ጥርጣሬ የሳይንስ ጅማሮ ነው። የማይጠረጥር የሚመረምረው ነገር የለም።
የማይመራመር ደግሞ አዲስ ነገር አይፈጥርም።
አዲስ ነገር መርምሮ የማያገኝ ደግሞ እውር ነው።
እውር እንደሆነም ይቀራል..”
የቻርለስ ዳርዊን ፎቶግራፍ ከድረ ገጽ የተገኘ
Statue of Sir Charles Darwin in natural history Museum in London, UK
ስለ ዳርዊን የዝግመተ ለውጥ ፅንሰ ሃሳብን አስመልክቶ የበለጠ ለማወቅና ግንዛቤን ለማዳበር በተለያዩ ቋንቋዎች የተፃፉ መጣጥፎች፣ ቻርለስ ዳርዊን እሳቢዎቹን ይፋ ያደረገባቸው የመፅሃፍ ህትመቶችና የተለያዩ ጊዜያዊ የሆኑ መጣጥፎች ጭምር በ www.darwin-online.org.uk ማግኘት ይችላል። የዚህ ፅሁፍ አቅርቢ በዋናነት የተጠቀመው ይህንኑ ድረ ገጽ ቢሆንም በመጠኑም ቢሆን የተለያዩ በርዕሱ ያተኮሩ የዜና መገናኛ ተቋማትንም ተጠቅሟል።
በ አኒሳ አብዱላሂ
ካለፈው የቀጠለ ክፍል ሁለት
27.06.2022
አንባቢያን ከላይ በጥቅስ መልክ ያስቀመጥኩትን አረፍተ ነገር ከየት እንዳገኘሁት ለጊዜው ቢጠፋኝም ለእውቀት ጠል ለሆኑ በጥሞና ቢያሰላስሉትና ውስጣዊ ይዘቱንም ቢገነዘቡት ይጠቅማቸዋል እንጂ አይጎዳቸውም በሚል ልገለገልበት መወሰኔ ይታወቅልኝ እላለሁ።
ይህ ፅሁፍ ሁለቱ (ሽፈራው ሉሉ ና እንግዳሸት ቡናሬ) የመጣጥፉ አቅራቢዎች ለማንፀባረቅ ስለሚሞክሩት እምነታቸው የሚለው ነገር የለም። ጨርሶ የሚመለከተውም አይደለም። ማንም ኢትዮጵያዊ ዜጋ የፈለገውን እምነት የመቀበል፣ ተቀብሎም አስተምህሮቱና የሀገሪቱ ሕግ በሚፈቅደው መሰረት የመፀለይ፣ ኃይማኖታዊ በአላቱን በአደባባይ በሰላማዊ ሁናቴ ለማክበር የማይሸራረፍ መብት ያላቸው መሆናቸውን የሚቀበል ነው። በተፈጥሮ ሳይንስ ምርምር የሚገኙ ውጤቶችን ለመቃወም፣ አሻፈርኝ አልቀበልም በማለት ተቃውሞ ማሰማትም የሚከበርላቸው መብታቸው ነው።
ኃይማኖትን ከመንፈሳዊ እምነት ውጪ በፖለቲካ ፍልስፍናነትና መመሪያነት መጠቀሚያ ለማድረግ እስካልተሞከረና መንግሥትና ኃይማኖት የተለያዩ በመሆናቸው መዋቅሮቻቸውም አንዱ በሌላው የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ሳይገባቡ ተከባብረው ሕዝብን ማገልገል መሰረታዊ የሆነውን የዴሞክራሲያዊ መርህ ተቀብለውና አምነውበትም ለተግባራዊነቱ የየበኩላቸውን ግዴታ እስከተወጡ ድረስ እንካ ሰላንቲያ የምነገባበት ምክንያት አይኖርም። ከዚህ ባለፈ ግን የራሳቸውን አጀንዳ በሌላው ላይ ለማስረገጥ ፍላጎት ሲያንፀባርቁ በዝምታ ማለፍ የሚቻል እንዳልሆነ ሊረዱት ይገባል። የዚህ ፅሁፍ አቅራቢ ኃይማኖትን በጅምላ የሚጠላ ሳይሆን እንደማንኛውም ለሀገሩና ለህዝቡ ቀናኢነት ያለው ዜጋ ሁሉ እንቅስቃሴያቸውን በአንክሮ (ክሪቲካሊ) የሚከታተል፣ የሰብአዊ ፍጡር የባህል ግምጃ፣ ለግብረገብ፣ ስነ ምግባር ለሌላም ምንጭ በመሆን የበኩላቸውን አስተዋፅዖ የሚያበረክቱ፣ እንደማንኛውም ሕዝባዊ ተቋማት ሁሉ ኃይማኖት የዘመናት የአስተሳሰቡና የተግባሩ ውጤቶች መሆናቸውን የሚገነዘብ፣ በመሆኑ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ የሚመለከት ነው። በመሆኑም በዚህ መጣጥፍ የማቀርበው ትችት አልዋጥ ብሏቸው የጭቃ ጅራፋቸውን ለማጮህ የሚቁነጠነጡ ካሉ በሌለሁበት ቢገርፉኝ አይሰማኝምና ተረጋጉ ከማለት ውጭ የምለው ምንም ነገር አይኖረኝም። አይ ካሉም በጊዜው አነጋገር ይመቻችሁ እላለሁ። ትኩረቴን ወደ ተነሳንበት ርዕስ ላድርግና፣
ዳርዊንን የሰው ፍጡር በአጋጣሚ ብቻ ሳይሆን ከዝንጀሮ የተገኘ ነው፤ ከሚል አሰተሳሰብ ጋር እያገናኙት መጠን የለሽ ተቃውሞና ሂስ በወቅቱ ከነበሩ የሙያ ባልደረቦችና የቅርብ የሥራ ጓደኞቹ (ተቀናቃኞቹም ጭምር)እንኳ ሳይቀሩ ፅንሰ ሃሳቦችህ ሰብአዊ ክብራችንን ክፉኛ ተዳፈረ በሚል ለበርካታ አመታት ሲዥጎደበጎደበት የነበረ ለመሆኑ በመስኩ የተፃፉ የታሪክ ድርሳናት የሚያመላክቱት ናቸው። እሱ ግን የምርምር ውጤቱን ተቀናቃኞቹ በሚያቀርቡት መልክ አለመግለፁን በተደጋጋሚ ቢያቀርብም በበርካታዎቹ ዘንድ የተሰሚነት እክል የገጠመው ለመሆኑ ደግሞ የተደበቀ ምስጢር አልነበረም።
በዚህ መጣጥፍ አማካኝነት ሂስ የሚቀርብባቸው ሁለቱ ፀሃፊዎች ስለ ዝግመተ ለውጥ ያየቀረቡት ትንታኔ መሰል ሀተታና የተሳሳቱ መረጃዎች ከጥቂት አመታት በፊት እልህ አስጨራሽ በሆነ ሁናቴ በመጠነ ሰፊ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻና የገንዘብ ድጎማ ዋና መቀመጫቸውን አሜሪካ ባደረጉት ክሬአሽኒስት(Creationist) ተብለው በሚጠሩ ስብስቦችና ደጋፊዎቻቸው ቀርበው የነበሩ ለመሆናቸው እነሱ ደጋግመው በሚጠቅሷቸው መረጃ ቢጤ ሰነዶች የሚያመላክቱ ናቸው። በመሆኑም በወቅቱ ከተፈጥሮ ሳይንስ ሊቃውንቶች (ምስጋና ይድረሳቸውና) ብቻ ሳይሆን ከኃይማኖት ተቋማት ጭምር ክፉኛ ሂስ ሲቀርብባቸው የነበሩ ለመሆናቸውም በጊዜው ለህትመትና ለእይታ የቀረቡ ትንታኔዎችንና በርካታ መፃህፍቶችን መመልከቱ ብቻ በማስረጂያነት ሊቀርቡ የሚችሉ ናቸው። የሌላ እምነት ተከታይ የሆኑትም ቢሆን (እስልምና፣ አይሁዳዊ) ሁናቴውና ግለቱ ይለያይ እንደሆነ እንጂ ከተቃውሞ ሰፈር መታየታቸው እንዲሁ ድብቅ አልነበረም።
ስለሆነም ሁለቱ ጦማሪዎች ዛሬ ሁኔታውን እንደ አዲስ በማቅረብ ያውም የጠብታ ውሃ ታክል እንኳን የግል ሳይንሳዊ ምርምር ባላደረጉበት ሁናቴ (ለመሆኑ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ምንድን ነበር ያስተማሯቸው?) ሌላውን በጅምላ ከመውቀሳቸው በፊት ከእምነት ወዳጅ ከሚሆኗቸው የኃይማኖት ጳጳሳትና ተቋማት ጠይቀው ለመረዳት ቢሞክሩ መልካም በሆነ ነበር። ነገር ግን አላማቸው በርእሱ የበለጠ ጥራት እንዲገኝ የታለመ ሳይሆን ከእምነታቸውና ፈጣሪያችን ከሚሉት ጉያ ተሸጉጠው የራሳቸውን ድብቅ አላማ ለማስረገጥ በመሆኑ በበርካታ ሕዝብ እንዲነበብላቸው በሪፖርተር ጋዜጣ ሳይቀር እንዲታተምላቸው ያደረጉት ጥረት ያሳብቅባቸዋል።
ይሁንናም የተቀናቃኝነት እንቅስቃሲዎች በግራም በቀኝም፣ በፊትም በስተኋላም ከላይም ከታችም ቢዥጎደጎዱም የዝግመተ ለውጥ ፅንሰ ሃሳቦችና የምርምር ውጤቶቹ በበርካታ ሊቃውንቶች ትክክለኛነታቸው በጥናታዊ ምርምር እየተረጋገጡ ተቀባይነት እያገኙ መምጣታቸው የተቃዋሚዎቹን ጅራፍ በተወሰነ ደረጃ ቢያለዝብም አለመገታታቸው በኛዎቹ ፅሁፍ አቅራቢዎች ከንቱ ልፋት የሚያረጋግጠውም ይህንኑ ክስተት እንጂ ሌላ አይደለም። ወደዚህ ሴረኛ ተግባር ከመሰማራታቸው በፊት ከነሱ በበለጠ እጅግ ተደማጭነት ያላት የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ለአመታት ስታስተናግደው የነበረውን ተቃውሞ እንዳለ መቀጠሉ ትርጉም የለሽ መሆኑን በመገንዘብ ሊቃነ ጳጳስ ዮሃንስ ፓወሎስ ሁለተኛ በኦክቶበር 22 ቀን 1996 አ.ም ለተሰበሰበው የካቶሊክ የምሁራን ሊቃውንት ጉባኤ” የሰው ፍጡር ሥዕላዊ ገፅታና ዘመናዊ የዝግመተ ለውጥ ፅንሰ ሃሳብ “ በሚል ርዕስ በተገለፀው መልዕክት ላይ የተጠቀሱት እሳቤና ሌሎች ተመሳሳይ መጣጥፎችን ቀደም ብለው ለማግኘትና ለማንበብ ቢጥሩ ኖሮ ከስህተት ጎዳና ከመሰማራት ያድናቸው ነበር።
ስለ ዝግመተ ለውጥ ፅናእ ሃሳብ ውስጣዊ ይዘቱን በቅጡ ያልተረዱ በመሆናቸው ይህንን ድክመታቸውን ለመሸፈን ባላቸው ውስጣዊ ፍላጎታቸው ገና ከጅምሩ አንስቶ ገጾቻችውን በስድብና የዛቻ ቃላቶች ብቻ ሳይሆን ከፅንሰ ሃሳቡ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት በሌላቸው ትርከቶች የተሞሉ ናቸው። ለምሳሌ በመሰረቱ የዝግመተ ለውጥ ፅንሰ ሃሳብ ትኩረት በሕይወት፣ ፍጥረታትና እጸዋት ላይ መሆኑ ወደጎን ተደርጎ ምንም አይነት ግንኙነት ከሌላቸውና የሰው ፍጡር የቴክኖሎጂ ምርምር ውጤት ከሆኑት የኮምፕዩተርና አውሮፕላን ቁሳቁስ አካላት ጋር በማገናኘት በተሳሳተ ጎዳና ተጉዘው ሌላውን አንባቢዮቻቸውን ግራ ለማጋባት ሲውገረገሩ ይስተዋላሉ።
በአሁኑ ወቅት በተፈጥሮ ሳይንስ በተለይም በባዮሎጂ ትምህርት ተመራማሪ ሊቃውንቶች እየተመረመረ ትክክለኛነቱ እየተረጋገጠና ከፍተኛ ተቀባይነቱ በካቶሊክ ሊቃነ ጳጳሱ ፓወል ሁለተኛ ሳይቀር ምስክርነት የተሰጠበትን የዝግመተ ለውጥ ፅንሰ ሃሳብ እንዳለ ጥላሸት መቀባት የሁለቱን ፀሃፊዎች ጥራዝ ነጠቅነት ከመግለፅ ውጭ በሌላ በምንም አይነት ሊተረጎም አይችልም። ማህበራዊ ዳርዊንዝምን ለመቃወም ከሆነ ይህም ቢሆን እንደ መስቲካ ታኝኮና ተተፍቶ ትቢያ የተጣለውን እንደ አዲስ አንስቶ ከስድብ ዛቻ ጋር ደባልቆ ያዙኝ ልቀቁኝ ማለት ምን የሚሉት ፉከራ ነው? የንቃተ ህሊና ዳብሮት ሳይሆን ዝቃጭነትን አመልካች ነው። ለእምነታቸውና ፈጣሪዬ ለሚሉት ጥብቅና ለመቆም ከሆነ በነሱ አነጋገር እነሱ ራሳቸው ከዲያቢሎስ ጠባይ በመራቅና በመላቀቅ እንደ ጠንሳሾቹ ከተሳሳተ መረጃ በመመርኮዝ ሳይሆን ኢትዮጵያዊ ጨዋነትና ምሁራዊነትን በተላበሰ ሁናቴ ተቀባይነትን ለማግኘት የኃይማኖታቸው አስተምህሮ በሚጠይቀው በፀሎትና በሰላማዊ መንገድ መጣር እንጂ በፉከራ መደንፋት እንኳን ለነሱ ለቀድሞ አባቶቻቸውም አለመሳካቱን በቅጡ ቢያጤኑት ይበጃቸው ነበር። ለነገሩ እውነተኛ አማኝ ለመምሰል ፈጣሪዬ፣ ፈጣሪዬ እየተባለ ተደጋግሞ ስለተፃፈና ስለተነገረ ከይሲነት ከተጠናወተው ከዲያቢሎስ መራቅ ሊሆን እንደማይችል ሁለቱ ፀሀፊዎች በማስረጃነት ሊቀርቡ የሚችሉ ናቸው።
ኒውተንና ጋሊሌዮ በፍዚክስ የትምህርት መስክ አዲስ የእውቀት ዘመን እንዳበሰሩት ሁሉ በጥናቱ ምርምሩ የደረሰበትን የዘር ምንጮች መፈጠርና የእድገት ሂደት ያመነጨው ቻርለስ ዳርዊንም በበኩሉ በሳይንስ የታሪክ ሂደት የክብር ካባ ለመላበስ የታደለ ብሩህና ዝነኛ ሊቃውንት ነበር። ለዚህም ያበቃው ልዩ ተአምር ኖሮት ሳይሆን ዋና ምክንያት ሆኖ የተከሰተው በምድር ላይ የነበሩ፣ ያሉ ወደፊትም የሚኖሩ የሕይወት ፍጥረታት የሰው ፍጡር ሳይቀር ከሚሊዮን እስከ ሚሊያርድ አመታት በሚቆጠር ጊዜ ውስጥ ራሳቸውን በተፈጥሮ ሂደት ከሚገኙበት ከበባዊ ሁናቴ ጋር በማስማማት፣ በማዛመድና በማዋሃድ እንጂ ከነሱ በላይ በሆነ አንዳች አደራጅና ንድፍ አውጪ ኃይል ሆነ ተብሎ የተቀነባበሩ እንዳልሆኑ በምርምር የማግኘቱ ሁናቴ ነበር። በዚህም የተነሳ የዳርዊን የዝግመተ ለውጥ ፅንሰ ሃሳብ ከኃይማኖት ከክርስትና ተቋማት ብቻ ሳይሆን ጤናማ አዕምሮ የተፈጥሮ እውቀት አላቸው ተብለው በሚገመቱት የሕብረተሰብ ክፍሎች ሳይቀር ለመረዳት መጀመሪያ ሰሞን በመቸገራቸው ተቃውሞ የገጠመው መሆኑ የሚያስገርም ሊሆን አይችልም።
ይህ በንዲህ እንዳለ የባዮሎጂ የዝግመተ ለውጥ ፅንሰ ሃሳብ በርካታ የምርምር ውጤቶችን በማቅረብ ከፍተኛ አድናቆት እያተረፈ በመስኩ በተሰማሩ ሊቃውንቶች ዘንድ የሕይወት ሳይንስን በጠንካራ አለት እየገነቡ ሄዱ። ከዚህ በፊት ይቀርቡ የነበሩት ተቃውሞዎች ጩኸታቸው ረገብ ቢልም በአሁኑ ወቅት የዝግመተ ለውጥ ፅንሰ ሃሳብ በቀለም ትምህርት በተሰማሩ ክፍሎች ክርክሩ ተቀባይነት ማግኘት አለማግኘት ብቻ ሳይሆን የአለም ሥዕላዊ ገፅታ በተፈጥሮ የዝግመተ ለውጥ ፅንሰ ሃሳብ ወይንስ በፈጣሪ ተቀናብሮ በሚደረግ የአፈጣጠር ሂደት መረዳት ይቻላል ወይንስ አይቻልም የሚል መልክ ተላብሶ አሁንም ድረስ ውይይቱ ቀጥሎ መገኘቱ ሁሉም የሚያስተውለው ክስተት ነው። 200ኛ አመቱ ሲከበር በሕዝብ የመገናኛ ተቋማት የተዘገቡት መጣጥፎች ይህንኑ የሚመሰክሩ ናቸው።
በሌላ በኩል ደግሞ በ19ኛው መቶኛ አመት መጨረሻ ዳርዊን በሕይወት እያለ የዝግመተ ለውጥ ፅንሰ ሃሳቡ በባዮሎጂ የትምህርት ሊቃውንቶች ዘንድ በከፍተኛ ደረጃ ውይይት እየተደረገበት ባለበት ወቅት በሕብረተሰቡ ውስጥ ሰፍኖና ተንዘራፎ የነበረውን ጨቋኝና በዝባዥ የፖለቲካና የኤኮኖሚ ስርዓት በምን ምክንያት ሊከሰት እንደቻለ ለመግለፅ የወሰኑ ብቅ ብቅ ማለት ጀመሩ። የቁራ መልዕክተኛና የጨቋኝና በዝባዥ ሥርአቱ ደጋፊ የመሆናቸው ክስተት በገሃድ ታየ። ከነዚህ ውስጥ አንዱ እንግሊዛዊ ፈላስፋ ሀርበርት ስፔንሰር (Herbert Spencer) የተባለው ሲሆን „Survival of the fittest“ የሚለውን እሳቤ ዋና አመንጭ በ 1864 ዓ.ም. „Principles of Biology“ በሚል ርዕስ ባሳተመው መፃፉ ለሴራ አላማው መጠቀሚያ ብቻ ሳይሆን ለመጀመሪያ ጊዜ እውቁ የኤኮኖሚ ባለሙያ አዳም ስሚዝ የኤኮኖሚ ስውር እጅ” በማለት እንዳስቀመጠው ሁሉ እሱም በበኩሉ “የዝግመተ ለውጥ ፅንሰ ሃሳብ ስውር እጅ” እሳቤውን በህረተሰቡ ላይ በመገልገያነት ተጠቃሚ ለማድረግ የጣረ ግለሰብ ነበረ። ማስረገጥና ማስተላለፍ የፈለገው እሳቤው ደግሞ ልዩ ነገር ሳይሆን በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ በማህበራዊና በኢኮኖሚ ፖለቲካ ጠንካራው አሸንፎ ሕይወቱን በቀጣይነት ሊያረጋግጥ ሲችል ደካማው ደግሞ በሂደት ውድመቱን ያፋጥናል የሚለውን የተሳሳተ እሳቤን ተቀባይነት ማስገኘት ነበር ዋና ሥራው። “የቻለ ያሸንፋል. ያልቻለ ይጠፋል” የሚለው እሳቤ ሰብአዊነት የጎደለው አስተሳስብ መሆኑ ለብዙሃኑ ሕዝብ ቀናኢነት ባላቸው በርካታዎች ትግል ከውዳቂነትና ከታሪክ ትቢያ እንዲጣል የተደረገ መሆኑ ደግሞ የታሪክ ድርሳናት የሚያመላክቱት ናቸው።
የሰው ፍጡር የመኖሩ ሕልውናው በፉክክር፣ በትግልና በጦርነት የሚመሰረት ብቻ ሳይሆን ለእድገቱም ሆነ ለውድቀቱ ተጠያቂ ራሱ ነው በማለት ፍፁም የሊበራል እይታው ላይ የተመሰረተ ጠንካራው የበላይነቱን ትርፍ ደካማው ደግሞ የድክመቱን ፅዋ መጎንጨት ይኖርበታል በማለት እጅግ የተሳሳተ እሳቤውን የገለፀ ነበር። በመሆኑም የሶሺያል ዳርዊኒዝም ፅንሰ ሃሳብ መሰረት ጣይ ስፔንሰር እንጂ ዳርዊን እንዳልነበረ በበርካታ መጣጥፎች የተገለፁ ናቸው። በመሆኑም ይላል ስፔንሰር “ደካሞችና በሽተኞች ከመንግስት ሆነ በግል ደረጃ የሚደረግላቸው እንክብካቤም ሆነ እርዳታ ቆሞ እነዚህን ዜጎች ማጥፋት ይገባል” ሲል የተሟገተ ሴረኛ ግለሰብ ነበር። ይህንን በሚገባ ሳያጤኑ ወይንም ደግሞ ሳይመለከቱ “በዳርዊን የዝግመተ ለውጥ ፅንሰ ሃሳብ (Darwins Theory of Evolution) መሰረት በተፈጥሮ ውስጥ የማያቋርጥ የመኖር ትግል እንደሚደረግና ፣ በዚህ ትግል ውስጥ አሸናፊ የሆኑት እንስሳትና እፀዋት ወይም ለተፈጥሮ ተስማሚ የሆነ የአካል ክፍል ያላቸው ሲቀጥሉ፣ ያልቻሉት ወይም ደካሞች እየጠፉ ለከባቢ ተፈጥሮ ተስማሚና ወይም አሸናፊዎች እየቀጠሉ፣ የተሻሉ ዝሪያዎች እየተፈጠሩ እንደሚመጡ ያስረዳሉ።” በማለት ውሸትና ግማሽ እውነት የተደበላለቀበት ትንታኔ በማውጣት ለጥላሸት ቀቢ እሳቤያቸው መጠቀሚያ ይገለገሉበታል።
በ 1920 ዓ.ም. ደግሞ ካርል ቢንዲንግ (Karl Binding) ና የፍራይቡርግ ሳይካታሪስት የነበረው አልፍሬድ ሖሀ Freiburg Psychaterist Alfred Hoche በጋራ በመሆን አካለ ጉዳተኞችን ለማጥፋት ፍቃድ ይሰጠን ብለው ጥያቄ ማቅረባቸው በታሪክ የተመዘገበ ኃቅ ነው። ከዚህ በኋላ እንግዲህ የዳርዊን የዝግመተ ለውጥ ፅንሰ ሃሳብ መሰረታዊ ይዘቱ እንዲዛባና ለራስ ኬይሲ አላማ እንዲስማማ በሀሰት መረጃም በማስደገፍ ለምሳሌ ለይሁዶች የዘር የማጥፋት ተግባር ሊፈፀምባቸው መሰረት ሆኖ ያገለገለው።
ከዚሁ ጋር በተያያዘም በዚሁ ጎዳና ለመጓዝ ይጥር የነበረው የእንግሊዙ ፈላስፋና የፍጥረታት ተመራማሪ የነበረው ፍራንሲዝ ጋልቶን(Francis Galton) “ምርጥ የሰው ዘር ለማፋሪያ” ባህላዊ ዳርዊኒዝም በተሰኘ እሳቤ ተንተርሶ ሲኳተን የነበረ ግለሰብ ነበር። መሰረቱ በፖላንድ ሀገር ከምትገኘው ካርካው ከተማ ነው ተብሎ የሚነገርለት የሶሲዮሎጂ ሊቃውንት (Ludwig Gumplowicz) ሉድዊግ ጉምፕሎዊች ደግሞ በበኩሉ በኢምፔሪያሊስቶች ኃይል ጥንታዊ ህዝቦችን ለማጥፋትና ለማውደም የተደረጉትን እኩይና አሰቃቂ ተግባራት በህይወት ለመኖር የተደረገ የዘር ትግል አድርጎ ለማቅረብ በዝግመተ ለውጥ ፅንሰ ሃሳብ ሽፋን ሥር የተደረገ ጥረት ሲሆን በጀርመን የናዚዎች ፍፁማዊ አምባገነን አገዛዝ ዘመንም ”እርባና የሌላቸው” በማለት በአካለ ስንኩልነት፣ በጤና ጉድለት ይሰቃዩ የነበሩትንና ዘራቸውን በዝቅተኛ ደረጃ የሚመለከቷቸውን ዜጎቻቸውን ሕይወት ለማጥፋት መሰረት ያደረጉት ማህበራዊ ዳርዊኒዝም (Social darwinism) የሚጠቀስ ነው።
ዳርዊን በበኩሉ ፅንሰ ሃሳቡን በጅምላ አንድን ህብረተሰብ ለመፈተኛ ሳይሆን በሕብረተሰቡ ያሉ ግለሰብ አባላትን የሚመለከት መሆኑን ለመግለፅ ቢጥርም ስለሚኖርበት ሀገርና የፖለቲካ ሥርዓቱ ከፍተኛ ግምት ይሰጥ ስለነበር ስለ ጥንታዊ ሕዝቦች የተሳሳተ ግንዛቤ ነበረው ተብሎ የሚታማ ነበር። ይህ ሁናቴ ከወቀሳ ባያድነውም ያበረከታቸው የምርምር ውጤቶችን አያሳንስበትም። በባህል ላይ የተመሰረተ ዝግመተ ለውጥ በሚያስደንቅ ፍጥነት በባዮሎጂ ዝግመተ ለውጥ በመተካቱ ይቀርቡ የነበሩ ችግሮች ሙሉ በሙሉ ባይቀረፉም ሚናቸው እጅግ በጣም ዝቀተኛ እንደሆነ የሚነገር ነው። ይህ ሆኖ ሳለ የዳርዊንን የዝግመተ ለውጥ ፅንሰ ሃሳብ ለሁሉም ተጠያቂ ለማድረግ መባዘን ከብት ባልዋለብት ኩበት ለመልቀም መኳተን ነው ተብሎ አፅንዖት በተመላበት ሁናቴ በተደጋጋሚ እየተገለፀ የሚገኘው። መንፈራገጥ የማይፈለግ ቢሆንም ጨርሶውኑ ይጠፋል ማለት እንዳልሆነ ግን መገንዘቡ መልካም በሆናቸው ነበር።
ለዚህም ነው የቻርለስ ዳርዊን ዝግመተ ለውጥ ፅንሰ ሃሳብን መሰረታዊ ጭብጡን በአግባቡ ለመረዳትና በስህተት ጎዳና ተጉዞ በማይሆን እንካ ሰላንቲያ ውስጥ ከመግባት ለመዳን እንደዚህ አይነት አመለካከቶችና ጥረቶች እንዴት ሊከሰቱ እንደቻሉ ለመገንዘብ የዝግመተ ለውጥ ግንዛቤ፣ ምንንነትና ከየትስ ሊመጣ እንደቻለ፣ በምንስ ሁናቴ ተጠቃሚ ሊሆን እንደሚችል በቅድሚያ ማወቁ ወሳኝነት አለው ተብሎ አፅንዖት በተሞላበት ሁናቴ በመስኩ የምርምር ተመክሮ ባካበቱ ሊቃውንቶች አማካኝነት ይህ ምሁራዊ ምክር የሚለገሰው። በአጭሩ እንመልከተው።
ቅድሚያዊ ሁናቴ
በበርካታ ምሁራን እንደሚገለፀው የተፈጥሮ ሳይንስ ፍልስፍናው የተፀነሰው የአለም ፍጥረትና በውስጡ የታቀፉት ሁሉ ከአንድ እሳቤ ነው ከሚለው የፕላቶ ትምህርት ነበር። ይህ አስተያየት የኋላ ኋላ ለሜታፊዚክስ ሥነ ትምህርት መፀነስና መስፋፋት መሰረት ሊሆን የበቃ አንድ የእውቀት ዘርፍ ነበር። ይህ በንዲህ እንዳለ አሪስቶተለስ የተባለው ፈላስፋ በበኩሉ አለምን በሶስት ደረጃ (ህይወት በሌለው፣ በእፀዋትና በእንስሳት) የከፈለበት የፍልስፍና ትምህርትና በዚህም የተመረኮዘ የአለም ሥዕላዊ ገፅታ በሚቀጥሉት ተከታታይ መቶኛ አመታት ውስጥ ዋነኛ ተፅዕኖ አሳዳሪ ሊሆን የቻለና በወቅቱ የእውቀት መሰረት ተብሎ የክብር ካባ የተደረበለት እንደነበር ሊቃውንቶቹ የሚመሰክሩት ነበር። በ17ኛውና በ 18ኛው መቶኛ አምት በወቅቱ የነበረው ህብረተሰብና የሳይንስ ዘርፎች ሁሉ በቤተክርስቲያንና እሷ ታስተናግደው በነበረው የአለም እይታዋ ተፅዕኖ ሥር የሆኑበት ወቅት ስለነበር ከእምነት አስተምህሮቱ የተዛነፈ ምርምር ለማቅረብ የሚታሰባቸው አልነበረም። በተለይም ተፈጥሮን አስመልክቶ ይደረጉ የነበሩቱ የምርምር ተግባሮች በአብዛኛው በመፅሃፍ ቅዱስ ውስጥ በተጠቀሰው የተፈጥሮ እይታ የተመረኮዙ ነበሩ። ፈጣሪ አለምን በስድስት ቀናት ውስጥ እንዲሁም እርስ በርስ ምንም ግንኙነት የሌላቸው እፀዋትንና እንስሳትን ፈጠረ። የዚህ ሂደት ዋነኛ ሆኖ የተስተናገደው ደግሞ ሰው ፍጡር ነው የሚለውን እምብርት አስተሳሰብን ተዳፍሮ ከጥያቄ ለማስገባት የሚሞክር የሚደርስበትን ምላሽ ከጋሌሊዮ ለመረዳት የሚያስቸግራቸው ስላልነበረ ጥንቁቅ መሆናቸው የሚያስገርም አልነበረም።
ይሁንናም ይህ እይታ ፍጥረታት ሁሉ በአንድ ጊዜ ምንም አይነት የለውጥ ሂደት ሊስተናገድበት በማይቻልበት ሁናቴ የተፈጠሩና የአለም ሥዕላዊ ገፅታም በዚሁ እይታ ዙሪያ ውስጥ የተመሰረተ ነው ተብሎ ይታመነበት የነበረው እሳቤ ሊቃውንቶችና ምሁራኖች በምርምር ከሚያገኙት ውጤቶች ጋር ግን ሊጣጣም አልተቻለውም። በመሆኑም ግትርነትን ሳይሆን ታታሪነትን በተላበስ እይታ ዋና ክብደቱ ፍጥረታት በተለያየ አቅጣጫ የሚጓዙ ብቻ ሳይሆን እርስ በርስም ግንኙነት ሊያደርጉ ይችላሉ በሚለው አስተሳሰብ የመተካቱ ሁናቴ የግዴታ እየሆነ ይከሰታል።
