June 8, 2024
14 mins read

ብቼኝነት ሞት ነው !Loneliness is Death! Eenzaamheid is dood!

Lonelinessሰኔ 1 ቀን 2016 ዓም(08-06-2024)

ቀኑ ጻሃያማና ወጣ ብሎ  ለመዝናናት የሚያመች በመሆኑ ከባለቤቴ ጋር  በምንኖርበት አካባቢ በየሳምንቱ የሚወጣውን የሜዳ ገበያ(OPEN MARKET) ስንዞር በአደባባዩ መሃል ላይ ይህ ከላይ የተቀመጠው ምስል ቀልባችንን ሳበውና ለማዬት ተጠጋን።ይህ የእጅ ሥራ ውጤት የሆነው አንገቱን የደፋ የወጣት ምስል ገና ሳይቀርቡት ስሜትን ይነካል፤ እዬቀረቡት ሲሄዱ በወጣቱ ዙሪያ የተቀመጠው መልእክትና የተደረደሩት የወጣቶች ፎቶግራፎች ይበልጥ ስሜትን ይቀሰቅሳሉ።መልእክቱ ከ30 ዓመት በታች ለሆኑ ወጣቶች እራሳቸውን ለማጥፋት የሚያስገድዳቸው ዋናው  ምክንያት ብቼኝነት እንደሆነ ይገልጻል።በምስሉ ስር የተደረደሩት የወጣቶቹ ፎቶዎችም በዚህ የብቸኝነት ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ውስጥ ገብተው እራሳቸውን ያጠፉትን የሚያሳይ ነው። ታዲያ ይህንን አሳሳቢ  መልእክት በግል ይዞ ከመቀመጥ ብቼኝነት  ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ ከማውቀው አንዳንድ ታሪክ ጋር አዛምጀ ለሌላው በተለይም ለወጣቱ ትውልድ ማካፈል እንዳለብኝ ህሊናዬ አስገደደኝ።

ስለሰው ልጆች ተፈጥሮ ያጠኑ ምሁራን በጥናታቸው የሰው ልጅ ብቻውን መኖር፣ብቻውን መስራት የማይችል መሆኑን፣  በብዙ ማህበራዊ  ሰንሰለቶች የተሳሰረ ፍጡር እንደሆነ በአጭር አገላለጽ ማህበራዊ እንስሳ ነው ( SOCIAL ANIMAL)በማለት ገልጸውታል።በአገራችንም አዛውንቶቹ ስለብቸኝነት ሲገልጹ ለብቻ በሰሃን መብላት ከመጣ ጀምሮ የሰው ልጅ ብቸኝነትን ለመደ፣አውሬ ሆነ ይላሉ፤አዎ በቀድሞ ጊዜ በአገራችን ቤተሰብም ሆነ ጎረቤት ሲገናኝና ዓመት በዓላትን ሲያከብር፣ደሃና ሃብታም የዚህ እምነት ወይም የዚያ ጎሳ ሳይባባል የሚመገበው በአንድ ሞሰብ ላይ የቀረበ ምግብ ተሻምቶ ፣እዬተጎራረሰ ፣ብላልኝ ብይልኝ እዬተባባለ ነበር።ያም በአንድ የበላና የጠጣ ለክፉ ነገር እንደማይፈላለግ የቃል ኪዳን ማሰሪያ ሆኖ አገልግሏል።እቁብ፣ማህበርና እድሩም የዚያ የአብሮነት መገለጫዎች ናቸው።ከነጠላ ይልቅ ብዙህነት ይደምቃል፣ ይሞቃል፣ከጥቃትም ያድናል።ሌላው ቀርቶ በአንድነት ተስማምተው የፈሱት ፈስ አይገማም  ይባል የለ!ብቻውን የቆመ ለጥቃት ይመቻል፣ ብቻውን የበላ ብቻውን ይሞታል ሲሉም ብቼኝነት ወይም ግለኝነት  ቀባሪ አልባ የመሆንን እጣ እንደሚዳርግ ለመግለጽ የተጠቀሙበት ብሂል ነው።

