October 16, 2023
16 mins read

“የሰንሹ የጦርነት ጥበብ” በሚል ርዕስ በመስፍን አረጋ ከተዘጋጀው መጽሐፍ የተቀነጨበ

የሰንሹ የጦርነት ጥበብይህ ጽሑፍ “የሰንሹ የጦርነት ጥበብ” በሚል ርዕስ በመስፍን አረጋ ከተዘጋጀው መጽሐፍ የተቀነጨበ ነው።

____________________________

ሰንሹ ወይም ሰንዙ (Sun Tzu) የሚባለው ግለሰብ  (Wu) በሚባለው ያሁኒቷን ሻንግሃይን በሚያጠቃልለው በታላቁ በያንግዚ (Yangzi) ወንዝ አፍ ላይ በሚገኘው የቻይና ምሥራቃዊ ግዛት ውስጥ በ 550 ዓ.ዓ አካባቢ የተወለደና “የጦርነት ጥበብ” (Art of War) የተሰኘውን መጽሐፍ የጻፈ የጦር አዛዥ፣ ወታደራዊ ትልመኛ (military strategist) እና ፈላስፋ ነው ተብሎ ይታመናል።  የሰንሹ የውልደት ስሙ ሰንው (Sun Wu) ሲሆን፣ ሰንዙ (Sun Tzu) ማለት ደግሞ ትርጉሙ አለቃ ዙ (master Sun) ማለት የሆነ የክብርና የማዕረግ ስም ነው፣ አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ፣ አለቃ ደሰታ ተክለወልድአለቃ ከበደ ሚካኢል እንዲሉ።

ባፈታሪክ መሠረት፣ ሰንሹ የጦርነት ጥበብ የተሰኘውን መጽሐፉን ከጻፈ በኋላ የ  (Wu) ግዛት ንጉስ የነበረው ሆሉ (Ho Lu) ወደ ቤተመንግስቱ ያስጠራውና “መጽሐፍህን አንብቤው ወደጀዋለሁ።  የበለጠ ትኩረቴን የሳበው ደግሞ ወታደሮችን ትእዛዝ አካባሪ ስለማድረግ ያወሳህበት ክፍል ነው።  በዚህ ክፍል ላይ የጠቀስካቸው ዘዴወች በርግጥም መሥራት አለመሥራታቸውን እዚህ እፊቴ ባጭር ምሳሌ በተግባር ልታሳየኝ ትችላለህ?” በማለት ይጠይቀዋል።

“በሚገባ” አለ ሰንሹ፣ ደረቱን ነፍቶ በመኩራራት።

“በሴቶች ላይ?” አለ ንጉሱ፣ በመጠራጠር ቅላጼ።

“እንዴታ፣ ምን ችግር አለው?” አለ ሰንሹ፣ የንጉሱን መጠራጠር ቸል በማለት።

ንጉሱም በቤተመንግስቱ ውስጥ ከሚገኙት አያሌ ውብ ሴቶች ውስጥ ፐውብ (ማለትም ይበልጥ ውብ፣more beautiful) የሆኑት ሃያወቹ ተጠርተው ከሰንሹ ፊት እንዲቀርቡ አዘዘ።  ሰንሹም ሃያወቹን ሴቶች (አስር አስር ሴቶችን ባካተቱ) በሁለት ቡድኖች ከፈላቸውና ቡድኖቹን አንደኛ ጭሬ (squad, squadron) እና ሁለተኛ ጭሬ ብሎ ሰየማቸው።  ከንጉሱ ቁባቶች (ማለትም ቅምጦች) ውስጥ በንጉሱ ይበልጥ ተወዳጅ የሆኑትን ሁለቱን ዥውብ (ማለትም እጅግ በጣም ወብ፣ most beautiful) ሴቶች ደግሞ ጭሬ አዛዥ (squad commanders) አደረጋቸው።

ቀጠለና ደግሞ ሁለቱን ጭሬ አዛዦች ከፊት ለፊት አድርጎ ሁለቱን ጭሬወች በሁለት ረድፍ (row) ከረደፋቸው በኋላ ሶማያ (በላይ ጦር፣ በታች ጅንፎ የተዋደደበት ዘንግ) ለሁሉም ሴቶች /አድሎ/ (አከፋፍሎ) አያያዙን ደጋግሞ አሳያቸው።

