September 30, 2022
30 mins read

ኦ – ብልፅግና. . . . አ – ብልፅግና (ኤፍሬም ማዴቦ)

murderer Abiy Ahmedኤፍሬም ማዴቦ ([email protected])

በህገ መንግስቱ ውስጥ ቋሚ ቦታ ያለው “ህብረብሔራዊ ፌዴራሊዝም” በቋሚነቱ ይቀጥላል እንጂ ለድርድር ቀርቶ ለውይይትም አይቀርብም። የብሔር ፌዴራሊዝምን ማንም ሊነካው የማይችል የኦሮሞ ቅዱስ ዕቃ ነው ብሎ ከማመኑ በፊት ኦህዴድ ወደ ምርጫ መግባት አይችልም። ጀዋር መሐመድ 2010  

አሁን ባለው ብሔር ተኮር ፌዴራሊዝም ላይ መግባባት ኖሮን የአንድነት ግንባር መፍጠር አለብን፣ ኦህዴድ ኮምፓሱ እንደጠፋበት መርከብ እዚህም እዚያም እንዲል አንፈቅድም፣ እነሱም ኦህዴድ የኛ ፓርቲ ነው ብለው ሊነግሩን አይችሉም ወይም የፈለጉትን ማድረግም አይችሉም  . . . . ይህንን በፍጹም አንፈቅድም። ጀዋር መሐመድ 2012

በአገራችን ለዘመናት የህዝቦች የእኩልነት ጥያቄዎች በህዝቦች መራራ መስዋዕትነት ህገ መንግስታዊ እውቅና እንዲያገኝ የተደረገው የብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በህገ መንግስቱ የተቀመጡ መብቶች ያለምንም መሸራረፍ ተፈጻሚ እንዲሆኑ ፓርቲያችን ይሰራል። ብልፅግና ፓርቲ ምርጫ ማኒፌስቶ

ጀዋር መሐመድ በ2018 እና በ2019 ዓ.ም. ከላይ በተቀመጡት ሁለት አረፍተ ነገሮች ውስጥ ቋጥሮ ያስተላለፋቸው ቁልፍ መልዕክቶች ብልፅግና ፓርቲ ከተመሰረተ ከአመት በኋላ የምርጫ ማኒፌስቶዉን ሲጽፍ እንደመመሪያ መጠቀሙን ማኒፌስቶው በግልጽ ይናገራል። ጠ/ሚ አቢይ አህመድ የአራት ብሔር ድርጅቶች ጥምረት የሆነው ኢህአዴግ ወደ አገራዊ ፓርቲነት ይለወጣል የሚል ቃል ከአፋቸው ሲወጣ፣ አባባሉ ወይም ዉሳኔው ኢትዮጵያ ዉስጥ የብሔር ፖለቲካ የመጨረሻው መጀመሪያ ነው ያሉ ብዙዎች ነበሩ። ነገር ግን ነገሩ “ድመት መንኩሳ ጠባይዋን አትረሳ” ነውና ስምንት የብሔር ድርጅቶችን አቅፎ በህዳር ወር 2012 ዓም የተመሰረተው ብልፅግና ፓርቲ ሳልስቱን ሳያከብር ነው “ኦሮሞ ብልፅግና”፣ “አማራ ብልፅግና” እያለ የስምንቱን ድርጅቶች ውህደት የውኃና ዘይት ውህደት ያስመሰለው።

ኦሮሞ ብልፅግናና አማራ ብልፅግና ሲባል ልዩነቱ የስም ብቻ ይመስላል። አይደለም! በሁለቱ ቡድኖች መካከል ያለው ልዩነት የፖለቲካ ሥርዓታችን መሰረት ዜግነት መሆን አለበት የሚልና፣ የለም የፖለቲካ ሥርዓታችን መሰረት ብሔር ሆኖ መቀጠል አለበት የሚል ትልቅ የፍልስፍና ልዩነት ነው። የሚገርመው ብልፅግና ፓርቲ በምርጫ ማኒፌስቶው ላይ ሁለቱንም ቡድኖች ለማስደሰት ሞክሯል። እንዴት?

ብልፅግና ፓርቲ ለ2013ቱ ምርጫ ባወጣው ማኒፌስቶ ምዕራፍ 1.1.1 ላይ እንዲህ የሚል አረፍተነገር አስቀምጧል – “ፓርቲያችን የህዝብ ሉዓላዊነት ተከብሮ የመንግስት ሥልጣን በህዝብ ይሁንታና ውክልና በዲሞክራሲያዊ ምርጫ ሊገኝ ይገባል ብሎ ያምናል”። በዚሁ ማኒፌስቶ ምዕራፍ 1.3.4 ላይ ደግሞ ህገ መንግስቱ ለብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የሰጠውን መብት ሳይሸራረፍ እናከብራለን ይላል። ኢትዮጵያ ውስጥ የሉዓላዊነት ማደሪያው ብሔር፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች እንደሆኑ ህገመንግስቱ በማያሻማ ቋንቋ ይናገራል፣ ታድያ እንዴት ሆኖ ነው ይህንን ህገ መንግስቱ ለብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የሰጠውን መብት ሳይሸራረፍ እናከብራለን የሚሉት ብልፅግናዎች የህዝብን ሉዓላዊነት አናስከብራለን የሚሉን? በነገራችን ላይ ብሔር፣ብሄረሰቦችና ህዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤት ናቸው በሚለውና የኢትዮጵያ ህዝብ የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤት ነው በሚለው አባባል መካከል ከፍተኛ ልዩነት አለ፣ልዩነት ብቻ ሳይሆን አባባሉ ተቃርኖም አለው። ብልፅግና አማራና ብልፅግና ኦሮሞ የዚህ ተቃርኖ ታላቅና ታናሽ  ልጆች ናቸው። ማን ታላቅ፣ ማን ታናሽ እንደሆነ “ሳይሸራረፍ እናከብራለን” የሚለው ሐረግ በግልጽ ይናገራል።

ብልፅግና ፓርቲ በወደፊቷ ኢትዮጵያ ላይ እንዲህ አይነት ከፍተኛ ተቃርኖ ያላቸውን ሁለት ግዙፍ ቡድኖች አቅፎ ነው ኢትዮጵያን አፍሪካዊት የብልፅግና ተምሳሌት እናደርጋለን ብሎ ጉዞ የጀመረው። እንኳን የአገር ጉዞ የሁለት ሰዎችም ጉዞ መግባባት ይፈልጋል፣ በተለይ ዛሬ ኢትዮጵያ ላለችበት ታሪካዊ ወቅት ደሞ በአንድ አፍ የሚናገር አመራር ያስፈልጋልና፣ ይህ አማራና ኦሮሞ ብልፅግና የሚሉት ዕዳ ባስቸኳይ ተከፍሎ ካካለቀ፣ በዕዳው የሚጠየቀው ብልፅግና ፓርቲ ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ነው።

ብልፅግና ፓርቲን ገና በልጅነቱ የተጠናወተው ‘አማራ-ኦሮሞ’ ብልፅግና የሚባል ልዩነት የስም ልዩነት ብቻ አይደለም፣የፖለቲካ ልዩነት ነው ተብሎ የሚታለፍም አይደለም። ታሪኩ ብዙ ነው። ህወሓት በብሔር ፖለቲካ ኮትኩቶ ያሳደጋቸው ኦዴፓዎች አገራዊ አጀንዳ ባለው ብሔራዊ ፓርቲ ውስጥ መካተት በፍጹም አልተዋጠላቸውም፣ በወቅቱ ከፍተኛ የህዝብ ድጋፍ ካላቸው የብልፅግና ፓርቲ አባት ጋር ፊት ለፊት መላተምም አልፈለጉም። ለዚህ ነው መደመሩም መቀነሱም አልሆን ብሏቸው በብልፅግና ጥምቀት እስኪጠመቁ ድረስ መሃል ላይ መቆሙን የመረጡት። ኦዴፓ መሃል ሰፋሪ ሆኖ “ኦሮሞ ብልፅግና” መባል ከመረጠ . . . . .  መከተል የለመደው አዴፓ ሌላ ምን አማራጭ አለው?

የኦሮሞ ብልፅግና እና የአማራ ብልፅግና አሁን ኢትዮጵያ ዉስጥ ባለው ብሔር ተኮር የፖለቲካ ሥርዓት  ለይም ሆነ የወደፊቷ ኢትዮጵያ ምን መምሰል አለባት በሚለው ጥያቄ ላይ ያላቸው አቋም ተቃራኒ ነው። የኦሮሞ ብልፅግና ፓርቲና አብዛኛው የኦሮሞ ልህቅ ታማኝነቱ ለብሔር ፖለቲካ ነው። የአማራ ብልፅግና ፓርቲና አብዛኛው የአማራ ልህቅ ግን ታማኝነቱ ለአገራዊ ፖለቲካ ነው፣ ሆኖም ይህ ታማኝነት ከቅርብ ግዜ ወዲህ በከፍተኛ ፍጥነት እየተሸረሸረ ነው። ለዚህ መሸርሸር ዋናው ምክንያት በአንድ በኩል ህወሓት ሂሳብ አወራርዳለሁ ብሎ አማራ ላይ ይዞት የመጣው የህልውና አደጋ ሲሆን፣በሌላ በኩል ደግሞ በኦሮሞ ልህቃንና በአማራ ልህቃን መካከል ያለው ከፍተኛ የፖለቲካ ልዩነትና ይህንን ልዩነት ተከትሎ በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች በአማራ ተወላጆች ላይ በተደጋጋሚ የሚደርሰው መፈናቀል፣ ስደትና የጅምላ ግድያ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ አማራውን ወደ ጫፍ ስለገፋው ነው።

የኦሮሞ ልህቃን ማነው በኦሮሞ ፖለቲካ የበላይ መሆን ያለበት በሚለው ጥያቄ ላይ ቢለያዩም፣ ኦሮሚያ በሚባለው ክልል፣ በ“ኦሮሞ ጥቅም” እና በአዲስ አበባ የባለቤትነት ጥያቄ ላይ ተናበው ይሰራሉ እንጂ አይለያዩም። ይህ ደሞ የተለያዩ የኦሮሞ ድርጅቶች በሚያወጧቸው መግለጫዎችና፣ መሪዎቻቸውና ደጋፊዎቻቸው በሚሰጧቸው ቃለመጠይቆች ላይ በተደጋጋሚ የታየ እውነት ነው። ለምሳሌ፣ በቅርቡ የኦሮሚያ ክልል መንግስት ባወጣው መግለጫ፣ ኦሮሚያ ውስጥ ባልታጠቁ ሰዎች ላይ የጦር ወንጀል የፈጸሙት “የአማራ ክልል መንግሥት ታጣቂዎች” ናቸው፣የግጭቱ መነሻ “ጽንፈኝነት እና የፖለቲካ አሻጥር” ነው ሲል የአማራን ክልል መንግስት ከሷል።  ይህንን ክስ ተከትሎ የአማራ ክልል በሰጠው ምላሽ፣ የኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ ባወጣው መግለጫ “እራሱ ከሳሽና ፈራጅ” ሆኗል ሲል መግለጫውን ኮንኗል።

አማራ ብልፅግና እና ኦሮሞ ብልፅግና የዛሬዋንና የወደፊቷን ኢትዮጵያ በተመለከተ በመካከላቸው ከፍተኛ  ልዩነት አለና አንዱ ሌላኛውን መኮነኑ ብዙም አይገርምም። የብልፅግና ፓርቲ ቁጥር አንድ ተቀናቃኝ የሆነውና በፕ/ር መረራ ጉዲና የሚመራው ኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ ፓርቲ ያወጣው መግለጫ ግን ከላይ የተለያዩ የኦሮሞ ድርጅቶችና ልህቃን ዋና ዋናዎቹን የኦሮሞ ጉዳዮች በተመለከተ ተመሳሳይ አቋም አላቸው የሚለውን ሃሳብ ሙሉ በሙሉ የሚደግፍ ነው። እንዲህ ነበር ኦፌኮ ያለው – “ከመደበኛው የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ባልተናነሰ መልኩ ፋኖ የሚባለው በአማራ ጽንፈኛ ኃይሎች የተገነባውና በክልሉ መንግስት እውቅና ታጥቆ የሚንቀሳወሰው የጥፋት ቡድን በተለያዩ የኦሮሚያ ዞኖች ሰብሮ በመግባት ብሔርን የለየ የጅምላ ፍጅት ሲያካሂድ፣ ቤቶችን ሲያቃጥል፣እህልና ከብቶችን ሲዘርፍ ቆይቷል”

