August 30, 2024
48 mins read

ወቅታውያን ሁኔታወቻችን በፍልሰታ

ነሐሴ 16 ቀን 2016 ዓ/ም

ቀሲስ አስተርአየ nigatuasteraye@gmail.com

 

ፍልሰታ  ሐዋርያት የእመቤታችን አካል ፈልገው ያገኙበትን የጸሎት መልስ የምናስታውስባት ናት፡፡ ከፍልሰታ ጋራ ያሉን ትስስሮች  ብዙ ናቸው፡፡ በእምነት ከሚመስሉን አብያተ ክርስቲያናት ጋራ  ከተሳሰርንባቸው ቀኖናወች አንዷ ናት፡፡  አካላችንን ከተለመደው እንቅስቃሴያችን ገተን  ሕሊናችንን ሰብስበን በመንፈሳዊ ተመስጦ ትኩረት የተሳሰርንባቸውን ነገሮች ሁሉ የምንቃኝባት የተሰወረብንን ፈልገን ለማግኘት የምንቃትታባት የተለየች ትውፊታችን ናት፡፡ ፍልሰታ ለኛ ለኢትዮጵያውያን ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ከብዙ ቅርሶቻችን ጋራ ተያይዛ ለብዙ ነገሮቻችን መሰረት ሆናለች፡፡  ጤዛማዋ ፍልሰታ ኢትዮጵያ በዐለም ከምትታወቅባቸው ከብዙ ቅርሶቻችን አንዱ  ከሆነችው ከእንጀራ እናታችን ከጤዛማዋ ጤፍ ጋራም የምንገናኝበት ዐባይ ቅርሳችን ናት፡፡ ባአመታዊ ዑደቷ የዶክተር ዮናስ ብሩን ኑዛዜና የንስሐ ጥሪ የመሳሰሉትን ገጠመኞችን (ክስተቶች) እያዘለች ብቅ የምትል ከባንዲራችን ጎን የምትታይ አርማችን ናት፡፡ ከዚህ ቀጥየ ጤዛማዋ ፍልሰታ ከጤዛማዋ ጤፋችን ጋራ ያላትን ግንኙነት ለማሳየት  በውሱን አቅሜ ይህችን ጽሑፍ እጀምራለሁ፡፡

1ኛ፦ ክጤዛማዋ ጤፍ ጋራ የተሳሰረችው ጤዛማዋ ፍልሰታ

ከብሉዩ መምህሬ ከየኔታ ጥበቡ እንደተረዳሁት፡ የጤፍ መግለጫ በዘጸ 16፡14_15 ላይ “ርእዩ ደቂቀ እስራኤል ወተበሀሉ በበይናቲሆሙ ምንት ውእቱ ዝ እስመ ኢያእመሩ ወቤሎሙ ሙሴ ዝ ውእቱ መና ዘወሀበክሙ እግዚአብሔር ከመ ትብልዑ” ተብሎ ከተጻፈው ጋራ የተመሳሰለ ነው፡፡ ጤዛማዋ ጤፍ ከጤዛማዋ ፍልሰታ ጋራ የገናዘበች ናት፡፡ እስራኤል በበርሀ ሳሉ  በመካከላቸው ድንገት  በጤዛ የታጀበ መና ወርዶ ባዩ ጊዜ ይህ ነግር ምንድነው ተባብለው እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ፡፡ ሙሴ ትበሉት ዘንድ እግዚአብሔር የሰጣችሁ መና ነው አላቸው፡፡ ሰወች ስላላወቁት “ኧረ እንጃ” ተባባሉ፡፡ ሙሴ መና ነው ብሎ ተረጎመላቸው፡፡ መና ማለት “መኑ” ከምትለው መጠየቂያ ቃል ጋር የተወራረሰች ምንድነው ማለት ነው፡፡  ይህም ማለት በግእዙ  “መኑ ውእቱ ዝንቱ” ማለት እሱ ማነው (ምንድነው ) ማለት ነው፡፡ ተጠያቂወች መልሱን ስላላወቁት እንጃኧረ ብለው መለሱ፡፡ “እንጃእረ” የምትለው ቃል  አንድ ሰው ስለማያውቀው ስላንድ ነገር ተጠይቆ የሚመልሰው መልስ ነው፡፡ ይህም ማላት እንጃረ ወይም ኧረኔእንጃ ወይም ኧረ እኔ አላውቅም ማለት ነው፡፡

ጤፍ መሠረታዊ አመጣጧ የማይታወቅ ከጠፍ ቦታ ብቅላ የተገኘች ዘር ናት፡፡ ጤፍ ማለት  አመጣጡ ያልታወቀ ትርጉሙ የጠፋ ጠፍ ማለት ነው፡፡ ትርጉሙ ለጣፋበት ነገር መልሱ ኧረእንጃ  እንጃረ እንደሁነ ፡ ከጠፍ ቦታ በቅላ ከተገኘችው ከጤፍ  ዘር የሚሰራውን ምግብ እንጀራ የሚል ስያሜ ተሰጠው፡፡ ጤዛማዋ ፍልሰታ ለኛ ለኢትዮጵያውያን ኦርቶዶክሶች ከንጀራ እናታች ከጤፍ የተገናኘች ወቅታዊት ናት፡፡

በጤዛ ታጅቦ የወረደውን መና (ምንድነው)  ክርስቶስ “ሰው ከርሱ በልቶ እንዳይሞት አሁን ከሰማይ የወረደው መና እኔ ነኝ” (ዮሐ 6፡51) በማለት ወደ አዲስ ኪዳን በማሻገር ራሱን ተክቶበታል፡፡ በመናው ላይ “እሱ ምንድነው” በሚል ከርከር እንደተካሄደበት በክርስቶስ መናነት ላይም “ይህ ሰው ሥጋውን ልንበላ ይሰጠን ዘንድ እንዴት ይቻላል በመብባል እርስ በርሳቸው ተከራከሩበት” 6፡52፡፡   ክርስቶስም “ሰው ከርሱ በልቶ እንዳይሞት አሁን ከሰማይ የወረደው መና እኔ ነኝ” አላቸው፡፡ ቤተ እስራኤል ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ክርስቶስ የገለጸበትን የመናን ምሥጢር  እንደኛ ባይቀበሉትና ከኢትዮጵያ ምድር በአካል ቢጠፉም በፍልሰታዋ ጤዛ ተዘርታ ከምትበቅለው ከጤፍ እንጀራቸው በቀላሉ የሚላቀቁ  አይምውስለኝም፡፡   