የሰው ልጅ ሁለት ዓይን፣ሁለት እጅና ሁለት እግርም ይዞ መፈጠሩ በአንድ ብቻ የተሟላ ቁመና፣ የማዬት ፣የመሥራትና የመንቀሳቀስ ችሎታው የመነመነና የማይቻል ስለሆነ ነው። የሰው  ልጅ እንኳንስ ኑሮውን ይቅርና ሞትንም ቢሆን በጋራ ሲቀበለው የሚያሳድረው ስሜት የተለዬ ነው።  አንዱ ለሌላው ለመሞት የሚሽቀዳደምበት ምስጢሩ ለአብሮነት ካለው ፍላጎት የመነጨ በመሆኑ ነው።ብቼኝነት ይህንን ሁሉ ለዛ ያለው አብሮነትን ያሳጣል።በአሁኑ ዘመን በተለይም በከበርቴው ዓለም የሰው ልጅ በተለይም ወጣቱ ወዶ ሳይሆን ተገዶ የሚገባበት መከራ ሆኗል። ከሰው ተወልዶ፣ ከሰው ጋር አድጎ ፣በሰው መካከል እዬኖረ ብቻውን ለመሆን የሚገደድበትና የሚገፋፋው ምክንያት ይኖረዋል።አብሮ ሮጦ፣ ተጫውቶ፣ስቆና ተሳስቆ ከኖረበት ማህበረሰብና አካባቢ ለመነጠል በከባድ አስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ ማለፍን ይጠይቃል።ወይም ምክንያቶች ይኖሩታል።ምንም እንኳን በዘርፉ ባለሙያ ባልሆንም ካዬሁትና ከሰማሁት እንዲሁም ካነበብኩት በመነሳት ከምክንያቶቹ መካከል በጥቂቱ የሚከተሉት ናቸው።

1 ቤተሰብ ለልጁ ካለው ፍቅርና መሳሳት፣ለወደፊቱ ለተሻለ ኑሮው ሲሉ  ልጅን ከሚችለው በላይ ወይም ከፍላጎቱ ውጭ እንዲያደርግማስጨነቅ፣እንዲሁም ከክፉ ነገር ከመጠበቅ የተነሳ ከውጩ ዓለም ወይም ከዕድሜ እኩያዎቹ ጋር እንዳይገናኝ በቤተሰቡ ዙሪያ ብቻ ወይም በራሱ ሳጥን ውስጥ እንዲቀመጥ የማድረጉ ሁኔታ ነፍስ እያወቀ ሲሄድ ለከባቢው ባዳና እንግዳ ይሆንና ከማያውቀው ዓለም የገባ ሲመስለው ፍርሃትና ጭንቀት ውስጥ  ይገባል፤ሌሎቹ የሚናገሩትና የሚያደርጉት አይገባውም፤ስለሆነም ከመቀላቀል ይልቅ እራሱን ይነጥላል።እራሱን የዓለም አካል አድርጎ አይቆጥረውም።ሁሉም ነገር አይጥመውም።ስለሆነም ከከባቢው መራቅን ባይተዋርነትን  ይመርጣል፤ ያም ስሜት እያደገ ሲሄድ መውጫ ሲያጣና አጣብቂኝ ውስጥ ሲገባ ፣ተስፋ መቁረጥ ያድርበታል እራሱን ለማጥፋት ውሳኔ ላይ ያደርሰዋል።

2 በዓለም ላይ የተዘረጉ የጥፋትና የልማት መንገዶች መኖራቸው አይካድም።የሰው ልጅ ከነዚህ ውስጥ አንዱን የመምረጥና የመከተል ችሎታ አለው።ይህ ችሎታው ግን በሌሎች ወይም በአካባቢው ባሉት የመዘወር ዕድሉ ብዙ ነው።ያንን ፈተና አሸንፎ መውጣት ብቃትን ይጠይቃል።በተለይም በጉርምስና ወይም በወጣትነት ዕድሜ  አንዱ ከሌላው ላለማነስ ወይም አንሶ ላለመታዬት ሲል ፉክክር ውስጥ ይገባና የጥሩ ወይም የመጥፎ ውጤት ሰለባ ይሆናል።መልካም ነገሮች እንዳሉ ሁሉ መጥፎና አደገኛ ነገሮችም ተዘርግተዋል።ከጥፋት መንገዶች መካከል ወጣቱን ለውድቀት የሚዳርጉት የአደገኛ ሱሶች ሰለባ መሆን ነው።በድራግ፣በአልኮል የመሳሰሉት ሱሶች መጠመድ ከማይወጡት መከራ ውስጥ ይከታል።በነዚህ ሱሶች የተነሳ እራስን በወንጀል ተግባር ላይ ማለትም፤በስርቆት ከዚያም በላይ በግድያ ላይ እንዲሰማራ  ይገፋፋዋል።ያም በእስር  ጉረኖ ውስጥ ገብቶ ብቻውን እንደ አውሬ እንዲኖር ልማድ ያዳብርበታል።በዚህ  ተግባር የተሰማራ በከባቢ የሚኖረውን ተቀባይነት ማጣት ብቻም ሳይሆን የተጠላና የተገፋ ያደርገዋል።አመል ያወጣል ከመሃል የሚለው ያገራችን አባባልም ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ነው።ይህ መገፋትና መጠላት ለብቼኝነት ኑሮ ያጋልጠዋል።የማታ ማታም ሁሉም ነገር ከአቅሙ በላይና ዙሪያው ገደል ሲሆንበት ህይወቱን ለማጥፋት ውሳኔ ላይ ያደርሰዋል።የታደለው ደግሞ ለመዳን የተከፈተለትን ዕድል ተጠቅሞ እራሱንም ማህበረሰቡንም የሚጠቅም ይሆናል።

3 የሰውን ልጅ በተለይም ወጣቱን በጥላቻ መንፈስ ሌላውን ብሎም እራስን ለማጥፋት ከሚገፋፉ ምክንያቶች ውስጥ አንዱ የሆነው በዓለም ወይም በሚኖርበት አገር የሰፈነው ስርዓት የሚወልደው የፍርሃት፣የጭንቀት፣የሽብር፣የኑሮ ሸክም፣እንዲሁም በሕዝቡ መካከል የሚረጨው የጥላቻና የልዩነት መርዝ ለተስፋ መቁረጥና ለአጥፍቶ መጥፋት የሚሰለፉበትን መንገድ ይቀይሳል።ከግለሰብ አልፎ ለማህበረሰብ ቀውስና ለአገር ሰላም መናጋት ይህ ትልቁ ምክንያት እንደሆነ አይካድም።በአገራችንም የሚታይ አደጋ  ነው።

እውጭ አገር በሚኖረውም ኢትዮጵያዊ ይህ  የብቸኝነት ችግርና በባዶ ቤት ሞቶ መገኘት የተለመደ ሆኗል።በተለይም በድራግና  በመጠጥ ሱስ ከመለከፍ ጀምሮ ለከባቢ ባይተዋርነት፣ለማያውቁት ቋንቋና ለማህበረሰብ ባህል እንግዳነት ከዚያም ባለፈ የዘር ተጽእኖ በሚያስከትለው መረበሽና ብስጭት፣ሥራ የማጣትና ያሰቡትን ያለማግኘት፣በቤተሰብ ናፍቆት ላይ የአገር፣በጎሳ የመከፋፈሉና ምስቅልቅል ሁኔታ መፈጠሩ፣እርስ በርስ መጠራጠሩና እንደ ጠላት በጎሪጥ መተያዬቱ ሲጨመርበት እራስን ከሌላው ለማራቅና  ህይወትን ለማጥፋት የሚያበቁ ምክንያቶች ሆነዋል።።

ከላይ ለተጠቀሰው ህይወትን እስከማጥፋት ድረስ ለሚያበቃው ብቸኝነት መፍትሄው የሰው ልጅ ብቻውን ለመኖር የሚገፋፉትን፣የሚለያዩትን ምክንያቶች ማሶገድና በዚህ የተጠመዱትን ለማዳን  ሁሉም መተባበር ይኖርበታል።በዚህ ልክፍት የተበከለውም ለመዳን ፈቃደኛ ሆኖ መገኘት አለበት።አውሬ ከሰው ጋር በሚኖርበት ዘመን ሰው ከሰው ተለይቶ መኖሩን መቀበል  ከአውሬ ያነሱ ሆኖ መገኘት ነው።

አሁን በዓለማችን ላይ ለሰፈነው ችግር፣ጦርነትና የአጥፍቶ መጥፋት ውድድር፣ለእርስበርስ እልቂት ምክንያቱ ለጋራ ጥቅም ሳይሆን የብቼኛነት ወይም ግለኝነት ህሳቤ በሚፈጥረው እራስ ወዳድነት የተነሳ ነው።ይህ የብቸኛነትና እራስ ወዳድነት ስሜት ሲወገደና ሁሉም ለሁሉም ማሰቡን ሲጀምር የመግደልና የመገዳደል በሽታ ያከትማል።የሰው ልጅ  ተወልዶ፣አድጎና ለቁም ነገር በቅቶ፣ የሚገጥሙትን ችግሮች በጋራ እያቃለለና እያሶገደ  በሰላምና በፍቅር ኖሮ የተመደበለትን የዕድሜ ገደብ አጠናቆ በተፈጥሮ ሞት ይለያል።ትውልድም ለዚህ የተፈጥሮ ሕግ እኩል ተገዥ ሆኖ እዬተተካካ ይቀጥላል።

ሰላማዊ ኑሮ  ለሰው ልጆች ሁሉ ይሁን!

አገሬ አዲስ

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

የአማራ ፋኖ በጎጃም ምክትል የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ የነበረው እና አሁን ላይ በአማራ ፋኖ በጎጃም የሁለተኛ (ተፈራ ) ክፍለጦር ሰብሳቢ የነበረው ፋኖ ዮሐንስ አለማየሁ በክብር ተሰዋ። የአማራ ህዝብ የተጋረጠበትን የህሎና አደጋ ለመቀልበስ ያለ

ከአማራ ፋኖ በጎጃም የተሰጠ የሐዘን መግለጫ ታጋይ ይሰዋል ትግል ይቀጥላል !

January 22, 2025
ዳግማዊ ጉዱ ካሣ “ይድረስ ለእገሌ” ማለቱ ሰለቸኝና ተውኩት እንጂ ዛሬም መጻፍ የፈለግሁት የአማራን ዕልቂት ለመታደግና የኢትዮጵያን ትንሣኤ ለማብሰር እየተዋደቁ ላሉት ወገኖቼ ነው – በፋኖም ይሁን በሌላ ስም፡፡ ኢትዮጵያን ወደቀደመ ክብሯ ለመመለስ የነገድና

ጀልባዋ አትሰምጥም፤ የሚሰምጥ ግን አለ!

[ማስታወሻ ከፍል አንድ፣ በዘሐበሻ ድረ ገጽ ላይ ኦፍ ጃዋር አንድ ኢትዮጵያ ተብሎ በእንግልዝኛ ወጥቷል] (https://zehabesha.com/of-jawar-and-ethiopia/) ባለፈው ሰሞን፣ ጃዋር መሐመድ ከደረጀ ኃይሌ ጋር  በነገራችን ላይ ክፍል ሁለት ባደረገው ቃለ ምልልስ ላይ ተመስርቼ ገንቢ አስተያየት ጽፌ በኢንግሊዝኛው ዘሐበሻ ድረ ገጽ ላይ አሳትሜ ነበር። አስተያየቴ በዚህ ቃለ ምልልስ

ስለ ጃዋርና ኢትዮጵያ (ክፍል ሁለት)

January 20, 2025 ጠገናው ጎሹ የአቤ ጎበኛው አልወለድም ለወገኖቹ መብት መከበር ሲል ባደረገው ጥረት ምክንያት እንደ ወንጀለኛ ተቆጥሮ ይሙት በቃ በፈረዱበት ጊዜ በምላሳቸው መልካም  አድርጎ ስለ መገኘት እያወሩ በድርጊት ግን ተቃራኔውን የሚያደርጉ ሁሉ

ወዮ ለመከረኛው የአገሬ ህዝብ እንጅ  ታየማ ታየ ነው

መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ “ ሰው የሰነፎችን ዜማ ከሚሰማ ይልቅ የጠቢባንን ተግሣጽ መስማት ይሻለዋል። ”   — መክብብ 7፥5 እስቲ ቆም ብለን በማሰብ  ራሳችንን እንፈትሽ ።  እንደ ሰው ፣ የምንጓዝበት መንገድ ትክክል ነውን ? ከቶስ ሰው መሆናችንን እናምናለንን ? እያንዳንዳችን ሰው መሆናችንን እስካላመንን ጊዜ ድረስ ጥላቻችን እየገዘፈ

 ለሀገር ክብርና ብልፅግና ብለን ፤ ቆም ብለን በማሰብ ፤ ህሊናችንን ከጥላቻ እናፅዳ

                                                         ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)                                                       ጥር 12፣ 2017(January 20, 2025) ጆ ባይደን ስልጣናቸውን ለማስረከብ ጥቂት ቀናት ሲቀራቸው በአሜሪካን ምድር በጣም አደገኛ የሆነ የኦሊጋርኪ መደብ እንደተፈጠረና፣ የአሜሪካንንም ዲሞክራሲ አደጋ ውስጥ ሊጥለው እንደሚችል ተናግረዋል።  ጆ ባይደን እንዳሉት በተለይም በሃይ ቴክ

አሜሪካ ወደ ኦሊጋርኪ አገዛዝ እያመራ ነው! ጆ ባይደን ስልጣን ለመልቀቅ ጥቂታ ቀናት ሲቀራቸው የተናዘዙት!!

ከነፃነት ዘገዬ የአራት ኪሎው ኦነግ ሸኔ ከቁጥር ጋር እንደተጣላ ዕድሜውን አገባደደ፡፡ ኦነግ/ኦህዲድ ዛሬም ሆነ ዱሮ፣ በቤተ መንግሥትም ይሁን በጫካ ቁጥር ላይ ያለው አቋም ምን ጊዜም ያስደንቀኛል፡፡ ደግሞም እየባሰባቸው እንጂ ሲቀንሱ አይታዩም፡፡ ጥቂት

80 ቢሊዮን ብር ስንት ብር ነው?

በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና

ሰው ሆይ!

Go toTop