ብዙዎቻችን አማራ ዘረኛ ሆነ፣ አማራ ከኢትዮጵያዊነት ሸሸ እያልን አማራን እንከሳለን። የአማራ ብሔረተኝነት እየገነነ የመጣው በአንድ በኩል ደደቢት በረሃ ዉስጥ በህወሓት የተሸረበና በተደጋጋሚ በተግባር የታየ በአማራው ላይ ያነጣጠረ የጥፋት ዘመቻ በመኖሩ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከላይ በተገለጸው መልኩ የተለያዩ የኦሮሞ ድርጅቶች አማራ ላይ በመተባበራቸውና የተከበሩ ዶር ሃንጋሳ ኢብራሂም በቅርቡ እንደተናገሩት ኦሮሚያ ውስጥ በአማራ ተወላጆች ላይ የሚደረገው ጭፍጨፋ መንግስታዊ ድጋፍ ያለው መሆኑ ነው።

በዛሬዋ ኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ላይ ግልጽ የሆነ ልዩነት ያላቸው ሁለት ትልልቅ ቡድኖች አሉ። እነዚህ ሁለት ቡድኖች በአቋማቸውም በፖለቲካ አሰላለፋቸውም “አማራ ብልፅግና” እና ”ኦሮሞ ብልፅግና” ዉስጥ ካሉ ኃይሎች ጋር በቅርብ የተሳሰሩ ናቸው። አንደኛው ቡድን እራሱን “ፌዴራሊስት ኃይሎች” እያለ የሚጠራው የብሔር ፖለቲካ አራማጆች ስብስብ ሲሆን ሲሆን፣ የዚህ ቡድን መንፈሳዊ መሪ ኦሮሚያ ክልል ነው፣ ሌላው የአንድነት ኃይል የሚባለው ስብስብ ሲሆን የዚህ ቡድን መሪ ደሞ አማራ ክልል ነው።

“ፌዴራሊስት ኃይሎች” ከመንፈሳዊ መሪያቸው ከኦሮሚያ ክልል ጋር ይግባባሉ፣ይናበባሉ፣የአላማ አንድነት ስላላቸው አብረው ይሰራሉ እንጂ እርስ በርስ አይባሉም። “ኢትዮጵያ” ፣ “ኢትዮጵያ” የሚለውና እራሱን የአንድነት ኃይል ብሎ የሚጠራው ቡድን ግን በውጭ አገሮችም ሆነ በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች በቁጥር ከፍተኛ ተከታይ ያለው ቡድን ቢሆንም፣ የቁጥሩን ያክል የተከፋፈለ፣ እርስ በርሱ የሚባላ፣በሆነው ባልሆነው የሚጨቃጨቅና ፅንፈኛው፣ ግራ ዘመሙ፣ቀኝ ዘመሙና በሁለቱ መሃል ላይ ያሉ ኃይሎች የሚገኙበት ከራሱ ጋር የተጣላ ስብስብ ነው። የአንድነት ኃይል በሚባለው ቡድን ውስጥ የሚገኙ ኃይሎችን የሚያገናኛቸው “አንድነት” የሚለው ቃል ብቻ ነው። ይህ ስሙን ቀይሮ “የልዩነት ቡድን” መባል ያለበት ቡድን ከመንፈሳዊ መሪው ከአማራ ክልል ጋርም አይግባባም።

ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ የምናየው የፖለቲካ ምስቅልቅል እነዚህ ሁለት ኃይሎች የኢትዮጵያን ፖለቲካ ለመቆጣጠርና የወደፊቷን ኢትዮጵያ በአምሳያቸው ለመቅረጽ የሚያደርጉት ትግል ዉጤት ነው። መከራው፣ግፉ፣ስደቱ፣መፈናቀሉና ሞቱ አማራው ላይ የበረከተው አማራው የሚገኝበት ጎራ የማይናበብ፣የማይግባባ አንድ ላይ ቆሞ እራሱን መከላከል የማይችል ሳይሆን ያልቻለ በመሆኑ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ በቅርቡ ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቀው አገራዊ ምክክር፣ እነዚህን ሁለት ቡድኖች አግባብቶ ኢትዮጵያ የህዝቦቿ እንጂ የአንድ ብሔር የበላይነት የማይነግስባት አገር መሆኗን ካላረጋገጠ እንደ አገር አደጋ ላይ ነን።

የአማራ ክልል እንደ ክልልም እንደ ፖለቲካ ማህበረሰብም ይህ ነው ተብሎ የሚነገር መሪም አመራርም የሌለው በአክቲቪስቶች፣ በባለኃብቶች፣ በዩቲዩብ አርበኞችና በተለያዩ የጎበዝ አለቆች የሚመራና በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ መጫወት የሚገባውን ትልቅ ሚና የዘነጋ ክልል ነው። የህወሓት ኃይሎች ወሎ፣ጎንደርና ሰሜን ሸዋ ድረስ ያለማንም ከልካይ እየዛቱ መጥተው ይህንን ህዝብ የዘረፉት፣ያፈናቀሉትና የጨፈጨፉት አማራው ባለፉት ሰላሳ አመታት በፖሊሲ ደረጃ በኢትዮጵያ የፖለቲካ፣ የኤኮኖሚና ማህበራዊ ህይወት ውስጥ መጫወት ያለበትን ሚና እንዳይጫወት ስለተደረገ ነው። ይህ ፖሊሲ ዛሬ በስራ ላይ አለ ብዬ ለመናገር አልደፍርም፣የለም ብዬ ለመናገርም እርግጠኛ አይደለሁም።

የአማራን ክልል ተቋማዊ በሆነ መልኩ የሚመራው ብልፅግና ፓርቲ ነው፣ ነገር ግን የአማራን ህዝብና የአማራ ብልፅግና ፓርቲን የሚያገናኛቸው እጅግ በጣም ቀጭን ክር ነው። ይህ ምን ግዜም ሊበጠስ የሚችል ክር እንደየሁኔታው ሊጠንክርና ጥንካሬው ለሌሎች “ኢትዮጵያ” ከሚባል ትልቅ የፖለቲካ ማህበረሰብ ዉጭ ሌላ አማራጭ ለሌላቸው አካባቢዎችም ተስፋ ሊሆን ይችላል። ይህ እንዲሆን የአማራ ክልል መሪዎች የአማራን ህዝብ መፈናቀል ማስቆም አለባቸው፣የአማራን ህዝብ  ስደት ማስቆም አለባቸው፣የአማራን ህዝብ ሞትና መከራ በድፍረት በቃ ማለት አለባቸው፣ ከሁሉም በላይ ግን የአማራ ህዝብ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ መጫወት ያለበትን ሚና ማወቅና አማራ ይህንን ሚናዉን እንዲጫወት አስፈላጊውን ሁሉ ማድረግ አለባቸው። የአማራ መሪዎች ይህንን ማድረግ የሚችሉትና ማድረግ ያለባቸውም “አማራ ብልፅግና” ፓርቲ ሆነው ሳይሆን የአማራ ህዝብ ትክክለኛ መሪ ሆነው ነው። የአማራ መሪዎች ታማኝነት ለአማራ ህዝብ ነው እንጂ ለብልፅግና ፓርቲ አይደለምና፣ እንዲህ አይነት ህዝባዊ ታማኝነት ሲኖር ብቻ ነው ብልፅግና ፓርቲም ሆነ ሌላ በምርጫ አሸንፎ ክልሉን የሚመራ ፓርቲ ከአማራ ህዝብ ጋር እጅና ጓንት ሆኖ ክልሉንም ኢትዮጵያንም ማሳደግ የሚችለው።