እኛ ኦርቶዶክስ ኢትዮጵያውያን “ከሰማይ የወረደው መና እኔ ነኝ” ብሎ ራሱ ክርስቶስ በነገረን መሠረት መናን በቁርባኑ ተክተን አማናዊ ሥጋ መለኮት ብለን እንቆርባለን ፡፡ የእለት ምግባችችን እንጀራን ከተመገብን በኋልም   “ለዘአብልአን ዘንተ ሕብስተ” ስንል በጤዛማዋ ፍልሰታ ከምትዘራው ከጤፏ ጋራ ያለንን ታሪክ እናስታውሳለን፡፡     

ጤፍ ጤዛማዋ ፍልሰታን ተንተርሳ የምትበቅልባት ወቅት  ናት፡፡ በጤዛማዋ ፍልሰታ ካህናቱ በመቀድስ በዜማ፡ ህዝቡ በየመንደሩ ሆኖ በጤፏ ላይ የተመሰረተ እንጉርጉሮ ለአምላካቸው ያቀርባሉ፡፡  ጤዛ እያራገፉ መና እንደለቀሙ እስራኤላውያን፡ ኢትዮጵያውያት ቆንጃጅት (ደናግል) ጤዛ እያረገፉ በሚነቅሉት እንግጫ እንደ ንብ አበባ የሚቀስሙትን  የሶሪትና የአደይ አበባ ጎንጉነው በደረታቸው አጥልቀው “አሸንዳየ” እያሉ በብቸና አውራጃ በነማይ በሸበል በበረንታ ወረዳወች እስከ ዓባይ ድንበር እስከፊላው ድረስ በተዘረጉት ሰፋፊ ሜዳወች ላይ በሰማይ  እንደሚታዩ ከዋክብት ደምቀውና ፈንድቀው የሚታዩባት ወቅት ነበር፡፡ በነገራችን ላይ ዛሬ አሸንዳ የሚባለው ለምን ለትግራይ ቆነጃጅት ብቻ ሆኖ እንደሚቀርብና በጠቀስኳቸው ቦታዎች ለምን ሲደርግ እንደማይታይ ገርሞኝ ለመጻፍ በማሰብ ላይ ሳለሁ፡ የዶክተር ዮናስ ብሩ ኑዛዜና  የንስሀ ጥሪ ጽሑፍ በዘመኑ ያለነውን ካህናት ከሳሽና አጋላጭ ሆና ፍልሰታን ትንተራሳ ብቅ በማለቷ  ትኩረቴት ሳበችብኝ፡፡   

ዶክተር ዮናስ በኑዛዜና በንስሐ ጥሪያቸው ያቀረቡትንና ሕዝበ ክርስቲያኑ በያመቱ በፍልሰታዋ ወቅት የሚያቀርቡትን እንጉርጉሮ ለማስከተል ቀሳውስቱ በፍልሰታ ወቅት በቤተክርስቲያን ውስጥ ሆነው በዜማ የሚያሰሙትን ተመሳሳይ ስሜት ከዚህ በታች ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡ 

3ኛ፦ ከቀሳውስቱ በዜማ የሚሰማው ድምጽ በፍልሰታ

ቀሳውስቱ በፍልሰታ ወቅት በዜማ የሚያሰሙት ድምጽ አኀት አብያተ ክርስቲያናት በማይጋሩን ሰአታት በሚባለው ድርሰት የሚያቀርቡት ጸሎት ነው፡፡ በዜማ የሚደረሰው ጸሎት የጤፏን መዘራት  በጭቃ ውስጥ መውደቅ መቀበር መፍረስና እንደ ገና በቅላ መንሳቷን የሚያሳየው ነው፡፡ “አትብ ወእትነሣእ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ፡ ሰለስተ አስማተ ነሢእየ እትመረጎዝ እመኒ ወደቁ እትነሣእ ወእመኒ ሆርኩ ውስተ ጽልመት እግዚአብሔር ያበርህ ሊተ በግዚአብሔር ተወከልኩ”(ሰአታት)፡፡ የሚል ነው፡፡ ይህም ማለት፦ “በጨለማ ውስጥ ብገባም እግዚአብሔር ያበራልኛል፡፡ ብወድቅም በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ስላሴወችን ይዤ በመመርኮዝ እነሳለሁ” ይህ አባባል  የጤፏ ዘር ከቤት (ከጎተራዋ )ወጥታ ከተዘራችበት ጀምሮ እንደገና ራሷን ሆና እስክትነሳ ድረስ የምታልፍባቸው ተግዳሮቶች በሰው ልጅ ላይ የሚካሄዱትን የመከራ አይነቶች የሚያመለከቱ ናቸው፡፡ የዘመናችን ቀሳውስት ይህን ትውፊት በመከተል  ዛሬ በኢትዮጵያ ላይ በተለይም በኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ላይ በመካሄድ ላይ ያለውን መከራና ስቃይ በሰአታቱ እንጉርጉሮና ትካዜ ሲገልጹት ሰንብተዋል፡፡ በየመቃብርቤቶች በደጀ ሰላሞች ወይም በየምንደሮች ያሉ እናቶችና አዛውንቶች  በፍልሰታዋ እንጉርጉሯቸው ሲገልጹት የሰነበቱበትን የእንጉርጉሮ ግጥም ከዚህ በታች እንደሚቀጠለው ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡  

4ኛ፦ከምእመናን የሚሰማው የእንጉርጉሮ ድምጽ በፍልሰታ

“ከሁሉ ሁሉ ጤፍ ታንሳለች

ወድቃ በስብሳ ትነሳለች”