የተፈጥሮ ሳይንስ ሚናም ፍጥረትን በአድናቂነት ብቻ የማንፀባረቅ ገደቡን እርግፍ አድርጎ ትቶ ፍጥረትና ራሱኑ የለውጥን ሂደትና የተፈጥሮ ሕግን በፊዚክስ የትምህርት ተቋም እንደሚደርገው መርምሮ ማሳወቅ ግዴታ ሆኖ ተከሰተ። በዚህ ጎዳና በርካታ ተመራማሪዎች ያስገኙት ውጤቶች በፈራ ተባ ድባብ ውስጥ የሚገኙትን ሳይቀር በምርምራቸው እንዲገፉበት ውስጣዊ ግፊት የተላበሰ እይታ በመፍጠሩ፣ እየዋለ እያደር ለዝግመተ ለውጥ ፅንሰ ሃሳብ በሁለት እግሩ እንዲቆም አስተዋፅዖ ለማድረግ ችለዋል። የዝግመተ ለውጥ ፅንሰ ሃሳብ በተወሰነ የተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፍ ብቻ የተመረኮዘ ሳይሆን በሌሎች ዘርፎች ለምሳሌ በቀድሞ ፍጥረታት የምርምር ስነ ትምህርት ሳይቀር እንደሚያሳየው የበርካታ ዘርፎች የጋራ ድምር ውጤት መሆኑን ያመላክታል። በመሆኑም የዝግመተ ለውጥ ፅንሰ ሃሳብ መሰረታዊነት የተለያዩ የተፈጥሮ ሂደቶችን ለመረዳት ዋና መሰረት ብቻ ሳይሆን ሁሉም የተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፎች በቅልጥፍና ምርምር እንዲያደርጉና አዳዲስ የሳይንስ ዘርፎችንም እንዲመሰረቱ የሚያበረታታ ግፊት አሁንም ድረስ እያደረገ ይገኛል።
የዳርዊን የምርምር ውጤት ያስከተለው መሰረታዊ ቁም ነገር ቢኖር በተፈጥሮ ሳይንስና በኃይማኖት ስነ ትምህርት መካከል የነበረውን የግንኙነት ገመድ ለመበጠስ መቻሉ ብቻ ሳይሆን የተፈጥሮ ሳይንስን ከኃይማኖት አስተምህሮት ጥገኝነት አላቆ ግላዊ የምርምር ነፃነቱን ማጎናፀፉና በራሱ ግላዊ ኃላፊነት ምርምሮችን እንዲያካሂድ ማስቻሉ ነበር። በዚህም የተነሳ በሁለቱ መካከል የወደፊት ግንኙነታቸው ምን መልክ መያዝ ይኖርበታል የሚለው ለበርካታ አመታት አነጋጋሪ ሆኖ የቀጠለ ነበር። በዚህ ብቻ አልተገታም። ዳርዊን በተደጋጋሚ ባደረገው ጥናታዊ ምርምር ለኢንተሊጀንት ዲዛይን በሚል በአጥባቂ ኃይማነተኞች ለዝግመተ ለውጥ ፅንሰ ሃሳብ እንደ አማራጭ ቀርቦ ለነበረው አስተያየት ምንም አይነት ማስረጃ ለማግኘት አለመቻሉ ዳርዊንን ይበልጥኑ ፅናትን አላበሰው እንጂ አላሸማቀቀውም። በምርምሩ ይበልጥ ገፋበት እንጂ አላሰነፈውም።
የዳርዊን የዝግመተ ለውጥ ፅንሰ ሃሳብ አንዳንዶች ለማመላክት ይሞክሩት እንደነበረው ለፀረ ኃይማኖት መስፋፋት ረግረግ አመቺ ሆኖ አልተከሰተም። ሆኖም በርካታ ንትርኮችን ያስከተለው የሰው ፍጡር ዝሪያው “ከዝንጀሮ ነው የሚለው እሳቤ “ በበርካታዎች ዘንድ ዜናው ተዛብቶ በመናፈሱ ምናልባትም በጣም አስደንጋጭና የልብ ትርታ መከሰት ጋር እንደሚያያዝ ቢነገርም ይህ ግንዛቤ/አረዳድ አዲስ ያልነበረ መሆኑ ቢታወቅም ዋናው ጉዳይ የሰው ፍጡር ከክርስትና ባጠቃላይ ከእምነት ተቋማት ባለሥልጣናት ጋር የነበራቸው ግንኙነትና የፍጥረት አረዳድ በፍፁምነት የሚታይና በምንም አይነት ከጥያቄ እንዳይገባ ይደረጉ የነበሩ ጥረቶች ሁሉ ለእምነታቸው ፅናትን ሳይሆን ከፍተኛ ብዥታና ጥርጣሬን እያስፈኑ መቀጠላቸው ነበር የስጋታቸው እምብርት ሆኖ የተከሰተው። በጭፍን የሚደረግ እምነት የኋላ ኋላ ውጤቱ ይህ ከመሆን እንደማያልፍ ለሁሉም ጠቋሚ ትምህርት በሆነ ነበር። ግና…..
የዳርዊን ፅንሰ ሃሳብ ፍፁም ተቃዋሚዎችም ሆኑ ሁለቱ ፀሃፊዎች በተፈጥሮ ሳይንስ ምርምር የሚገኙ የእውቀት ውጤቶች ጠል ለመሆናቸው “በዝግመተ ለውጥ ፍልስፍና ሰው በዝግመተ ለውጥ የተለያዩ ደረጃዎች አልፎ ዘመናዊ ሰው የተባለው ሆሞ ሳፒየንስ (Homo Sapiens)200, 000 – 300, 000 አመት በፊት እንደተገኘ ያስረዳል። ከዚያ በኋላ አሁን ያለበት የማህበረሰብና የሥልጣኔ እድገት ለመድረስ ቢያንስ 200 000 አመትን ፈጅቶበታል። ሆሞ ሳፒየንስ በመጀመሪያ በአፍሪካ እንደነበረና 180, 000 – 50, 000 ከአፍሪካ ወደ ተለያዩ የአለም ክፍሎች እንደተሰራጨ ይተርካል።” ካሉ በኋላ “የታሪክ የመፅሃፍ ቅዱስ፣ የአርኪዎሎጂና የስነ ሕዝብ መረጃዎች ግን የሰው ልጅ በዝግመተ ለውጥ፣ በአጋጣሚዎች ጋጋታ በአፍሪካ እንደተገኘና ከአፍሪካ ለመውጣቱ አያረጋግጥም።” በማለት የእውቀት ጠልነታቸውን አስፍነው የተፈጥሮ ሳይንስ ተመራማሪዎችን በውሸታምነት እየከሰሱ የራሳቸውን “በመፅሃፍ ቅዱስ መሰረት የተደረጉት የታሪክ፣ የአርኪዎሎጂና የስነ ሕዝብ ጥናቶች የሰው ልጅ ሥልጣኔ የቅርብ ጊዜ መሆኑን ነው የሚያረጋግጡት” በማለት ይፈጠማሉ። በቅርቡ ለአለም ሕዝብ ይፋ የሆኑ ለህይወት ጠቃሚነት በዋና መሰረታዊነት የሚታዩ እፀዋትን አስመልክቶ በተለያዩ የአለማችን አካባቢዎች በጥናታዊ ምርምር የተደረሱበትን ውጤቶች፣ እንዲሁም በአፍሪካ ድንቅነሽን የመሰሉ በተለያዩ የአፍሪካ አካባቢዎች በተለይም በሞሮኮ ጀበል ኢርሁድ (Jebel Irhoud) የተገኙ የምርምር ውጤቶችን ፈልገው ቢመለከቱ ከመሰል ስህተቶች ይድኑ ነበር።2,3,4 ለራስ እምነትና መረጃ ጥብቅና መቆም ባያስቀጣም በበርካታ ተመራማሪዎች የተገኙ ውጤቶችን በውሸታምነት መፈረጅ ግን ቢያንስ ያስገምታል። ዋጋም ያስከፍላል።
Jean-Jacques Hublin, Abdelouahed Ben-Ncer, Shara E. Bailey, Sarah E. Freidline, Simon Neubauer, Matthew M. Skinner, Inga Bergmann, Adeline Le Cabec, Stefano Benazzi, Katerina Harvati, Philipp Gunz
New fossils from Jebel Irhoud (Morocco) and the Pan-African origin of Homo sapiens
Nature, 7 June 2017, DOI: 10.1038/nature22336
