ሰኔ ሁለት ሺ አስራ አራት ዓ. ም.
በላይነህ አባተ ([email protected])
“የፍትህና የነፃነት አርበኞች ነን” እያሉ ሕዝብ እንደ ጥገት ሲያልቡ ኖረው ለቆሻሻ ስልጣንና ትቢያ ለሚሆን የቅንጦት ገላ ሳስተው እንደ ደን በተጨረገደ የሕዝብ ሬሳ ክምር ተቀምጠው ተገዳይና አስገዳይ ጭራቆች እየተሞዳሞዱና እጅ እየነሱ ከርሳቸውን የሚሞሉ ይሁዳን ያስከነዱና የሰማእታትን ሥጋ የሚዘነችሩ ሆዳሞች እያሉ አንተን ውሻን “ውሻን ውሻ በበላበት ይጮኻል” እያልኩ ስተርት በመኖሬ ተጸጽቻለሁ፡፡
“ውሻ በበላበት ይጮኻል!” የውሻ ባህሪ መስሎኝ በሰም ለበስ የወርቅ ግጥምና በንጥጥር ጦማር ሳነሳ ስጥልህ ኖሪያለሁ፡፡ ለሆዱና ለጥቅሙ ተንከባክቦ አሳዳጊውን ሕዝብና አገሩን የሚክድ ባለሁለት እጅ ፍጡር እንደ አሸን መፍላቱን ባለመገንዘብ ብዕሬን በአንተ እጅ ሳይኖረህ በትጉህ ሥራህ በምትታወቀው ሳነሳ ኖሬአለሁ፡፡
ውሻ ሆይ! በጦቢያ እርስ በርሳቸው የተገለባበጡ አራት ገዥዎችን በጌታነት እያቀያየሩ በጉርሻ ሎሌ የሆኑ ህሊና ቢሶች ፕሬዘዳንትና ሚኒሲቴር ሲባሉ እያየሁ “ውሻ በበላበት ይጮኻል!” እያልኩ እንዴት ልናገር እችላለሁ? ክርስቶስ የተሰቀለበትን መስቀል በአንገታቸው አንጠልጥለውና መንኩሰ ሞተ የምትልዋን ቆብ በራሳቸው ደፍተው በቤተክርስትያኗ አስራት ማጅራታቸውን ያሳባጡ ጳጳሳት በቤተክርስትያኗና በምዕመናኗ ላይ ለዘመቱ አሪዎስ ገዥዎች እጅ ሲነሱ እያየሁ “ውሻ በበላበት ይጮኻል!” እያልኩ ያንተን ስም የማነሳበት ሃይማኖት ተየት አመጣለሁ?
ወሻ ሆይ! “ባለ ዲግሪ ነን፣ ዶክተር ነን፣ ፕሮፈሰር ነን” እያሉ አንተ በንቀት አሽተህ የምታልፈውን እንጀራ ለመብላት ለነፈሰ-ገዳዮች፣ ለጆሮ ጠቢዎችና ለዘራፊዎች የካድሬ ቡችላ ሆነው “ዋው! ዋው!” ብለው ሲጮሁ እየሰማሁና እንደ ጅራት ሲንጦሎጦሉ እያየሁ “ውሻ በበላበት ይጮኻል!” የሚያሰኝ ህሊና ተየት አገኛለሁ? በካናዳ ስንዴና ሳልባጅ ልብስ እየደለሉ “ሃይማኖት” የሚያስፋፉ በሆድ ተደለለውም እምነታቸውን የሚለውጡ የሃይማኖት ደላሎች እያየሁ “ውሻ በበላበት ይጮኻል” እያልኩ የምሰብክበት ህሊና ተየት አመጣለሁ?
ውሻ ሆይ! በመለኮት መንበር ተቀምጠውና ጥቁር ካባ ደርበው በንፁኻን እየፈረዱ በኮረንቲ የሚያስጠብሱ እርጉም ዳኞች እያስተዋልኩ “ውሻ በበላበት ይጮኻል” እያልኩ የምለካበት ሚዛን ተየት አመጣለሁ? ተራዲዮና ተተሌቪዥን ድምጥ ማጉያ አፋቸውን ደቅነውና በሌባ ጣታቸው ኮቢ ይዘው ግሳንግስ ጋዜጣ እየጫሩ በሆዳቸው ነፍሰገዳይ ገዥዎችን የሚያገለግሉ “ጋዜጠኞች” እያየሁ አንተ እርቦህ ሳለም ከሙያህ ዝንፍ ሳትል አጥር ግቢ የምትጠብቀውን ባለውለታ ፍጡር የምወቅስበት አንጀት ተየት አመጣለሁ?