ያዳም ልጅ ሁሉ ሰነፈና

ወድቆ ቀረ አሉ በጎዳና፡፡

ያዳም ልጅ የሆንክ አትስነፍ

ሥራ እየሰራህ እለፍ” እያሉ ያንጎራጉራሉ፡፡

በሰው ልጅ የሚደርሰውን ተግዳሮቶች የሚገልጸውን ይህን ትካዜ በጤፏ ላይ መስርተው ያንጎራጎሩት የቀደሙ አባቶቻችንና እናቶቻችንን ስሜት በዚህ ዘምን ላይ ካለን አባቶችና አናቶች ስሜትና ስነልቡና ጋራ የሚያገናኝ ቀጣይ ቅርስ ነው፡፡ ይሁን እንጅ እንደቀደሙ ኢትዮጵያውያን ወላጆቻችን በግንዛቤ ካልተጠቀምንባት ጧት ከበረት ወጥተው፤ ማታ ወደ በረት ከሚመለሱ ከብቶች የተለየን አያደረገንም፡፡ በፍልሰታ ከተከሰቱት ብዙ ነገሮ አንዷ ከቀሳውስቱና ከምእመናኑ እንጉርጉሮ ጋራ የተያያዛቸው ከዚህ ቀጥየ የማቀርባት የዶክተር ዮናስ ብሩ ኑዛዜና  የንስሀ ጥሪ ናት፡፡

5ኛ፦ ዶክተር ዮናስ ብሩ ያሰሙት የኑዛዜና የንስሐ ጥሪ ድምጽ በፍልሰታ

የዘንድሮዋ ፍልሰታችን ብዙ አስከፊ ክስተቶችን ደራርባ ያዘለች ብትሆንም፦ “ብትክ ወምትር ኩሎ ማእሰረ ኃጣዊነ ለእመ አበስነ ለከ እግዚኦ በአእምሮ አው ዘእንበለ አእምሮ አው በጽልሑት አው በእከየ ልብ አው በገቢር ወበተናግሮ አው በናእሰ ልብ”(ሥ ቅ ቁጥ 58) ብሎ ራሱ ንስሀ ገብቶ ለንስሀ ህዝቡን የሚጠራ ካህን በጠፋበት በዘንድሮዋ ፍልሰታ ተደርበው ዶክተር ዮናስ ብሩ “The confession challenge starts with my own confession” እያሉ ብቅ አሉ፡፡ በዘንድሮዋ ፍልሰታ ላይ ተደራርበው ከተከሰቱት አዳዲስ ብዙ ክስተቶች፡ ተደርባ ብቅ ያለችው  የዶክተር ዮናስ ኑዛዜ ትኩረቴን የማረከችብኝ ከቀኖናችን ጋራ ተያይዛ ስላገኘኋት ነው፡፡

 በቀኖናችን መጽሐፍ ፍ አ 11 ክቁ 468_470 ላይ ተመዝግቦ የምናነበው ህልም ተርጓሚወች፤ ሀሰት ተራኪወች፤ መሠርያን ትንቢት ተናጋሪወች ፡ የሀሰት ኩርባብች ከታቢወች፡  ውሐ ረጭወች፡ እንደ ክረምት አሸን የፈሉትን የሚያወግዝ ነው፡፡ ቀኖናችን ከሚያወግዛቸው ክፉ ባህርያት ውስጥ ያስኳላው ተማሪ ዶክተር ዮናስ ብሩ ቢያንስ በትርጓሜ ፈጠራ (በተሳሳተ ትርክት ) በመሳተፍ አገራቸውን ጎድተዋታል፡፡ ኢትዮጵያ ከፍረሰችባቸው ክፉና አደገኞች አንዱና እጅግ የከፋው ትርጓሜ ፈጠራ ነው፡፡ ዶክተር ዮናስ በፈጸሙት ተጸጽተው “The Ethiopian poletical confession chalenge” የሚለውን ያቀረቡልን በፍልሰታዋ ወቅት August 19 2014 ነው፡፡  ባቀረቡልን ኑዛዜ ከዚህ ቀደም እንደ መልካም ምሳሌ ካቀሩቡት ሲኖዶስ በላይ እንደ ጠንካራ ካህን ሰንጥቀው የወጡ መሰለኝ፡፡ በዘንድሮዋ ፍልሰታ ተደርባ የተከሰተችውን የዶክተር ዮናስን የኑዛዜ ቃል የኔን የቄሱን ድካም አሳየችኝ፡፡ 

ዶክተር ዮናስ ብሩ ከዚህ ቀደም በቀኖናችን መለኪያ ለምሳሌነት ሊጠቀስ የማይገባውን ሲኖዶሱን በመልካም ምሳሌነት በመጥቀሳቸው ከቀኖናው ትውፊት ጋራ ስለታጋጨ  በተቃራኒ መንፈስ ልዩነቴን ለማሳየት ስማቸውን ጠቅሸ ነበር፡፡ በዚህ አመት ፍልሰታ ወቅት የተከሰቱትን ስዳስስ ዶክተር ዮናስ ብሩ ያቀረቡት የኑዛዜ ሐሳብ ከፊቴ ተደቀነች፡፡ ዶክተር ዮናስ “ወእመሰ ኮነ ዝንቱ ከመዝ ኢንፍቱ እንከ ከዊነ ሊቅ ለእመ ያመጽእ እኪተ ወሙስና” (ድርሳን ሰላሳ  ቁጥ 11) ያለውን ዮሐንስ አፈወርቅ የተናገረውን በተግባር ከተረጎሙት ሊቃውንት መካከል አንዱ ሆኑ፡፡  ይህም ማለት ባስኳላው ትምህርታችን ላይ ብቻ የተመሠረተው ሊቅነታችን ችግርና ጥፋት የሚያስከትል ከሆነ መለስ ብለን እንፈትሸው ብለው ብቅ ያሉ መሰሉኝና  ከመምህሮቼ እንዳንዱ ሆኑ፡፡ አደነኳቸው፡፡

ዶክተር ዮናስ ምንም እንኳ ትኩረታቸውን በ12ቱ አቻወቻቸው ቢያደርጉም “members of the silent majority are also challenged to the point because their silence in the face of their nation’s existenial crisis is complacency” የሚለው አባባላቸው፡ በፍልሰታዋ ወቅት ቀሳውስቱ በቤተ መቅደስ ሆነው  “በጨለማ ውስጥ ብገባም እግዚ ያበራልኛል፡፡ ብወድቅም በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ስላሴወችን ይዤ በመመርኮዝ ከወደቁበት እነሳለሁ” የሚሉትንና ህዝበ ክርስቲያንም  (ፋኖወች)

“ያዳም ልጅ የሆንክ አትስነፍ

ሥራ እየሰራህ እለፍ” እያሉ የሚያንጎራጉሩትን ጎትቶ አመጣብኝ፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡ ዶር ዮናስ “The goal is not to point fingers on others, but to confess our own sins in terms of causing or exacerbating the current crisis” ባሉት አባባላቸው በቅስናው ዙሪያ ያለነውን ሁላችንን ከተኛንበት የሚቀሰቅሰን መሰለኝ፡፡ በተልይም በዘመናችን ያሉት ፓትርያርክ የሲኖዶሱ ጸሀፊ የገዳሙ አበምኔት ከሀላፊነታቸው ርቀው እየተወቀሱና እየተከሰሱ ባሉብት ይህችን ጦማር ማቅረባቸው “ወለእመኒ ኖሙ ረሲ አክናፈ መላእክት ይክድኖሙ ክበደ ንዋም ኢያስጥሞሙ ዘውእቱ አምሳሊሃ ለሞት”(86) ማለትም፦ የሞት ትንሽ ወንድም የሆነው እንቅልፍ አሰጠሟቸው ድብን ብለው የተኙትን ጳጳሳት መላክ ልከህ ቀስቅሳቸው እያለ ድምጹን አስምቶ የጮኸውን ሊቁን ያዕቆብ ዘሥሩግኝ መሰሉኝ፡፡

ዶክተር ዮናስ ቀጥለው “I cannot deny my contribution to the creation of one of the worst and most dangerous psychopath to consolidate power” “For that I feel both regretful and accountable.” ብለው የተናገሩት “ኢትፍራህ ተጋንዮ በንተ ጽድቅከ ወኢትወስክ ኃጢአተ በዲበ ኃጢአትከ”(5፡5)፡፡ ብሎ ጠቢቡ ሲራክ ከተናገረው ጋራ ገጠመብኝ፡፡ ይህም ማለት ውደቀትህን ስህተትህን ለመናዘዝ አትፈር! ገበናህን ለመሸፈን የሚሟገትህን ህሊናህን አሸንፈህ ሰንጥቀህ የወጣህ ጀጋና ሁን”  የሚለውን “The confession challenge starts with my own confession” በማለት የገለጹት፡፡

ዶክተር ዮናስ ከነበሩበት ስህተት ራሳቸውን ብቻ በማውጣት ሳይወሰኑ ያጣጣሙትን ኑዛዜ “I then tap or challenge 12 intellectuals and activists to participate by sharing their onfession and tapping or challenging 12 others of their choice to do the same”   ብለው ለሚወዷቸው ወገኖቻቸው ጥሪውን ማቅረባቸው የበለጠ እንዳደንቃቸው አደረገኝ፡፡ ከራስ ወዳድነት የወጡና በውስጣቸው ያለውን ወንድማዊ ፍቅር  (ፍቅረቢጽ ) የበለጠ እንዳክብራቸው አድረጎኛል፡፡

ይልቁንም ራሳችን ንስሀ ስንገባ  “ዘትፌውስ ቁስለ ነፍስነ ወሥጋነ ወመንፈሰነ. . . . ወዓዲ ለትሕትና  ዚአየኒ አነ ገብርከ ኃጥእ ወአባሲ ፍትሐኒ”(ቅ ሐ ቁ 76) እያልን በህዝብ ፊት ቆመን በማነብነብ ላይ ያለነውን በዚህ ዘመን የምንገኘውን የኦርቶዶክስ ካህንት አጋለጡን፡፡ Thus, shall I stand before God and you my country women and men to confess, repent, redeem, and ask for forgiveness” በማለታቸው  ወገኖቻቸውን እምላካቸውን ይቅርታ እየጠየቁ ተጸጽተዋል ተናዘዋል አገራቸውን እንደገና ለመገንባት በህዝባቸው ፊት ቆመዋል፡፡ አቻወቻቸውም ከሳቸው ጋራ እንዲሰለፉ ጥሪ አቅርበውላቸዋል፡፡ እጅግ አስደናቂ ግሩምና ወሸው (ወይሰው! ) የሚያሰኝ ነው፡፡  

በዚህ ወቅት ዶክተር ዮናስ ለአስራሁለት አቻወቻቸው ያቀረቡላቸው የንስሀ ጥሪ ሁላችንንም ያካተተ እንደ ወቅታዊቷ ጤፍ መዘራታችንን መበተናችንን በኃጢአት መጨቅየታችንን መውደቃችንን መፍረሳችንን እያሳየ እንደገና መነሳትን ማንሰራራትን መገንባትን የሚያረጋግጥ ብሩህ ተስፋ የምታሳይ ናት፡፡ ሆኖም ዶክክተር ዮናስ የጠቆሙን  ተስፋው ወደ ኩነት ሊለወጥ የሚችለው ፤ ከጤፍ ጋራ የተያያዘውን ወንፈል የሚባለውን ትውፊት ፋኖ ሲጥቀም ብቻ ይመስለኛል፡፡