“ደረትና ጀርባ በየት በኩል እንደሆኑ ታውቃላችሁ?” አለ ሰንሹ፣ በሶማያ አያያዝ እንደተካኑ ካረጋገጠ በኋላ ።  ሴቶቹም “ምን ዓይነት ብሽቅ ጥያቄ ነው፣ ሕጻን አደረገን እንዴ” በሚል እሳቤ ሳቃቸውን በግድ አፍነው “አወ፣ እናውቃለን” አሉት።

“ግራና ቀኝስ በየት በኩል እንደሆኑ ታውቃላችሁ?” አለ ሰንሹ፣ የሴቶቹን ፌዝ ከቁብ ሳይቆጥር።

“አወ” አሉ ሴቶቹ፣ ሳቃቸው ይበልጥ እየተናነቃቸው።

“በጣም ጡሩ” አለ ሰንሹ፣ በተረጋጋ መንፈስ ኮራ ብሎ።  “አሁን እንግዲህ የምሰጣችሁን ትእዛዞች ወለም ዘለም ሳትሉ ማክበር አለባችሁ።  ደረት ስል ወደ ፊት፣ ጀርባ ስል ወደኋላ፣ ግራ ስል ወደ ግራ፣ ቀኝ ስል ደግሞ ወደ ቀኝ ዙሩ።  ትዛዜ በትክክል ገብቷችኋል?”

“አወ ገብቶናል”

“ወታደሮቸ የታዘዙትን ለመፈጸም ዝግጁ ናቸው” አለ ሰንሹ፣ አልፍኝ ተቀምጦ በግርምት ያስተውለው ወደነበረው ንጉስ ዙሮ እጅ ከነሳ በኋላ።

“አሳየና” አለ ንጉሱ፣ በጥርጣሬ ቅላጼ

ሰንሹ የሥራ ውጤቱን ለንጉሱ ላማሳየት በመጓጓት ነጋሪቱን ሦስት ጊዜ ከጎሰመ በኋላ “ቀኝ” አለ።

ሴቶቹ ግን እንደታዘዙት ወደ ቀኝ በመዞር ፋንታ ሳቃቸውን አፈንድተው ሰውነታቸውን እያንዘፈዘፉ በቆሙበት ይንከተከቱ ጀመር።

ሰንሹ ግን የሴቶቹ ሳቅና ስላቅ ግድ ሳይሰጠው “ወታደሮቹ ትዕዛዙን በትክክል ካልተረዱ፣ ጥፋቱ ያዛዡ ነው” አለና፣ ትዛዙን እንደገና ሦስት ጊዜ ከደጋገመ በኋላ “ትዛዜ በትክክል እንደገባችሁ እርግጠኞች ናችሁ?”  ብሎ ጠየቀ።

“አወ እርግጠኞች ነን” አሉ ሴቶቹ።

“እርግጠኞች ናችሁ?”  በማለት በድጋሚ ጠየቀ፣ ሰንሹ።

“አወ እርግጠኞች ነን” አሉ ሴቶቹ፣ በተሰላቸ ስሜት ባንድነት በመናገር።

“በጣም ጡሩ” አለና ነጋሪቱን ሦሰት ጊዜ ከጎሰመ በኋላ “ቀኝ” ብለ አዘዘ።

ሴቶቹ ግን እንደታዘዙት ወደ ቀኝ በመዞር ፋንታ በሳቅ ፈነዱ፣ ሰልፋቸውም ፈርሶ ተመሰቃቀለ።

ሰንሹም ቆጣ፣ ቆፍጠን ብሎ “ትእዛዞቸ ግልጽ ካልተደረጉ ያዛዡ ጥፋት ነው።  ትእዛዞች ግልጽ ተደርገው በትክክል ካልተፈጸሙ ግን የመስመር መኮንኖች ጥፋት ነው” አለና፣ ሁለቱ ጭሬ አዛዦች እንዲሰየፉ (በሰይፍ እንዲመተሩ) አዘዘ።

ንጉሱም የሰንሹ የስየፋ ትዛዝ ሰቀጠጠውና “በቃህ፣ በቃህ፣ አቁም።  ወታደሮችን ትዛዝ አክባሪ ማድረግ እንደምትችል አይቸልሃለሀ።  እነዚህ ሁለት ሴቶች ግን ነፍሶቸ ስለሆኑ እንዲሞቱብኝ ቀርቶ እንዲጎዱብኝ አልፈልግም” አለ።

