የጂምላ እልቂት፤ የጂምላ እስራት፤ የጂምላ እንግልት፤ የጂምላ ፍልሰት፤ የጂምላ የስነልቦና ጦርነት፤ የጂምላ የተቋማት ውድመትና የማህበረሰባዊ ኢኮኖሚ ምክነት የሚካሄድበት ሕዝብ አማራው መሆኑ አያከራክርም። ለዚህ ነው፤ የአማራው ሕዝብ ለመጀመሪያ ጊዜ እየተናበበ ትግል የጀመረው። ለዚህ የተቀደሰ የፍትህ፤ የእኩልነት፤ የኢትዮጵያዊነት፤ የዜግነት መብትና የዲሞክራሲ ትግል ድርሻየን በመወጣት ላይ እገኛለሁ።
ጥራት ያለው ዘገባ እስካደረጉ ድረስ ነጻ ሜድያዎች ከፍተኛ ሚና አላቸው። የሃሜት፤ የስም ማጥፋት፤ የድብቅ አጀንዳ ምሺግ ከሆኑ ግን ጉዳታቸው ያመዝናልል። በተሳሳተ ትርክት የሚሰቃየው የአማራ ሕዝብ በራሱ ስም ሜድያዎች የተሳሳቱ፤ ሃሜታዊ፤ ክሳዊና ሹሙጣዊና አማራውን ከአማራ የሚለያዩ ትርክቶችን ካስተጋቡና የገቢ ምንጭ ካደረጉ የአማራውን የፍትህ ትግል ይበርዙታል። በአሁኑ የሞት የሺረት ወቅት፤ አማራው ወዳጅ እንጂ ሰው ሰራሽ ጠላት አያስፈልገውም። አማራው ተባብረህ ምታው እንጂ ከፋፍለህ ብላው አይፈልግም።
የዚህ ሃተታ መሰረት በቅርቡ ሃብታሙ አያሌው የ360 ቴሌቪዢን ሜድያ ሚናውን ተጠቅሞ፤ ያለ አግባብና ያለ ቦታው የኔን ስም ለይቶ ያሰራጨውን ስም ማጥፋት ዘገባ ለማውገዝና እንዲስበው ለማሳሰብ ነው። 360 የዘለፋ፤ የስም ማጥፊያ ሜድያ መሆኑን በፍጥነት ማቆም አለበት። ሃብታሙ በኔ ላይ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም የታወቁ አማራዎች ላይ የስም ማጥፍት ዘመቻ አካሂዷል። ለምሳሌ፤ ከታች አባሪ ያደረግሁት የዘሃበሻ ዘገባ እንደሚያሳየው 360 በባለ ኃብቱ የአማራ ትግል ደጋፊ በወርቁ አይተነውም ላይ ተመሳሳይ የስም ማጥፋት ዘመቻ አካሂዷል። ወርቁ አይተነው ከሃገሩ ሸሺቷል።
ሃቁ ምንድን ነው?
ሃብታሙ አያሌው እኔን ሳይጠይቀኝና ሳያጣራ፤ አምብሳደር ስለሺ በቀለ ባከሄዱት የዙም ስብሰባ ላይ “ዶር አክሎግ” ተገኝቷል ብሏል። በሃብታሙ ስሌትና ዘገባ በዚህ የሕዳሴ ግድብ ሙሌት ስብሰባ ላይ መገኘቴ በራሱ ከአብይ መንግሥት ጋር ቅርበት እንዳለኝ ያሳያል ማለቱ ነው። ለሃቅ ከቆመ፤ ሃብታሙ እኔን ይህ ስብሰባ በምን አርእስት ላይ ነው? ብሎ ሊጠይቅ ይችል ነበር። የቀደመው ህወሃት መሰል ሴራውን ስኬታማ ለማድረግ በሚመስል መልኩ የኔን ስም ማንሳቱ የተለየ ቅቡልነት ያስገኛል የሚል እምነት ስላለው ይመስለኛል። ስም ማጥፋት ከሜድያ ነጻነት ጋር አብረው አይሄዱም ብየ ነግሬዋለሁ፤ አይሰማም።
