February 18, 2016
12 mins read

ከአነጋገር ይፈረዳል ከአያያዝ ይቀደዳል – ጥላሁን ዛጋ

ጥላሁን ዛጋ /fikireyohanis@yahoo.com

የአደባባይ ሰው የሚባለው፣ በአንድም በሌላም መልኩ ራሱን ለማህበረሰብ እይታ ገሃድ ያወጣ አኗኗሩ፣ አዋዋሉና አነጋገሩ በማህበረሰቡ ዘንድ በአዎንታዊም ይሁን አሉታዊ መንገድ ተጽእኖ ሊፈጥር የሚችል ግለሰብ ማለት ነው። አንድን ሰው የተለያዩ ኩነቶች አደባባይ ያወጡታል፣ ከነዚህም ጥቂቶቹና ዋናዎቹ ሊባሉ የሚችሉት ኪነ ጥበብ፣ ፖለቲካና የቴክኖሎጂ ፈጠራ /ሌሎች ካሉ ጨምሩባቸው/ ናቸው። በነዚህና በመሳሰሉት ዘርፎች በማህበረሰቡ ዘንድ ውስንም ይሁን ጉልህ ድርሻ ያላቸው ሰዎች፣ እንዲህና እንዲያ ብለዋል እየተባለ ንግግራቸውና አባባላቸው ለሌሎች ማጣቀሻ እየሆነ ይቀርባል፤ ሌላው ቀርቶ የሚበሉትና የሚጠጡት እየተነገረ፣ እነሱን መከተል ልማድ ነው።

አንድ ወቅት ግሩም ኤርሚያስ የተባለ አርቲስት “በጭስ ተደብቄ“ የሚለውን ወጥ ሲኒማ በዋና ገጸ ባህሪ ለመስራት የሄደበት መንገድ ለብዙዎች መነጋገሪያ መሆኑ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። አርቲስቱ የአደንዛዥ እጽ ሱሰኛ የሆነውን ገጸ ባህሪ ለመጫወት እጹን ከሚወስዱ ሰዎች ጋር ብዙ ጊዜ እንዳሳለፈና እጹንም እንደሞካከረ ሲነገር፣ አድናቂዎቹን እዚህና እዚያ ከፍሎ ለወራት ሲያነታርክ እንደነበር አስታውሳለሁ።

ይህ አደንዛዥ እጽ አሁን አሁን በተለይ በመዲናዋ አዲስ አበባ እንደፋሽን ከተያዙ ጎጂና አውዳሚ ልምዶች እንደአንዱ ሆኖ በሱሱ ተጀንጅነው በየመንገዱ የምናያቸው በርካታ ወጣቶች ቢኖሩም እንደዚያን ሰሞን መነጋገሪያ የሆነበትን ጊዜ ግን አላስታውስም። የሆነ ሆኖ አርቲስቱ እንዲህ አደረገ የተባለው ዜና ግን ባደባባይ ብዙዎችን አነታርኳል፣ ምክንያቱም በኪነ ጥበቡ ዘርፍ የራሱ የሆኑ አድናቂና ተከታዮችን በማፍራት ራሱን ለአደባባይ በማብቃቱ ነው።

የዛሬ ስንት ዓመት ግድም እንደሆነ አላስታውስም፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በዋልታ ኢንፎርሜሽን ስቱዲዮ Exclusive ቀርቦ ስለቤተሰብ ህይወቱ ተጠይቆ የሰጠውን መልስ እዚህ ላይ ማምጣቴ የላይኛውን ሃሳብ ያበረታዋል፣ ከጋዜጠኛው ጋር ሌሎች ብዙ ነገሮችን አንስተው ከጣሉ በኋላ ሃዘን፣ ሰርግና የመሳሰሉት ማህበራዊ መስተጋብሮቹን በተመለከተ ሲጠየቅ እምብዛም እንደሆነና፣ እንዲህ ያሉት መስተጋብሮች በጥቂት በተለይም በቅርብ ጓደኞችና ቤተሰቦች ብቻ የተወሰነ እንደሆነ ተናግሮ፣ በነዚህ አካባቢዎች ላይ በሚነሱ ጨዋታዎችና ወጎች እንደልብ እንደማያወጋና “ቀልድ እንኳ ቢያምረኝ . . . አምሮኝ ይቀራል እንጂ . . . መቀለድ አልችልም“ ምክንያቱም እንዲህና እንዲያ ብሎአል እየተባለ በህዝቡ ላይ የሚፈጥረው ተጽእኖ ቀላል አይሆንም፣ አንዳንዴም ልቅሶ ቤት ያወራከው እንደድርጅት አቋም ተደርጎ ሲወራ ዞሮ ይደርስሃል፣ ብሎ ሲናገር ሰምቻለሁ።

