March 2, 2023
7 mins read

የ127ኛ ዓመት የዓድዋ በዓል አከባበርን አስመልክቶ ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የተሰጠ መግለጫ

abnየአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ የ127ኛ ዓመት የዓድዋ ድል በዓል አከባበር ዝግጅትን በአንክሮ ሲከታተል ቆይቷል። በዚህም በመንግስት ደረጃ መዋቅራዊና ሥርአታዊ በሆነ መልኩ ታሪክ ለመበረዝ የተሄደበትን ርቀት ተመልከተናል። በዓሉ ለዘመናት ሲከበርበት ከነበረው ምኒልክ አደባባይ ከመቀየር አንስቶ የዓድዋ ድል ዋና አምድ የሆኑ መሪዎችን በተለይም የመሪውን አፄ ሚኒሊክን ሚና ለማሳነስ እና ለማኮሰስ የተደረገው የተቀናጀ መንግስታዊ የበዓል አዘገጃጀት ሂደት እጅግ አሳዛኝ እና በዚህ ዘመን ይደረጋል ተብሎ የማይታሰብ አሳፋሪ ድርጊት ሆኖ አግኝተነዋል።
በሌላ በኩል በዕለቱ በመንግስት ደረጃ ቦታ በመቀየር በዓሉን ለማክበር መሞከሩ ሳያንስ በዓሉን በታሪክ ሲከበር በነበረበት ሚኒሊክ አደባባይ ለማክበር በተሰበሰበው ሕዝብ ላይ የተፈፀመው ነውረኛ ድርጊት ከባንዳነት የማይተናነስ አፀያፊ የታሪክ ኩነት ሆኖ ተመዝግቧል።
ከኢትዮጵያ አልፎ የጥቁር ሕዝብ ሁሉ የኩራት ምንጭ የሆነው የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓል እንደወትሮው በምንሊክ አደባባይ ሕዝብ ተስብስቦ እንዳያከብረው በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች አላስፈላጊ ኃይል የተቀላቀላበት እርምጃ የተነሳ በመስተጓጎሉ ንቅናቄያችን ድርጊቱን በፅኑ ያወግዛል!
ግብር ከፋይ ዜጎች የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓልን በፈለጉበት ስፍራ እንዳያከብሩ የሚከለክላቸው ሕግ የለም። የመንግስት ድርሻ ዜጎች በነፃነት ሃሳባቸውን እንዲገልፁ ምቹ ሁኔታ መፍጠር እና ሰላምና ደህንነትን ማስከበር ነው!
መንግሥት በእጁ ያለው ሉዓላዊ ስልጣን ከዜጎች በውክልና ያገኘውና ግብር የሚሰብስብበት በመሆኑ የዜጎችን ሰላም እና ደህንነት የመጠበቅና ማስጠበቅ ግዴታ ያለበት ከመሆኑም በተጨማሪ ከሕግ አግባብ ውጭ የትኛውንም አይነት አመለካከት እና እምነቱን አስገድዶ በዜጎች ላይ መጫን እንደማይችል ሊገነዘበው ይገባል! የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ የዛሬውን የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓል አከባበር በተመለከተ ከሕግ እና ሥርአት ውጭ ሕዝብ በፈለገው ስፍራ እንደፈቀደው እንዳያከብር መንግሥት የፈጠረውን እክል በፅኑ ያወግዛል። ከኢትዮጵያውያን አልፎ ለጥቁር ሕዝብ ሁሉ መመኪያ የሆነው የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዚህ ደረጃ የውርደት እና መከፋት ስሜት በሚፈጥር ድባብ እንዲያልፍ መደረጉ እጅግ አሳዝኖናል። መንግሥት ሆነ ብሎ ከሳምንት በፊት የጀመረው የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓልን የሚያደበዝዝ ሸፍጥ የወለደው የታሪክ ብረዛ ስራና ከፋፋይ የዘረኝነት ፖለቲካ የተነሳ በድምቀት፣ በኩራት እና አልበገር-ባይ ኢትዮጵያዊ ወኔ መከበር የነበረበት የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓል በዚህ ሁኔታ በጭስ ቦንብ እና ዱላ የጸጥታ ኃይሎች ያለርህራሄ ዜጎችን ወደሚያጠቁበት ትራጄዲ መቀየሩ ጥልቅ መከፋትን ይፈጥራል። የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች በየአደባባዩ የተገኘው ዜጋ ላይ ፍፁም አላስፈላጊ የኃይል እርምጃ ከመውሰድ አልፈው በቤተክርስቲያን ውስጥ የጭስ ቦንብ በመወርወር በቅዳሴ ሥነ ሥርአት ላይ በነበሩ ምእመናን እና ካህናት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል::የዳግማዊ ምኒሊክ መሰናዶ ትምህርት ቤት የፊዚክስ መምህር የነበረው የአብን አባል ሚሊዮን ወዳጀ ከመንግስት ጸጥታ አካላት በተተኮሰ ጥይት ተገድሏል። የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ይህን ሕገወጥ ድርጊት በፅኑ ያወግዛል!
ስለሆነም:-
፩. መንግስት የፈፀመውን ሕገወጥ ድርጊት በማመን ሕዝብን በይፋ ይቅርታ እንዲጠይቅ ና እንዲህ አይነት ሕገወጥ ድርጊት በድጋሜ እንደማይከሰት ማረጋገጫ እንዲሰጥ እናሳስባለን::
፪. ይኸ ሕገወጥ ድርጊት እንዲፈፀም ትዕዛዝ የሰጡ ባለስልጣናት እና የተሳተፉ የጸጥታ ኃይሎች ተለይተው ለሕግ እንዲቀርቡ እንጠይቃለን!
በዚህ አጋጣሚ መንግስት በተቀናጀ ሁኔታ ታሪክን በመበረዝ እና በማፈራረስ ከታሪኳ የተፋታች አገርን ለመገንባት የሚያደርገውን ያልተቀደሰ ጉዞ እንዲያቆም እናሳስባለን። በዛሬው እለት በነፃነት በዓል ላይ በመገኘቱ ምክንያት የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች በወሰዱት ርምጃ ውድ ሕይወቱን በግፍ ለተነጠቀው ወንድማችን ጥልቅ ሃዘናችንን እየገለፅን ለወዳጅ ዘመዶቹ መፅናናትን እንመኛለን።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)
አዲስ አበባ፣ ሸዋ፣ ኢትዮጵያ
የካቲት 23 ቀን 2015 ዓ.ም

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop