ኦፌኮ በምስራቅ ሀረርጌ አያሌ ሺዎች በተገኙበት የምርጫ ቅስቀሳ አደረገ። ኦነግ በሚሌኒየም አዳራሽ ደጋፊዎቹ ጋር ጉባዔ አካሄደ። ኢዜማ በአዲስ አበባ በተለያዩ ወረዳዎች ቅስቀሳውን ቀጠለ። ልደቱ አያሌው ለኢዜማ እውቅና እንዳይሰጠው ምርጫ ቦርድን ጠየቀ። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በደቡብ አፍሪካ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር በስታዲየም ተወያዩ። እስክንድር ነጋ በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል የጠራው የፓርቲ መስራች ጉባዔ ተከለከለ። ሆቴሉ ተደራቢ የሙዚቃ ዝግጅት በመኖሩ ለሌላ ቀን አስተላልፉት አልኩ እንጂ አልከለከልኩም ሲል አስታወቀ። እስክንድር ”ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ” የተሰኘ ፓርቲ መመስረቱን ከተከለከለው አዳራሽ ውጭ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ይፋ አደረገ። ወለጋን ከኦነግ ሸኔ ርዝራዥ የማጽዳቱ ዘመቻ ተጠናክሮ በመካሄድ ላይ ነው። የደምቢዶሎው የተማሪዎች እገታ ላይ የመንግስት መግለጫ በማስረጃ የተደገፈ ባለመሆኑ ቅሬታን ፈጠረ። ሌላም …ሌላም።
ኦፌኮ በአንድ እግሩ ምርጫ ላይ ቆሟል። በሌላኛው እግሩ ደግሞ ከአንድነት መንግስት ውጪ የአብይ ብልጽግና ብቻውን መንግስት የማይሆንበትን የትኛውንም እንቅስቃሴ በማድረጉ ላይ በእጅ አዙር እየሄደበት ነው። ኦነግን የተጣመረበትና የኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ ባለቤትን ወደ ፓርቲው ያስገባበት ምክንያት ምርጫን ብቻ ታሳቢ በማድረግ ነው የሚለው ግርድፍ ድምዳሜ ስህተት ነው። ምርጫ ከመካሄዱ በፊት የአንድነት መንግስት ጥያቄ ጤናማ አይደለም። ካላሸነፍን አልያም የአንድነት መንግስት ካልተቋቋመ ሀገሪቱን በቀውስ ሲጥ እናደርጋታለን የሚል መልዕክትም ያዘለ ይመስላል። ለዚህም ፓርቲውን የተቀላቀለው የኦኤም ኤን ባለቤት ”election has consequences” ብሎ ቀድሞ ነግሮናል። ዶ/ር አብይና ፓርቲያቸውን ጥምብ እርኩሳቸውን እያወጣ በገለጸበት በቅርብ ጊዜው ቃለመጠይቅም ለአቅመ መንግስት የሚያበቃ ወንበር ካነሳቸው እንኳን ከህወሀት ጋርም ቢሆን ተጣምሮ ቤተመንግስት ለመግባት እቅድ እንዳለው አስታውቋል። ህወሀትን መጣመር ኢትዮጵያ ላይ መዓት ከማምጣት ያለፈ ትርጉም የለውም። ፕ/ር ህዝቄልን ከጀርባው ያነገበው የኦፌኮና የኦነግ ጥምር ጉዞ በምርጫ ለማሸነፍና ካልተሳካም ለመጪው ምርጫ ለመዘጋጀት ነው ብሎ የሚጃጃል ያለ አይመስለኝም። ምርጫን ማሸነፍ አልያም ሞት ብሎ ከተነሳው ጥምረት የሚጠበቀው ምን ሊሆን እንደሚችል የኢትዮጵያን ፖለቲካ በቅርበት ለሚከታተልና የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶችን አካሄድ ለሚመረምር ተመልካች በቀላሉ የሚረዳው ነገር ነው።
ኦፌኮ ምስራቅ ሀረርጌን በደጋፊዎቹ ሲያጥለቀልቅ ኦነግ ደግሞ ደጋፊዎቹን በአውቶቢስ ጭኖ ከተለያዩ የኦሮሚያ ክልል አከባቢዎች አዲስ አበባ በማስገባት በሚሌኒየም አዳራሽ ጉባዔውን አካሂዷል። ኦነግ በአዲስ አበባ ጉባዔ የመጥራት መብት እንዳለው እሙን ነው። አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያዊ መዲና እስከሆነች ድረስ። ሆኖም ወለጋን በእጅ አዙር እያመሱ አዲስ አበባ ላይ ለምርጫ የሚሆን ግርግር መፍጠሩ ግምት ላይ ይጥላል። በመሰረቱ ”አዲስ አበባ የኦሮሞ ናት” የሚል የቁም ቅዥት ውስጥ የሚንሳፈፈው የኦሮሞ ኢሊቶች አደገኛ አካሄድ የገፋው እንጂ አዲስ አበባ ለኦነግ የምርጫ ቅስቀሳ ትክክለኛ ቦታ ሆና አይደለም። ኦነግ አሁን ካለው ቁመና አንጻር ከወለጋ ውጪ የመራጭ ውክልና የለውም። እንኳን አዲስ አበባ ቀርቶ ጂማ፡ አዳማ፡ ባሌና በበርካታ አከባቢዎችም የኦነግ ህዝባዊ መሰረት የላላና በሌሎች የኦሮሞ ድርጅቶች የበላይነት የተያዙ ናቸው። በቀላል ስሌት ካሰብነው ደግሞ ጥቂት በማይባሉ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች የኢትዮጵያ ብሄርተኝነትን የሚያቀነቅኑና በዜግነት ፖለቲካ ላይ የተመሰረቱ ሃይሎች ከኦነግ የበለጠ ተቀባይነት አላቸው። እናም የኦነግ የአዲስ አበባው የዛሬው ግርግር የምርጫ ቅስቀሳ አካል ከመሆኑ ይልቅ ”አዲስ አበባ ኬኛ” የሚለው ቅዠት ማሳያ መድረክ ነው ማለት ይቻላል።
ኢዜማ ድምጹን አጥፍቶ እየሰራ ይመስላል። ከሰሜን መቀሌ እስከደቡብ ሀዋሳ፡ በመሀል አዲስ አበባ እያደረገ ያለው ቅስቀሳ ከሌሎች ፓርቲዎች በተሻለ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ የሚያመላክት ነው። ከእነጉድፎቹም ቢሆን ኢዜማ ሀሳብ ላይ ያተኮረ፡ ከዘርና ጎሳዊ አመለካከት የራቀ ፖለቲካዊ ፉክክርን የመረጠ ለመሆኑ በየከተሞቹ ከሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች መረዳት ይቻላል። ለእኔ የዜግነት ፖለቲካን የሚያራምድ የትኛውም የፖለቲካ ድርጅት ምርጫዬ ነው። ኢትዮጵያን በጎሳ ከረጢት ውስጥ አስገብቶ ዲሞክራሲንና ፍትህን አመጣለሁ የሚል የፖለቲካ ሃይል ቀድሞውኑ ባይፈጠር እመርጣለሁ። ከተፈጠረም