አንድ ሌላ ምሳሌ ልጨምርና በቀጥታ ወደዛሬው የጽሁፌ ዓላማ ላምራ . . . ወቅቱ እኤአ በ1950ዎቹ ነበር፣ ከሮዛሪዮ አርጀንቲና ተነስቶ ወደሰሜናዊ ላቲን አሜሪካ ሃገራት በማቅናት በቺሊ፣ ቦሊቪያ፣ ጓቲማላና ኩባ ህዝቦች ላይ የካፒታሊስቱ በዝባዦች የሚሰሩትን ኢኮኖሚያዊ ሸፍጥ የታዘበው፣ ጀብደኛው አብዮተኛ ኤርኔስቶ ቼ ጉቬራ . . . ከወጣበት ሳይመለስ ነበር ሜክሲኮ ድንበር ላይ ተሰባስበው፣ በካፒታሊስቶቹ ምእራባውያን የሚደገፈውንና ለብዝበዛቸው ህጋዊ ከለላ የሚሰጣቸውን የኩባ አምባገነናዊ አገዛዝ ፉልጌንቾ ባቲስታን ስርወ – አገዛዝ ለመገርሰስ በቁጥር 80 ከሚሆኑና በፊደል ካስትሮ ከሚመሩት የጉሬላ ተዋጊዎች ጋር የተቀላቀለው።

በጀብደኝነቱ፣ በአንባቢነቱ፣ በአብዮተኛነቱና በጸሃፊነቱ በብዙዎች ዘንድ ስሙ የናኘው ቼ . . . እሱ በሚመራቸው የጉሬላ ግንባሮች ላይ የሚፈጽማቸው ጀብዱዎችና ሌሎች ወጣ ያሉ ተግባራት፣ ካስገኙለት እውቅና አንጻር እሱን ለመምሰልና እንደሱ ለመሆን የሚጥሩ በርካታ ሰዎችን በየጎዳናው ላይ ማየት የተለመደ ሆኖ ነበር። የሱን ዓይነት ኮፍያ፣ እንደሱ ዓይነት ቄንጠኛ የሲጋራ አያያዝ፣ እንዲሁም እንደሱ ዓይነት አንባቢና ጸሃፊ ለመሆን የሚሞክሩ “የቼ ደቀመዛሙርት“ የሚባሉ ፋኖዎች ነበሩት።

ቼ ጉቬራ በተለይ ከባቲስታ ደህንነት ቢሮ በሚስጥር ለሚላኩ ሰላዮች አንዳች ርህራሄ ያልነበረው ፍጹም ጨካኝ እንደሆነ ይታወቃል፣ የቼ ደቀመዛሙርትም እንዲሁ ከመንፈስ አባታቸው ያዩትንና የሰሙትን ለመድገም ሲታትሩ ማየት የተለመደ ዓይነት /Fashion/ ነበር። እጅግ ብዙ ቁጥር ባላቸውና ከዋለበት ውለው ካደረበት አድረው የህይወቱን ልምድ ከቀሰሙት ደቀመዛሙርቱ ባሻገር ሌሎች በብዙ ሚሊዮን በሚቆጠሩ ወጣት ጀብደኞች ላይ ያሳደረው ተጽእኖ ቀላል አልነበረም፣ የቼ ቄንጠኛ የሲጋራ አያያዝ፣ የኮፍያ አደራረግና፣ ቄንጠኛ ሞሎቶቭ ኮክቴል ቦምብ አጣጣልን በወቅቱ የነበሩ ወጣቶች በየአካባቢው ሲለማመዱት ማየት የተለመደ ነገር ነበር።

