July 5, 2022
53 mins read

የዐማራው መብትና ህልውና ካልተከበረ የማንም መብትና ህልውና ሊከበር አይችልም

አክሎግ ቢራራ
“ከሞትን አይቀር እንደ መይሳው ካሳ ታግለን፤ ተዋግተን እንሙት”

ኢትዮጵያዊ ፕሮፌሰር

እኔ እስከማውቀው ድረስ እኛ ኢትዮጵያዊያን ባለፉት አርባ ዓመታት፤ የንጹሃንን ሞት በሌላ ሞት፤ ረሃብን በረሃብ፤ እልቂትን በባሰ እልቂት፤ ስደትን በሌላ ስደት፤ መፈናቀልን በባሰ መፈናቀል፤ አገራዊ ወይንም ብሄራዊ ውርደትን በሌላ ውርደት (የሱዳን ወረራን መመልከት በቂ ነው) ወዘተ እንዴት ይሆናል እያልን ከመተቸትና ከመወቃቀስ ባሻገር መሰረታዊና መዋቅራዊ ተግዳሮቶችን (The root causes of Ethiopia’s dilemma) ምንድን ናቸው? ብለን፤ በጠረጴዛ ዙሪያ በጋራ ጥያቄዎችን አስተናግደን፤ ልዩ ልዩ የመፍትሄ አማራጮችን አቅርበን ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የአዲስ ምእራፍ መሰረት ልንፈጥር አልቻልነም።

በማህበረሰባዊ ሜድያ የሚለፈፈውን የስድብ ናዳ፤ ስም ማጥፋት፤ እርስ በእርስ መወነጃጀል ስመለከት የአሁኑ የአሁኑ የኢትዮጵያ ትውልድ “ተረግሟል” እንዴ? የሚል ጥያቄ አነሳለሁ። የምሁራኑንና ልሂቃኑን፤ የተፎካካሪ ፓርቲዎች መበታተን ስመለከት፤ እኛ ኢትዮጵያዊያን መቸ ይሆን ለዓላማ አንድነት፤ ልፍትህ-ርት፤ ለእውነተኛ የዜጎች እኩልነትና ዲሞክራሳዊ መብት በአንድነት የምንነሳው? የሚል ጥያቄ አቀርባለሁ።

እርስ በእርስ መወነጃጀሉ ለማንም አያዋጣም። የትግራይ ወይንም የኦሮሞ ወይንም የሶማሌ ወይንም የአፋር ወዘተ ተራ ሕዝብ የዓማራ ሕዝብ ጠላት አይደለም። በኢትዮጵያዊነት የዜግነት መብቱ ተማምኖ፤ ከነዋሪው ሕዝብ ጋር ተጋብቶ፤ ተዋልዶና ተዘማዶ በመላው ኢትዮጵያ የሚኖረው በብዙ ሚሊየን የሚገመተው የዐማራ ሕዝብ አፋሩ፤ ኦሮሞው፤ አኟኩ፤ ትግሬው፤ ጉራጌው፤ ወላይታው ወዘተ “ጠላቴ ነው” ብሎ የተናገረበትና የሰራበት ጊዜ ፈልጌ ለማግኘት አልቻልኩም።

ሆኖም፤ በዐማራው ላይ፤ በዐማራነቱ ብቻ፤ “የዐማራ ጠልነት” እና የእምየ ምኒልክ ከፍተኛ የነጻነት ሚና ከሃዲነት ብሂሎች ስር ሰደዋል። ህወሃትና ኦነግ ከተመሰረቱበት ጀምሮ እስካሁን የሚያካሂዱት የተቀነባበረ ጸረ-ዐማራና ፀረ-ኢትዮጵያ/ ኢትዮጵያዊነት ዘመቻ ከእነዚህ ጥላቻዎች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው። በቋንቋና በዘውግ ልዩነቶች ላይ የተመሰረተውን ፀረ-ዐማራ፤ ፀረ-ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ሕገ መንግሥት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የጫኑት እነዚህ ኃይሎች ናቸው።

ይህንን ለኢትዮጵያ አለመረጋጋት፤ ለዐማራው ተከታታይ ጭፍጨፋ፤ ለድህነትና ለኋላ ቀርነት ምክንያት የሆነ ተከታታይ ሁከት ተግባራዊ ያደረጉት የውስጥ ሽብርተኛ ኃይሎች ድርጊቶቻቸውን የሚፈጽሙት ደግሞ ከኢትዮጵያ የውጭ ጠላቶች፤ በተለይ ከግብፅ መንግሥት ጋር እያበሩ ነው።

በሁኑ ፈታኝ ወቅት፤ የግብፅና በጦር ኃይሎች የበላይነት በጀኔራል አልቡህራን የሚመራው የሱዳን መንግሥት ዋና ትኩረት በኦሮምያ ክልል፤ በተለይ በወለጋ የሚኖረው የዐማራው ሕዝብ የኦነጋዊያና ተባባሪዎቻቸው ሽብርተኞች ኢላማ እንዲሆን፤  የዐማራው ሕዝብ ጥላቻ ከፍ እንዲል፤ መላው የዐማራ ሕዝብ እንዲማረርና በጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ መንግሥት ላይ እንዲነሳ ለማድረግ እንደ ሆነ እገምታለሁ።

ኢትዮጵያዊያን፤ በተለይ የዐማራው ሕዝብ የዛሬ ሁለት ሳምንት በወለጋ የተካሄደውን የዐማራ ጭፍጨፋ እያወገዙ፤ ጨፍጫፊዎቹ በሃላፊነት ለሕግ ይቅረቡ እያለ በሚንቀሳቀስበት ወቅት፤ በቀለም፤ ወለጋ፤ ኦሮምያ፤ በአሜሪካ የነጻነት ቀን (July 4, 2022) ከ 800 በላይ ዐማራዎች ተጨፍጭፈዋል።  የግብፅ እጅ እንዳለበት በብኩሌ አልጠራጠርም። ምክንያቱን የሱዳንን ወረራ በሚመለከት በእንግሊዝኛ በጻፍኩት ሃተታ ላይ መመልከት ይቻላል። ይህ የዐማራ ጭፍጨፋ እንደሚቀጥል አስባለሁ፤ እፈራለሁ፤ አሳስባለሁ።

በዘላቂነት፤ መሰረታዊና መዋቅራዊ ተግዳሮቶችን ደፍረን ለመፍታት ካልቻልን መረዳት ያለብን፤ ዐማራን፤ ትግሬን፤ አፋርን፤ ሶማሌን፤ አኟክን፤ ጉራጌን፤ ወላይታን፤ ኦሮሞን ወይንም ሌላውን ኢትዮጵያዊ በድሎ፤ ከስልጣንና ከሃላፊነት አባርሮ፤ ጨፍጭፎ፤ ከቀየው አፈናቅሎና መሬቱን ነጥቆ፤ ዲሞክራሳዊ መብቱን ተጠቅሞ የሚተቸውንና የሚቃወመውን ሁሉ ለምን ድምጽ አሰማህ ወይንም ለምን እኔን ተቸሕ? በሚል ብሂል አስሮ፤ ሰላምን፤ እርጋታን፤ ብልጽግናን ስኬታማ ለማድረግ አይቻልም። መንግሥትን መተቸት ዲሞክራሳዊ መብት ነው። ሰላማዊ ሰልፍ ማካሄ መብት ነው። ዐማራውን አትጨፍጭፉ ማለት ኢትዮጵያንም መታደግ ነው።

በኢትዮጵያ ምድርና ከኢትዮጵያ ውጭ የሚኖር ተቆርቋሪዎች ማሰብና አስቦ ወደ ተግባር መጓዝ ያለባቸው/ያለብን እነዚህን የመሳሰሉ ግፍና በደሎች ስናይ ነገ በራሴም መድረሱ አይቀርም የሚለውን መርህ  ማስተናገድ ነው። በኔም ላይ ሊደርስ ይችላል ብሎ ማሰብ ብልሃት ነው። መዘናጋትና ማዘናጋት ግን ኢ-ፍትሃዊና ኢ-ኢትዮጵያዊ ሂደት ነው።

የነገው ትውልድ ዐማራውን ማሳተፍ አለበት!

መሰረታዊ ችግሮችን በግልጽ ማንሳትና መፍትሄ መጠቆም ለነገው ትውልድ ማሰብ ነው። ይህንን ማድረግ ደግሞ ኢትዮጵያ ነገ እንደ ሶርያ፤ እንደ ዩጎዝላቭያ ወዘተ እንዳትሆን ለማድረግ የሚያስችል ሁኔታን ሊፈጥር ይችላል። “ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ” እንዲሉ፤ ይህንን ደፍረን ዛሬ ካላደረግነው ነገ ብንጮህና አቤቱታ ብናቀርብ ማንም የሚሰማን ኃይል የለም።

እንደኔ በኢትዮጵያዊነታችሁ የዜግነት መለያ የምታምኑ፤ ዐማራው ለኢትዮጵያ ደጀን ሆኖ ሃገሩን ሲታደግ የኖረው በኢትዮጵያዊነቱ እንጅ በዐማራነቱ አለመሆኑን የመቀበል ግዴታ አለባችሁ። እየፋፋ የመጣው የዐማራ ብሄርተኛነት በማንም ላይ ጥቃት ለማካሄድ አይደለም። የፖለቲካ ሥልጣን የበላይነት ለመያዝም አይደለም። የዐማራው ብሄርተኛነትና መደራጀት  ራሱን ከእልቂት፤ ከውርደት፤ ከስደት፤ ከድህነት፤ ከመፈናቀል ለማዳን ነው። ስለዚህ፤ የዐማራው “ብሄርተኛነት ስጋት” ሊሆን አይችልም። በጠባብ ብሄርተኛነት እና በጽንፈኛነት የተበከለው የኢትዮጵያ የቋንቋና የዘውግ ፖለቲካ ስርዓት መሪዎች “የዐማራው ብሄርተኛነት ያሰጋናል” ብለው ሲናገሩ ትችታቸው ውሃ አይቋጥርም። ጽንፈኛው ማነው? ሽብርተኛው ማነው? የእርስ በእርስ ጦርነት የሚያካሂደው ማነው? ከግብፅና ከሌሎች ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች ጋር የወገነው ከሃዲው ማነው? ከአሜሪካና ከዩጋንዳው መሪ ከሙሴቬኒ ጋር የሚዶልተው ማነው? የዐማራውን ብሄርተኛነት ከማውገዘ ይልቅ፤ ዐማራውን የሚጨፈጭፈው፤ የመላው ዓለም ሕዝብ ያወገዘው ማንን ነው? የሚሉትን መሰረታዊ ጥያቄዎች መልሱልን እላለሁ።

የኢትዮጵያዊነት የዜግነት መለያ ግዴታ የማን ነው?

የዐማራው ሕዝብ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት የማንነት መለያው የሚያምን ሕዝብ ነው። በዚህ አቋሙና መለያው ማንም ሊተቸው አይችልም። በዚህ እሴት በማመኑ በመላው ኢትዮጵያ ከሌሎች ወገኖቹ ጋር ተጋብቶ፤ ተዛምዶ፤ ተከባብሮ ይኖራል። በተፃራሪው ይህንን የጋራ ኢትዮጵያዊነት መለያ የማይቀበሉና የማያስተናግዱ የዘውግ ጽንፈኞች፤ አክራሪዎችና ተገንጣይ ኃይሎች የሚያደርጉት የሚያሳየው ሃቅ ግን ዐማራው “መጤ፤ ወራሪ፤ ጨቋኝ፤ ነፍጠኛ፤ ቅኝ ገዢ ነው” በሚል የተሳሳተ ትርክት ዐማራውን መጨፍጨፍና ከቀየው ማባረር ነው። በሰላም ሰርቶ መኖር ያስመሰግናል። ዐማራው የእልቂት ኢላማ እንዲሆን መፍቀድ ወይንም ማመቻቸት ያስጠይቃል።

ሁሉም በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ የዘውግ አባላት በኢትዮጵያዊነት የማንነት መለያ የግለሰቦች መብት ቢያምኑ ኖሮ በዐማራው ላይ የሚካሄደው ጭፍጨፋ አይከሰትም ነበር። ህወሃትና ኦነግ በጋራ ሆነው በቋንቋና በዘውግ መለያዎች የመሰረቱት ሕገ መንግሥት እና የክልል አስተዳደር ለኢትዮጵያዊነት ዋና መሰናከል ሆኗል። ይህ ሁኔታ በአዲስ ዲሞክራሳዊና ፌደራላዊ ሕገ መንግሥት እስከሚለወጥ ድረስ ዐማራው ያለው አማራጭ ራሱን አደራጅቶ ህልውናውን መታደግ ነው።

በተጨማሪ፤ ዘላቂ መፍትሄ እስኪገኝ ድረስ በወለጋ የሚኖረው ዐማራ ሙሉ በሙሉ እንዳይጨፈጨፍ ካለበት ቀየ ወደ ዐማራው ክልል እንዲሄድ ቢመቻችስ? ወደ ሌላ አገር–ኬንያ፤ ደቡብ ሱዳን– ሊሄድ አይችልም። አማራጮች እናቅርብ። ምክንያቱም እልቂቱ የሚቆም መስሎ አይታይም።

ላም አለኝ በሰማይ!   

የዜግነት መብት (ኢትዮጵያዊነት) እስካሁን አልተከበረምና አልሰራም የሚለው ምክንያታዊ ሃሳብ የማይዋጥላቸው የዐማራ ምሁራን፤ ልሂቃን፤ የፖለቲካ መሪዎች፤ ስብስብቦች ወዘተ አሉ። እነሱ የሚሉት ዐማራው እየተጨፈጨፈም ቢሆን በኢትዮጵያና በኢትዮጵዊነቱ ማመኑን መቀጠል አለበት ነው። እኔ የምከራከረው ግን፤ ዐማራው በኢትዮጵያዊነቱ ማመኑ ኢላማ አድርጎታል እንጅ ከእልቂት አላዳነውም ነው። የኢትዮጵያዊነት የማንነት መለያ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ግዴታ እንጅ የእልቂት ሰለባ የሆነው የዐማራው ሕዝብ ግዴታ ብቻ አይደለም ነው።

ዐማራው በኢትዮጵያዊነቱ የሚያምን መሆኑ እየታወቀ፤ ለኢትዮጵያ በተደጋጋሚ መስዋእት ከፍሎ፤ ዳር ድንበሩን አስከብሮ  በተፃራሪው ግን ተጎዳ፤ ተፈናቀለ፤ የእልቂት ኢላማና ሰለባ ሆነ እንጅ ተጠቃሚ አልሆነም ነው።

ዐማራውን እንወክላለን የሚሉት የብአዴን/ የዐማራ ብልፅግና አመራሮችም ለዐማራው እልቂት የማያሻማና ቆራጠኛነት የሚያሳይ አቋም አልወሰዱም። በአጭሩ ዐማራው መሪ አልባ ሆኗል።

የአገር ውስጥ አለመረጋጋት ለውጭ ኃይሎች ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።

በመሬት ላይ የተከሰተውን ግፍና በደል አጋልጠው ሰላማዊ ሰልፍ ያደረጉት የጎንደር፤ የባህር ዳር፤ የአዲስ አበባ፤ የደብረ ብርሃንና ሌሎች የዩንቨርስቲ ተማሪዎች፤ አስተማሪዎች፤ ሰራተኞች፤ ሕዝብ፤ በተዛማጅ ሌሎች የዐማራ ሕዝብ ወዳጆች ወገኖቻችን እምቢተኛነት እጅግ በጣም የሚያኮራ እንቅስቃሴ መሆኑን አሰምርበታለሁ። ይህንን እንቅስቃሴ ግን ለራሳቸው የፖለቲካ ጥቅም ለማዋል የሚሞክሩ የአገር ውስጥና የውጭ አጥፊና ሽብርተኛ ኃይሎች መኖራቸውን አስተናግዳለሁ። በባህር ዳር ከተማ የተፈጸመው የቦምብ ጥቃት ከዚህ ሴራ ጋር የተያያዘ ነው።

ሁሉም ነገር ወደ ዐባይ ወንዝ (የሕዳሴ ግድብ ውዝግብ)

በተጨማሪ፤ የሕዳሴ ግድብ ሶስተኛ ሙሌት እንዳይሳካ ለማድረግ የሱዳን፤ የግብፅ መንግሥታት እና ህወሃት (ሳምሪ) በጋራ በኢትዮጵያ ላይ የሚያካሂዱት የጦር ጫሪነት እርምጃ በኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰተውን የዐማራ እልቂት፤ አለመረጋጋት፤ አለመተማመን፤ የእርስ በእርስ ጦርነት፤ የመንግሥት አፈናና ወዘተ ወንፊት (Sieve) ፈጣሪ ክስተት በመጠቀም መሆኑን ማስተናገድ አለብን።

የጎንደር ዩንቨርስቲ ተማሪዎችና አስተማሪዎች ሰላማዊ ሰልፍ አድርገው የፈጠሩት ሕዝባዊ እንቅስቃሴና እምቢተኛነት የሚከተሉትን አቅጣጫዎች ቀይሰውልናል፤

  1. የተራው  ሕዝብ እምቢተኛነት እና ሚና ወሳኝ መሆኑ፤
  2. የእምቢተኛነት ትግሉ እንደ ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ያሉ የማይበገሩ፤ የማይደለሉ፤ የማይፈሩ፤ በእውቀትና በሞያ የተካኑ፤ የሞራል ልእልና ያላቸው መሪዎችን መንከባከብ፤ ማጎልመስ አስፈላጊ መሆኑ፤
  3. ትግሉን በስልትና በዐማራ የጨዋነት ፖለቲካ ባህልማስተጋባት አስፈላጊ መሆኑ;
  4. የኃይል አሰላለፉን በሚገባ ማወቅና ማንጸባረቅ ለዐማራው ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ለመላውበኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነቱ የማንነት መለያ ለሚያምነው ሕዝብ ቁልፍ መሆኑ፤
  5. የኢትዮጵያዊነትን የማንነት መለያን መሸከም ያለበት ዐማራው ብቻ አለመሆኑ፤

 