እንዳይሳካለት ምኞቴ ነው። ለኢዜማም ሆነ በኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ላይ ለተቋቋሙ ቡድኖች ያለኝ አወንታዊ አመለካከት ከዚህ መርህ ብቻ የመነጨ ነው። እነልደቱና ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት የመሰረቱት ”አብሮነት” ከመጠላለፍ ወጥተው፡ ቀውስ ከማራገብ አጀንዳ ርቀው፡ ባነሷቸው ኢትዮጵያን የማዳን አቋሞች ላይ ትኩረት በመስጠት ቢሰሩ እኔን መሰል ደጋፊ ማግኘታቸው አይቀርም። ኢዜማ ፍቃድ አይሰጠው የሚለው የልደቱ አዲሱ ነጠላ ዜማ ባለቀ ሰዓት መለቀቁ አብሮነታቸው የፖለቲካ ስልጣን ለመያዝ ያለመ ሳይሆን ባይሳካም እንኳን ሌላውን ጠልፎ ለመጣል በመሆኑ ለደጋፊዎቻቸው ቅስም የሚሰብርና ያልተጠና እርምጃ ነው።
የእስክንድር የዛሬው ውሎ በእጅጉን ስሜቴን ነክተውታል። የእስክንድር ዓላማ ምንም ይሁን ምን የተጠራው ስብሰባ መደናቀፍና መከልከል የለበትም። ኦነግ አዲስ አበባ ላይ አሸሼ ገዳሜ እያለ፡ እነኢዜማ ያለከልካይ እንዳሻቸው ቅስቀሳ እያደረጉባት ባለችው ከተማ እስክንድርና ደጋፊዎቹን መሰብሰቢያ ቦታ መከልከል በየትኛውም መለኪያ ተቀባይነት የለውም። ጉዳዩን በተመለከተ በግሌ ለማጣራት ሞክሬአለሁ። የአዲስ አበባ ፖሊስ ም/ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ ጋር ተደጋጋሚ ስልክ ደውዬ አልተሳካልኝም። አዲስ አበባ ከንቲባ ጽ/ቤት የፕሬስ ሴክሬተሪያቷን ግን በስልክ አዋርቼአታለሁ። የበላይ አካል ከልክሏል የሚባለው ትክክል አይደለም ብላኛለች። ምክንያቱን ራሱ ሆቴሉ መግለጫ ይሰጥበታል በማለት የስልክ ንግግራችን ተቋጭቷል። ኋላ ላይ የሆቴሉን መግለጫን ሰማሁት። ቀልድ ነው። እንዲህ ዓይነት ሰበብ ለፖለቲካችን አይመጥንም። ከዚህ ቀደም እስክንድር የጠራቸው መድረኮች የተከለከሉበት ምክንያትን በተመለከተ አንዳንድ ለአደባባይ መብቃት የማይችሉ ጉዳዮች ስላሉ እዚህ ላይ ማንሳት አያስፈልግም። የዛሬው ግን ፈጽሞ ተገቢ አይደለም። ለማርተኞችና ቀውስ ጠማቂ ዩቲዩበር ሚዲያዎች የወሬ ቀለብ ከማቀበል ያለፈ አንዳችም ጥቅም የለውም።
ማጠቃለያ
መጪውን ጊዜ በተመለከተ የእኔ አቋም ነው። የመጀመሪያው አቋም ምርጫው በዚህን ወቅት ባይካሄድ የሚል ነው። መንግስት ከቆረጠና ምርጫ ቦርድም ተዘጋጅቼለሁ ብሎ ከወሰነ ግን የሆነ ነገር መደረግ ያለበት ይመስለኛል። የዚህ ምርጫ ትልቁ ስኬት መሆን የሚገባው ሰላማዊ መሆኑ ብቻ ነው። የ2012 ምርጫ ሀሳቦች የሚፋጩበት፡ ስልጡን የሆነ የምርጫ ፉክክር የምናይበት አይደለም። ለዚያ የተዘጋጁ በጣት የሚቆጠሩ ፓርቲዎች ካልሆኑ በቀር አብዛኞቹ ጡንቻቸውን ተማምነው፡ ቀውስን ግብ አድርገው የሚንቀሳቀሱ ናቸው። አንዳቸውም የኢኮኖሚም ሆነ መሰል አማራጭ ሀሳቦች የላቸውም። ፕሮግራም እንኳን ቀርጸው የሚንቀሳቀሱ አይደሉም። አንድዬና ብቸኛ የምርጫ መቀስቀሺያ አጀንዳቸው ጥላቻ ነው። ግባቸው ወንበር አግኝተው ኢትዮጵያን በፈለጓት መልኩ ከእንደገና ጠፍጥፎ መስራት ካልሆነም መበታተን እንጂ ከዛ ያለፈ አጀንዳ የላቸውም። ኢትዮጵያ እነዚህ ሃይሎች የፖለቲካ ስልጣን ከያዙባት ብትንትኗ መውጣቱ የማይቀር ነው። ኦነግና ጥምረቱ ኦሮሚያ ክልል ላይ መንግስት ሆኖ፡ ህወሀት ትግራይን ይዞ፡ ሌሎች ጽንፈኛ ሃይሎችም እንደየድርሻቸው ወንበር አግኝተው የሚያጠናቅቁት ምርጫ ከሆነ በማግስቱ ኢትዮጵያ ስለምትባል ሀገር ማሰብ ቂልነት ነው። ይህ ምርጫ ኢትዮጵያ እንደሀገር ትቀጥል ወይስ የዩጎዝላቪያ ዓይነት ትንንሽ ሀገራት ወደምትሆንበት ምዕራፍ ጉዞ ትጀምር የሚል ምርጫዎች የቀረቡበት ምርጫ ነው።
የኢትዮጵያ ህዝብ ኢትዮጵያን የማዳን እድሉን በእጁ ይዟል። በዚህ ምርጫ በሚሰጠው ድምጽ የኢትዮጵያን ህልውና ያረጋግጣል። በግሌ ይህ ምርጫ ዲሞክራሲያዊ፡ ፍትሃዊ ምናምን የሚሉት መገልጫዎች የቅንጦት ይመስሉኛል። ብልጽግና ፓርቲ የ2012ቱን ምርጫ ሰላማዊ ብቻ እንዲሆን በማድረግ ለሚቀጥለው ለ2017 ኢትዮጵያን ማዘጋጀት ይኖርበታል። በግርግር ወንበር ይዘው ሀገሪቱን ወደትርምስ ለመክተት ቀን ከሌሊት የሚሰሩ ሃይሎች በሚርመሰመሱባት ኢትዮጵያ ስልጣን ላይ ያለው መንግስት ትልቅ ሃላፊነት አለበት። ጫጫታ ሊፈጠር ይችላል። ድምጻችን ተሰረቀ የሚል እስከ ቀውስ የዘለቀ ማዕበል ሊቀሰቅሱ እንደሚችሉ ይገመታል። ለእነዚህ ሃይሎች በምርጫ ስም ሀገሪቱን አሳልፎ ከመስጠት የበለጠ ቀውስ ግን ኢትዮጵያ ላይ እንደማይፈጠር መታወቅ አለበት።
እናም ብልጽግና ፓርቲ ይህን ምርጫ ሰላማዊ ሂደቱን ጠብቆ እንዲካሄድ በማድረግ በሚቀጥሉት አምስት አመታት ምርጫ ቦርድን ጨምሮ ሌሎች የዲሞክራሲና የፍትህ ተቋማትን ገለልተኛ ተቋማዊ አቅም ገንብተው ለዲሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ምርጫ እንዲዘጋጁ ቃል ገብቶ ሀገር የመምራት ሃላፊነቱን ሊቀጥል ይገባል። መጀመሪያ ኢትዮጵያ መቀጠል አለባት። ይህ ምርጫ ኢትዮጵያን አረጋግቶ የማስቀጠል ሃላፊነት ለብልጽግና ፓርቲ ከመስጠት ያለፈ ውጤት እንዲኖረው መደረግ የለበትም።
(በሀሳብ ለሚሟገት የውይይት መድረኩ ክፍት ነው። የስድብና የዘለፋ አቁማዳውን ሸክፎ ገጼ ላይ ለሚመጣ ግን ጆሮ ግንዱን ብዬ እስከማባረር የደረሰ በፌስቡክ የተሰጠኝ መብት እንዳለኝ ለማስታወስ ያህል ነው