አውሎግሶን አንድነት-Awulogson Andinet
ሚያዝያ 2/2017 ፣ አዲስ አበባ- ኢትዮጵያ
በእነ ዶ/ር ወንደሰን አሰፋ መዝገብ በሌሉበት ከተከሰሱት ውጭ በቃሊቲ እና በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የሚገኙ ተከሳሾች በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ቀርበዋል።
ሚያዚያ 2/2017 በነበረው ችሎት የተገኙት ተከሳሾች የዐቃቤ ሕግ ምስክሮችን ለመስማት ተዘጋጅተው ቢመጡም ዐቃቤ ሕግ ምስክሮችን ለማቅረብ አልቻለም።
ዐቃቤ ሕግ በድምሩ 96 ምስክሮች አሉኝ ያለ ቢሆንም እስካሁን 45 ምስክሮችን ብቻ ነው ያስመሰከረው ፤ ቀሪ 51 ምስክሮችን ገና አላስመከረም ።
ዐቃቤ ሕግ ሚያዝያ 2/2017 በነበረው ችሎት በቀጠሮው መሰረት ለማስመስከር ያልቻለው በአማራ ክልል ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት ምስክሮችን ወደ ኮምቦልቻ ለማንቀሳቀስ ባለመቻሉ መሆኑን ገልጧል።
ይሁን እንጅ ለዛሬ መድረስ ባይችሉም ነገ ሚያዝያ 3/2017 ለሚቀርቡ 7 ምስክሮች የአውሮፕላን ትኬት ተቆርጦላቸው ለመምጣት በዝግጅት ላይ ይገኛሉ ሲል ለፍርድ ቤቱ አሳውቋል።
ምስክሮቹ የሚደርሱት ሚያዚያ 3/2017 ከረፋዱ 4 ሰዓት ቀኋላ ነው ያለው ዐቃቤ ሕግ ከእኛ ጋር ለመነጋገር ጊዜ ስለሚያስፈልግ ለፊታችን ሰኞ ሚያዝያ 6/2017 እንዳቀርባቸው ይፈቀድልኝ ሲል ጠይቋል ።
ዐቃቤ ሕግን የተቃወሙ የተከሳሾች ጠበቆችም ከ52 ቀናት በላይ ተሰጥቶት ምስክሮችን አለማዘጋጀቱ ትጋት አለማሳየቱን ያመላከተ ነው ሲሉ ተቃውመዋል።
ከዚህም በላይ ፍርድ ቤቱ ተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ እንደሚሰጠው በመተማመን ነው ዐቃቤ ሕግ ሆነብሎ የፍትህ ሂደቱን እያዘገዬው ያለው በሚልም ተወቅሷል።
ስለዚህ ዐቃቤ ሕግ አላማው በእውነት ተከራክሮ እና ምስክሮችን በማስመስከር ለማስቀጣት ሳይሆን በተንዛዛ የፍትህ ሂደት እንድንታሰር ነው የፈለገው” በማለት ተከሳሾች የዘገዬ ያሉትን አካሄድ ተቃውመዋል።
“የዘገዬ ፍትህ እንዳልተሰጠ ይቆጠራል” እንደሚባለው በእለቱ ከፍትህ ሂደቱ ጋር በተያያዘ ቅሬታቸውን ካቀረቡት ተከሳሾች መካከልም እነ ዶ/ር ሲሳይ አውግቸው፣ አርቲስት ዮርዳኖስ አለሜ፣ መንበረ አለሙ እንዲሁም ጋዜጠኞቹ ዳዊት በጋሻው፣ ጎበዜ ሲሳይ እና ገነት አስማማው በተጨማሪም ጠበቃ እና የህግ ባለሙያው አለልኝ ምህረቱ ይገኙበታል።
በእለቱ ችሎት አጠቃላይ የፍትህ ሂደቱን በተመለከተ ተቃውሟቸውን ካሰሙ የሕሊና እና የፖለቲካ እስረኞች መካከል የጋዜጠኛ ገነት አስማማውን ፣ መንበር አለሙን እና አርቲስት ዮርዳኖስ አለሜን ቅሬታ እንደሚከተለው ለማቅረብ ተችሏል፦
- ጋዜጠኛ ገነት አስማማው ፦
“የአማራ የፖለቲካ እስረኞችን ለመዳኘት አቅምና ህሊና የላችሁም። ምክንያቱም ህሊና ያለው ዳኛ ይህንን የውሸት ክስ ለማየት አይመጣምና።” ስትል የዳኞችን አካሄድ ተቃውማለች።
ጋዜጠኛ ገነት ስትቀጥል “ዳኝነት መለኮታዊ እንጅ ሰዋዊ ብቻ አይደለም ፤ እናንተ እዚህ ወንበር ላይ ስትቀመጡ በሰዎች ህይወት ላይ ከእግዚአብሄር በታች ፍርድ እንድትሰጡ ነው ፤ ስለዚህ እኛ ከመብት አንጻር ለምንጠይቃቸው ጥያቄዎች ስለምን ይበሳጫሉ?” ስትል የመሀል ዳኛ ፈይሳ ቀዳዳን ጠይቃለች።