ነገሩን የከረረ የሚያደርገውና 360 ዘገባውን እንዲስበው የሚያስገድደው ሃብታሙ አያሌው የ360 ን መድረክ ተጠቅሞ የኔን ስም ክሳዊና የአቢይ መንግሥት ወገንተኛ ለማስመሰል የኢትዮጵያ ኢምባሲ የዓምት መቀየሪያ ግብዣ በኤምባሲው ባካሄደበት ወቅት መሆኑ ነው።
እኔ ለፌስታው አልተጋበዝኩም። ብጋበዝም አልሳተፍም። ያልተጋበዝኩበት ዋና ምክንያት እኔ በአብይ ዘግናኝ መንግሥት የኦሮሙማ አጀንዳ ላይ የምጽፈውና የምናገረው የማያሻማ አቋም መያዜን የሚያሳይ በመሆኑ ነው።
ሃብታሙ አያሌው ፌስታውንና የሕዳሴ ግድቡን ቀደም ሲል የተካሄደ የዙም ስብሰባ ለምን አቆራኝቶ አወጣው? በኔ ስሌት ያወጣው ሆነ ብሎ እንጂ ሳያስበው አይደለም። በጀርባ ሌላ ነገር አለ የምለው ለዚህ ነው።
የ360 ታዳሚዎችና መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲያውቀው የምፈልገው የሚከተለውን ነው።
- የሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ሁሉንም ኢትዮጵያዊያን፤ አማራውን ጨምሮ ይመለከታል። እኔ አምባሳደር ስለሺ በሰጡት ማብራሪያላይ እንድገኝ ተደውሎ የተጠየቅሁበት ዋና ምክንያት ፕሬዝደንት ትራምፕ “ግብፅ ግድቡን ቦምብ የማድረግ መብት አላት” ባሉበት ወቅት ከቅርብ ባለሞያ ጓደኞቸ ጋር ሆነን አቤቱታ ለተባበሩት መንግሥታት፤ ለአሜሪካ የፋይናንስ ተቋምና (ትሬዠሬ)፤ ለዓለም ባንክ ፕሬዝደንትና ቦርድ ባለሥልጣናት የአቋም ደብዳቤ አዘጋጅተን ዶር አክሊሉ ኃብቴ፤ ፕሮፌሰር አልማዝ ዘውዴና እኔ በአካል ዋሺንግቶን ዲሲ ለሚገኙት ባለሥልጣናት ሁሉ አቅርበናል።
- የአራተኛውን የሕዳሴ ግድብ ሙሌት በሚመለከት እኔ እንድገኝ የተጠራሁበት ምክንያት አንድ፤ በአባይ ወንዝ የኢትዮጵያ ባለቤትነት ላይ በጥናትና ምርምር የተደግፉ ትንተናዎችንና ምክረ ሃሳቦችን ስላቀረብኩ፤ ሁለት፤ እኔ የኢትዮጵያ ውሃዎች መማከርት ካውንስል (Ethiopian Waters Advisory Council) መስራችና ሊቀ መንበር ሆኘ ስላገለግልኩ ነው።
ለ 50 ዓመታት ስሟተትላት ለቆየኋት ኢትዮጵያ፤ ህወሕት/ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘበት ጀሞሮ የህልውና አደጋ ለተከሰተበትና ለምታገልለት ለአማራ ሕዝብ እና ለኢትዮጵያ ልማት አግባብ አለው ብየ አሁንም፤ ወደፊትም ለምደግፈው ለሕድሴ ግድብ ሙሌት ዘገባ እንኳን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ቀርቶ፤ የግብጽና የሱዳን መንግሥት ጥሪ ቢያደርጉልኝ እገኛለሁ።
ለመሆኑ ሃብታሙ አየሌው እኔ በሕድሴ ግድብ ውዝግብ አል ጃዚራ ጋብዞኝ ዶሃ ፤ ክታር መሄዴን ያውቅ ይሆን?
ስለሆነም በአምባሳደር ስለሺ የዙም ስብሰባ ተገኝቻለሁ። ወደፊትም ከጋበዙኝ እገኛለሁ። አለመገኘት ድንቁርና ነው። ሕዳሴ፤ የአማራውን ህይወት በቀጥታ ይመለከተዋል። የአባይ ወንዝ እኮ የአማራ ሕዝብ እምብርትና ህይዎት ነው።
ሃብታሙ አያሌው የማያውቀው ሃቅ አለ። ይኼውም ግድቡ የተጸነሰው በአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግስት፤ ፕሮጀክቱ የተጀመረው በጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ፤ ሕዳሴ ግድብን በሚመለክት የሶስተዮሽ ውል የተፈረውመው በጥቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ መሆኑና የአራተኛው ግድብ ሙሌት ስኬታማ እንዲሆን ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አህመድ ገንቢ ሚና መጫወታቸውን፤ ይህ ግዙፍ ግድብ ስኬታማ እንዲሆን $5 ቢሊየን ዶላር ያዋጣው የኢትዮጵያ ሕዝብ መሆኑን፤ ግብጽ አሁንም ይህ ግድብ ያቋተው ግዙፍ ውሃ ወደፊት ድርቅ ሲከሰተ የአስዋንን ግድብ ለመሙላት ከሕዳሴ ኃይቅ ውሃ ቋት ልቀቁልን ብላ የምትከራከር መሆኑንና ኢትዮጵያ ሌሎች ግድቦች በተለይ የመስኖ እርሻን ለሚያስፋፋ ግድቦች መሰናክል እንደምትሆን ይገነዘብ ይሆን? መልሱን እራሱ ይናገር።
ባጭሩ መንግሥት ቢቀያየርም እንኳን፤ የሕዳሴ ግድብ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ሃውልት ነው። ከአብይ መንግሥት በላይ ነው፤ ከአቢይ ጋር ሊያያዝ አይችልም። ይያያዛል ብሎ መተቸት ከድንቁርና በላይ ድንቁርና ነው።
ይህንን ትችት ከመጻፌ በፊት በተደጋጋሚ ሃብታሙ አያሌው የተናገረውን ሺሙጥና ክስ እንዲስብ ጠይቄው እንደ ነበረ ልታውቁት ይገባል። ጓደኞቸም እንደ ጠየቁት አምናለሁ።
በራስህ ሜድያ አቅርበኝና ሃቁን ልናገር ብየው እሺ ካለ በኋላ ቃሉን አላከበረም። እኔ በሱ ሜድያ ብቀርብ ይህንንና ሌሎች ጉዳዮችን አነሳ ነበር።
የ360 ሜድያን ፕላትፎርም ተጠቅሞ ምንም በማያውቀው ጉዳይ የሰውን ስም መዝለፍ፤ መተቸት፤ መክሰስና ማሺሟጠጥ በሃልፊነት ያስጠይቃል። የሜድያውንም ተአመኔታ ወደ ጥርጣሬ ሊያሸጋግር ይችላል።
የሃብታሙ አያሊው ሽሙጥና ስም ማጥፋት እኔ ቀን ከሌት ለምታገልለት፤ ለምሟገትለት፤ እውቀቴን፤ ልምዴን፤ ገንዘቤን ፈሰስ ለማደርግለት ለአማራው ሕዝብ የኢምንት ያህል አስተዋጾ አያደርግም። እኔም የሱን ትችት ምክንያት አድርጌ ከቆሙኩለትን አላማ ፍንክች አልልም። የአማራው ጉዳይ ከ360 በላይ ነው።
የሚታዘበውና የሚፈርደው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፤ በተለይ አማራው።
ሜድያዎችንና ታዳሚዎችን አደራ የምልው በአማራው ሕዝብ ስም አማራውን አትከፋፍሉት። አማራውን ጠላት አታብዙበት። አማራውን እንደኔ በግልጽ ሆነ ወይንም በህቡእ የሚደግፉትን ግለሰቦች፤ ባለ ኃብቶች፤ ምሁራንና ሌሎች አትዘለፉ። አማራው ወዳጂ እንጂ ተጨማሪ ጠላት አይፈልግም።
ፈረንጅዎች አለማወቅን ማወቅ ራሱ እውቀት ነው ይላሉ። ሃብታሙ አያሌው አለማወቁን አያውቅም። እኔ ብቻ አውቃለሁ የሚለው የአብይ ግትርነት አገርና ሕዝብን ዋጋ እያስከፈለ ነው። ይሄ ተመሳሳይ ችግር የተለያዩ ሀሳቦችን ማስተናገድ ወዳለበት የሀሳብ ገበያ መሆን የሚገባው የሚዲያ መድረክ፤ በግለሰቦች አዛዥነት፤ ታዛዥነት፤ ዳኝነትና የውስጥ አጀንዳ የሚከሰት ከሆነ ጥፋት ያመጣል፡፡ ትግሉን ከመጥቀም ይልቅ ለአማራ ሕዝብ ጠለፋን በማመቻቸት፤ ተጨማሪ ጠላት እያመጣ፤ እርስ በእርስ መደማመጥ እንዳይኖር ያደርጋል፡፡
በመጨረሻ፤ በግልጽ መናገር እንዲሚቻለው ይህ ስም የማጥፋት መንገድ ጨርሶ የአማርን ሕዝብም ሆነ ትግሉን አይጠቅምም፡፡
የአማራው የፍትህ ትግል ይለመልማል!!!
ዘረኝነት ይውደም!!!
September 19, 2023
https://youtu.be/LIqGVHG_hls?si=9xP9R8GcmHDiIwV6