  1. ዐማራው በኢትዮጵያዊነቱ እየተጨፈጨፈና ከቀየውበተከታታይ የተፈናቀለ መሆኑ።

ይህንን በሚመለከት የጎንደር ዩንቨርስቲ ተማሪዎች ሰልፈኞች ጠላትንና ወዳጅን ለይተዋል። “የኦሮሞና የትግራይ ወይንም ሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የዐማራው ሕዝብ ጠላት” አለመሆኑን በማያሻማ ደረጃ  አስምረውበታል። ይህም ለመላው ኢትዮጵያ ሰብሳቢ ፍኖተ ካርታ ሆኖ ሊያገለግል የሚችል መሆኑን ላሰምርበት እፈልጋለሁ። በተለይ፤ ወላዋይ የሆነው የዐማራ ምሁር፤ ልሂቅ፤ አክቲቪስት ነኝ ባይ ወዘተ ይህንን ፍኖተ ካርታ ሊያስተናግድ ይችላል። ተራው የኦሮሞ ሆነ የትግራይ፤ የወላይታ ሆነ የሶማሌ፤ የጋምቤላ ሆነ የአፋር ሕዝብ የዐማራ ሕዝብ ጠላት አይደለም፤ ሆኖም አያውቅም።

  1. የዐማራው ዋና ጠላት ህወሃት ለራሱ አገልጋይና ታዛዢሆኖ እንዲያገለግል የመሰረተው፤ ያጎለመሰው፤ ስልጣን እንዲይዝ ያመቻቸው፤ “የሙታን ስብስብ፤ የትርፍ አንጀት” ወዘተ የሚሉ አሉታዊ መለያዎች የተሰጡት ብአዴን ወይንም የዐማራ ብልፅግና ፓርቲ መሆኑን ለይተው አስቀምጠውታል።

ይህ ስያሜ የሚያስታውሰኝ ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ዐማራውን ከእልቂት ለመታደግ የሞትና የሽረት ትግል ሲያካሂዱ እሳቸውን ከውስጥ ሆኖ ያስቸገራቸው “ሆዳም ዐማራ” ብለው የሰየሙት መሆኑን ነው። ዛሬ ያለውን አገዛዝ የሚመራው ኃይል ህወሃት አይደለም እየተባለ ቢለፈፍም የህወሃት መርህ፤ የህወሃት ካድሬ፤ የህወሃት ተቋማዊ ሰንሰለት፤ የህወሃት የሌብነት፤ የጉቦ፤ የሙስና፤ የአድልዎ፤ የአስተዳደር ብልሹነት ባህልና ልምድ፤ የህወሃት የኢ-ፍትሃዊነት እና የፖለቲካ ስልጣን፤ የኢኮኖሚ የበላይነትና ተተኪነት ርእዮት በግልጽ ህወሃትን መሰል ነው። ኢትዮጵያዊያንን ሊመጥን አይችልም።

ከላይ ያቀረብኩት እንዳለ ሆኖ፤ የጎንደርን፤ የባህር ዳርን፤ የአዲስ አበባን፤ የደብረ ብርሃንንና የሌሎችን ከፍተኛ ተቋም ተማሪዎችና አስተማሪዎች እና ወጣቱን ትውልድ የምመክረው አንድ መሰረታዊ ነገር አለ። ይኼውም ጥቂት መሆናቸው ባይካድም፤ በዐማራው የብልፅግና ፓርቲ ውስጥ ለዐማራው ሕዝብ ህልውና፤ መብትና ዘላቂ ጥቅም የሚከራከሩ ግለሰቦች መኖራቸውን መቀበልና ሕዝባዊ እምቢተኛነቱን እንዲቀላቀሉ መጎትጎት አስፈላጊ መሆኑን ነው። የዘውግና  የመንግሥት ጥላቻ ዐማራውን የማይወክል ሂደት መሆኑን አሰምርበታለሁ።

ሁለተኛ፤ የዐማራው ሕዝብ ተቆርቋሪዎችና ጠበቃዎች መጠንቀቅ ያለባቸው የብአዴንን (የዐማራ ብልፅግናን) እና በጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ በበላይነት የሚመራውን የብልፅግናን መንግሥት ሲቃወሙ ለመላው የኢትዮጵያና የዓለም ሕዝብ ግልፅ ማድረግ ያለባቸው የኢትዮጵያን የውስጥ ተግዳሮቶች እድል በመጠቀም የኢትዮጵያ የውጭ ጠላቶች፤ በተለይ ሱዳንና ግብፅ የሚያካሂዱትን የጦርነት ፕሮፓጋንዳና ትንኮሳ የሚቃወሙ መሆናቸውንም ነው። “የጠላቴ ጠላት ወዳጀ” ነው የሚለው ብሂል አያስኬድም። በደርግ መንግሥት ጊዜ ይህንን ብሂል ተከትለው የሶማሌን ወራሪ ኃይል የደገፉና የተቀላቀሉ ከሃዲ ኃይሎች እንደ ነበሩ አስታውሳለሁ። ይህ ሂደት ራሱ ክህደት ነው፤ አያዋጣም።

የዐማራው ጠላት በበዛባት ኢትዮጵያ ጠላትን ከማብዛት ትርክት መቆጠብ አለብን። በዐማራው ስም የሚነግዱ ብዙ ግለሰቦችና ቡድኖች መኖራቸውን ማመን አለብን። ለዐማራው ተቆርቋሪ የሆኑ ግለሰቦችን በያሉበት እየፈለጉና እየተወዳጁ ለዐማራው ሕዝብ አቅም አጎልማሽ የሆኑትን እንዲናበቡና የዐላማ አንድነት እንዲመሰርቱ ማድረግ ወሳኝ ነው። ከእነዚህ መካከል እንደነ መምህር ታየ ቦጋለ፤ እንደነ አቶ ወንድሙ ኢብሳ፤ እንደነ አቶ ኦባንግ ሜቶ፤ እንደነ መምህር፤ ጋዜጠኛ ታዲዎስ ታንቱ፤ እንደነ አቶ መኮንን ዶያሞ፤ እንደነ ዶር አረጋዊ በርሄ ወዘተ ያሉ ለዜጎች ደህንነት፤ እኩልነት፤ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ፤ ለኢትዮጵያ ዘላቂነት የሚከራከሩ ግለሰቦች መኖራቸውን አንርሳ።

ፍኖተ ካርታ

ፍኖተ ካርታ ፈጣሪ የሆነው የጎንደር ዩንቨርስቲና የዚህንን ታሪካዊ ተቋም ሰላማዊ ሰልፍ ፈለግ ተከትለው በአዲስ አበባ፤ በባህር ዳር፤ በደብረ ብርሃንና በሌሎች ተቋማት እምቢተኛነት ያሳዩት ወገኖቻችን በምን ላይ ተስማሙ? የሚለውን ጥያቄ በውጭ የሚኖረው ተቆርቋሪ ሁሉ እንዲወያይበት አሳስባለሁ።

እኔ እንደ ተከታተልኩት ከሆነ በሚከተሉት ላይ ስምምነት አለ።

  1. የዐማራው ሕዝብ ራሱን ከእልቂት ለመታደግ ከፈለገ በብልሃት መደራጀትና አመራር መፍጠርአለበት፤
  2. የዐማራው ሕዝብ የትግል አማራጭ ዘዴ ሰላማዊ እምቢተኛነትእንጅ የትጥቅ አመፅ አይደለም፤ ትግሉ የሚጀምረው ግን በዐማራው ክልል በብአዴን፤ የአማራ ብልፅግና አመራር “ሙታን ስብስብ” ባንዳዎች፤ መረብ ላይ መሆን አለበት፤
  3. የወለጋውን ተደጋጋሚና የሚዘገንን የዐማራ ጭፍጨፋማውገዙና ጥፋተኞቹ በሃላፊነት እንዲጠየቁ ማድረጋችን እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በአሁኑ ወቅት፤ የዐማራው ሕዝብ፤ ተማሪው፤ አስተማሪው፤ ባለ ኃብቱ ወዘተ ትኩረትና ለይቶ መታገል ያለበት በዐማራው ጥቅም ላይ የሚካሄድበትን ድብቅ (ስውር) ድርድር በሚመለከት ነው። ይኼውም የወልቃይት ጉዳይ ለድርድር ሊቀርብ ይችላል ተብሎ የሚሰማው ብሂል ለዐማራውና ለኢትዮጵያ ዘላቂ ጥቅም የህልውና ጥያቄ መሆኑ ነው።

በምክትል ጠቅላይ ሚንስትርና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን ሰብሳቢነት የተዋቀረው ሰባት አባላት ያሉት (1ኛ. አቶ ደመቀ መኮንን ሰብሳቢ (Amhara)–2ኛ. ዶ/ር ጌድዮን ጢሞቲዎስ…. አባል (Southern) 3ኛ. አቶ ተመስገን ጥሩነህ አባል (Amhara) 4ኛ. አምባሳደር ሀሰን አብዱልቃድር. አባል (Afar) 5ኛ. አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን…. አባል (Seltie) 6ኛ. ሌ/ጀኔራል ብርሀኑ በቀለ…. አባል (Oromo) 7ኛ. ዶ/ር ጌታቸው ጀምበር. አባል (Amhara) የሰላምና የድርድር ኮሚቴ የሚደገፍ እርምጃ ነው። አነጋጋሪ የሆነው ድርድሩ ማንን ያከስራል? ማንን ይጠቅማል? የሚለው ግልጽነት የሌለው ጥያቄ መሆኑ ነው።

ወልቃይት ለድርድር አይቀርብም

ብዙ መስዋእት ተከፍሎ ወደ ዐማራው ኢትዮጵያዊ ባለቤትነትና ማንነት የተመለሰውን ወልቃይትን ለድርድር ማቅረብ ሌላ የእርስ በእርስ ጦርነት እንዲጀመር መጎትጎት መሆኑን ላሰምርበት እፈልጋለሁ። ዋናዎቹ ተጠቃሚዎች ግብፅና ሱዳን እንድሚሆኑ አልጠራጠርም። ወልቃይትን ለህወሃት ማስረከብ ማለት በዚህ ወሳኝ አካባቢ የውጭ ጠላትን አቅም ማጎልመስ፤ በር መክፈት ማለት ነው። ይህ ችግር የዐማራው ብቻ አይሆንም። የኢትዮጵያ ማነቂያ/ ተግዳሮት ነው።

ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ እንዳሳሰብኩት ወልቃይት፤ ጠገዴ፤ ጠለምትና ራያ ቀይ መስመር ነው። ምክንያቱም ይህ አካባቢ በህወሃት የተነጠቀውና ወደ “ታላቋ ትግራይ” የተቀላቀለው ህወሃት ነዋሪውን ሕዝብ ከጨፈጨፈ፤ ከቀየው ካባረረና የትግራይን ተወላጆች ካሰፈረ በኋላ ነው። የህግ እውቅና የሰጠው ደግሞ ህወሃት የፖለቲካ ሥልጣን ከያዘ ከ1995 ዓ. ም በኋላ ነው። ህወሃት መሬቱን ከመንጠቁ በፊት ነጠቃው በሕዝብ ድምጽ አልተካሄደም። የነዋሪውን ሕዝብ ህልውናና ማንነት አድቅቆ የወሰነው የፖለቲካ ውሳኔ ነው። የሕዝብ ድምጽ (Referendum) ይሰጥ የሚል ፖለቲካዊ ብልጣ ብልጥነት ተቀባይነት አይኖረውም የምለው በዚህ ምክንያት ነው።

ከህወሃት ጋር የሚካሄደው ድርድር ለምን ያስጨንቅሃል? ለሚለው ጥያቄ የሚከተለውን ላቅርብ።

ባለፉት ሰላሳ ዓመታት ተቋማዊና መዋቅራዊ የሆነው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ዐማራ ጠል፤ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ጠል ነው። ሕገ መንግሥቱ ጸረ ዐማራ ነው። ሕገ መንግሥቱ የዘውግ ማንነትን ከፍ የሚያደርግ፤ መገንጠል የዘውግ መብት ነው የሚል፤ ኢትዮጵያዊነትን ዝቅ የሚያደርግ ነው።

ዐማራ ጠልነት ከጣልያን ወረራ ጀምሮ ስርአታዊና መዋቅራዊ ቅርጽ ይዟል። የተባባሰው ከ1960ዎቹ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ወዲህ ነው። እኔ መሰረታዊ የአስተሳስብ ለውጥ ይካሄዳል በሚል ተስፋ አድርጌ የነበረው የሚከተሉት ብሂሎች ሲነገሩ ነበር።

  • “ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው”–አቶ ለማ መገርሳ ያሉት፤
  • “ስንኖር ኢትዮጵያዊ፤ ስንሞት ኢትዮጵያ”– ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ የተናገሩት።