ዳርዊን በ 1882 ዓ.ም. በ 73 አመቱ በደረሰበት የልብ ድካም ህመም ምክንያት ከዚች አለም በሞት ሲለይ የቅርብ ዘመዶቹ የመጨረሻውን የህይወቱን 40 አመታት ባሳለፈበት መንደር ለመቅበር ዝግጅት በሚያደርጉበት ወቅት የቅርብ ወዳጆቹና አክባሪ የሥራና የሙያ ባልደረባዎቹ በታዋቂው በለንደን ዌስትሚኒስትር አቤይ የቀብር ቦታ እንዲቀበር ባደረጉት መጠነ ሰፍ ቅስቀሳ፣ እንዲሁም የቀብሩ አስተዳደርና የሕዝቡም መልካም እይታ ታክሎበት የሙያ ጓደኞቹ ጆን ሀርሸልና አይሳክ ኒውተን ዘለአለማዊ እረፍታቸውን ባገኙበት አቅራቢያ በ 26 አፕሪል 1882 ዓ.ም ተቀበረ። የዳርዊን ሥዕላዊ ገፅታ ለባህር ጉዞው የተጠቀመበት የመርከብ ሥዕልና የማጉሊያ መነፅር ጋር በ 10 የእንግሊዝ ፓውንድ የመገበያያ ገንዘብ ላይ ከ 2000 ዓ.ም. ጀምሮ ለ 18 አመታት የዘለቀ ከበሬታን እንዲላበስ በማድረግ ለሊቃውንቱ ዳርዊንና ድንቅ ስራዎቹ ያላቸውን ልዩ ከበሬታ አሳይተዋል።
ዳርውንና ስተፈን ሆውኪንግ የተቀበሩበት ቦታ(ከድረ ገጾች የተገኙ)
ዳርዊን የራሱን የዝግመተ ለውጥ ፅንሰ ሃሳቡን የገነባው በተለያዩ ዝነኛና ታዋቂ ሊቃውንቶች ለምሳሌ ጊዮርገስ ቡፎን፣ ዣን ባፕቲስታ ላማሬክ፣ ከዳርዊን አጎት ከሆነው ኤራስሙስ ዳርዊን ከተገኙ የተለያዩ የምርምር ውጤቶችን በማዳበርና በማዋድ ላይ በመመርኮዝ ነበር። ዳርዊን ከመቶ አመት በበለጠ ጊዘ ውስጥ የተገኙትን የምርምር ውጤቶች አቀናብሮና አዳብሮ ለህትመት በማብቃቱ ፅንሰ ሃሳቡ በራሱ ሥም እንዲጠራ ስለተደረገለት (Sir) የተሰኘውን የክብር ካባ ሊላበስ በቅቷል። በፅንሰ ሃሳቡ ተመርኩዞም የሰው ፍጡር በጊዜ ሂደት የአካል ቅርፃዊ ለውጥ እያመጣ በዚሁ ለውጥም ተመርኩዞ እያደገና እየዳበረ እንደሚሄድ አስተማረ። ማስተማር ብቻ ሳይሆን ዝንጀሮና የሰው ፍጡር የጋራ ዝሪያ እንደነበራቸውም ይፋ አደረገ። የዳርዊን አስተምህሮት ወደ ጂኦሎጂ፣ ቦታኒክ ና ባዮሎጂ የትምህርት መስክ በሞላ ተሰራጨ። ተቀባይነትም እያገኘ በመሄድ ዛሬ ያለንበት ደረጃ ተደርሷል። በተለይ ሁለቱ ዋና እሳቤዎቹ ማለትም “ዝሪያዎች ይለዋወጣሉ” የሚለውና “ይህ ለውጥም የሚካሄደው በተፈጥሮ ምርጫና በአካባቢው በሚገኘው ሁናቴ ራሱን በማስማማት/ማዋሃድ/ማላመድ ራሱን ለማኖር በሚደረግ የጥረት ትግል “ በአሁኑ ወቅት እነዚህ እሳቤዎች ትምህርት ቀመስ በሆኑ ብቻ ሳይሆን በበርካታ ተራው ሕዝብ ዘንድም የሚታወቁ ሊሆኑ በቅተዋል። ሆኖም የተለየ ትርጉም/ግንዛቤ ተሰጥቷቸው ለእኩይ አላማና ተግባር መገለገያ ከመሆን አልተረፉም።
በዚህም የተነሳ ከነዚህ እኩይ ተግባር አቀንቃኞችና አጃቢዎቻቸው ዳርዊን ራሱን አግሎ በራሱ እይታ ብቻ በመጓዝ የሰው ፍጡር ከተወሰነ እድገት በኋላ የባህል እሳቤና በሕብረተሰቡ ላይ ባለው ተፅዕኖ ዝሪያውን እንዳለ ለማቆየትና ለማዳበር ዋና ምክንያት እንደሆነ አስተማረ። በዚሁ እሳቤው ላይ በመመርኮዝም መንፈሳዊ ዳብሮት (ሞራል፣ እሴቶች፣ ማህበራዊ ግንኙነት አዕምሯዊ እድገት) የመሳሰሉትንና ሌሎችንም በጥልቀትና በስፋት እንዲመረምራቸው ውስጣዊ ግፊት ሰጥተውታል። ከምርምርም ውጤቶች ከፍተኛ አድናቆትን ያበረከቱለት የሰው ፍጡር ከሌሎች ፍጥረታት ጋር ሲነፃፀር ልዩነታቸው አጅግ በጣም አናሳ እንጂ ሰው የተለየ ልዩ ከፍታ ቦታ እንደሌለው በርካታ ማስረጃዎች ለማቅረብ መቻሉ ነበር። በዚህም የተነሳ ለእንስሶች እንክብካቤ እንዲደረግ የመንፈስና የሞራል መሰረት ለመጣል የቻለ ሊቃውንት ነበር ቻርለስ ዳርዊን ። ሆኖም ይህ ቀና አስተሳሰቡ የተለያየ ትርጓሜ እየተሰጠበት በነበረው “ለመኖር የሚደረግ ትግል” እሳቤ ተሸፍኖና ተውጦ ወደ ሕዝብ ጆሮ በአግባቡ ሊደርስ አለመቻሉ በዋና ምክንያትነት እየቀረበ ያለ እንደሆነ በበርካታ አድናቂዎች ዘንድ ተበክሮ የሚገለፅ ነው።
የዳርዊን የዝግመተ ለውጥ ፅንሰ ሃሳቦች ለእውቀት መገኘትና መዳበር ከፍተኛ ቦታ በሚሰጡ ሕብረተሰቦች ዘንድ በትምህርት ተቋማት ውስጥ እንደ አንድ መደበኛ የትምህርት መስክ በተለይም በባዮሎጂ ትምህርት ተማሪዎች እንዲማሩት የበቃ ነበር አሁንም ነው። ፅንሰ ሃሳቦቹ ትክክለኛ ለመሆናቸው በተለያዩ ጥናት አቅራቢዎችና ተመራማሪዎች ዘንድ ተረጋገጡ እንጂ ከኃይማኖት ጀርባ ተሸጉጠው ጥላሸት በመቀባት ምንም አይነት ተቀባይነት እንዳያገኝ ለማድረግ ከሚጥሩት ባላንጣዎቹ እንደፈለጉትና እንደተመኙት ከታሪክ ትቢያ ለመጣል አልተቻላቸውም። ፅንሰ ሃሳቦቹ ይበልጡኑ እየጎለበቱ፣ በአዳዲስ ውጤቶችም እየታጀቡ የዳብሮት ጉዟቸውን ቀጠሉበት እንጂ። ለነገሩ የፅንሰ ሃሳቡ የለውጥ ዳብሮት በመከሰቱ ራሱ ዳርዊን ዝግመተ ለውጥን ሥር ነቀል ለውጥ ብሎ እንደሰየመው፣ ተጨባጭ የሆነ የሕይወት መሰረታዊ ጠባይ መሆኑ እንዲረጋገጥ የበኩሉን ከፍተኛ አስተዋፅዖ አበርክቷል።
ተፈጥሯዊ ተመራማሪ የነበረው ቻርለስ ዳርዊን የራሱን ድንቅ ሥራዎች በጠንካራ ማስረጃዎች በማስደገፍና ግልፅነትን በተላበሰ መልኩ ያበረከታቸው ስድስት የምርምር ውጤቶች እትመት ጠቅለል ተደረገው ሲቀርቡ፣
ከ 1838 እስከ 1836 ዓ.ም. አምስት አመት የፈጀ የመርከብ ጉዞ በማድረግ ለፅንሰ ሃሳቡ መሰረት ሊሆኑ የሚችሉ በርካታ መረጃዎችን ስብስቦ ወደ ሀገሩ ተመለሰ።
ከ 1838 እስከ 1843 የጉዞው ውጤትን Zoology of the Voyage of HMS Beagle በተሰኘ የዝግመተ ለውጥ ፅንሰ ሃሳብ ፍንጭን ያካተተበት መፅሃፉን ይፋ አደረገ።
