አውራምባ ታይምስ (አዲስ አበባ) ላለፉት 20 ዓመታት መኖሪያውን በሰሜን አሜሪካ አድርጎ የቆየውና በተለያዩ የኮሜዲ ስራዎቹ የሚታወቀው ኮሜዲያን መስከረም በቀለ ከሁለት አስርት አመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አገሩ ሲገባ ከአዲስ አበባ ኤርፖርት ተይዞ መታሰሩ ተገለፀ።
ቤተሰቦቹን ለመጠየቅና ለአንድ ሳምንት ያህል በአገሩ ለማሳለፍ ከትናንት በስቲያ ከዋሽንግተን ዲሲ አዲስ አበባ የገባው ኮሜዲያን መስከረም ሐሙስ ዕለት ቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርስ በስፍራው የነበሩ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ኦፊሰሮች ለጥያቄ እንደሚፈለግ ከገለፁለት በኋላ ይዘውት መሄዳቸውን ቤተሰቦቹ ለዝግጅት ክፍላችን ገልፀዋል።
ኮሜዲያን መስከረም የአሜሪካ ዜግነት ያለው በመሆኑ በቁጥጥር ስር መዋሉ ከተሰማ በኋላ ቤተሰቦቹ አዲስ አበባ ለሚገኘው የአሜሪካን ኤምባሲ ሪፖርት እንዳቀረቡ ለማወቅ ተችሏል።
በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ አውራምባ ታይምስ ያነጋገራቸው የኢምባሲው ቃል አቀባይ ዳያን ብራንት ‹‹ኢምባሲው ስለጉዳዩ በቂ መረጃ አለው›› ካሉ በኋላ ‹‹ነገር ግን የአሜሪካ ዜጎችን በሚያካትት መሰል ጉዳይ ላይ ኢምባሲው አስተያየት አይሰጥም›› ብለዋል።
ጋዜጣችን ወደ ህትመት እስከገባችበት ትናንት ምሽት ድረስም ኮሚዲያኑ እንዳልተለቀቀ የደረሰን መረጃ ያሳያል። ስለ ጉዳዩ ዝርዝር መረጃ ለማግኘት የቦሌ ኤርፖርት የኢሚግሬሽን ቢሮ ኃላፊዎችን ለማግኘት ጥረት ብናደርግም ጉዳዩ
ይመለከታቸው የተባሉ ሃላፊ ሰብሰባ ላይ እንደሆኑ ስለተነገረን ምላሻቸውን ማካተት አልቻልንም።