ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)
ሚያዚያ 22፣ 2016 (ሚያዚያ 30፣ 2024)
Sapere Aude-Have the courage to use your own mind (Immanuel Kant)
በገጽ ሁለት በአንቀጽ ሁለት ላይ፣ „As recent political developments have proven, traditional political and sociological tools are not capable of explaining Ethiopia`s perceived and/or real socio-political phenomena that have many moving parts that are constantly crisscross and disrupting each other.” ዮናስ ብሩ ከላይ ሊያስገነዝበን እንደሚፈልገው ጥንታዊው የሆኑት የፖለቲካና የሶስዮሎጂ መሳሪያዎች(Traditional political and sociological tooles) የኢትዮጵያን የተወሳሰቡ ችግሮች እንድንረዳ የሚያስችሉን አይደሉም። በሌላ ወገን ግን ዮናስ ብሩ እነዚህ “ጥንታዊ የፖለቲካና የሶስዮሎጂ መሳሪያዎች” ምን እንደሚመስሉና መቼስ በኢትዮጵያ ምድር ተግባራዊ እንደሆኑ ሊነግረን አልቻለም። እንዲያው ብቻ እነዚህ ሁለት “ጥንታዊ የፖለቲካና የሶስዮሎጂ መሳሪያዎች” የኢትዮጵያን ሁኔታ በሚገባ ሊገልጹና መፍትሄም ማቅረብ ስለማይችሉ ያለን አማራጭ ኳንተም ፊዚክስን በመጠቀም ወይም እሱን እንደመመራመሪያ መሳሪያ በመውሰድ ብቻ ነው ሁላችንንም ሊያግባባ ወደሚችለው ብሄራዊ ውይይት ለመድረስ የምንችለው ይለናል።
የፖለቲካ ቲዎሪን ወይም ፍልስፍናን አፀናነስ ታሪክ ተመራምረን እንደሆን በኢትዮጵያ የህብረተሰብ አገነባብ ታሪክ ውስጥ የፖለቲካና የሶስይሎጂ ቲዎሪዎች አልተፀነሱም። በዘመነ-ፊዩዳሊዝም አፄ ኃይለስላሴ ከስልጣን እንዲወርዱ እስከተደረጉበት ጊዜ ድረስና በደርግ የ17 ዓመት የስልጣን ዘመንና በኋላ ላይና እስከዛሬም ድረስ አንዳችም ቦታ ላይ የኢትዮጵያን የህብረተሰብ ችግር ፖለቲካዊና ሶስዮሎጂያዊ በሆነ መንገድ እየተጠናና ምርምር እየተደረገ እየተወሳሰቡ ለመጡት ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ የባህልና የስነ-ልቦና ችግሮች መፍትሄ ለመስጠት አልተሞከረም። ማለት የሚቻለው ሁሉም ነገር በአቦሰጡኛና በጉልበት ተግባራዊ የሚሆኑ ነበሩ፤ ናቸውም። ይህም ማለት ያለፉት ሶስት አገዛዞችና የአሁኑም በአቢይ ህመድ የሚመራው “አገዛዝ” ካላንዳች ፍልስፍና፣ ፖለቲካዊና ሶስዮሎጂያዊ መመሪያዎች ነው ዝም ብለው አገራችንን የሚያተረማምሱት፤ የኢኮኖሚ ፖሊሲያቸውም ከውጭ የመጣና በህዝባችን ላይ የተጫነ እንጂ የህዝባችንን መሰረታዊ ፍላጎቶች ደረጃ በደረጃ በመፍታት፣ አገራችንን በጠንካራ መሰረት ላይ እንድትገነባ የሚያደርጉ አይደሉም። ከዚህም በላይ ስልጣንን ከያዙት የገዢ መደቦች ውጭ በምሁር ደረጃም የኢትዮጵያን የህብረተሰብ ችግር በመረዳት ጥናት፣ ውይይትና ክርክር ተካሂዶ አያውቅም። ይደረገ የነበረው ”ምሁራዊ ውይይት” በተማሪው እንቅስቃሴ ዙሪያ ነበር። እሱም ቢሆን ከፖለቲካና ከሶስዮሎጂ አንፃር የአገራችንን ችግሮች ደረጃ በደረጃ በማጥናትና ምርምር በማድረግ በዚህ መልክ ነው የተወሳሰቡትን የአገራችንን ችግሮች መፍታት የሚቻለው ተብሎ አንዳችም ትንተና አይቀርብም ነበር። ይደረግ የነበረው ትግል በመሬት ለአራሹና በጣም ውስን በሆነ መልክ በዲሞክራሲ ጥያቄ ዙሪያ ነበር። ስለሆነም በአገራችን ምድር “ጥንታዊው የፖለቲካና የሶስዮሎጂ መሳሪያ “ እንደዚህ ነበር፣ የተወሳሰበውንም የአገራችንን ችግሮች በበቂው ለመረዳት የሚያስችል ስላልነበር መፍትሄ ሊሰጠንና ወደ ተረጋጋ ሁኔታ ሊያመጣን አልቻለም ብሎ ዮናስ ብሩ በፍጹም ሊነግረን አልቻለም። በሌላ አነጋገር፣ ጥንታዊው የሶስዮሎጂና የፖለቲካ ቲዎሪዎች ምን እንደሆኑ ለማብራራት በፍጹም አልቻለም። ለመሆኑ ጥንታዊ የሚባሉ የሶስዮሎጂና የፖለቲካ ቲዎሪዎች አሉ ወይ? ካሉ ግልጽ በሆነ መልክ መቀመጥ አለባቸው። በደፈናው ጥንታዊ የፖለቲካና የሶስዮሎጂ መሳሪያዎች ብሎ ማስቀመጥ አንባቢን ግራ ማጋባት ብቻ ይሆናል።
በአጠቃላይ የኢትዮጵያን የፖለቲካና የሶሽዮ ኢኮኖሚ አወቃቀር በምንመረምርበት ጊዜ ኢትዮጵያ ሶስት ዐይነት የፖለቲካ አወቃቀሮችን በማለፍ በዛሬው ወቅት በአራተኛው ላይ ትገኛለች። እነዚህም ቢሆን ሆን ተብለው በመጠናት የተዋቀሩ ሳይሆኑ ፊዩዳሊዝም ኢቮሉሺነሪ(Evolutionary) በሆነ መልክ እያደገ የመጣ ሲሆን፣ ሌሎቹ የኋላኛዎቹ ደግሞ የጊዜው አዝማሚያዎች(Zeit Geist) ውጤቶች ናቸው ማለት ይቻላል። በአፄ ኃይ‹ለስላሴ ዘመን የነበረው ግማሽ ፊዩዳሊዝም ግማሽ ቢሮክራቲክ ካፒታሊዝም በመባል የሚታወቅ ሲሆን፣ በደርግ ዘመን ይህንን ስርዓት እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ “በማስወገድና” የመንግስቱን መኪና ለሱ በሚስማማ መልክ በማዋቀር ከተወሰነ ጊዜ “ዲሞክራሲያዊ የሂደት ሁኔታ” በኋላ ወደ ጨቋኝነትና ዲሞክራሲ አፋኝነት በመሸጋገር ሁለ-ገብ የሆነ የኢኮኖሚ ዕድገት ተግባራዊ ለማድረግ አልተቻለም። ደርግና አማካሪዎችም ስለኢኮኖሚ ቲዎሪና ፖሊሲ አጠቃላይ ግንዛቤ ስላልነበራቸው በመንግስትና በግለሰብ ተሳትፎ ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ስርዓት ያለውና ሰፊውን ህዝብና የጥሬ-ሀብትን በማንቀሳቀስ አገርን በአስተማማኝ ሁኔታ መገንባት አልተቻለም። የደርግን የኢኮኖሚ ፖሊሲ በምንመረምርበት ጊዜ የመሬት ላራሹን ከማወጅና ኢንዱስትሪዎችንና የመድህን ኩባንያዎችን በመንግስት ቁጥጥር ስር ከማድረግ በስተቀር አገሪቱን ሁለ-ገብ በሆነ መልክ ሊያስገነባ የሚያስችል የኢኮኖሚ ቲዎሪና ፖሊሲ በፍጹም አልነበረውም። በደፈናው ደርግ ይከተል የነበረው “የዕዝ ፖሊሲ” ነው እየተባለ ይነገረን ነበር። በሌላ ወገን ግን “የዕዝ ፖሊሲው” መሰረተ-ሃሳብና ቲዎሪው ግልጽ አልነበሩም።
በአጠቃላይ ሲታይ ደርግ በሶሻሊስት ርዕዮተ-ዓለም የሚመራ አገዛዝ ነው ቢባልም፣ በቲዎሪ ላይ በተደገፈ ጥናት በመመርኮዝ በጊዜው የሚታየውን በብሄረሰብ ትግል ዙሪያና በሌሎችም አኳያ የሚካሄደውን ይሁንና ግን በአንዳች ቲዎሪና ሳይንስ የማይደገፈውን ትግል በአርቆ አስተዋይነትና ጥበብ በተሞላበት ፖለቲካ ሊፈታው አልቻለም። ደርግ ከሚሊታሪ የተውጣጣ ስብስብ እንደመሆኑና ፖለቲካሊ እንዲያስብ ሆኖ የሰለጠነ ባለመሆኑ መንፈሱ ውስጥ በተቀረፀው የሚሊታሪ አስተሳሰብ ብቻ በመመራት ነበር ችግሩን በጦርነት ለመፍታት ታጥቆ የተነሳው። ሌሎችም ብሄራዊ ባህርይ አለን የሚሉ ድርጅቶችም በፖለቲካና በሶስዮሎጂ ቲዎሪ እየተመሩ ሁኔታውን ለማረጋጋትና ሰላም ለማስፈን ከመፈለግ ይልቅ እልክ ውስጥ በመግባት ነው ወደ መጠፋፋት ውስጥ የገቡት። ይህ ዐይነቱ አስተሳሰብና ድርጊት የሚያረጋግጠው በጊዜው በፖለቲካ ዓለም ውስጥ ይሳተፉ የነበሩ ልዩ ልዩ ኃይሎች በሙሉ መንፈሳቸው ወይም አዕምሮአቸው በዕውቀት ያልታነፀና የተገለፀላቸውም እንዳልነበሩ ነው። ይም ማለት ግን አርቀው ማሰብ የሚችሉና የተካረረውን ሁኔታ በሰላምና በውውይት ለመፍታት የሚጥሩ ግለሰቦች አልነበሩም ማለት አይደለም። በአጠቃላይ ሲታይ ግን መንፈሱ ወይም አዕምሮው በጥሩ ዕውቀት ያልተኮተኮተና ያልዳበረ ሰው ወይም ድርጅት ደግሞ የመከራከር፣ ሌላው የሚለውን የማዳመጥና የራሱን አስተያየት ሲቪል በሆነ መልክ በማብራራት ወደሚያግባባ ነገር ላይ ለመድረስ አይፈልግም። የጊዜው አዝማሚያም ሃሳቤን ትቀብላለህ ወይም አትቀበልም፣ የእኔ ወዳጅ ያልሆነ ጠላቴ ነው በሚል ፖለቲካን በወዳጅና በጠላት በመከለል ወደግብግብ ለማምራት የሚሯሯጥ ነበር። ስለሆነም በኢትዮጵያ የህብረተሰብ ታሪክ ውስጥ ፖለቲካዊና ሶስዮሎጂያዊ ውይይቶች የሚታወቁ አልነበሩም፤ ዛሬም አይታወቁም። የሁላችንም መንፈስ ማለት ይቻላል በአመጽና በቂም-በቀል አስተሳሰብ የታነፀ በመሆኑ የመጨረሻ መጨረሻ ያለን አማራጭ ሌላውን አጥፍቶ ራስንም ማጥፋት ነው። ይህም በራሱ የሚያረጋግጠው ታጋይ ነን የሚሉ ኃይሎች በሙሉ ምንም ዐይነት ህብረተሰብአዊ ፕሮጀክት እንዳልነበራቸው ነው። ጠቅላላውን ህዝባችንን በማሰተባበር፣ በማንቃትና በማደራጀት አዲስ ኢትዮጵያን መገንባት አለብን ብለው የተነሱ አልነበሩም፤ ዛሬም የሉም። ዋና ዓላማቸውም አንድና አንድ ነገር ብቻ ነበር፤ ስልጣን ላይ ወጥቶ የጥፋትና የቂም-በቀል ፖለቲካ ማካሄድ። ይህ ዐይነቱ አካሄድ ደግሞ ፖለቲካዊ ሳይሆን እንዲያው በደመ-ነፍስ በመመራት ዘለዓለማዊ ትርምስ እንዲፈጠር ማድረግ ነው።
“በአብዮቱ ወቅት” ደርግ የተለያዩ በማርክሲዝም ሌኒንዝም ስም ይታገሉ የነበሩትን ድርጅቶች ቀስ በቀስ ካኮላሸ ወይም ከመታ በኋላ ኢሰአፓ የሚባለውን “ድርጅት” በመመስረት የድርጅቱ አባል ያልሆነ በሙሉ ፀረ-አብዮተኛ በመባል በጥርጣሬ የሚታይና ክትትልም የሚደረግበት ነበር። በሌሎች የማርክሲስት ሌኒንስት ድርጅቶች መሀከልም የነበረው ችግር በሌላ መልክ ይህንን የሚመስል ነበር። አንድ ሰው አይ የመኢሶን ወይም ደግሞ የኢህአፓ አባል መሆን ነበረበት። ይህም ማለት ለሌላ አስተሳሰብና ለፖለቲካ ዲስኮርስ ክፍት ያልነበረን ሁኔታ እንመለከታለን። ስለሆነም ሁለም እንደ ጠላት የሚታያዩ እንጂ በሚያስማማ ነገር ላይ በመስማማት አገራችንን በጋራ እንገንባ ብለው የሚያስቡ አልነበሩም። ይህ ዐይነቱ አስተሳሰብ ደግሞ ከማርክሲዝም አስተሳብ ጋር የሚሄድ ሳይሆን፣ ሆበስ የሚባለው በ17ኛው ክፍለ-ዘመን ላይ የነበረው የእንግሊዙ የፖለቲካ ፈላስፋ ያዳበረውን፣ “ማንኛውም ሰው እንደቀበሮ የሚታይና፣ አንዱ ሌላውን የማያምንና መንፈሱ በመጠራጠር ላይ የተመሰረተ ነው” የሚለውን የተሳሳተ አስተሳሰብ ያስታውሰናል። በሌላ አነጋገር፤ ማንኛውም ሰው እንደ ጠላት የሚታይ እንጂ እንደተፎካካሪ፣ አሊያም ደግሞ እንደ አጋር ወይም እንደ ወዳጅ የሚታይ አይደለም። በሆበሰ ዕምነት የሰው ልጅ በአፈጣጠሩ ለራሱ ብቻ የሚያስብ ስለሆነ መንፈሱ የሚጠራጠርና ሌላውን የማያምን ነው። ለዚህ ዐይነቱ የቀበሮዎች ዐይነት ባህርይ ሆበስ የሰጠው መፍትሄ ሁሉንም አንቀጥቅጦ ሊገዛ የሚችል አስፈሪ ሞናርኪያዊ አገዛዝ ስልጣን ላይ መውጣት አለበት። በዚህ መልክ ብቻ በአንድ አገር ውስጥ መረጋጋት ይኖራል ይለናል። ይህ ዐይነቱ የሆበስ አባባል ግን በአንትሮፖሎጂ ጥናትና በህብረተሰብ የዕድገት ታሪክ ውስጥ ያልተረጋገጠ ነው። የሰው ልጅ ማህበራዊ (Social Being) እንደሆነና፣ አንደኛው ለሌላኛው እንደሚያስብ በእሱ ዘመን በነበሩ እንደ ሁም፣ ሎክና የኋላ ላይ ደግሞ በእነ አዳም ስሚዝ ትችት እንደደረሰበትና የሆበስ አባባልም ትክክል እንዳልሆነ ለማረጋገጥ ችለዋል። ይሁንና ግን በተለይም በካፒታሊዝም ዕድገትና መስፋፋት የተነሳ አንዳንዱ ከነበረበት ማህበረሰብና አካባቢ እየራቀ ሲመጣና በግለሰብ ደረጃ ሲኖር ግለሰብአዊነት እየተባለ መሰበክ ሲጀምር የመስገብገብና አልፎ አልፎም የመጠላላት ባህርይ ለመዳበር እንደቻለ እንመለከታለን። በሌላ አነጋገር፣ የሰው ልጅ ማህበራዊ ከሆነው የአኗኗር ልማዱና ከሚኖርበት አካባቢ እየራቀ ሲመጣ አንዳንዱ የመንፈስ ጭንቅት ውስጥ ሲገባ፣ ሌላው ደግሞ ወደ አልባሌ ስራዎች ላይ በመሰማራት የሚሆነውን የማይሆነውን ለመስራት ይችላል። ሌላው ትንሽ የማሰብ ኃይል ያለው ከሆነ ደግሞ እንደምንም ብሎ በመፍጨርጨር ራሱን ለማሸነፍና ወደ ተሻለ ደረጃም ሊደርስ የሚችል እንዳለ የተረጋገጠ ጉዳይ ነው።
ለማንኛውም ካፒታሊዝም በአፍላው ወቅት ሲስፋፋ ራሳቸው ካፒታሊስቶች የሚባሉት ስለህብረተሰብና ስለማህበረሰብ የጠለቀ ዕውቀት ስላልነበራቸው ገንዘብ በማግኘትና ትርፍ በማካባት ላይ በማትኮር ብዙ ነገሮችን ለማመሰቃቀል ችለዋል። ለዚህም ነው እንደሶሶዮሎጂና የስነ-ልቦና ሳይንስ የመሳሰሉት ዕውቀቶች በመፈጠርና በትምህርት መልክ በየዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በመሰጠት በህብረተሰብ ውስጥ የሚታዮ መመሰቃቀሎችና የስነ-ልቦና መቃወስ ዕርማት እንዲደረግባቸው ትግል ማድረግ የተጀመረው። ወደ እኛ አገር ስንመጣ ግን ይህ ዐይነቱን ህብረተሰብአዊ መመሰቃቀልና የስነ-ልቦና ቀውስና የባህል ውድመት ምክንያቶችን እየተከታተለ የሚያጠናና ለውይይትም የሚያቀርብ ግለሰብም ሆነ የተደራጀ ኃይል ባለመኖሩና በአገዛዙ ላይም ጫና ስለማይደረግ መንግስት የሚባለው አካል ተግባራዊ የሚያደርገው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ከፍተኛ ጉዳት ለማድረስ ችሏል። በተለይም የህወሃት አገዛዝ የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ የሚባለውን የዛሬ ሰላሳ አምስት ዓመት ተግባራዊ ማድረግ ከጀመረ ወዲህ በአገራችን ምድር እጅግ አስከፊ ክስተቶች ሊፈጠሩ ችለዋል። ማፊያዊ ተግባሮች ሊስፋፉ ችለዋል። ሙስናና ዝሙት፣ እንዲሁም በግልጽ መደረግ የሌለባቸው ነገሮች እየተደረጉ ድርጊቱ እንደኖርማል ሊወሰድ በቅቷል። በአንዳንድ የብልግና መድረኮች ላይ ወጣት ሴቶች ራቁታቸውን ሲደንሱ ይታዩ ነበር። በተለይም በገንዘብ እየናጠጠ የመጣው ከበርቴ መሳይ በዚህ ዐይነቱ የብልግና ትዕይንት የሚደሰትና የሚዝናና ነበር። ለአንዳንዱም ይህ ዐይነቱ ብልግና የዘመናዊነት መገለጫ መስሎ ይታየው ነበር። ሌሎች እንደ ገብረ-ሰዶማዊነት የመሳሰሉት አፀያፊ ነገሮችና በሴቶችና በልጆች ላይም የሚደርሱ ፆታዊ ጥቃቶች እየተስፋፉ የመጡት የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ መሆን ከጀመረና ግሎባላይዜሽንም ሰተት ብሎ ከገባ ወዲህ ነው። ይህም የአሜሪካኖች ፖሊሲ ሲሆን፣ በዚህ መልክ እያንዳንዱ ህብረተሰብ በመወብዝና አንዳንድ ግለሰቦችም የሚሰሩትን እንዳያውቁ በመደረግ ለማስተዳደር የሚያስችግር ሁኔታ መፈጠር አለበት። በዚህ መልክ አንድን አገር በሁሉም አቅጣጫ ማዳከም ሲቻል የጥሬ-ሀብቷንም በቀላሉ መበዝበዝና ወደ ውጭ ማስወጣት ይቻላል። ይህ ዐይነቱ ትንተና የኮንሲፒራሲ ቲዎሪ ሳይሆን በግልጽ የሚታይና በሶስዮሎጂና በስነ-ልቦና ሳይንስ ተመራማሪዎችና፣ እንዲሁም በተገለጸላቸው ኢኮኖሚስቶች ተጠንቶ የቀረበ ነው። በናኦሚ ክላይን የተደረሰውን „The Shock Doctrine” የሚለውን ግሩም መጽሀፍ መመልከትና ማረጋገጥ ይቻላል።