በበቀለው ጤፍ መካከል የበቀለውን አረም እንደ ሚመለከት ንቁ ጤፍ ዘሪ ገበሬ ዶክተር ዮናስ በጥቂቱም ቢሆን በፋኖ መካከል የሚያዳክም አረም ያዩ መስለውኛል፡፡ ከጤፍ ጋራ ተቀላቅሎና ተቆራኝቶ ለመለየት የሚያስቸግረው መጥፎ ትውፊት አረም ነው፡፡ ለጤፍ አምራቹ ገበሬ ትልቁ ተግዳሮትም ማረሙ ነው፡፡ እንደዚሁ ሁሉ በመውደቀና በመነሳት ላይ ላለው ፋኖም ትልቁ ተግዳሮት  መስሎና ተቀላቅሎ በመካከል የሚከሰተው ከቀድሞ ጀምሮ የነበረ መጥፎ ቅርስ አስመሳይ ባንዳ ነው፡፡ ወንፈል (ደቦ) በሚባለው ማህበራዊ ኃይል ኃይል ካልሆነ በቀር በጤፍ መካከል የሚበቅለውን አረም በጥቂት ሰወች ብቻ ማረም አይቻልም፡፡  እንደዚሁ ሁሉ ፋኖ በመካከሉ የሚከሰተውን አረም (ባንዳ) ማስወገድ የሚችለው ከቤተ ክህነት እነ መምህር ፈንታሁን ዋቄንና ዲያቆን ዮሴፍ ከተማን የመሳሰሉትን፡ ከአስኳላ ምሑራን እነ ዶክተር ዮናስ ብሩንና ለንስሀ የጠሯቸውን ልሂቃን አስተባብሮ ማሰልፈ ሲችል ብቻ ይመስለኛል፡፡

 ሕዝበ ክርስቲያኑ ከኛ ከመንፈሳውያን አባቶች ተጠምቶ ያላገኘውን የንስሐ ጥሪ ከዶክተር ዮናስ ስሰማ  “ከመ ማይ ቆሪር ለነፍስ ጽምዕት አዳም፡ ከማሁ ዜና ሠናይት እምድር ርኁቅ”(ተግ 1፡25) እንዳለው ከሩቅ የምትሰማ የዜና ብሥራት በጥም ለተቃጠለች ሰውነት እያበረደች የምታረካ ቀዝቃዛ ውሀ ናት” ብሎ ሰሎሞን የገለጻትን ጥም አርኪ ውሀ ያጠጡኝ መሰለኝ፡፡  ይህም ብቻ አይደለም “  . . . ትግሀታተ ከንቱ ኢይምጻኦሙ እንተ ይእቲ አማሳኒሃ ለንፍስ፡፡ ወለመኒ ኖሙ ረሲ አክናፈ መላእክት ይክድኖሙ ክበደ ንዋም ኢያስጥሞሙ ዘውእቱ አማሳሊሁ ለሞት . . . . 85_86” ብሎ ታላቁ የቤተ ክርስቲያናችን ሊቅ ያዕቆብ ዘሥሩግ የተናገረውን ለህዝበ ክርስቲያኑ የሚናገር ካህን መስለው ብቅ አሉ፡፡

ከውጭ በተረከቡት በድርጅታዊ ሐሳብ ኢትዮጵያን ሲያፈርሱ የነበሩ ያስኳላ ተማሪወች ከስህተታቸው መላቀቅ ተስኗቸው ጭንቅላታቸውን ካልቆለፉት በቀር ዶክተር ዮናስ ብሩ ባቀረቡት ኑዛዜ  የቀረባላቸውን የንስሀ ጥሪ እንዲቀበሉ በሕሊናቸው ላይ ትልቅ ተጽእኖ የሚፈጥርባቸው መሰለኝ፡፡ ዶክተር ዮናስ ብሩ የንስሀን ጥቅም በተረዱት መጠንና መንገድ በዘንድርዋ ፍልሰታ ያቀረቡት ኑዛዜ የንስሀ ጥሪ እኔንም ስለቀሰቀሰችኝ በኦርቶዶክሳዊት ቅስናየ በተረዳሁበትና ቀኖናው በሚመራኝ መንገድ ሐላፊነቴን ለመወጣት ተሰጥኦውን መልሻለሁ፡፡ ባለአገሮች አባቶቻችን ኢትዮጵያን የገነቡባቸውን እሴቶች ዶክተር ዮናስ በንስሀ ጥሪያቸው እንዲተባበሯቸው ጥሪ ላቀረቡላቸው ለአስኳላ ምሁራን ወንድሞቻቸን ከዚህ ቀጥየ ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡  

የባለአገሮች (ኋላ ቀሮች) የሀገር ግንባታ እሴቶች በፍልሰታዋ ቅኔያችን

የኛ የባለ አገሮች (ኋላቀሮች)ቅኔያችን ባለብዙ መንገዶች ነው፡፡ ከብዙወቹ መንገዶች ሰምና ወርቅ፡ ውስጠዘ ፤ ውስጠወይራ ጎዳና ሠረዝ የሚባሉትን ብቻ  እጠቃሳለሁ፡፡ እነዚህ ቅኔወቻችን ያስኳላው ተማሪወች ባለአገር እያሉ የሚንቋቸው አባቶቻችን  ለኢትዮጵያ ግንባታ የተጠቀሙባቸውን እሴቶች አጠናቅረው የያዙ ናቸው፡፡ በፍልሰታ መምህራን የሚዘረፏቸው ቅኔወችና ተማሪወች የሚቆጥሯቸው ቅኔወች  ከጽንፍ እስከ ጽንፍ በተዘርጋው ኢትዮጵያ ላይ ተሰናስለው የሚኖሩትን ኢትዮጵያውያንን ያስተሳሰሩባቸውን እሴቶች የሚገልጹ ናቸው፡፡ ጉባኤቃና የምንላት የመጀመሪዋ ቅኔያችን  የተሸከመችውን ሕብረተ ሰባዊ ትስሥር  ለመግለጽ እሞክራለሁ፡፡