“ከዚህ በፊትም ረቡማ የሚባሉ ዳኛ አማራ ጠል መሆናቸውን ስለምናውቅና የሚወስኑት ውሳኔ ተገቢ ስላልሆነ ቅሬታ አቅርበን አስነስተናቸዋል ፤ እርሰዎንም ነገ ከዚህ ችሎት ልናስነሳዎት እንችላለን ፤ እናም ያንን ለመቀበል ዝግጁ መሆን ነው ያለብዎት እንጅ መበሳጨት አይገባምም።” ስትል ቁጣቸው የተቃርኖ መሆኑን ገልጻለች።
የሕሊና እስረኛዋ ገነት “በዚህ ችሎት ተመድባችህ የአማራ ተከሳሾችን ጉዳይ ስትይዙ በምን መስፈርት እንደሆነ እናውቃለን”
ማለቷ የግራ ዳኛ ጌትነት መዲናን በማስቆጣቱ ንግግርዋን እንዲቋረጥ አድርገዋል ፤ “እንዴት እንዲህ ትያለሽ? እንኳን እናንተ እኛም የት ችሎት እና በምን ጉዳይ እንደምንመደብ አናውቀውም” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።
በአጭሩ ጋዜጠኛ ገነት በእለቱ ከተናገረችው መካከል የሚከተለው ይገኝበታል ፦
እኛ የፖለቲካ እስረኞች ነን ፤ ፍትህ ተጓድሎብናል ፤ ከታሰርን ሁለት ዓመታችን ነው። ህሊና ያለው ዳኛ ስለሌለ እየቀለዳችሁብን ነው።
ጭራሽ እዚህ አትናገሩን ትላላችሁ እንዴ? ገና ምን አይታችሁ? ታግሰናችሁ እንጅ እናንተ እኮ ህሊና ያላችሁ ዳኞች አይደላችሁም ።
ሲጀመር የአማራ የፖለቲካ እስረኞችን ለመዳኘት አቅምና ህሊና የላችሁም። ምክንያቱም ህሊና ያለው ዳኛ ይህንን የውሸት ክስ ለማየት አይመጣምና።
እናም እዚህ የውሸት ችሎት ላይ ለመምጣት ህሊና ቢስ መሆን በቂ ነው።
- መንበረ አለሙ “ዐቃቤ ህግ ይሄን ቀልድ የሚቀለደው፣ ፍትህን እየቀበረ ያለው፣ ችሎቱን ጭምር እየመራ ያለው፣ በዳኞች ይሁንታ ነው፣ ስለሆነም ችሎቱ ዐቃቤ ህግን ሀይ ሊለው ይገባል”
መንበር አለሙ ሚያዚያ 2/2017 በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በነበረው ችሎት በፍትህ ሂደቱ ላይ ቅሬታቸውን ካቀረቡ የማንነት፣ የሕሊና እና የፖለቲካ እስረኞች መካከል አንዱ ሲሆን አጠር ያለ ንግግሩ በጽሁፍ ከዚህ እንደሚከተለው ቀርቧል፦
ያለ ፍትህ በአገዛዙ ከታገትን 2 ዓመት አልፎናል።
የተከሰስነው ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን በሀይል ለመናድ ተንቀሳቅሳችኋል ተብለን ነው።
በሚገርም ሁኔታ ግን የዜጎችን የተፋጠነ ፍትህ የማግኘት ህገ-መንግስታዊ መብት በግላጭ እየጣሰ ያለው የአገዛዙ ምልምል ካድሬ (ዐቃቤ ህግ) ያለ ከልከይ ፍትህን ነፍጎን ለ2 ዓመት አግቶን አልረካ ብሎ እየቀጠለ ነው።
የአገዛዙ ካድሬ ዐቃቤ ህጎች ምስክሮችን ማምጣት ያልቻልነው በሰላም መደፍረስና መንገድ ስለሚዘጋ ነው በሚል ይደሰኩራሉ።
ለመሆኑ አገዛዙ ሰሞኑን አማራ ክልል ከሁሉም አካባቢ የተውጣጡ የብልፅግና ታማኝ አባላት፣ ወጣትና ሴት ሊግ የድርጅት አባሎቹን በማደናገሪያ መሳሪያው የምክክር ኮሚሽን ባህርዳር እያወያየሁ ነው በማለት በአገዛዙ ልሳን በሚላቸው የቴሌቪዥን መስኮቶቹ ነግሮናል።
አረ ለመሆኑ አገዛዙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ታማኝ አባላቱን ለድንግርግር ኮሚሽን ወደ ባህር ዳር አጓጉዞ ሰብስቦ ማወያየት ከቻለ በኛ ላይ ይመሰክራሉ ብሎ ያሰለጠናቸውን ቀሪ 50 የከሚሴ ሸኔ አባላት ለምስክርነት ማቅረብ ለምን ተሳነው?
