በልጅግ ዓሊ
[email protected]
ግንቦት ልደታ ሆላንድ
ሲሞላ ሲሞላ ጨዋታቸችን ሌላ፤
ሲጎድል ሲጎድል ሰው አንቀን ልንገድል።
የአማርኛ አባባል
እንደ መንደርደሪያ
ጀሚላ የትግራይ ልጅ የሆነች የኢሕአሠ(የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ሠራዊት) አባል ነበረች። በኢሕአፓ ታሪክ ውስጥ ከሚጠቀሱ ጀግና ሴቶች መካከል አንዷ ነች። የደርግን ፋሽሽታዊ መንግሥት በመቃወም በተደረገው ትግል ወቅት ወልቃይት ውስጥ ነበረች። በኢሕአፓ/ ኢሕአሠ በወቅቱ የነበረው ትግል ድርብ ነበር። ይኸውም ከፋሽሽታዊ መንግሥትና ከዘረኛና ከአገር ገንጣዮች ጋር ኢሕአሠ ትግል ላይ ነበር። በዚህ ወቅት ነበር ጀሚላ በወያኔዎች እጅ የወደቀችው። የትግራይ ልጅ በመሆኗ ቅጣቷ በወያኔ እጥፍ ድርብ ነበር። ግን የደረሰባት መከራ ከዓላማዋ ፈቀቅ አላደረጋትም። በቆራጥነት ዘረኝነትን እያወገዘች ወደ መገደያ ቦታ ትወስዳለች። እስከመጨረሻው በኢትዮጵያውነቷ እንደኮራች በጥይት ተደብድባ ትገድላለች። ዛሬ የጀሚላ ገዳዮች በሠሩት አሰቃቂ ግፍ ከሕሊናቸው ጋር ሲሟገቱ ጀሚላ በኢትዮጰያ ታሪክ ውስጥ በማይጠፋ ቀለም ተጽፋ አልፋለች። የጀሚላን የሕይወት ታሪክ የሚያውቁት ወደ ፊት በሰፊው እንደሚጽፉት አልጠራጠርም።
ተስፋዬ ደበሳይ የኢሕአፓ መሪና የትግራይ ሰው ነበር። ብዙዎቹ ጓዶቹ ይህንን ግለሰብ ያለውን ችሎታ ያደንቁታል። ተስፋዬ ደበሳይ አዲስ አበባ ውስጥ ከደርግ ጋር ሲፋለም ቆይቶ በመጨረሻም እጄን ለፋሽስቶች አልሰጥም ብሎ በኢትዮጵያውነቱ እንደኮራ ከፎቅ ዘሎ መስዋትነትን ከፍሏል። የእሱም ስም በማይጠፋ ቀለም በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ሰፍሯል። ስለ ተስፋዬም የሕይወት ታሪክ ወደፊት በሰፊው ይጻፋል የሚል እምነት አለኝ።
ገብረእግዚያብሔር ጋይም ወያኔ ያስጨነቀ የኢሕአፓ መሪ ነበር። ወያኔ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በኋላ በወያኔ ታጣቂዎች አዲስ አበባ ውስጥ ተገድሏል። ጋይም እስከለተ ሞቱ ድረስ ኢትዮጵያን ሳይከዳ፣ ዘረኝነትን እንዳወገዘ መስዋትነትን ከፍሏል።
ወያኔ አዲስ አበባን ተቆጣጠሮ በነበረበት ወቅትና የሽግግር መንግሥት ብሎ የዘር ፖለቲካውን ሲረጭ፣ ይህንንም ተቀብለው ብዙዎቹ ሲሮጡ እነ ገለብ ዳፍላ ፣ እነ አምባዬ ፣ እነ ጸጋዬ ደብተራው ሌሎችም ብዙዎች ከወያኔና ከሻብዕያ ጋር የመጨረሻውን ፍልሚያ ያደርጉ ነበር። ብዙዎችም መሰዋትነትን ከፍለዋል። ታሪክ ይህንንም መዝግቦ ይዞታል።