ውሻ ሆይ! የአገር ድንበራቸውን በመጠበቅ ፋንታ በሆዳቸው ተገዝተው ከሀዲ ገዥዎችን ተወንበር ለማቆየት ሕዝብን የሚጨፈጭፉትን ወታደሮች እያየሁ አንተ ሌት ተቀን አጥር ግቢህን በትጋት የምትጠብቀውን ወጥቶ አደር “ውሻ በበላበት ይጮኻል” እያልኩ የማብጠለጥልበት ህሊና ተየት አመጣለሁ?
ውሻ ሆይ! ባህራቸውን፣ ወንዛቸውንና ድንበራቸውን እንደ ጣቃ ጨርቅ እየቦጨቁ ለባዕድ ጌቶቻቸው መቅቡጥ የሚሰጡ ባንዳ ገዥዎች እያየሁ እንኳን የራስህን የጎረቢትህን ቤት በትጋት የምትጠብቀውን አርበኛ “ውሻ በበላበት ይጮኻል” እያልኩ የምወቅስበት ልሳን ተየት አመጣለሁ? ሕዝባቸውን ገደል ይዘው የሚገቡ የህሊና እውር “መሪዎች” እያየሁ አንተ ዓይነ ስውርን መርተህ ተገደል፣ ተእሾህና ተጋሬጣ የምታተርፍ የብርሃን መንገድ “ውሻ በበላበት ይጮኻል!” እያልኩ የምተርትበት አንደበት ተየት አገኛለሁ?
ውሻ ሆይ! ሳይርባቸው የበለጠ ለመብላት፣ የበለጠ ለመድለብ፣ የበለጠ ለመክበር፣ የበለጠ ለመዝረፍ ጌታ እያቀያየሩ በበሉበት የሚጮሁትን እኔ ተሞትኩ ሰርዶ አይብቀል የሚሉ የጋማ ከብቶች እያስተዋልኩ አንተ ሲሸጡህና ሲያስርቡህ ጌታ ልትቀይር የምትችለውን የተገፋህ ፍጡር በምን አፌ “ውሻ በበላበት ይጮኻል” ብዬ ልወቅስ እችላለሁ?
ውሻ ሆይ! በሆዳምነትና በአድርባይነት ተገዝተን በዘራቸውና በሃይማኖታቸው ምክንያት የተፈጁትን ወገኖቻችንን እርም እየጠሸቀምንና በሬሳቸው እየተራመድን ተገደሏቸውና ታስገደሏቸው ወንጀለጆች ጋር የምንወባራውን እርመ በላዎች እያለን አንተን የሞቱ ውሻዎችን ሬሳ ተራምደህ የማትሄደውን ባለ ህሊና እንሰሳ የምወቅስበት ይሉኝታቢስነት ተየት አመጣለሁ?
ውሻ ሆይ! ሰፈር፣ አገር፣ አሀጉርና ዓለም ሐብት ሳያጣ በሆዱ ለጌታው በሚገዛ ካድሬ፤ ዲግሪውን ጭኖ በከርሱ በሚሸመት ምሁር፣ የመጣፍ ቃል እያነበነበ በሆዱ በሚገዛ ቀጣፊ ፓስተር፣ ቁራንን እየጠቀሰ በከርሱ በሚቀወር ሼህና ቆቡን ደፍቶ በሆዱ በሚቸበቸብ ጳጳስ ተሞልታ እያየሁ አንተን በከንቱ ስወቅስ ስለኖርኩ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡
“ጠበቃዎች ነን፣ መሀንዲሶች ነን፣ ሐኪሞች ነን፣ የምጣኔ ሐብት ጠበብት ነን፣ የተማርን ነን፣ የሃማይማኖት መሪዎች ነን፣ የሰበአዊ መብት ተሟጋቾች ነን፣ ጋዜጠኞች ነን፣ ዳኞች ነን፣ ምሁራን ነን ወዘተርፈ” እያልን በበላንበት የምንጮህ ባለ ሁለት እጅ አውሬዎች እንደ አሸን በፈላንበት ዘመን “ውሻ በበላበት ይጮኻል!” እያልኩ ያንተን ስም በከንቱ በማንሳቴ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡ ውሻ ሆይ ድንጋይ ተሸክሜ ተእግርህ ስር ተደፍቻለሁ፡፡ ውሻ ሆይ ይቅር በለኝ ስል እለምናለሁ፡፡ ውሻ ሆይ ይቅር በለኝ ብያለሁ!
ሰኔ ሁለት ሺ አስራ አራት ዓ. ም.