ህወሓት ከሎሌው ከኦነግ ጋር ኢትዮጵያ ውስጥ የገነባው የብሔር ፖለቲካ ሥርዓት ኢትዮጵያዊያን ማንነታቸውን ብቻ ሳይሆን ገሃዱን አለም ጭምር በብሔር መነጽር ብቻ እንዲመለከቱ በማድረጉ ዛሬ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የኢትዮጵያ ህዝብ ኢትዮጵያዊ ማንነቱን ከመናገር እኔ ኦሮሞ ነኝ፣ ትግሬ ነኝ፣ ሲዳማ ነኝ፣ ወላይታ ነኝ ወዘተ ማለት ይቀለዋል። ይህ ግራ የተጋባ ቁንፅል አመለካከት ሁላችንም የምንጋራውንና የአንድ አገር ዜጎች የሚያደርገንን ኢትዮጵያዊ ማንነት ረግጠን፣ የማንጋራውንና የሚለያየንን የብሔር ማንነት እንድንመርጥ አድርጎናል፣እኛ ኢትዮጵያዊያን የአንድ አገር ልጆች መሆናችንን ዘንግተን እርስ በርስ እንድንገዳደል አድርጎናል፣ ስለ ጋራ አገራችን ሳይሆን ስለጎጣችን ብቻ እንድናስብ አድርጎናል። ትናንት “ኦሮሚያ ላይ የሚፈሰው ደም የኔም ደም ነው” እያለ ህወሓትን ከሥልጣን ያባረረ ህዝብ፣ ዛሬ እሱ እራሱ ጎራ ለይቶ አንዱ አሳዳጅ ሌላው ተሳዳጅ ሆኗል። ጀምበር የወጣችለት ጎራ ህወሓቶች የሚጠጡትን የመጠጥ አይነት፣ ህወሓቶች የሚበሉትን የምግብ አይነትና ህወሓቶች ያዘወትሩ የነበረውን የመዝናኛ ቦታ ይጠይቃል፣ቀን የጨለመበት ጎራ ደሞ ህወሓቶች ሂሳብ እናወራርዳለን እያሉ ይሳለቁበታል።

ኢትዮጵያዊያንን ሁሉ በእኩልነት የማያይ እንደዚህ አይነት የጨለማ አስተሳሰብ በምንም አይነት የወደፊቷ ኢትዮጵያ መሰረት ሊሆን አይችልም። በእኩልነት የማንጋራትንና የበላይና የበታች ሆነን የምንኖርባትን ኢትዮጵያ በጋራ ገንቡ ልንባል አይገባም። “ኢትዮጵያን አፍሪካዊት የብልፅግና ተምሳሌት እናደርጋለን” የሚለው መፈክር ሁላችንንም የሚያግባባውና በእርግጥም አገራችን ኢትዮጵያን የአፍሪካ የዕድገትና ልማት ተምሳሌት የምናደርጋት፣ እንደዛሬው በብሔር ተከፋፍለንና በየጎጣችን ተኮፍሰን ሳይሆን፣ በስምም በመልክም የማናውቃቸውን ሰዎች ካለምንም የጥርጣሬ መንፈስ ወገኖቼ ብለን እንድንጠራ የሚያስችለንና፣ አንድም ቀን በአይናችን አይተን በእግራችንም ረግጠን የማናውቀው የአገራችን መሬት በጠላት ሲደፈር በጋራ ህይወታችንን እንድንሰጥ ብርታት የሚሆነን ኢትዮጵያዊ ማንነትን የጋራ መታወቂያችን ስናደርግ ነው።

አገራችን ኢትዮጵያን በኤኮኖሚ የበለጸገች አገር የምናደርጋትና ከሩቅና ከቅርብ ጠላት መጠበቅ የምንችለው፣ የራሱን ህዝብ ከሌላ አገር ህዝብ አብልጦ የሚወድ ነገር ግን የሌላን አገር ህዝብ የማይጠላና የማያርቅ ኢትዮጵያዊ ብሔረተኝነትን ስንገነባ ብቻ ነው። በአለማችን ውስጥ አፈታሪክ እየፈጠረ የአንድ አገር ህዝብ የሚያደርገውን አገራዊ ብሔረተኝነት ሳይገነባ ነጻነቱንና የግዛት አንድነቱን አስከብሮ ካደጉ አገሮች ተርታ የተሰለፈ አንድም አገር የለም።

እኛ ኢትዮጵያዊያንም ባለፉት ሰላሳ አመታት እየረገጥን የመጣነውን ኢትዮጵያዊ ማንነት ከወደቀበት አንስተንና አክብረነው በዚህ ክቡር ማንነት ዙሪያ ካልተሰባሰብን፣ “ህብረብሔራዊ ወንድማማችነት” እያልን ሺ ግዜ ብናቆሎጳጵሰውና ብናሽሞነሙነው፣ህወሓቶች ያለበሱንን የብሔር ድሪቶ አውልቀን ሳንጥል ኢትዮጵያ የምትባል ተከብራ የምታስከብረን ትልቅ አገር መገንባት አንችልም። ኦሮሞ፣ አማራ፣ ትግሬ ወዘተ ብሎ የተደራጀ ነጠላ ብሔረተኝነት (Ethnic Nationalism) ከራሱ ውጭ የሆነውን ብሔር ያርቃል እንጂ አያቀርብም፣ይንቃል እንጂ አያከብርም፣እኔ እበልጣለሁ ይላል እንጂ ሌላውን በእኩልነት አይመለከትም። ያለፈው 30 አመት ታሪካችን የሚያሳየን ይህንን ሃቅ ነው። ብሔረተኝነት ትልቅ የጋራ አገር መፍጠር ቀርቶ ጎረቤት፣ ስራ ቦታና ትምህርት ቤት ውስጥ ጭምር የራሳችንን ብሔር እየመረጥን እንድንሰባሰብ ያደርገናል እንጂ ሰውን በሰውነቱ ብቻ እንድንመለከት አያደርገንም። ትግሬው፣ አማራው፣ ኦሮሞው፣ ሱማሌው፣ ወላይታው፣ ሲዳማው ወዘተ እንዱ የሌላውን ማንነት እያከበረም እየተጋራም የበለጸገች ኢትዮጵያን በጋራ መገንባት የሚችሉት በኢትዮጵያዊ ብሔረተኝነት (Ethiopian Nationalism) ጃንጥላ ስር ሲሰባሰቡ ብቻ ነው።

በሰሜናዊው የአገራችን ክፍል የሚካሄደውን ጦርነት በሰላም ለመጨረስ፣ በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች የሚታዩትን ብሔር ተኮር ግጭቶችና ግድያዎች ለማቆምና የኢትዮጵያን እንደ አገር ቀጣይነት ለማረጋግጥ ከፈለግን፣ ገዢው ፓርቲ ብልፅግና “ከፈተና ወደ ልዕልና” ከሚለው መሪ መፈክሩ ባሻገር አማራ ብልፅግና እና ኦሮሞ ብልፅግና በቅርጽ፣በይዘት፣ በአላማና በግብ አንድ መሆናቸውን በተግባር ማሳየት አለበት። ብልፅግና ፓርቲ፣ መንግስት፣የክልል መንግስታት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሌሎችም የተለያዩ ባለድርሻዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ብሔርና ፖለቲካ ተፋተው ዳግም አንድ ቤት ውስጥ አብረው መኖር እንዳይችሉ የተቻላቸውን ሁሉ ማድረግ አለባቸው። የኢትዮጵያ ህዝብ ልጆቹ በብሔር ጎራ ለይተው ሲተላለቁ ማየት አንገሽግሾታል፣ማለቂያ የሌለው የእርስ በርስ ጦርነት ሰልችቶታል፣የኢትዮጵያ ህዝብ ረሃብና መፈናቀል ሰልችቶታል፣ የኢትዮጵያ ህዝብ እየታደነ መገደል ሰልችቶታል፣የኢትዮጵያ ህዝብ በብሔር አጥር ዉስጥ መኖር ሰልችቶታል። ሠላም የናፈቀው የኢትዮጵያ ህዝብ ማየት የሚፈልገው የኦሮሞን በአማራ ላይ ወይም የአማራውን በኦሮሞ ላይ መተባበር ሳይሆን፣ ሁለቱ የአገራችን ትልልቅ ብሔሮች ኢትዮጵያን ከገባችበት ማጥ ውስጥ ለማውጣት ሲተባበሩ ማየት ነው።

 

 

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
Go toTop