የድሮው ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፣ ባጭር ቋንቋ የትውልድ መምሕር ነበር፡፡ የተዋጣለት ሰባኪና ጸሐፊ ነበር፡፡ እንዲህ እንዳሁኑ የናዚዝም አረንቋ ውስጥ ተዘፍቆ ጨለማ ኮከብ ሳይሆን በፊት፣ እንደአብዛኞቹ የኔ ዘመን ወጣቶች አክባሪው ፣ተማሪው ነበርኩ፡፡ ጽሁፎቹን አንብቤ፣ ስብከቶቹን አዳምጬ አልጠግባቸውም ነበር፡፡ የሱን ስብከት ለመስማት ከቤተ ክርስትያን ቤተክርስትያን ተዛዙሬአለሁ፣ በሱ ምክንያት ጥቂት ከማይባሉ ጓደኞቼ ጋር ተጋጭቻለሁ፡፡ስለሱም ጽፌአለሁ፡፡ ወዘተ፣ አሁን ግን በዛ፡፡ አወዳደቅና አሰባበርም ልክ አለው፡፡ በዚህ ደረጃ ሲዘቅጥ ግን ዝም ማለትም ወንጀል መስሎ ታየኝ፡፡
ሰው ሰውን አይገድልም፡፡ ሰው ፣ ሰውን እንዲገድል የሚያደርገው አዕምሮው ውስጥ የሚያስቀምጠው ስዕል ነው፡፡ የሚገድለው ሰው ሳይሆን እንስሳ ወይም ርካሽ ነገር እንደሆነ ሲያምን ብቻ ነው ስውን ባሰቃቂ ሁኔታ የሚገድለው፡፡ ስለዚህ ትልቁ ወንጀለኛ ይሄን የአዕምሮ አጠባ ( brain washing) ሥራ የሚሰራው የተረገመ ሰው ነው፡፡
በዘር ማጥፋት ( ጄኖሳይድ) ሳይክል ውስጥ አንዱ ምዕራፍ ዲሁማናይዜሽን ነው፡፡ ይህም ምዕራፍ ፣ ወንጀለኞች ጠላት ብለው ያሰቧቸውን ሰዎች ከእንስሳ ጋር በማመሳሰልና ታናሽ ፍጥረት አድርገው የሚስሉበት ምዕራፍ ነው፡፡ Dehumanization ይሉታል፡፡ Dehumanisation – To deny the humanity of one group, and associate them with animals or diseases in order to belittle them፡፡
በናዚ ዘመን ፣ ጀርመኖች አይሁዳውያንን እንደእንስሳ እንጂ እንደ ሰው እንዳይቆጥሯቸው የአዕምሮ አጠባ ሥራ ስለተሰራ ነው ናዚዎች በርካታ ሚሊዮን አይሁዳውያንን የጨረሱት፡፡ ይሄንን የሰራው ትልቁ ወንጀለኛ ጆሴፍ ጎብልስ ነበር፡፡ በሩዋንዳውም ጦርነት ፣ ለዛ ሁሉ ሕዝብ መጨፍጨፍ ዋናው መንስኤ ይሄው ሰውን እንስሳ ያውም ኮክሮች አድርጎ እንዲታይ የተሰጠው ስብከት ነው፡፡ ትልቁን አዕምሮ የመቀየር ሥራ የሰራው ኖኤል ሂቲማና ነበር፡፡ ኖኤል ቱትሲዎችን ኮክሮች(በረሮ) ናቸው እያለ ነበር የሚጽፈው ፣ በሬድዬ ሲያስተጋባ ሚውለው፡፡ጆሴፍ ጎብልስም አይሁዳውያን ላይ ተመሳሳይ ከሰው በማሳነስ እንስሣዊ ገጸ ባሕርይ በመስጠት ፣ በመርዘኛ ብዕሩ ለናዚ እርድ ያመቻች የነበረው፡፡
ዳንኤል ክብረትም “ እንደ ንጉሡ አጎንብሱ” በማለት ጀምሮ አሁን ሌላ ምዕራፍ ላይ ደርሷል፡፡ ጃውሳ የሱ ስያሜ ነው፡፡ ያው የምትገሉት አጋሚዶ፣ ሌባ ነው እንጂ ሰው አይደለም የሚል ስዕልን ለመሳል ነው፡፡ ቀጠለ የምትገሏቸው ሰዎች ድመቶች ናቸው ለማለት ደፈረ፡፡ ዓላማውም ፣ ሊገድል የሄደውን ወታደር የምትገለው የቤት እንስሳ እንጂ ሰው አይደለም ብሎ ለማደፋፈር ነው፡፡ አሁን ደግሞ የምትገሏቸው ሰዎች ጃርቶች ናቸው ላይ ደርሷል፡፡ አሁንም ሰው እየገደላችሁ አይደለም ጃርት እንጂ አይነት የአእምሮ ስዕል ለመፍጠር ነው፡፡ ባጭሩ የዲሁማናይዜሽኑን ሥራ በሚገባ ተያይዞታል፡፡
ይሄ ሁሉ በድሮን የሚጨፈጨፍ ወጣት፣ የምትደፈር ሴትና እናት፣ በየቤቱ እየተጎተተ ለሚገደል ኣዛውንት ሀላፊነቱን ከሚወስዱት ዋንኛ ሰዎች አንዱ እሱ ነው፡፡ የምትገሉት ሰው ሳይሆን ጃውሳ ነው፣ ድመት ነው፣ ጃርት ነው በማለት የግድያው ideological leader እሱ ነውና፡፡የማይነጋ ሌሊት የለም፡፡ ሲነጋ ለፍርድ ከሚቀርቡ ዋነኛ የደም ሰዎች አንዱ የሚሆነው እሱ ነው፡፡
ለልጆቹ፣ ለሚስቱ፣ ለራሱም ሌጋሲና ታሪክ አለማዘኑ ይደንቃል፡፡ የትውልድ መምሐር የነበረ ሰው፣ ለማይረባ ስልጣን ሲል ፣ትውልድ ገዳይ እና አስገዳይ ሆነ፡፡ ከንግዲህ ዳንኤል ሲታወስ ስለ ስልጣን ፍቅር ሲል ከልዕልና ወደ መቀመቅ የወረደ ሰው ምሳሌ በመሆን ነው፡፡
ይሁዳ ለሰላሳ ዲናር እውነትን እንደሸጣት ፣ ዳንኤልንም ፍቅረ ሲመት ከክብሩ ፈጠፈጠው፡፡
የሚደንቀው ታሪኩ ከጆሴፍ ጎብልስ ጋር መመሳሰሉ ነበር፡፡ የሂትለር አይዶሎጂካል መሪ ጆሴፍ ጎብልስ የሊትሬቸርና ፊሎሎጂ ተማሪ ነበር፡፡ እርግጥ ነው ጎብልስ እስከ ዶክትሬት ተምሯል፡፡ ዳንኤል ግን ከአንደኛ ዲግሪ አላለፈም፡፡ጎብልስ የተዋጣለት ጸሐፊና ጊፍትድ የሚባል ተናጋሪ ነበር፡፡ቤተሰቦቹ ካህን ይሆናል ብለው ተስፋ ያደርጉ ነበር፡፡ እሱም ቄስ የመሆን ፍላጎት አሳይቶ ነበር፡፡ ባንዲት ክፉ ቀን ግን ናዚዎች የመጽሔት ኤዲተርና ንግግር ጸሐፊ እንዲሆን መለመሉት፡፡ ጎብልስም የቁልቁለቱን መንገድ ተያያዘው፡፡
ጎብልስና ዳንኤል ልዩነታቸው ጎብልስ ዶክትሬት ዲግሪውን መጨረሱ ነው፡፡የሊትሬቸር ሰው መሆናቸው፣ የተዋጣላቸው ጸሐፊ መሆናቸው፣ የንግግር አቅማቸው፣ ለሃይማኖት የነበራቸው ዝንባሌ፣ ወደ ክህነት ለመቅረብ የነበራቸው ተነሳሽነት፣ … ታሪካቸው ተመሳሳይ ነበር፡፡ ሁለቱም ለማገልገል ለመረጡት ንጉሥ ፣ የመጽሔት አርታኢና ንግግር ጸሐፊ በመሆን ነበር ፖለቲካን የጀመሩት፡፡ በዚህ አካሄዱ፣ ዳንኤል ክብረትም ኢትዮጵያዊው ጎብልስ ወደመሆን እየዘቀጠ ነው፡፡
ሚስቱ ጽላት ፣ ልጆቹም ያሳዝኑኛል፡፡ ወዳጆቹ አልቅሱለት
\ዘ አዲስ