እነዚህ ዜጎቻችንንና ብዙ ሌሎችም የኢሕአፓ ታጋዮች እንደ አጼ ቴዎድሮስ፣ እንደ አጼ የሐንስ፣ ደማቸውን ለሃገራቸው አፍስሰዋል። እነዚህ ቆራጦች ለሃገራቸው ሲሞቱ እኛ የት ነበርን? ኢትዮጵያውነትን ከፍ አድርገን ከላይ እንደጠቀስኳቸው ታግለናል ወይስ ከዘረኞች ጎን ቆመን ገድለናል? ዛሬስ ለሠራነው ስህተት ተጸጽተናል ወይስ አሁንም ሃገራችንን እያደማን ነው? አዎ የነ ጀሚላ ፣ የነተስፋዬ ገዳዮች አሁንም እንደፎከሩ ነው። አዎ ዛሬም የታሪክ ድልድይ እንሰራለን በሚሉ ደላላ አሳታሚዎች የእነዚህ ነፍስ ገዳዮች መጽሐፍ እያተሙ ታሪክን ሲያዛቡ እያየን ነው። ለመሆኑ በዚያ የትግል ወቅት የት ነበርን ? ለሠራነው ብቻ ሳይሆን መሥራት ስንችል ላልሰራነውም መጠየቅ ይኖርብናል። ከሕሊና ወቀሳ ነጻ እንድንሆን ከተፈለገ።
ብአዴን ማነው ? ከገብረመድህን አርአያ
ብአዴን ማን ነው? በሚል የጻፉትን ተመልክቼ ምንም እንኳን የተስማማሁበት ነጥብቢኖረውም የማልስማማባቸውን ለመጻፍ ተገድጃለሁ። በመሠረቱ ይህንን ጽሁፍ እውነት አቶ ገብረ መድህን አርአያ ጻፉት ወይ በሚል ብዙዎችን ጥርጥር ውስጥ ከቶ ነበር። እውን እኚህ ብዙ የትግል ልምድ ያላቸው ግለሰብ፣ እኚህ ወያኔን አምርረው ያጋለጡ ግለሰብ፣ እኚህ ለብዙ ዓመታት ፖለቲካ ውስጥ የነበሩ ግለሰብ ይህንን ጽሁፍ ጻፉት ብሎ ለማመን ያዳግታል። ቢሆንም ጥርጣሬን ይዞ ከመቀመጥ ማጣራት ይሻላል በሚል ተሞክሮ ጸሐፊው እሳቸው መሆናቸውን ከራሳቸው ማረጋገጥ ተችሏል። በዚህም ምክንያት መላክ ያልነበረበት ይህ ደብዳቤ ታሪክን ማስተካከል አስፈላጊ በመሆኑ ግልጽ ተደርጎ ዘግይቶም ቢሆን ተልኳል።
ከጽሁፋቸው እጠቅሳለሁ፡-
“ይህግራአክራሪስታሊኒዝም በቀ. ኃ. ሥ. ዩኒቨርሲቲይማሩበነበሩየተሰባሰበቡድን፣የወቅቱአብዮተኞችተገቢውንመልክየያዘአደረጃጀትያልነበረው፣ አብዮተኛየሚልስምበማግኘታቸውብቻ “ዲሞክራሲያ” ተብሎየሚታወቀውንየኢህአፓልሳንበየሳምንቱበመበተንአሁን ኢትዮጵያየደረሰባትናእየደረሰባትያለውከባድችግርየከፈተውእነዋለልኝመኮንንእናየኢህአፓግብረአበሮቹየስታሊንደቀ መዛሙርትኢትዮጵያንአደጋወስጥጣሏት።”
ብአዴን ማነው – ገብረመድህም አርአያ ገጽ1
በጽሁፋቸው ላይ የኢትዮጵያ ችግሮች የተከፈቱት እነ ዋለልኝ በተደጋጋሚ በጻፉት ምክንያት ነው በማለት ሃገራችንን ለአደጋ ተጥላለች ብለው ወንጅለዋል። እነዚህ ችግሮች በ60ዎቹ ዓመታት ውስጥ በኢሕአፓ ወይም በተማሪዎች እንቅስቃሴ የተፈጠሩ ስለሆኑ ኢትዮጵያን አደጋ ውስጥ ጣሏት በማለት መደምደማቸው የሚገርም ሆኖ አግኝቸዋለሁ።
የፖለቲካ ሀ ሁ የሚያውቅ ሰው እንኳን ይህንን ያምናል ብዬ ለማማን ያዳግተኛል። ለመሆኑ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ባይኖር ይህ ተማሪዎች ያነሱት ችግር አይኖርም ማለታቸው ይሆን? ምንም እንኳን እሳቸው ተማሪዎቹ ካነሱት ጥያቄ ውስጥ ለጽሁፋቸው ያመቻል የሚሉትን ብቻ ቢወስዱም እኔ በበኩሌ ታሪክ በግማሽ አይጻፍምና ሌሎችንም ጥያቄዎች መግደፍ ጽሁፉን ሙሉ አያደርገውም የሚል እምነት አለኝ። መሬት ላራሹ ፣ ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት ፣ የብሔረሰቦች የመብት ጥያቄ ፣ የኤርትራን ጥያቄ ፣ የዴሞክራሲ ጥያቄ ፣ የድርጅት ጥያቄ . . . ወዘተ የተማሪዎች እንቅስቃሴ የፈጠረው ችግር ነው ለማለት መድፈር እንዴት ይቻላል?
የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ባይኖር ችግሮቹ አይኖሩም ብለን ካሰብን፣ ችግሮቹን የፈጠረው የተማሪዎች እንቅስቃሴ ነው ብለን ካመንን፣ ችግሩን የፈጠረው ዋለልኝ የጻፈው ጽሁፍ ነው ተብሎ ከተደመደመ፣ የዋለልኝ መገደል ችግሩን መፍትሔ ይሰጠው ነበር። ግን እንደዛ እንዳልሆነ ታሪካዊ ሃቅ ያስተምረናል። በሃገራችን የብሔረሰቦች የመብት ጥያቄ ነበር። መልስም ያስፈልገው ነበር። በዚያ ጊዜ የነበሩ ወጣቶች መፍትሔ የሚሉትን ጠቁመዋል። ችግሩ የተፈጠረው በሁለት ጽንፍ የሆነ አቋም ባላቸው ቡድኖች ምክንያት ነው። በአንድ በኩል በአንድነት ስም ጭፍጨፋ ባደረጉ ፋሽሽቶችና በሌላ በኩል ደግሞ በብሔር ጭቆና ስም የሃገሪቷን ጠላቶች መፈክር ባነገቡ ዘረኞች በተፈጠረው ትውልድ ጨራሽ ራዕይ የሌለው ትግል ነው።
ይህ የዋለልኝ ጉዳይ በብዙ ሰዎች በተለይ አርፍድው ለሕዝብ መብት መታገል በጀመሩ ምሁራን ሲነሳ ይደመጣል። ደካሞች መፍተሄን ከመፈለግ የመፍትሔ ሃሳብ የሰጡትን ሲወቅሱ እናያለን። ይህንን የሚያነሱት ደግሞ በእድሜ ከዋለልኝ የሚበልጡ መሆናቸው የሚገርም ነው። ለሃገሪቱ ችግር መፈትሄ ሳይሰጡ የራሳቸውን ኑሮ ሲያደላድሉ ኖረው አሁን በስተርጅና ለትችት መዘጋጀት ባይከለከልም እኔስ ለሃገሬ ምን ሠራሁ? ብሎ ራስን መጠየቅ ያስፈልጋል። ለሠራነው ብቻ ሳይሆን መሥራት ሲገባን ሣንሰራው ላለፍነውም ተጠያቂ የሚያደርገን ሕሊና ሊኖረን ይገባል።
ይህ የችግሩ መንስዬ ዛሬ በተለይ በደርግ በአንድነት ስም የተደረገው ጭፍን ጭፍጨፋ ምክንያት የኤርትራም ሆነ የወያኔን ዘረኛ ተገንጣይ ኃይሎች መጠናከርን ላለመግለጽ መጣርና ችግሩን መንሴውንም በተማሪዎች ንቅናቄ ላይ ማድረግ ቢያንስ ከትዝብት ይጥላል። ወያኔም ሆነ ሻዕብያ የተጠናከሩት ለችግሩ መፍትሔ መፈለግ ተትቶ በጭፍን ጭፍጨፋ ማመን በተጀመረበት ወቅት ነው። ራዕይ ያላቸው የሃገሪቱ ብሩህ ተስፋዎች እየተረሸኑ፣ ለአንድነት የቆሙት እን ጀሚላ ፣ እነ ተስፋዬ ደበሳይ . . . ወዘተ እየተገደሉ እነ መለስ ፣ እነ ስብአት . . . ወዘተ እንዲለመልሙ የተደረገውን ታሪክ ጽፎ ይዞታል። ይህንን ፋሽሽታዊ ተግባር ለመሸፋፈን ተራ ፕሮፖጋንዳ በመጠቀም ሰማዕታትን ለማዋረድ የሚደረገው ጥረት በአሁኑ ወቅት አነስተኛ አይደለም። ግን