አንዱ ዓለም ተፈራ
እሁድ፣ የካቲት ፭ ቀን ፪ ፻፲ ፭ ዓ. ም.
በአንድ አገር የሚኖረው የአስተዳደር ሁኔታ፤ በሁለት ዋና ዋና ጉዳዮች ይሽከረከራል። የመጀመሪያው የአገሩ ሕዝብ ያለበት የፖለቲካ ንቃት ደረጃ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ፤ በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙት የፖለቲካ ልሂቃን መሠሪነት ነው። ይኼ የኔ ትንታኔ ነው። በዚህ ጽሑፍ፤ እኒህን በመተንተን እጀምርና፤ በአገራችን ያለውን ሀቅ ተንተርሼ፤ ወደፊት መከተል የሚገባውን፣ ሊሆን የሚችለውን ወይንም የማይችለውን የፖለቲካ ለውጥ አመላክታለሁ።
“እያንዳንዱ አገር፣ ተገቢውን መንግሥት ያገኛል” በማለት በአስራ ስምንተኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻና በአስራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ የኖረው ጆሴፍ ደ ማያስትረ በፈረንሳይኛ አስቀምጦታል። ፈላስፋውን ከሚያደንቁት ወገን ባልሆንም ይሄን አባባሉን እወድለታለሁ። እንደሱ ጽሑፍ፤ የዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ፤ “ጨካኝ፣ ዘረኛ፣ ራሳቸውን በመውደድና ከሁሉ በላይ በማድረግ የተኮፈሱ፣ ጭንቅላተ ጠባብ ዜጎች ያሉባት አገር መሆኗን ያሳየናል።” ብላ አስፍራለች አንጋ ሳንደርስ። ወደኛ አገር ስንመጣ፤ የመንግሥቱ ኃይለማርያምም ሆነ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥቶች ምን ተብለው እንደሚገለጡ እኔ ባሰፍር፤ ለቀባሪው ማርዳት ይሆንብኛል። የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ መንግሥት ኢትዮጵያ እና ሕዝቧ እንዴት ተብለን እንገለጣለን? ይሄን ወደፊት ለታሪክ እተወዋለሁ።
ወደ ትንታኔዬ ልመለስ። በአንድ አገር ያሉ ዜጎች፤ በአገራቸው የሚካሄደውን የፖለቲካ ክንውን የሚከታተሉት፤ እንደ የፖለቲካ ሂደቱ ዕውቀታቸውና የንቃታቸው ደረጃ ነው። ዜጎች ዕውቀታቸውና ንቃታቸው ከፍ ያለ ከሆነ፤ አብዛኛው ሕዝብ ማለቴ ነው፤ በመንግሥት ሥልጣን ላይ ያለው ክፍል እንደልቡ ያፈተተውን ከማድረግ ያግዱታል። በሌላ በኩል ደግሞ፤ በዕለት ተዕለት ኑሮው ላይ የተጠመደ፣ የፖለቲካ ዕውቀቱና ተሳትፎው ዝቅተኛ የሆነ ሕዝብ፤ በመንግሥት ሥልጣን ላይ የተቀመጡት የፈለጋቸውን ቢያደርጉም የሱ አጣዳፊ ጉዳይ ስለማይሆን፤ ያሻቸውን እንዲያደርጉ መንገዱን ይከፍትላቸዋል። ለዚህ ነው የአገሩ ሕዝብ ያለበት የፖለቲካ ዕውቀትና የንቃት ደረጃ አሽከርካሪ ነው ያልኩት። ሕገ መንግሥት፣ መተዳደሪያ ደንቦች፣ የተለያዩ ተቋማት፣ ሕግን ተርጓሚና ሕግ አስፈጻሚ አካላት፤ ቦታ ቦታ አላቸው። እኒህ እንግዲህ፤ ከራሳቸው ማንነት ጀምሮ እስከ አፈጻጸማቸው ድረስ፤ ተግባራዊ የሚሆኑትና አገልጋይነታቸው፤ ጥብቅና የሚቆሙላቸው ግለሰቦች እና ቡድኖች ሲኖሩ ነው። ለዚህ ነው ዋና ዋና ካልኳቸው ያላካተትኳቸው። በርግጥ ሕግን የሚያከብሩ ባለሥልጣናትና ሕዝብ ያለበት አገር፤ ቀድሞዉኑ ተገቢ ሕገ-መንግሥት እንዳለውና አስተዳደሩ ትክክለኛ እንደሚሆን ተጨባጩ ሀቅ ይመሰክራል።
ወደ ሁለተኛው ጉዳይ ልሂድ። ይሄ ሰፋ ያለ ትንታኔን ይሻል። በአንድ አገር ያሉ የፖለቲካ ልሂቃን ከፍተኛ ሚና አላቸው። በአብላጫው ብዙኀኑን ምሁራን የሚዘውራቸው፤ የየራሳቸው የአመለካከት መነሻ የሆኑት የአድሎዖ ሚዛናቸው ናቸው። እናም የነሱን ፍላጎት የሚጠመዝዙት እኒህ ሚዛኖች፤ በትክክል ሁሉን ነገር ሁሉም እኩል ከመመልከት ይልቅ፤ የተለያየ መነፅር አጥልቀው ብቅ እንዲሉ ያደርጓቸዋል። ስለዚህ ምሁራን ማለት የተለያየ አመለካከት ያላቸው እንጅ፤ አንድ እንዳልሆኑ ከወዲሁ ማስመሬ ይታሰብልኝ። እናም፤ በጭፍን ሁሉንም ምሁራን ባንድ ላይ አጅሎ፤ ትክክለኛ ወይንም ትክክለኛ ያልሆኑ ብሉ መፈረጅ አይቻልም። ከዚህ ተነስቼ ነው፤ በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙት የፖለቲካ ልሂቃን መሠሪነት ወሳኝ ነው ያልኩት። በአንድ የታሪክ ወቅት ባሉ ምሁራን መካከል ያለው ስምምነት ወይንም ተፎካካሪነት፣ ጥላቻ ወይንም በመንግሥታዊ ሥልጣኑ ያላቸው ቦታ፤ በአገሪቱ ላለው አስተዳደር በጎነት ወይንም በጎ አለመሆን ወሳኝ ነው። በምሁራን የመኢሶን አባላት የተደገፈው የመንግሥቱ ኃይለ ማርያም አረመኔ መንግሥት በጎ አልነበረም። ምሁራን፤ እንዳልተማረው ሕዝብ ሁሉ፤ ለአገር አሳቢ ወይንም የየራሳቸው ጥቅም አሳዳጅና ጨካኞች ሊሆኑ ይችላሉ። ምሁራን በብዛት በመንግሥት ሥልጣን ዙርያ ስለሚገኙ፤ የኒህ ተሳትፎ ከፍተኛ የአሽከርካሪ ወሳኝነት አለው። እናም ዋና ዋና ካልኳቸው አስቀምጨዋለሁ።
በአገራችን የፖለቲካ ሂደት ተሳታፊ የሆኑ ምሁራን ቁጥር በጣም አነስተኛ በነበረበት ሀቅ፤ አሁን ያለው ሕገ-መንግሥት ጸድቆ በሥራ ላይ ዋለ። የምሁራን ድርቀት ያደረበት የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት፤ በእወደድ ባይና ጥቅም አሳዳጆች ተሞልቶ፤ ሕገ-መንግሥቱ ብቻ ሳይሆን አገር አፍራሽ የሆነ የአስተዳደር ሥርዓት በአገራችን አስቀመጠ። ይህ ሂደት አሁንም በተተኪው ተረኛ የባለሥልጣን ቡድን እንደቀጠለ ነው። አሁን ያለውን የአገራችንን የፖለቲካ ሥልጣን የጨበጠውን ክፍል ለመረዳት፤ የዚህን ክፍል የትውልድ ሂደቱን፣ አስተዳደጉንና ያሳለፈውን ታሪክ መመልከት ግድ ይላል። ከሰማይ ዱብ ያለ አካል አይደለም። ያለው መንግሥት ደግሞ ዶክተር አብይ አሕመድ ብቻ አይደሉም። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ ብቻቸውን ለውጥ አይስከትሉም። ያለው መንግሥት ብልፅግና ብቻም አይደለም። መንግሥቱ፤ ከመሪ ግለሰቡና ከመሪ ፓርቲው ሌላ፤ ተከታይና ደጋፊዎች ብቻ ሳይሆን፤ የራሱ የሆነ ሕገ-መንግሥት፣ የራሱ የሆነ ደንብና የራሱ የሆነ አስራር ያለው አካል ነው። እንደ ተቋም፤ መሠረት አበጅቶ፤ ራዕዩን በሕዝቡ ላይ እየጫነ ያደገ ክስተት ሆኗል፤ ራዕዩ በተለያየ መመዘኛ ምንነቱ ከአንድ ጫፍ እስከ ሌላው ጫፍ ተለያይቶ ቢተረጎምም። ይህ መንግሥት መሠረቱ ፀረ-ኢትዮጵያዊነት ነው። ስለሆነም፤ ይዘግይም እንጂ፤ በኔ እምነት፤ ኢትዮጵያዊ ባለመሆኑ ከሳሚ ነው። አንድም አገር በታትኖ ራሱ ይጠፋል፤ አለያም ሕዝቡ በኢትዮጵያዊነቱ ተነስቶ ኢትዮጵያን ያቆማታል። አገር ወዳድነት የሌለው የአገር ሥልጣን፣ አገር ወዳድነት የሌለው ጀግንነት፤ ቅንነት የሌለበት ቅን ነኝ ባይነት፣ ራስን በአገር ንብረት እያሳደጉ የአገር ብልፅግና፤ ሩቅ አያስኬድም። ለዚህ ነው የዚህ መንግሥት አይቀሬ ከሳሚነቱ። በተጨማሪ ደግሞ፤ ሌሎች ከሚያከስሙት ይልቅ፤ በራሱ መክሰሙ የበለጠ ዕድል አለው።
ወደፊታችን ምን ይመስላል?
አሁን አገራችን በቋንቋ የተለያዩ የጎሳ ክልሎች ስብስብ ሆና በትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር እንደተዋቀረች፤ ተረኛው ገብቶ ይሄኑ ቀጥሎበታል። ሕገ-መንግሥቱ ይሄን ሕጋዊ አድርጎ አስቀምጦታል። ኢትዮጵያዊ ግለሰብ የለም። ያለው የክልሉን ታርጋ የለጠፈ ኢትዮጵያዊ ነው። እናም ታርጋው እንጂ ኢትዮጵያዊነቱ የማይገልጠው ግለሰብ፤ ውስን መብት ነው ያለው። አብዛኞች ኢትዮጵያዊያን ከአንድ ጎሳ ሳይሆን ከተለያዩ ጎሳዎች የተገኙ ናቸው። ይህ ብዙኅነት ያለው ክፍል ግን፤ በአገራችን ሕገ-መንግሥት ቦታ የለውም። እናም ለኢትዮጵያ ሊታገል የሚችለው ሕዝብ፤ ትርጉም የሌለው ሆኖ በሕገ-መንግሥቱ ታጥሯል። ቀሪው ቅድሚያ ክልሉን መጠበቅ ዋና ኃላፊነቱ ሆኖ፣ መብቱን በሙሉ ለክልሉ አስረክቦ የክልሉ አስረኛ ሆኗል። ለዚህ ነው የትግሬዎች ሲኖዶስና አምልኮት፣ የኦሮሞዎች ሲኖዶስና አምልኮት፣ እያለ እያንዳንዱ ክልል በማንኛውም መንገድ ራሱን የቻለ መንግሥት፣ አገር፣ ሃይማኖት፣ የራሱ ቋንቋ ያለው. . . ወዘተ ወደ መሆን እየገሰገሰ ያለው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሒዶ ቤተክርስትያን ጥፋቷ፤ ኢትዮጵያዊ መሆኗ ነው። የኢትዮጵያ እስልምና ኅብረተሰብ ጥፋታቸው ኢትዮጵያዊ መሆናቸው ነው። ሌሎችም በኢትዮጵያዊነታቸው የሚያምኑ ተከታዮች ያሉባቸው የእምነት ስብስቦች ይሄው ውንጀላ ተለጥፎባቸዋል። ሃይማኖትን በተመለከተ፤ ኢትዮጵያዊት የፕሮቴስታንድ ተከታይ የሆነችው እህት ሰብለ በቀለ ግዛው በትክክል አስቀምጣዋለች።
ታዲያ ይሄን መከፋፈል አልቀበልም ያለውና ግራ የተጋባው የታጋዮች ሰፈር አጀንዳው ምንድን ነው? የትግሬው መጎዳት አጀንዳ ለሆነበት ትግሬ፣ የኦሮሞ መጎዳትና ጥቅም አጀንዳው ለሆነበት ኦሮሞ፣ የአማራው መበደል አጀንዳው ለሆነበት አማራ፣ የሲዳማው ራሱን ችሎ አለመከለል አጀንዳው ለሆነበት ሲዳማ፣ . . . ወዘተ. ትግሉ ምንድን ነው ትርጉሙ? ለራሱ የክልል ወገኑ ጥብቅና መቆም? ወይንስ ኢትዮጵያ በኢትዮጵያዊነት ላይ የተመሠረተች እንድትሆን መታገል? ይህ ነው የታጋዩን ክፍል ወጥሮ የያዘው ጥያቄ። በጎሳ እንታገል ወይንስ በኢትዮጵያዊነት? የትጥቅ ትግል ነው ወይንስ የሰላማዊ ሰልፍና የአቤቱታ? አክራሪ እንሁን ወይንስ ለዘብተኛ? ባገር ውስጥ ነው ወይንስ በውጪ መደራጀት? በውጪ በሚገኘው ክፍል ደግሞ፤ መሳሪያ ገዝተን እንሥጣቸው ወይንስ ገንዘቡን እንላክላቸው? እኒህ በሽፍንፍን የተቀመጡ ጉዳዮች ናቸው። እኔ ለነዚህ መሠረት የሆነውን የአገር እንዳገር መቀጠል ወይንም አለመቀጠል አጀንዳ እስካልተነጋገርንበት ድረስ፤ የእሬያ መታጠብ ሆኖ ባለንበት መዳከር ነው፤ እላለሁ።
ታሪክን በትክክል መማሪያ አድርጎ ከመጠቀም ይልቅ፤ ግለሰቦች ለሚፈልጉት ግብ ጠምዝዞ መተርጎምና ወይንም ፈጥሮ መውሰድ፤ በአገር ዘለቄታ የሆነ መፍትሔ አያስከትልም። ለትክክለኛው ታሪክ ጥብቅና መቆም ቢያስቸግርም፤ ጠምዛዡም ጠምዛዥ አለበት! ጉዳዩ በትረ-ሥልጣኑን የጨበጠው ማነው? ነው። በርግጥ እንደሚባለውም፤ ሥልጣን ያባልጋል። ፍጹም ሥልጣን ደግሞ ለወሰን የለሽ ብልግና ይዳርጋል። ቁንጮው ላይ የተቀመጡት ሥልጣናቸውን ለመጠበቅ ሲሉ የማይፈጽሙትና የማይደፍሩት የግፍ ወሰን የለም። ይህ በምንም መንገድ ትክክለኛ አይደርጋቸውም።
ወደ ውስጣችን እንመለከት። ሁሉን አሰባሳቢ የመወያያ መድረክ በሌለበት ሀቅ፤ በአብዛኛዎቻችን የሚንጸባረቀው፤ እያዳንዳችን በቡድንም ሆነ በግለሰብ፤ የየራሳችንን አመለካከትና መፍትሔ ብለን የምናምንበትን ለየብቻችን ይዘን መሮጥ ነው። በአገር ውስጥም ሆነ በውጪ አገር፤ ኢትዮጵያዊያን ባንድ ተቀምጠን፣ የተለያዩ አቋሞችን ይዘን፣ በትክክለኛ መንገድ ተወያይተን፣ የምንስማማበትን እና የምንለያይበትን አስፍረን፣ ወደሚቀጥለው መሄድ አልታየብንም። የዚህ አንጸባራቂ፤ በብዛት የተፈለፈሉት ፓርቲዎች፤ ተቀራርበው የሚስማሙበትንና የሚለያዩበትን አሰቀምጠው በሚስማሙባቸው አብረው ጉልበታቸውን አጠናክረው በጥቂት ፓርቲዎች ዙሪያ መሥራቱ ላይ ዳ እንዳላቸው መታየቱ ነው። በጣም ጥቃቅን በሆኑ መለያያ ነጥቦች ለየብቻቸው እንደሄዱ ዓይተናል።
ታዲያ በዚህ ሀቅ እየዋኘን፤ ምን ይመጣል? ብለን እናስባለን። እስካሁን እኔም እንደሌሎቻችሁ፤ ችግሩን ከመዘርዘርና በጉዳዩ ከማላዘን አልወጣሁም። ነገር ግን ሀቁን በግልጥ አውጥቼ አስቀምጨዋለሁ። “የት ሄደች ኢትዮጵያ!” የሚል የልቤን ቁስል የሚገልጥ ግጥም ሰሞኑን ለወዳጆቼ ልኬ ነበር። ያንተ ብቻ አይደለም፤ የኛም ነው! ያሉኝ አሉ።
ወደፊት ልመልከት። ሕገ-መንግሥቱ ትክክለኛ አይደለም። ትክክለኛ ያልሆነ ሕገ-መንግሥት ደግሞ አገርን ወደ ዝቅጠት እንጂ ወደ ሰላምና ሥልጣኔ አይወስድም። መንግሥትን በተመለከተ፤ ቶማስ ፔን፤ “መንግሥት፤ በጣም ጥሩ በሆነበት ጊዜ እንኳን አስፈላጊ መጥፎ አካል ነው። አስከፊ በሆነበት ወቅት ደግሞ፤ መጥፎ አንገፍጋፊ አካል ነው!” ብሏል። እኛው ፈጥረን እኛው ተጎዳን! ሲል ይገልጠዋል። በኛም አገር የሚታየው ይሄው ሀቅ ነው። አዎ! መንግሥት ያስፈልጋል። የሚያስፈልገው ደግሞ ትክክለኛ የሆነ መንግሥት ነው። በኢትዮጵያ ትክክለኛ መንግሥት የለም።
መቋጫ! ከላይ የመንግሥቱንና የሕግ-መንግሥቱን ምንነት ገልጫለሁ። ትግሉ በተናጠልና በያለንበት ጎሳ እስከሆነ ድረስ፤ ኢትዮጵያን የማፍረስ ሩጫ ዙሪያ ሽክርክር ነው። እንዱ ጎሳ በሌላው ላይ የበላይነቱን ጭኖ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ አትሆንም። በትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ያየነው ይሄኑ ነው። አሁን ደግሞ ተረኛው ያንኑ እየዘመረ ነው። ክልሎች ተለያይተው አገር ሆነው ሊቀጥሉ የሚችሉበት እውነታ የለም። ክልሎች ትክክለኛ ወሰኖች አይደሉም። እናም ርስ በርስ መናኮርና መባላት እንጂ ጎረቤት ሆኖ መቀጠሉ ሕልም ነው። ከዩጎዝላቪያና ከሱማሊያ መማሩ ይረዳል። አንድና አንዱ መፍትሔ በአገር ደረጃ መሰባሰቡና መምከሩ ነው። እኔ መፍትሔ የምለው አብረን እንምከር ነው። መነሻው ይሄ ሆኖ፤ በምክር የምንደርስበት ውሳኔ ገዢ ይሆናል። የአንድ ሰው የግል እምነት የአንድ ሰው ነው። ብዙዎች የሚደርሱበት ምክር አገር ይመራል።
እስኪ ይሄ መነሻ ሆኖ ምክሩን እንድፈረው።
አንዱ ዓለም ተፈራ