ዐቃቤ ህግ ይሄን ቀልድ የሚቀለደው፣ ፍትህን እየቀበረ ያለው፣ ችሎቱን ጭምር እየመራ ያለው፣ በዳኞች ይሁንታ ነው፣ ስለሆነም ችሎቱ ዐቃቤ ህግን ሀይ ሊለው ይገባል፤ ገለልተኛ ሁኖ ይዳኘን እሱ የማይሆን ከሆነ ግን
”ዳኛውም ….
መፋረጃው ገደል
ወይት ላይ ተሁኖ ይነገራል በደል”
የሚለውን የፋሲል ደመወዝ ዘፈን ጋብዘናችሁ ከነ አካቴው ፍርድ-ቤት የምንቀር መሆናችን ልንገልፅላችሁ እንገደዳለን!
- አርቲስት ዮርዳኖስ አለሜ ሚያዚያ 2/2017 በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በነበረው ችሎት “ሁሌም ከእውነት ጋር የምትጋጩት እስከመቼ ነው ? በቃን ከሀቅ ጎን እንቁም የምትሉትስ መቼ ነው?” በማለት ዳኞችን ጠይቋል።
“ዐቃቤ ሕጎች ባለፈው ስለ ምስክሮች ዝግጅት በዚህ ችሎት ስትናገሩ እኛ ሳንሆን ከጀርባችን ያለ ግዙፍ የመንግስት ሀይል ነው ምስክሮችን የሚያቀርብና የሚያዘጋጀው ብላችኋል” ሲል ቃላቸውን አስተውሷል።
“ይህ ቡድን እንደ እናንተ በችሎት ፊት አይቀርብም ፤ እናንተ ግን በቀረባችሁ ቁጥር ሁሌም ከእውነት ጋር የምትጋጩት እስከመቼ ነው ? በቃን ከሀቅ ጎን እንቁም የምትሉትስ መቼ ነው?” ሲልም ጠይቋል።
“ችሎቱ በእኔ ስም በተከፈተ መዝገብ ዐቃቤ ህግ በዓመቱ የመጣ የሲዲ ማስረጃ ስለተቀበለው አሁንም በዚህ መዝገብ በፈለገው ጊዜ ምስክር ማቅረብ እንደሚችል ስለተማመነ ነው 55 ቀን ተሰጥቶት ምስክር ያላቀረበው” በማለት ቅሬታውን አሰምቷል።
በተመሳሳይ ማስረሻ እንየው ሕክምና የማግኘት መብቱ መነፈጉን እና ቢሰጥ ተረፈ ደግሞ በማያውቀው ነገር በቂሊንጦ ማ/ቤት በተደጋጋሚ እየደረሰብኝ ነው ያለውን ድብደባ እና እንግልት በመግለጽ አሁንም ስጋት ስላለብኝ መፍትሄ ይሰጠኝ ሲል ጠይቋል።
ተገቢ የሆነ የህክምና አገልግሎት እያገኘሁ አይደለም ያለው ማስረሻ እንናንተ የምትሰጡት ትዕዛዝ በአግባቡ እየተፈፀመልኝ አይደለም ፤ ጉዳይ አስፈጻሚውም “በአንተ ጉዳይ ወደ ቢሮ ስሄድ ጥሩ ፊት እያሳዩኝ አይደለም” በማለት ነግሮኛል ሲልም አስተውሷል።
ጠበቃ እና የህግ ባለሙያ አለልኝ ምህረቱ በበኩሉ ፍ/ቤቱ ገለልተኛ እና ትክከለኛ ውሳኔ የሚሰጥ ቢሆን ኑሮ ዐቃቤ ሕግን ተጠያቂ ያደርግ ነበር ፤ ነገር ግን ጊዜው ደርሶ በእኛ ላይ የተፈፀመውን እስር እስክትቀምሱት ድረስ ግድ የለም በጀመራችሁት መንገድ ቀጥሉበት ስለማለቱ ተገልጦል።
በመጨረሻም ዐቃቤ ሕግ አሉኝ ያላቸውን ቀሪ ምስክሮች ከሚያዚያ 3 ጀምሮ እስከ ሚያዚያ 22/2017 የሚያሰማ መሆኑ ታውቋል።