ሰንሹ ግን “ንጉስ አዛዥ እንጅ ፈጻሚ አይደለም።  ማናቸውም የጦር አዛዥ አንዴ ግዳጅ ከተሰጠው በኋላ አፈጻጸሙን ሙሉ በሙሉ የሚቆጣጠረው እሱ ራሱ ብቻ ነው” አለና፣  ለቀሩት ሴቶች መቀጣጫ እንዲሆኑ የሁለቱን ሴቶች አንገት ሰይፎ ከነሱ የሚቀጥሉትን ሁለቱን ሴቶች ጭሬ አዛዥ አደረጋቸው።

ከዚህ በኋላ ሴቶቹ ቀሉ፣ ሰሉ፣ ተገሩ፣ ሾሩ።  ቀኝ ሲል ወደ ቀኝ፣ ግራ ሲል ወደ ግራ እየዞሩ የታዘዙትን ሁሉ ወለም ዘለም ሳይሉ በቅልጥፍናና በትክክል መፈጸም ጀመሩ።  ሳቅና ስላቅ በሰጥ ለጥ ተተካ።  ሰንሹ አዛዥ፣ ናዛዥ ሆነ።

“ወታደሮቸ የታዘዙትን ሁሉ በሙሉ ልብ ለመፈጸም ሙሉ ዝግጁ ናቸው” አለ ሰንሹ፣ የሰንሹ ድርጊት ወደ ሰቀጠጠው ንጉስ ዙሮ እጅ ከነሳ በኋላ።  “ከእልፍኝወ ይውረዱና ይዘዟቸው።  ገደል ግቡ ቢሉ ቢሏቸው ሳያንገራግሩ ገደል ይገባሉ።”

“በል በቃህ።   አሁን ወደ ቤትህ ሂድ።  እንኳን የተረፉትን ገደል ግቡ ልላቸው፣ የሞቱትም ቆጭቶኛል” አለ ንጉሱ፣  በመቀፈፍ ስሜት ፊቱን ከሰንሹ በማዞር።

“ታዲያ ሴቶቸን ታዛዥ አድርግ ብለህ ለምን አዘዘከኝ?” አለ ሰንሹ፣ በቅሬታ ስሜት ንጉሱን አንተ በማለት።  “ለማዘዘህ እንጅ ትዛዝህ ለመተግበር አለመተግበሩ ግድ ከሌለህ ንጉስነትህ ምኑ ላይ ነው?”

ንጉሱም የሰንሹን ወታደራዊ ብቃት በመረዳት በመስክ ኦላሳ (field marshall) ማዕረግ የጦሩ ዋና አዛዥ አደረገው።  ሰንሹም ኃያላን የሚባሉትን የንጉሱን አጎራባች መንግስታት ተራ በተራ ድል በመንሳት የንጉሱን ግዛት አስፋፍቶ የተፈራና የተከበረ ታላቅ ግዛት አደረገው።

የሚከተለው ደግሞ “ትንሽ ሰጥቶ ትልቅ መቀበል” የሚሰኘውን የሰንሹን የጦርነት መርሕ የተመለከተ አፈታሪክ ነው።

ከንጉስ ሆሉ (Ho Lu) ተወዳጅ መዝናኛወች ውስጥ አንዱ ከታላላቅ መሳፍንትና መካንንት ጋር የፈረስ እሽቅድድም ቁማር መጫወት ነበር።  ከዕለታት ባንዱ ቀን ንጉሱና አንድ ታላቅ መስፍን እያንዳንዳቸው ምርጥ የሚሏቸውን ሦስት ፈረሶች አቅርበው፣ በምርጥ ጉደጮች (ጋላቢወች፣ jockey) እያስጋለቡ አሽቀዳድመው፣ ተሸናፊ ምርጥ ቁባቱን ለአሸናፊ አሳልፎ ለመስጠት ተስማሙ።  ንጉሱም ሥርቁባቱን እጅግ ያፈቅራት ነበርና አሳልፎ እንዳይሰጣት በመሰጋት ውድድሩን የሚያሸንፍበትን ዘዴ እንዲጠቁመው ሰንሹን ጠየቀው።

“ሰንሹ፣ መጽሐፍህን እንዳነበብኩትና እንደገባኝ ከሆነ፣ በመጽሐፉ ውስጥ የተካተቱት ዘዴወች ለጦርነት ብቻ ሳይሆን በጦርነት ሊመሰሉ ለሚችሉ ማናቸውም ድርጊቶች (ንግድ፣ ስፓርት፣ ፖለቲካ ወዘተ.) የሚያገለግሉ ናቸው።  ስለዚህም ያንተን ዘዴወች በመጠቀም ይህን ውድድር የማሸንፍበትን መንገድ ልትጠቁመኝ ትችላለህ?”

“በደስታ” አለ ሰንሹ፣ በደስታ ስሜት ፊቱን አፍክቶ።  “ነገር ግን ዘዴውን ልጠቁምህ የምችለው የሁለታችሁንም ፈረሶች ጥንካሬወችና ድክመቶች በደንብ ከለየሁ በኋላ ነው።”

“የማሸነፊያውን ዘዴ ጠቁመኝ እንጅ፣ ያሻህን አድርግ” አለ ንጉሱ።

ሰንሹም በመጀመርያ ሦስቱን የንጉሱን ፈረሶች በእውቅ ጉድጮች (ጋላቢወች) አስገምግሞ ጥንካሬወቻቸውንና ድክመቶቻቸውን አጣርቶ አወቀ።  ቀጠለና ደግሞ ሦስት እርስ በርስ የማይተዋወቁ እውቅ ጉደጮችን ሰላይ እንዳደረጋቸው ሳያውቁ ሰላይ አድርጎ በተለያዩ ጊዜወች ወደ መስፍኑ በመላክ፣ እያንዳንዱ ሰላይ ሦስቱንም የመስፍኑን ፈረሶች እንዲገመገም ካደረገ በኋላ፣ ግምገማወቻቸውን እያመሳከረ በማገናዘብ ስለ መስፍኑ ፈረሶች ጥንካሬወችና ድክመቶች በደንብ ተረዳ።  በዚህም አንደኛው የንጉሱ ፈረስ፣ አንደኛ ከሚባለው የመስፍኑ ፈረስ ጋር፣ ሁለተኛው የንጉሰ ፈረስ፣ ሁለተኛ ከሚባለው የመስፍኑ ፈረስ ጋር፣ ሦስተኛው የንጉሱ ፈረስ ደግሞ ሦስተኛ ከሚባለው የመስፍኑ ፈረስ ጋር ከሞላ ጎደል አቻ እንደሆኑ ተገነዘበ።

“እህሳ” አለ ንጉሱ፣ ሰንሹ በንጉሱና በመስፍኑ ፈረሶች ድክመቶችና ጥንካሬወች ላይ ያካሄደውን ጥልቅና ሰፊ ጥናት ማጠናቀቁን ሲነግረው።

“አርግ የምልህን ካደረክ ያለ ምንም ጥርጥር ታሸንፋለህ” አለ ሰንሹ።

“ለማሸነፍ ስል የማላረገው የለም” አለ ንጉሱ፣ የማሸነፍ ጉጉቱ በፊቱ ላይ ጎልቶ።

“ያንተን ሦስተኛ ደረጃ ፈረስ፣ ከመስፍኑ አንደኛ ደረጃ ፈረስ ጋር፣ ሁለተኛ ደረጃ ፈረስ ከመስፍኑ ሦስተኛ ደረጃ ፈረስ ጋር፣ አንደኛ ደረጃ ፈረስ ደግሞ ከመስፍኑ ሦስተኛ ደረጃ ፈረስ ጋር አጋጥማቸው።

ንጉሱም ሰንሹ እንደመከረው በማደረግ የመጀመርያውን ወድድር ተሸንፎ የሚቀጥሉትን ሁለቱን በማሸነፍ አጠቃላይ አሸናፊ ሆነ።

“አሳይቶ መንሳት ይሉሃል ይሄ ነው።  ትልቁን ለማስገበር ትንሹን መገበር” አለ ሰንሹ፣ ንጉሱ ምስጋናውን ሲገልጽለት ኮራ፣ ጀነን ብሎ።

 

 

መስፍን አረጋ

mesfin.arega@gmail.com

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop