የአገዛዙ መልክ ሜክ አፑ እየለቀቀ አሁን ትክክለኛ ገጽታው እየታየ ነው- ዜጠኛ መሳይ መኮንን

ዛሬ የሆነው ወዴት እንደሚወስደን ለመግለጽ ነብይ መሆን አይጠይቅም። በሚኒሊክ አደባባይ የአድዋ ድል እንዳይከበር መደረጉ ነገ ምን ዓይነት እርምጃ ሊወስዱ ምልክት እያሳዩን እንደሆነ በግሌ ገብቶኛል። ጊዮርጊስ አጠገብ የቆመውን የሚኒሊክ ሀውልት ማፍረስ በቀጣይ የምንመለከተው ነገር እንደሚሆን አልጠራጠርም። የሀጫሉ ሞት ጊዜ ታስቦ እንደነበረ አስታውሳለሁ። አዲስ አበባን ስሟን ቀይሮ ወደ ኦሮሚያ ክልል የመጠቅለል ውሳኔም ከጠረጴዛ ላይ የተቀመጠ ፋይል ሆኗል። ከወደጨፌ ኦሮሚያ ሀሳቡ ተነስቶ አራት ኪሎ ቆይ ትንሽ ታገሱ ብሎ እንዳዘገየው ሽው የምትል መረጃ ከጆሮዬ ከጠለቀች ሰነባብታለች።
የኦሮሚያ ብልጽግና የኦነግን አጀንዳ አንድ በአንድ በማስፈጸም ላይ ይገኛል። ከእንግዲህ ሸኔ ሰው ማረድ አያስፈልገውም። ኦነግ ነፍጥ ተሸክሞ ጫካ ለጫካ መርመጥመጡ ትርጉም የለውም። በኢትዮጵያ ስም የሚምምል በገቢር ኢትዮጵያን የሚገዘግዝ መንግስት አጀንዳቸውን በቅደም ተከተል እያስፈጸመላቸው ነው።
ጎበዝ፥ ኦነግ ሸኔ ብላችሁ በማጉሊያ መነጽር ሩቅ አትመለከቱ። ያርዳል፡ ይጨፈጭፋል ብላችሁ ስትርግሙት ስትከሱት ከኖራችሁት ቡድን ላይ የጠነቆላችሁትን ጣት አንሱት። ኦነግ ሸኔ የጦስ ዶሮ ነው።
ኢትዮጵያ ብርቱ አደጋ ላይ ናት። የተፈራው ነገር ድሆ ድሆ መጥቷል። የኢትዮጵያዊነት ካባ ለብሶ አራት ኪሎ የገባው አገዛዝ ቀስ በቀስ፡ እያስታመመ የመገዝገዝ ስራውን አከናውኖ አሁን በአደባባይ ተግባራዊ ወደማድረግ ምዕራፍ በይፋ ገብቷል። ለጨዋታ ማሳመሪያና፡ በድንዛዜ ውስጥ ላሉት፡ ዓይን ልቦናቸው በባዶ ትርክት ለተሸበቡት ወገኖች አሁንም ‘ኢትዮጵያ አትፈርስም’ ዲስኩር እየተለቀቀላቸው ጥቂት ጊዜያት መቆየቱ አይቀርም። ኢትዮጵያን የማወላለቁ ስራ ከጓዳ ወደ ደጅ መውጣቱን የሚያሳዩ ተግባራት በየዕለቱ እየበረከቱ መጥተዋል። መደባበቅ አያስፈልግም። በሀገር ጉዳይ መሽክርመሙ ዋጋ እያስከፈለ ነው። ይህ ሟርተኝነት አይደለም። ካስባለም እኔ ሟርተኛ ሆኜ ልቅር፡ ይሄን ሳልተነፍስ ከምቀር።
ኢትዮጵያን ለማዳን ጊዜው አልረፈደም። በጣም ከባድ ቢሆንም የማይቻል ግን አይደለም። መቃብር የማሱላትን ወደጥልቁ መቃብር የከተተች ተአምረኛ ሀገር ናት። አለቀላት ሲባል ብድግ ብላ የምትገዝፍ ድንቅ ሀገር ባለቤቶች ነን። አጎንብሰን ሊሆን ይችላል እንጂ አልተሰበርንም። መጀመሪያ በድንዛዜ ያሉ የቀሩ ወገኖች እንዲነቁ ማድረግ ቢቻል ጥሩ ነው። ካልሆነም ለውጥ ለማምጣት ጥቂት የቆረጡ በቂ ናቸው። እናስብ። ምን እየተደረገብን እንዳለ በጥልቅ እንመርምር። እየሆነብን ያለውን ከፍርሃት ወጥተን እንፈትሽ። ኢትዮጵያ ስሟ ደስ ስለሚለን፡ ስለምንወዳት አይደለም። ህልውናችን ስለሆነች እንጂ!
ተጨማሪ ያንብቡ:  ከኦሮሙማው የፋሽስት መንግሥት ጋር ድርድር አይሞከር፤ ለፋሽስቶች ድርድር ጠላቶቻቸውን አዘናግቶ ማጥፊያ መሳሪያ ነውና!!

2 Comments

  1. ሽመልስ አብዲሳን ኦሮምያን ማስተዳደር ስላልቻለ ከቦታው ይባረር ይታሰር ተጠያቂ ይሁን

  2. የኦሮሞ አክቲቪስቶች ከ ሙሲቬኒ ንግግር ምን ይማሩ ይሆን፡ ለምን አልተገዛንም ብለው አኩርፈው ነው?

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share