May 18, 2023
9 mins read

እኔና ፕሮፌሰር አስራት፤ እሱም እኔም ሳናስበው አስተማሪዬ እንዴት በሽተኛዬ እንደሆነ – ዶ/ር አበበ ሐረገወይን

Prof Asrat Woldeyes 1 1
#image_title

ፕሮፌሰር አስራት በጣም የምናከብረውና የምንፈራው በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የቀዶ ጥገና መምሕራችንና በኋላም ዲናችን የነበረ ፣ በቀዶ ጥገና ጥበቡና ለበሽተኞቹ በነበረው ልዩ እንክብካቤ ተምሳሊታችን አድርገን የምናደንቀው ልዩ ባለ ሞያ ነበር። ዶክተር አስራት አይኑም፣ መልኩም፣ ሰውነቱም፣ ድምጹም ያምበሳ አይነት ስለ ነበርና ጥሩ አስተማሪም ስለነበርና መውተፍተፍ ስለማይወድ ከተቆጣን በድንጋጤ እንንቀጠቀጥ ነበር። ካለ ምክንያት ስለማይቆጣ ቢጮህብንም አባታችን እንደ ተቆጣን ነበር አይተን የምናልፈው። እገሌ ተገሌ ሳይል ሁሉንም እኩል ስለሚያይ ቀን የጎደለበትን ተረኛ ካልሆን ደስታችን ነበር።

.

የሕክምና ትምሕርት ጨርሰን የድህረ ምረቃ ልምድ በውስጥ ህክምና ልምድ ለማግኘት ጥቁር አምበሳ ከጎጃም እንደ ተመለስኩ መጀመሪያ በዶክተር ኢያሱ ሀብተጋብር ጭፍራነት ተመድቤ ነበር። አንድ ጠዋት እኔም ከኔ በታች ያሉኝን ደቀ መዝሙሮች እያንጋጋሁ በሽተኛ ስናይ የሆስፒታሉ ሜትረን እያለከለከች ዶክተር አስራት ቤቱ ታሞ ስልክ ደውሎ ድረሱልኝ ይላል፣ ምን እንደሆነ ግን የማውቀው የለም፣ ምን ይደረግ አለች። እኛ ዶክተር አስራት ታሟል ብሎ ከማመን ዝቋላ እግር አውጥቶ ካገር ጠፋ ቢሉን ለማመን ይቀለን ነበር። ነገሩን አቃለን ድንገት ወድቆ እግሩ ወለም ብሎት ሊሆን ይችላል ወዘተ ተባብለን ለማንኛውም አምቡላንስ ቤቱ ይላክለት፣ አንተስ አቤ ብትሄድና ብታየው እኔ በሽተኞችህን አይልሀለሁ ብሎኝ ዶር ኢያሱ እኔ በአምቡላንስ ተሳፍሬ ልእልት ጸሀይ ሆስፒታል ዶር አስራት የሚኖርበት ቤት ሄድን። በሩን ብናንኳኳ ተቆልፎ ነበር። በር የሚከፍትም አቤት የሚልም ድምጽ ከውስጥ አይወጣም። ተደናግጠን መስኮት ሰብረን አብሮን የነበረ ጤና ረዳት ውስጥ ገብቶ ዞሮ በሩን ከፈተልን። ውስጥ ስንገባ ዶክተር አስራት ደረቱን ግጥም አድርጎ ይዞ ፊቱ በላብ ተዘፍቆ ሲያቃስት አገኘነው።

.

በጣም ተደናግጠን ስንጠይቀው ከረጅም ካንድ ከሁለት ሰአት በፊት ከዚህ በፊት አይቶት የማያውቀው ውጋት ግራ ደረቱን ይዞት መንቀሳቀስ እንደቸገረና ይተወኛል ብሎ ቢጠብቅ እየባሰበት እንደሄደ ነገረን። እኔም ነገሩ ገብቶኝ ኸርት አታክ ነው ስለው፣ ሕመሙን ረስቶ እንደ ዱሮው እንዳስተማሪነቱ አይኑን አፍጥጦብኝ አበድክ መሰለኝ ፣ እኔን እንዴት ይሄ ይይዘኛል ብለህ ታስባለህ አለኝ። እኔም ባዲስ ድፍረት ምንም ጥርጥር የለኝም ስለው ፣ በጣም የሚወደውና የሞተ ጓደኛውንና አስተማሪያችን የነበረውን ስም ጠርቶ፣ ምነው አድማሱ በነበር አለ። እኔም መልሼ ፣ ምነው ዶክተር አስራት እኛም እኮ በደምብ ያስተማርከን ተማሪዎችህ ነን፣ ለምን አትኮራብንም ስለው፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ፈገግ አለና እርግጥ ነው እንዲያውም አንተ ጎበዝ ተማሪዬ ነበርክ እንሂድ ብሎ ከተቀመጠበት ሊነሳ ሲሞክር እኔም እጁን ግጥም አድርጌ ይዤ፣ መነሳትና መንቀሳቀስ በጭራሽ የለብህም በስትረቸር ነው መሄድ ያለብህ አልኩት። እሱ እንኳን በሕይወቴ እያለሁ ሬሳዬም በስትረቸር አይወጣም ብሎ አሻፈረኝ አለ። ግሉኮስ ይጀመር ብለውም እምቢ አለ። እንደምንም ከግራና ከቀኝ ደግፈን አምቡላንስ አስገብተን ጥቁር አምበሳ ወሰድነው።

