረዳና ድምጽንም ኮረጆ ውስጥ መክተት ብቻ ሳይሆን ከኮረጆውም “ተንኖ” እንዳይጠፋ ዘብ መቆም የሚችል ንቁ ዜጋ ለመፍጠር መቻል የያንዳንዳችን የቤት ሥራ መሆን አለበት፡፡
መ) የፖሊቲካ ፓርቲዎችን በተመለከተ፣ እስከ ዛሬ ድረስ፣ አንዳቸው ከሌላውና ዛሬ ሥልጣን ላይ ካለው መንግሥት ምን የተሻለ ወይም የተለየ የትምሕርት፣ የኤኮኖሚ፣ የመከላከያ፣ የጤናና ወጣቱን ሥራ የማስያዝ ወዘተ የመሳሰሉት ፕሮግራም እንዳላቸው የነገሩን ነገር የለም፡፡ በኔ ግምት፣ እነዚህ ፓርቲዎች፣ አገር አቀፍ በሆኑ ማህበራዊና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን አቋምና ከዓቢይ መንግሥትና ከእርስ በርሳቸውም የሚለያዩበትንና የተሻለ ነው ብለው የሚያምኑበትን ፕሮግራማቸውን ዛሬውኑ ለሕዝብ አቅርበው የማሳመኛ ቅስቀሳ ማድረግ ወቅቱ አሁን ይመስለኛል፡፡ በፕሮግራማቸው ይህን ያህል የሚለያያቸው ከሌለ ደግሞ አንዱ ባንደኛው ውስጥ የማይቀልጡበት ምክንያት የለም፡፡ አለበለዚያ ግን ሁላቸውም ከተለያየ አቅጣጫ ዝም ብሎ የማይዳሰስና የማይጨበጥ ግን ደግሞ ስሜትን ለመቀሰቀስ የሚረዳ “ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለማስፈን” የሚል አንድ ዓይነት መፈክር ብቻ በማሰማት ሕዝቡን ማማለል ትርፍ አይኖረውም፡፡ ስለዚህ ያላቸውን አጄንዳ እና እኛም የዓቢይን መንግሥት ትተን እነሱን እንዲመርጥ የሚያሳምኑበትን አገር አቀፍ ፕሮግራም ዛሬውኑ አቅርበው እኛን ማወያየት አለባቸው፡፡ ከመንግሥት የተሻለ ፕሮግራም ከሌላቸው ደግሞ፣ በምርጫ ሰበብ የሕዝብን ኃብትና ጊዜ ከማቃጠል፣ አንደኛውኑ ከመንግሥት ጋር ቢወግኑ፣ ከብዙ ጣጣ እንድናለን ባይ ነኝ፡፡
ሠ) ፖሊቲካ ጥበብ ነው፡፡ በፖሊቲካ ዓለም ተፎካካሪ እንጂ ጠላት የሌለውን ያህል ቋሚ ጠላት ወይም ወዳጅም የለም፡፡ ሁሉም እንደ ሁኔታው ሊቀያየር ይችላል፡፡ ቋሚ ጠላት እስከሌለ ድረስ ደግሞ፣ “ይህኛውን ሃሳብ ከሚያራምደው ተፎካካሪ ጋር አልደራደርም” “በፌዴራሊዝም አንደራደርም” “ከጽንፈኞች ጋር አንደራደርም” ብሎ ቅድመ ሁኔታዎችን ማስቀመጥ ለችግሮቻችን ማባባሻ እንጂ መቅረፍያ አይሆኑም፡፡ ላንዲት አገር የሚመጥን “ብቸኛና አማራጭ የሌለው” ብሎ ፕሮግራም ነገር የለም፡፡ ዋናው እና ወሳኙ እያንዳንዱ የፖሊቲካ ድርጅት ላገሪቷ ተስማሚ ነው ብሎ የሚያምንበትን ፕሮግራም ለሕዝብ አቅርቦ እንዲመርጡት ሰላማዊ በሆነ መንገድ መቀስቀስ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ግን፣ እኔ ያዘጋጀሁት ፕሮግራም ብቻ ትክክለኛ ስለሆነ ሌላው ሁሉ ላገራችን አይጠቅምምና የተፎካካሪው ፓርቲ ሃሳብ ብቻ ሳይሆን ሃሳቡንም ያፈለቁ የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች መገለል አለባቸው ብሎ መቀስቀስ የፖሊቲካን ሀሁ አለማወቅ ነው፡፡ የፖሊቲካ ድርጅቶቻችን ጠንቅቀው ማወቅ ያለባቸው ዋነኛው የፖለቲካ ዕውቀት መገለጫ ምልክት የሆነውን “የሰጥቶ መቀበልን” ጥበብ ጠንቅቆ ማወቅ ነው፡፡ ባልና ሚስት ትዳር መሥርተው ብልኮ ተጋፍፈው ልጆች አፍርተው የሚኖሩት በመካከላቸው የማያግባባቸው ነገር ስላልኖረና ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ሆኖ ሳይሆን፣ “በሰጥቶ መቀበል መሪህ መሠረት” በሚያግባባቸው ጉዳዮች ላይ ጠንካራ መሠረት እያኖሩ በማያግባባቸው ላይ ደግሞ አንደኛው የሌላውን ፍላጎት ተረድቶ ላለመስማማት ተስማማተው ነው፡፡ ያ ባይሆን ኖሮ ተከታታይ ትውልድ፣ ማህበረሰብና አገርም አይኖርም ነበር፡፡ ስለዚህ የተፎካካሪን ሃሳብ በመጥፎ ዓይን አትዩት ማለቴ ነው፡፡ ለማንኛውም፣ እናንተ እኮ ሕዝብን ወክላችሁ ይህኛው ሃሳብ ከዚያኛው ለሕዝቡ ይጠቅማል ብሎ የመወሰን መብት ያላችሁ አይመስለኝም፡፡ ሕዝቡም ለዚህ ማንዴት አልሰጣችሁም፡፡ የናንተ ሚና መሆን ያለበት፣ ሕዝቡ ባቀረባችሁለት ፕሮግራም ላይ በነጻ ተወያይቶበት የሚበጀውን ለመምረጥ የሚችልበትን ነጻና ዲሞክራሲያዊ መድረክ ማመቻቸት ብቻ ነው፡፡
ስለዚህ ወገኖቼ፣ ሌላ በድብቅ የምታስተናግዱት አገሪቷን የመበታተን ዓላማ ከሌላችሁና ባንዲት ኢትዮጵያ በምትባል አገር ውስጥ በሰላም ተከባብረን አብረን እንድንኖር የምትመኙና ለዚያም የምትተጉ ከሆነ፣ ከላይ ያስቀመጥኳቸውን ወንድማዊ ምክሮቼን በተግባር ለማዋል ሞክሩ፡፡ የምንታገለው “ለአንዲት ዲሞክራሲያዊት አገር” እና “በማንነቱ ኮርቶ ከሌላው ጋር በእኩልነት ለሚኖር ሕዝብ” ከሆነ፣ ሁላችንም በእኩልነት ደረጃ ቁጭ ብለን ከመወያየት ሌላ አማራጭ የለንምና በጥብቅ አስቡበት፡፡ አገር ማለት ግዑዙ አፈር ሳይሆን በላዩ ላይ የሚኖሩ ሕዝቦች ማለት ስለሆነ፣ ለኢትዮጵያ ሕዝቦች አንድነት ሳይሆን ለኢትዮጵያ የግዛት አንድነት እታገላለሁ ማለቱን ትተን የሕዝባችንን ጥቅም እናስቀድም! እናት ኢትዮጵያም አፍ ቢኖራትና ብትናገር ኖሮ፣ ሁሉንም ልጆቿን እኩል እንደምትወደንና ተቻችለን እንድንኖር በአንክሮ ትመክረን ነበር እንጂ አንዳችንን ከሌላው ለይቼ እወደዋለሁ የሚል ቃል አይወጣትም ነበር፡፡ ስለዚህ በትናንቱ መንጋጋ የዛሬውን ቋንጣ ማኘክ ትተን፣ የየግላችንን አስተሳሰቦች እያስተናገድን ግን ደግሞ በጋራ ሆነን ሕዝባችንን ዛሬ ካለበት የድህነት መቀመቅ አውጥተን ሰላም በሠፈነበት አገር ውስጥ ቢያንስ ቢያንስ በቀን አንድ ጊዜ ጠግቦ ሊበላ የሚችልበትን አገር ለመፍጠር እንድንችል መትጋት የቅንጦት ሳይሆን የዜግነት ግዴታችን መሆኑን ማወቅ ዋነኛው የቤት ሥራችን መሆን አለበት ባይ ነኝ፡፡ ይህንን የቤት ሥራችን በትክክል ከሠራን ፈጣሪም ተባብሮን ባገራችን ሰላምን ያሰፍናል ባይ ነኝ፡፡ በቸር ይግጠመን፡፡
*****
Geneva, 10 January, 2020