  ገባዔ ቃና

በጉባኤ ቃና የምንጀምረው ቅኔ በኅብረ ቀለማት ተጠላልፎ እንደተሸመን  ጥንግድርብ (ጥበብ ኩታ) በብዙ ምሥጢራት የተጠናቀረ ነው፡፡ ጥንግ ድርብ የሚባለው ሸማ በተለያዩ ኅብረ ቀለማት ተጠላልፎ የተሰራ ያንዱን ቀለም ሌላው ሳይወጠው  ቀለማቱ ሳይጠፋፉ በሚያሳዩት ነጸብራቅ የጥበብነቱን ውበት የሚያንጸባርቅ ነው፡፡

ጉባኤቃና አራት ስንኞች ሁለት ግጥሞች አሏት፡፡ ሁለቱ ግጥሞች መነሻወችና ተቀባዮች ሁለት ሁለት ሐረጎች አሏቸው፡፡ ይህች በአራት ስንኞችና በሁለት ሐረጎች የተገጠመች ቅኔ ባንዲት ጎጆ የሚኖሩትን  ባልና ሚስቶች ትወክላለች፡፡ እያንዳንዳቸው ባልና ሚስት ከናቶቻቸውና ካባቶቻቸው ከሁለት አካላት ከ4 አያቶች የመጡ ናቸው፡፡ ከሁለት እናትና አባት ከ4 ሴትና ወንድ አያቶች የመጡ ሲጋቡ  (ሲጋጠሙ)  ቤት ሠሩ (ገጠሙ )ይባላል፡፡ በግጥም የሚዘጋጀውን ጽሑፍ ግጥም (ቤት መታ) እንለዋለን፡፡ ከጋብቻ የሚፈልቁት ልጆች በናትና ባባት በኩል ከተለያዩ አቅጣጫወች በቅብብሎሽ የመጣውን አካል አዋህደውና አስተባብረው በህብርንትን የገለጹ ጥንግድርቦች ናቸው፡፡

ያለ ግጥም የሚዘጋጀውን ጽሁፍ ስድ ንባብ እንለዋለን፡፡ በስነ ጽሁፋችን የተጠቀሰ ሁሉ ማህበራው ገላጭነት ሙያ አለውና፡፡ ስድ ንባብ የምንለው ስነ ጽሑፍ ላቅመ አዳም የደረሰ ወንድና ለአቅመ ሄዋን የደርሰች ሴት ከጋብቻ ርቀው በላጤነት የሚኖሩትን የሚገልጽ ነው፡፡ አልገጠሙም፤ ቤት አልሰሩም፤ ወይም ቤት አልመቱምና፡፡

ዛሬ ዓለምን የሸፈነው የሰው ዘር፡ ሐርግ አልባ ከሆኑት ከአዳምና ከሄዋን  የፈለቀ ቢሆንም፡ በአክሱም የከተሙ ሰወች አዝጋሚ ሰባዊ ሂደታቸው እስከ ዘመነ አኩስም መድረሱን አባቶቻችን ስይዘነጉ፦ የአክሱምን ከተማ የሰሩት  ከሩቅ ምሥራቅ ሳይቀር ከየአካባቢው ወደ አኩስም መጥተው ከነባሮች ጋራ ተቀላቅለው በህብርነት ኢትዮጵያውነትን ገነቡ እያሉ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት አባቶቻችን ይነግሩን ነበር፡፡

 የአክሱምን ከተማ የገነባ ከአንድ ዘር የመጣ ብቻ ሳይሆን ከሩቅ ምሥራቅ ሳይቀር የመጣ ከቅርብና ከሩቅ አገሮች ተሰብስቦና ተቀላቅሎ በመከተም ይኖር የነበር ህዝብ ነው፡፡ ይህ ተቀላቅሎ በአኩስም ከትሞ ይኖር የነበረው ህዝብ  በዮዲት ዘመን ተፈናቅሎ ወደ ማያውቀው ወደ መላ ኢትዮጵያ ተበተነ፡፡ በየደረሰበት ከማያውቀው ሕዝብ ጋር  ተቀላቀሎና ተመሳቅሎ በሰላም ተረጋግቶ ሲኖር፦ በግራኝ መሀመድ ወረራ  እንደገና በመላ ኢትዮጵያ ተበትኖ ተመሰቃቀሎና ተቀላቅሎ ኖረ፡፡ እንደገና በጣሊያኖች ወረራ ተመሳሳይ  መመሰቃቀል ገጠመው፡፡ በቀዳማዊ ንጉሥ ኃይለ ስላሴ ዘመን የነበሩት ልሂቃን የኢትዮጵያን ሕብረተሰብ በገምቢ ስልቶቻቸው ገንብተውት በመኖር ላይ ሳለ የደርግ መንግሥት መጣ፡፡ የደርግ መንግሥት ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ባይመጣም ኢትዮጵያን የመራበት መንገድ ከኢትዮጵያዊነት ጋራ የሚቃረን በመሆኑ በመጀመሪያ ጊዜ በተሰራችበት በአክሱም የተወለዱ ወያኔወች ካስኳላው ትምህርት ቤት በቀሰሙት አፍራሽ ትርክት ኢትዮጵያን በታተኑ፡፡ እየተገነባ የመጣውን የኢትዮጵያን ሕብረተሰብ ከአኩስም በፊት ወደነበረው ወደ primive ሰውነት  ወደ ኋላ የንግላል እንዲወድቅ አደረጉት፡፡ ከዚህ ቀጥየ ከአክሱም መፍረስ በኋላ ኢትዮጵያ በፈረሰችባቸው ዘመናት ሁሉ አባቶቻችን ሊቃውንት ኢትዮጵያውያን መልሰው ለመገንባት የተጠቀሟቸውን አምስቱን እሴቶች ለማሳየት እሞክራለለሁና በጥንቃቄና በትኩረት እንደትመለከቱት በትሕትና እጠይቃለሁ፡፡ 

አባቶቻችን ሊቃውንት ኢትዮጵያውያን መልሰው ለመገንባት የተጠቀሟቸው አምስቱ እሴቶች 

ኢትዮጵያ በፈረሰችባቸው ዘመናት ሁሉ የቀደሙ አባቶቻችን ኢትዮጵያውነትን እየመለሱ የገነቡባቸው ስልቶቻው ባአምስት  ቁልፎች ላይ የተመሠረቱ ነበሩ፡፡

1ኛ ባለጋራ

2ኛ ባለደም

3ኛ ባለአምጣ

4ኛ ባለቤት

5ኛ ባለአገር፦ እነዚህ  አምስቱ ቃላት  ባለ የምንላትን ሁለት ፊደላት መነሻ በማድረግ የኢትዮጵያዊነት ሕብርነት የተመሰረተባቸውን ስልቶች የሚገልጹ ናቸው፡፡ ባለ የምንላት አገባብ አንድ አካል በሌላው አካል ላይ ያለውን ባለቤትነትን የምታጎላምስ አገባብ ናት፡፡ ከዚህ በታች ከደም በመነሳት በዝርዝር እንመልከታቸው፡፡

1ኛ፦ባለ_ደም፦ ባለ የምንላት ሁለት ፊደል ከደም ጋር ስተደመር ባለደም ተብላ ትነበባለች፡፡  ማለት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ  ከያንዳንዱ ጋራ ባለ ደም ነው፡፡ ለደሙ ከራሱ ሌላ ባለቤት አለው፡፡ ይህም ማለት ኢትዮጵያዊ ሁሉ ከራሱ ሌላ ዜጋው ሁሉ ለደሙ ባለቤት ነው፡፡ ከተለያዩ አቅጣጫወች እየተጓተት እየተሳሳበ ሐረግ እየሰራ ቤት እየገጠመ የተዋለደው ሁሉ ባለ ደም ነው፡፡ ሁሉም ደሙን ይጋራዋል፡፡ ሌላውም ሌላው ባለደም ነው፡፡ በኢትዮጵያ ምድር ተወልዶ ደም ያልተወራረሰና ያልተቀዳዳ ባእድ የለም፡፡ ከዘመናት በኋላ ባስኳለው ተማሪ ትርጉሙ ከሰውነት ወደ ቁስነት ተለውጦ በሚደረገው ሽኩቻ ባለደም የሚለው በተገዳዳይነት በጠላትነት ተፈላላጊ ሆኖ ትርጉሙ ተገለበጠ፡፡ በወያኔ ጊዜ እጅግ የከፋ ሆነ፡፡ ባለደም አይደለሁም፡፡ ባባቶቻችን ግንዛቤ እኔ ለሌላው ባለደም አይደለሁም ፡ ወይም ባለደም የምለው የለኝም የሚል ኢትዮጵያዊ ካለ ሰርጎ የገባ ወፍ ዘራሽ  መጤ ተብሎ  ከኢትዮጵያ ሊባረር  ይገባል፡፡

2ኛ፦ ባለ _ቤት፦ ባለ የምንላት ፊደል ከቤት ጋራ ስትደመር ባለቤት ተብላ ትነበባለች፡፡ ከተሰራች ክንዲት ቤት ጋራ የተገናዘበ እንደፈለገ የሚኖርባት ሰው ማለት ነው፡፡ በቅኔያችን እንደተገለጸው ቤት በጋብቻ ተጣምረው ለሚኖሩባት ባልና ሚስት ባለቤትነታቸው የሚገለጽባት ናት፡፡  ከሁለት እናትና አባት ከአራት አያቶች ተጣምረው የሚኖሩ ባልና ሚስት የሚሰሯት ጎጆ  ገጠሙ ወይ ቤት መቱ ይባላል፡፡  በጎጆዋ ወይም በቤቷ የሚኖሩት ሁለቱም ለሚኖሩባት ጎጆ ባለቤቶች ናቸው፡፡  ስለዚህ ሚስት ባሏን ባለቤቴ ትለዋለች ባልም ሚስቱን እንደዚሁ ባለቤቴ (እመቤቴ) ማለትም የቤቴ እናት ይላታል፡፡  አካባቢውም የሚያውቃቸው በባለቤትነታቸው ነው፡፡  በግጥም ያልተጻፈውን ጽሑፍ ስድ ንባብ እንለዋለን፡፡  ስድ የምትለውን ቃል ወደ ሕበረተሰቡ በማምጣት በትዳር ያልተጋጥሙትን (ቤት ያልመቱትን)  ላጤ ( ልቅ)  እንላቸዋለን ፡ ይህም ያላገባ በጋብቻ ሕግ ያልታሰረ ያለባለቤትነት የሚኖር ማለት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር እያንዳንዱ ዜጋ ከኢትዮጵያ ጋራ ባለው ዜጋዊነት ከጽንፍ እስከ ጽንፍ ላለችው ኢትዮጵያ ባለቤት ነው፡፡ በየደረሰበት በጋብቻ እየተጋጠመ ቤት እየመሰረተ የመኖር ሙሉ ባለቤት ነው፡፡ በመላ ክልሎች የሚኖረው ሁሉ ኢትዮጵያዊ ከጽንፍ እስከ ጽንፍ ለተዘርጋው ኢትዮጵያ ገጽ ምድር ባለቤት ነው፡፡ ይህን የሚቃረን ኢትዮጵያዊ ካለ ጸረ ኢትዮጵያ ተብሎ ከኢትዮጵያ ሊባራረ ይገባል፡፡