.

ጥቁር አምበሳ እንደደረስን ዶክተር ኢያሱም ሲያየው ተደናግጦ እኔ በጠረጠርኩት በሽታ ተስማምቶ የልብ ምርመራ ሲደረግ ተረጋገጠና፣ ዶር አስራት እራሱን እየነቀነቀ፣ ይሄን አልጠረጠርኩም ነበር ብሎ ተገረመ። የማይፈልገውንም ግሉኮስ እጁ ላይ ሰክተን ነፍስ አድን መዳህኒቶች በደም ስር ስንሰጠው ህመሙ ወዲያው ሲለቀው ፣ እግዚአብሔር ይባርካችሁ ልቤ አሁን መለስ አለች ብሎ እጄን ይዞ ካሁን በኋላ ታዛዥ ነኝ አለ። እንግዲያው ኦክስጂን ያስፈልግሀል ስለው እምቢ ሊል ጀምሮ ሳይጨርስ ቃሉ ትዝ ብሎት እሺ ይሁን አለና ጭምብላውን እራሱ አጠለቀው። ከዚያም እንደ ቁልቢ ገብርኤል ንግስ መታመሙን የሰማ ሁሉ ከየቦታው ስለመጣ ወደ ክፍል ለመውሰድ መንገዱ በሰው ማእበል ሞላ። ዘበኛ ጠርተን ወሬኞችን ካስባረርን በኋላ ወደሚተኛበት ክፍል ወሰይነው። እዚያም ብዙ አጀብ ስለ ነበረ ዘበኛ ቆሞ እኛ ያልፈቀድንለት ሰው እንዳይገባ ከለከልን።

.

ወደ ማታ ሲሆን ህመሙ በደምብ ሲለቀው የዱሮው አምበሳ ተመለሰ፤ ፊቱም ወዲያው በራ። ግሉኮሱንም ኦክስጂኑም ካሁን በኋላ አያስፈልገኝም ብሎ እኛም ተስማምተን ተነቀለለት። እንደዱሮውም ጨዋታና ትእዛዝም ጀመረ። የጀመርኩትን መጽሐፍ አልጋዬጋ ታገኘዋለህ አምጣልኝ ፣ በተጨማሪም ሸሚዝ ክራባትና ሱሪና ኮቴን አምጣልኝ አለኝ። መጽሐፉን ብቻ ነው የማመጣልህ፣ ልብስ የማመጣልህ የት ለመሄድ ነው፣ እኛ ሳንፈቅድ ካልጋህ ንቅንቅ የለም ስለው ለመጀመሪያ ጊዜ ሆዱን ይዞ ተንከትክቶ ሳቀ። ምነው ብለው ከልጅነቴ ወዲህ እንዲህ አይነት ቀጭን ትእዛዝ የተሰጠኝና እኔም ሰጥ ለበጥ ብዬ ትእዛዝ የተቀበልኩት ዛሬ ስለሆነ ነው ያሳቀኝ ብሎኝ አብረን ብዙ ሳቅን። የጀመረውም መጽሐፍ ደራሲው ማሪዮ ፑዞ እንደነበር ትዝ ቢለኝም አስእስቱን ረስቼዋለሁ። መጽሐፉንም ያንኑ ሌሊት አምብቦ ጨርሶ ከፈለክ አምብበው ብሎ ሰጠኝ። እኔም ጥሞኝ የማፊያ ታሪክ ስለ ነበር ቶሎ ጨርሼ ለሚፈልግ አስተላለፍኩ።

የተቀረውን ታሪክ ለሌላ ጊዜ ትቸዋለሁ

.

ቸሩ አምላክ የፕሮፌሰር አስራትን ነፍስ ይማርልን።

ዶ/ር አበበ ሐረገወይን

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop