ግልፅ ደብዳቤ ለኢትዮጵያ ሕዝበ ቤተሰብ። በደወል 1 ዘ ኢትዮጵያ በሚድን በሽታ ተይዛ ግን በሽታው እየገደላት ያለች ሀገር ኢትዮጵያን አየን። በደወል 2 ዘ ኢትዮጵያ፥ ለዚህ በሽታ ያልተጠቀምንበትን ቀዳሚው ፍቱን መድኃኒት ምን እንደሆነ ተመለከትን። አሁን በደወል 3 ዘ ኢትዮጵያ መድኃኒት መስሎን የምንወስደው ዘረኝነት ገዳይ መርዝ እንደሆነ እናያለን።
ሰው የሚድን በሽታውን ለማሻል የሚያድን መድኃኒት ይወስዳል እንጂ ጭራሽ ለሞት የሚያጋልጠውን መርዝ በመድኃኒት ስም አይወስድም። ኢትዮጵያ ግን የብሔር ብሔረሰብን እኩልነት ለማምጣት ዘረኝነትን እንደ መድኃኒት እየወሰደች የማያቆም የስቃይ ድራማና ምስቅልቅል ያለ ጉዞ ተያያዝን። የኢትዮጵያ ሕልውናም ቦግ ድርግም እያለ፥ በቁልቁለት ጉዞ ፀሐይ እስክትጠልቅባት ድረስ የሚሄደው ለዚህ ነው። መፍትሄው አንድ ነገር ነው። የዐሳብ ልዕልና መውጫ መንገዳችን ነው። የዐሳብ ልዕልና ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን፥ ሲያሸንፍ ዘለቄታ ያለው መፍትሄ ጭምር ሰጥቶ ነው።
ለመግባባት አንድ መሠረት መኖሩ ወሳኝ ነው። ኢትዮጵያ በብዝሀነት የበለፀገች ናት። የሁሉም ውበት ደምቆ እንዲወጣ፥ የሁሉም ስብዕና እና እሴቶች በሙሉ በእኩልነት እንዲታዩ፥ ከዚህ አልፎ ልዩነቶቹ እርስ በርስ እየተመጋገቡ እንዲጎለብቱና በዘለቄታ እንዲዘልቁ ከተፈለገ፥ ሁላችንም አንድ መሠረት ሊኖረን ያስፈልጋል። ያም መሠረት አብሮነት ይባላል። ግን ዘረኝነት አብሮነታችንን እየገዘገዘ ብትንትናችን እንዲወጣ መንገድ ይጠርጋል። ያኔ ባለጊዜና ያሸነፈ የሚመስለው ተረኛ፥ ራሱን መሠረት ለማድረግ ይሞክራል። በዚህ ሂደት ሁሉም ይከስራል። ይህ እንዳይሆን ያልታሰበውን ማሰብ መጀመር አለብን።
ያልታሰበውን ማስብ፦ የዐሳብ ልዕልና
ያልታሰበውን ለማሰብና የዐሳብ ልዕልናን ለመጨበጥ፥ እኛ ራሳችንን የምናይበትን ዕይታና ሌሎችን የምናይበትን ዕይታ መቀየር አለብን። ምክንያቱም በተለመደው ዕይታ ዘረኛው ሁልጊዜ ሌላኛው ነው እንጂ እኛ አይደለንም። ለአብሮነት መሠረት ደግሞ እንቅፋት የሆነው ዘረኝነት ነው። ቋንቋችን የሚደባለቀው እዚህ ላይ ነው። አንዱ ከሳሽ፥ ሌላኛው ተከሳሽ እየሆንን ስለ ቁምነገር መነጋገር አንችልም። ነፃ የሚያወጣን ሁላችንም ወርደን ታች ዝቅ ብለን እግዚአብሔር እኛን የሚያይበትን ዕይታ ማየት ነው። ያኔ ሁላችንም ዘረኛ እንደሆንን ይታየናል። ዘረኝነት በተፈጥሮ ያለ ነገር ነው። ከዘረኝነት የምንወጣው በፍቃዳችን ነው። ያንንም በአሸናፊነት የምንወጣው፥ ሁላችንም አብረን ዘረኞች እንደሆንን ሁሉ፥ ሁላችንም ከዚያ ተላቀን ሰው መሆንን ስንፈቅድ ነው።
አንዱ በብሔሩ ዘረኛ ሲሆን፥ ሌላኛው በዜግነቱ ዘረኛ ይሆናል። አንዱ ብሔሩን ሲያስቀድም፥ ሌላኛው ዜግነቱን ያስቀድማል። አንዱ የብሔር ዘረኛ የራሱን ብሔር ለብቻው ሊያገን ሲፈልግ፥ ለኢትዮጵያ አብሮነት መሠረት ውጋት ይሆናል። እንደዚሁም የዜግነት ዘረኛ ኢትዮጵያን ለብቻዋ እንድትገን ሲፈልግ፥ በጨለማ ላለ ጥቁር አፍሪካ ሕዝብ አንድነት ውጋት ይሆናል። አንድ ብሔር እንዲሰለጥን የሚፈልግ ዘረኛና፥ አንድ ኢትዮጵያን ለማግነን የሚፈልግ ዘረኛ፥ አንድ አፍሪካን ሕልም አድርጎ የሚያስቀር ነው። ይህን በማድረግ አፍሪካን ብቻ ሳይሆን፥ ዓለምን ያጨልማል።
በኢትዮጵያ ዘረኝነት እንደ መድኃኒት መወሰድ የተጀመረው በጭቆና ተሳቦ ነው። ጨቋኝ ሁልጊዜ ሕዝብ ሳይሆን የተረኛ መንግስት ውጤት ነው። የጨቋኝ እናት ደግሞ በጥቁር ሕዝብ ላይ የተፈፀመው ጭቆና ነው። ኢትዮጵያ በአድዋ የነፃነት ምልክት የሆነችውና ለፓን አፍሪካ መነሻ ያደረጋት፥ እንድትመፃደቅበት ሳይሆን፥ ለእውነተኛው ጭቆና መልስ እንድትሰጥ ነው። ኢትዮጵያ የጥቁር ሕዝቦችን ጭቆና ለመፍታት እስካልተነሳች ድረስ፥ ራሷን በራሷ ተጠላልፋ የብዙዎች እንቆቅልሽ መሆን ይሆናል እድል ፈንታዋ።
ያለን ዘረኝነት የብሔር ዘረኝነት እና የዜግነት ዘረኝነት ነው። እዚህ ላይ መሀል ሰፋሪ የለም። መሀል ነኝ ብሎ የብሔር ዘረኝነትን ጠባብ የሚልና የዜግነት ዘረኝነትን አሕዳዊ የሚል ፖለቲካዊ ብልጣብልጥነት ነው። አሁን ሁላችንም ብንፋቅ ወይ የብሔር ዘረኛ ነን፤ አለበለዚያ ደግሞ የዜግነት ዘረኛ ነን። እውነተኛይቷ ኢትዮጵያ የምትገለጠው ልጆቿ የተፈጥሮ ዘረኝነትን በፍቃዳቸው ለመላቀቅ የሚያስችላቸውን ሃይል እንዲላበሱ የኢትዮጵያን ተልዕኮ ሲያውቁ ነው።
በመጀመሪያ የኢትዮጵያ ልጆች ከዘረኝነት ወጥተን ሰው በመሆናችን፥ ለጥቁር ሕዝብ ጭቆና መልስ መሆን ተልዕኳችን መሆኑን እንወቅ። ችግራችን የሚፈታው ከራሳችን በላይ ማሰብ ስንጀምር ነው። በዓለም እስካሁን ካልታዩት የተሻለ ሥርዓት ሊያመጡ የሚችሉ አቅም ያላቸው ልጆች እናታችን ኢትዮጵያ አላት። ከዘረኝነት የምንወጣው በፍቃዳችን እንጂ በተፈጥሯችን አይደለም።
የራስን ባህል ቋንቋ እሴት ማዳበር ሰውዋዊነትና ኢትዮጵያዊነት ነው። ነገር ግን የብሔር ዘረኝነት ራስን መንከባከብ ላይ ብቻ አያቆምም። ራስን በሌላው ላይ ጭኖ መግነን ነው የሚፈልገው። ጨቋኝነት ከባለጉልበታምነት (ተረኛ ባለጊዜነት) የሚመነጭ ነው። ራስን በትዕቢት ከሁሉ የበላይ ነኝ የሚል መንፈስ የእኩልነት ጠላት ነው። የብሔር ዘረኝነት የብሔርን ክብር የሚያዋርድ ነው። ብሔር ክብሩና ውበቱ የሚገለጠው በእውነተኛ ኢትዮጵያዊ አብሮነት ውስጥ ነው።
የአድዋ ታሪካችን ፈጣሪ ለጥቁር ሕዝብ ፋና ወጊ እንድንሆን ዕድል የሰጠን መሆኑን የሚያሳይ ነው። ለራስ ብቻ ከመኖር ለሌሎች ለመኖር እንድንፈልግ ነው። ኢትዮጵያ ትልቅ እንጀራ እንዲወጣላት ከፈለግን ማወቅ ያለብን ነገር አለ። ያም ለአፍሪካ እንጀራ እንዲወጣላት ኢትዮጵያ እርሾ እንደሆነች ነው። ኢትዮጵያ ከእኛ በላይ ትልቅ ካልሆነች፥ በእኛው ልክ ብቻ ከሰፋናት፥ እሺ ብላ አትሰፋልንም። ይልቁንም ትበጣጠስብናለች።
ሰው መሆን ማለት ምን ማለት ነው? ሰው ሰውን ገዥና ለሰው ተገዥ ሆኖ እንዲኖር በፈጣሪ አልተፈጠረም። ሰው ተፈጥሮን እንዲገዛ እንጂ። ሰው ግን ተባብሮና ተዋዶ ምድርን እየገዛ የምድርን በረከት ከመብላት ይልቅ፥ አንዱ ሌላውን ለመግዛት እየሮጠ እርስ በርስ መበላላትን መረጠ።
ሰው መሆን ሲመነዘር በዜግነት የሚወሰን ሳይሆን በአህጉራችን ጥቁር ሕዝብነት ነው የሚታየው። ያኔ ነጭ ጥቁር ሳንል ለሰው ፍጡር ሁሉ ፈውስ ምክንያት እንሆናለን። አፍሪካ ስትድን ያኔ ሁላችንም እንድናለን። ይህንን መንገድ ካልመረጥን ግን በተናጥል እያንዳንዳችን በጠላት እንመታለን። አብረን ካልቆምን ለየብቻችን የዓለምን ተፅዕኖ አሸንፈን ከጨለማ አህጉርነት ወደ ብርሃን አህጉርነት አንሻገርም። ኢትዮጵያ ደግሞ ለዚህ በመሪነት እንድትቀደም በታሪክ አጋጣሚ ይሁን በፈጣሪ ፍቃድ ብቻ እሙን ነው።
ዘረኝነት ራሱን አንደኛ ያደርጋል። የአብሮነት ድምፅ አልባ አጥፊ ነው። ዘረኝነት በመጨረሻ ሄዶ ሄዶ ከራሱ ጋር ይጣላል። ዛሬ ብሔሩን አስቀድሞ ከሌላው ብሔር ጋር የሚጋጭ፥ ትንሽ ቆይቶ ወደ ጎሳው ዝቅ ብሎ በብሔሩ ካሉት ከሌሎች ጎሣዎች ጋር ይጋጫል። ከዚያ እየወረደ ወደ ቤተሰብ ወርዶ ከቤተሰቡ ጋር ይጋጫል። በመጨረሻ ከራሱ ጋር ይጣላል። የዘረኝነት ሩጫ ወደ ውስጥ ነውና ሄዶ ሄዶ ከራሱ ጋር ይላተማል።
የነገሩ ፍፃሜ ምንድነው?
ምርጫችን የትኛው ነው? ለዘመናት “የኢትዮጵያ ሕዝብ” ስንባል ቆየን። ይህ አጠራር የዜግነት ዘረኝነታችንን ያሳብቃል። ዘመን አመጣሹ “ብሔር ብሔረሰብ ሕዝቦች” ብሎ ይጠራን ጀመር። ይህ አጠራር የብሔር ዘረኝነታችንን ያሳብቃል። ያልታሰበው ዐሳብ ደግሞ “የኢትዮጵያ ቤተሰብ” ሊለን ይፈልጋል። ክፋቱ ፖለቲካችን ለራሱ ፍላጎት የሚጠቅመውን እንዲጭንብን ያደርጋል እንጂ ለሕዝብ የሚጠቅመውን አያደርግም። ኢትዮጵያ ራሳችን እንደሆንን በዚያ ማንነታችን እንታወቅ ዘንድ አልቻልንም (Ethiopia: To Be Known As We Truly Are)። ዘረኝነት ካመጣብን ከዚህ የማንነት ጭንብል ማን ይገላግለናል? “እግዚአብሔር አንድ ጊዜ ተናገረ፥ እኔም ይህን ብቻ ሰማሁ፤ ኃይል የእግዚአብሔር ነው” (መዝሙረ ዳዊት 62፡11)። በተከታታይ እንመለከታለን፥ በደወል 4 ዘ ኢትዮጵያ እንገናኝ።
ፀሐፊውን ለማግኘት: www.myETHIOPIA.com