ታሪክ ደግሞ ሐቅን ይዞ ተቀምጧል። በምንም መለኪያ ጀሚላ ወይም ተስፋዬ ደበሳይ . . . በዘረኝነት አይታሙም። በምንም ታሪክ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ታሪክ (በኢሕአፓም ይሆኑ በመኢሶን ወይም በሌሎቹ ) በዘረኝነት አይታሙም። ከታሙም በአለም አቀፋዊነት እንጂ።
ጸሐፊው ለመጥቀስ ያልፈለጉት የኢትዮጵያ ተማሪዎች ትግል በሁሉም አካባቢ የቆሙ ግለሰቦችን ያቀፈ መሆኑን ነው። እነ ሐይሌ ፊዳ ፣ እነ ተስፋዬ ደበሳይ ወዘተ . . . ሌሎችም የኢትዮጵያ ተማሪዎች ትግል አባል ናቸው። ጸሐፊው የተማሪዎችን ትግል ከኢሕአፓ ጋር መያያዛቸው ግልጽ አይደለም። ሶሻሊዝም በኢሕአፓ ብቻ ሳይሆን በወቅቱ በብዙሃኑ ተቀባይነት ያገኘ እንደነበረ መካድ አይቻልም።
የብሔር ጥያቄን የፈጠረው ዋለልኝ አይደለም። ዋለልኝ ዛሬ ሊፈጠር የሚችለውን ወይም የተፈጠረውን ችግር ቀደም ብሎ በመገንዘቡ መፍትሔ ፍለጋ በመጣሩ ብቻ የችግሩ መንስዔ ዋለልኝ ወይም የተማሪዎች እንቅስቃሴ ነው ብሎ ማመን መፍትሔ ከመፈለግ ሊገድብ የሚችል አዘናጊ፣ ወይም አደገኛ አዝማሚያ ነው። ልምድ ካለው ፖለቲከኛም የማይጠበቅ ነው። አንባቢያን ይህ አሁን በወያኔ ሕዝብን ለመከፋፈል የተጠቀመበትን ሁኔታ ሕዝባዊ በሆነ መንገድ መፍትሔ ቢፈለግለት የስንት ንጽሁ ዜጎቻችን ሕይወት ይተርፍ እንደነበር መገመት ይቻላል። እንደ ወያኔ ዓይነት ጸረ ኢትዮጵያ ድርጅቶችም ዓላማቸው ግቡን ላይመታ ይችል ነበር።
አንድን ጥያቄ ወይም ችግር ራስ ተገንዝቦ መፍትሔ መፈለግ ብልህነት ነው ብዬ አምናለው። ለምሳሌ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ካነሳው ጥያቄና ዋነኛው የሆነው መሬት ላረሹ መፍትሔ ባያገኝ ኖሮ ዛሬ ወያኔም ሆነ የኢትዮጵያ ጠላቶች ይህንን ሁኔታ እንዴት ይጠቀሙበት ነበር? የወያኔ ፕሮፖጋንዳ ምን ይሆን ነበር ? አንባቢያን አንድ ጊዜ ይህንን እንዲያስቡት እጠይቃለሁ።
የመሬት ላራሹ ጥያቄ መፈታት ቢያነስ “አማራው ጭሰኛ አድርጎሃልና ጠላትህ ነው“ የሚለውን የወያኔን ፕሮፖጋንዳ አክስሞታል። በኢትዮጵያ ውስጥ ለተነሱት ጥያቄዎች መልስ ማግኘት ችግሮችን ይፈታል ብለን ካመንንና እውነትን ከተገነዘብን መፍትሔ የፈለጉትን ከማውገዝ እንቆጠባለን። ችግሩ አሁንም በአንድነት ስም ለጭፍጨፋ መዘጋጀቱ ላይ ነው። የነበሩትን ስህተቶችን አምኖ ለወደፊት ራዕይ ያለው መፍትሔ መፈለግ የግድ ይላል። በዘር ፖለቲካ ከተሸነሸነ አፓርታይድ ወጥተን ዴሞክራቲክ ወደ ሆነ ሥርዓት እንዴት እንመጣለን? የሚለው ጥያቄ ዛሬም ቢሆን ወቅታዊ ነው።
ዛሬ ብዙ መጽሐፍት በተጻፈበት ፣ ብዙ መረጃ ባለበት ሁኔታ ዋለልኝ የጻፈው እራፊ ወረቀት ሃገር አስገነጠለች ብሎ ማሰብ በታሪክ የተጻፉትን መረጃዎችን እንደ ሃሰት መቁጠርና ማጣጣል ነው ። ዛሬ የሃገራችን ሕዝብ ስለ ኤርትራ ፌደሬሽን መፍረስ እስከ ደርግ ጭፍጨፋ፣ ከሻብያ ጠላትነት እስከ ትላንትናው እና የዛሬው የሻዕቢያ ወዳጅነት ብዙ የተማርን ስለሆነ ፕሮፖጋንዳ ብቻ ታማኝነት አይኖረውም። ታሪክም ትክክል ባልሆነ ትንተና መጻፍ አስተማሪነት ሳይሆን የተሳሳተ ትንተና በወጣቱ ትውልድ ውስጥ መሰረጽ ይሆናል። አደገኛም ነው። ይህ በወያኔ አዲስ የታሪክ አጻጻፍ ላይ ያየነው ነው።
“ከላይየተጠቀሱትሁለትነጥቦችየኢህፓአመራርበዲሞክራሲያልሳኑደጋግሞበመዘርዘርጠባቦችናጸረኢትዮጵያአንድነትና ሉአላዊነትሃይሎችእንዲፈጠሩአደረገ። ጠባብናዘረኛውጸረ-ኢትዮጵያሉአላዊነት፣ጸረ-ሕዝብናአንድነትማገብት – ማህበርገስገስቲብሄረትግራይ – ተሓህትየዛሬው ህወሓትሊፈጠርቻለ።ይህየኢህአፓርእዮተዓለምናአቋምኢትዮጵያናሕዝቧንለዛሬውክፉአደጋዳርጓትአልፏል።”
ብአዴን ማነው – ገብረመድህም አርአያ ገጽ1
“ኢሕአፓ የኤርትራን ቅኝ ግዛትነት በማመኑና ኢትዮጵያ የብሔረሰቦች እስር ቤት ነች በማለቱ ጸረ አንድነት ኃይሎች ተፈጠሩ“ የሚለውን አገላለጽዎን ለማመን አዳግቶኛል። በአለም አቀፋዊነት የሚምነው፣ በእርስዎ አገላለጽ “የእስታሊን ደቀ መዝሙር የሆነው ኢሕአፓ“ ወያኔን ፈጠረ ማለት ትንሽ የሚያስቸግር ነው። ከላይ እንደ መንደርደሪም የጠቀስኳቸው ግለሰቦች ሃቁ ሌላ እንደሆነ ያስረዳሉ። ወያኔ በሚመለከት ደግሞ መሪዎቹ እርስዎም ደጋግመው በሌለቹ ጽሁፎቹ እንደገለፁት ገና ከመጀመሪው ጸረ ኢሕአፓ መሆናቸውን ስላመኑ አሁን መመለስ አያስፈልግም። ከትግራይ የኢሕአፓ ልጆች በሻቢያና በወያኔ እንደተባረሩ እርስዎም አልካዱትም።
ውድ አቶ ገብረመድህን ፡ –
ሻብዕያም ሆነ ወያኔ የተፈጠሩበትና ለሥልጣን የበቁበትን ምክንያት በትክክል መግለጽ ካልተቻለ እንዴትስ አድርገውን ነው መፍትሔ የምንፈልገው?
ጽሁፉ የእርስዎ ለመሆኑ ያጠራጠረበትም ዋንኛው ምክንያት በጽሁፎ የተቃረነ አመለካከትን ነው። አንድ ለእውነት የቀረበ ሌላ አንድ ደግሞ ለሃሰት የቀረበ አመለካከት በውስጡ ይገኝበታል። እውነቱ ከዚህ በፊት ከጻፏቸው ምስክርነት ጋር እንዳይጋጭ የሞከሩ ይመስላል።
“የኢህአፓአመራርበኢትዮጵያፈጥሮትያለፈውግዙፍስህተቶችበርካታስለሆኑከላይየጠቀስኩትመሰረታዊስህተትሆኖ በራሱምላይድክመቶቹለጥቃትሊዳርገውቻለ።በወቅቱየተሰባሰቡትአመራርስለኢትዮጵያሁኔታበቅጡያልተገነዙቡጭፍን በሆነአመለካከት በማርክሲዝምሌሊኒኒዝምአብዮተኝነትደንዝዘውመጥፎውንእናደጉንማየትየተሳናቸውነበሩ።”
ብአዴን ማነው – ገብረመድህም አርአያ ገጽ1
“ኢህአፓጠንካራጎኖችምየነበሩትመሆኑየሚዘነጋአይደለም።ዘውዳዊውስርዓትተንኮታኩቶእንዲወድቅማድረጉናመሬት ላራሹየመጀመሪያመፈክሩተግባራዊመሆኑናሌሎችምአሉት።”
ብአዴን ማነው – ገብረመድህም አርአያ ገጽ4
እነዚህን ሁለቱን ጽሁፎቾን ለማጣጣም ብዙ ጥሬ ነበር። ግን አልተቻለኝም። “ከደነዘዘ ጭንቅላት፣ስለኢትዮጵያሁኔታበቅጡካልተገነዘበ ጭንቅላት ፣ ጭፍን ከሆነ አመለካከት” የወጣው መሬት ላራሹ የሚለው ጥያቄ የሃገሪቷን ከፍተኛ ችግር እንደፈታ እንዴት መገመት ያዳግታል? ኢሕአፓ እንደ ድርጅት፣ በተለይ ብዙሃኑ አባላት ከነበራቸው ንጹህ የሃገር ፍቅር አንጻር፣ ከነበረው አለም አቀፍ ሁኔታ ጋር ስንመለከተው በአንድ መስመር “የደነዘዙ” በሚል መተንተኑ የሚቻል አይሆንም። አዎ ተስፋዬ ደበሳይ ዘረኝነትን እንቢ ብሎ በኢሕአፓ ስም ሞትን ተቀብሏል . . . ጋይም ገብረእግዚብሔር ፣ ብርሃኒ እጅጉ ፣ ቢንያም አዳነ ወዘተ . . . ሞትን ለሕዝብ ተቀብለዋል። የደነዘዘ ጭንቅላት ብሎ ሁሉንም በአንድነት መፈረጅ ይቻል ይሆን ? እንግዲህ ያልደነዘዘው ማን ይሆን ? ጽሁፉ ጅምላ ወቃሽ ይቅርታ ሊጠየቅበት የሚገባ ሃላፊነት የጎደለው አባባል ነው።
የኢሕአፓ አመራር ስህተት አልሰራም ብዬ መጻፍ አልፈልግም። ግን ኢሕአፓ አንድ ትልቅ ድርጅት ነበር። በውስጡ ብዙ ዓይነት አባሎችንንም አመራሮችንም ይዟል። ለሃገራቸው ራሳቸው ከስዉ ለጠላት እጃቸውን እስከሰጡ፣ ለሕዝብ ጥቅም ቆመው በወጣትነታቸው ከተቀጩ ለግል ጥቅም ደፋ ቀና እስከሚሉ ድረስ ነበሩበት። ድርጅት ነውና አሁንም ይሁን ወደ ፊትም በኢሕአፓም ውስጥ ሆነ በሌሎች ድርጅቶች ውስጥ እንደዚህ አይነት አጋጣሚዎች ይኖራሉ። በከድርጅት ወጥቶም ወደ ሌላ ድርጅት መግባት ትልቅ ቁም ነገር አይደለም። ግለሰቦች ያደርጉታል። ኢሕአፓም ሆነ የተማሪዎች ትግል ለነበሩት ጥያቄዎች መልስ በመፈለጋቸው ወያኔን እና ፀረ አንድነት ኃይሎችን ኢሕአፓ መሠረተ ለማለት መሞከር ግዙፉን ሐቅ እንደ መካድ ነው።
ግን ደግሞ የኢሕአፓን ታሪክ በየወቅቱ የወሰዳቸውን አቋሞች በመሸፈን፣ በደርግና በጠባቦች የደረሰበተን ጭፍጨፋ እንደዘነጉ በማለፍ፣ የአባላትን ቆራጥነትነና ዲሲፕሊንን በማጣጣል፣ ለራስ ትንታኔና ለወቅታዊ የፖለቲካ ድጋፍ ተብሎ ጀግኖችን፣ ለሃገራቸውን የሞቱትን ማጣጣል ተተኪው ትውልድ ትምህርት እንዳያገኝ መጣር እንዳይሆን መጠንቀቅ ይኖርብናል። ጀግናን ሲያደንቁ ብቻ ነው ጀግና የሚፈጠረው።
በተለይ ኢሕአሠን በሚመለከት የጻፉትን ለእርስዎም መልስ መስጠት የሚችሉ ብዙ የዛን ጊዜ መሪዎች የነበሩ አሁንም በሕይወት አሉ። ዝምታቸውን ሰብረው እውነቱን በማስረዳት ትምህርት ለሚቀጥለው ትውልድ መስጠት ይኖርባቸዋል። ኢሕአሠ ለምን ፈረሰ? የሚለው ጥያቄ ዛሬም መልስ ይሻል። በአቶ ገብረ መድህን ስለ ኢሕአሠ የተነሳው ጥያቄ መልስን ይሻል። ዝምታ መስማማት እንዳይሆን እውነቱና ሐሰቱ በግልጽ ለሕዝብ መቅረብ አለበት። በዚሁ አጋጣሚ የኢሕአሠን መሪዎች እውነትና ውሸቱን ግልጽ እንዲያደርጉልን እጠይቃለሁ።
በዚሁ አጋጣሚ የደርጅቱን የኢሕአፓን ታሪክ በተጠና ሁኔታ አለመጻፍ ለሚፈጠሩ የስም ማጥፋቶች ክፍተት መፍጠሩ ዛሬ የጎላ ሆኗል። እስከ ዛሬ ሕዝብን ሲጨፈጭፉ የነበሩ እንደ ፍቅረ ሥላሴ ዓይነት እንግዴ ልጆች ሳይቀሩ “እኛ ትክክል ነበርን“ ብለው ሲጽፉ ስለተጻፈ ብቻ ሐቅ ነው ብለው የሚቀበሉ ትንሽ አይደሉም። በአሁኑ ወቅት ያለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከ60% ከ40 ዓመት በታች ነው። ይህ ትውልድ ስለነበረው ሁኔታ አያውቅም። ይህንን ታውልድ ለማታለል ታሪክን መነገጃ ያደረጉ ሁሉ ውሸትን እየጻፉ እንዳይነግዱ መቃወምና እውነቱን ለማጋለጥ የሚደረገው ጥረት መቀጠል ይኖርበታል። በዚህ አጋጣሚ የወግደረስን ውሸት ያጋለጡት ሁሉ ሊመሰገኑ ይገባል።
አቶ ገብረመድህንም ሰፋ ባለ ትንታኔ የሕብረተሰቡን ችግር የፈጠረው ኢሕአፓ ነው የሚለው አዲስ ንድፈ ሃሳብ ሊያሰፉትና መረጃ ሊያቀርቡበት ይገባል። የመደብ ትግል ወይስ በብሔር ትግል ይቀድማል በሚል በወቅቱ የነበረውን ትግል ማስረዳት አስፈላጊ ነው። አለበለዚያ ግን ውሃ የማይቋጥር ትንተና ከተራ ፕረፖጋንዳ አያልፍም። አቶ ገብረመድህን ደግሞ በእነደዚህ ዓይነት ፕሮፖጋንዳ ውስጥ ይገባሉ የሚል እምነት የለኝም።
በመጨረሻም አንድ ሳላነሳው የማላልፈው ጉዳይ አለ። ለመሆኑ ስለ ብአዴን ሲጠቀስ ያሬድ ጥበቡ(ጌታቸው ጀቤሳ) ተረስቶ ነው የተተወው? መልስ ከአቶ ገብረ መድህን እጠብቃለሁ።
ስለ ሃገራችን የሚያስቡ በሰላም ይክረሙ !