በ 1858 ዓ.ም. ዳርዊንና አልፍሬድ ሩሰል ዋላስ (Alfred Russel Wallace) ሁለት የተለያዩ በለንደን ሊኒአን ማህበረሰብ አቅርበው አምብዛም የአድማጩንና የአንባቢውን ትኩረት አልሳበም ነበር። ሆኖም ዳርዊን በተከታዩ አመት ፅንሰ ሃሳቡን ( ሀ. አለም ባለችበት መንቀሳቀስ የማትችል ቁም ቀር ሳትሆን በእድገት ለውጥ ውስጥ የምትገኝ መሆኗ፣
ለ. የለውጥ ሂደት የሚከናወነው ደረጃ በደረጃና በቀጣይነት መሆኑ፣
ሐ. የሰው ፍጡር የፍጥረቱ ሂደት እንደ ሌሎች ሕይወት ካላቸው ጋር ተዛማጅና ተጓዳኝ ስለመሆኑ፣
መ. የተፈጥሯዊ አማራጭ ክስተት በሁለት (በውልደትና ለመኖር ከከባቢ ሁናቴ ጋር በመላመድ) መስኮች እንደሚከናወን በስፋት ያቀረበበት “The origin of Species“ መፅሃፉ ከፍተኛ ተቀባይነት እያገኘ መጣ። ይሁንናም በመጀመሪያው ወቅት ተቃውሞ የገጠመው ቢሆንም ያስከተለው ብዥታ እምብዛም ነበር።
በ 1859 ዓ.ም. “On the origin of Species” በሚል ርዕስ ያቀረበው መፅሃፉ ታትሞ ወጣ። በዚህ መፅሃፉ እንስሳትና እጸዋት በሰው ፍጡር ተፅዕኖ አሳዳሪነት እንዴት እንደሚለዋወጡ ያሳየበት ሲሆን በ 1930 ዓ.ም. በዳርዊን ቀርቦ በነበረው ተፈጥሯዊ ምርጫ (natural selection>) “የጌነቲክ አባት” የሚል የእውቅና ካባ በተላበሰው ግሬጎር ሜንደለ ካቀረበው የዘር መወራረስ ሕግ ጋር ተዛምዶ Synthetical theory of the Evolution ኒኦዳርዊኒዝም ተብሎ በሚጠራው ለሰው ሰራሽ ለውጥ መሰረቱን ጣለ።
በ 1871 አ.ም. ደግሞ „ The descent of man and Selection in relation to Sex.” የሰው ፍጡር ዝግመታዊና ባዮሎጂካል አስተያየቱን፣ የሰው ፍጡር የት ቦታ እንዴትስ ዳብሮቱም ሆነ እድገቱ ሊከሰት እንደሚችል፣ ከሌሎች እንስሳት የሚለይበትንና ተመሳሳይነት የገለጠበት መፅሃፉን አሳተመ።
በ 1872 ዓ.ም. “On the expression of the Emotion in the man and Animals„ ሰውም ሆነ እንስሳ ተመሳሳይ የአካል ምልክትና ግልፅነት ያለው መልዕክት እንደሚያሳዩ የገለፀበትን መፅሃፉን አሳትሞ አወጣ።
በ 1881 ዓ.ም. ስለ ትል (worm) የነበረውን የተሳሳተ ዝንባሌ ያረመበትን The informatiom of vegetable mould, through the Action of Worms with observation on their habit የረጅም ጊዜ ጥናት ያደረገበትን የምርምር ውጤቱን የገለፀበት መፅሃፍ አሳተመ። ይህ ጥናታዊ ውጤት በእርሻ ሳይንስና በመሬት እንክብካቤ/ጥበቃ በርካታ ተመክሮ ባካበቱ ባለሙያዎች ዘንድ ጠቄሜታ እንዳለው የተነገረለት ነው። በነገራችን ላይ ጆን ባንቲስተ ላማርክ የተሰኘ ሊቃውንትም በወቅቱ አቅርቦት በነበረው እሳቤ በእንግሊዝ ሀገር ለፖለቲካውና ለኃይማኖታዊ ሥርአቱ አደገኛ የሚል ታርጋ ተለጥፎበት በተፈጥሮ ሳይንስ ሊቃውንቱ ዘንድ ከዳርዊን ባልተናነሰ መልኩ ክፉኛ ተቃውሞና ሂስ አድርሰውበት እንደነበር የሚታወስ ብቻ ሳይሆን መጠቀሱም አግባብነት ያለው የታሪክ እውነታ ነው።
አንባቢያን የዳርዊን ፅንሰ ሃሳብ መሰረት ናቸው ተብለው አፅንዖት ተሰጥቶበት የሚጠቀሱት እሳቤዎች ሲጠቃለሉ ከታች በሚገለጡት መልክ ማቅረብ ይቻላል።
ሀ. መራባት፣ ግለሰቦች የራሳቸውን ዝሪያዎች ለማቆየት ከሚያስፈልጋቸው ቁጥር የበለጠ የደሚያፈሩ ስለመሆናቸው፣
ለ. ልዩነትን ማንፀባረቅ፣ የአንድ ህብረተሰብ አባላት አንድ አይነት ሳይሆን የተለያየ የመለያ ምልክቶች ያሏቸው ስለመሆናቸው፣
ሐ. የሚያማርጡት መኖር፣ በወቅቱ ከሚኖረው የተፈጥሮ ከባቢ ሁናቴ ጋር ራሳቸውን ከሌላው በበለጠ ለማስማማት ውስጣዊ ግፊት የሚያድርባቸው ግለሰቦች ለስኬታቸው የተሻለ የተፈጥሮ አማራጭና ረዥም ጊዜ ለመኖር ጥሩ እድል ይኖራቸዋል; በዚህም የተነሳ የራሳቸውን የተለየ መለያቸውን ለሚቀጥለው ትውልድ የማስተላለፍ ችሎታቸው ከሌሎች የተሻለ ስለመሆኑ፤
መ. ማውርስ፣ የሚለዩ ምልክቶች በተወሰነ ደረጃ ለሚቀጥለው ትውልድ ማስተተላለፍ መቻላቸው የተሰኙ እሳቤዎች በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው።
ታዲያ ከዚህ በመነሳት ዝግመተ ለውጥ ፅንሰ ሃሳብ ውስጣዊ ይዘቱ ምንድን ነው? ለሚለው ጥያቄ
“ሕይወት ያላቸው ፍጥረታት ከአካባቢያቸው ሁናቴ ጋር ራሳቸውን ከቀድሞው በተሻለ ደረጃ በማላመድ ከትውልድ ወደ ትውልድ በሚደረገው ቅብብሎሽ የሚያሳዩት እድገትና የለውጥ ሂደትን የሚያመላክት ነው። በዚህም ሁናቴ ዝሪያቸው በቀጣይነት የመኖር እድላቸው ከፍ ያለ ነው። በዚህም ምክንያት ነው የፍጥረታት የእድገት ታሪካቸው የለውጥ ታሪክ ተብሎ የሚገለፀው። እስካሁን ድረስ ወደ 1.8 ሚሊዮን የሚገመቱ ዝሪያዎች በዚህች አለም የሚኖሩ እንዳሉ ይገመታል። “
በመልስነት ማስቀመጥ የሚቻል ነው።
ከሕብረተሰብና ከኃይማኖት ተቋማት በተለየ ለዝግመተ ለውጥ ፅንሰ ሃሳብ በባዮሎጂ የእውቀት መስክ ያልተቋረጠና ከፍተኛ የሆነ ተቀባይነት ቢያገኝም ስለ ተፈጥሮ አማራጭ ቴክኒካል ይዘቱን አስመልክቶ ግን ንትርኩ አስከ 20ኛው መቶኛ አመተ ምህረት አጋማሽ ድረስ መዝልቁ አልቀረም ነበር። የሲንቴቲካል (ሰው ሰራሽ) ዝግመተ ለውጥ መዳበር ነው ይህንን የተፈጥሮ አማራጭ ፅንሰ ሃሳብን ከከፍታ ቦታ እንዲገኝና ለተቀባይነት ማግኘትም ከፍተኛ አስተዋፅዖ ሊያበረክትለት የቻለው።