ለማንኛውም አብዮቱ ከከሸፈ በኋላ የመጣውን ሁኔታ ስንመለከት ቀስ በቀስ ወደ ማህበረሰብና ህብረተሰብ በመሽጋገር ላይ የነበረውን አገር ወደ ጎሳ ፌዴራሊዝም በመለወጥ አንዱ በሌላው ላይ እንዲነሳና፣ አንደኛው ብሄረሰብ ሌላውን እንዳያምን የተደረገበትን የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ ሁኔታ እንመለከታለን። በዚህ መልክ በአንዳች ዐይነት የፖለቲካና የሶስዮሎጂ ቲዎሪ በመመራትና መንፈስን በማነፅ አገርን በጋራ መገንባት በፍጹም እንዳይቻል የተደረገበት ሁኔታ ሊፈጠር ችሏል። ይህ ዐይነቱ አካሄድ የህብረተሰብንም ሆነ የተፈጥሮን ህግ የሚፃረርና፣ አንደኛው በሌላው ላይ በመመካትና በመተጋገዝ አንድ አገር በጋራ እንዳይገነባ የሚያደርግ አካሄድ ነው። በሌላ አነጋገር፣ አንዱ ሌላውን እየፈራና እየተጠራጠረ እንዲኖር የሚያደርግ አካሄድ ነው። ይህ ዐይነቱ ሁኔታ ደግሞ የተለያዩ ብሄረሰቦችን እንወክለዋልን፣ ጥቅሙንም እናስጠብቃለን ለሚሉት ኤሊት ነን ባዮች አመቺ ሁኔታን የከፈተና እነሱን ያደለበ ነው። ስለሆነም ይህ ዐይነቱ የተበላሸ አስተሳሰብና ከፖለቲካና ከሶስዮሎጂ ቲዎሪ ውጭ የሆነ የፖለቲካ አወቃቀር በተስፋፋበት አገር ውስጥ የየብሄረሰቡን ችግር ሊቀርፍ የሚያስችል ሁለ-ገብ የሆነ በትናንሽና በማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎች ላይ የተመረኮዘ የኢንዱስትሪና ሁለ-ገብ የሆነ የእርሻ ፖሊሲ መከተል አይቻልም። ማድረግ የተጀመረው ለውጭ ገበያ የሚያመች የፕላንቴሽን ኢኮኖሚ ላይ መረባረብ ነው። በተለይም ወጣት ሴቶችን አበባ ተካይ በማድረግ በተሻለ ሙያ ሰልጥነው ራሳቸውን እንዳይችሉና ሰው መሆናቸውን እንዳይገነዘቡ ኤሊቱ ከዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ጋር በመመሰጣጠር በደቡቡ የኢትዮጵያ ክፍል ኋላ-ቀርነትና ብዝበዛ እንዲስፋፋ ለማድረግ በቅቷል። ለምሳሌ በኦሮሚያ ክልል አበባዎችን እየተከሉና እየቆረጡ ኤክስፖርት ማድረግ ዋናው የኤሊቱ የገቢ ምንጭ ሆኖ ነበር ማለት ይቻላል። ይህ ዐይነቱ በሳይንስ ላይ ያልተደገፈ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አብዛኛውን የኦሮሞ ተወላጅ ነኝ የሚለውንና ሌላውንም ቀጭጮ እንዲቀር ያደረገ ነው። ለዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያት የዕውቀት ማነስ፣ በተለይም ሶስዮሎጂና የኢኮኖሚ ቲዎሪዎች ምን እንደሚመስሉና፣ አንድን አገርስ በምን ዐይነት የኢኮኖሚ ፖሊስ መገንባት ይቻላል? የሚለውን አስተሳሰብ ካለማወቅ የተነሳ ነው። በሌላ አነጋገር፣ በተለያየ አካባቢ የሚገኘውና የራሱን ህዝብ እወክለዋለሁ የሚለው ኤሊት በዓለም አቀፍ ተዋንያን ነን በሚሉ ኤክስፐርቶች እየተታለለ ህዝቡን ወደ ባርያ ስራነት እንደለወጠው እንገነዘባለን። ስለሆነም በአገራችን ምድር ጥንታዊ የፖለቲካና የሶስዮሎጂ መሳሪያዎች ለአገራችን መፍትሄ ሊሆኑ አልቻሉም የሚለው የዮናስ ብሩ አባባል ከተጨባጩ የአገራችን ሁኔታ ጋር የሚሄድ አይደለም። ምክንያትም ራሱ ኤሊት ነኝ የሚለውና ከዚኸኛው ወይም ከዚያኛው ብሄረሰብ የተውጣጣው በምን ዐይነት የፖለቲካና የሶስይሎጂ ቲዎሪና፣ በተለይም ደግሞ የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንደሚመራ ስለማያውቅ ነው።
በአሁኑ በአቢይ አህመድ የአገዛዝ ዘመን ያለንበትን ሁኔታ ስንመለከት ፖለቲካ ብለን ከጠራነው የዚያ ተቀጥያ የሆነና በጦፈ መልክ የሚካሄድ ነው። ይህ ዐይነቱ የፖለቲካ አካሄድ ደግሞ አንድን ሰው ማዕከል በማድረግና የብሄረሰብን ጥያቄ በተሳሳተ መልክ በመተርጎም ጥቂት ኤሊቶች የራሳቸውን ኤጎ ተግባራዊ የሚያደርጉበትን ሁኔታ እንመለከታለን። በህወሃት የአገዛዝ ዘመንም የነበረው ሁኔታ ይህን የሚመስል ነበር። ህወሃት በትግራይ ህዝብ ስም በመነገድና ጥቅሙንም ያስጠብቅ ይመስል ራሱን ከማደለብ አልፎ ለሰፊው የትግራይ ህዝብ የሰራው ጠቃሚ ነገር አልነበረም። ከሰማንያ በመቶ በላይ የሚሆነውን የትግራይ ብሄረሰብ ተወላጅ በንቃተ-ህሊናም ሆነ በማቴሪያላዊ ሁኔታ ከሌሎች ሻል ብሎ እንዲገኝ አላደረገውም። ትላልቅ ሆቴልቤቶችን ከመስራትና አንዳንድ ኢንዱስትሪዎችን ከመትከል ውጭ ሰፊውን ህዝብ ከድህነትና ከኋላ-ቀርነት ሊያውጣ የሚያስችለው ሁለ-ገብ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ ማድረግ አልቻለም። ባጭሩ ሰፊው የትግራይ ህዝብ እዚያው ቀጭጮ እንዲቀርና ራሱን ከሌላው ነጥሎ እንዲያይ ሊደረግ በቅቷል። በአሁኑ ወቅትም ያለው ሁኔታ ይህንን የሚመስል ሲሆን፣ በአጠቃላይ ሲታይ ጠቅላላውን ኢትዮጵያ በኦሮሞ የበላይነት በመሰልቀጥ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበረሰብአዊ ዕድገት እንዳይመጣና ጠቅላላው ህዝባችን እንዳይተሳሰር ከፍተኛ መሰናክል የፈጠረ አደገኛ አካሄድ በግልጽ ይታያል። ኃይል ወይም ጦርነት ዋነኛው መሳሪያ በመሆን ማንኛውም የህብረተሰብ ጥያቄ በፖለቲካ ውይይት እንዳይፈታ ለመደረግ በቅቷል። በሌላ አነጋገር፣ በዛሬው ወቅት በአቢይ አህመድና በሺመልስ አብዲሳ የሚመራው አገዛዝ በኃይልና በጦርነት ብቻ የሚያምን እንጂ በአርቆ-አሳቢነት በመመራት በፖለቲካ ቲዎሪና ፍልስፍና በመመራት የአገራችንን የተወሳሰቡ ችግሮች በውይይት፣ በክርክርና በጥናት ለመፍታት የሚችል አይደለም። ይህም የሚያረጋግጠው የወያኔም ሆነ የአሁኑ የአቢይ አህመድ አገዛዝ መንፈሳቸው የቀጨጨና የሚያደርጉትን የሚያውቁ አይደሉም ማለት ነው። በዝቅተኛ ስሜት በመመራትና ጥላቻን በማራገብ ሺህ ዓመት ይኖሩ ይመስል ከፍተኛ ህብረተሰብአዊ መመሰቃቀል ለመፍጠር ችለዋል፤ እየፈጠሩም ነው። የእነዚህ ዐይነት ሰዎችንም ጭንቅላት መግራትና እንደ ሰው እንዲያስቡ ለማድረግ በፍጹም ስለማይቻል ያለው አማራጭ ከስልጣን እንዲወገዱ ማድረግና በምንም ዐይነት ስልጣን አካባቢ ተመልሰው እንዳይመጡ መንገዱን ሁሉ መዝጋት ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን ብሄረሰብን ተገን አድርጎ የሚደረግ “ፖለቲካዊ እንቅስቃሴና ፓርቲ” መመስረት በህግ መከልከል አለበት። ፖለቲካ የአንድን ህብረተሰብ ችግር መፍቻና ታሪክን መስሪያ መሳሪያ እንደመሆኑ መጠን ብሄረሰብን ተገን አድርጎ የሚደረግ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለምሁራዊ እንቅስቃሴና ለአርቆ አሳቢነት መዳበር መሰናክል ይሆናል። ሳይንስና ቴክኖሎጂም እንዳይዳብሩና የኢኮኖሚው መሰረት እንዳይሆኑ ያግዳል።
በአጠቃላይ ሲታይ የወያኔም ሆነ የአቢይ አህመድ አገዛዝ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተዘረጋው የካፒታሊስት ወይም ኢምፔሪያሊስታዊ የአገዛዝ ስርዓት ውስጥ ተካተው በመግባትና አገልጋይ በመሆን በአገራችን ምድር ግለሰብአዊም ሆነ ህብረተሰብአዊ ነፃነት እንዳይመጣ ለማድረግ በቅተዋል። በሌላ አነጋገር፣ ሁለቱም አገዛዞች እንወክለዋለን የሚሉትን የብሄረሰባቸውን ጥቅም የሚያስቀድሙና የሚያስጠብቁ ሳይሆኑ የግሎባል ካፒታሊዝምን፣ በተለይም ደግሞ የአሜሪካን ካፒታሊዝምን ጥቅም የሚያስቀድሙ ናቸው ማለት ይቻላል። ለዚህ ማረጋገጫው ደግሞ በ1992 ዓ.ም ተግባራዊ የሆነው የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ዋናው ማረጋገጫ ሲሆን፣ ይህ ዐይነቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ደግሞ በማኑፋክቸሪንግ ላይ ለተመሰረተ የሁለ-ገብ የኢኮኖሚና የህብረተሰብ ዕድገት የሚያመች አይደለም። በዚህ መልክ በውጭ ኃይሎች ትዕዛዝ በህዝባችን ላይ የተጫነውና ጥቂቱን የህብረተሰብ ክፍል ሊያደልብ የቻለው የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ በአገራችን ምድር ለተስፋፋው ልዩ ዐይነት ብልግና፣ ሙስናና መካካድ፣ እንዲሁም ግድያ ዋናው ምክንያት ሊሆን ችሏል። ስለሆነም በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የሚመራው ግሎባል ካፒታሊዝም አመፅንና ብልግናን በዓለም አቀፍ ደረጃ በማስፋፋት፣ የከፋፍለህ-ግዛውን የፖለቲካ ፖሊሲ በመከተል በየአገሮች ውስጥ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል የሚጠቅም ሁለ-ገብ የኢኮኖሚና የህብረተሰብ ግንባታ እንዳይካሄድ ለማድረግ በቅቷል። አንድ ህብረተሰብና አገር የሚመሩበት መመሪያ ከሌላቸው ደግሞ ስማርት በሚመስሉ ዓለም አቀፋዊ ተዋንያን በመታለል ሀብታቸው እንዲበዘበዝ ይደረጋል፤ ህዝቦችም ለዝንተ-ዓለምም ተዋርደው እንዲኖሩ ይደረጋሉ። ከዚህ አጠር መጠን ያለ ሁኔታ ስንነሳ በአገራችንንም ሆነ በተቀሩት የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ያለው ሁኔታ ከዘመነ-ፊዩዳሊዝም የባሰና ወደ ጨለማው ዘመን የሚያመራ ነው ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል። በኳንተም ፊዚክስ አምናለሁ የሚለው ዶ/ር ዮናስ ብሩ እነዚህን የተወሳሰቡና የዓለምን ማህበረሰብ የሚያተራምሱ ሁኔታዎችን በሙሉ ጠጋ ብሎ ለማየት በፍጹም አልቻለም። አስተሳሰቡም በአሜሪካን የበላይነት እንዲያምን የታነፀ በመሆኑ የአንድን ህብረተሰብ ዕድል ከአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም አንፃር በመመልከትና በማያያዝ ነው ሊረዳና መፍትሄም ለመፈለግ ይቻላል ብሎ የሚያስበውና የሚያምነው ። ይህ ዐይነቱ ግንዛቤ ደግሞ የኢንላይተንሜንትን መንፈስንና የኳንተም ፊዚክስን መሰረተ-ሃሳቦች ይፃረራል። ለማንኛውም ይህንን ካልኩኝ በኋላ እሱ ወዳነሳውና እንደመፍትሄም ሊሆን ይችላል ብሎ ወዳቀረበው ሀተታ ደረጃ በደረጃ ልምጣ።
የፖለቲካንና የሶስዮሎጂ ቲዎሪም፣ እንዲሁም የኢኮኖሚክስና ሌሎች የተፈጥሮ ሳይንስ ቲዎሪዎችን አፀናነስ ጉዳይ ስንመለከት በመጀመሪያ ደረጃ በግሪክ፣ የኋላ ላይ ደግሞ ከ15ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ በጣሊያን ምድርና ቀጥሎም በኢንላይተንሜንት ዘመን በእንግሊዝና በተቀሩት የአውሮፓ አገሮች ቀስ በቀስ እየዳበሩ የመጡና ተቀባይነትም ያገኙ ናቸው ማለት ይቻላል።
በመጀመሪያ ደረጃ የፖለቲካ ቲዎሪን አፅናነስ ታሪክ ስንመለከት የተያያዘውም ከፍልስፍና ጋር ሲሆን፣ በጊዜው ለነበረው በፖለቲካ አካባቢ፣ በተለይም ጎሳ መልክ በመያዝ ይደረገ የነበረውን ጦርነትና ውዝግብ አስመልክቶ የተፈጠር አስተሳስብ ነው። ከሶክራተስና ከፕሌቶ በፊት የነበሩት ተመራማሪዎች “የተፈጥሮ ፈላሳፋዎች” የሚባሉት ዋናው ምርምራቸው በኮስሞስና እንዲሁም ደግሞ በቀጥታ የሚኖሩበትን ተፈጥሮን በመመራመርና ራሷ ተፈጥሮ ከምን ምን ነገሮች እንደተሰራችና፣ ምን ምን ነገሮችስ እንዳያያዟት ለመረዳት ነበር የሚደረገው ጥረት። እነሶክራተስና ፕሌቶ ብቅ ሲሉ በጊዜው በምድር ላይ ይታይ የነበረውን ህብረተሰብአዊ ችግር ለመረዳት መነሻ ያደረጉት የአዕምሮን ወይም የመንፈስን ጉዳይ ማዕከላዊ ቦታ በመስጠት ነበር። በሶክራተስም ሆነ በሶክራተስ ተማሪ በሆነው በፕሌቶ ዕምነት የሰው ልጅ ዋናው ችግር አርቆ አለማሰብ ነው። በሌላ አነጋገር፣ የሰው ልጅ አዕምሮ ወይም መንፈስ ቢኖረውም እነዚህን በተሟላ መልክ ስለማይጠቀም አስተሳሰቡና ድርጊቱ ሁሉ አርቆ-ባለማሰብ ላይ የተመሰረተ ነው የሚል ነው። ይህ ሊሆን የቻለው ደግሞ አብዛኛው የሰው ልጅ፣ በተለይም ስልጣንን የያዙ ሰዎች በተሳሳተ ዕውቀት ስለሚመሩና ራሳቸውን ወደ ውስጥ ለማየትና ጥያቄም ለመጠየቅ ስለማይችሉ ነው። ባጭሩ በደመ-ነፍስ ስለሚመሩ ነው። በተለይም ፕሌቶ ይህንን አስተሳሰብ ለሀብትና ለስልጣን መስገብገብ(Greed and Power) ብሎ ሲጠራው፣ በዚህ ዐይነት መንፈሱ የተጠመደ የፖለቲካ ኤሊትና ተከታዮቹ ከጥፋት በስተቀር ሌላ የሚያመጡት ነገር የለም። መንፈሳቸው ሀብትን በማግበስበስና ለስልጣን በመስገብገብ ስለሚጠመድ የፖለቲካ ስልታቸው ተንኮል ማውጠንጠን፣ አንዱን በማቅራብ፣ ሌላውን ደግሞ በማራቅና በጥርጣሬ በመመልከት የተመሰረተ ስለነበር ራሳቸው የሚፈጥሩትን ማንኛውንም ህብረተሰብአዊ ችግር በአመጽ ወይም በጦርነት ብቻ ለመፍታት የሚቻል ይመስላቸው ነበር።
በአጭሩ የመጀመሪያው የፖለቲካ ቲዎሪና ፍልስፍና በሶክራተስና በፕሌቶ፣ ቀጥሎም በአርስቲቶለስ የዳበረ ሲሆን፣ ሞራልን፣ ፍትሃዊነትንና አርቆ-አሳቢነትን ማዕከላዊ ያደረገና፣ ማንኛውንም የአንድ ህብረተሰብ ችግር በውይይት፣ በተለይም ዲያሌክቲካዊ በሆነ የጥያቄና የመልስ ዘዴ መፍታት ይቻላል ብሎ የሚያምን ነው። ለዚህ ዐይነቱ የፖለቲካ ሂደት ደግሞ ስልጣን ላይ የሚወጡትና የአንድን ህዝብ ወይም ህብረተሰብ ዕድል የሚወስኑ ሰዎች ጭንቅላታቸው በፍልስፍናና በልዩ ልዩ ዕውቀቶች የተኮተኮተና የተገነባ መሆን አለበት። ሰውነታችን ጥሩ ጥሩ ምግብና ጂምናስቲክ እንደሚያስፈልገው ሁሉ ጭንቅላትም የግዴታ በጥሩ ወይም በትክክለኛው ዕውቀት መኮትኮትና መታነፅ ሲገባው፣ ልክ እንደሰውነታችን የግዴታ ጂምናስቲክ ያስፈልገዋል የሚል ዕምነት ነበራቸው። በሌላ አነጋገር፣ ራስን መጠየቅ፣ ሌሎች ለጭንቅላት መጎልመስ የሚጠቅሙ ነገሮችን፣ ለምሳሌ እንደዮጋና ሜዲቴሽን የመሳሰሉትን በየቀኑ መስራት ራሳችንን እንድናውቅና በሌላው ላይ ጉዳት እንዳናደርስ ያደርጉናል። ይህ ሲሆን ብቻ ነው በአንድ አገር ውስጥ የሰለጠነና ህዝብን የሚያረጋጋ፣ እንዲሁም እያንዳንዱ ዜጋ በራሱ እንዲተማመንና ፈጣሪ የሚያደረገው ታሪካዊ ስራን መስራት የሚቻለው።
በአጠቃላይ ሲታይ በግሪክ ዘመን አገርን በስነስርዓት ለመገንባትና ህብረተሰቡንም ለማያያዝ ትላልቅ የቲያትር የመሰብሰቢያ ቦታዎች መገንባት፣ የተለያዩ የስፖርት ዐይነቶችን መፍጠርና ህዝቡ እንዲሳተፍ ማድረግ ሁለተኛው ዘዴ ነበር። ለምሳሌ ኦሎምፒክ የሚባለውና ብዙ የስፖርት ዐይነት ተሳትፎ የሚደረግበት ትዕይንት ከዚያ በዚያን ግዘመን የፈለቀና የተወሰደ ሲሆን እስካሁንም የሚሰራበት ነው። በግሪክ ፈላስፋዎች ዕምነት የሰው ልጅ ጭንቅላት ጥበባዊ በሆነ መልክ እንዲገነባ ከተፈለገ አካባቢውም ጥበባዊ በሆነ መልክና መንፈስን እንዳይረብሹ ሆነው መገንባት አለባቸው። የመጀመሪያው በዕቅድ መልክ የተገነባው ከተማና የጋርደን አስተሳሰብ በግሪክ ፈላስፋዎችና በአርክቴክተሮች የተፈጠረ ሲሆን፣ ዓላማውም የሰውን ልጅ ከአውሬነት ባህርይው እንዲላቀቅ በማድረግ በመፈቃቀር እንደማህበረስብ ሊኖር የሚችልበትን ሁኔታ ማደራጀት ነበር። በግሪክ የስልጣኔ ዘመን ከፍልስፍና፣ ከተፈጥሮ ሳይንስ፣ አንትሮፖሎጂና ከፖለቲካ ቲዎሪ በስተቀር እንደ ኢኮኖሚክስና የሶስዮሎጂ ቲዎሪዎች አይታወቁም ነበር። ይሁንና ግን ሶክራተስ፣ ፕሌቶና አርስቲቶለስ አንድ ህብረተሰብ ከላይ ከተጠቀሱት ነገሮች ባሻገር በስራ-ክፍፍልና(Division of Labour) በንግድ መያያዝ እንዳለበት የሚያምኑ ነበሩ። ገንዘብ ለዕቃዎች መገበያያ ዋናው መሳሪያ እንደሆነም ከፍተኛ ግንዛቤ ነበራቸው። ይህም ማለት ማንኛውም ህብረተሰብ በአንድ ተቀባይነት በሚኖረውና የሁሉም ዕቃዎች ማዕከል በሆነ ገንዘብ ተብሎ በሚጠራ መተመንና የመገበያያም መሳሪያ መሆን እንዳለበት ያምኑ ነበር። ይሁንና ግን የሰው ልጅ በገንዘብ እንደሚታለልና ሞራሉም ሊላላ እንደሚችል ያውቁ ነበር። ስለሆነም የሰው ልጅ በማቴሪያላዊ ነገሮች መታለል እንደሌለበት ሶክራተስ፣ ፕሌቶና አርስቲቶለስ፣ እንዲሁም ኋላ ላይ የተነሱት ስቶይክስ የሚባሉት ፈላስፋዎች በሚገባ ያስተምሩ ነበር።
የግሪክ ስልጣኔ ከፈረሰና ሮማውያን ስልጣንን ከተቀዳጁ በኋላ አንዳንድ የሮማውያን መሪዎችና ፈላስፋዎች በመንፈስ የበላይነት ቢያምኑም በመሀከላቸው ባለው የስልጣን ሽኩቻና፣ በአጠቃላይ ሲታይ የመስፋፋት ፖሊሲ ምክንያት የተነሳ እያበጠና እየተስፋፋው የመጣው የሮማውያን ኢምፓዬር በብዙ የአውሮፓ አገሮች ከተማዎችንንና የካናል ሲስተሞችን ቢገነባም የኋላ ኋላ ላይ ኃይሉ እየተሟጠጠ በመምጣት በምትኩ የጨለማው ዘመን ሊመጣ ችሏል። በተለይም የካቶሊክ ኃይማኖት መሪዎችና ፊዩዳሎች የፖለቲካውን መድረክ በመቆጣጠር ከካቶሊክ አስተሳሰብ ውጭ ማስብና ማመን በፍጹም አይቻልም ነበር። ይህ ዐይነቱ ፖለቲካዊና ሳይንሳዊ አስተሳሰብን ያፈነው የካቶሊክና የፊዩዳሎች አስተሳሰብ ለምርትና ለንግድ እንቅስቃሴ እንቅፋት በመሆን በቁጥር እየጨመረ የመጣውን ህዝብ የሚመግብና በተለያዩ ሙያዎች የሚያሳትፍ የስራ መስክ ባለመኖሩ በአውሮፓ ምድር ረሃብና የተስቦ በሽታ የተስፋፋ ነበር። በተለይም በተስቦ በሽታ የተነሳ የጥቁር ሞት(Black Death) እየተባለ በሚጠራው በሽታ በአንዳንድ የአውሮፓ “ከተማዎች” ሁለት ሶስተኛው የሚሆነው ህዝብ እንዲያልቅ ወይም እንዲሞት ተድርጓል። ይህንን የተገነዘቡ አንዳንድ ምሁራን፣ በተለይም እነ ዳንቴ የመሳሰሉት ምሁራን የግሪክን ዕውቀት በመተርጎምና ከጊዜው ጋር እንዲስማማ በማድረግ በተለይም በጣሊያን ምድር የመጀመሪያው በዕውቀት ላይ የተመሰረተ እንቅስቃሴ እንዲነሳና እንዲስፋፋ ለማድረግ ተችሏል። ይህ ዐይነቱ የመንፈስ ተሃድሶ እንቅስቃሴ ውብ ውብ ለሆኑ ህንፃዎች ግንባታ፣ ለዕደ-ጥበብ፣ ለንግድ እንቅስቃሴ፣ ለስዕልና ለስክሌፕቸር፣ የኋላ ኋላ ደግሞ ለተፈጥሮ ሳይንስ መዳበር መንገዱን ያመቻቸ ነበር ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል። ዳቪንቺ፣ ሚቼል አንጄሎና ጋሊሌዬና ሌሎችም የተፈጥሮ ሳይንስ፣ የፍልስፍናና የማቲማቲክስ ተመራማሪዎች የሬናሳንስ እንቅስቃሴ ውጤቶች ናቸው ማለት ይቻላል። ይህም የሚያረጋግጠው ቆንጆ ቆንጆ ነገሮች በሚሰሩበት አካባቢ ወይም ከተማ ውስጥ የሰው ልጅ ጭንቅላትም የመፍጠር ኃይሉ ሊዳብር እንደሚችል ነው። ከስግብግብነትና በማቴሪያል ቀድሞ ከመገኘት ይልቅ መንፈሱን በማነጽና የመንፈስን የበላይነት መመሪያ በማድረግ ለሰው ልጅ የሚጠቅሙ ዘላቂነት የሚኖራቸውን ነገሮች ሊፈጥር ይችላል ማለት ነው።
ከዚያ በኋላ የተፈጠረው የፖለቲካ፣ በተለይም በኤንላይተንሜንት ላይ የተመሰረተው ልዩ ልዩ ዕውቀትና እንቅስቃሴ ጊዜው ያስገደደውና፣ የአንድ አገርና ህዝብ ዕድል በጥቂት ሰዎች የበላይነት መወሰን የለበትም ብለው በተነሱና ጭንቅላታቸውን በማስጨነቅ ልዩ ልዩ ዕውቀቶችን ባፈለቁና ባዳበሩ ጥቂት ምሁራን አማካይነት ነው። ይህ ዐይነቱ ሰፋ ያለና በጭንቅላት ላይ ያተኮረ እንቅስቃሴ ከሌሎች ነገሮች ጋር በመዳበል ዲስፖታዊ አገዛዞችን መፈናፈኛ ያሳጣ ነበር። በዚህም ምክንያት የተነሳ በድሮው መልክ ለመቀጠል በሚፈልጉና መንፈሳቸውን ክፍት በማድረግ በሊበራሊዝምና በህግ-የበላይነት መመራት አለብን በሚሉ ኃይሎች መሀከል ብዙ ጦርነቶች ተካሂደዋል። ይህም ማለት እነማርክስና ኤንግልስ ከመነሳታቸውና ስለአብዮትና ስለሶሻሊዝም አስተሳሰብ ከመስበካቸው በፊት በጦርነት ላይ የተመረኮዘ የከበርቴው አብዮት ተካሂዷል። በተለይም በእንግሊዝ አገር ከሃያ ዐመት በላይ የፈጀው የርስ በርስ ጦርነት የሚያረጋግጠው የኋላ-ቀርነት አስተሳሰብን በሚያራምዱና፣ የለም በኋላ-ቀር አስተሳሰብ መገዛት የለብንም፣ የጊዜው መንፈስም መገለጽና(Enlightenment) የህግ የበላይነት መስፈን አለባቸው ብለው በሚታገሉ ሁለት ተፃራሪ ኃይሎች መሀከል ነበር። ከዚህ ዐይነቱ እንቅስቃሴ በኋላና የፖለቲካው መድረክም ክፍት እየሆነ መምጣት ከጀመረና ህዝቡም በየፊናው ተፍ ተፍ ማለት ሲጀምር ይህንን ጠጋ ብለው የተመለከቱና የተመራመሩ እንደነ አዳም ስሚዝ የመሳሰሉ የሞራል ፈላስፋና የኢኮኖሚ ምሁር አማካይነት The Wealth of Nations የሚባለው የኢኮኖሚ መመሪያ የሆነ ሊጻፍና ተቀባይነትም ሊያገኝ ቻለ። በአዳም ስሚዝ ዕምነትም፣ በትክክል በአንድ አገር ውስጥ ህዝባዊ ሀብት(National Wealth) ሊዳብር የሚችለው የስራ-ክፍፍል ሲኖር ብቻ ነው። የተለያዩ ባለሙያዎች የተለያዩ ነገሮችን ሲያመርቱ ይህ ዐይነቱ የልዩ ልዩ ነገሮች መመረትና በገበያ ላይ መቅረብ ለንግድ እንቅስቃሴና ለገንዘብ መዳበር አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል። ለስራ-ክፍፍል መዳበር ደግሞ ዋናው መሰረት ማኑፋክቸሪንግ ሲሆን፣ በዚህ አማካይነት ገበያው የመስፋትና የማደግ ኃይል ይኖረዋል። በሌላ አነጋገር፣ የስራ-ክፍፍል ባልዳበረብት፣ ማኑፋክቸሪንግ በሌለበትና ገበያ በክልል ወይም በወረዳ ደረጃ በሚካሄድበት አገር ውስጥ ነፃ ገበያን ማዳበር በፍጹም አይቻልም። በአዳም ስሚዝም ሆነ በሌሎች የክላሲካል ወይም ጥንታዊ ኢኮኖሚስቶች ዕምነት የተቋማት ግንባታ፣ የመንገድና የካናላይዜሽን ስራ በመንግስት ትከሻ ላይ የሚወድቁ መሆን አለባቸው። ከዚህም በተጨማሪ የአንድ መንግስት ዋናው ተግባር በአገሩ ውስጥ ሰላምን ማስፈንና ሰፊው ህዝብ አመኔታ እንዲኖረው ማድረግ ነው። ይህም ማለት ፀጥታ በጎደለበትና መንግስት ወይም አንድ አገዛዝ ወደ ዘራፊነት በተሸጋገረብት አገር ውስጥ የነፃ ገበያ የሚባለውን ማዳበር በፍጹም አይቻልም ማለት ነው። ፈጣሪነት፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂም ብቅ ሊሉና ሊዳብሩ በፍጹም አይችሉም። መንግስት የሚባለው አገዛዝ ተራ ዘራፊ ከሆነና ተግባሩም በየቦታው ጦርነትን መቀስቀስ ከሆነ ይህ ዐይነቱ አስተሳሰብና ድርጊት አንድን ህብረተሰብ እንዳለ ያናጋል። በተለይም ደካማው ህዝብ እንዲጠቃ ይደረጋል። ዛሬ በአገራችን ምድር የምናየው ይህንን ሀቅ ነው። ልቅ የሆነ በኦሮሞ ኤሊቶች የሚካሄድ ዘራፊነትና ለወጭ ኃይሎች ተገዢ በመሆን ስልጣን ላይ ብቻ ለመቆየት ሲባል አገርን በሁሉም አቅጣጫ ማፈራረስና አናርክሲዝምን ማስፋፋት የሚያረጋግጠው የጭንቅላትን ወይም የአዕምሮን መቀጨጭ ነው። ሰሞኑን ሺመልስ አብዲሳ ራሱ በሚያስተዳድረው ክልል ውስጥ ምንም ዐይነት ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንደሌለና ሁኔታውንም ለመቆጣጠር እንዳልቻለ አምኗል። በሌላ ወገን ግን ሺመልስ አብዲሳና የተቀረው የኦሮሞ ኤሌት ነን ባዮች ሊገባቸው ያልቻለው ጉዳይ ይህ ዐይነቱ አናርክሲዝም በራሳቸው እንደተፈጠረ ነው። የሰላም እጦትና የኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ መዳከም የጭንቅላታቸው መቀጨጭ ውጤት መሆኑን በፍጹም አልገባቸውም። በአንድ ክልል ወይም አገር ውስጥ ለማስተዳደር የሚያስቸግር ሁኔታ የሚፈጠረው ራሱ አገዛዙ የማሰብ ኃይሉ በጣም ደካማ ከሆነና ለኢኮኖሚና ለሌሎች ህብረተሰቡን ለማያያዝ ለሚችሉ ልዩ ልዩ እንቅስቃሴዎች አመቺ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ያልቻለ እንደሆነ ብቻ ነው። በዚህም ምክንያት የተነሳ አንዳንድ ታዳጊ ወጣቶች መንፈሳቸው በተሳከረና በተደራጁ ኃይሎች ይገደላሉ። ሌብነትና ቀማኛነት ሊስፋፉ ችለዋል። ጦርነት የአገዛዙ ዋና ፍልስፍና በመሆን በማኑፋክቸሪንግ፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ ከተመሰረተ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ይልቅ ውንብድናና ቀማኛነት ተስፋፍተዋል። በአጭሩ ያለንበት ዘመን 21ኛው ክፍለ-ዘመን ሳይሆን በማዕከለኛው ክፍለ-ዘመን ያለን የሚመስል ነው።
አዳም ስሚዝና ተከታዮቹ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴንና ዕድገትን እንደ ተፈጥሮአዊ ህግ አድርገው ቢመለከቱትምና፣ በተለይም የነፃ ንግድን አስፈላጊነት ቢሰብኩም፣ ይህ ማለት ግን በሁሉም የአውሮፓ አገሮችና ምሁራን ዘንድ አስተሳሰባቸው ሙሉ በሙሉ ተቀባይነትን ሊያገኝ አልቻለም። ምክንያቱም የአዳም ስሚዝ አቀራረብ በጣም ተምኔታዊ ወይም አይዲያሊስት የሆነ አቀራረብ ሲሆን፣ የካፒታሊዝምን የውጣ ውረድ ጉዞና አብዛኛውን ጊዜ ሳይታወቅ ለካፒታሊዝም ዕድገት መነሻ የሆኑ በተለይም የመንፈስን ተሃድሶ አስፈላጊነትን ለማተት ባለመቻሉ ነው። ሌላው የአዳም ስሚዝ ስህተት ቀደም ብሎ በመንግስታት ወይም በፍጹም ሞናርኪስቶች አማካይነት በአንዳንድ የአውሮፓ አገሮች ውስጥ ሁለ-ገብ ዕድገት እንዲመጣ ተግባራዊ ያደረጓቸውን ኢኮኖሚያዊ ዕርምጃዎችን በቁጥር ውስጥ አላስገባም። ስለነፃ ንግድ አስፈላጊነት ሲያወራ፣ በሌላው ወገን ግን ከእንግሊዝ ጋር ሲወዳደሩ ወደ ኋላ የቀሩ የምዕራብ አውሮፓ አገሮች በማደግ ላይ ያሉ ኢንዱስትሪዎቻቸውን ከውጭ በሚመጣ ተመሳሳይ ምርት እንዳይመቱ መውሰድ የሚገባቸውን የዕገዳ ዕርምጃ ፖሊሲዎች አስፈላጊ መሆናቸውን አልተገነዘበም። እንዲያውም የዕገዳ ፖሊሲ(Protectionism) ለነፃ ገበያና ለኢኮኖሚ ዕድገት ጠንቅ እንደሆነ አድርጎ ነው የተረዳው። ይህም የሚያረጋግጠው አዳም ስሚዝ የኢኮኖሚ ጽሁፉን ሲጽፍ ከእንግሊዝ ሁኔታ በመነሳት እንጂ የሌሎች አገሮችን ተጨባጭ ሁኔታ በማንበብና በማገናዘብ አልነበረም። ለምሳሌ እያንዳንዱ አገር የተጓዘበትን የታሪክ ጉዞ፣ የባህልን ዕድገት ጉዳይና፣ የመንፍሰ ተሃድሶ ተደርጎ ወይም አልተደረገ እንደሆነና፣ በተለያዩ አገሮች ውስጥ የሰፈነውን የመንግስት አወቃቀርና፣ ይህ ዐይነቱ ሁኔታ ለሁለ-ገብ የኢኮኖሚ ዕድገት ጠንቅ መሆኑን ወይም አለመሆኑን ግንዛቤ ውስጥ አላስገባም። በእሱ ዕምነት እያንዳንዱ አገር በሩን ቢከፍትና የንግድ ልውውጥ ቢያደረግ ባህላዊ ለውጥም ሊያመጣ ይችላል የሚል ግምት ነበረው። ይሁንና ግን የነፃ ገበያና የንግድ ልውውጥ እንደታሰበው በየአገሮች ውስጥ ስር-ነቀል ለውጥ በማምጣት ለሁለ-ገብ የኢኮኖሚ ዕድገት አመቺ ሁኔታን ለመፍጠር አልቻለም። ይባስ ብሎ አንድ የዕድገት ደረጃ ላይ ሳይደርሱና የሰለጠነ መንግስታዊ መዋቅር ሳይገነቡ በነፃ ንግድ ውስጥ የተሳተፉ ወይም በራቸውን ለውጭ ዕቃ ክፍት ያደረጉ አገሮች ከፍተኛ የባህል ውድመትን ሊጎናፀፋ ችለዋል። ይህ ብቻ ሳይሆን ወደ ውስጥ ያተኮረ ሰፋ ያለ ኢኮኖሚ እንዳይገነቡና ጥሬ-ሀብት አምራች ብቻ ሆነው እንዲቀሩ ተገደዋል።