እነዚህን ሳቢና ማራኪ የሆኑ ብሂሎች ሙሉ በሙሉ የተቀበለው፤ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነቱ መለያዎች የሚያምነው የዐማራ ሕዝብ ነው ብል አልሳሳትም። ይህ ብቻውን ግን ኢትዮጵያን ከአደጋ ሊታደጋት አይችልም። ከጥቂት ጽንፈኞች ውጭ የኦሮሞው ሕዝብም በተደጋጋሚ በማያሻማ ደረጃ (አድዋ፤ ካራ ማራ፤ ባድመ፤ መቀሌ) ከዐማራውና ከሌላው ወንድም፤ እህቱ ጋር ሆኖ ኢትዮጵያን በተደጋጋሚ የታደገው በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነቱ ስለሚያምን ነው።

ስለ ዐማራ ጠልነት መንስኤ፤ እኔ ከማቀርበው በተሻለ ዶር ሃብታሙ ተገኝና አቶ አቻምየለህ ታምሩ በአብራር ዩቲውብ የሰጥቱን ቃለ ምልልስ ማዳመጡ ይረዳል።

የኔ ትችት ከላይ አቶ ለማ መገርሳና ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ የተናገሯቸውን ማራኪ ንግግሮች ለምን ተግባራዊ ለማድረግ አልተቻለም? የሚል ነው። ግለሰቦቹን እንደ ግለስብ አከብራለሁ። ሆኖም፤ የኢትዮጵያ ችግር የግለሰብ አይደለም። ማነቆው ሆነ ተብሎ የተቀነባበረው ዘውግ ተኮር ስርዓትና መዋቅር ነው ። ዘረኝነት፤ የዘውግ ጥላቻ፤ ባለፈ ታሪክ ቂም በቀልነት፤ የብሄር ጽንፈኛነት፤ የብሄር ትምክኽተኛነት፤ ተገንጣይነት፤ ተተኪነት ለብዙ ሽህ ዓመታት ተከብራና እውቅና ተቀዳጅታ የቆየችውን ኢትዮጵያን እያደማት ነው። የዐማራውን ጭፍጨፋ ከዚህ አንጻር ነው የምመለከተው።

የተከበበው የዐማራ ሕዝብ እና ዘውግ ተኮሩ ሕገ መንግሥት

ህወሃት በሰሜን እዝ ላይ የክህደት ወንጀል የፈፀመው ሕገ መንግሥቱን መሰረት አድርጎ ነው። በተለይ የትግራይ ሕዝብ የራሱን እድል በራሱ የማስተዳደር መብት አለው የሚለውን ከፋፋይ አንቀፅ (39) ተጠቅሞ። እኔ ኢህአዴግ ከተመሰረተበት ከ 1991 ዓ.ም. ጀምሮ በተደጋጋሚ የተከራከርኩት ይህ አንቀፅ ኢትዮጵያን ይከፋፍላታል፤የእርስ በእርስ ግጭት ይፈጥራል በሚል ነበር፤ አሁንም ነው። በተመሳሳይ ሌሎች ኢትዮጵያዊያንም ሳይሰለቹ ሕገ መንግሥቱ እንዲቀየር አሳስበዋል፤ ሰነድም ያዘጋጁ አሉ።

ለምሳሌ፤ ወንድማችን አቶ መኮንን ዶያሞ ስራውን ወደ ጎን ትቶ፤ ልዩ ልዩ ባለሞያዎችን አስተባብሮ አዲስ ዲሞክራስዊና ፌደራላዊ ሕገ መንግሥት ረቂቅ አዘጋጅቷል። ይህንን ረቂቅ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን እንዲያነቡትና እንዲረባረቡበት አሳስባለሁ። ቢቻል ተቆርቋሪ ኢትዮጵያዊያን በአካል ተገናኝተው ቢመካከሩበትና ለመላው ዓለምና ለኢትዮጵያ ሕዝብ በአስቸኳይ ቢያቀርቡት ይመረጣል። እኔ የድርሻየን ለመወጣት ዝግጁ ነኝ።

የውጭ ታዛቢዎች ሳይቀሩ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት፤ በተለይ “የራስን እድል በራስ መወሰን እስከ መገንጠል ድረስ” የሚለው ሃረግ ኢትዮጵያን ሊበታትናት እንደሚችል አሳስበዋል። ከእነዚህ መካከል ዴቢድ ኦታዌ፤ “ Ethiopia faces dire consequences of ethnic federalism,” July 28, 2021; “Ethnic federalism and its discontents,” International Crisis Center, September 4, 2009; “The trouble with Ethiopia’s ethnic federalism,” New York Times, January 3, 2019; and “Ethnic Federalism: its promise and pitfalls for Africa,” Alemante Gebreselassie, School of Law, William and Mary, 2003 ሊጠቀሱ ይችላል።

የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢስይያስ አፈወርቂ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አገሪቱን ሊያፈርሳት ይችላል፤ የእርስ በእርስ ጦርነት ይፈጥራል ብለው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድን እንደ መከሩ ይነገራል። ፕሬዝደንቱ ሊደነቁ የሚችሉበት ሌሎች ሁለት ሊጠቀሱ የሚገባቸው ጉዳዮች አሉ።

አንድ፤ የዐማራውን ሕዝብ በወዳጅነቱ፤ በለጋስነቱ፤ በቅንነቱ አመስግነው በዐማራው ላይ ፓርቲያቸው የተከተለውን የተሳሳተ ትርክት ተችተዋል፤ የዐማራውን ሕዝብ “ይቅርታ” ጠይቀዋል።

ሁለት፤ በወልቃይት ዐማራነት ላይ የኤርትራ መንግሥትና ሕዝብ ያለውን የማያሻማ አቋም ገልፀዋል።

“የኤርትራ መንግሥስት እና ሕዝብ እስከሚያውቀው እና እስከሚረዳው ድረስ ወልቃይት ጠገዴ የጎንደር ክፍለ ሀገር አካል የዐማራ መሬት ይዞታ ነው። ከዚህ በተረፈ የሚወራው ሌላው ግን ባለፈው የሠላሣ ዓመት ወስጥ የተፈጠረ የወያኔ ፍጹም ውሸት የሆነ ልብ ወለድ ድርሰት ነው።”

