#ወይ_ልምጣ__ወይ__ምጣ …!
“…..ዕንባዬን መቆጣጠር አልቻልኩም፤እጅግ በጣም ያሳዝናል፤ ትዕግስትንም ይፈታተናል። ይባስ ብሎ ያለመወርቅ የተዳፈነውን እሳት ቆሰቆሰችው። ያለም ዛሬ በፋኖ ላምሮት የዘፈነችው “ወይ ልምጣ ወይ ምጣ” የተሰኘውን የዛሬ አመት መሰሉ ፋንታሁን የሰራችው ክሊፕ ኤልያስ መልካ ነበር የሰራው። ዘፈኑ የናፍቆት ወይንም የፍቅር ይመስላል ግን አይደለም። በኋላ ላይ መሰሉ ስለዚህ ሥራ ስታወራ ኤልያስ መልካ በህመሙ ሲሰቃይ…ጣር ሲበዘባት …
“አገሩና ደጁ ሩቅ እየመሠለኝ
እንደ ወፍ እንግዳ እያብሰለሰለኝ
ዘመድ እንደሌለው እንደ ባዕድ አገር ሰው
እንደ ቀልድ ባይተዋር ሆዴን እየባሰው
ወይ ልምጣ ወይ ምጣ
ከሆንክ የእኔ ዕጣ
በምን ጥፋቴ ነው ልቤ እንዲህ ሚቀጣ
እህህ… እህህ ..እህህ…
እህህ ..ወየው ጉድ ስንት አለ በሆዴ
አምቄው ነው እንጂ ኑሮየን በዘዴ
አለ ጋደም ጋደም ሰው ሁሉ ሊተኛ
እኔ ቁጭ ብያለሁ ያንተ በሽተኛ” በማለት ከአምላኩ ጋር “ወይ እኔን ውሰደኝ አሊያም አንተ ና” በማለት ሙግት የገጠመበት ሥራው ነው ስትል ተናግራ ነበር።
በርግጥም እውነቷን ነው። ዘፈኑ ለፍቅር የተዘፈነ አልነበረም። ኤልያስ መልካ ከመሞቱ ጥቂት ቀናት በፊት ሥራውን ባጠናቀቀው “ወይ ምጣ ወይ ልምጣ” ሙዚቃ ውስጥ ሰዋዊ ሕመሙን ለመተንፈስ የሞከረበት ሥራው ነው። ኤልያስ መልካ ህመሙን፣ መከፋቱን፣ ማዘኑን፣ አምላኩን መናፈቁን ያሳየበት ሥራው ነው።
“እጆቼን ዘርግቼ እቀበለው ነበር
የውሃ ሽታ ሆኖ ሄዶ በዛው ባይቀር” በማለት ኤልያስ መልካ አምላኩን መናፈቁን፣ ህመም ሲበዛበት ሞት ከሱ መራቁን በቁጭት የፃፈው ስንኝ ነበር።
ውነት ለመናገር ከመሰሉ ንግግር በኋላ ይሄን ሙዚቃ ላለማዳመጥ ወሰኜ ነበር። ዛሬ ደግሞ ምታሃተኛዋ ያለመወርቅ ብሶታችንን ቆሰቆሰችው፥ ሁሉም ኤልያስ መልካን እያሰበ በዕንባ ተራጨ። ዳኞችም ዕንባቸውን መቆጣጠር ተስኗቸው ዋለ።
መሰሉ እንኳን “ይሄን ዘፈን አልዘፍነው ይቅርብኝ ብዬ ኤልያስ ነው በግድ ያዘፈነኝ” ትላለች እዛው ቃለመጠይቋ “ለምን?” ስትባል ምክንያቱም እሷ ዘፈኑን ስትሰራው በጣም ትረበሽ እንደነበረ ተናግራለች።
ኤልያስ መልካ በመጨረሻም በዚህ ሥራው ምንም ሳይደብቅ ከአጠገቡ ሰው ማጣቱን፣ ከአምላኩ እቅፍ ለመግባት ምን ያህል መጓጓቱን፣ ሞትና እንቅልፍ እንዴት እኩል እንደራቁት ነግሮን ነው የተሰናበተው።
አምላኩስ “ወይ ልምጣ ወይ ምጣ” የሚለው መልእክት ደርሶት ነው ወይ “ኧረ አንተ ና ልጄ” ብሎ የወሰደው ይሆን? ፀፀት|||Melkam Gebeya
——————————–
ጎንደሮች አቀባበላችሁ እንዴት ይሆን?!
የአለምወርቅ የተባለች ኮከብ ጀንበሩን ሰንጥቃ ወጣች!
****
ጎንደርየ የአለም ወርቅ ልጅሽ መላ ኢትዮጵያን በስሜት ሰቅዛ በጥዑም ቅላፄ እየተስረቀረቀች ፍፃሜውን አሳምራዋለች! እንኳን እኔ የሙዚቃ ዳኞችም ቃላት አጥተውላታል። ትእንግርት ክስተት ናት። ፊሽካው ተነፍቶ ውድድሩ ባያልቅም አለምየ አዲሷ ኮከብ አሸንፋለች! ሕዝባችን ከድብት ድባብ ይወጣ ዘንድ ኪነጥበብ ታብብ!
====================
የእግርጌ ማስታወሻ:- ከጎንደር ከተማ ወደ የአለም ወርቅ የትውልድ ቀየ የጀግኖች ስፍራ ወደ በለሳ ለመሄድ ቅርብ ቢሆንም መንገዱ አሁንም ድረስ ገረጋንቲ ኮረኮንች ነው…ልማት ይጠላባቹሃል ተብለን አንቅር እንጅ…
ሙሉነህ ዮሐንስ