3 ባለ_ጋራ፦ ባለ  የምትለው ቃል ጋራ ከምንላት ቃል ጋራ ስትደመር ባለጋራ ተብላ በመነበብ አጫፋሪ (መስተጻምር) ትሆናለች፡፡ ሁለትና ከሁለት በላይ የሆኑ አካላት የሚጣመሩበት ነገር ያላቸው መሆናቸውን ታመለክታለች፡፡ በመካከላቸው እርስ በርስ የሚያጓትታቸው ነገር ያለቸው ማለት ሲሆን፦፡ አንዱ ያላንዱ መኖር የማይችል መሆኑን የምትገልጽ ናት፡፡ያስኳላው ተማሪ እየበዛ ሲሄድ መሠረታዊ ትርጉሙን ለቆ መጋራቱ መጣመሩ ፈርሶ በጥላቻ ወደ መገፋፋት ስሜትነት ተለወጠ፡፡ በመላ ክልሎች የሚኖረው ሁሉ ኢትዮጵያዊ ከጽንፍ እስከ ጽንፍ ለተዘርጋው ኢትዮጵያ ገጽ ምድር ባለቤት ነው፡፡ የትም ሄዶ ቤት ሠርቶ ትዳር መስርቶ ለመኖር የምይገሰሥ ስልጣን አለው፡፡ ይህን የሚቃረን ኢትዮጵያዊ ካለ በውጭ ጠላት የተቀጠረ ጸረ ኢትዮጵያ ተብሎ ከኢትዮጵያ ሊባራረ ይገባል፡፡

4 ባለ_አገር፦ ባለ የምንላት ቃል ከአገር ጋራ ስትደመር ባለአገር ተብላ ትነበባለች፡፡ ኢትዮጵያ በምትባለው አገር የተወለደ ሁሉ ከጽንፍ እስከ ጽንፏ ለኢትዮጵያ ባለአገርነቱን ትገልጻለች፡፡ ያስኳላው ትምህርት ሲመጣ ከትሞ የሚኖረውን ከባለአገርነቱ ቆርጦ ከተሜ (አራዳ) አለው፡፡ በገጠር የሚኖረውን ህዝብ በከማ ከሚኖረው ህዝብ ለይቶ ባለአገር አለው፡፡ ይህም ማለት ያልሰለጠነ ኋለ ቀር ማለት ነው፡፡ በከተማና በገጠር የሚኖረውን ኢትዮጵያዊ ለያየው አናናቀው ከፋፈለው ራሱን ተማሪውንም ከውጭ የመጣ ወራሪ ባእድ አድርጎ በወራሪነት ያለ ሐፍረት ራሱን እንዲሰይም አደረገው፡፡ የኔ ቢጤውን አገር በቀል ተማሪ ባለአገር አለው፡፡ ከዳር እስከዳር ለተዘረጋቸው አገር ባእድ ወራሪና አስወራሪ አደረገው፡፡  በመላ ክልሎች የሚኖረው ሁሉ ኢትዮጵያዊ ከጽንፍ እስከ ጽንፍ ለተዘርጋው ኢትዮጵያ ገጽ ምድር ባለአገር ነው፡፡ ማንም ማንንም ባለአገር አይደለህም ሌለው ፈጽሞ ስልጣን የለውም፡፡ ይህን ለማለት የሚደፍር ካለ በውጭ ጠላት የተቀጠረ ጸረኢትዮጵያ በመባል ተፈርጆ በከባድ ወንጀል ሊቀጣ ይገባዋል፡፡

5 ባለ_አምጣ፦ ባለ የምንላት ቃል ከአምጣ ጋራ ስትደመር ባለአምጣ ተብላ ተነበባለች፡፡ ከመነሻዋ ተነጥላ ብቻዋን ስትሆንና ባአንድ ሰው ስትገለጥ፡  ተነጋሪው በቅርቡ ካለው ሰው አንድ ነገር ፈልጎ እንዲሰጠው መጠየቂያ ቃል ናት፡፡ ይህም ማለት አንዱ ካንዱ የሚፈልገውን ነገር እንዲሰጠው እንዲያቀብለው ወይም እንዲሰጣጡ እንዲቀባበሉ በጎ ፈቃዳቸውን የምታሳይ ቃል ነት፡፡ ሁሉ ባለአምጣ ነው፡፡ በመላ ክልሎች የሚኖረው ሁሉ ኢትዮጵያዊ፡ ወደ ሌላ ክልል ቢሄድና ለመኖር ፈልጎ በሰላም በፍቅር የሚፈልገውን ቢጠይቅ ፤ በቋንቋው በሃይማኖቱ የሚነፍግ ኢትዮጵያዊ የተረገመ ነው፡፡ ባለአምጣ አይደለሁም፡፡ ወይም ለአምጣልህ  የምለውና አምጣልኝ የሚለኝ የለም የሚል ኢትዮጵያዊ ቢኖር በሌላ ፕላኔት እንደሚኖር ተፈርጆ ከኢትዮጵያ ሊባረር ይገባል፡፡

ዶክተር ዮናስ ብሩ “We (intellectuals, activists and political junkies) are an integral part of the national political crisis by omission or commission whether our transgressions are misfeasance or malfeasance in nature. If we are to save our people who have become victims of political conflicts that have become accustomed to brewing and fomenting, we must start with our confession, repentance, and redemption” ያሉት በዚህች ጦማር የተገለጹትን እሴቶቻችንን ላፈረሰው ትርክት ተሳታፊ በመሆናቸው መሰለኝ፡፡ አለዚያማ  ለምኑ ነው የሚጸጸቱት? ምኑን ከምኑ ጋራ ቀላቅለውና በርዘውት ነው brewing and formenting የሚሉት? ፡፡ Redemption የሚሉትስ  የሚታደጉት ምኑን ይሆን? መልሱን ከራሳቸው እጠብቃለሁ፡፡ በተረፈ የዘንድሮዋን ፍልሰታ በዚህ እንድናልፋት የፈቀደ አምላክ፦ የከርሞዋን ፍልሰታ ዶተር ዮናስ ብሩ ባቀረቡልን የንስሀ ጥሪ ንስሀ ገብተን፡  የአባቶቻችን የግንባታ እሴቶች ተጠቅመን፡ እንደጤፏ የወደቀችውን ኢትዮጵያን ለማንሳት፡ ወያኔወች በፈጠሩት ክልል የተቆራረጠውን ህዝባችንን ለመሰብሰብና ኢትዮጵያውነታችን እንደገና በቅላ እንድትነሳ ለማድረግ ያብቃን፡፡

የአባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔር የከርሞ ሰዎች ይበለን!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop