ዶ/ር በቀለ ገሠሠ ([email protected])
ሀ) የተባረከች ሀገር ነበረች፣
የምድሯን ስፋት፣ የወንዞችዋንና የሃይቆችዋን ብዛትና ግዙፍ የተፈጥሮ ሃብቶችዋን ስንመለከት በእርግጥ አምላክ ሁሉንም አሟልቶ እንደፈጠራት እናያለን። ውድ ሀገራችን ነፃነቷንም ጠብቃ የኖረችው በአባት አያቶቻችን ደምና አጥንት ነበር። እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር እየዘረጋች የጌታን በረከት ትቀበል ነበር (ኢትዮጵያ ታበጽእ እዴዊሃ ሃበ እግዚአብሔር የተባለው ለዚህ ነበር)።
እንግዳ ተቀባይነት፣ ያለውን ማካፈል፣ የወደቀውን ማንሳት፣ የሞተውን አለመርሳት የመሳሰሉ ቅዱስ ተግባራት ቆንጆ ትውፊቶቻችን ነበሩ።
ለ) ዛሬ ግን እጅግ ከባድ መከራ ላይ ለምን ወደቅን?
ዛሬ ምን መጣና የሰው ህይወት እንደዚህ ረከሰ? እርጉዝ ሴቶችን፣ አረጋውያንና ሕፃናትን እንደዚህ ሲያሰቃዩና ሲጨፈጭፉ እንዴት ኃፍረት አይሰማቸውም? እያንዳንዳችን ራሳችንን እንጠይቅና መልስ እንፈልግ፣ እንታረም።
እግዚአብሔር ባምሳሉ የፈጠረን እንድናስብና በጎውን ከክፉ እንድንለይ ነው። ከከብቶች በታች ሆነን የዓለም መሳቂያና መሳለቂያ ሆነን ስንገኝ እጅግ በጣም ማዘን ይኖርብናል። ንፁሀን ምስኪን ዜጎችን መግደል፣ ማፈናቀልና ማሰቃየት ለምን ተመረጠ? ይሄ ከእግዚአብሔርና ከስብዕና ጋር ክፉኛ እንደሚያጋጫቸው እንዴት ማወቅ ተሳናቸው? ይዋል ይደር እንጂ በፍርድ ቤቶችም ሊያስጠይቁ እንደሚችሉ ማወቅ እንዴት ተሳናቸው? ልጆቻቸውና የልጅ ልጆቻቸው ዕድሜ ልካቸውን በኃፍረት እየተሸማቀቁ እንዲኖሩስ ለምን ተመረጠ?
ሕፃናትን መንከባከብና ማስተማር ሲገባ ለጦርነትና ለስደት መማገድ ትልቅ ኃጢአት መሆኑስ እንዴት ተረሳቸው?
ገበሬው ወጥቶ በሰላም ካላረሰ፣ ነጋዴው በሰላም ተዘዋዉሮ ካልነገደ ምን ሊበላ ነው?
አማራ ወይም ኦርቶዶክ ስለሆኑ ብቻ እየተመረጡ የሚጨፈጨፉት ዜጎች ደም ወደእግዚአብሔር ይጮሃል። ደጋግሜ እንደጠቀስኩት ውዲቷ አገራችን የምድር ላይ ገነት ናት። ይህችን የመሰለች ቅድስት አገር ማውደምና ማፍረስስ ለምን አስፈለገ? ማንን ለመጥቀም ነው? ተያይዞ መጥፋት ካልሆነ ማንም በተናጠል ሊጠቀም እንደማይችል ማወቅ አለባቸው።
ሕዝባችን ለብዙ ሺ ዓመታት በነፃነት ወጥቶ በሰፈረበት ምድር ላይ እዚህ አትገቡም፣ እዚያ አትኖሩም እያሉ ንፁሃን ዜጎችን መጨፍጨፍና ማፈናቀል ምን ይባላል?
ውሎ ሳያድር ተንበርክከን ከእግዚአብሔር ይቅርታን እንጠይቅ፣ ንስሐ እንግባ። እያንዳንዳችን በሚከተሉት መንገዶች ግዳጃችንን እንወጣ።
ሐ) የመንግሥት ዋናው ኃላፊነት የዜጎችን መሠረታዊ መብቶች ማስጠበቅ ነው። የተጎዱትን መንከባከብ ነው። የመከላከያ ኃይሎች ዋና ኃላፊነት ድንበሮቻችንን መጠበቅ ነው። የፓሊስ ሠራዊት ወንጀለኞችን ለፍርድ ማቅረብና ፀጥታን ማስጠበቅ ነበር። እነዚህ ሁሉ ዛሬ አይታዩም።
መ) የኃይማኖት አባቶች ኃላፊነት የተሸከሙትን የጌታ መስቀልና ቁራን ማክበር፣ ለሰላም መጸለይና እውነትን መመስከር ነው።
ሠ) የሀገር ሽማግሌዎች ህዝብን ማቀራረብና የተጋጩትን ወገኖች ማስታረቅ ይጠበቅባቸዋል።
ረ) ወጣቶች በዘርና በኃይማኖት መከፋፈል የለባቸውም። ነግ በኔ ብለውም ማሰብ ያስፈልጋል። ስለዕውነት መቆም አለባቸው። ለመብት በጋራ መታገል ይጠበቅባቸዋል። ሀገር ለመረከብ መዘጋጀት አለባቸው።
በመጨረሻ እየተካሄደ ያለው በተለይ አማራውን የማሰቃየት የእብደት ዘመቻ ቶሎ መቆም እንዳለበት በአጽንዖት ላሳስብ እወዳለሁ።
የጭቁኖች አምላክ እርዳታ አይለየን።