ሲጠቃለል በአሁኑ ወቅት በዳርዊን የተፀነሰውና ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ለመዳበር የቻለው የዝግመተ ለውጥ ፅንሰ ሃሳብ ለባዮሎጂ የእውቀት ዘርፍ መሰረታዊነት ለማግኘት የቻሉ ፅንሰ ሃሳቦችን ለማትረፍ የበቃ ነው። በምሳሌነትም ስለ እንስሳት ህይወት ስነ ትምህርት(zoologie)፣ ስለ እፀዋት ስነ ትምህርት (ቦታኒክ) ስለ ጠባይ ስነ ትምህርት ስለ ኤምብሪዮሎጊክ፣ ያዝርዕትና ያትክልት ጥናት (Embryologic and Botanic) አጠቃልሎ በመያዝና ሰው ሰራሽ የዝግመተ ለውጥ የሚል ስምን ተቀዳጅቶ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ በመደበኛ የሥርአተ ትምህርትነት ለታዳጊ ተመራማሪዎች በእውቀት ምንጭነት ለመገልገያ በቅቶ የሰው ፍጡር አሁን ካለንበት ደረጃ ለመድረስ በቅቷል። በዚህም ነው ቻርለስ ዳርዊን የዝግመተ ለውጥ ፅንሰ ሃሳብ አባት ተብሎ ለመጠራት የበቃው አለምክንያት እንዳልሆነ ተደጋግሞ እየተገለፀ የሚገኘው።
ስለሆነም ዳርዊንና መሰል ሊቃውንቶች ባቀረቡት ፅንሰ ሃሳቦቻቸው ላይ ተገቢ ሂስ ለማቅረብ የሚጥር ማንኛውም ግለሰብ ሆነ ቡድን እንዲሁ በጅምላ ሳይሆን ፅንሰ ሃሳቦቹን በሚገባ ተረድቶ ውስጣዊ ይዘታቸውንም ገለጥለጥ አድርጎና አፍታቶ ሊሆን ሲገባው ሁለቱ ጸሃፊዎቻችን ግን ከገጽ አንድ አንስቶ እስከ መደምደሚያቸው ድረስ በጥላሸት መቀባት ተጀምሮ በዚሁ እሳቤ የሚደመደም ነው።
ታዲያ ይህንን በአለም አቀፍ ደረጃ እውቅናን ያተረፈን ሊቃውንትና ፅንሰ ሃሳቦችን ጭምር
“ኃይማኖትና እምነት የለሽ፣
ከሃዲ፣
በክፉ አስተሳሰብ የተሞላ፣
ሰውን ከሕሊና ውጭ ያደረገ፣
ለብዙ ሚሊዮን ሕዝብ ሞት ምክንያት የሆነ፣
ሰውን ከእግዚአብሄር የለየ፣
ሰዎች በሰላም፣ በአንድነት እንዳይኖሩ፣ ልዩነት በመፍጠር እንዲጠፋፉ ያደረገ፣
ማሰቢያ አዕምሮ የሌለው፣
ከ 19ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በተሳካ ሁኔታ በእለማችን የተተከለው የክፉ ሃሳብ የዝግመተ ለውጥ ፅንሰ ሃሳብ
በእለማችን አስከፊ ለሚባሉት የሰው ልጅ የእርስ በርስ መጨፋጨፍ፣ የግብረገብና የስነምግባር ውድቀት ምክንያት የሆነ” ወዘተ እያሉ ጥላሸት ሲቀቡ ትንሽ እንኳን የስቅጠጥ ምልክት አይታይባቸውም።
በዚህ ብቻ አያቆሙም። በተፈጥሮ ሳይንስና በእምነት መካከል (በዝግመተ ለውጥና የአለም በአምላክ መፈጠር) የአቀራረብ እንጂ መሰረታዊ ልዩነት እንደሌለ ለማስረዳት መጠነ ሰፊ ጥረት ያደረጉ አማኞች እንኳ ወደ ጎን ተጥለው ሁሉንም ኬይሲ ተግባር በዝግመተ ለውጥ ለማላከክ እንዲህ ይላሉ። “ይህ አስተሳሰብ” የዝግመተ ለውጥን ፅንሰ ሃሳብ ማለታቸው ነው “አለምን ከመቆጣጠሩ የተነሳ የእግዚአብሄርን ቃል እንኳን የዚህ አስተሳሰብ ደጋፊ ለማድረግ ብዙ ጥረት ተደርጓል። በለፀጉ/ሰለጠኑ የምንላቸው አገሮች በዚህ ፅንሰ ሃሳብ በመወሰዳቸው በአሁኑ ዘመን በአውሮፓና በአሜሪካ በእግዚአብሄር/ በፈጣሪ ማመን የድህነትና ኋላቀርነት ምልክት እንደሆነ ተደርጎ እንዲታሰብ ሆኗል።” እያሉ የራሳቸውን ምናባዊ አሰተያየት በማስቀመጥ ራሳቸውን በከሳሽነት ፈርጀው ለራስ እሳቤ ተስማሚ የሆነ ፖለቲካዊ ፍርጃ ይሰጣሉ። በሌላ በኩል ደግሞ የዶ/ር በየነ ተማሪ የነበረ ወጣት “ዶክተር በየነ የሚያስተምሩን የዝግመተ ለውጥ ትምህርት ምንም ማረጋገጫ የለውም፣ አንዱ ከአንዱ ተለወጠ ተለወጠ ….ከማለት ውጭ እንዴት እንደተለወጠ፣ እንዴት ሊለወጥ እንደሚችል ሊለወጥም የሚያሳይ መረጃ የለውም በማለት ይከራከር ነበር። በውቅቱ ይህንን ወጣት እንደ ጤናማ አልቆጠርነውም ነበር። እንዴት አይገባውም ብለን የተናደድንም ነበርን።” በማለት እነሱ ራሳቸው በሌላው ላይ አንድ ጣታቸውን ሲቀስሩ ሌሎቹ አራቶቹ በነሱ ላይ የተቀሰረ መሆኑ የሚታያቸው አልሆነም። ለነገሩ ዶክተር በየነ ሲሰጣቸው የነበረው ትምህርትን “አሜን ብለው ከመቀበላቸው በፊት ያየነውና ያረጋገጥንበት አሳማኝ መረጃ አልነበረም “ ብሎ ከመዝለፍና ሀሜታን ከመንዛት በፊት በግልም ሆነ ትምህርቱ በሚሰጥበት አዳራሽም ሆነ ላቦራቶሪ የበለጠ መረጃ ለማግኘት ለምንስ አልጠየቁም? ምንስ አገዳቸው? ለመሆኑ ይህንንስ ትምህርት ለመማር ምንስ ገፋፋቸው? ለመሆኑ የዝግመተ ለውጥ ፅንሰ ሃሳብ ፀረ ኃይማኖታዊነት መቼና እንዴትስ ተገለጠላቸው?
ለማንኛውም እኔ በፈጣሪ አምናለሁ፣ ስለሆነም የዝግመተ ለውጥ ፅንሰ ሃሳብን ጨርሶ አላምንበትም ማለት እኮ የተከለከለ አይደለም። ግን ውሸትን ፈጥሮና ፈብርኮ “ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮሃል” እንደሚባለው የውሸት ፍርድ ሰጪ ሆነው እየተከሰቱ እንዴትስ ጥላቻ የተጋገረበት የጥቅስ ጋጋታ ስላዥጎደጎዱ ተአሚነት ማግኘት ይቻላል? ምነዋ ጎበዝ ! እየተስተዋለ ማለቱ አግባብነት አለው ቢባል ከእውነቱ መራቅ ይሆን?
በክፍል ሶስት ይቀጥላል።