ሃቆች

  • ይህንን አቋም ማነፃፀር የምፈልገው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ከሚናገሩት እጅግ በጣም ከተሳሳተው ዐማራውን ለእልቂት ከሚያጋልጥ አቋማችው ጋር ነው። “እኔን የሚያስፈራኝ የዐማራው ብሄርተኛነት ነው” ያሉትን ለመጠቆ ነው። ይህ ለዐማራው ጥቃት የፈጠረ አነጋገር ያሰጋኛል። የዐማራው ሕዝብ፤ የዐማራው ተገን ፋኖው፤ የዐማራው ልዩ ኃይል ወደ ኦሮሞው ክልል ሄዶ ንጹሃንን አልጨፈጨፈም።
  • የዐማራው ክልል የኦሮሞ ልዩ ዞን ፈጥሯል። በተጻራሪው በመተከል ሆነ በኦሮሞያ የዐማራው ሕዝብ ልዩ ዞን የለውም። የባሰውን በእነዚህ አካባቢዎች በተከታታይ የዐማራ ጭፍጨፋ ተካሂዷል።
  • ስለሆነም፤ የዐማራው ሕዝብ ምን ወንጀል ፈጽሞ ነው ለጠቅላይ ሚንስትሩ “አስፈሪ “ ሁኔታ የፈጠረው? “አያ ጅቦ ጅቦ ሳታመኻኝ ብላኝ” እንዲሉ፤ ጠቅላይ ሚንስትሩ በረባ ባልረባው ዐማራውን የሚያስሩበት፤ ዐማራውን የሚወንጅሉት፤ የዐማራ ሕዝብ መሪ እንዳይኖረው የሚያደርጉበት ወዘተ ለሌላ ምክንያት መሆኑ ይታያል።
  • ዐማራው መሪ አልባ እንዲሆን ተደርጓል። ለምሳሌ፤ የነ ዶር አምባቸው መኮንን፤ የነ ጀኔራል አሳምነው ጽጌ፤ የነ እንጂኔር ስመኘው በቀለ እልቂት፤ ግድያ፤ ሞት እስካሁን ድረስ አልተጣራም። ለምን?
  • “የዐማራው ሕዝብ የህልውና መብቴ ይከበር” ከማለት ውጭ የሰራው ወንጀል የለም።

የብአዴን (የዐማራ ብልፅግናና የጠቅላይ ሚንስትሩ ብልፅግና በጋራ ሆነው በጎንደር፤ በአዲስ አበባ፤ በባህር ዳር፤ በደብረ ብርሃን የተካሄዱትን የዩንቨርስቲ ተማሪዎችን ድምጽንና መብትን ለማፈን የሚያካሂዱት መረን የለቀቀ ግፍና በደል በአሁኗ ኢትዮጵያ ሌላው ቀርቶ ዲሞክራሳዊ መብትን በሰላም ለመግለጽ የማይችል መሆኑን ያሳያል። ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይን “የዐማራ ጠላት ነው” ብሎ መናገር ሊዋጥልን የማይችል ግለሰቦችና ስብስቦች ልንኖር እንችላለን። ለኔም አይዋጥልኝም፤

ግን፤ ይህ ትችት በመሬት ላይ የሚደረገውን ግፍና በደል የሚያንፀባርቅ መሆኑን እያወቅን (“እኔን የሚያሳስበኝ የዐማራው ብሄርተኛነት ነው” ያሉትን ጨምሮ ስገመግመው፤ ሌሎቻችን ለምን ትችት አታቅርቡ እንላለን? ለምሳሌ፤ አንድ ወዳጀና የማክብረው ኢትዮጵያዊ ዐማራው ተደራጅቶ ራሱን ከእልቂት መታደግ አለበት ያልኩትን “ለምን በኢትዮጵያዊነትን መለያ ብቻ ስትታገል ኖረህ አሁን ዐማራው በዘውግ ይደራጅ አልክ?” ብሎ ተቸኝ። ይህ ትችት ትክክል ነው።

እኔን ያሳሰብኝ አስኳል ጉዳይ ባለፉት አርባ ዓመታት በዐማራው ላይ የተካሄደው እልቂት በዐማራው ማንነት ምክንያት መሆኑን በመረጃ ስለ ተገነዘብኩ ነው። በሰሜን በዐማራው ላይ ህወሃት ያካሄደውና አሁንም የሚያካሂደው እልቂት በማን ስም ተደራጅቶ ነው? በትግራይ ስም። በደቡብ የኦነግ የነጻነት ሰራዊት በዐማራው ላይ የሚካሂደው ጭካኔ የተሞላበት ጭፍጨፋ በማን ስም ነው?  በኦሮሞው ሕዝብ ስም። በሰሜንም ሆነ በደቡብ ተራው ትግሬና ተራው ኦሮሞ እልቂት አያካሂድም። እልቂቱን የሚያካሂዱት በዘውግ ነጻነት አውጭነት የተደራጁት ህወሃት፤ ኦነግ ወዘተ ኃይሎች ናቸው።

ለማጠቃለል፤

  1. ለዐማራው ደህንነት መታገል ያለበት በመጀመሪያ ደረጃ ዐማራው ነው። የዐማራው ዐመራር ሽባና ታዛዢ መሆኑ አያከራክርም። የብአዴን/ የዐማራ ብልፅግና አመራር ለዐማራው ሕዝብ በቆራጥነት፤ በደፋርነት ድምፁን አሰምቶ በዐማራው ሕዝብ ላይ የሚካሄደው እልቂት (Amhara genocide) ባስቸኳይ ይቁም ብሎ ሲናገር አልሰማሁም። ባለማድረጉ ታሪክ በሃላፊነት ይወቅሰዋል። የዐማራው ወጣት ሕዝብም በሃላፊነት ይጠይቀዋል።

ይህንን ከተቀበልን ዐማራው ራሱን ከእልቂት ለማዳን፤ መደራጀት አለበት ማለት ነው። ዐማራው ሲጨፈጨፍ እያለቀሰ፤ ሰላማዊ ሰልፍ ብቻ እየወጣ ዐማራን ከባሰ ተከታታይ እልቂት ሊታደገው አይችልም።

  1. የዐማራው ኢትዮጵያዊነትለክርክር ሊቀርብ አይችልም። ዐማራው በኢትዮጳያዊነቱ ያተረፈው ምንድን ነው? ብለን መጠየቅ አለብን። መረጃዎች የሚያሳዩት ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊነት ከፍተኛ መስዋእት የከፈለው የዐማራ ሕዝብ በራሱ አገር ደህንነቱ፤ ሰብእነቱና ሰብአዊ መብቱ ሊከበር አለመቻሉን ነው። ኢትዮያዊነት የዐማራ ኃላፊነት ብቻ ሊሆን አይችልም። ዐማራው በኢትዮጵያዊነቱ በማመኑና በመላው ኢትዮጵያ በመኖሩ የጽንፈኞች፤ የብሄርተኞችና የሽብርተኞች ኢላማ መሆን የለበትም። ግን ነው። የዐማራ ጭፍጨፋ ይቁም ብለን የምንነሳበትና ዐማራውን ያለ ማመናታት የምንደግፍበት ወቅት አሁን ነው። ይህንን ጥሪ ማድረግ ያለበት ዐማራው ብቻ ሊሆን አይችልም። በዜግነት መብትና በኢትዮጵያዊነት የሚያምነው ሁሉ ድምፅ ማሰማት አለበት።

 

  1. ጠቅላይ ሚንስትሩ “እኔን የሚያስፈራኝ የዐማራው ብሄርተኛነት ነው” ያሉት ሃላፊነት የጎደለው አነጋገር ነው ለማለት እንድፈር። የፌደራል መንግሥት የመከላከያ ኃይል ኢላማ ማድረግ ያለበት በህወሃት፤ በኦነግ የነጻነትና የመገንጠል መብት ሰራዊትና ተመሳሳይ ሽብርተኛ ኃይሎች ላይ ሊሆን ይገባል። ለኢትዮጵያ ደጀን በሆነው በፋኖው ላይ የሚካሄደው አፈናና ትጥቅ ማስፈታት ዙሮ ዙሮ ኢትዮጵያን ያስጠቃታል።

 

  1. የጎንደር ወጣት በገፍ ሰላማዊ ሰልፍ አድርጎ፤ ፋኖ፤ ፋኖ፤ “እኔም ፋኖ ነኝ”እያለ ያሰማውን ድምፅና አቤቱታ እኔም ሙሉ በሙሉ እደግፋለሁ። ስለ ፋኖ ከዚህ በፊት የተከራከርኩበት መሰረታዊ ምክንያት ፋኖው የዐማራው ብቻ ሳይሆን፤ የኢትዮጵያም ባለውለታና ደጀን በመሆኑ ነው።

 

  1. በወለጋ፤ ኦሮምያ የተፈፀመውን ተደጋጋሚ የዐማራ ሕዝብ ጭፍጨፋ (Amhara genocide) የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሺነር መስሪያ ቤት ከአቻው ከአፍሪካ አንድነት ተቋም ጋር ተባብሮ በአስቸኳይ ጥናቱን፤ ምርመራውንና ምክሩን እንዲያካሂድ አደራ እላለሁ።

 

  1. በማመነታት ላይ ለምትገኙ ኢትዮጵያዊያን የማሳስበው በዘላቂነት ስገመግመው፤ እያንዳዱ የዘውግ አባል፤ እያንዳንዱ የዘውግ ተቋምና ምሁር በኢትዮጵያዊነቱ ለማመንና አንድ አንድ አገር፤ አንድ ሕዝብብሎ ሲነሳ የዐማራው በዘውግ መደራጀት አስፈላጊንት ፋይዳ ቢስ እንደሚሆን ነው። ላሰምርበት የምፈልገው የዐማራው መደራጀት አስፈላጊነት የህልውና ጥያቄ መሆኑን ነው።

 

  1. ይህንን መርህ የማያስተናግድ የዐማራ ምሁር፤ ልሂቅ፤ ጋዜጠኛና ሌላ ችግሩን በሚገባ አልተረዳውም ለማለት እደፍራለሁ። ስርአቱና መዋቅሩ ዘውጋዊ እንጅ ኢትዮጵያዊ አይደለም።ሕገ መንግሥቱ እኮ ጸረ-ዓማራና ፀረ-ኢትዮጵያ ነው። በዜግነት መብት ላይ የተመሰረተ፤ ኢትዮጵያዊና ሰብአዊ ቢሆን ኖር ዐማራው በየለቱ አይጨፈጨፍም ነበር። በወለጋ፤ ኦሮምያ የተከሰተው እልቂት አይከሰትም ነበር። ለማስታወስ ይህንን የመሰለ እልቂት ለአርባ ዓመታት ተካሂዷል።

 

  1. ታላቁ ምሁር፤ የህክምና ባለሞያ ፕሮፌሰር አስራትወልደየስ “የዐማራ” ድርጅት የመሰረቱበትን ምክንያት ወደ ኋላ ሂደን እንገምግመው። ስንት ንጹህ ዓማራ ነው ከተራራ (አርባ ጉጉ ወዘተ) የተወረወረው? ስንት ነው ታርዶ የሞተው? ከዚህ በኋላ በየአካባቢው (በቡራዩ፣ በሻሸመኔ፤ በደራ ወዘተ) የሞተውስ? ማን በሃላፊነት ታሰረ?

 

  1. ተፎካካሪ ፓርቲዎችን የምመክረው፤ በቋንቋና በዘውግ የተዋቀረው ሕገ መንግሥት በአስቸኳይ እንዲሻሻል በጋራ ውይይት እንድታደርጉና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ድምፅ እንዲሰጥበት እንድታደርጉ ነው። ይኼ ለነገ የሚባል አይደለም።

 

  1. በመጨረሻ፤ የጎንደርን፤ የባህር ዳርን፤ የአዲስ አበባን፤ የደብረ ብርሃን ዩንቨርስቲ ተማሪዎች፤ አስተማሪዎችና ደጋፊዎች ስር ነቀል የሆነ ሕዝባዊ እምቢተኛነት እንዲጀመር ማድረጋቸውን አደንቃለሁ። ሕዝባዊ እምቢተኛነቱን በዘላቂነት እንድትይዙት እመክራለሁ። ሌሎችም ኢትዮጵያዊያን እንዲሳተፉ ቀስቅሱ የሚል ምክር እለግሳለሁ።

እትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!

July 5, 2022

የጎንደር ወጣቶች ፈለግ ፈጣሪዎች ሆነዋል

 

 

 

https://youtu.be/R_pjfG1bg_Q

ዶር ሃብታሙ ተገኝና አቶ አቻምየለህ ታምሩ በአብራ ሜድያ ስለ ዐማራ ጠልነት መንስኤ ያደረጉት ቃል መጠይቅ

https://youtu.be/7OX8uIpA5Sg

https://youtu.be/Vd6D1hQE3gU

መምህር ታየ ቦጋለ ስለ ብሄርተኛነት በሽታ

 

 

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
Go toTop