እንግዲህ እሳቸው እንዳሉት ብለን ወደቀደመው ነገራችን ስንመለስ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት . . . አዎንታዊም ይሁን አሉታዊ ተጽእኖ ያላቸው በተለይም የአደባባይ ሰዎች ናቸው የሚባሉት ግለሰቦች ተግባራቸውና ንግግራቸው ማህበረሰቦች ላይ ተጽእኖ ማሳረፉ ሃቅ ነው፣ ልክ የዛሬ ሁለት ዓመት ግድም እንደተከሰተችው “የሜንጫ“ ታሪክ ማለት ነው።

አሁን አሁን የሃገሪቱ ስስ ብልት ሆኖ አስታምመው ካልያዙት እንደምርቅዝ ቁስል እዚም እዚያም በሚለበልበው የፖለቲካችን ዓውድ፣ ባልተገራ አንደበታችን የምንናገራቸው ቃላትና ዓረፍተ ነገሮች ሲውል ሲያድር ቆምንለት ለምንለው ስብስብ ብቻ ሳይሆን እኛንም /ተናጋሪዎቹን/ ጭምር ዋጋ እንዳያስከፍለን መጠንቀቅ ብልህነት ብቻም ሳይሆን ከሚመጣው አደጋ ማምለጫ መንገድም ጭምር ነው።

“አፍ ሲከፈት ጭንቅላት ይታያል“ እንዲሉ . . . ንግግራችን የእኛነታችን ነጸብራቅ፣ የአስተሳሰባችንም ውጤት ነው፣ በተለይም በፖለቲካው ንፍቅ ላይ ታች የምትሉ ወገኖች የአንደበቶቻችሁ ቃላቶች በአንድም በሌላ፣ በጥቂቱም ይሁን በብዙሃኑ ላይ አርፈው በበጎም ይሁን በክፉ ጫና መፍጠራቸው እሙን ነው፣ ስሜት ለመቀስቀስ ብለን በስሜት በምንናገራቸው ንግግሮች እንዳይፈረድብን፣ ከአያያዛችን ደካማነት የተነሳም እንዳይቀደድብን ጥንቃቄ ማድረጉ የነገ ሳይሆን የዛሬ ይልቁንም የአሁኗ ሰዓት ስራችን መሆን አለበት። እኔ ያለሁበት አካባቢ 100% እንደዚ ነው፣ እኔ ያለሁበት ደግሞ 80% እንደዚያ እያሉ፣ አጓጉል የሆኑና ምናልባትም ውለው አድረው ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጠንቅ የሚያመጡ እሰጥ-አገባዎች ሜዳ ላይ መገኘቱ፣ ምርኮውን ለገዢዎች ዳረጎት ከማቅረብ የዘለለ ፋይዳ የለውም።

ሰሞኑን እዚም እዚያም ተቃጠሉ የተባሉት አብያተ-እምነቶች ጉዳይ የሜንጫዋ ግብዝ ታሪክ ድግምት ላለመሆኑ አስረጂ የለንም፣ በተለይ ደግሞ ትናንትናና ከትናንት በስቲያ በአርሲና መሰል የኦሮሚያ አካባቢ የሆነው፣ አድጦንም ይሁን ሆን ብለን የተናገርነውን ውጤት እያየን እንደሆንስ ማን ያውቃል ? ? ? ፖለቲከኞች ነን ካልን፣ ይህንና ያኛውን ማህበረሰብ እንወክላለን ካልን፣ ጥቂትም ይሁን ብዙዎችን ወክለን ከፊት መስመር /ከፊት ለፊት/ ቆመናል ካልን፣ ለራሳችንም ይሁን ቆመንለታል ላልነው ማህበረሰብ ስንል ንግግራችን የታረመ፣ ተግባራችን ሃላፊነት ያለበት ሊሆን ይገባዋል፣ አልያ ግን “አንደበት እሳት ነው“ እንደተባለው፣ ወላፈኑ ለእኛም /ለተናጋሪዎቹ/ ለሌሎችም መትረፉ አይቀርም . . . “ከአነጋገር ይፈረዳል፣ ከአያያዝ ይቀደዳል“ . . . ነውና።

Go toTop