ሌላው ስሚዝ ያላገናዘበው ነገር እንግሊዝ ወደ ኢንዱስትሪ አብዮት ልትሸጋገርና በኢኮኖሚ ዕድገት የበላይነትን ለመቀዳጀት የቻለችው በተለያዩ ጊዜያት የነበሩ አገዛዞች የዕገዳ ፖሊሲን(Protectionst Measure) ተግባራዊ በማድረጋቸው የተነሳ ነው። በዚህም ምክንያት የተነሳ ነው ቀስ በቀስ ወደ ውስጥ የግለሰብ ታታሪነት ሊዳብር የቻለው። ይህንን አስመልክቶ በጀርመን አገር በ19ኛው ክፍለ-ዘመን በነበሩ የኢኮኖሚ ዕድገት ታሪክ ተማሪዎች(Historical School) ተብለው በሚጠሩት ዕምነት አንድ አገር ገበያዋን ከውጭ ለሚመጣ ዕቃ ልቅ ከማድረጓ በፊት በሁሉም አቅጣጫ በማኑፋክቸሪንግ ላይ የተመሰረተ የውስጥ ገበያ ማስፋፋትና ማዳበር አለባት። የጠነከረና ህዝቡን የሚያስተሳሰር መንግስት መገንባት አለባት። ልዩ ልዩ ተቋማት በየቦታው መገንባት አለባቸው። ለኢኮኖሚ ዕድገት የሚያመቹ ከተማዎች በስነ-ስርዓት መሰራት አለባቸው። እነዚህም በተለይም በጊዜውና አሁንም ቢሆን በባቡር ሃዲድ መያያዝ አለባቸው። ከዚህ በተረፈ የኢኮኖሚው ዋና ሞተር ማኑፋክቸሪንግ፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ መሆን አለባቸው። በዚህ መሰረት አንድ አገር ቀስ በቀስ ግን ደግሞ በእርግጠኝነት በሁሉም አቅጣጫ ከተገነባች በኋላ ኢኮኖሚዋን ከውጭ ለሚመጣ ዕቃ ክፍት ማድረግ ትችላለች። ይህንን ዐይነቱን ታሪክን ቁጥር ውስጥ ያስገባና የሰለጠነ መንግስት መኖር አስፈላጊነትን የሚያሰምር የኢኮኖሚ ፖሊሲ አሜሪካን በእነ አብርሃም ሊንከንና በእነ ሃሚልተን ዘመን የተከተለችው ስትራቴጂ ነው። በ19ኛው ክፍለ-ዘመን የነበረው ታዋቂው የኢኮኖሚክ ታሪክ ተመራማሪ ፍሪድሪሽ ሊስት የሚባለው አሜሪካ ድረስ በመጓዛና ከእነ ሃሚልተን ጋር ሃሳብ ለሃሳብ በመለዋወጥ ተመሳሳይ ግንዛቤ ላይ ለመድረስ ችለዋል። አንድ አገር ልዩ ዐይነት የክሬዲት ሲይስተም በመፍጠር ለባቡር ሃዲድ ግንባታና ለማኑፋክቸሪንግ ማበብ ቅድሚያ መስጠት እንዳለባት ስምምነት ላይ ደርሰዋል። ይህም ዕቅዳቸው የእንግሊዝን የነፃ ንግድ ዶክትሪን የሚቃወም ነበር። ፍሪድሪሽ ሊስትም ከአሜሪካ ጉዞው ሲመለስ ከሌሎች ተመሳሳይ አስተሳሰብ ካላቸው ጓደኞቹ ጋር በመገናኘትና በመንግስት ላይ ከፍተኛ ግፊት በማድረግ በጊዜው የነበረው የጀርመን አገዛዝ ለኢንዱስትሪ አብዮት የሚያመች የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ ለማድረግ ችሏል። ሌላው የአዳም ስሚዝ ትልቁ ስህተት ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ቆሞ እንደሚቀር(Static) ወይም ውስጣዊ ኃይል እንደሌለው አድርጎ ነው የተመለከተው። ለምሳሌ ካርል ማርክስ ሰለካፒታሊዝም ውስጣዊ ህግ፣ እንቅስቃሴና ዕድገት በሶስት ቅፅ መጽሀፎቹ ውስጥ ሲያትት ካፒታሊዝም ከተራ የምርታ ምርት እንቅስቃሴ በመነሳት ወደ ሞኖፖሊ ካፒታሊዝም እንደሚሸጋገርና ዓለም አቀፋዊ ባህርይም እንደሚይዝ ለማስረዳት ሞክሯል። በተለይም ገንዘብ ራሱ ልዩ ዐይነት ሚናን በመውሰድና ወደ ፊናንስ ካፒታል በመለወጥ በባንኮችና በኢንዱስትሪዎች መሀከል በሚደረግ የተወሳሰበ ግኑኝነት ወደ ካፒታል የተለወጠው ገንዘብ ለካፒታሊዝም በፍጥነት ማደግ አመቺ ሁኔታን እንደፈጠረና ሊፈጥር እንደሚችል በሰፊው አትቷል። በሌላ አነጋገር፣ አዳም ስሚዝ የገበያ ኢኮኖሚን በትናንሽ አምራች ኃይሎች ብቻ ተወስኖ እንደሚቀር ነው የተመለከተው። በጊዜው በትናንሽ አምራች ኃይሎች ላይ የተመሰረተው ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እያደገ በመምጣትና ከባንኮች ጋር በመቆላለፍ ወደ ሞኖፖሊ ካፒታሊዝም ሊሸጋገር እንደሚችል ቀድሞ ለመመልከት አልቻለም። ይሁንና ግን በአዳም ስሚዝና በማርክስ መሀከል ያለው ስምምነት የዋጋ ዋናው ምንጭ የጉልበት ስራ(Labour is the Source of Value) የሚለው አስተሳሰብ ነው። በዚህም ምክንያት የተነሳ የሰው ጉልበት፣ የማሰብ ኃይልና ከተፈጥሮ ውስጥ የሚገኝ ሀብትና በማሰብ ኃይል አማካይነት በኢንዱስትሪ ምርታዊ ክንዋኔ ወደ ፍጆታ ዕቃ የሚለወጠው አንድ ላይ በመሆን ለህዝባዊ ሀብት(National Wealth) መፈጠር ዋና መሰረቶች ወይም ምንጮች ይሆናሉ። በሌላ አነጋገር፣ የአንድ ዕቃ ዋጋ የሚተመነው በአቅራቢና በጠያቂ ህግ(The Law of Supply & Demand) መሰረት ሳይሆን በሰው የስራ-ጉልበት ብቻ ነው።
በአጭሩ የተለያዩ የኢኮኖሚ ቲዎሪዎችንና ከታሪካዊ ሂደት ጋር በመጣመር የተጻፉ መጽሀፎችን በምናነብበት ጊዜ ዛሬ የነፃ ገበያ እየተባለ የሚወደሰውና የዓለምን ህዝብ የሚያተራምሰው፣ በተለይም ካለምንም ትችታዊ ወይም ሂሳዊ አመለካከት እንደመጽሀፍ ቅዱስ የተወሰደው አስተሳሰብ ብዙ ውጣ ውረድን አሳልፎና ህዝብን ከውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ በማመሰቃቀልና ከቀዬው በማፈናቀል እዚህ ዐይነቱ የተወሳሰበ የዕድገት ደረጃ ላይ ሊደርስ የቻለ መሆኑን ግንዛቤ የለም። ይህ ብቻ ሳይሆን ካፒታሊዝም እዚህ ዐይነቱ የዕድገት ደረጃ ላይ ሊደርስ የቻለው በተለይም አፍሪቃንና የደቡብ አሜሪካ አገሮችን የጥሬ-ሀብት አምራች ሆነው እንዲቀሩ በተመሰጣጠረ መልክ በማስገደዱ ነው። ለዚህ ደግሞ በአዳም ስሚዝና በዴቪድ ሪካርዶ የረቀቀው ዓለም አቀፋዊ የስራ ክፍፍል(International Division of Labour) ዐይነተኛ መሳሪያ ነው። በየዩኒቨርሲቲዎችም ውስጥ ካለምንም ትችታዊ ወይም ሂሳዊ አመለካከት ለዕድገት ዋናው አንቅሳቃሽ ኃይል እንደሆነ ተማሪዎች እንዲማሩት ይደረጋሉ። በዚህ ቲዎሪ መሰረት አንድ አገር ሪሶርስስ ወይም የጥሬ-ሀብት ካለው፣ መሬቱና አየሩ የተለያዩ ፍራፍሬዎችን ለማብቀል የሚያመች ከሆነና፣ በዚህ ላይ ብቻ ካተኮረ፣ ካፒታል ወይም ቴክኖሎጂ ያለው ደግሞ በዚያው ላይ ከገፋበት፣ በሁለቱ አገሮች፣ በአጠቃላይ ሲታይ በተለያዩ አገሮች መሀከል በሚደረገው የንግድ ልውውጥ የመጨረሻ መጨረሻ ሁሉም አገሮች ተጠቃሚ ይሆናሉ ይለናል። ይሁንና ግን ይህ ቲዎሪ በተግባር ሲታይ የጥሬ ሀብታቸውን እያወጡ ሳይፈበርኩና ለፍጆታ ወይም ለመጨረሻ ጠቀሚታ እንዲሆን አድርገው የማያቀርቡ አገሮች ወደ ውስጥ ያተኮረ የውስጥ ገበያን(Home Market) ለማሳደግ እንደማይችሉ ነው። በጥሬ-ሀብት ማውጣትና ኤክስፖርት በማድረግ ብቻ የሰለጠኑ አገሮች ደረጃ በደረጃ ሊካሄድና ርስ በርሱ ሊያያዝ የሚችል(Value added chain) የምርት ክንዋኔ እንዳያዳብሩ ይገደዳሉ።። በዚህም ምክንያት የተነሳ በማኑፋክቸሪንግ፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴና ዕድገት ተግባራዊ እንዳይሆን ከመጀመሪያውኑ ይታገዳል። በዘመነ ግሎባላይዜሽን የተፈጠረው ሌላው የሶስተኛው ዓለም አገሮችን የማቀጨጭ ፖሊሲ፣ ለምሳሌ የመዋቅር ማስተካከያ(Structural Adjustment Program) ተሳቦ ተግባራዊ የሚሆነው የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ በአፍሪካ አገሮች ውስጥ የተስተካከለና ለሰፊው ህዝብ የስራ መስክ ሊከፍት የማይችል ሰፋ ያለ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴና ዕድገት እንዳይመጣ የሚያግድ ነው። በዕዳ በመተብተብና የወለድ ወለድ ከፋይ እንዲሆኑ በማድረግ አገሮችን እዚያው ቀጭጨው እንዲቀሩ የሚያደርግ አደገኛ ፖሊሲ ነው። በተለይም አንድ አገር ገንዘቧን ከዶላር ጋር ሲነፃፀር ዝቅ(Devaluation) ማድረግ አለባት የሚለው ሳይንሳዊ መሰረት የሌለውና፣ ራሳቸው የካፒታሊስት አገሮችም በኢኮኖሚ ዕድገት ታሪካቸው ውስጥ ተግባራዊ ያላደረጉት ነገር ነው። አብዛኛዎቹ የካፒታሊስት አገሮች የየራሳቸውን ገንዘብ በማተም፣ ማዕከላዊ ባንክ በመፍጠርና፣ በተለይም ልዩ ዐይነት የክሬዲት ሲስተም በመፍጠር ነው በማኑፋክቸሪንግ ላይ የተመሰረተ የውስጥ ገበያን ለማዳበር የቻሉት። አንድም አገር ከውጭ በመበደርና ሌላውን በመተማመን ካፒታሊዝምን አልገነባም። ይህም የሚያረጋግጠው የመጀመሪያ መጀመሪያ በአንድ አገር ውስጥ የተስተካከለ ዕድገት ሊመታ የሚችለው በራስ በመተማመንና ጭንቅላትን በመጠቀም ነው። ለማንኛውም እንደኛ አገር በመሰለው ተግባራዊ የሚሆነው የገንዘብ ቅነሳ ለዕድገት የሚያመች አይደለም። በገንዘብ ቅነሳው(Devaluation) የተነሳም የገንዘቡ የመግዛት ኃይል ስለተዳከመና ስለሚዳከም በተለይም ሰፊው ተጠቃሚ ህዝብ እንዲጎዳ ለመደረግ በቅቷል። ይህ ዐይነቱ የገንዘብ ቅነሳም ለጥቁር ገበያ መስፋፋት አመቺ ሁኔታን በመፍጠር የማዕከላዊ ባንክና የንግድ ባንኮች ውስጥ ሊገባ የሚችለውን የውጭ ምንዛሪ፣ ማለትም ዶላርንና ኦይሮን በመሻማት ጤናማ ለሆነ የኢኮኖሚ ዕድገት አመቺ ሁኔታ እንዳይፈጠር አድርጓል። የሚያሳዝነው ነግር ግን የገንዘብ ቅነሳንና ብድርን እንደፈሊጥ አድርጎ መውሰዱና፣ እነዚህ ነገሮች ወደፊት እንድንራመድ ለማድረግ እንዳልቻሉ ፖሊሲ አውጭዎቻችን ለመገንዘብ አለመቻላቸው ነው።
የመዋቅር ማስተካከያ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የሚባለው ነገር በመሰረቱ ኢ-ሳይንሳዊና የእየአንዳንዱን አገር ሁኔታ ሰፋ ባለ መልክ ሳይጠና የማክሮ-ኢኮኖሚ መዛባት አለ በሚል በተለይም በተወሰነና ሰፊውን ህዝብ በማይመለከት “የማክሮ-ኢኮኖሚ ፖሊሲ መሳሪያዎች” ብለው በሚጠሯቸው ላይ ብቻ በማትኮር ተግባራዊ እንዲሆን የተደረገው ፖሊሲ በሁሉም መስኮች ዘንድ መዛባት እንዲፈጠር አድርጓል። በከፍተኛ ደረጃ የንግድ ሚዛኑ ተዛብቷል። የውጭው ዕዳ እየተቆለለ ሊመጣ ችሏል። አንድ አገር ደግሞ በየጊዜው ዕዳውን ለመክፈል ካልቻለች በቀላሉ ሌላ ብድር ማግኘት አትችልም። ሌላ ብድር ማግኘት ከፈለገች ደግሞ የግዴታ የዓለም የገንዘብ ድርጅትን ቅድመ-ሁኔታ ማሟላት አለባት። ይህም ማለት በተከታታይ ገነዘቧን ከዶላር ጋር ሲነፃፀር መቀነስ አለባት። ይህ በራሱ የውጭ ዕዳዋ እንዲያድግና የወለድ ወለድ(Compound Interest) ከፋይ እንድትሆን ያደርጋታል፡፡ በአጭሩ የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት የተቋም ማስተካከያ ፖሊሲ አንድ አገር እዚያው በዚያ እየተንደፋደፍች እንድትሰቃይ የሚያደርግ ነው። ሁል-ጊዜ ድረሱልኝ፣ ችግር ውስጥ ገብቻለሁ የሚያስብል ዐይነት አካሄድ ነው። ለማንኛውም የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት የተቋም መስተካከያ ፖሊሲ የሚያተኩረው የመንግስትን ባጀት ቅነሳ፣ የውጭውን ገበያ ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት የማድረግ፣ በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉ ሀብቶችን ወይም ኢንዱስትሪዎችን ወደ ግል ማዘዋወር ወይም ለሀብታሞች መሸጥ…ወዘተ. ወዘተ በሚሉት ላቅይ ሲሆን፣ በመሰረቱ እነዚህ እንደመሳሪያ የሚታዩ ጉዳዮች ለሁለ-ገብ የኢኮኖሚ ዕድገት የሚያመቹ አይደሉም፤ የስራ-ክፍፍልም እንዲዳብር የሚያደርጉ አይደሉም። እነዚህም የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ መሳሪያኦች ሊሆኑ በፍጹም አይችሉም። ምክንያቱም ማክሮ የሚለው ፅንሰ-ሃሳብ አጠቃላይ ሁኔታዎችን የሚመለከትና፣ ራሱም የጥቃቅን ወይም ሚክሮ ነገሮች ውጤት በመሆኑ ነው። ስለሆነም የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ መሳሪያ እያሉ የሚጠሯቸው እጅግ አሳሳች የሆኑና የኬይንስንም የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ አስተሳሰብ የሚፃረሩ ናቸው። በኬይንስ ዕምነትና በተግባርም እንደታየው የአንድ አገር ኢኮኖሚ ሊገነባና ጥንካሬም ሊያገኝ የሚችለው በፊስካል ፖሊሲ አማካይነት መንግስት የጣልቃ-ገብነት(Interventionist) ፖሊሲ ከተከተለ ብቻ ነው። ይህም ማለት ኬይንስ የማክሮ ኢኮኖሚ ቲዎሪውንና ፖሊሲውን ሲያዳብር በፍጹም ስለገንዘበ ቅነሳ አላነሳም። በመሰረቱ ይህ ዐይነቱ በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትና በሌሎች ዓለም አቀፋዊ ተቋማት ግፊት እንደኛ ባለው አገር ውስጥ የሚተገበረው የኢኮኖሚ ፖሊሲ የእነ አዳም ስሚዝን መሰረታዊ አስተሳሰብንም የሚፃረር ነው። የተቋም ፖሊሲው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሳይሆን አፋኝና እንደኛ የመሰለው አገር ቀጭጮና ተዝረክሮኮ እንዲቀር የሚያደርግ ነው። በተለይም እንደኛ የመሰለው በጣም ወደ ኋላ የቀረ አገር በመጀመሪያ ደረጃ ተግባራዊ ማድረግ ያለበትን፣ ለምሳሌ መሰረታዊ ፍላጎቶችን(Basic Needs) የማሟላት ጉዳይ ከቁጥር ውስጥ እንዳያስገባ ወይም አትኩሮ እንዳይሰጥ የሚያደርግ መሰሪህ አካሄድ ነው። አንድ አገር ከታች ወደ ላይ ባይሎጂያዊ በሆነ መልክ እንዳትገነባና ቀስ በቀስም በሳይንስ እየተመራች የቴክኖሎጂ ባለቤት በመሆን ችግሮቿን እንዳትፈታ የሚያደርግ ነው። ለምን የእኛ አገር መሪዎችና አማካሪዎቻቸው ይህንን ዐይነቱን ህዝብን የሚያደኸይና አገርን የሚያዳክም ፖሊሲ ብለው የሚጠሩትን ከሰላ አምስት ዓመት በላይ በተከታታይ ተግባራዊ እንደሚያድርጉ ግልጽ አይደለም። ለመሆኑ ያሉበትን አገር ሁኔታና የህዝባቸውን የኑሮ ሁኔታ ይመለከታሉ ወይ? የኢኮኖሚ ፖሊሲ ዋናው ተግባሩስ ምንድነው? ድህነትን ማስወገድና ጤናማ የኢኮኖሚ ስርዓት መገንባት አይደለም ወይ? ይህንን ግልጽ ቢያደርጉልን ደስ ይለናል።
ያም ሆነ ይህ ወደ መሰረተ-ሃሳቡ ስንመጣ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የሶስዮሎጂ ዕውቀቶች በአውሮፓ ምድር የተፈጠሩና የዳበሩ ናቸው። ዕውቀቶችም ከጊዜው ሁኔታ በመነሳትና ሁኔታዎችን በማንበብ የተጻፉ ናቸው። ማርክስ በ16ኛው ክፍለ-ዘመን ቢኖር ኖሮ ዳስ ካፒታልንም ሆነ የፖለቲካና የሶስዮሎጂ ቲዎሪዉን ባልጻፈ ነበር። አዳም ስሚዝም በጊዜው የነበረውን ሁኔታ በማንበብ ነው The Wealth of Nations የሚባለውን መጽሀፉን ሊጽፍ የቻለው። ማክስ ቬበር የሶይሶሎጂ ቲዎሪዎን የጻፈው የኢንዱስትሪ አብዮት ከተካሄደ በኋላ በ19ኛው ክፍለ-ዘመን መጨረሻ ላይ ነው። ሌሎችም ቀደም ብለው የተነሱ ምሁራኖች የህብረተሰቦቻቸውን ለውጥና በጊዜው እየተወሳሰበ የመጣውን ችግር የተመለከቱትና ምክንያቱንም ለመረዳትና መፍትሄም ለመስጠት የተነሱት አዳዲስ ቲዎሪዎችን በማዳበር ነው። የግሪክ ፍልስፍና፣ የተፈጥሮ ሳይንስና ሌሎች ዕውቀቶችም በኋላ ላይ ብቅ ላሉት የአውሮፓ ምሁራን መመሪያዎቻቸው ነበሩ ማለት ይቻላል። ከእንግሊዝ የኢንላይተንሜንት እንቅስቃሴ በፊት የነበሩና፣ ራሳቸውም የኢንላይተንሜንት አፍላቂዎች ከግሪክ ዕወቀት ጋር ሳይተዋወቁና በበቂው ሳይመራመሩ አዳዲስ ቲዎሪዎችን ማዳበር ባልቻሉ ነበር። ራሱ አዳም ስሚዝም የስራ-ክፍፍል የሚባለውን ፀንሰ-ሃሳቡን የወሰደውና ከጊዜው ጋር እንዲስማማ አድርጎ ያዳበረው የእነ ሶክራተስን የአንትሮፖሎጂ ጽሁፍ በማንበቡ ነው።ኋላ ላይ የኢንዱስትሪ አብዮት ከተካሄደና ካፒታሊዝም እየተስፋፋ ሲመጣ ልዩ ልዩ ማህበራዊ ቀውሶች በመፈጠራቸው ምክንያቶቻቸውን ለመፈለግና መፍትሄም ለመስጠት ሲባል አዳዲስ አስተሳሰቦች መፈጠር ቻሉ። ማክስ ቬበር ኢንቴሌክችዋሊዝምና ራሽናሊዝም(Intellectualization and Rationalization ) ብሎ የሚጠራቸው ፅንሰ-ሃሳቦች ከካፒታሊዝም ዕድገት ጋር የተያያዙ ናቸው። በሌላ አነጋገር፣ የካፒታሊዝም ማደግና መስፋፋት በተለይም የምሁራንን ጭንቅላት ማዳበርና ጥያቄም እንዲጠይቁ አስችሏቸዋል። ስለሆነም ሁሉም በየፊናው ሁኔታዎችን በተለያየ መነጽር በማንበብ ለሚታዩት ችግሮች መፍትሄ ማቅረብ ተገደደ። በተጨማሪም እንደ ሶሻሊዝም የመሳሰሉት አስተሳሰቦች መስፋፋት ራሱ የካፒታሊዝም ውጤቶች ናቸው። በጊዜው የነበረው ከካፒታሊዝም መስፋፋት ጋር የተያያዘው ማህበራዊ ቀውስ፣ የስራ-አጥነት፣ በቆሻሻ ቦታዎች ላይ መኖር፣ ሰፊው ህዝብ ወደ ለማኝነት መለወጥና፣ በራሱም በየፋብሪካዎች ውስጥ የነበሩ የስራ ሁኔታዎች የግዴታ አዳዲስ ቲዎሪዎችን ማዳበር አስገደዱ። ስለሆነም ነው ሁኔታውን ጠጋ ብለው የተመለከቱና የተመራመሩ ማርክስና ኤንግልስ የመሳሰሉት ምሁራን ልዩ ልዩ የሶስዮሎጂ፣ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ቲዎሪዎችን በመጻፍና በማሰራጨት ወዝ-አደሩን በማስተማርና እንዲነቃም በማድረግና የራሱን የሙያ ድርጅት በመመስረት መብቱን እንዲያስጠብቅ ያስደረጉት። በተለይም በሶሻሊዝም አስተሳሰብ መስፋፋት የተደናገጡ ምሁራን የራሳቸውን የሶሻል ቲዎሪ በማዳበር መንግስት ተግባራዊ ማድረግ የሚገባውን ነገር ማድረግ እንዳለበት ግፊት በማድረግ በተለይም በጀርመን ምድር በኦቶ ፎን ቢስማርክ አማካይነት የመጀመሪያው የጀርመን ጠቅላይ ሚኒስተር የማህበራዊ ህግ እንዲወጣና እንዲፀድቅ ለማድረግ ተቻለ። በዚህም አማካይነት ወዝ አደሩ በሙያ ማህበር መደራጀቱ ብቻ ሳይሆን፣ በፋብሪካ ውስጥ መብቱ እንዲጠበቅለት ተወካዮችን እንዲመርጥና፣ ሰራተኛውም ሆነ አሰሪው በእኩልነት የሚሳተፉበት የጤንነት መድህንና የጡረታ አበል ሁኔታዎች በህግ ለመጽደቅ ቻሉ። ይህም ማለት ሰራተኛው ሰራተኛ ብቻ ሳይሆን የማህበረሰብ አካል ሆኖ በመታየት በበሽታ ሲጠቃ በቀላሉ ሊታከም የሚችልበትና ጡረታም ከወጣ በኋላ በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲኖር የሚያስችል ህግ በመጽደቅ ማህበራዊ ውዝግብ እንዳይኖር ለማድረግ ተቻለ። ይሁንና በዘመነ ግሎባላይዜሽን በሰራተኛውና በካፒታሊስቶች መሀከል ያለው የገቢ መጠን እየሰፋና፣ ሰራተኛው ሳያቋርጥ አርባ ዓመት ያህል ከሰራ በኋላ በአስተማማኝ ሁኔታ ሊኖር እንዳይችል የተደረገበትን ሁኔታ እንመለከታለን። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ በተለይም ሰራተኛው መሬት የመግዛትና የራሱን የግል ቤት ሰርቶ የመኖር ችሎታና አቅምም የለውም። መሬትም ሆነ ልዩ ልዩ በገንዘብ የሚተመኑ ሀብቶች 5% በመቶ በሚሆኑ ካፒታሊስቶች ቁጥጥር ስር ያሉ ናቸው። እንደ አሜሪካ በመሳሰሉት አገር ውስጥ ደግሞ 1% የሚሆነው የህብረተሰብ ክፍል 90% የሚሆነውን ሀብት ይቆጣጠራል።
ለማንኛው ይህንን ዐነቱን አሉታዊ ሁኔታ ወደ ጎን ትተን የተለያዩ ዕውቀቶችን አፈላለቅ ስንመረምር ከግሪክ ስልጣኔ ጀምሮ እስከ ኢንላይተንሜንት ድረስ ያለውን ሁኔታ ስንመለከት የተገለጸላቸው ምሁራን ጭንቅላታቸውን በማስጨነቅና ተፈጥሮንና ህዋን፣ እንዲሁም በሰዎች የሚፈጠሩ አዳዲስ ሁኔታዎችን በማየትና በማጥናት ነው በተለያዩ ጊዜያት አዳዲስ ዕውቀቶችን ለማፍለቅና ለተከታታዩ ትውልድ ለማስተላለፍ የቻሉት። በተለያዩ የአውሮፓ አገሮች ምሁራን ዘንድ፣ በጀርመን ፈላስፋዎችም ሆነ ሳይንቲስቶችና በእንግሊዝ ፈላስፋዎች መሀከል የአስተሳሰብ ልዩነት ቢኖርም፣ ለምሳሌ የዕውቀትን አፈላለቅ ጉዳይ አስመልክቶ የሁሉም ዋና ዓላማ ህዝቦቻቸውን በጊዜው ከነበሩበት ጨለማዊ ሁኔታ አውጥቶ ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግ ነበር። ለዚህ ደግሞ በየአገሩ የሰፈኑት ዲስፖታዊ አገዛዞች መወገድና የህግ የበላይነት መስፈን አለበት የሚል ስምምነት አለ። በዚህ መልክ መታገልና በመንፈስ የበላይነት መመራት፣ ጥያቄዎችን መጠየቅና መልስም ለማግኘት መጣር በራሱ የኳንተም-ፊዚክስ መሰረታዊ አስተሳሰብ ነው። ይህም ኳንተም ኮንሺየስነስ ወይም ንቃተ-ህሊና በመባል ይታወቃል። በሌላ አነጋገር፣ ወደ ውስጥ ጠለቅ ብሎ በማየትና በመመራመር ብቻ ነው ዐይነተኛ ለውጥ ሊመጣ የሚችለው። አንድ አገርና ህዝብም በመንፈስ የበላይነት ሲመሩና በየጊዜው ጭንቅላታቸውን በዕውነተኛ ዕውቀት ሲያዳብሩ ብቻ ነው ራሳቸውን በማግኘት ፈጣሪና ስላማዊ ዜጋ ለመሆን የሚችሉት። ይህ ነው የኳንተም ፊዚክስ ዋናው መሰረተ-ሃሳብና መልዕክት።
ከዚህ አጭር ሀተታ ስነሳ የእኛ አገር ምሁራን ችግር ከተለያዩ ምሁራዊ እንቅስቃሴዎች ጋር ለመተዋወቅና የማሰብ ኃይልን ለማስፋት አለመሞከር ነው። ሁሉም ማለት ይቻላል ከተማረው ትምህርት ውጭ እንዳያስብ ሆኖ መንፈሱ የተቀረጸ ይመስል ሌሎች አማራጭ ቲዎሪዎችንና ፖሊሲዎችን ሲሰማ መደናገጥ ይጀምራል፤ አንዳንዱ ደግሞ እሱ ከሚያስበው አስተሳሰብ ሌላ አማራጭ ጽሁፍ ሲያነብ ጸሀፊውን እንደ ጠላት ማየት ይጅምራል። የሚገርመው ደግሞ አውሮፓም ሆነ አሜሪካን የተለያዩ በተለይም የኢኮኖሚክስ ዕውቀቶች ቲዎሪዎችና ፖሊሲዎች ይሰጣሉ። መጻህፍቶችም እንደልብ ይገኛሉ። በነፃ መዋስና እስከስድስት ወር ጊዜ ድረስ ከቤት ሆኖ በኢ-ሜልይ በየወሩ በማስረዘም ማንበብና መመራመር ይቻላል። ይህ የማያመቸው ደግሞ ከሰከንድ ሃንድ የመጻህፍት መደብር በመሄድ በአንድና በሁለት ዶላር ወይም ኦይሮ መጻህፍቶችን መግዛት ይቻላል። በዚህ መልክ የማሰብ አድማስን ማዳበርና ከሪጂድ ወይም ከከረረ አስተሳሰብ መላቀቅ ይቻላል። በየጊዜው የተለያዩ መጽሀፎችን በማንበብና በማነፃፀር ብቻ ነው አዕምሮን ወይም መንፈስን ማጎልመስ የሚቻለው። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ከተለያዩ አስተሳሰቦች ጋር መተዋወቅ ሲቻል ብቻ ነው የሌላውን አስተሳሰብ መረዳት የሚቻለው። ለምሳሌ በኢኮኖሚክስ ቲዎሪ፣ የፊዚዮክራቲክስ፣ የክላሲካል፣ የማርክሲዝም፣ የኒዎ-ክላሲካል፣ የኬይኔሲያን፣ የኒዎ-ሊበራልና የኢንስቲቱሽናል የኢኮኖሚ ቲዎሪዎች የሚባሉ አሉ። የሚያሳዝነው ነገር ግን በየዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በተለይም ከ50ኛው ዓመተ ምህረት ጀምሮ የተጻፈው የእነሳሙዔልሰን የኢኮኖሚክስ መጽሀፍና የኒዎ-ሊበራል አስተሳሰብ በመዳበሩና አብዛኛዎቻችንም በዚህ የሰለጠን በመሆናችን ሌላ አስተሳሰብ ያለ አይመስለንም። በሌላ ወገን ግን በተጨባጭ የካፒታሊስት አገሮችን የኢኮኖሚ ግንባታ ታሪክ ስንመለከት የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚክስ ምሁራን እንደሚሉት ሳይሆን በመንግስት ጣልቃ ገብነትና ድጎማ የተገነቡ ናቸው። አሁንም ቢሆን በአብዛኛዎቹ የካፒታሊስት አገሮች ውስጥ የመንግስት ጣልቃ-ገብነት ከፍተኛ ሚናን ይጫወታል። የምርምርና ዕድገት(Research & Development) ጉዳዮች በሙሉ በመንግስት የሚደገፉ ናቸው። በእነዚህ የምርምር ማዕከሎችም ውስጥ ቴክኖሎጂዎች ይፈጠራሉ። ኢንዱስትሪዎችም ወደ ተግባር እንዲለውጧቸው ተባብረው ይሰራሉ። ሀቁ ይህ ሆኖ ሳለና የኢኮኖሚክስ ግንባታ ታሪክ የሚነግረን ሀቅ ሌላ እየሆነ እያለ የእኛ አገር ምሁራን የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚክስ ቲዎሪን የሙጥኝ ብለው በመያዝ ይኸው እንደምናየው አገራችን ልትወጣ የማትችለው ማጥ ውስጥ ከተዋታል። ሁሉም ነገር ካለውጭ ዕርዳታ ሊሰራ አይችልም እየተባለ ብዙ ነገሮችን፣ የገንዘብንም ሚና በማንሻፈፍ ስርዓት ያለውና ህዝቡን የሚያስተሳስረውና ሊደግፈው የሚችል የኢኮኖሚ ስርዓት እንዳይገነባ ተደርጓል። በተለይም የነፃ ኢኮኖሚ ወይም ገበያ ካለማኑፋክቸሪንግ፣ ካለሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ ካለተቋማት ግንባታ፣ እንዲሁም ከከተማዎችና ከመንደሮች፣ ከልዩ ልዩ ከተማዎችንና መንደሮችን ከሚያገናኙ መመላለሻዎች፣ ማለትም የባቡር ሃዲድ፣ ሰብ ዌይ፣ ትራምና ጠበብ ያሉም ሆነ ስፋ ያሉ አንዱን ከተማ ከሌላው ጋር የሚያገናኙ መንገዶች ውጭ የሚንቀሳቀስ አድርጎ በመቀነስና፣ የኢኮኖሚን አስተሳሰብ ወደ ሸቀጣ ሸቀጥ አስተሳስብ በመቀነስ ወይም ዝቅ አድርጎ በማየትና ገንዘብን ብቻ በማግኘት፣ ገበያም በአቅራቢና በጠያቂ(Supply & Demand) “ህግ” አማካይነት ነው የሚሰራው በማለትና ሰፋ ያለውንና ከልዩ ልዩ ዕውቀቶች ጋር መያያዝ የሚገባውን የኢኮኖሚ አስተሳሰብ በማኮላሸትና ተግባራዊ በማድረግ በአገራችን ምድር ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ፣ የባህልና የስነ-ልቦና ቀውስ እንዲከሰትና ሰፊው ህዝባችንም ግራ እንዲጋባ ለመደረግ በቅተዋል።
ይህንን ካልኩኝ በኋላ ዮናስ ብሩ ወዳነሳው ወደ ኳንተም ፊዚክስ(Quantum Physics) ጉዳይ ላይ ልምጣ። የኳንተም ፊዚክስ አነሳስ የኒውተንን አስተሳሰብ በተለይም ክላሲካል ፊዚክስ የሚለውን አስተሳሰብ አይ ሙሉ በሙሉ አሊያም ደግሞ በከፊል ውድቅ በማድረግ የተነሳ አዲስ አስተሳሰብ ነው። በኒዎተን የክላሲካል ፊዚክስ አማካይነት ማንኛውም ነገር በተናጠል የሚታይ ለምሳሌ ቦታና(Space) አንድ አካል(Body) ተነጥለው የሚታዩ ሲሆን ጊዜና ቦታ ፍጹማዊ ናቸው። ከዚህ በመነሳት ኃይል(Force)፣ እንቅስቃሴና(Motion) ስበትን(Gravity) በማደባር ለመካኒክስ መሰረት ጣለ። ይህም የኒውተን አስተሳሰብ ኮስሞስን በማንበብና በመመራመር የፈለቀ ሲሆን፣ ኒውተንም ይህንን የክላሲካል ፊዚክስ አስተሳሰብን ለማዳበር የቻለው እሱ እንደሚለው ቀደም ብለው በነበሩ ትላልቅ ትከሻዎች ላይ፣ እነ አርቺመዲሲ፣ ጋሊሌዬ ጋሊሊና ኬፕለር ትከሻ ላይ በመውደቁና የእነሱን ግኝት ወይም ምርመር መሰረት በማድረግ ነው ታላቅ ስራውን ለማዳበር የቻለው። በኒውተን ዕምነት ሁሉም ነገሮች በተናጠል የሚታዩ ሲሆን፣ በአምላክ ጣልቃ-ገብነት መስመር እንዲይዙ የሚደረጉ ናቸው የሚል ነው። ይሁንና ይህ የኒውተን አስተሳሰብ በሌላው የጀርመን ፈላስፋና የተፈጥሮ ሳይንስ ተመራማሪ በላይብኒዝ ውድቅ ለመሆን ችሏል። ኒውተንም ሆነ ላይብኒዝ አንዱ የሌላውን ግኝት ሳያገኝና ሳይኮረጅ ሁለቱም በየፊናቸው ለመካኒክስ በጣም ጠቃሚ የሆነውን ካልኩለስ የሚባለውን የሂሳብ ምርምር ሊያፈልቁ ችለዋል። ይህ ሲባል ግን የኒውተን አስተሳሰብ ውድቅ ነው ማለት አይደለም። ኒውተን በጊዜው በትላልቅ ነገሮች ላይ በማትኮሩና ማተርንም ህይወት እንደሌለው ነገር አድርጎ በማየቱና በተለይም እንደ አቶም የመሳሰሉና የአቶም መሰረቶች የሆኑ ጥቃቅን ነገሮችን ከቁጥር ውስጥ ማስገባት አልቻለም። ይሁንና ግን የቴክኖሎጂ ዕድገት እዚህ ዐይነቱ ደረጃ ላይ ሊደርስ የቻለው የኒውተንን አስተሳሰብ መሰረት በማድረግ ነው። ለማንኛውም የኋላ ኋላ ላይ የተነሱ ፕላንክና አነስታይን የመሳሰሉ ሳይንቲስቶች ወደ ውስጥ በመግባት የኮስሞስን፣ በተለይም የጊዜንና የአካባቢን(Space & Time) ፍጹማዊ(Absolute) እንዳልሆኑ ለመገንዘብ ችለዋል። ስለሆነም በተለይም በጥቃቅን ነገሮች ላይ፣ አቶምና የአቶም መሰረት በሆኑ፣ ጥቃቅን ነገሮች ላይ በማትኮር ለኳንተም-ፊዜክስ መሰረት ለመጣል ችለዋል። በዚህ መልክ ጥቃቅን ነገሮችን ለማየትና እያንዳንዱ ፓርቲክል ውስናዊ ባልሆነ መልክ እንደሚንቀሳቀስ ለመረዳት ችለዋል።
ለማንኛውም የኒዎ-ክላሲካልና የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ቲዎሪ በኒውተን አስተሳሰብ ላይ የተመሰረተ ሲሆን፣ ሁሉም በተናጠል የሚታይና ውድድርም የሚያደርግ ነው። ይህ ዐይነቱ የኒውተን አስተሳሰብ በተለያዩ ነገሮች መሀከል መተሳሰር እንዳለና አንደኛው በሌላው ላይ እንደሚመካ አያምንም። ሁሉም በየፊናው የሚሯሯጥና የራሱን ጥቅም ከፍ ለማድረግ የሚጥር ወይም እሽቅድምድሞሽ አካሄድ ነው የሚያስመስለው። በቀጥታ ግን ራሱ ኒውተን እንደዚህ ብሎ ጽፏል ለማለት ሳይሆን በዚህ መልክ የተረዱት የኒዎ-ክላሲካል ኢኮኖሚ ቲዎር አፍላቂዎች የኢኮኖሚ ቲዎሪዎቻቸውን ፊዚክስን መሰረት በማድረግ ለማዳበር ችለዋል። ይህም ማለት ዮናስ በተሳሳተ መልክ የኳንተም ፊዚክስን መሰረታዊ አስተሳሰብ በግለሰብአዊነት(Methodological Individualism) ላይ በመመስረት ነው የሚሰራው የሚለው በቀጥታ ከዚህ ዐይነቱ የኒዎ-ክላሲካል ወይም የኒዎ-ሊበራል የተሳሳተ አስተሳሰብ የተወሰደ ነው። በኳንተም ፊዚክስ መሰረት እያንዳንዱ ጥቃቅን ነገር ወይም ፓርቲክል የራሱ ነፃነት ቢኖረውምና አካሄዱም ከመጀመሪያውኑ የተወሰነ ባይሆንም በእያንዳንዱ ፓርቲክል ወይም ሰብ-አቶሚክ በሆኑ ጥቃቅን ነገሮች መሀከል፣ ማለትም በፕሮቶን፣ በኔዎትሮንና እንዲሁም በኤሌክትሮንና ከዚያም በታች በሚገኙ ጥቃቅን ፓርቲክሎች መሀከል ተራርቀው ቢገኙም መረጃዎችን ወይም ኢንፎርሜሽኖችን ይለዋወጣሉ። ይህም ኳንተም ኢንታንጀልሜንት በመባል ይታወቃል። ከዚህ ስንነሳ የኳንተም ፊዚክስ አስተሳሰብ በሁለ-ገብነት(Holistic) ህግ ላይ የተመሰረተና፣ አንደኛው ከሌላው ጋር የተያያዘ ነው። በሌላ አነጋር፣ አንደኛው ነገር ቢጠፋ ሌላው ሊሰራ ወይም ሊንቀስቃስ አይችልም። ትናንሽ ነገሮችን ትተን ለምሳሌ ትልቁን ፀሀይን ብንወስድ ፀሀይ ባልታወቀ ምክንያት ስራዋን ብታቆም፣ ሙቁትም ሆነ ብርሃንን ለተወሰኑ ዐመታትም ሆነ ለዘለዓለም ለመለገስ ባትችል ራሱ ፍጥረት የሚባለውም ሆነ የሰው ልጅ እንዳለ ይወድማሉ። ይህም የሚያረጋግጠው ተፈጥሮም ሆነ የሰው ልጅ ካለ ኃይል(Energy)፣ ሙቀትና ብርሃን በፍጹም ሊታሰቡና ሊኖሩም እንደማይችሉ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን በተፈጥሮ ውስጥ ያሉ ነገሮች በመተሳሰርና አንደኛው በሌላኛው ላይ ተፅዕኖ በማሳደር ነው ሊያድጉ የሚችሉት። ለምሳሌ ካለብዙ እሳቤ ለብዙ መቶ ዓመታት ያደጉ ትላልቅ ዛፎች እንዳለ ከወደሙ ያ አካባቢ ቀስ በቀስ ወደ በረሃነት ይለወጣል። መሬቱን የሚከላከለው ነገር ስለወደመበት ኃይለኛ ነፋስ በሚነፍስበት ጊዜ የመሬቱ ፍሬያማ ክፍል በነፋስ ኃይል እየተጠረገ ይወሰዳል። ዝናብም በበቂው ስለማይዘንብ ልዩ ልዩ አትክልቶች የማበብ ኃይላቸው ይዳከማል። ባጭሩ መረዳት ያለብን ጉዳይ እያንዳንዱ ነገር በተናጠል የሚታይ ሳይሆን ሁሉም ነገሮች የተያያዙ ናቸው። በሰዎችም መሀከልም የሚኖረው ግኑኝነት የተሳሰረ ነው። በአካል ባንገናኝም በመንፈስ የምንገናኝ ብዙዎቻችን ነን።
የኒዎ-ክላሲካል ወይም የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚስክ አስተሳሰብ ግለሰብአዊ ጥቅምን በማሳደድና(Utility and Profit maximization) ነገሮችን በተናጠል በማየት ላይ የተመሰረተ አስተሳሰብ በመሆኑ የአገራችንንም ሆነ የአብዛኛው የአፍሪቃ አገሮች ዕድገት ሊዘበራርቅና ሊሳሳት ችሏል። ስለሆነም ይህ ዐይነቱን በግለሰብአዊ ጥቅምና ጥቅምን በማሳደድ ላይ የተመሰረተው አስተሳሰብ የኳንተም ፊዝክስን ህግ እንዳለ የሚፃረር ነው። በመተባበርና በመተጋገዝ፣ አንዲሁም አንደኛው ለሌላው በማሰብ የሚሰራበትና ማህበራዊ ኃላፊነት እንዲሰማ የሚያደርግ ሳይሆን ወደ ሶሻል ዳርዊኒዝም ወይም ደግሞ የበላይነትን የተቀዳጀው ኃይል ወይም ግለሰብ በአሸናፊነት የሚወጣበትንና የሚኖርበትን፣ የአንድ አገርም ህዝብ ዕድልና ኖርም በጥቂቶች የሚወሰነብትን የሚያረጋግጥ ነው። ስለሆነም ካፒታሊዝም በአሸናፊነት ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ፣ በተለይም ባለፉት 75 ዓመታት ሌሎች አስተሳሰቦችን በመርገጥና በማገድ የዓለም ህዝብ አስተሳሰብ፣ ድርጊትና የፍጆታ አጠቃቀም በአንድ ወጥ አስተሳሰብ እንዲደነገግና ተቀባይነትም እንዲኖረው በማድረግ ነፃ አስተሳሰብን፣ ሁለ-ገብና ሚዛናዊነት ያለው ዕድገት በእየአገሮች ውስጥ እንዳይተገበርና ዕውንም እንዳይሆን ለማድረግ በቅቷል። ይህ ዐይነቱ እሽቅድምድሞሽና አንድ ወጥ አስተሳሰብ ደግሞ መንፈሳዊ አስተሳሰብን በመርገጥ የገንዘብና የፍጆታ አጠቃቀም የበላይነትን እንዲጎናጸፉ የተደረገበትን ሁኔታ ነው። እንደምንመለከተው ይህ ዐይነቱ የተሳሳተ አስተሳስብ በዓለም አቀፍ ደረጃ በመስፋፋቱ ለጦርነት ዋናው መንስዔ በመሆን በቀጥታ የህዝብን ዕልቂት በማስከተል፣ አንዳንድ አገሮች ደግሞ ወደ ጦር አውድማነት የተለወጡበትን ሁኔታ እንመለከታልከን። ስለሆነም በማቴሪያሊዝም ላይ የተስፋፋው አስተሳሰብ የበላይነትን በመቀዳጀት መንግስት የሚባለው አካል ራሱ ዘላቂ ሰላምንና የተሟላ ዕድገት እንዳይመጣ እንቅፋት ለመሆን በቅቷል። በመመረጥ ወይም በአንዳች ዐይነት ስልጣን ላይ የሚወጡ ኃይሎች የመንግስትን መኪና የራሳቸው የግል ሀብት አድርገው በመቁጠር በተለይም እንደኛ ባለው ኋላ-ቀር አገርና ምሁራዊ ኃይል ባልዳበረበት፣ የተገለጸለትና የተደራጁ ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍል ተጠሪዎች በሌሉበት አገር ውስጥ የፈለገውን ለማድረግ የሚችል እየመሰለው የተፈጥሮንና የህብረተሰብን ህግ የሚፃረሩ ስራዎችን ተግባራዊ በማድረግ ህብረተሰብን በማዘበራረቅ ላይ ይገኛል። በተለይም ባለፉት አርባ ዓመታት ግሎባላይዜሽን የሚባለው አስተሳሰብ ከተስፋፋ ወዲህና፣ አብዛኛዎች አገሮችም የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲን ተግባራዊ ማድረግ ከጀመሩና፣ ዓለምም በአንድ ኃያል መንግስት የምትመራ ናት፣ ስለሆነም እያንዳንዱ አገር በህግ ላይ የተመሰረተ ስርዓት(Rule Based System) መከተል አለበት እየተባለ መሰበክ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች፣ በተለይም ኢትዮጵያችን ሙሉ በሙሉ ብሄራዊ ነፃነቷ ሊደፈር ችሏል። የኳንተም ፊዚክስ አስተሳስብ እንደዚህ ዐይነቱን በጥቂቶች የበላይነት የሚመራውንና ለልዩ ልዩ አስተሳሰቦች መፈናፈኛ የማይሰጠውን አስተሳሰብ እንዳለ የሚፃረር ነው። ምክንያቱም በኳንተም ፊዚክስ ዕምነት እያንዳንዱ ጥቃቅን ነገር የራሱ ነፃነት ያለው ሲሆን፣ በመወስን ሳይጓዝ ይሁንና ግን ከሌላው ጋር በመተሳሰብ ወይም በመተባበር የሚሰራ በመሆኑ ነው። ከዚህም በላይ ኳንተም ፊዚክስ ዲያሌክቲካዊ ክንዋኔ ነው። በቅራኔ ህግጋት የሚመራና አንደኛው ነገር ከአንድ ሁኔታ ወደ ሌላ በመለወጥ ዕድገት ለማምጣት እንደሚችል ያረጋግጣል። ይህም በራሱ የተፈጥሮ ህግ ነው። ለምሳሌ ለዘር የሚሆንን ማንኛውንም ፍሬ ወይም እህል በምንወስድበት ጊዜ ሲዘራ፣ አካባቢው አመቺ ከሆነና ዝናብም ሆነ ፀሀይ በተፈላጊው መጠን የሚገኙ ከሆነ የተዘራው ለምሳሌ አተር ቀስ በቀስ ስር ያበቅላል። በስሮች አማክይነት ከመሬት ውስጥ ውሀንና ልዩ ልዩ ሚኒራሎችን ይስባል። ቀስ በቀስም ፍሬዎችን የሚሸከም ግንድና ቅርንጫፍ በማብቀል ከአበበ በኋላ ከአንድ አተር ብዙ አተሮች ይገኛሉ። ይህ ዐይነቱ ሂደት ቴሲስ፣ አንቲ-ቴሲስና ሲንቴቲስ (Thesis, Anti-Thesis, Synthesis) ተብሎ ይጠራል። ይህ ዐይነቱን ተፈጥሮአዊና የኮስሞስን ህግ ስንረዳ ብቻ ነው ህብረተሰብአዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጥንና ዕድገትን ለማምጣት የምንችለው። ከዚህ ውጭ በነፃ ገበያ አማካይነትና በጠያቂና በአቅራቢ መሀከል በሚደረግ ግኑኝነት ለውጥ ይመጣል ብሎ ማሰብ ሳይንሳዊና ተፈጥሮአዊ ወንጀል እንደመስራት ይቆጠራል። አንድ ህብረተሰብና አገር እንዳለ ይዘበራረቃሉ። ከአርቆ-አሳቢነትና አስተይዋነት ይልቅ ማንም እየተነሳ የሚቧርቅበትና የሚጨፍርበት አገር ይመሰረታል። በዚያውም መጠን ከዓለም አቀፍ ካፒታሊዝም ጋር የተሳሰረ የንዑስ ከበርቴው ፋሺሽታዊ አገዛዝ በመመስረት ተፈጥሮን ወደ ተራ ተበዝባዥነት ይለውጣታል። ባጭሩ በተፈጥሮና በታሪክ ላይ እንዳለ በመዝመት ጨለማዊ ስርዓት እንዲመሰረት ያደርጋል። በተለይም በዛሬው ወቅት በአገራችን ምድር ያለው ሀቅ ይህንን የሚመስል ነው።
የኳንተም ፊዚክስን መዳበር ስንመለከት ቀደም ብለው ያልታዩና በማቴሪያሊዝም ላይ ብቻ የተመሰረተውን አስተሳሰብ በመፃረር የመንፈስን የበላይነት በማስመር የዳበረ ልዩ ዐይነት ዕውቀት ነው። ለዚህም ነው ኳንተም ኮንሺየስነስ፣ ኳንተም ሶሻል ሳይንስና ኳንተም ኢኮኖሚክስ እየተባለ ሊዳብር የቻለው። በተለይም በካፒታሊዝም ልቅ የሆነ ዕድገትና ለሰው ልጅ ጠቀሜታ የማያስፈልጉ ልዩ ልዩ ምርቶች ስለሚመረቱና፣ የካፒታሊስቶችም ዋናው ዓላማ ምርትን አምርቶ ትርፍን ከማካበት ውጭ ስለማይታሰብ ይህ ዐይነቱ በሰው ልጅና በተፈጥሮ ላይ የሚደረገው ዘመቻ በጣም አደገኛ መሆኑን የተገነዘቡ የፊዚክስ፣ የባይሎጂ ምሁራንና ፈላስፋዎች ጭምር የመንፈስን የበላይነት መዳበር በማስገንዘብ የሰው ልጅ ራሱ የተፈጥሮ አካል መሆኑን በማስገንዘብና፣ ህይወቱም ከተፈጥሮ ውጭ ሊታሰብ እንደማይችልና አሁን ካለበት በጣም ዝቅተኛ አስተሳሰብ በመላቀቅ መንፈሱን በማደበር አዲስ የአመራረትና የፍጆታ አጠቃቀም ስልት ማዳበር እንዳለብት ያስተምራሉ። ይህም ማለት ማንኛውም ሰው ማቴሪያላዊ ፍላጎቱን ማሟላቱ የተፈጥሮ ህግ ቢሆንም፣ ከሚያስፈልገው በላይ የሚደረጉ ነገሮች ተፈጥሮን ይጎዳሉ፤ አስተሳሰብንም ያዛባሉ። አንዳንድ ሳይኮሎጂስቶችና ፈላስፋዎች እንደሚያስተምሩን ከሆነ፣ ትክክልም ነው፣ በአሁኑ ወቅት ቴክኖሎጂ በተስፋፋበትና ብዙ ነገሮችም እንደልብ በሚገኙበት ዓለም ውስጥ የሰው መንፈስ እንዳለ በማቴሪያል ቁጥጥር ስር ሊወድቅ ችሏል፤ ተገዢ ለመሆን በቅቷል ይሉናል። በማሰብ ኃይሉ በመመራት የራሱን ዕድል ራሱ ሊወስን እንዳይችል ለመደረግ ተገዷል፤ ይህም ማለት በቀላሉ ሊታለል የሚችል ሆኗል። ስለሆነም የሰው ልጅ አሁን ካለበት የመንፈስ ቀውስ እንዲላቀቅ ከተፈለገ ማቴሪያላዊ ፍላጎትን በተንዛዛ መልክ ማየት ያለበት ሳይሆን ህይወቱ በመንፈስ የበላይነት በመመራት ጥበባዊ የአኗኗርና ተሳስቦ የመኖርን መንፈስ ማዳበር እንዳለበት ያሳስባሉ። ይህ ብቻ ሳይሆን የኳንተም ፊዚክስ አስተሳበ በግለሰብአዊነት አስተሳሰብ(Methodological Individualism) ላይ የተመሰረተውን አስተሳሰብ ውድቅ በማድረግና የሰው ልጅ ማህበራዊ መሆኑን በማስገንዘብ በአንድ አገር ውስጥና በተለይም በመንደሮችና በትናንሽ ወረዳዎች ውስጥ ህዝባዊ መተሳሰር እንዲኖር በማድረግና በጋራ በመንቀሳቀስ በየአካባቢው ለውጥ እንዲመጣ ማድረግ የኳንተም ሶሽል ሳይንስ መሰረታዊ አስተሳሰብ መሆኑን የሚውጡ ሀተታዎች ያረጋግጣሉ። በተለይም የካፒታሊዝምን ልቅ ዕድገት ጠጋ ብለው ያጠኑ ሶስይሎጂስቶች፣ ለምሳሌ እነ ዱርክሃይምና ሌሎችም በካፒታሊዝም ማደግ የተነሳ ከህዝባዊ መተሳሰር ይልቅ የተናጠል ሂደትና ግለሰብአዊ የአኗኗር ስልት እንደኖርምና እንደዘመናዊነት እየተወሰደ በመምጣቱ በተለይም በትላልቅ ከተማዎች ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የስነ-ልቦና ቀውስ ሊፈጠር እንደቻለና ይህ ዐይነቱ የአኗኗር ስልትም ለህብረተሰብ መናጋት አንደኛው ምክንያት እደሆነ ያሳስባሉ። የስነ-ልቦና መቃወስም እያንዳንዱ ግለሰብ ራሱን ወደውስጥ እንዳያይና ሰው መሆኑንም እንዳይገነዘብ ለማድረግ በቅቷል። ይህ ዐይነቱ ግለሰብአዊ የአኗኗር ስልትና የግለሰብአዊነት መንፈስ በመስፋፋቱ በተለይም በአንዳንድ ትላልቅ የአሜሪካ ከተማዎች ውስጥ ንጹህ ዜጋዎች በጠብመንጃ በጠራራ ፀሀይ ላይ እንዲገደሉ ዋናው ምክንያት ለመሆን በቅቷል። በተለይም የመሳሪያ ሎቢይስቶች ባስፋፉትና በሚያስፋፉት አደገኛ አስተሳሰብ፣ እያንዳንዱም ግለሰብ እንደ ጠላት የሚታይ ስለሆነና ሁሉም ራሱን ለመከላከል ሲል ጠብመንጃ መታጠቅ አለበት የሚለው አስተሳሰብ ስለተስፋፋ የሜሪካንን ህብረተሰብ ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ከቶታል። በመሆኑም በአሜሪካን ምድር በተለይም በትላልቅ ከተማዎች ውስጥ በየቀኑ እስከ 700 ሰዎች ያህል እንደሚገደሉ ይነገራል። በአንዳንድ ትምህርትቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎችም ውስጥ ተማሪዎች የወላጆቻቸውን መሳሪያ ይዘው በመምጣት በግቢ ውስጥ ምስኪን ተማሪዎችን እንደሚገድሉ በየጊዜው የምንሰማው አሳዛኝ ዜና ነው። ስለሆነም ይህ ዐይነቱ ዮናስ ብሩ Methodological Individualism በማለት የሚጠራው በአሜሪካን ቀኞችና፣ ሊበራሎችም ነን በሚሉ የሚስተጋባውና እንደ ርዕዮተ-ዓለም መመሪያም የተወሰደው አስተሳሰብ በጣም አደገኛና ትችታዊ በሆነ መልክ መመርመር ያለበት ጉዳይ ነው። በዚህም ምክንያት የተነሳ እያንዳንዳኑ ግለሰብ ራሱን መቻል አለበት፣ በራሱ ጥረት ብቻ ነው ከፍተኛ ቦታ ሊደርስ የሚችለው የሚለው እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ ትክክል ቢሆንም ይህ ዐይነቱ አስተሳሰብና እንደ ርዕዮተ-ዓለማዊ ቀኖና የተወሰደው በተግባር ሲታይ ግን ሀብታሞችንና ይህንን ዐይነቱን ርዕዮተ-ዓለም የሚሰብኩትን ብቻ ነው የሚጠቅመው። በመጀመሪያ ደረጃ እያንዳንዱ ግለሰብ አንድ ከፍተኛ ደረጃ ቦታ ለመድረስና ሀብታምም ለመሆን የቤተሰቡ መሰረት ወይም የመጣበት ቤተሰብ ወሳኝ ነው። ከደሃ ወይም ከሀብታም ቤተሰብ ከተወለደ ጥሩ ትምህርትቤት የመግባትና በኋላም የታወቁ የአሜሪካን ዩኒቨርሲቲዎችን ውስጥ ገብቶ የመማርና ትልቅ ቦታ የመድረስ ዕድሉ በጣም ከፍ ያለ ነው። እንደሚታወቀው አሜሪካን አገር ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ገብቶ ለመማር በየሰሚስተሩ ብዙ ሺህ ዶላር መክፈል ያስፈልጋል። በዓመት እስከ 40 ሺህ ዶላር ወይም ከዚያም በላይ መክፈል ያስፈልጋል። ይህንን ያህል ገንዘብ በመክፈል ልጆቻቸውን የሚያስተምሩ ደግሞ በጣም ሀብታም የሆኑ ወላጆች ብቻ መሆን አለባቸው፤ ናቸውም። በአጠቃላይ ሲታይ ግለሰብአዊነት የሚባለው አስተሳሰብና በዚህ ላይ በመመርኮዝ የሚደረገው ሰበካ ቀኖናዊ አስተሳሰብ ብቻ ሳይሆን መንግስት በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በሌሎች መስኮች ተግባራዊ ማድረግ የሚገባቸውን ነገሮች እንዳያደርግ የሚያግድ ነው። በተለይም ደሃውን ለማግለልና ወደ ተሻለ ደረጃ ላይ እንዳይደረስ መስናካል የሚፈጥር የቀኞችና የጥቂት ሀብታሞች ሰበካና የእነሱንም የበላይነት የሚያጠነክር ነው።
ይህ ዐይነቱ የግለሰብአዊነት አስተሳሰብ ሰበካና ተቀባይነትም ማግኘት በቤተሰብ ምስረታ ላይ ወይም ተጋብቶ ልጅ በመውለድ ላይ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ ነው። በሌላ አነጋገር የአብዛኛው ሰው አዝማሚያ ተጋብቶና ተዋልዶ ከመኖር ይልቅ በብቸኝነት መኖር እንደ ስልትና የስልጣኔ መለኪያ እየተወሰደ ነው። ስለሆነም በአንዳንድ ትላልቅ ከተማዎች ውስጥም ተጋብተውና ልጅ ወልደው በጋራ ከሚኖሩት ቤተሰቦች ይልቅ በተናጠል መኖር(Single Households) የተለመደና ቁጥሩም እየጨመረ በመምጣቱ ማህበራዊና የስነ-ልቦና ቀውስ ሊፈጥር ችሏል። ስለሆነም ኳንተም ሶሻል ቲዎሪ፣ ከሶስዮሎጂ፣ ከስነ-ልቦና ሳይንስ፣ ከፍልስፍና፣ ከከተማ የአሰራር ዕቅድና ሌሎች አካባቢን ውበት ከሚሰጡ ነገሮች ጋር በመዳበል አንድ አገር ጥበባዊና ማህበራዊ ሆኖ እንዲገነባ የሚያሳስብ መመሪያ ነው። እንደኛ ወደ መሰለው አገር ስንመጣ ግን አሁን እንደዘይቤ የተወሰደው የቤቶች አሰራር የግለሰብአዊነት መንፈስን የሚያስፋፋ ነው። የቤቶችም አሰራር ጥበባዊ የሆነ የከተማ ዕቅድን መሰረተ-ሃሳብ ያላደረገ በመሆኑና ከረጅም ጊዜ አንፃር ሳይታሰብ በሬል ስቴት ስም የሚሰሩ ትላልቅ ፎቅ ቤቶች ለማህበራዊ ኑሮ የሚያመቹ አይደሉም። አብዛኛዎቹ ህንፃዎች በተናጠል የሚገኙና በአካባቢያቸውም መናፈሻና ለህፃናት መጫወቻ የሚሆን አረንጓዴ ሜዳ ባለመኖሩ ወና ነው የሚመስሉት። አብዛኛዎቹ ህንፃዎችም ከአብዛኛው ህዝብ ፍላጎት፣ የመግዛትና የመከራየት አቅም ውጭ ስለሚሰሩ እንደምንሰማው ከሆነ ሳይከራዩ ቆመው ቀርተዋል። እንደዚህ ዐይነቱ የህንፃ አሰራር ማህበራዊና የስነ-ልቦና ቀውስንም ያስከትላል። ስለሆነም ስለኳንተም ፊዚክስ፣ ስለኳንተም ሶሻል ሳይንስ፣ ስለ ኳንተም ኢኮኖሚክስ በሚወራበት ጊዜ እነዚህ ነገሮች በሙሉ ቁጥር ውስጥ መግባት አለባቸው።
ስለሆነም ኳንተም ፊዚክስ ዮናስ ብሩ እጅግ በተሳሳተና በተቆነፀለ መልክ ለማቅረብ እንደሞከረው ሳይሆን የመንፈስን የበላይነት ማዕከላዊ በማድረግ የሰው ልጅ ራሱን በመቆጣጠርና የተፈጥሮ አካል በመሆን የሚጓዝበትን ማስተማሪያና መመሪያ መንገድ ነው ማለት ይቻላል። ይህም ማለት ኳንተም ፊዚክስ ከጭንቅላት ጋር በቀጥታ የሚያያዝ ሲሆን፣ ሴሎቻችንና ሴሎቻችንን የሚያያዙ ኖይሮሲስ የሚባሉትን ሁሉ የሚመለከት ነው። ወደ ጭንቅላታችን ስንመጣ የሰው ልጅ 5% ብቻ በሚሆነው የማሰብ ኃይሉ የሚመራ ሲሆን፣ 95% የሚሆነውን የማሰብ ኃይሉን በፍጹም አይጠቀምም ወይም በደመ-ነፍስ በመመራት ነው ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ስነ-ልቦናዊና ባህላዊ ቀውሶችን በመፍጠር በአንድ አገር ውስጥ የሚኖር ህዝብ በስምምነት፣ በመግባባትና በመቻቻል እንዳይኖር የሚያደርገው። አንደኛው የሌላው ጠላት ይመስልና መጥፎ አስተሳሰቦችን በመንዛት የማያቋርጥና ህዝብን ጨራሽ ጦርነት እንዲቀሰቀስ በማደረግ፣ የተፈጥሮ ሀብትም እንዲወድም መደረጉ ብቻ ሳይሆን የሰው ልጅም አስተሳሰብ በመጥፎ ነገሮች እንዲጠመድ በማድረግ ርስ በርሱ የሚያያዝ፣ ቀስ በቀስ የሚያድግና ሁሉንም የህብረተስብ ክፍል ሊጠቅም የሚችል ሁለ-ገብ ዕድገት እንዳይመጣ ለማድረግ በቅቷል። በዚህ መልክ በራሱ በኒዎ-ሊበራሊዝም አስተሳሰብ የሚመራ አገዛዝና ኤሊትም የዕድገትን ትርጉም በማጣመም አንድ ህብረተሰብና አገር ወደ ብልግናና መገደያያ፣ ባህለ-ቢስና ልዩ ልዩ ለመንፍስ የሚሰቀንኑ ተግባሮች የሚካሄዱበት መድረክ እንደሆነ በተለይም በኤሊቱ መንፈስ ውስጥ ተቀርጿል። ከመንፈሳዊ የበላይነትና በእግዚአብሄር ከማመን ይልቅ በሰይጣን ማምለክ የኤሊቱ ኖርም በመሆን ሌላውም የህብረተሰብ ክፍል እንዲቀበለው ግፊት እየተደረገ ነው። ከዚህ ውስጥ የእግዚአብሄርንና የተፈጥሮን ህግ የሚፃረረው ግብረሶዶማዊነትና የአቢይ አህመድ አገዛዝ በአለቆቹ በመታዘዝ ተግባራዊ ያደረገው ህግ በቂ ማስረጃ ነው። የካፒታሊስት አገሮች አገዛዝም፣ በተለይም አሜሪካ፣ እንግሊዝና ሌሎችም በዚህ ዐይነቱ ሰይጣናዊ አስተሳሰብ የሚመሩና ግብረሰዶማዊነት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ እንዲሆን የሚገፋፉና የሚያስገድዱም ናቸው። ይህንን የአሜሪካንና የግብረአበሮቹን ሰይጣናዊ የሆነውንና የእግዚአብሄርን አስተሳሰብ የሚፃረር እንደጠላት በመታየት ማዕቀብ ይደረግብታል። ለምሳሌ በሙዘቤኒ የሚመራው የዩጋንዳ አገዛዝና የህዝብ ተጠሪዎች ግብረሰዶማዊነትን የሚቀናቀን ህግ አውጥተዋል፤ በህግም ጸድቋል። ይህንን ይፋ በሆነ መልክ የሚቀሰቅስና በይፋ ተያይዞ የሚሄዱ ወንዶች እስከሞት ድረስ የሚያደርስ ቅጣት ይደርስባቸዋል። ይህም በህገ-መንግስቱ እንዲጻፍ ተደርጓል። ይህንን የሰማው የባይደን አገዛዝ በዩጋንዳ የህዝብ ተጠሪዎች ላይ አሜሪካ እንዳይገቡ ዕገዳ ሲያደርግ፣ የዓለም ባንክ ደግሞ ለዩጋንዳ መንግስት ዕርዳታም ሆነ ብድር እንደማይሰጥ አስታውቋል። ወደኛ አገርና ወደ ጥንታዊቱ የክርስቲያን አገር ስንመጣ ግን ነገሩ የተገላቢጦሽ ሆኗል። በማን አለብኝነትና በአሜሪካን በመታዘዝ አቢይ አህመድ ግብረ-ሰዶማዊነት በህግ እንዲፀድቅና ተቀባይነትም እንዲኖረውም ለማድረግ በቅቷል። በጣም የሚያሳዝን ድርጊት ነው።
ይህንን ካልኩኝ በኋላ ዮናስ ብሩ አቅራቢንና ጠያቂን(Supply & Demand) ከኳንተም ፊዚክስ ጋር በማያያዝ እንደመፍትሄ ያቀረበው ሃሳብ የተሳሳተ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ በኒዎ-ክላሲካል ኢኮኖሚስቶች አስተሳሰብ የአንድ ዕቃ ዋጋ የሚተመነው በአቅራቢና በጠያቂ ህግ መሰረት ነው የሚል አስተሳሰብ ተስፋፍቷል። ይህ ዐይነቱ አስተሳሰብ ግን በአዳም ስሚዝ፣ ሬካርዶና በማርክስ፣ እንዲሁም በስትራፋ ተቀባይነት የለውም። በእነዚህ አራት ኢኮኖሚስቶችና በሌሎችም ጥንታዊ ኢኮኖሚስቶች ዕምነት የዋጋ ምንጭ ወይም መሰረት የሰው ጉልበት ነው የሚል ነው። ራሳቸውም ለምርት ክንዋኔ የሚውሉ ማሽኖች በሙሉ በሰው የማሰብ ኃይልና ጉልበት አማካይነት ነው ሊፈጠሩ የሚችሉት። ወደ ተጨባጭ ነገሮች ስንመጣና በተግባርም ስንመለከት አንድ አምራች ካፒታሊስት ምርቱን ገበያ ላይ አውጥቶ ከመሸጡ በፊት ለጠቅላላው ምርት ያወጣውን ወጭ(Fixed & Variable Costs) ደረጃ በደራጃ ይተምናል። በዚህም መሰረት የእያንዳንዱን ምርት ዋጋ በመተመን ትርፍ ጨምሮበት ለአከፋፋይ ወይም ለተራ ሺያጮች ዕቃዎቹን ይሸጣል። እነሱም በተራቸው የራሳቸውን ውጭና ደሞዝ በማስላት የገዙትን ምርት ይሸጣሉ። ይህም ማለት የማንኛውም ምርት ዋጋ በአቅራቢና በጠያቂ የሚወሰን ሳይሆን ላይ እንደተነተንኩት ለጠቅላላው ምርት ማምረቻ የወጣውን ወጪ በማስላት ብቻ ነው። የአቅራቢና የጠያቂ ህግ ግን እንደገበያው ሁኔታ በምርት ዋጋ ላይ የተወሰነ ተፅዕኖ ሊኖራቸው ይችላል።
ሌላው የዮናስ ብሩ ትልቁ ስህተት በአንድ አገር ውስጥ የሚካሄድ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴና ዕድገት በአቅራቢና በጠያቂ ህግ (The Law of Supply & Demand) ብለው በሚጠሩት ህግ መሰረት እንደሚገዛ ነው። ይህም ህግ የኢኮኖሚ ዕድገት ዋናው መሰረት ነው የሚል በህብረተሰብ ግንባታና በኢኮኖሚ ዕድገት ታሪክ ውስጥ ያልተረጋገጠ ጉዳይ ለመማሪያ በመሆን በየዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ሳይንሳዊና ትክክልም እንደሆነ ይሰጣል። ለምሳሌ የካፒታሊዝምን ከሁለት መቶ ዓመት በላይ የፈጀ የዕድገት ታሪክ በምንመረምርበት ጊዜ በአቅራቢና በጠያቂ ህግ ላይ በመመሰረት እዚህ ዐይነቱ የተወሳሰብ የዕድገት ደረጃ ላይ የደረሰ አይደለም። ካፒታሊዝም እዚህ ዐይነቱ ከፍተኛ የዕድገት ደረጃ ላይ ሊደርስ የቻለውና ዓለም አቀፋዊ ለመሆን የበቃው ብዙ ውጣ ውረዶችን በማለፍ ነው። ከመጀመሪያውኑ ጀምሮ ካፒታሊዝም በስምምነትና ጤናማ በሆነ መልክ ያደገበት ጊዜ አልነበረም፤ የለምም። ዕድገቱና የበላይነትም መቀዳጀቱ የአጋጣሚና፣ ከብዙ ጊዜ ልምድና ሙከራ በኋላ እዚህ ዐይነቱ የዕድገት ደረጃ ላይ የደረሰ ነው። ለምሳሌ ኡልሪከ ኸርማን የምትባለው የጀርመን የታወቀች ኢኮኖሚስት የካፒታሊዝም በአሸናፊነት መውጣት(The Victory of Capitalism) በሚለው ግሩም መጽሀፏና ሌሎችም እንደሚያረጋግጡት ካፒታሊዝም ከመጀመሪያውኑ ታቅዶና ታስቦበት እዚህ ዐይነቱ የዕድገት ደረጃ ላይ እንዳልደረሰ ነው። የሰፊውን ህዝብ የፍጆታ አጠቃቀም(Mass Consumption) ዕድገት ስንመለከት ህዝባዊ የፍጆታ አጠቃቀም እያደገ የመጣው ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት፣ በተለይም ከ1960ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ ነው። እስከዚያ ጊዜ ድረስ አብዛኛዎች የፍጆታ ዕቃዎች እንደቅንጦት ዕቃዎች የሚታዩና በጣም ጥቂቱም፣ በተለይም ከፍተኛ ገቢ ያለው የህብረተሰብ ክፍል ብቻ እየገዛ የሚጠቀምባቸው ነበሩ። አብዛኛዎች ኢንዱስትሪዎች በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እየተደገፉ በፍጥነት ሲያመርቱ የግዴታ የሚመረቱት ምርቶች መሸጥ ስላለባቸው አዳዲስ ዘዴዎች መፈጠር ቻሉ። አብዛኛው ህዝብ ደግሞ እየሰራ በሚያገኘው ገቢ ብቻ ለምሳሌ እንደቴሌቪዥን፣ ማቀዝቀዣ፣ የልብስና የዕቃዎች ማጠቢያ ማሺኖች፣ እንዲሁም መኪናዎችን እየገዛ ለመጠቅም ስለማይችል ባንኮች የብድር ስይስተም(Credit System) ማስፋፋት ጀመሩ። በዚህም ምክንያት የተነሳና የፍጆታ አጠቃቀም እየተለመደ ሲመጣና፣ በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች በመደገፍ ምርታማነትን ማሳደግ ሲቻልና የማምረቻ ዋጋም ሲቀንስ የሚመረቱ ምርቶችን መሸጡ እየተለመደና አዳዲስ ምርቶችንም መጠቀም እንደዘመናዊነት እየታየ መጣ። አምራቾችም የፍጆታ ዕቃዎችን ባማረ መልክ ማምረት ሲጀምሩና፣ በየጊዜውም ለምሳሌ የመኪናዎች ዲዛይን ሲቀየሩና ለመንዳትም አመቺ እንዲሆኑ ሲያደርጉ ተጠቃሚው ኃይል ቆንጆ ሆነው በሚመረቱና ለገበያ በሚቀርቡ የፍጆታ ዕቃዎች ሲማረክ የመግዛት ፍላጎቱም እያደገ መምጣት ቻለ። ሌሎችም እንደስማርት ፎን የመሳሰሉት የሰውን መንፈስ የመሳብ ኃይል እንዲኖራቸው ሆነው ስለሚመረቱ ተጠቃሚው፣ በተለይም ወጣቱ የመግዛት ፍላጎቱ እያየለ ሊመጣ ቻለ።ከዚህም በላይ አምራቾች ምርቶቻቸውን ለመሸጥ ሲሉ ልዩ ልዩ ማራኪ ማስታወቂያዎችን(Advertisement) በቴሌቪዥንም ሆነ በሬዲዮ ስለሚያስተላልፉ በዚህ ዐይነቱ ማራኪ ማስታወቂያ የሚታለለው ሰው በዚህም በዚያም ብሎ የፍጆታ ፍላጎቱን ለማሟላት ሲል መሯራጥ ጀመረ። ይህ በራሱ በምርት ክንዋኔ፣ በፍጆታ አጠቃቀምና በባንኮች መሀከል ልዩ ዐይነት ግኑኝነት በመፍጠር ለጠቅላላው ኢኮኖሚ ዕድገት አመቺ ሁኔታን ሊፈጥር ቻለ። በምርት፣ በገቢና በፍጆታ አጠቃቀም(Production, Income Distribution, Consumption) መሀከል ልዩ ዐይነት ግኑኝነት በመፈጠር አጠቃላይ የሆነ የኢኮኖሚ ዕድገት ሊመጣ ቻለ። የገንዘብም የመሽከርከር ኃይል ሲጨምር(Velocity of Money) አጠቃላይ የሆነ የሀብት ክምችት ሊፈጠር ቻለ። በሌላ አነጋገር፣ በተለያዩ ኢንዱስትሪዎች መሀከል ያለው መተሳሰር ሲጠነክር፣ በዚያው መጠንም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን መፍጠር ተቻለ። ለካፒታሊዝም መስፋፋትና ማደግ በኢንዱስትሪዎች መሀከል ያለው የስራ ክፍፍልም በጣም ወሳኝ ነው። በማርክስ አገላለጽ እነዚህም ክፍል አንድና (Department I) ክፍል ሁለት(Department II) በመባል ይታወቃሉ። በክፍል አንድ የተለያዩ የምርት ማምረቻ ማሺኖች ወይም ኢንዱስትሪዎች ይመረታሉ። ለማሺኖች መመረት ደግሞ የግዴታ የብረታ ብረት ፋብሪካና ማሺኖችን ዲዛይን የሚያደርግ ልዩ ክፍል አለ። በዚህ ክፍል የተመረቱት ማሺኖች ወይም ኢንዱስትሪዎች ልዩ ልዩ ምርቶችን ለማምረት ለአምራች ካፒታሊስቶች ይሸጣሉ። እንደየፍላጎታቸውና፣ እንደ ሀብት ወይም ካፒታል መጠናቸው የተለያዩ ኢንዱስትሪዎችን ገዝተው ልዩ ልዩ የረዥም ጊዜና የአጭር ጊዜ ዕድሜ ያላቸውን ምርቶችን በማምረት ለተጠቃሚው ያቀርባሉ። በሌላ ወገን ደግሞ ለምሳሌ በክፍል አንድ ውስጥ ተቀጥሮ የሚሰራው ሰራተኛ በክፍል ሁለት ውስጥ የሚመረተውን ልዩ ልዩ የፍጆታ ዕቃዎችን በመግዛት ይጠቀማል። በዚህ መልክ ሰራተኛው ልዩ ልዩ የፍጆታ ዕቃዎችን እየገዛ ሲጠቀም ከክፍል ሁለት በገበያ አማካይነት ገንዘብ ወደ ክፍል አንድ ይተላለፋል። ካፒታሊስቶችም የበለጠ ተወዳዳሪ ለመሆን ሲሉ የተወሰነውን ትርፍ ለመዋዕለ-ነዋይ ያውሉታል። ውድድር ራሱ የካፒታሊዝም ዋናው አንቀሳቃሽ ኃይል ስለሆነ አንደኛው ካፒታሊት ከሌላው በልጦ ለመገኘት ሲል የተሻለ ምርት በማምረት ለተጠቃሚው ያቀርባል። ባጭሩ የካፒታሊስት ኢኮኖሚ በዚህ ዐይነቱ የስራ-ክፍፍልና መተሳሰር ነው የሚሰራው። ይህም የሚያረጋግጠው ዮናስ ብሩ ሊያሳምነን እንደሚሞክረው የአንድ አገር የኢኮኖሚ ክንዋኔና ዕድገት በአቅራቢና በጠያቂ ህግ ብለው በሚጠሩት እንደማይሰራ ነው።
ከዚህ አጠር መጠን ያለ ሀተታ በአቅራቢና በጠያቂ ህግ ብለው በሚጠሩት ላይ በመመርኮዝ ሳይሆን ኢኮኖሚው ሊያድግ የሚችለው በተጠናና የሰፊውን ህዝብ መሰረታዊ ፍላጎት ሊያሟላና ሰፊውንም ህዝብ ሊያስተሳሰር የሚችል ሰፋ ያለ በማኑፋክቸሪንግ ላይ የተመሰረተ ምርታዊ ክንዋኔ ሲታቀድና ተግባራዊም ሲሆን ብቻ ነው። በተለይም ትናንሽና ማዕከለኛ ኢንዱስቱሪዎች እንደ አሸን መፍለቅ ሲኖርባቸው፣ እነዚህ ደግሞ በምርምርና በጥናት መደገፍና መደጎም አለባቸው። መንግስት የሳይንስና የቴክኖሎጂ የምርምር ጣቢያዎችን በየቦታው በማቋቋም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችና የምርት ማምረቻ መሳሪያዎች ሊመረቱና ለአምራቹ ኃይል በተመጣጣኝ ዋጋ ሊሸጡ የሚችሉበት ሁኔታ እንዲፈጠር ማድረግ አለበት። ለዚህ ዐይነቱ ጤናማና ሁለ-ገብ ዕድገት ደግሞ የሰለጠነና በመጀመሪያ ደረጃ ሰላምን የሚያስቀድም መንግስትና አገዛዝ በጣም አስፈላጊና ወሳኝም ነው። ይህ ዐይነቱ አገዛዝና መንግስትም ከወጭ ኃይሎች ቁጥጥር ነፃ የሆነና በራሱ አስተሳሰብና በምሁራንና በተመራማሪዎች የሚመራ መሆን አለበት። ዞሮ ዞሮ ለዚህ ደግሞ ከፍተኛ ንቃተ-ህሊናና የአገር ወዳድነት ስሜት እንዲኖር ያስፈልጋል። በኳንተም ፊዚክስ ላይ የተመሰረተው ኳንተም ሶሻል ሳይንስና ኳንተም ኢኮኖሚክስ መሰረተ ሃሳብም በዚህ ላይ የሚመረኮዝና የመንፈስን የበላይነት የሚያስቀድም ነው።
ይህንን ካልኩኝ በኋላ ዮናስ ብሩ ሌላው ያነሳው የብሄራዊ ዕርቅና ንግግር ጉዳይ አለ። ዮናስ ብሩ ማን ከማን ጋር እንደሚነጋገርና፣ ማን ከማን ጋርስ እርቅ እንደሚያደርግ ግልጽ አላደረገልንም። ሌላው ዮናስ ብሩ ሊገነዘብ ያልቻለው ድንቁርና ባየለበት አገርና፣ በደመ-ነፍስ በመመራት ዘር-ተኮር እልቂት በሚፈጸምበት አገር ውስጥ ማን ከማን ጋር ቁጭ ብሎ እንደሚነጋገር ግልጽ ለማድረግ አልቻለም። ወያኔም ሆነ የዛሬው በአቢይ አህመድ የሚመራው አገዛዝና፣ ጠቅላላው የኦሮሞ ኤሊት ነኝ የሚለው ሁሉ አገራችንና ህዝባችንን፣ እንዲሁም ታሪካችንና ባህላችንን እንደዋና ጠላት በማየት ወያኔ 27 ዓመት ያህል፣ አቢይ አህመድና ግብረአበሮቹ ደግሞ ባለፉት ስድስት ዓመታት ሲያሰቃዩት የኖሩ ናቸው። ከዚህ ሀቅ ስንነሳ እስካሁን ድረስ በአገራችን ምድር የሚካሄደው ጦርነትና ግብግብ ከተጨባጭ ሁኔታ የራቀ፣ ታሪካዊ መሰረትና ማስረጃ የሌለውን የየራሳቸውን አጀንዳ ይዘው ጭቅጭቅ በሚፈጥሩ ደንቆሮ ኃይሎች መሀከል ነው። በሌላ ወገን ግን እነዚህ ሁለት ኃይሎችም ሆነ ቀደም ብለው የነበሩ ልዩ ልዩ ኃይሎች የህዝባችንና የአገራችን ጠላት በመሆን አገራችንን አሁን ያለችበት እጅግ የሚዘገንን ሁኔታ ውስጥ እንድትወድቅ ለማድረግ በቅተዋል። እነዚህ ኃይሎች ደግሞ በተለያዩ ጊዜያት ከውጭ ኃይሎች ጋር በመቆላለፍና አጀንዳ አስፈጻሚ በመሆን በህዝባችን ላይ ዕልቂት የሚያወርዱና ምስቅልቅል ሁኔታዎችን የፈጠሩና የሚፈጥሩም ናቸው። ስለሆነም ዮናስ ብሩ እነዚህን ነገሮች በሚገባ ቢገነዘብ ኖሮ የብሄራዊ ውይይትና ዕርቅን ጉዳይ በፍጹም ባላነሳ ነበር። እንደዚህ ብሎ ማሰብም ወያኔም ሆነ የዛሬው የአቢይ አህመድ አገዛዝ የፈጸሟቸው ወንጀሎች በሙሉ ትክክል ናቸው ብሎ አምኖ እንደመቀበል ይቆጠራል። ይህም ማለት ነፍሰ-ገዳዮችን፣ የአገርን ባህል ያወደሙና የታሪክ ወንጀል የፈጸሙ፣ የውጭ ኃይሎችን አጀንዳ ያስፈጸሙና አገራችንን ወደ ምስቅልቅል ሁኔታ ውስጥ በመክተት ሁሉንም ነገር ያዘበራረቁ፣ በገዢ መደብ ስም ሁሉንም ማድረግ የሚችሉ መስሏቸው እዚህ ዐይነቱ ሁኔታ ውስጥ እንድንወድቅ ያደረጉንን ኃይሎች በሙሉ በይቅርታ መታለፍ አለባቸው ማለት ነው፤ ከደሙ ንጹህ በመሆን እንደገና ለገዢነት ይታጩ እንደማለት የሚቆጠር ነው። የእነዚህ ዐይነት ሰዎችን ንቃተ-ህሊና ደግሞ እንደገና እንዲያንሰራራና እንደሰው እንዲያስቡ ማድረግ አይቻልም። መንፈሳቸው የደነዘዝ ስለሆነና ማንኛውም የሰው ልጅ ሊኖር የሚገባው ባህርይ ከጭንቅላታቸው ውስጥ ተሟጦ ያለቀ ስለሆነ፣ ወይም ከመጀመሪያውኑ አብሯቸው ያልተፈጠረ በመሆኑ ከእነዚህ ሰዎች ጋር ቁጭ ብሎ መነጋገር በፍጹም አይቻልም። በምንስ ቋንቋ ነው መግባባት የሚቻለው? ስለሆነም የዮናስ ብሩ ሃሳብ ውድቅ ነው። ካለብዙ የጭንቅላት ማውጣትና ማውረድ በኋላ የተጻፈ ጽሁፍ አይደለም። የአገራችንንም ሆነ የዓለም አቀፍን ሁኔታ በሚገባ ያገናዘበ አይደለም።
ሌላው የዮናስ ብሩ የተሳሳተ ግንዛቤ የአገራችንን ዕድል ሊወስን የሚፈልገው ከአሜሪካን ኤምፔሪያሊዝም ጋር በማያያዝና የኢትዮጵያን ህዝብ የአሜሪካ አሽከር አድርጎ በማየት ነው። የዓለም ኮሙኒቲው እያለ የሚጠራው ኢ-ሳይንሳዊ አባባል አለ። ይህ ዐይነቱ አስተሳሰቡም ስለ ግሎባል ካፒታሊዝምና ስለ ኢምፔሪያሊዝም ያለውን የተጣመመ ወይም የተሳሳተ አስተሳሰብ የሚያረጋግጥ ነው። ኳንተም ፊዝክስም ሆነ የኢንላይተንሜንት አስተሳሰብ ይህን ዐይነቱን ኢምፔሪያሊስታዊ አስተሳሰብና ድንጋጌ ይቃወማሉ። በኳንተም ፊዚክስም ሆነ በኢንላይተንሜንት አስተሳሰብ እያንዳንዱ ግለሰብ ነፃ ነው። በተለይም ደግሞ የሰው ልጅ በእግዚአብሄር አምሳል የተፈጠርና፣ አንደኛው ከሌላው የማይበልጥ ስለሆነ ማንኛውም ሰው ሆነ ድርጅት በአንድ ግለሰብና በአንድ አገር ላይ የመወሰን መብት የላቸውም። ሁሉም የሰው ልጅ በእግዚአብሄርና በህግ ፊት እኩል ናቸው። ይሁንና ግን በአንድ አገር ውስጥ ጠቅላላውን ህዝብ የሚጠቅምና መብቱንም የሚያስጠብቅ ህገ-መንግስት ካለና፣ በተግባርም የሚመነዘር ከሆነ እያንዳንዱ ግለሰብ ህገ-መንግስቱን የማክበር ግዴታ አለበት። በሌላ ወገን ደግሞ የራሱን ህግ-መንግስት እየጣሰ የፈለጉትን ነገር አደርጋለሁ ብሎ የሚያስብ አገዛዝ ስልጣን ላይ ካለ አንድ ህዝብ በተባበረ ክንድ እንደዚህ ዐይነቱን በማንአለኝበት የሚመራ አገዛዝ ከስልጣኑ የማስወገድ መብት አለው፤ በህገ-መንግስት እያሳበቡ አገርን ማተራመስና ህዝብን መጨፍጨፍ አይቻልም።
ከዚህ ሀቅ ስንነሳ፣ የአገራችንን ሁኔታ ወደጎን በመተው ወደ አሜሪካ ስንመጣ በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የሚበወዘው ዓለም የኳንተም ፊዝክስን፣ የኢንላይተንሜንትን አስተሳሰብና የእግዚአብሄርን ህግ የሚፃረር ነው። እያንዳንዱ አገር በራሱ ጥረት፣ ዕውቀትና ልምድ በመነሳት ከታች ወደላይ ቀስ በቀስ መውሰድ የሚገባውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግንባታ የሚቃወምና፣ ከእኔ ትዕዛዝ ውጭ ማድረግ የለብህም እያለ የሚያስፈራራ ነው። በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና በግብረ-አበሮቹ ዕምነት ማንኛውም አገር በአንድ ህግ(Rule Based System) መመራት አለበት። የሜሪካንና የግብረአበሮቹን የበላይነት መቀበል አለበት። በራሱ የማሰብ ኃይል በነፃ ማሰብና የመፍጠር መብት የለውም። ይህንን የኢምፔሪያሊስቶችን ሰይጣናዊ ህግ የማይቀበል የፍየል ወጠጤ ይዘፈንበታል። ባጭሩ የቦምብ ናዳ ይወርድበታል። ከዚህ አጠር መጠን ያለ ትንተና ስነሳ ዮናስ ብሩ ያነሳው የኳንተም ፊዚክስ አስተሳሰብ መልካም ቢሆንም በተጣመመ መልክና ግልጽ ሳያደርግ ማቅረቡ አብዛኛውን ህዝብ ግራ እንዲጋባ ለማድረግ በቅቷል። በምክንያቶችና በውጤታቸው መሀከል ያለውን ልዩነት፣ እንዲሁም በነገሮች መሀከል ያለውን መተሳሰር በሚገባ ቁልጭ አድርጎ ለማቅረብ ያልቻለ ነው። አብዛኛው አንባቢም ኳንተም-ፊዚክስ የሚባለውን ፅንሰ-ሃሳብ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲያነብ ግራ መጋባቱ የማይቀር ነው። ስለሆነም አንዳንድ ጽሁፎችን ስንጽፍና የማይታወቁ ፅንሰ-ሃሳቦችንም በምንጠቀምበት ጊዜ አንባቢያን በሚረዱት መልክ መጻፉ ወይም ግልጽ ማድረጉ ከግራ መጋባት ሊያድነን ይችላል የሚል ዕምነት አለኝ። መልካም ግንዛቤ!!
Aglietta, Michel(1979): A Theory of Capitalist Regulation. Th US Experiece,
London
Alfred Korzybski; (19021) Manhood of Humanity: The Science and Art of Human
Engineering, New York
Alexander Wendt;(2004) Social Theory as Cartesian Science: An Auto-Critique
from a Quantum Perspective, Ohio State University.
Amit Gosawami (2009): How Quantum Activism Can Save Civilization,
Charlottesville.
Artur Bogner(1989): Zivilization and Rationalization: The Theory of Civilization by Max Weber, Norbert Elias, and the Frankfurt School, Darmstadt.
Samir, Amin(1974): Accumulation on a World Scale: A Critique of the Theory of
Underdevelopment, New York & London
Tamara van Halm & Michael Byrnes,(2010) Quantum Economis Initiative www
powerofone.org
https://www.marxist.com/quantum-society.htm; Quantum Physics, dialectics and
society: from Marx and Engels to Khrennikov and Haven.
ማሳሰቢያ፤ እንደዚህ ዐይነቱን ሳይንሳዊ ጽሁፍ ለማቅረብ ብዙ ጥናትና ትግስት ይጠይቃል። የራስንም ጊዜ ይፈጃል። እንደሚታወቀው በካፒታሊስት አገሮች ውስጥ ጸሀፊዎች ሳይንሳዊ ጽሁፍ ሲያቀርቡ ይከፈላቸዋል። የራሳቸው ድረ-ገጽ ያላቸው ከሆነ ደግሞ ይደገፋሉ። በአገራችን ምድር ግን ይህ ዐይነት ልምድ ስለሌና አንድ ሰው እንደዚህ ዐይነቱን ሳይንሳዊ ጽሁፍ ሲጽፍ ዝም ብሎ የሚለቀልቅ ይመስል ዝም ብሎ ይታለፋል። ባጭሩ እንደዚህ ዐይነት ሳይንሳዊ ጽሁፎች ሲጻፉ ጸሀፊውን ለማበረታታት ሲባል በፈቃደኝነት መደገፍ አለባቸው። ይህ ጸሀፊ መጽሀፎችም ጽፎ ትንሽ ከተሸጠ በኋላ ብዙ ጊዜንና ገንዘብን የፈጁ መጽሀፎች ተወዝፈዋል፤ ወይም ሳይሸጡ ተቀምጠዋል። ይህ ጸሀፊ በዚህ ዐይነቱ ሳይንሳዊ ትንተናው እንዲቀጥል ከተፈለገ ድረ-ገጹ ውስጥ በመግባት ዶኔት የሚለውን በመጫን መጠነኛ ገንዘብ መለገስ ይቻላል። ይህ ሲሆን ብቻ በተከታታይ ጥናታዊና ለአገር ግንባታ የሚሆኑ ጽሁፎችን ማቀረብ ይቻላል። የዚህን ጸሀፊ የአጻጻፍ ስልት በሚገባ ለተከታተለ በዐይነትም ሆነ በስልት ከሌሎች ይለያል። ጥያቄዎችን በማንሳት መፍትሄም ለመፈልግ የሚያስችል የአጻጻፍ ስልት ነው።